በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ

አምላክ

ፍቺ:- ከማንም፣ ከምንም በላይ የሆነው አካል። ተለይቶ የሚታወቅበት ስሙ ይሖዋ ነው። የዕብራይስጥ ቋንቋ “አምላክ” ለሚለው ቃል የብርታት፣ የግርማ፣ የክብር፣ የበላይነት ሐሳቦችን በሚያስተላልፍ ቃል ይጠቀማል። እውነተኛ አምላክ እንዳለ ሁሉ ሐሰተኛ አማልክትም አሉ። አንዳንዶቹ ራሳቸውን በራሳቸው አማልክት ያደረጉ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ አምላክነት የተሰጣቸው ከሚያገለግሏቸው ሰዎች ነው።

  በአምላክ መኖር ለማመን የሚያበቁ ጥሩ ምክንያቶች አሉን?

መዝ. 19:1:- “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፣ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል።”

መዝ. 104:24:- “አቤቱ፣ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፤ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፣ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች።”

ሮሜ 1:20:- “የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና።”

ኒው ሳይንቲስት የተባለው መጽሔት እንዲህ ብሏል:- “ተራ ሰዎች ሳይንቲስቶች ሃይማኖት ‘ውሸት መሆኑን ያረጋገጡ’፣ ፈጽሞ በአምላክ የማያምኑ፣ ዳርዊን የአምላክን አለመኖር አረጋግጦ አምላክን በሬሳ ሣጥን ውስጥ የከተተ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተከታታይ የታዩት የሳይንስና የቴክኖሎጂ ግኝቶች ሃይማኖት ፈጽሞ ሊያንሰራራ እንዳይችል ያደረጉ መስሎ ይታያቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በጣም ስህተት ነው።”—ግንቦት 26, 1977፣ ገጽ 478

አንድ የፈረንሳይ የሳይንስ አካዳሚ አባል እንዲህ በማለት ገልጸዋል:- “የተፈጥሮ ሥርዓት በሰው አእምሮ የተፈጠረ ወይም በአንድ ዓይነት የማስተዋል ኃይል የተዘጋጀ አይደለም። . . . ሥርዓት መኖሩ ሥርዓቱን ያደራጀ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል መኖሩን ያመለክታል። ይህም የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ከአምላክ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም።”—ዲዩ ኤግዚስት? ዊ (አምላክ አለ? አዎን)፣ (ፓሪስ፣ 1979)፣ ክርስቲያን ሻባኒስ፣ ፒየር ፖል ግራሴን በመጥቀስ፣ ገጽ 94

የሳይንስ ሊቃውንት ከ100 የሚበልጡ የኬሚካል ንጥረ ነገሮችን ወይም ኤለመንቶችን ለይተው አውቀዋል። የኤለመንቶቹ የአቶም አሠራር ውስብስብ የሒሳብ ስሌት የሚጠይቅ የእርስ በርስ ዝምድና እንዳላቸው ያመለክታል። ፔሬዲክ ቴብል የተባለው የእነዚህን ንጥረ ነገሮች መለያ ባሕርያት የሚያሳይ ቻርት ንድፍ ወጥቶላቸው የተፈጠሩ መሆናቸውን በግልጽ ያመለክታል። ይህን የመሰለ ንድፍ በአጋጣሚ ብቻ የተገኘ ሊሆን አይችልም።

ምሳሌ:- ካሜራ፣ ሬዲዮ፣ ወይም ኮምፒውተር ስናይ በአንድ ጥሩ የማሰብ ችሎታ ባለው ሰው የተሠሩ መሆናቸውን ወዲያው እናምናለን። ታዲያ ከእነዚህ ይበልጥ ውስብስብ የሆኑት እንደ ዓይን፣ ጆሮና የሰው አእምሮ የመሰሉት ነገሮች አንድ ሠሪ ሳይኖራቸው እንዲሁ ተገኙ ማለት ምክንያታዊ ነውን?

በተጨማሪ ገጽ 83–85 ላይ “ፍጥረት” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።

 ክፋትና መከራ መኖሩ አምላክ እንደሌለ ያረጋግጣልን?

የሚከተሉትን ምሳሌዎች ተመልከት:- ቢላዋ ለሰው መግደያነት መዋሉ ቢላዋን የሠራ ሰው እንደሌለ ያረጋግጣልን? ጀት አውሮፕላኖች በጦርነት ጊዜ ቦምብ ለማዝነብ ማገልገላቸው ጀቶቹን ንድፍ አውጥቶ የሠራ ሰው እንዳልነበረ ያረጋግጣልን? በሰው ልጆች ላይ ኀዘን ያስከተለው የእነዚህ ነገሮች አጠቃቀም አይደለምን?

