በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትንሣኤ

ትንሣኤ

ፍቺ:- “ትንሣኤ” ተብሎ የተተረጎመው አናስታሲስ የተባለ የግሪክኛ ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ “ዳግመኛ መቆም” ማለት ሲሆን ከሞት መነሣትን ያመለክታል። “የሙታን ትንሣኤ” የሚለው ሙሉ ሐረግ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ብዙ ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። (ማቴ. 22:31፤ ሥራ 4:2፤ 1 ቆሮ. 15:12) የዕብራይስጡ ቃል ቴኪያት ሐሜቲም ሲሆን ትርጉሙ “የሙታን ወደ ሕይወት መመለስ” ማለት ነው። (ማቴ. 22:23አዓት ባለማጣቀሻ እትም የግርጌ ማስታወሻ) ከሞት የሚነሣ ግለሰብ ቀድሞ የነበረው ሕይወት ይመለስለታል። የግለሰቡ ሕይወት ዓይነት በአምላክ ዝክር ውስጥ ይገኛል። አምላክ ለግለሰቡ ባለው ፈቃድ መሠረት ሰብዓዊ ወይም መንፈሳዊ አካል ይዞ ይነሣል። በሞተበት ጊዜ የነበረውን ባሕርይና የሚያስታውሳቸውን ነገሮች ይዞ ስለሚነሣ ግላዊ ማንነቱ አይለወጥም። የሙታን ትንሣኤ አስደናቂ የሆነ ይገባናል የማንለው የይሖዋ ደግነት መግለጫ ነው። ጥበቡንና ኃይሉን የሚያንጸባርቅ ከመሆኑም በላይ ለምድር ያወጣው የመጀመሪያ ዓላማ የሚፈጸምበት ዝግጅት ነው።

ትንሣኤ ረቂቅ የሆነችው ነፍስና የሥጋ ዳግም ውኅደት ማለት ነውን?

ይህ እውነት እንዲሆን የሰው ልጆች ከሥጋዊ አካል የምትለይ ረቂቅ ነፍስ እንድትኖራቸው ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን እንዲህ ዓይነት ነገር አለች ብሎ አያስተምርም። ይህ እምነት ከግሪካውያን ፍልስፍና የተወሰደ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ የሚሰጠው ትምህርት በገጽ 374–377 ላይ ቀርቧል። ረቂቅና የማትሞት ነፍስ አለች ስለሚለው የሕዝበ ክርስትና እምነት አመጣጥ ለመረዳት ገጽ 377, 378 ተመልከት።

 ኢየሱስ ከሞት የተነሣው ሥጋዊ አካል ይዞ ነውን? በአሁኑስ ጊዜ በሰማይ ሥጋዊ አካል አለውን?

1 ጴጥ. 3:18:- “ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ።” (ኢየሱስ መንፈሳዊ አካል ይዞ ከሞት ተነሥቷል። “ሥጋ” እና “መንፈስ” የሚሉት ቃላት በግሪክኛው ጽሑፍ ውስጥ እርስ በእርሳቸው ተነጻጽረው የተገለጹ ስለሆኑ ሁለቱም ቃሎች ቀጥተኛ ተሳቢ ሆነው የገቡ ናቸው። ስለዚህ አንድ ተርጓሚ “በመንፈስ አማካኝነት ” ብሎ ከተረጎመ “በሥጋ አማካኝነት ” ሥጋ” ካለ ደግሞ “መንፈስ” ብሎ መተርጎም ይኖርበታል።)

ሥራ 10:40, 41:- “እርሱን [ኢየሱስ ክርስቶስን] እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን አስነሣው ይገለጥም ዘንድ ሰጠው፤ ይኸውም ለሕዝብ ሁሉ አይደለም ነገር ግን በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተመረጡ ምስክሮች ለሆንን ለእኛ ነው እንጂ።” (ሌሎች ጭምር ለምን አላዩትም? መንፈሳዊ ፍጡር ስለነበረ ነው። መላእክት ያደርጉት እንደነበረው ሥጋዊ አካል ለብሶ የታየው ደቀ መዛሙርቱ በሚገኙበት ቦታ ብቻ ነው።)

1 ቆሮ. 15:45:- “ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም [አዳም በተፈጠረ ጊዜ የነበረው የፍጽምና አቋም የያዘው ኢየሱስ ክርስቶስ] ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ።”

ሉቃስ 24:36–39 ኢየሱስ ከሙታን ስለተነሣበት አካል ምን ያስረዳል?

