በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተአምራዊ ፈውስ

ተአምራዊ ፈውስ

ፍቺ:- በአካል፣ በአእምሮ ወይም በመንፈስ የታመመን ሰው ጥሩ ጤና እንዲያገኝ ማድረግ። ከክርስትና በፊት የነበሩ ጥቂት ዕብራውያን ነቢያት፣ እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስና የጥንቱ ክርስቲያን ጉባኤ አንዳንድ አባሎች በአምላክ መንፈስ እርዳታ ተአምራዊ ፈውስ ለማድረግ ችለው ነበር።

በዘመናችን የሚደረገው ተአምራዊ ፈውስ በአምላክ መንፈስ እርዳታ የሚከናወን ነውን?

ተአምር የማድረግ ችሎታ ከእውነተኛው አምላክ ብቻ ሳይሆን ከሌላም ምንጭ ሊገኝ ይችላልን?

ሙሴና አሮን በግብፁ ፈርዖን ፊት ቀርበው እስራኤላውያንን ወደ ምድረ በዳ ሄደው ለይሖዋ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ እንዲለቃቸው ጠየቁት። ጥያቄያቸው መለኮታዊ ድጋፍ ያለው መሆኑን ለማረጋገጥ ሙሴ አሮንን በትሩን እንዲጥል አዘዘው። በትሩም እባብ ሆነ። ይህ ተአምር የተሠራው በአምላክ ኃይል ነበር። ይሁን እንጂ አስማት የሚያደርጉ የግብፅ ካህናትም በትሮቻቸውን ሲጥሉ በትሮቻቸው እባቦች ሆኑ። (ዘጸ. 7:8–12) ይህን ተአምር የሠሩት በማን ኃይል ነው?—ከ⁠ዘዳግም 18:10–12 ጋር አወዳድር።

በ20ኛው መቶ ዘመን የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በሚያከናውኑት የአምልኮ ሥርዓት የእምነት ፈውስ ይደረጋል። ክርስቲያን ካልሆኑት ሃይማኖቶች መካከል የቩዱ ካህናት፣ ጠንቋዮች፣ አስማተኞችና ሌሎች ሰዎችም ይፈውሳሉ። እነዚህ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የጥንቆላና የአስማት ሥራ ይሠራሉ። አንዳንድ “ምትሐታዊ ፈዋሾች” (ሳይኪክ ሂለርስ) እነርሱ የሚሰጡት ፈውስ ከሃይማኖት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው ይናገራሉ። እነዚህ ሁሉ ፈውስ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ኃይል ያገኙት ከእውነተኛው አምላክ ነውን?

ማቴ. 24:24:- “ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፣ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና [“ተአምራትና” ቱኢቨ፣ የ1980 ትርጉም ] ድንቅ ያሳያሉ።”

ማቴ. 7:15–23:- “ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። . . . በዚያ ቀን ብዙዎች:- ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፣ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፣ በስምህስ ብዙ ተአምራት [ጀባ፣ ኒኢ፣ ቱኢቨ ] አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም:- ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።”

በዘመናችን ይደረጋሉ የሚባሉት ስሜት ቀስቃሽ ፈውሶች የሚከናወኑት ኢየሱስና የጥንት ደቀ መዛሙርቱ ያከናውኑ በነበረው መንገድ ነውን?

የአገልግሎት ዋጋ:- “በሽተኞችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አድኑ፤ አጋንንትን አስወጡ፤ በነፃ የተቀበላችሁትን በነፃ ስጡ። ” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ማቴ. 10:28 የ1980 ትርጉም ) (የዛሬዎቹ ፈዋሾች ኢየሱስ በነፃ ስጡ ብሎ እንዳዘዘ በነፃ ይሰጣሉን?)

ፈዋሾቹ ምን ያህል ይሳካላቸዋል? “ከእርሱም [ከኢየሱስ] ኃይል ወጥቶ ሁሉን ይፈውስ ነበርና ሕዝቡ ሁሉ ሊዳስሱት ይሹ ነበር።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ሉቃስ 6:19) “ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከእነርሱ አንዱን ይጋርድ ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋና በወሰካ ያኖሩአቸው ነበር። ደግሞም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካለችው ከተማ ድውያንንና በርኩሳን መናፍስት የተሳቀዩትን እያመጡ ብዙ ሰዎች ይሰበሰቡ ነበር፤ ሁሉም ይፈወሱ ነበር። ” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ሥራ 5:15, 16) (በዘመናችን ፈውስ ለማግኘት ወደ ሃይማኖታዊ ፈዋሾች ወይም ወደ አምልኮ ቦታዎች የሚሄዱ ሁሉ ይፈወሳሉን?)