ብዙ በሽታ ሊኖር የቻለው ሰው ራሱ መጥፎ የሆነ የአኗኗር ልማድ ስለሚከተልና ራሱንና ሌሎች ሰዎችን በሚጎዳ መልኩ አካባቢውን ስለሚያበላሽ አይደለምን? ለሰው ልጆች ሥቃይ ምክንያት ከሆኑት ዐበይት ነገሮች መካከል ሰዎች ያካሄዷቸው ጦርነቶች አይደሉምን? በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ምግብ አጥተው እየተሰቃዩ አንዳንድ አገሮች ግን የተትረፈረፈ እህል እንዳላቸው ስናይ ዋነኛው ችግር የሰዎች ስስት መሆኑን አናስተውልምን? እነዚህ ሁሉ ነገሮች አምላክ አለመኖሩን ሳይሆን ሰዎች አምላክ የሰጣቸውን ችሎታና ምድርን በሚያሳዝን ሁኔታ አላግባብ መጠቀማቸውን ነው።

አምላክ በሰው ልጆች ላይ ስለሚደርሰው ነገር ግድ አለውን?

አዎ፣ ግድ አለው። ማስረጃውን ተመልከት:- አምላክ አዳምን ፈጥሮ ሕይወቱን በፍጹም ሁኔታ እንዳስጀመረው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፍ. 1:27, 31፤ ዘዳ. 32:4) ያም ሆኖ ግን ሰው የአምላክን ሞገስ እንዳገኘ ለመቀጠል የሚችለው ፈጣሪውን ሲታዘዝ ብቻ ነበር። (ዘፍ. 2:16, 17) ሰው ፈጣሪውን ቢታዘዝ ኖሮ ሕመም፣ ሥቃይና ሞት ሳያይ በፍጽምና እየተደሰተ ይኖር ነበር። ፈጣሪ አስፈላጊውን መመሪያ ለሰው ከመስጠት በተጨማሪ በኃይሉ በመጠቀም በሰው ልጆች ላይ ምንም ዓይነት ጥፋት እንዳይደርስ ይከላከል ነበር። ሰው ግን የአምላክን መመሪያ ንቆ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር መረጠ። ከተፈጠረበት ዓላማ ውጪ የሆነ ነገር ለማድረግ ሲሞክር በራሱ ላይ መከራ አመጣ። (ኤር. 10:23፤ መክ. 8:9፤ ሮሜ 5:12) ያም ሆኖ ግን አምላክ ባለፉት መቶ ዘመናት እርሱንና መንገዶቹን ስለሚወዱ ብቻ ሊያገለግሉት የሚፈልጉ ሰዎችን በትዕግሥት ሲፈልግ ቆይቷል። ሰዎች ከፍጽምና ጉድለትና ትክክለኛ ካልሆነ አገዛዝ የተነሣ አጥተዋቸው የነበሩትን በረከቶች በሙሉ አግኝተው የሚደሰቱበትን አጋጣሚ ከፊታቸው ዘርግቷል። (ራእይ 21:3–5) አምላክ ሰዎችን ከኃጢአትና ከሞት ለመዋጀት በልጁ በኩል ያደረገው ዝግጅት ለሰው ልጆች ላለው ታላቅ ፍቅር ጥሩ ማስረጃ ነው። (ዮሐ. 3:16) ከዚህም በላይ አምላክ ምድርን የሚያጠፉትን የሚያጠፋበትንና ጽድቅ ወዳዶች ከመጀመሪያ ዓላማው ጋር በመስማማት ደስ ብሏቸው እንዲኖሩ የሚያደርግበትን ዘመን ቀጥሯል።—ራእይ 11:18፤ መዝ. 37:10, 11፤ በተጨማሪ “መከራ” እና “ክፋት” የሚሉትን ዋና ዋና ርዕሶች ተመልከት።

አምላክ በእርግጥ የተወሰነ አካል ነውን?

ዕብ. 9:24:- “ክርስቶስ . . . እግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።”—ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

ዮሐ. 4:24:- “እግዚአብሔር መንፈስ ነው።”

ዮሐ. 7:28 አዓት:- ኢየሱስ “የላከኝ እውን ነው” ብሏል።

1 ቆሮ. 15:44:- “ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ።”

አምላክ በሕይወት የሚኖሩ ሰዎች ያላቸው ዓይነት ስሜት አለውን?

