በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታላቂቱ ባቢሎን

ታላቂቱ ባቢሎን

ፍቺ:- ትምህርቶቻቸውና ተግባሮቻቸው ብቻውን እውነተኛ አምላክ ከሆነው ከይሖዋ አምልኮ ጋር የማይስማሙ ሃይማኖቶችን ሁሉ ያቀፈች የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ናት። የሐሰት ሃይማኖት የተጀመረው ከኖኅ የጥፋት ውኃ በኋላ በባቤል (በኋላ ባቢሎን በተባለው ቦታ) ነው። (ዘፍ. 10:8–10፤ 11:4–9) ከጊዜ በኋላ ባቢሎናዊ የሆኑት ሃይማኖታዊ እምነቶችና ልማዶች ወደ ብዙ አገሮች ተሰራጩ። ስለዚህ ታላቂቱ ባቢሎን የሚለው ስም ለጠቅላላው የሐሰት ሃይማኖት ተስማሚ መጠሪያ ሆኖ ተገኝቷል።

በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸችውን የታላቂቱ ባቢሎንን ማንነት ለመለየት የሚያስችለን ምን መረጃ አለ?

ታላቂቱ ባቢሎን የጥንቷ የባቢሎን ከተማ ልትሆን አትችልም። የራእይ መጽሐፍ የተጻፈው በአንደኛው መቶ ዘመን እዘአ መጨረሻ አካባቢ ሲሆን የሚገልጸውም እስከ ዘመናችን ድረስ የሚፈጸሙትን ሁኔታዎች ነው። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና እንዲህ ይላል:- “ከተማዋ [ባቢሎን] በ539 ከዘአበ በታላቁ ቂሮስ በሚመሩት ፋርሳውያን ተማርካለች። ከዚያም ቆይቶ ታላቁ እስክንድር ባቢሎንን ለምሥራቃዊው የግዛቱ ክፍል ዋና ከተማ ለማድረግ ዕቅድ ነበረው። እርሱ ከሞተ በኋላ ግን ባቢሎን ቀስ በቀስ እየከሰመች ሄደች።” (1956፣ ጥራዝ 3፣ ገጽ 7) ዛሬ ከተማዋ ማንም የማይኖርባት የፍርስራሽ ክምር ሆናለች።

በራእይ መጽሐፍ ምሳሌያዊ አገላለጽ ውስጥ ታላቂቱ ባቢሎን በሌሎች ነገሥታት ላይ የምትሠለጥን “ታላቅ ከተማ” እንዲሁም “መንግሥት” እንደሆነች ተገልጿል። (ራእይ 17:18 አዓት ) እንደ አንድ ከተማ በውስጥዋ ብዙ ድርጅቶች ይኖሯታል። ግዛቷም ብዙ ነገሥታት እንደሚገኙበት ሠፊ ግዛት ዓለም አቀፋዊ ስፋት ይኖረዋል። ከፖለቲካ ገዥዎች ጋር እንደምታመነዝርና በንግድ ሥራ ለተሰማሩት ብዙ ትርፍ እንዳስገኘችላቸውም ተገልጿል። እንዲሁም የዓለም ሦስተኛ ክፍል በመሆን “የአጋንንት ማደሪያ” እና ‘ነቢያትንና ቅዱሳንን’ የምታሳድድ እንደሆነች ተገልጿል።—ራእይ 18:2, 9–17, 24

የጥንቷ ባቢሎን በሃይማኖቷና ይሖዋን በማቃለሏ የታወቀች ነበረች

ዘፍ. 10:8–10 አዓት:- “ናምሩድ . . . ይሖዋን በመቃወም ኃያል አዳኝ ሆነ። . . . የግዛቱም መጀመሪያ . . . ባቤል [በኋላ ባቢሎን እየተባለ የሚታወቀው] . . . ነበር።”

ዳን. 5:22, 23:- “አንተ [የባቢሎን ንጉሥ ብልጣሶር] . . . በሰማይ ጌታ ላይ ኮራህ . . . ከብርና ከወርቅም ከናስና ከብረትም ከእንጨትና ከድንጋይም የተሠሩትን የማያዩትንም የማይሰሙትንም የማያውቁትንም አማልክት አመሰገንህ፤ ትንፋሽህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ አላከበርኸውም።”

