በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአካል መነጠቅ

በአካል መነጠቅ

ፍቺ:- ታማኝ ክርስቲያኖች በሥጋ እንዳሉ “በአየር ላይ” ከክርስቶስ ጋር ለመሆን ከዓለም ተለይተው ከምድር በሥጋ እንዳሉ በቅጽበት ይነጠቃሉ የሚለው እምነት በእንግሊዝኛ “ራፕቸር” (በአካል መነጠቅ) ይባላል። ሁሉም ሰዎች ባይሆኑም 1 ተሰሎንቄ 4:17 የሚናገረው በአካል ስለመነጠቅ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ። በመንፈስ አነሣሽነት በተጻፉት ጽሑፎች ውስጥ በአካል መነጠቅ (“ራፕቸር”) የሚል ቃል አይገኝም።

ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች “ከክርስቶስ ጋር ለመሆን” ይነጠቃሉ ባለ ጊዜ እያብራራ የነበረው ርዕሰ ጉዳይ ምን ነበር?

1 ተሰ. 4:13–18 የ1980 ትርጉም:- “ወንድሞች ሆይ! ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች እንዳታዝኑ፣ ስለሞቱት [ቱኢቨ፣ ጀባ፤ “በሞት ስላንቀላፉት” ኒኢ፤ “አንቀላፍተው ስላሉቱ” የ1954 ትርጉም ] ሰዎች እውነቱን እንድታውቁ እንወዳለን። ኢየሱስ እንደሞተና ከሞትም እንደተነሣ እናምናለን፤ ስለዚህ በኢየሱስ አምነው የሞቱትን እግዚአብሔር ከኢየሱስ ጋር ያመጣቸዋል። ከጌታ በተቀበልነው ቃል መሠረት የምንነግራችሁ ይህ ነው፤ ጌታ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ሕያዋን ሆነን የምንገኝ የሞቱትን አንቀድምም። የትእዛዝ ድምፅ፣ የመላእክት አለቃ ድምፅ፣ የእግዚአብሔር መለከትም ይሰማል፤ ጌታ ራሱም ከሰማይ ይወርዳል፤ በክርስቶስ አምነው የሞቱትም አስቀድመው ይነሣሉ። ከዚህ በኋላ እኛ በሕይወት የምንገኘው ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ ለዘላለምም ከጌታ ጋር እንሆናለን። ስለዚህ በዚህ ቃል እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ።” (የተሰሎንቄ ክርስቲያን ጉባኤ አንዳንድ አባሎች ሞተው እንደነበር ከዚህ መረዳት ይቻላል። በሕይወት የነበሩት እርስ በርሳቸው በትንሣኤ ተስፋ እንዲጽናኑ ጳውሎስ አበረታቷቸዋል። ኢየሱስ ከሞተ በኋላ እንደተነሣ ካስታወሳቸው በኋላ ከመካከላቸው የሞቱት ታማኝ ክርስቲያኖች ጌታ ሲመጣ ከእርሱ ጋር ለመሆን ይነሣሉ ሲል ገለጸላቸው።)

በ⁠1 ተሰሎንቄ 4:17 ላይ እንደተገለጸው ‘በደመና ውስጥ የሚነጠቁት’ እነማን ናቸው?

ቁጥር 15 እንደሚገልጸው በደመና ውስጥ የሚነጠቁት ‘ጌታ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ሕያው ሆነው የሚቆዩት’ ታማኞች ናቸው። ይህም ማለት አሁንም በጌታ መምጫ ጊዜ ውስጥ ይኖራሉ ማለት ነው። ወደ ፊትስ ይሞቱ ይሆን? በ⁠ሮሜ 6:3–5 እና በ⁠1 ቆሮንቶስ 15:35, 36, 44 መሠረት ( በገጽ 313, 314 ላይ ተጠቅሰዋል) ሰማያዊ ሕይወት ለማግኘት ከመቻላቸው በፊት መሞት አለባቸው። ነገር ግን ሞተው የክርስቶስን መመለስ እየተጠባበቁ መቆየት አያስፈልጋቸውም። ወዲያውኑ “በቅጽበት ዓይን” ከጌታ ጋር እንዲሆኑ “ይነጠቃሉ።”—1 ቆሮ. 15:51, 52፤ እንዲሁም ራእይ 14:13

ክርስቶስ በደመና እየታየና ዓለም እየተመለከተው ታማኝ ክርስቲያኖችን ወደ ሰማይ ይወስዳቸዋልን?

