በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በራስ መመራት

በራስ መመራት

ፍቺ:- “በራስ መመራት” ሲባል አንድ ሰው የሌሎች ጥገኛ የማይሆንበት ወይም ጥገኛ እንደሆነ የማያስብበት፣ በሌሎች መመሪያና ተጽዕኖ የማይገዛበት ሁኔታ ነው። ሰዎች የፈቀዱትን የማድረግ ነፃነት የተሰጣቸው በመሆኑ መጠነኛ የሆነ በራስ የመመራት ፍላጎት ወይም በራስ ፈቃድ የመመራት የተፈጥሮ ፍላጎት አላቸው። ይሁን እንጂ ይህ ፍላጎት ከገደብ አልፎ ሲሄድ ወደ አለመታዘዝ እንዲያውም ወደ ዓመፅ ያደርሳል።

ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን የአቋም ደረጃዎች ወደጎን ገሸሽ በሚያደርጉበት ጊዜ እውነተኛ ነፃነት ያገኛሉን?

ሮሜ 6:16, 23:- “ለመታዘዝ ባሪያዎች እንድትሆኑ ራሳችሁን ለምታቀርቡለት፣ ለእርሱ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን? ወይም ለሞት የኃጢአት ባሪያዎች ወይም ለጽድቅ የመታዘዝ ባሪያዎች ናችሁ። . . . የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።”

ገላ. 6:7–9:- “አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋው መበስበስን ያጭዳልና፣ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል። ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት።”

የፆታ ሥነ ምግባር:- “ዝሙትን የሚፈጽም ሰው በገዛ ሰውነቱ ላይ ኃጢአት ያደርጋል።” (1 ቆሮ. 6:18 የ1980 ትርጉም ) “ከሴት ጋር የሚያመነዝር . . . ነፍሱን ያጠፋል።” (ምሳሌ 6:32) (ግብረ ሰዶምን በተመለከተ ሮሜ 1:24–27⁠ን ተመልከት።) (የተከለከለ የፆታ ግንኙነት ለጊዜው የሚያስደስት ሊመስል ይችላል። ነገር ግን መጥፎ በሽታዎች፣ ያልተፈለገ እርግዝና፣ ፅንስ ማስወረድ፣ ቅናት፣ የኅሊና መረበሽ፣ የስሜት መጐዳት ያመጣል። እንዲሁም የወደፊቱ የሕይወት ተስፋችን በተመካበት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነትን እንድናጣ ያደርገናል።)

ቁሳዊ ሀብት ማሳደድ:- “ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ [“ቆርጠው የተነሡ” አዓት] በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጐዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ [“የጎጂ ነገሮች” አዓት] ሥር ነውና፣ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ፣ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።” (1 ጢሞ. 6:9, 10) “ነፍሴንም አንቺ ነፍሴ፣ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፣ ዕረፊ፣ ብዪ፣ ጠጪ፣ ደስ ይበልሽ እላታለሁ አለ። እግዚአብሔር ግን:- አንተ ሰነፍ፣ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል? አለው። ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፣ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው።” (ሉቃስ 12:19–21) (ቁሳዊ ሀብት ዘላቂ ደስታ አይሰጥም። ሀብታም ለመሆን የሚደረግ ጥረት ብዙ ጊዜ በቤተሰብ ውስጥ ደስታ ማጣትን፣ የጤና መቃወስ፣ መንፈሳዊ ውድቀት ያስከትላል።)

አልኮል ያለልክ መጠጣት:- “ዋይታ ለማን ነው? ኀዘን ለማን ነው? ጠብ ለማን ነው? ጩኸት ለማን ነው? ያለምክንያት መቁሰል ለማን ነው? የዓይን ቅላት ለማን ነው? የወይን ጠጅ በመጠጣት ለሚዘገዩ አይደለምን? የተደባለቀ የወይንን ጠጅ ይፈትኑ ዘንድ ለሚከተሉ አይደለምን? በኋላ እንደ እባብ ይነድፋል፣ እንደ እፉኝትም መርዙን ያፈስሳል።” (ምሳሌ 23:29, 30, 32) (አንድ ሰው ከልክ በላይ መጠጥ ሲጠጣ በመጀመሪያ ላይ ችግሮቹን በሙሉ እንዲረሳ የሚረዳው ይመስለዋል። ይሁን እንጂ ችግሮቹ እንዳሉ ናቸው። ስካሩ ሲበርድለት ችግሮቹ ሊወገዱ ቀርቶ እንዲያውም ሌላ ችግር ጨምረው ያገኛቸዋል። አልኮል ከልክ በላይ ከተወሰደ ክብረ ኅሊናን ያሳጣል፣ ጤናን፣ የቤተሰብን ኑሮና ከአምላክ ጋር ያለንን ግንኙነት ያበላሻል።)

አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ:- በገጽ 106–112 ላይ “አደንዛዥ ዕፅ” በሚለው ሥር ተመልከት።

