በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አይሁዳውያን

አይሁዳውያን

ፍቺ:- በዛሬው ጊዜ ቃሉ በብዛት የሚሠራበት የዕብራውያን ዝርያ ያላቸውንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡትን ሰዎች ለማመልከት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈሳዊ ሁኔታ አይሁዳውያን የሆኑና “የአምላክ እስራኤል” የተባሉ ክርስቲያኖች እንዳሉ ያስገነዝባል።

የዛሬዎቹ ሥጋዊ አይሁዳውያን የአምላክ ምርጥ ሕዝብ ናቸውን?

ብዙዎቹ አይሁዳውያን እንደዚህ እንደሆኑ ያምናሉ። ኢንሳይክሎፔድያ ጁዳይካ (ኢየሩሳሌም፣ 1971፣ ጥራዝ 5፣ ዓምድ 498) እንዲህ ይላል:- “ምርጥ ሕዝብ የሚለው አጠራር የእስራኤል ሕዝብ ተለይቶ የሚታወቅበት የተለመደ መጠሪያ ሲሆን ይህ ሕዝብ ከአጽናፈ ዓለሙ አምላክ ጋር ለማንም ሌላ ሕዝብ ያልተሰጠና ልዩ የሆነ ግንኙነት ያለው መሆኑን ያመለክታል። ይህ ሐሳብ በአይሁዳውያን ታሪክ ሁሉ ማዕከላዊ ቦታ ይዞ ቆይቷል።”— ዘዳግም 7:6–8፤ ዘጸአት 19:5⁠ን ተመልከት።

በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች ከዚህ ጋር የሚመሳሰል አመለካከት አላቸው። የአትላንታው ጆርናል ኤንድ ኮንስቲትዩሽን (ጥር 22፣ 1983፣ ገጽ 5–ቢ) “ሃይማኖት” በሚለው ዓምድ ሥር እንዲህ በማለት ሪፖርት አድርጓል:- “[በፊላደልፊያ የቴምፕል ዩኒቨርስቲ የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ፖል ኤም ቫን ቡረን] አብያተ ክርስቲያናት አምላክ ሕዝቡ የነበሩትን እስራኤላውያንን ትቶ ‘በአዲስ እስራኤል’ ተክቷቸዋል የሚለውን ለበርካታ መቶ ዘመናት የቆየ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት በመቃረን ‘በአምላክና በአይሁዳውያን ሕዝብ መካከል ያለው ቃል ኪዳን ዘላለማዊ ነው’ ይላሉ በማለት ተናግረዋል። ይህ አስደናቂ የሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ወዲህና ወዲያ ማዶ በሚገኙት አገሮች በሚኖሩት ፕሮቴስታንቶችም ሆነ ካቶሊኮች ላይ ታይቷል።” ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ (የካቲት 6፣ 1983፣ ገጽ 42) እንዲህ ሲል ጨምሮ ይገልጻል:- “በጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የሃይማኖት ፕሮፌሰርና የዌስሊያን ወንጌላዊ የሆኑት ቲሞቲ ስሚዝ ‘ወንጌላዊው የምዕራቡ ዓለም ለእስራኤል ከፍተኛ ግምት ስላለውና አምላክ ከእስራኤል ጐን ስለሆነ እስራኤል ለምታደርገው ሁሉ ድጋፍ መሰጠት አለበት የሚል እምነት አለው’ ብለው ተናግረዋል።” በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ አንዳንዶች ሥጋዊ እስራኤላውያን በሙሉ በመጨረሻ ወደ ክርስትና ተለውጠው ይድናሉ ብለው ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ በአምላክና በእስራኤል መካከል ተፈጥሮ የቆየው ትስስር ጽኑ ስለሆነ በክርስቶስ በኩል መታረቅ ያለባቸው አሕዛብ ብቻ ናቸው የሚል ሐሳብ ያቀርባሉ።

እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ እንመልከት:- እስራኤላውያን ከባቢሎን ግዞት በኋላ ወደ አገራቸው በተመለሱ ጊዜ እውነተኛውን አምልኮ አምላክ በሰጣቸው ምድር ላይ መልሰው ማቋቋም ነበረባቸው። በቅድሚያ ማከናወን ከነበረባቸው ነገሮች እንዱ በኢየሩሳሌም የይሖዋን ቤተ መቅደስ እንደገና መሥራት ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ቤተ መቅደስ በ70 እዘአ በሮማውያን ከጠፋ ወዲህ ዳግመኛ ተሠርቶ አያውቅም። እንዲያውም የጥንቱ ቤተ መቅደስ በነበረበት ቦታ ላይ የእስላሞች መስጊድ ይገኛል። ታዲያ ዛሬ በሙሴ ሕግ እንገዛለን የሚሉት አይሁዳውያን በኢየሩሳሌም ከተማ የሠፈሩት የአምላክ የተመረጡ ሕዝቦች ስለሆኑ ቢሆን ኖሮ ለአምላካቸው አምልኮ የተወሰነውን ቤተ መቅደስ መልሰው አይሠሩትም ነበርን?

ማቴ. 21:42, 43:- “ኢየሱስ [የካህናት አለቆችንና በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩትን የአይሁድ ሽማግሌዎች] እንዲህ አላቸው:- ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከእግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] ዘንድ ሆነ፣ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን? ስለዚህ እላችኋለሁ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች።”

ማቴ. 23:37, 38:- “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፣ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም። እነሆ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል።”

አምላክ ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን አይሁዳውያን ምን ጊዜም የአምላክ የተመረጡ ሕዝቦች ሆነው እንደሚኖሩ ዋስትና ይሰጣቸዋልን?

ገላ. 3:27–29:- “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና። አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፣ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፣ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና። እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ፣ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ስለዚህ በአምላክ አመለካከት የአብርሃም ዘር ለመሆን በሥጋ ከአብርሃም መወለድ አስፈላጊ መሆኑ ቀርቷል።)

ወደፊት አይሁዳውያን በሙሉ ክርስቶስን አምነው ዘላለማዊ መዳን ያገኛሉን?

ሮሜ 11:25, 26:- “ወንድሞች ሆይ፣ ልባሞች የሆናችሁ እንዳይመስላችሁ ይህን [“ቅዱስ” አዓት ] ምሥጢር ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፤ የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ ድንዛዜ በእስራኤል በአንዳንድ በኩል ሆነባቸው፤ እንደዚሁም [“በዚህ መንገድ” ቱኢቨ፤ “ስለዚህ” ኮክ፣ ባይ፤ “በዚሁ ዐይነት” የ1980 ትርጉም፣ አዓት፤ በግሪክኛ ሆውቶስ ] እስራኤል ሁሉ ይድናል።” (“እስራኤል ሁሉ” የሚድኑት አይሁዳውያን በሙሉ ሲለወጡ ሳይሆን ከአሕዛብ ዘንድ ሰዎች ‘በመምጣታቸው’ እንደሆነ ልብ በል። አንዳንድ ተርጓሚዎች ቁጥር 26⁠ን በሚከተለው መንገድ ተርጉመውታል:- “ከዚህ በኋላ የቀሩት እስራኤል ይድናሉ።” ኤ ማኑዋል ግሪክ ሌክሲከን ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት [ኤድንበርግ፣ 1937፣ ጂ አቦት–ስሚዝ፣ ገጽ 329] ሆውቶስ የሚለውን ቃል “በዚህ መንገድ፣ እንደዚሁ፣ ስለዚህ” በማለት ተርጉሞታል።)

በ⁠ሮሜ 11:25, 26 ላይ የተመዘገበውን በትክክል ለመረዳት ቀደም ብሎ በሮሜ መጽሐፍ ላይ “ከውጪ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለም፣ ከውጪ የሚደረግ የሥጋ መገረዝም መገረዝ አይደለም። ከውስጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፤ ግርዘቱም በመንፈስ የተደረገ የልብ መገረዝ እንጂ በተጻፈ ሕግ አይደለም” የሚለውን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት አለብን። (2:28, 29 አዓት ) “ከእስራኤል የሚወለዱ ሁሉ እስራኤል አይደሉም።”—9:6

አይሁዳውያን ለመዳን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ያስፈልጋቸዋልን?