ፈዋሾችየሚገኙበት ድርጅት አባሎች አኗኗራቸው የአምላክ መንፈስ እንዳላቸው ያሳያልን?

በቡድን ደረጃ ፍቅር፣ ትዕግሥት፣ የዋህነት፣ ራስን መግዛትና የመሳሰሉትን የመንፈስ ፍሬዎች ጐላ ብሎ በሚታይ ሁኔታ ያሳያሉን?—ገላ. 5:22, 23

በዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ባለመግባት በእርግጥ ‘የዓለም ክፍል አለመሆናቸውን’ አሳይተዋልን? በጦርነት ጊዜ ከሚፈሰው የደም ዕዳ ንጹሖች ናቸውን? ከዚህ ዓለም ምግባረ ብልሹ ጠባይ የራቁ ናቸው የሚል መልካም ስም አትርፈዋልን?—ዮሐ. 17:16፤ ኢሳ. 2:4፤ 1 ተሰ. 4:3–8

በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች ተለይተው የሚታወቁት ተአምራዊ ፈውስ ለማድረግ ባላቸው ችሎታ ነውን?

ዮሐ. 13:35:- “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” (ኢየሱስ የተናገረው ይህንን ነበር። እርሱን የምናምን ከሆነ ለእውነተኛ ክርስቲያንነት ማረጋገጫ አድርገን የምንመለከተው ተአምራዊ ፈውስን ሳይሆን ፍቅርን ይሆናል።)

ሥራ 1:8:- “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ . . . እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።” (ኢየሱስ ሐዋርያቱን ትቶ ወደ ሰማይ ከመመለሱ በፊት እንዲያከናውኑ የነገራቸው ትልቅ ሥራ ይህ ነበረ እንጂ ፈውስ አልነበረም። በተጨማሪም ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20⁠ን ተመልከት።)

1 ቆሮ. 12:28–30:- “እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን፣ አስቀድሞ ሐዋርያትን፣ ሁለተኛም ነቢያትን፣ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፣ ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን፣ ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ፣ እርዳታንም፣ አገዛዝንም፣ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጎአል። ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን? ሁሉስ ተአምራትን ይሠራሉን? ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸውን?” (ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች የመፈወስ ስጦታ እንደማይኖራቸው በግልጽ ያሳያል።)

የታመሙትን የመፈወስ ችሎታ የአማኞች መለያ ምልክት እንደሚሆን ማርቆስ 16:17, 18 ይናገር የለምን?

ማር. 16:17, 18:- “ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል፤ በስሜ አጋንንት ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ እባቦችን ይይዛሉ፣ የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጐዳቸውም፤ እጃቸውን በድውዮች ላይ ይጭናሉ እነርሱም ይድናሉ።”

እነዚህ ቁጥሮች የሚገኙት በአንዳንድ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ብራና ጽሑፎችና በአምስተኛውና በስድስተኛው መቶ ዘመን እዘአ በተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ነው። ይሁን እንጂ ከዚያ ቀደም ብለው በአራተኛው መቶ ዘመን በተጻፉት የሳይናቲክስና የቫቲካን ኤም ኤስ 1209 የጥንት የግሪክኛ ብራና ጽሑፎች ውስጥ አይገኙም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ የብራና ጽሑፎች ሊቅ የሆኑት ዶ/ር ቢ ኤፍ ዌስትኮት እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “እነዚህ ቁጥሮች . . . እንደ ቅጥያ ሆነው የገቡ ናቸው እንጂ የመጀመሪያው ትረካ ክፍል አይደሉም።” (አን ኢንትሮዳክሽን ቱ ዘ ስተዲ ኦቭ ዘ ጎስፕልስ (የወንጌል ጥናት መግቢያ)፣ ለንደን፣ 1881፣ ገጽ 338) የአምስተኛው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ የነበረው ጀሮም “ይህ ጥቅስ በሁሉም የግሪክኛ የተጠረዙ መጻሕፍት [ኮዴክስ] ውስጥ አይገኝም” ብሏል። (ዘ ላስት ትዌልቭ ቨርስስ ኦፍ ዘ ጎስፕል አኮርዲንግ ቱ ሴንት ማርክ (የቅዱስ ማርቆስ ወንጌል የመጨረሻ አሥራ ሁለት ቁጥሮች)፣ ለንደን፣ 1871፣ ጄ ደብልዩ ቡርጎን፣ ገጽ 53) ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ (1967) እንዲህ ይላል:- “በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ ያሉት ቃላትና የአጻጻፍ ስልት ከቀሪው የማርቆስ ወንጌል ጋር ብዙ ልዩነት ስላላቸው የነዚህ ቁጥሮች [ከቁጥር 9–20] ደራሲ ማርቆስ ራሱ ነው ለማለት ያስቸግራል።” (ጥራዝ 9፣ ገጽ 240) የጥንት ክርስቲያኖች አማኝ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ሲሉ መርዝ እንደጠጡ ወይም እባብ እንደያዙ የሚገልጽ ታሪክ የለም።

በአንደኛው መቶ ዘመን ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች በተአምር የመፈወስ ችሎታ የተሰጣቸው ለምን ነበር?