መጥፎ ጓደኝነት:- ዱርዬዎች አለብዙ ድካም በርካታ ገንዘብ ማግኘት የሚቻልበትን ዘዴ እንደሚያውቁ ቢነግሩህ ከእነርሱ ጋር ትተባበራለህን? “ከእነርሱ ጋር በዚያ መንገድ አብረህ አትሂድ። እግርህን እነርሱ ከሚሄዱበት መንገድ አርቅ። እግራቸው ወደ መጥፎ ነገር ይሮጣል፣ ደም ለማፍሰስም ይቸኩላል።” (ምሳሌ 1:10–19 አዓት) አንድ ሰው ይሖዋን የማያመልክ ቢሆንም ጥሩ ሰው ስለሚመስል ብቻ ጥሩ ጓደኛ እንደሆነ አድርገህ ትመለከተዋለህን? ሴኬም የከነዓናውያን አለቃ ልጅና መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “በአባቱ ቤት ካሉት ሁሉ የከበረ” ሰው ነበር። ነገር ግን ዲናን “ወሰዳትም ከእርስዋም ጋር ተኛ፣ አስነወራትም።” (ዘፍ. 34:1, 2, 19) ሌሎች ሰዎች ከአምላክ ቃል የተማርኸውን እውነት አለማመናቸው በጓደኛ አመራረጥህ ላይ ልዩነት ሊያመጣ ይገባዋልን? “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል።” (1 ቆሮ. 15:33) ይሖዋን የማይወዱትን ሰዎች ጓደኛ አድርገህ ብትመርጥ ይሖዋ ምን ይሰማዋል? ይሖዋን የማይወድ ጓደኛ ስለመረጠ የይሁዳ ንጉሥ አንድ የይሖዋ መልእክተኛ:- “ስለዚህም ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ ቁጣ ሆኖብሃል” ብሎታል።—2 ዜና 19:1, 2

ሰዎች የአምላክን ትእዛዞች ቸል በማለት በራሳቸው ተመርተው ያሻቸውን ለመወሰን እንዲፈልጉ የገፋፋቸው ማን ነው?

ዘፍ. 3:1–5:- “እባብም [ሰይጣን በአፈ ቀላጤነት የተጠቀመበት፣ ራእይ 12:9⁠ን ተመልከት] . . . [ሴቲቱን:-] በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዟልን? አላት። ሴቲቱም ለእባቡ አለችው:- በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን፤ ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፣ እግዚአብሔር አለ:- እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም። እባብም ለሴቲቱ አላት:- ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካሙንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።”

አንድ ሰው የግል ፍላጎቱን ለማርካት ሲል የአምላክን ፈቃድ ችላ በሚልበት ጊዜ በምን ዓይነት መንፈስ እየተነዳ ነው?

ኤፌ. 2:1–3:- “በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፣ በዚህ ዓለም [ሰይጣን ገዥው በሆነው ዓለም] እንዳለው ኑሮ፣ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፣ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፣ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፣ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን።”

አምላክን እናገለግላለን የሚሉት ሰዎች ማስወገድ የሚገባቸው የትኞቹን በራስ የመመራት ፍላጎቶች ነው?

ምሳሌ 16:18:- “ትዕቢት ጥፋትን፣ ኩሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል።”

ምሳሌ 5:12 የ1980 ትርጉም:- “እንዲህም ትላለህ፣ የማልማረውና የሰውን ተግሣጽ የማልቀበለው ከቶ ለምንድን ነው?” (ከጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚገልጸው እንዲህ የመሰለ ዝንባሌ አንድን ሰው ወደ ከባድ ችግሮች ይመራዋል።)

ዘኁ. 16:3:- “[ይሖዋ ለሕዝቦቹ የበላይ ተመልካቾች አድርጎ ይጠቀምባቸው በነበሩት] በሙሴና በአሮን ላይ ተሰብስበው:- ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፣ እግዚአብሔር በመካከላቸው ነውና እናንተ እጅግ አብዝታችኋል፤ በእግዚአብሔር ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ? አሉ።”

ይሁዳ 16 የ1980 ትርጉም:- “እነዚህ ሰዎች ሁልጊዜ የሚያጉረመርሙና በምንም ነገር የማይደሰቱ ናቸው፤ የራሳቸውን ክፉ ምኞት የሚከተሉ ናቸው፤ አፋቸው በትዕቢት ቃል የተሞላ ነው፤ የራሳቸውን ጥቅም በመፈለግ ሰውን ይለማመጣሉ።”

3 ዮሐ. 9:- “ዋናቸው ሊሆን የሚወድ ዲዮጥራጢስ አይቀበለንም።”

ምሳሌ 18:1:- “መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፣ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል።”

ያዕ. 4:13–15 አዓት :- “አሁንም:- ‘ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህ ከተማ እንሄዳለን፤ በዚያም ዓመት እንኖራለን እንነግዳለን፣ እናተርፋለንም’ የምትሉ እናንተ፣ ተመልከቱ፣ ነገ የሚሆነውን አታውቁምና። ሕይወታችሁ ምንድን ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፋሎት ናችሁና። በዚህ ፈንታ:- ‘ጌታ ቢፈቅድ፣ ብንኖርም፣ ይህን ወይም ያን እናደርጋለን’ ማለት ይገባችኋል።”

አንድ ሰው በራስ የመመራት ፍላጎቱ ከክርስቲያን ጉባኤ ውጪ ያለውን ዓለም ወደ መምሰል ካደረሰው በማን ቁጥጥር ሥር መሆኑ ነው? ይህንንስ አምላክ እንዴት ይመለከተዋል?

1 ዮሐ. 2:15፤ 5:19:- “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።” “ዓለምም በሞላው በክፉው [ተይዟል።]”

ያዕ. 4:4 አዓት :- “የዓለም ወዳጅ ለመሆን የሚፈልግ ሁሉ ራሱን የአምላክ ጠላት ያደርጋል።”