በድንጋይ ላይ የተቀረጸ አንድ የጥንት የፋርስ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “በባቢሎን ውስጥ በጠቅላላው ለዋና ዋናዎቹ አማልክት 53 ቤተ መቅደሶች፣ ለማርዱክ 55 የጸሎት ቤቶች፣ ለምድራዊ አማልክት 300 የጸሎት ቤቶች፣ ለሰማይ አማልክት 600፣ ኤሽታር ለተባለችው እንስት አምላክ 180 መሠዊያዎች፣ ኔርጋልና አዳድ ለተባሉት ጣዖታት 180 መሠዊያዎች የነበሩ ሲሆን ሌሎች የተለያዩ አማልክት ደግሞ 12 መሠዊያዎች ነበሩአቸው።”—ዘ ባይብል አዝ ሂስትሪ (መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ታሪክ መጽሐፍ ተደርጎ ሲታይ) ከተባለው መጽሐፍ የተጠቀሰ (ኒው ዮርክ፣ 1964) ደብልዩ ኬለር፣ ገጽ 301

ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና እንዲህ በማለት ያትታል:- “በሱሜራውያን ሥልጣኔ [የባቢሎን ግዛት ክፍል የነበረ ነው] ካህናት የበላይነት ነበራቸው። ርዕሰ ብሔር የነበረው ሉጋል (ቃል በቃል ሲተረጎም ‘ታላቁ ሰው’) የአማልክት ወኪል ነበር።”—(1977)፣ ጥራዝ 3፣ ገጽ 9

በዚህም ምክንያት በራእይ መጽሐፍ የተጠቀሰችው ታላቂቱ ባቢሎን ሃይማኖትን የምታመለክት ናት ቢባል ምክንያታዊ ነው። በአንድ ከተማና በሰፊ ንጉሣዊ ግዛት ስለተመሰለች በአንድ ሃይማኖታዊ ቡድን የተወሰነች ብቻ ሳትሆን እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን የሚቃወሙትን ሃይማኖቶች ሁሉ ያቀፈች ነች።

የጥንቷ ባቢሎን ሃይማኖታዊ ፅንሰ ሐሳቦችና ልማዶች በዓለም በሙሉ በሚገኙ ሃይማኖቶች ውስጥ ሰርጾ ይገኛል

“ግብፅ፣ ፋርስና ግሪክ የባቢሎን ሃይማኖት ተጽዕኖ ታይቶባቸዋል . . . በጥንቱ የግሪክ አማልክት አፈ ታሪኮችና ተረቶች ውስጥ ብዙ ሴማዊ ባሕርያት መኖራቸው በብዙ ምሁራን የታመነ ስለሆነ ተጨማሪ ሐተታ አስፈላጊ አይደለም። እነዚህ ሴማዊ ባሕርያት በአብዛኛው ከባቢሎን የተወረሱ ናቸው።”—ዘ ሪሊጅን ኦቭ ባቢሎንያ ኤንድ አሲሪያ (የባቢሎንና የአሦር ሃይማኖት)፣ (ቦስተን፣ 1898)፣ ጁንየር ኤም ጃስትሮው፣ ገጽ 699, 700

አማልክታቸው:- ሦስትነት በአንድነት ያላቸው አማልክትን ያመልኩ የነበረ ሲሆን ከአማልክታቸው መካከል የተለያዩ የተፈጥሮ ኃይላትንና የሰው ልጆችን የተወሰኑ ተግባራት የሚቆጣጠሩ ይገኙባቸዋል። (ባቢሎኒያን ኤንድ አሲሪያን ሪልጂን (የባቢሎናውያን እና የአሦራውያን ሃይማኖት)፣ ኖርማን፣ ኦክላሆማ፣ 1963፣ ኤስ ኤች ሁክ፣ ገጽ 14–40) “የክርስትና አብያተ ክርስቲያናት የሚያስተምሩት የመለኮታዊ አማልክት የአካል ሦስትነት የተገኘው ፕላቶ አሻሽሎ ካቀነባበረው የጥንት ሕዝቦች የአማልክት ሥላሴነት ፅንሰ ሐሳብ ነው። . . . ይህ ግሪካዊ ፈላስፋ [ፕላቶ] የነበረው የመለኮታዊ ሥላሴ ፅንሰ ሐሳብ . . . በሁሉም የጥንት [አረማውያን] ሃይማኖቶች ውስጥ ሊገኝ ይችላል።”—ኑቮ ዲክሲዮኔር ኡኒቨርሴል (አዲሱ ዓለም አቀፋዊ መዝገበ ቃላት)፣ (ፓሪስ፣ 1865–1870) በኤም ላሻትር የተዘጋጀ፣ ጥራዝ 2፣ ገጽ 1467