ዕብ. 2:3, 4:- “እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው እንዴት እናመልጣለን? ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፣ የሰሙትም ለእኛ አጸኑት፣ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ እንደ ፈቀደ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም፣ መንፈስ ቅዱስንም በማደል አብሮ መሠከረለት።” (በዚያን ጊዜ የነበረው አዲስ የክርስቲያን ጉባኤ በእርግጥ የአምላክ ጉባኤ እንደነበረ እነዚህ ተአምራትና ድንቆች አረጋግጠዋል። የክርስቲያን ጉባኤ በእርግጥ የአምላክ ጉባኤ መሆኑ አንድ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ከተረጋገጠ በኋላ ግን ደጋግሞ ማረጋገጥ አስፈላጊ ይሆናልን?)

1 ቆሮ. 12:29, 30፤ 13:8, 13:- “ሁሉ ነቢያት ናቸውን? . . . ሁሉ የመፈወስ ስጦታ አላቸውን? ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን? . . . ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ . . . እንዲህም ከሆነ፣ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።” (እነዚህ ተአምራዊ ስጦታዎች ዓላማቸውን ካከናወኑ በኋላ አንድ ቀን ማቆም ነበረባቸው። እጅግ ውድ ባሕርያት የሆኑት የመንፈስ ፍሬዎች ግን በእውነተኛ ክርስቲያኖች አኗኗር ውስጥ መታየታቸው መቀጠል አለበት።)

አንድ ሰው እስከተፈወሰ ድረስ ፈውሱ የተከናወነበት መንገድ ያን ያህል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነውን?

2 ተሰ. 2:9, 10 የ1980 ትርጉም:- “የዐመፅ ሰው የሚመጣው በሰይጣን ኀይል አሳሳች ተአምራትንና ምልክቶችን፣ አስደናቂ ነገሮችንም በማድረግ ነው፤ . . . እነዚህ ሰዎች የሚጠፉትም ለመዳን የሚያበቃቸውን እውነት ስላልወደዱ ነው።”

ሉቃስ 9:24, 25:- “ነፍሱን [“ሕይወቱን” ሪስ፣ ጀባ፣ ቱኢቨ ] ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ አትርፎ ራሱን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?”

ከማንኛውም ሕመም እውነተኛ ፈውስ ለማግኘት ምን ተስፋ አለን?

ራእይ 21:1–4:- “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፣ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፣ . . . [አምላክ] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።”

ኢሳ. 25:8:- “ሞትን ለዘላለም ይውጣል፣ ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።” (በተጨማሪም ራእይ 22:1, 2)

ኢሳ. 33:24:- “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም።”

አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-

‘በፈውስ ታምናለህ?’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘አምላክ የመፈወስ ኃይል እንዳለው የማያምን ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ያምናል ለማለት አይቻልም። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ሰዎች ይህን የፈውስ ጉዳይ በትክክል የተረዱት አይመስለኝም።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድ ጥቅስ ላንብብልዎትና በዘመናችን ከሚደረገው ነገር በጣም የተለየ ነገር ይፈጸም እንደነበረ እስቲ ልብ ይበሉ። (ማቴ. 10:7, 8) . . . በተጨማሪም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደሚያደርጉ የተነገረና የዘመናችን ፈዋሾች ግን ሊያደርጉ የማይችሉት ነገር እንደተገለጸ አስተውለዋል? (የዛሬዎቹ ፈዋሾች ሙታንን ማስነሣት አይችሉም።)’ (2) ‘በሌሎች ሰዎች ላይ የመፍረድ ሥልጣን የለንም። ቢሆንም ራሳችንን ከአንድ ነገር መጠበቅ እንደሚያስፈልገን በ⁠ማቴዎስ 24:24 ላይ ተገልጾልናል።’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፈውስ የሚናገረው ሁሉ እውነት እንደሆነ በእርግጥ አምናለሁ። ነገር ግን በዚህ የነገሮች ሥርዓት የሚደረግ ፈውስ የሚያስገኘው ጥቅም ጊዜያዊ ብቻ ነው፤ አይደለም እንዴ? በመጨረሻ ሁላችንም እንሞታለን። ሰዎች ሁሉ መልካም ጤንነት አግኝተውና ሞት ቀርቶላቸው እየተደሰቱ የሚኖሩበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? (ራእይ 21:3, 4)’