በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንደገና መወለድ

እንደገና መወለድ

ፍቺ:- እንደገና መወለድ በውኃ መጠመቅን (‘ከውኃ መወለድን’) እና በአምላክ መንፈስ ተወልዶ (‘ከመንፈስ በመወለድ’) የአምላክን ልጅነት አግኝቶ በመንግሥቱ የመካፈልን ተስፋ ማግኘትን የሚያጠቃልል ነገር ነው። (ዮሐ. 3:3–5) ኢየሱስና ከእርሱ ጋር ሆነው ሰማያዊውን መንግሥት የሚወርሱት 144,000ዎች ይህን ዓይነት ልደት አግኝተዋል።

“እንደገና መወለድ” ለአንዳንድ ክርስቲያኖች አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

አምላክ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው የታመኑ ሰዎች በሰማያዊው መንግሥት ከኢየሱስ ጋር እንዲሆኑ ዓላማ አለው

ሉቃስ 12:32:- “አንተ ታናሽ መንጋ፣ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ።”

ራእይ 14:1–3:- “አየሁም፣ እነሆም፣ በጉ [ኢየሱስ ክርስቶስ] በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፣ ከእርሱም ጋር . . . [ከምድር የተዋጁት] መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ።” (“ሰማይ” በሚለው ርዕስ ገጽ 166, 167⁠ን ተመልከት።)

ሰዎች ሥጋና ደም ይዘው ወደ ሰማይ ሊሄዱ አይችሉም

1 ቆሮ. 15:50:- “ወንድሞች ሆይ፣ ይህን እላለሁ:- ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፣ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም።”

ዮሐ. 3:6:- “ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፣ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው።”

ከሰማያዊቱ መንግሥት ተካፋይ የሚሆኑት እንደገና የተወለዱትእና በዚህ ምክንያት የአምላክ ልጆች ለመሆን የበቁት ብቻ ናቸው

ዮሐ. 1:12, 13 የ1980 ትርጉም:- “[ኢየሱስ ክርስቶስን] ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑ [“ለብዙዎች፣” አዓት ] የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን መብት ሰጣቸው። እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሰው ዘር ማለትም ከሥጋ ልማድ ወይም ከሰው ፈቃድ አልተወለዱም።” (‘ለተቀበሉት ለብዙዎች’ የሚለው አነጋገር በክርስቶስ ያመኑ ሰዎች ሁሉ ማለት አይደለም። በቁጥር 11 ላይ የተጠቀሱት ጥቅሱ የሚናገርላቸው ሰዎች እነማን እንደሆኑ ልብ በል። [“የገዛ ወገኖቹ” ማለትም አይሁዳውያን ናቸው።] ይኸው መብት ለሌሎች የሰው ዘሮችም ቀርቦላቸዋል። ሆኖም ግን ይህን መብት የሚያገኘው “ታናሹ መንጋ” ብቻ ነው።)

ሮሜ 8:16, 17:- “የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፣ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።”

1 ጴጥ. 1:3, 4:- “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፣ እድፈትም ለሌለበት፣ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ይህም ርስት . . . በሰማይ ቀርቶላችኋል።”

ወደ ሰማይ ሄደው ምን ያደርጋሉ?

ራእይ 20:6:- “የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።”

1 ቆሮ. 6:2:- “ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን?”

‘እንደገና ያልተወለደ’ ሰው ሊድን ይችላልን?

ራእይ 7:9, 10, 17:- “ከዚህ በኋላ [ሐዋርያው ዮሐንስ ‘እንደገና የሚወለዱትን’፣ ወይም መንፈሳዊ እስራኤል የሚሆኑትን፣ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚሆኑትን ቁጥር ከሰማ በኋላ፣ ከ⁠ሮሜ 2:28, 29 እና ገላትያ 3:26–29 ጋር አወዳድር] አየሁ፣ እነሆም፣ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮኹ:- በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ። . . . በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ [ኢየሱስ ክርስቶስ] እረኛቸው ይሆናልና፣ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና።”

ዕብራውያን 11:39, 40 ከክርስትና በፊት የነበሩ ብዙ የእምነት ሰዎችን ከዘረዘረ በኋላ እንዲህ ይላል:- “እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፣ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና።” (እዚህ ላይ “እኛ” የተባሉት እነማን ናቸው? ዕብራውያን 3:1 እንደሚያሳየው እነዚህ “ከሰማያዊ ጥሪ ተካፋዮች” የሆኑት ናቸው። ስለዚህ ከክርስትና በፊት የኖሩት የእምነት ሰዎች በሰማይ ሳይሆን በሌላ ቦታ ፍጹም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ነበራቸው ማለት ነው።)

መዝ. 37:29:- “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።”

ራእይ 21:3, 4:- “እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”

አንድ ሰው ‘እንደገና ሳይወለድ’ የአምላክን መንፈስ ሊያገኝ ይችላልን?