ሉቃስ 24:36–39:- “ይህንም ሲነጋገሩ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ:- ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው። ነገር ግን ደነገጡና ፈሩ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። እርሱም:- ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? እኔ ራሴ እንደሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፣ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው።”

የሰው ልጆች መናፍስትን ለማየት ስለማይችሉ ደቀ መዛሙርቱ አንድ ዓይነት ምትሀት ወይም ራእይ የሚመለከቱ መስሏቸው ነበር። (ከ⁠ማርቆስ 6:49, 50 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ ምትሀት እንዳልሆነ አረጋገጠላቸው። ሥጋዊ አካሉን ሊያዩና አጥንቶቹን ሊዳስሱ ይችሉ ነበር። በተጨማሪም ከእነርሱ ጋር ሆኖ በላ። በቀድሞ ዘመናትም መላእክት በተመሳሳይ ሥጋ ለብሰው ታይተዋል፣ ምግብ በልተዋል፣ እንዲያውም አንዳንዶች ሚስት አግብተው ልጆች ወልደዋል። (ዘፍ. 6:4፤ 19:1–3) ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ሁልጊዜ በአንድ ዓይነት ሥጋዊ አካል አልታየም። (ምናልባት ይህን ያደረገው መንፈስ መሆኑን ሊያስገነዝባቸው ፈልጎ ይሆናል።) በዚህም ምክንያት በቅርብ ያውቁት የነበሩ ሰዎች እንኳን ወዲያው ሊለዩት አልቻሉም። (ዮሐ. 20:14, 15፤ 21:4–7) ይሁን እንጂ በተደጋጋሚ ሥጋ ለብሶ በመታየቱና ከዚህ በፊት ያውቁት የነበረው ኢየሱስ ራሱ መሆኑን የሚያሳውቁ ነገሮችን በመናገሩና በማድረጉ ከሙታን ስለመነሣቱ የነበራቸውን እምነት አጠንክሮላቸዋል።

ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን አሁን በሰማይ ባለው አካል ተመልክተውት ቢሆን ኖሮ ጳውሎስ የበለጠ ክብር ስለተቀዳጀው ክርስቶስ በሚናገርበት ጊዜ ኢየሱስ “የክብሩ [የአምላክ ክብር] መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ” ነው አይልም ነበር፤ ምክንያቱም አምላክ መንፈስ ስለሆነና ሥጋ ሆኖ ስለማያውቅ ነው።—ዕብ. 1:3፤ ከ⁠1 ጢሞቴዎስ 6:16 ጋር አወዳድር።

ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ስለታየባቸው ጊዜያት የሚተርኩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በምናነብበት ጊዜ 1 ጴጥሮስ 3:18⁠ንና 1 ቆሮንቶስ 15:45⁠ን በአእምሮአችን ብንይዝ ታሪኩን ለመረዳት አዳጋች አይሆንብንም። እነዚህ ጥቅሶች  ገጽ 333 ላይ ተጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በገጽ 218, 219 ላይ “ኢየሱስ ክርስቶስ” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።

ከክርስቶስ ጋር የሰማያዊ ሕይወት ተካፋይ ለመሆን የሚነሡት እነማን ናቸው? በሰማይስ ምን ያደርጋሉ?