ኢየሱስ ዓለም በሥጋዊ ዓይኖች እንደገና እንደሚያየው ተናግሮ ነበርን?

ዮሐ. 14:19:- “ገና ጥቂት ዘመን አለ ከዚህም በኋላ ዓለም አያየኝም፤ እናንተ [የእርሱ ታማኝ ሐዋርያት የሆኑት ማለት ነው] ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ከ⁠1 ጢሞቴዎስ 6:16 ጋር አወዳድር።)

የጌታ ‘ከሰማይ መውረድ’ ትርጉሙ ምንድን ነው?

በ⁠1 ተሰሎንቄ 4:16 ላይ እንደተገለጸው ጌታ በሥጋዊ ዓይኖች ሳይታይ ‘ከሰማይ ሊወርድ’ ይችላልን? በጥንቶቹ የሰዶምና ገሞራ ዘመን ሰዎች የሚሠሩትን ‘ለማየት ወደ ምድር እንደሚወርድ’ ይሖዋ ተናግሮ ነበር። (ዘፍ. 18:21) ይሖዋ ያንን ሕዝብ ሲፈትሽ የተመለከተ ሰው አልነበረም። እርግጥ እርሱ ተወካዮች አድርጎ የላካቸውን መላእክት ሰዎች አይተዋቸዋል። (ዮሐ. 1:18) በተመሳሳይ መንገድ ኢየሱስ ሥጋ ለብሶ መመለስ ሳያስፈልገው በምድር ላይ ላሉት ታማኝ ተከታዮቹ የታማኝነት ዋጋቸውን ለመስጠት ትኩረቱን ወደ ምድር ሊመልስ ይችላል።

እንግዲያው ጌታ ‘በደመና ሲመጣ’ ሰዎች ‘የሚያዩት’ በምን መንገድ ነው?

ኢየሱስ “የሰው ልጅ [ኢየሱስ ክርስቶስ] በኃይልና በብዙ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል” በማለት ተናግሮ ነበር። (ሉቃስ 21:27) ይህ ዐረፍተ ነገር ወይም በሌሎች ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት ተመሳሳይ አገላለጾች በ⁠ዮሐንስ 14:19 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ኢየሱስ የተናገረውን ቃል በምንም መንገድ አይቃረንም። እስቲ ይህን ጉዳይ ተመልከት:- በ⁠ዘጸአት 19:9 ላይ እንደተገለጸው አምላክ ‘ወደ ሕዝቡ በከባድ ደመና በመጣ’ ጊዜ በሲና ተራራ ላይ ምን ነገር ሆነ? አምላክ በማይታይ አኳኋን ተገኝቶ ነበር፤ የእስራኤል ሕዝብ የእርሱን መገኘት የሚያረጋግጥ የሚታይ መረጃ አይቶ ነበር፤ ነገር ግን አንዳቸውም ቢሆኑ አምላክን በዓይናቸው አላዩትም። ስለዚህ ኢየሱስ “በደመና” እመጣለሁ ብሎ ሲናገር ለሰው ዓይን እንደማይታይ፣ ግን ሰዎች የእርሱን መገኘት መገንዘብ እንደሚችሉ መናገሩ ነበር። በዓይነ ሕሊናቸው ‘ያዩታል፤’ መገኘቱን ያስተውላሉ። (ለተጨማሪ ማብራሪያ “የክርስቶስ መመለስ” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት።)

ክርስቲያኖች ከነሥጋዊ አካላቸው ወደ ሰማይ ሊወሰዱ ይችላሉን?