ኢሳይያስ 53:1–12 ‘የብዙዎችን ኃጢአት ለመሸከምና በደለኞችን ለማስታረቅ’ መሲሕ እንደሚሞት ትንቢት ተነግሯል። ዳንኤል 9:24–27 የመሲሕን መምጣትና መሞት ‘ከኃጢአት ፍጻሜና ከበደል ሥርየት’ ጋር ያያይዘዋል። አይሁዳውያን አማላጅና የኃጢአት ሥርየት ያስፈልጋቸው እንደነበረ ሁለቱም ጥቅሶች ያሳያሉ። መሲሑን ሳይቀበሉ መሲሑን የላከውን አምላክ ሞገስ ለማግኘት ይችላሉን?

ሥራ 4:11, 12:- “[ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ ተገፋፍቶ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ለነበሩት የአይሁድ አለቆችና ሽማግሌዎች ስለ ክርስቶስ እንዲህ ሲል ተናገረ:-] እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፣ የማዕዘን ራስ የሆነው ይህ ድንጋይ ነው። መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።” (የሥጋዊ የእስራኤል ብሔር በአምላክ ዘንድ የነበረውን ልዩ የሆነ መለኮታዊ ሞገስ ቢያጣም ግለሰብ አይሁዳውያን እንደ ማንኛውም ሌላ ሕዝብ በመሲሑ ኢየሱስ በኩል ከተገኘው መዳን ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ በሩ ተከፍቶላቸዋል።)

ዛሬ በእስራኤል ምድር የሚታዩት ሁኔታዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ናቸውን?

ሕዝ. 37:21, 22:- “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- እነሆ፣ የእስራኤልን ልጆች ከሄዱባቸው ከአሕዛብ መካከል እወስዳለሁ ከሥፍራውም ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ፤ በምድርም ላይ በእስራኤልም ተራሮች ላይ አንድ ሕዝብ አደርጋቸዋለሁ፣ አንድ ንጉሥም በሁላቸው ላይ ይነግሣል።” (ዛሬ እስራኤል ከዳዊት ንጉሣዊ መስመር የተገኘ ንጉሥ የላትም። የዛሬዎቹ እስራኤላውያን ያላቸው መንግሥት ሪፑብሊክ ነው።)

ኢሳ. 2:2–4:- “በዘመኑም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፣ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፣ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበሰባሉ። . . . ብዙዎች አሕዛብ ሄደው:- ኑ፣ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በጐዳናውም እንሄዳለን ይላሉ። . . . ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።” (የጥንቱ ቤተ መቅደስ በነበረበት በኢየሩሳሌም ዛሬ ‘የያዕቆብ አምላክ ቤት’ አይገኝም። ከዚህ ይልቅ ቤተ መቅደሱ በነበረበት ቦታ ላይ የሚገኘው የእስላሞች መስጊድ ነው። እስራኤልም ሆነች ጐረቤቶቿ ‘ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ ለማድረግ’ የወሰዱት ምንም እርምጃ የለም። ለኅልውናቸው የሚታመኑት በወታደራዊ ዝግጁነታቸው ላይ ነው።)

ኢሳ. 35:1, 2:- “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፣ በረሃውም ሐሴትን ያደርጋል እንደ ጽጌ ረዳም ያብባል። እጅግ ያብባል በደስታና በዝማሬ ሐሴትን ያደርጋል፤ የሊባኖስ ክብር፣ የቀርሜሎስና የሳሮን ግርማ ይሰጠዋል፤ የእግዚአብሔርንም ክብር የአምላካችንም ግርማ ያያሉ።” (በእስራኤል ምድር በደን ተከላና በመስኖ ሥራ ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል። ይሁን እንጂ መሪዎቿ ለጌታ አምላክ ክብር አልሰጡም። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ቤንጉሪዮን እንደተናገሩት:- “እስራኤል . . . በሳይንስ ኃይልና ቀዳሚ የመሆን መንፈስ በመያዝ በረሃውን ለማሸነፍና ዲሞክራሲ እንዲያብብ ለማድረግ ቆርጣለች።”)