ሉቃስ 12:32:- “አንተ ታናሽ መንጋ፣ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጐ ፈቃድ ነውና አትፍሩ።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (የእነዚህ ቁጥር የተወሰነ በመሆኑ እምነት ያላቸው ሰዎች በሙሉ በዚህ ቡድን ውስጥ የተካተቱ አይደሉም። ወደ ሰማይ የሚሄዱት ለአንድ ዓላማ ነው።)

ራእይ 20:4, 6:- “ዙፋኖችንም አየሁ፣ በእነርሱም ላይ ለተቀመጡት ዳኝነት ተሰጣቸው፤ . . . በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፣ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።”

በተጨማሪም በገጽ 162–168 ላይ “ሰማይ” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።

ሰማያዊ ሕይወት አግኝተው የሚነሡት ሰዎች በሰማይ የበለጠ ክብር ያለው ሥጋዊ አካል ይኖራቸዋልን?

ፊልጵ. 3:20, 21 የ1980 ትርጉም:- “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ . . . ይህንን የተዋረደውን ሰውነታችንን በመለወጥ፣ የእርሱን ክቡር ሰውነት እንዲመስል ያደርገዋል፤ ይህንንም የሚያደርገው ሁሉን በሥልጣኑ ሥር ለማድረግ በሚያስችለው ኀይል ነው።” (ይህ ማለት በመጨረሻ በሰማያት የበለጠ ክብር የሚቀዳጀው ሥጋዊ አካላቸው ነው ማለት ነውን? ወይስ ወደ ሰማያዊ ሕይወት በሚነሡበት ጊዜ ዝቅተኛ የሆነው ሥጋዊ አካላቸው ቀርቶ የበለጠ ክብር የተቀዳጀ መንፈሳዊ አካል እንደሚለብሱ ማመልከቱ ነው? የሚቀጥለው ጥቅስ መልሱን ይስጠን።)

1 ቆሮ. 15:40, 42–44, 47–50:- “ሰማያዊ አካል አለ፣ ምድራዊም አካል አለ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካል ክብር ልዩ ነው፣ የምድራዊም አካል ክብር ልዩ ነው፤ የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ . . . ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፣ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። . . . የፊተኛው ሰው [አዳም] ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው [ኢየሱስ ክርስቶስ] ከሰማይ ነው። መሬታዊው እንደ ሆነ እንዲሁ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው፣ ከሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው። የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ነገር ግን፣ ወንድሞች ሆይ፣ ይህን እላለሁ:- ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም።” (እዚህ ላይ ሁለቱ ዓይነት አካሎች አንድ ናቸው ወይም ሥጋዊ አካል ወደ ሰማይ ይሄዳል ተብሎ የተገለጸ ነገር የለም።)

ኢየሱስ ትንሣኤ ለሰው ልጆች በአጠቃላይ የሚኖረውን ትርጉም ያሳየው እንዴት ነው?

ዮሐ. 11:11, 14–44:- “[ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ:-] ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ አላቸው። . . . ኢየሱስ በግልጥ:- አልዓዛር ሞተ [አላቸው።] . . . ኢየሱስም በመጣ ጊዜ [አልዓዛር] [“በመታሰቢያ” አዓት ] መቃብር እስከ አሁን አራት ቀን ሆኖት አገኘው። . . . ኢየሱስም [ለአልዓዛር እህት ለማርታ:-] ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ [አላት።] . . . በታላቅ ድምፅ:- አልዓዛር ሆይ፣ ወደ ውጭ ና ብሎ ጮኸ። የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፊቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበረ። ኢየሱስም:- ፍቱትና ይሂድ ተዉት አላቸው።” (ኢየሱስ አልዓዛርን ከፍተኛ ደስታ ከሚገኝበት ሌላ ሕይወት መልሶት ከነበረ ይህ ደግነት ነው ለማለት አይቻልም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ አልዓዛርን ከበድንነት ሁኔታ ወደ ሕይወት መመለሱ ለአልዓዛርም ሆነ ለእህቶቹ በጣም ታላቅ የደግነት ድርጊት ነበር። አልዓዛር እንደገና ሕያው ሰው ሆነ።)