ዮሐ. 16:27:- “እናንተ ስለወደዳችሁኝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ እኔ እንደወጣሁ ስላመናችሁ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋልና።”

ኢሳ. 63:9:- “በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ፣ . . . በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው።”

1 ጢሞ. 1:11 አዓት:- “ደስተኛው አምላክ።”

አምላክ መጀመሪያ አለውን?

መዝ. 90:2:- “ተራሮች ሳይወለዱ፣ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ።”

አምላክ መጀመሪያ የለውም ማለት ምክንያታዊ ነውን? ይህን ጉዳይ አእምሯችን ሙሉ በሙሉ ሊረዳው አይችልም። ለመረዳት አለመቻላችን ግን ይህን ሐቅ ላለመቀበል ምክንያት አይሆነንም። የሚከተሉትን ምሳሌዎች ተመልከት:- (1) ጊዜ:- ጊዜ የጀመረው በዚህ ዓመት ነው ሊል የሚችል ማንም የለም። ሌላው ጉዳይ ደግሞ ሕይወታችን መጨረሻ ያለው ሲሆን ጊዜ ግን መጨረሻ የለውም። ስለዚህ ጊዜን በተመለከተ ሙሉ በሙሉ መረዳት የማንችላቸው ነገሮች ስላሉ ብቻ ጊዜ የሚባል ነገር የለም አንልም። እንዲያውም ሕይወታችንን የምንመራው በጊዜ ነው። (2) ኅዋ:- የጠፈር ተመራማሪዎች የጠፈርን መጀመሪያና መጨረሻ አላገኙም። በጽንፈ ዓለም ውስጥ ይበልጥ ሩቅ የሆነውን አካባቢ በተመለከቱ መጠን ከዚያ ወዲያም ሌላ ነገር ያለ ሆኖ ያገኙታል። ያገኙትን መረጃ አንቀበልም አይሉም። ብዙ ሊቃውንት ጠፈር ወይም ኅዋ መጨረሻ እንደሌለው ይናገራሉ። የአምላክ ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይደለም።

ሌሎች ምሳሌዎች:- (1) የጠፈር ተመራማሪዎች የፀሐይ እምብርት የሙቀት መጠን 15,000,000 ዲግሪ ሴንቲግሬድ (27,000,0000 ፋራናይት) እንደሆነ ይናገራሉ። ስለዚህ ከፍተኛ የሆነ የሙቀት መጠን ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ስለማንችል ሐሳቡን አንቀበልም እንላለንን? (2) እኛ የምንገኝበት ሚልኪ ዌይ የተባለው የከዋክብት ረጨት (ጋላክሲ) ትልቅ ከመሆኑ የተነሣ ብርሃን በአንድ ሴኮንድ ከ300,000 ኪሎ ሜትር (186,000 ማይልስ) እየተጓዘ ከአንዱ ጫፍ ወደ አንዱ ጫፍ ለመድረስ 100,000 ዓመት ይወስድበታል። አእምሯችን እንዲህ የመሰለውን ርቀት ይረዳልን? ቢሆንም በሳይንሳዊ መረጃ የተደገፈ ስለሆነ እንቀበለዋለን።

ይበልጥ ምክንያታዊ የሚሆነው የትኛው ነው? ጽንፈ ዓለም ሕያው በሆነና የማሰብ ችሎታ ባለው ፈጣሪ የተገኘ ነው ማለት ወይስ ጽንፈ ዓለም ሕይወት ከሌለው ነገር የማሰብ ችሎታ ያለው ሠሪ ሳያስፈልግ በአጋጣሚ ተገኘ ማለት? አንዳንድ ሰዎች ሁለተኛውን አባባል ይመርጣሉ። ይህን የሚመርጡት ባሕርዩን ሙሉ በሙሉ የማይረዱትን ፈጣሪ ሕልውና አምነው ለመቀበል ስለማይፈልጉ ነው። ይሁን እንጂ ሳይንቲስቶች በሕያዋን ሴሎች ውስጥ የሚገኙትና የእነዚህን ሴሎች እድገት የሚቆጣጠሩት ጂኖች (የዘር ባሕርያት ተሸካሚዎች) እንዴት እንደሚሠሩ ሙሉ በሙሉ እንደማያውቁ የታወቀ ነው። የሰው አእምሮም የሚሠራውን ሥራ ሙሉ በሙሉ አያውቁም። ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሮች ፈጽሞ የሉም ብሎ የሚክድ ሰው አለን? ታዲያ በጣም የተወሳሰበ ንድፍና እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለውን ጽንፈ ዓለም ስላስገኘው ታላቅ አምላክ በዝርዝር ማወቅ ይገባናል ብለን ማሰብ እንችላለንን?

በአምላክ ስም መጠቀም አስፈላጊ ነውን?