1 ቆሮ. 15:50:- “ወንድሞች ሆይ፣ ይህንን እላለሁ:- ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፣ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም።”

በነቢዩ ኤልያስ ላይ የደረሰው ነገር ከዚህ ጋር ይቃረናልን? በፍጹም አይቃረንም። ኢየሱስ ከበርካታ መቶ ዘመናት በኋላ ከተናገረው ግልጽ ቃል አንጻር ነገሩን መረዳት ያስፈልጋል። “ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም” ብሎ ነበር። (ዮሐ. 3:13 የ1980 ትርጉም ) ኤልያስ ‘በአውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ሲወጣ’ ቢታይም ወደ ረቂቁ መንፈሳዊ ዓለም ሄደ ማለት ግን አይደለም። ለምን እንደዚያ እንላለን? ምክንያቱም ከጊዜ በኋላ ለይሁዳ ንጉሥ የወቀሳ ደብዳቤ እንደላከለት ተገልጿል። (2 ነገ. 2:11፣ 2 ዜና 21:1, 12–15) ሰዎች አውሮፕላን ከመፈልሰፋቸው በፊት ይሖዋ ኤልያስን ከመሬት አንሥቶ ወፎች ወደሚበሩበት ሰማይና ከዚያም ወደሌላ ቦታ ለማጓጓዝ የራሱን መንገድ (የእሳት ሰረገላና አውሎ ነፋስ) ተጠቅሟል።—ከ⁠ዘፍጥረት 1:6–8, 20 ጋር አወዳድር።

ታማኝ ክርስቲያኖች ሳይሞቱ ከምድር ላይ ተሰውረው በምሥጢር ወደ ሰማይ ይወሰዳሉን?

 ሮሜ 6:3–5:- “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? . . . ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን።” (በኢየሱስ ላይ የደረሰው ሁኔታ ምሳሌ ይሆነናል። ኢየሱስ እንደሞተ ደቀ መዛሙርቱም ሆኑ ሌሎች ያውቁ ነበር። ኢየሱስ ከመሞቱና ከሙታን ከመነሣቱ በፊት ወደ ሰማያዊ ሕይወት አልተመለሰም።)

1 ቆሮ. 15:35, 36, 44:- “ነገር ግን ሰው:- ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል። አንተ ሞኝ፣ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፣ መንፈሳዊ አካል ይነሣል።” (ስለዚህ አንድ ሰው ይህንን መንፈሳዊ አካል ከመቀበሉ በፊት መሞት ይኖርበታል።)

ጌታ ሁሉንም ታማኝ ክርስቲያኖች ከታላቁ መከራ በፊት በተአምር ከምድር ይወስዳቸዋልን?

ማቴ. 24:21, 22:- “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።” (ጥቅሱ ‘የተመረጡት’ ሁሉ ከታላቁ መከራ በፊት ወደ ሰማይ ይወሰዳሉ አይልም። ከዚህ ይልቅ ከሌሎች ተባባሪዎች ጋር በመሆን አንዳንድ ቅቡዓን ይህንን በምድር ላይ የሚመጣ ታላቅ መከራ በሕይወት የሚያልፉ መሆናቸውን ሊያመለክት ይችላል።)

ራእይ 7:9, 10, 14:- “ከዚያ በኋላ አየሁ፣ እነሆም፣ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮኹ:- በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ። . . . እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው።” (አንድ ሰው ከአንድ ነገር ‘ከመምጣቱ’ ወይም ከመውጣቱ በፊት ወደዚያ ነገር መግባት ወይም በዚያ ነገር ውስጥ መሆን ይኖርበታል። ስለዚህ እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ታላቁን መከራ ያዩና ከዚህ እልቂት በሕይወት የተረፉ ሰዎች መሆን አለባቸው።) (በምድር ላይ ስለመሆናቸው ገጽ 167, 168⁠ን ተመልከት።)

በታላቁ መከራ ጊዜ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ምን ጥበቃ ይደረግላቸዋል?