ማር. 5:35–42:- “ከምኩራብ አለቃው ቤት ዘንድ የመጡት:- ልጅህ ሞታለች፤ ስለ ምን መምህሩን አሁን ታደክመዋለህ? አሉት። ኢየሱስ ግን የተናገሩትን ቃል አድምጦ ለምኩራቡ አለቃ:- እመን ብቻ እንጂ አትፍራ አለው። . . . የብላቴናይቱን አባትና እናትም ከእርሱ ጋር የነበሩትንም ይዞ ብላቴናይቱ ወዳለችበት ገባ። የብላቴናይቱንም እጅ ይዞ:- ጣሊታ ቁሚ አላት፤ ፍችውም አንቺ ብላቴና ተነሽ እልሻለሁ ነው። ብላቴናይቱም የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረችና ወዲያው ቆማ ተመላለሰች። ወዲያውም ታላቅ መገረም ተገረሙ።” (በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት አጠቃላይ ትንሣኤ በምድር ላይ ሲጀምር በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ወላጆችና ልጆቻቸው እንደገና ሲገናኙ በጣም እንደሚደሰቱ አያጠራጥርም።)

በምድር ላይ ለመኖር ከሞት የሚነሡ ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት ይጠብቃቸዋል?

ሉቃስ 23:43 አዓት:- “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ።” (መላዋ ምድር በክርስቶስ የንግሥና ዘመን ወደ ገነትነት ትለወጣለች።)

 ራእይ 20:12, 13:- “ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፣ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ። . . . እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ።” (የመጻሕፍት መከፈት ስለ መለኮታዊው ፈቃድ ትምህርት የሚሰጥበት ጊዜ እንደሚሆን ያመለክታል። ይህም ከኢሳይያስ 26:9 ጋር ይስማማል። “የሕይወት መጽሐፍ” መከፈቱ ደግሞ ይህን ትምህርት የሚቀበሉ ሰዎች ስማቸውን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ለማስመዝገብ አጋጣሚ እንደሚኖራቸው ያመለክታል። ከፊታቸው ለዘላለም በሰብዓዊ ፍጽምና የመኖር አጋጣሚ ይከፈትላቸዋል።)

በተጨማሪም በገጽ 228–232 ላይ “መንግሥት” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።

አንዳንዶች የሚነሡት ፍርድ ተሰጥቷቸው ወደ ሁለተኛ ሞት እንዲጣሉ ነውን?

የ⁠ዮሐንስ 5:28, 29 ትርጉም ምንድን ነው? እንዲህ ይላል:- “[“በመታሰቢያ” አዓት] መቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ።” ኢየሱስ እዚህ ላይ የተናገረውን ቃል ቆየት ብሎ ለዮሐንስ ከሰጠው ራእይ ጋር በማገናዘብ መረዳት ይኖርብናል። (ራእይ 20:12, 13⁠ን ተመልከት።  በገጽ 336 ላይ ተጠቅሷል።) በቀድሞ ዘመን መጥፎ ያደረጉም ሆኑ መልካም ያደረጉ “እንደ ሥራቸው ይፈረድባቸዋል።” የሚፈረድባቸው ወይም የሚፈረድላቸው በየትኛው ሥራቸው ነው? ሰዎች በቀድሞው ሕይወታቸው በሠሩት ሥራ መሠረት ይፈረድባቸዋል ብለን የምናስብ ከሆነ ይህ አስተሳሰባችን ከ⁠ሮሜ 6:7 ጋር ይጋጫል። ይህ ጥቅስ “የሞተ ከኃጢአቱ ጸድቋል [“ነጻ ሆኗል” አዓት ]” ይላል። በተጨማሪም ሰዎችን ከሞት አስነሥቶ መልሶ ማጥፋት ምክንያታዊ አይደለም። ስለዚህ ኢየሱስ በ⁠ዮሐንስ 5:28, 29 ላይ ወደ ፊት ስለሚፈጸመው ትንሣኤ ሙታን ካመለከተ በኋላ በቁጥር 29 ላይ ወደ ሰብዓዊ ፍጽምና ደረጃ ከደረሱና ፍርድ ከተሰጣቸው በኋላ የሚሆነውን መግለጹ ነበር።

ራእይ 20:4–6 ከሙታን ተነሥተው በምድር ላይ ስለሚኖሩ ሰዎች ምን ያመለክታል?