በምስሎች መጠቀም:- “ርካሽ የሆኑ የአማልክት ምስሎች በብዛት መገኘታቸው ምስሎች [በሜሶጶጣሚያ ሃይማኖት] በቡድንም ሆነ በግል የአምልኮ ሥርዓታቸው ውስጥ ከፍተኛ ቦታ እንደነበራቸው ያመለክታል። አንድ ምስል የአንድን አምላክ አንዳንድ ገጽታዎችና ጌጦች የሚያሳይ ከሆነና በተገቢ ሁኔታ የሚያዝ ከሆነ ያ አምላክ በምስሉ ውስጥ እንደሚኖር ይታመን ነበር።”—ኤንሸንት ሜሶፖታሚያፖርትሬት ኦቭ ኤ ዴድ ሲቪላይዜሽን (የጥንቷ ሜሶጶጣሚያ—የሞተ ሥልጣኔ ምስል) (ቺካጐ፣ 1964)፣ ኤ ኤል ኦፕንሄም፣ ገጽ 184

ስለ ሞት የነበራቸው እምነት:- “[በባቢሎን ይኖሩ የነበሩ] ሕዝቦችም ሆኑ የሃይማኖት መሪዎች አንድ ጊዜ በሕይወት መኖር የጀመረ አካል ሲሞት ፈጽሞ ይጠፋል የሚል እምነት ኖሯቸው አያውቅም። ሞት ማለት ወደ ሌላ ዓይነት ሕይወት መሸጋገር ማለት ነበር።”—ዘ ሪሊጅን ኦቭ ባቢሎንያ ኤንድ አሲርያ (የባቢሎንና የአሦር ሃይማኖት)፣ ገጽ 556

ካህናት የነበራቸው ቦታ:- “ሃይማኖቱ [የባቢሎናውያን ሃይማኖት] ተለይቶ ከሚታወቅባቸው ባሕርያት አንዱ በካህናትና በምዕመናን መካከል ግልጽ የሆነ ልዩነት መኖሩ ነበር።”—ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ (1948)፣ ጥራዝ 2፣ ገጽ 861

ኮኮብ ቆጠራ፣ ጥንቆላ፣ መተትና የአስማት ሥራ:- የታሪክ ምሁር የሆኑት ኤ ኤች ሴይክ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “[በ]ጥንቷ የባቢሎን ሃይማኖት . . . እያንዳንዱ ዕቃና የተፈጥሮ ኃይል አስማተኞች ወይም ጠንቋዮች ሊቆጣጠሩ የሚችሉት ወይም መንፈስ አለው ተብሎ ይታመን ነበር።” (ዘ ሂስትሪ ኦቭ ኔሽንስ (የብሔራት ታሪክ)፣ ኒው ዮርክ፤ 1928፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ 96) “የጥንት ከለዳውያን [ባቢሎናውያን] ወደፊት የሚሆነውን ነገር በከዋክብት አማካኝነት ለማወቅ ባደረጉት ጥረት በሥነ ፈለግ (አስትሮኖሚ) ትልቅ ዕድገት አድርገዋል። ይህንን ጥበብ ‘ኮኮብ ቆጠራ’ ወይም ‘አስትሮሎጂ’ ብለን እንጠራዋለን።”—ዘ ዶውን ኦቭ ሲቪላይዜሽን ኤንድ ላይፍ ኢን ዘ ኤንሽንት ኢስት (በጥንቱ ምሥራቅ ዓለም የሥልጣኔና የኑሮ ንጋት)፣ (ቺካጐ፣ 1938)፣ አር ኤም ኢንግበርግ፣ ገጽ 230