ዘካ. 8:23:- “በዚያን ዘመን ከአሕዛብ ቋንቋ ሁሉ አሥር ሰዎች የአንዱን አይሁዳዊ ሰው ልብስ ዘርፍ ይዘው:- እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ ይላሉ።” (ትንቢቱ የሚናገረው ስለ የትኛው አምላክ ነው? ከቅዱሳን ጽሑፎች አንዱ በሆነው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ብቻ የአምላክ ስም በዕብራይስጥ ቋንቋ [יהוה አብዛኛውን ጊዜ ይሖዋ ተብሎ የሚተረጐመው] ከ130 ጊዜ በላይ ተጽፎ ይገኛል። ዛሬ አንድ ሰው ይህንን ስም ቢጠራ አይሁዳዊ መሆን አለበት ብለው ሰዎች ያስባሉን? በጭራሽ አያስቡም። አይሁዳውያን በሙሉ ከአጉል እምነት የተነሣ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ጀምረው የአምላክን የግል ስም አይጠሩም። ዛሬ በሥጋዊ እስራኤላውያን ላይ ሃይማኖታዊ ስሜት መቀስቀሱ የዚህ ትንቢት ፍጻሜ ሊሆን አይችልም።)

ታዲያ፣ ዛሬ በእስራኤል ምድር የሚታዩትን ሁኔታዎች እንዴት መመልከት ይገባል? እነዚህ ድርጊቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተተነበዩት ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች አንድ ክፍል ብቻ ናቸው። ከእነዚህ በትንቢት ከተነገሩት ሁኔታዎች መካከል ጦርነት፣ ዓመፅ፣ የፍቅር መቀዝቀዝና የገንዘብ ፍቅር ይገኝበታል።—ማቴ. 24:7, 12፤ 2 ጢሞ. 3:1–5

እስራኤል ተመልሳ እንደምትቋቋም የሚናገሩት ትንቢቶች በዛሬው ጊዜ የሚፈጸሙት በእነማን ላይ ነው?

ገላ. 6:15, 16:- “አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። በዚህ ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን።” (ስለዚህ “የእግዚአብሔር እስራኤል” መሆን የሚቻለው በቤቱ ውስጥ የሚገኙትን ወንዶች ሁሉ እንዲገርዝ ለአብርሃም የተሰጠውን ብቃት በማሟላት አይደለም። ከዚያ ይልቅ በ⁠ገላትያ 3:26–29 ላይ እንደተገለጸው ለክርስቶስ የሆኑትና በመንፈስ የተወለዱት የአምላክ ልጆች ‘በእውነት የአብርሃም ዘር ናቸው።’)

ኤር. 31:31–34:- “እነሆ፣ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፣ ይላል እግዚአብሔር . . . እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፣ እያንዳንዱም ወንድሙን:- እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፣ ይላል እግዚአብሔር።” (ይህ ቃል ኪዳን የተገባው ከሥጋዊ እስራኤል ጋር ሳይሆን የሰማያዊ ሕይወት ተስፋ ካላቸው ከኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሣዊ ተከታዮች ጋር ነው። ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ ባቋቋመ ጊዜ ጽዋውን አንስቶ ለተከታዮቹ ሰጣቸውና እንዲህ አለ:- “ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው።” [1 ቆሮ. 11:25])

ራእይ 7:4:- “የታተሙትንም ቁጥር ሰማሁ፤ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ።” (በሚቀጥሉት ቁጥሮች ላይ ‘የሌዊ ነገድ’ እና ‘የዮሴፍ ነገድ’ ተጠቅሰዋል። እነዚህ ነገዶች ግን ከ12ቱ የሥጋዊ እስራኤል ነገዶች ዝርዝር ውስጥ የሉም ነበር። ከእያንዳንዱ ነገድ የመጡት ሰዎች ሁሉ ማኅተም እንደተደረገባቸው ሲናገር የዳንና የኤፍሬም ነገዶች ግን አልተጠቀሱም። [ከ⁠ዘኁልቁ 1:4–16 ጋር አወዳድር።] ይህ ጥቅስ የሚናገረው ከክርስቶስ ጋር ሰማያዊ መንግሥት ይወርሳሉ በማለት ራእይ 14:1–3 ስለሚናገርላቸው የአምላክ መንፈሳዊ እስራኤል መሆን ይኖርበታል።)

ዕብ. 12:22:- “ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፣ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፣ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት [ደርሳችኋል።]” (ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች የአምላክ ተስፋዎች ይፈጸሙባታል ብለው ተስፋ የሚያደርጉት “ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም” እንጂ ምድራዊቱ ኢየሩሳሌም አይደለችም።)