ራእይ 20:4–6:- “ዙፋኖችንም አየሁ፣ በእነርሱም ላይ ለተቀመጡት ዳኝነት ተሰጣቸው፤ ስለ ኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቆረጡባቸውን ሰዎች ነፍሳት . . . አየሁ፤ . . . ከክርስቶስም ጋር ሺህ ዓመት ኖሩና ነገሡ። የቀሩቱ ሙታን ግን ይህ ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በሕይወት አልኖሩም። ይህ የፊተኛው ትንሣኤ ነው። በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፣ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፣ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።”

አዓት እና ሞፋት አንባቢው ሐሳቦቹን እንዲያገናኝ ለመርዳት ሲሉ “የቀሩት ሙታን ግን ሺው ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በሕይወት አልኖሩም” የሚለውን ክፍል በቅንፍ ውስጥ አስገብተውታል። በግልጽ እንደተመለከተው በመጀመሪያው ትንሣኤ የሚካፈሉት “የቀሩት ሙታን” አይደሉም። ይህን ትንሣኤ የሚያገኙት ከክርስቶስ ጋር ሺህ ዓመት የሚነግሡት ናቸው። ታዲያ ይህ ማለት በሺው ዓመት ዘመን ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ከሚኖሩት ሌላ በሕይወት ያለ ማንም ሰው አይገኝም ማለት ነውን? አይደለም። ምክንያቱም እንዲህ ቢሆን ኖሮ በመጀመሪያው ትንሣኤ የሚካፈሉት ካህናት ሆነው የሚያገለግሏቸው ሰዎች አይኖሯቸውም ነበር። ምድራዊ ግዛታቸውም ማንም ሰው የማይኖርበት ጠፍ ምድር ይሆን ነበር።

ታዲያ የቀሩት ሙታን እነማን ናቸው? በአዳማዊ ኃጢአት ምክንያት የሞቱና ይህ ኃጢአት ካስከተለባቸው ሞት ነፃ መውጣት የሚያስፈልጋቸው፣ ከታላቁ መከራ በሕይወት ያለፉትና በሺው ዓመት ግዛት ውስጥ የሚወለዱ ሰዎች ናቸው።—ከ⁠ኤፌሶን 2:1 ጋር አወዳድር።

ሺው ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በሕይወት ያልኖሩት በምን መንገድ ነው? ይህ ትንሣኤያቸውን የሚያመለክት አይደለም። ይህ በሕይወት መኖር ሰብዓዊ ሕልውና ከማግኘት የበለጠ ነገርን የሚመለከት ነው። አዳማዊው ኃጢአት ካስከተላቸው ወጤቶች ሁሉ ነፃ ወጥቶ ሰብዓዊ ፍጽምና ላይ መድረስ ማለት ነው። ይህ በቁጥር 5 ላይ የሰፈረው አነጋገር በሰማይ የሚሆኑት ‘በሕይወት ኖሩ’ ከሚለው ከቁጥር 4 ቀጥሎ እንደሆነ ልብ በል። ይህ በሰማይ የሚሆኑት የሚያገኙት ሕይወት ከኃጢአት ውጤቶች ነፃ የሆነ ነው። እንዲያውም ያለመሞትን ባሕርይ ይለብሳሉ። (1 ቆሮ. 15:54) ስለዚህ “የቀሩት ሙታን” በሕይወት መኖራቸው ሰብዓዊ ፍጽምና ደረጃ ላይ ደርሰው ሙሉ ሕይወት ማግኘታቸውን ማመልከት ይኖርበታል።

ምድራዊ ትንሣኤ የሚያገኙት እነማን ናቸው?