ታላቂቱ ባቢሎን በአስነዋሪ የድሎት ኑሮ እንደምትኖር ምግባረ ብልሹ ጋለሞታ ናት

ራእይ 17:1–5 እንዲህ ይላል:- “ና በብዙ ውኃዎች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን ጋለሞታ ፍርድ አሳይሃለሁ፤ የምድርም ነገሥታት [የፖለቲካ ገዥዎች] ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ በምድርም የሚኖሩ ከዝሙትዋ ወይን ጠጅ ሰከሩ። . . . በግምባርዋም ምሥጢር የሆነ ስም:- ታላቂቱ ባቢሎን የጋለሞታዎችና የምድር ርኩሰት እናት ተብሎ ተጻፈ።” ራእይ 18:7 እንዲህ ይላል:- “ራስዋን [በአሳፋሪ ሁኔታ] . . . አከበረችና . . . አቀማጠለች።”

ታላላቆቹ የሃይማኖት ድርጅቶች ለተራው ሕዝብ ስቃይ ያስከተሉበት ቢሆንም ሥልጣንና ሀብት ለማግኘት ሲሉ ከፖለቲካ ገዥዎች ጋር መሻረካቸው እውነት አይደለምን? በተጨማሪም ከፍተኛ ቦታ ያላቸው የእነዚህ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ቀሳውስት ሊያገለግሏቸው የሚገባቸው ተራ ሰዎች በከባድ ድህነት እየኖሩ እነርሱ ግን በቅንጦት የተሞላ የድሎት ኑሮ መኖራቸው እውነት አይደለምን?

ክርስቲያን ነን የሚሉ ሃይማኖቶች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ምንም ነገር ከማያውቁት ሃይማኖቶች ጋር በአንድ ወገን ተመድበው የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል ሆነው ሊቆጠሩ የሚችሉት ለምንድን ነው?

ያዕ. 4:4:- “አመንዝሮች ሆይ፣ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።” (ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ የሚናገረውን ቢያውቁም የዓለምን መንገዶች በመከተል የዓለምን ወዳጅነት ከመረጡ ራሳቸውን የአምላክ ጠላቶች ያደርጋሉ።)

2 ቆሮ. 4:4፤ 11:14, 15:- “ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፣ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ።” “ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።” (ስለዚህ ክርስቲያኖች ነን ብለው ቢናገሩም እውነተኛውን አምላክ እርሱ በመረጠው መንገድ የማያመልኩ ሁሉ የይሖዋ ዋነኛ ጠላት የሆነውን ሰይጣን ዲያብሎስን ያከብራሉ። በተጨማሪ 1 ቆሮንቶስ 10:20⁠ን ተመልከት።)

ማቴ. 7:21–23:- “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፣ [ኢየሱስ ክርስቶስን] ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። በዚያ ቀን ብዙዎች:- ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፣ በስምህስ አጋንንት አላወጣንምን፣ በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም:- ከቶ አላወቅኋችሁም፣ እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።”

በአስቸኳይ ከታላቂቱ ባቢሎን መውጣት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ራእይ 18:4:- “ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሰፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ።”

ራእይ 18:21:- “አንድም ብርቱ መልአክ ትልቅ ወፍጮ የሚመስልን ድንጋይ አንሥቶ ወደ ባሕር ወረወረው እንዲህ ሲል:- ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ ተገፍታ ትወድቃለች፤ ከእንግዲህም ወዲህ ከቶ አትገኝም።”

ሉቃስ 21:36:- “እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፣ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ [“ንቁ።” አዓት]”

የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል ሆነው የኖሩ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ግን ሳያውቁ የሞቱ ሰዎች ወደፊት ምን ይሆናሉ?

ሥራ 17:30:- “እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል።”

ሥራ 24:15:- “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን [ይነሣሉ።]” (“ዓመፀኞች” ከተባሉት መካከል እነማን እንደሚነሡ የሚወስነው አምላክ ነው።)

ኢዮብ 34:12:- “በእውነት እግዚአብሔር ክፉ አይሠራም፣ ሁሉን የሚችል አምላክ ፍርድን ጠማማ አያደርግም።”