ሮሜ 10:13:- “የጌታን [“የይሖዋን” አዓት] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።”

ሶፎ. 2:3:- “እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ፣ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን” አዓት፣ አስ፣ ያን፣ ባይ ] ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፤ ትሕትናንም ፈልጉ፤ ምናልባት በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።” (በተጨማሪም ኢሳይያስ 26:20)

እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ ከታላቁ መከራ በኋላ ወደ ሰማይ ይወሰዳሉን?

ማቴ. 5:5:- “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፣ ምድርን ይወርሳሉና።”

መዝ. 37:29:- “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።” (በተጨማሪም ቁጥር 10, 11, 34)

1 ቆሮ. 15:50:- “ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም።”

በተጨማሪም “ሰማይ” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት።

አንዳንድ ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ጋር እንዲሆኑ ወደ ሰማይ የሚወሰዱት ለምንድን ነው?

ራእይ 20:6:- “የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፣ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።” (ከክርስቶስ ጋር የሚገዙ በመሆናቸው የሚገዟቸው ሰዎች መኖር አለባቸው። እነዚህ ተገዥዎች እነማን ናቸው? ማቴዎስ 5:5 እና መዝሙር 37:29⁠ን ተመልከት።)

በተጨማሪም “እንደገና መወለድ” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት።

ወደ ሰማይ የሚሄዱት በገነት ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ወደ ምድር ይመለሳሉን?

ምሳሌ 2:21:- “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርሷ ይኖራሉና።” (ጥቅሱ እነዚህ ቅኖች ወደ ምድር እንደሚመለሱ ሳይሆን በምድር እንደሚቀመጡ [“እንደሚቀሩ ” “አዓት ”] ይናገራል።)

1 ተሰ. 4:17:- “እንዲሁም [እኛ ወደ ሰማይ የምንወሰደው ክርስቲያኖች] ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።”—ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-

‘በአካል መነጠቅ እንዳለ ታምናለህ?’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ሁሉ ሰው ስለ መነጠቅ ያለው አስተሳሰብ አንድ ዓይነት እንዳልሆነ ተገንዝቤአለሁ። እርስዎ ስለ መነጠቅ ያልዎት አሳብ ምን እንደሆነ ይነግሩኛል? . . . በማንኛውም ጉዳይ ላይ የራሳችንን አስተሳሰብ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው ጋር ብናነጻጸር ጠቃሚ ይሆናል። (ከላይ ከቀረቡት ሐሳቦች ውስጥ ተስማሚ የሆኑትን ጥቀስ።)’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘በአካል መነጠቅ ክርስቲያኖች ከጥፋት እንዲያመልጡ የተደረገላቸው ዝግጅት እንደሆነ ተነግሮኛል። ብዙዎች ከሚመጣው ታላቅ መከራ የሚያመልጡት በዚህ መንገድ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እርስዎስ የሚሰማዎት እንደዚህ ነው?’ ከዚያ ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘በእርግጥ በዚህ የመከራ ጊዜ የአምላክን ጥበቃ ለማግኘት እፈልጋለሁ። የአምላክን ጥበቃ እንዴት ማግኘት እንደምንችል የሚገልጹ ጥቅሶች በጣም ያበረታቱኛል። (ሶፎ. 2:3)’ (2) ‘መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ታማኝ ሰዎችን እዚሁ ምድር እንዳሉ እንደሚጠብቃቸው ይናገራል። (ምሳሌ 2:21, 22) ይህም አምላክ አዳምን በመጀመሪያ ሲፈጥርና በገነት ሲያስቀምጠው ከነበረው ዓላማ ጋር የሚስማማ ነው።’

ሌላ አማራጭ:- ‘መነጠቅ ሲሉ በሥርዓቱ መጨረሻ ጊዜ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ እንደሚወሰዱ መናገርዎ ነው አይደለም? . . . ግን ሰማይ ከሄዱ በኋላ ምን እንደሚሠሩ አስበው ያውቃሉ? . . . ራእይ 20:6 (እና 5:9, 10) ምን እንደሚል ልብ ይበሉ። . . . ግን የሚገዙት እነማንን ነው? (መዝ. 37:10, 11, 29)’