ዮሐ. 5:28, 29 አዓት:- “በመታሰቢያ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን [የኢየሱስን ድምፅ] ሰምተው የሚወጡበት ሰዓት ይመጣልና በዚህ አታድንቁ።” (“የመታሰቢያ መቃብር” ተብሎ የተተረጐመው የግሪክኛ ቃል ታፎስ [መቃብር፣ የአንድ ግለሰብ የመቀበሪያ ቦታ] ወይም ሔድስ [መቃብር፣ የሞቱ ሰዎች የጋራ መቃብር] አይደለም። ምኔሜይኦን [መታሰቢያ፣ የመታሰቢያ መቃብር] ከሚለው ቃል የተተረጎመ ነው። ቃሉ አጉልቶ የሚገልጸው የአንድ የሞተ ሰው ዝክር ወይም መታሰቢያ አለመጥፋቱን ነው። እነዚህ ሰዎች ሥርየት የሌለው ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት በገሃነም ተጥለው ዝክራቸው ጨርሶ የጠፉ ሰዎች ሳይሆኑ አምላክ አስታውሶ የሚያስነሣቸውና የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ የሚከፍትላቸው ሰዎች ናቸው።—ማቴ. 10:28፤ ማር. 3:29፤ ዕብ. 10:26፤ ሚል. 3:16)

ሥራ 24:15:- “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ።” (ከአምላክ የጽድቅ ሕግጋት ጋር ተስማምተው የኖሩም ሆኑ ካለማወቅ የተነሣ ኃጢአት የሠሩ ሰዎች ከሙታን ይነሣሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እገሌ ይነሣል ወይም አይነሣም ስለማይል አንዳንድ ግለሰቦች ስለመነሣታቸው የሚቀርበውን ጥያቄ በሙሉ አይመልስልንም። ይሁን እንጂ ሁሉን ነገር የሚያውቀው አምላክ በምሕረት የለዘበ ፍርድ እንደሚሰጥና የጽድቅ ደረጃዎችን ችላ ሳይል አድልዎ የሌለበት ውሳኔ እንደሚያደርግ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ከ⁠ዘፍጥረት 18:25 ጋር አወዳድር።)

ራእይ 20:13, 14:- “ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፣ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፣ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ። ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው።” (ስለዚህ በባሕርም ሆነ የሰው ልጆች ምድራዊ የጋራ መቃብር በሆነው በሲኦል የተቀበሩ በአዳማዊው ኃጢአት ምክንያት የሞቱ ሁሉ ከሙታን ይነሣሉ።)

በተጨማሪም “መዳን” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት።

በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሙታን የሚነሡ ከሆነ የት ይኖራሉ?

በምድር ላይ የኖሩ ሰዎች ጠቅላላ ብዛት ግፋ ቢል 20,000,000,000 እንደሚደርስ ይገመታል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው እነዚህ ሰዎች በሙሉ ከሙታን አይነሡም። ሁሉም ይነሣሉ ብለን ብንገምትም እንኳን ለእነዚህ ሰዎች በሙሉ የሚበቃ መኖሪያ ይኖራል። በአሁኑ ጊዜ የምድር የቆዳ ስፋት 147,600,000 ስኩዌር ኪሎሜትር ያህል ነው። ከዚህ ቆዳ ስፋት ግማሽ የሚያክለው ለተለዩ ዓላማዎች ቢውል እንኳን ለእያንዳንዱ ሰው 0.4 ሄክታር የሚያክል ቦታ ይደርሰዋል። ይህም በቂ እህል ሊያበቅልለት ይችላል። በአሁኑ ጊዜ ረሀብ የኖረው ምድር በቂ ምግብ ማስገኘት ስላልቻለች ሳይሆን የፖለቲካ ፉክክርና የንግድ ስግብግብነት በመኖሩ ነው።

በተጨማሪም በገጽ 116, 117 ላይ “ምድር” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።