የይሖዋ መልአክ ስለ አጥማቂው ዮሐንስ እንዲህ ብሏል:- “ገና በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል።” (ሉቃስ 1:15) ኢየሱስም ከጊዜ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። [ለምን? ምክንያቱም ዮሐንስ ወደ ሰማይ አይሄድም፤ ስለዚህ ‘እንደገና መወለድ’ አያስፈልገውም።] ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ [ኢየሱስ ይህን እስከተናገረበት ጊዜ ድረስ] መንግሥተ ሰማያት ሰዎች ለመግባት የሚጋደሉባት ግብ ሆናለች። እየተጋደሉ ወደፊት የሚገፉ ሁሉም ያገኟታል።”—ማቴ. 11:11, 12 አዓት

የይሖዋ መንፈስ በዳዊት ላይ አድሮ “ይሠራ” ነበር፣ በእርሱም ‘ተናግሮአል።’ (1 ሳሙ. 16:13 አዓት፤ 2 ሳሙ. 23:2) ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ “እንደገና ተወልዶ ነበር” ብሎ የተናገረበት ቦታ የለም። ‘እንደገና’ መወለድ አላስፈለገውም፤ ምክንያቱም ሥራ 2:34 “ዳዊት ወደ ሰማይ አልወጣም” ይላል።

ዛሬ የአምላክ መንፈስ ያላቸው ሰዎች እንዴት ሊታወቁ ይችላሉ?

በገጽ 380, 381 ላይ “መንፈስ” በሚለው ዋና ርዕስ ሥር ያለውን ተመልከት።

አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-

‘እንደገና ተወልጃለሁ’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘እንዲህ ሲሉ አንድ ቀን በሰማይ ከክርስቶስ ጋር እንደሚሆኑ ተስፋ ያደርጋሉ ማለት ነው፤ አይደለም እንዴ? . . . ነገር ግን ወደ ሰማይ የሚሄዱ ሰዎች ወደዚያ የሚሄዱት ምን ለማድረግ እንደሆነ አስበው ያውቃሉ?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘ከክርስቶስ ጋር ነገሥታትና ካህናት ሆነው ይገዛሉ። (ራእይ 20:6፤ 5:9, 10) እነዚህ “ታናሽ መንጋ” እንደሚሆኑ ኢየሱስ ተናግሯል። (ሉቃስ 12:32)’ (2) ‘ነገሥታት ከሆኑ ደግሞ የሚገዟቸው ተገዥዎች መኖር አለባቸው። ታዲያ እነዚህ እነማን ናቸው? . . . ሰዎች ሲነግሩኝ በጣም አስገራሚ ሆነው ያገኘኋቸውን አንዳንድ ነጥቦች ብገልጽልዎት ደስ ይለኛል። (መዝ. 37:11, 29፤ ምሳሌ 2:21, 22)’

‘እንደገና ተወልደሃል?’

እንዲህ ብለህ ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ሰዎች ‘እንደገና ስለ መወለድ’ ጉዳይ ሁልጊዜ አንድ ዓይነት ትርጉም እንደማይሰጡ ተረድቻለሁ። እርስዎ “እንደገና መወለድ” ሲሉ ምን ማለትዎ እንደሆነ ሊነግሩኝ ይችላሉ?’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘ኢየሱስን እንደ ግል አዳኜ አድርጌ በመቀበል መንፈስ ቅዱስ የተሰጠኝ መሆኑን ለማወቅ ነው የፈለጉት፤ አይደለም? እንደዚህ ከሆነ መልሱ አዎን የሚል መሆኑን ላረጋግጥልዎት እወዳለሁ። ይህ ባይሆን ኖሮ ስለ ኢየሱስ ከእርስዎ ጋር ባልተነጋገርሁ ነበር።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘መንፈስ ቅዱስ ስለመቀበል በማስብበት ጊዜ ክርስቲያን ነን በሚሉት በብዙዎች ዘንድ ያ መንፈስ እንደሌለ የሚያሳይ ማስረጃ አያለሁ። (ገላ. 5:22, 23)’ (2) ‘ሁሉም ሰዎች እነዚህን አምላካዊ ባሕርያት ቢያሳዩ ኖሮ በዚህች ምድር ላይ መኖር አያስደስትዎትም ነበር? (መዝ. 37:10, 11)’

ሌላ አማራጭ:- ‘እንደዚህ ሲሉ “ክርስቶስን እንደ አዳኝህ አድርገህ ተቀብለኸዋል ወይ?” ማለትዎ ከሆነ መልሴ አዎን ነው። ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስን እንደዚያ አድርገው ይመለከቱታል። ነገር ግን ለእኛ እንደገና መወለድ ሲባል ከዚህ የበለጠ ነገርን ይጨምራል።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘ኢየሱስ እንደገና ስለመወለድ በገለጸበት ጊዜ ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት ይኸውም የአምላክ መንግሥት አባል ወይም የሰማያዊ አስተዳደሩ ክፍል ለመሆን እንደገና መወለድ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐ. 3:5)’ (2) ‘ከዚህ በተጨማሪ ግን መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉ ብዙ ሰዎች የዚያች መንግሥት ደስተኛ ተገዥዎች ሆነው በዚህች ምድር ላይ እንደሚኖሩ ይገልጻል። (ማቴ. 6:10፤ መዝ. 37:29)’

ተጨማሪ ሐሳብ:- የሰማያዊ ክፍል የሆኑት እንዲህ ብለው ሊመልሱ ይችላሉ:- ‘አዎን እንደገና ተወልጃለሁ፤ ነገር ግን ስለተሰጠን ቦታ ከመጠን ያለፈ እንዳንመካ መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችንንም ያስጠነቅቃል። አምላክና ክርስቶስ ከእኛ የሚፈልጉብንን በእርግጥ እያደረግን መሆናችንን ለማረጋገጥ ራሳችንን መመርመር ያስፈልገናል። (1 ቆሮ. 10:12)’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘ኢየሱስ በእውነተኛ ደቀ መዛሙርቱ ላይ ምን ኃላፊነት ጥሎባቸዋል? (ማቴ. 28:19, 20፣ 1 ቆሮ. 9:16)’