ሮሜ 10:13:- “የጌታን [“የይሖዋን” አዓት] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።”

ሕዝ. 39:6 አዓት:- “እኔ ይሖዋ መሆኔንም ሰዎች ማወቅ ይኖርባቸዋል።”

ኢየሱስ ለአባቱ “ስምህን [ለተከታዮቼ] አስታወቅኋቸው፣ አስታውቃቸውማለሁ” ብሎአል።—ዮሐ. 17:26

በተጨማሪ በገጽ 197, 198 ላይ “ይሖዋ” በሚለው ሥር ተመልከት።

አንድ ሃይማኖት እስከኖረን ድረስ የትኛውንም አምላክ ብናገለግል ለውጥ ያመጣልን?

1 ቆሮ. 10:20:- “አሕዛብ የሚሠዉት ለአጋንንት እንዲሆን እንጂ ለእግዚአብሔር እንዳይሠዉ እላለሁ።”

2 ቆሮ. 4:4:- “የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፣ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ።” (እዚህ ላይ ዲያብሎስ “አምላክ” ተብሎ ተጠርቷል። 1 ዮሐንስ 5:19፤ ራእይ 12:9⁠ን ተመልከት።)

ማቴ. 7:22, 23:- “በዚያ ቀን ብዙዎች [ኢየሱስ ክርስቶስን]:- ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፣ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፣ በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም:- ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።” (ክርስቲያን ነኝ ማለት እንኳን ብቻውን ተቀባይነት ባለው መንገድ እውነተኛውን አምላክ በማገልገል ላይ ለመሆናችን ዋስትና አይሆንም።)

በተጨማሪ በገጽ 321, 322 ላይ “ሃይማኖት” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።

ይሖዋ ‘ብቸኛው እውነተኛ አምላክ’ ከሆነ ኢየሱስ ምን ዓይነት “አምላክ” ነው?

ኢየሱስ ራሱ አባቱን “ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከው” ብሎ ጠርቶታል። (ዮሐ. 17:3 የ1980 ትርጉም ) ይሖዋ ራሱ “ከእኔ ሌላ አምላክ የለም” ብሏል። (ኢሳ. 44:6) ሐዋርያው ጳውሎስ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች “አንድ አምላክ አብ . . . አለ” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 8:5, 6) ስለዚህ ይሖዋን የመሰለ አካል የለም። ማንም የእርሱን ቦታ አይጋራም። ይሖዋ አምልኮ ከሚሰጣቸው ጣዖታትና ሰዎች እንዲሁም ከሰይጣን በጣም የተለየ ነው። እነዚህ ሁሉ ሐሰተኛ አማልክት ናቸው።

ኢየሱስ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “አምላክ” እና “ኃያል አምላክ” ተብሎ ተጠርቷል። (ዮሐ. 1:1 አዓት፤ ኢሳ. 9:6) ይሁን እንጂ ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ ሲገለጽ ኢየሱስ ግን አንድም ቦታ ላይ ሁሉን ቻይ ተብሎ አልተጠራም። (ዘፍ. 17:1 የ1980 ትርጉም ) ኢየሱስ የአምላክ ‘ክብር ነጸብራቅ’ እንደሆነ ተነግሯል። እሱ የሚያንጸባርቀው ክብር ምንጭ ግን አብ ነው። (ዕብ. 1:3) ኢየሱስ በምንም መንገድ የአባቱን ቦታ ለመውሰድ አይፈልግም። እንዲያውም “ለጌታ [“ለይሖዋ” አዓት ] ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ” ብሏል። (ሉቃስ 4:8) ኢየሱስ “በአምላክ መልክ” ይኖራል። “በኢየሱስ ስም ጉልበት ሁሉ እንዲንበረከክ” አብ አዝዟል። ይህ ሁሉ የሆነው ግን “ለእግዚአብሔር አብ ክብር” ነው።—ፊልጵ. 2:5–11 አዓት፤ በተጨማሪ ገጽ 213–217⁠ን ተመልከት።

አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-

‘በአምላክ አላምንም’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ምን ጊዜም በአምላክ አምነው አያውቁም? . . . ወደዚህስ መደምደሚያ ከመድረስዎ በፊት ሊያሳምንዎት የሚችሉ መረጃዎችን መርምረዋል?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘ይህ እንድንወያይበት በጣም የምፈልገው ርዕስ ነው። ብዙ አስቤበታለሁ። የሚከተሉትን ነጥቦች በጣም ጠቃሚ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። . . . ( በገጽ 146 ላይ “በአምላክ መኖር ለማመን የሚያበቁ ጥሩ ምክንያቶች አሉን?” የሚለውን ንዑስ ርዕስ ተመልከት። በተጨማሪ በገጽ 83–85 ላይ “ፍጥረት” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።)’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘ፈጣሪ አለ ብዬ አላምንም ማለትዎ ነው ወይስ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ብዙ ግብዝነት ስላዩ በሚያስተምሩት ትምህርት አላምንም ማለትዎ ነው?’ መልሳቸው ሁለተኛው ከሆነ እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘በሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናትና በእውነተኛው ክርስትና መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። ሕዝበ ክርስትና ሰዎችን እንደምትጨቁን የታወቀ ነው፣ ክርስትና ግን ሕዝቦችን አልጨቆነም። ሕዝበ ክርስትና ጦርነት አካሂዳለች፣ የክርስትና እምነት ግን አላካሄደም። ሕዝበ ክርስትና ተገቢ የሥነ ምግባር መመሪያ አትሰጥም፣ የክርስትና እምነት ግን ይሰጣል። የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ሕዝበ ክርስትናን አይደግፍም። እንዲያውም ሕዝበ ክርስትናን ያወግዛል።’

ሌላ አማራጭ:- ‘እንደ እርስዎ ከሚሰማቸው ሌሎች ሰዎች ጋር ደስ የሚል ውይይት አድርጌ ነበር። አንዳንዶች እውነት አምላክ ካለ በምድር ላይ ይህን የሚያክል ሥቃይና ክፋት የኖረው ለምንድን ነው? ይላሉ። እርስዎስ እንዲህ ይሰማዎታል? (ይህ ከሆነ  በገጽ 147, 148 ላይ “ክፋትና መከራ መኖሩ አምላክ እንደሌለ ያረጋግጣልን?” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር በቀረበው ሐሳብ ተጠቀም።)’

‘የማምነው የማየውን ብቻ ነው፤ አምላክን ግን አይቼው ስለማላውቅ አላምንበትም’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘እንዲህ የመሰለ አመለካከት በዛሬው ጊዜ የተለመደ ሆኗል። ይህም የሆነበት ምክንያት አለው። የምንኖረው ቁሳዊ ሀብትን ከሁሉ በላይ ከፍ አድርጎ በሚመለከት ኅብረተሰብ ውስጥ ነው። እርስዎ ግን ከሐቁ ለመሸሽ የሚፈልጉ ሰው አይደሉም። ልክ አይደለሁም?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘አንዳንድ ነገሮችን በዓይናችን ለማየት ባንችልም መኖራቸውን የሚያሳምነን ጥሩ ምክንያት ስላለን አሉ ብለን እናምን የለም? የምንተነፍሰውን አየር እንውሰድ። ነፋስ ሲነፍስ አየር እንዳለ ይሰማናል። የማናየው ነገር ቢሆንም ሳንባችን ውስጥ ገብቶ እንደሚሞላው ለመናገር እንችላለን። አየር መኖሩን እንድናምን ያደረገን ውጤቱን ለማየት መቻላችን አይደለም?’ (2) ‘የመሬትን የስበት ኃይልም ማየት አንችልም። አንድ ነገር በምንጥልበት ጊዜ ስበት እንዳለ እንረዳለን። ሽታም ቢሆን አይታየንም። አፍንጫችን ግን ሽታውን ይለያል። የድምፅ ሞገዶችንም ልናያቸው አንችልም፣ ጆሯችን ግን ይጠልፋቸዋል። እንግዲያው ልናያቸው ባንችልም በቂ ምክንያት እስካለን ድረስ የምናምንባቸው ነገሮች መኖራቸው እውነት አይደለም?’ (3) ‘ታዲያ የማይታየው አምላክ በእርግጥ እንደሚኖር የምናምንበት ማስረጃ ይኖራል? ( በገጽ 146, 147 ላይ “በአምላክ መኖር ለማመን የሚያበቁ ጥሩ ምክንያቶች አሉን?” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ተመልከት።)’

‘ስለ አምላክ የራሴ የሆነ አስተሳሰብ አለኝ’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ስለዚህ ጉዳይ በጥሞና የሚያስቡና በአምላክ የሚያምኑ ሰው ሆነው በማግኘቴ ደስ ብሎኛል። ግን ስለ አምላክ ያለዎት አስተሳሰብ ምንድን ነው?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘የምናምንበት ነገር አምላክ ከተናገረው ጋር የሚስማማ መሆኑን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን እንደሚቀበሉ እርግጠኛ ነኝ። በዚህ ጉዳይ ላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሐሳብ ባካፍልዎትስ? (መዝ. 83:18)’