በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክህደት

ክህደት

ፍቺ:- የይሖዋን አምልኮና አገልግሎት መተው ወይም ጥሎ መሄድ ማለት ነው። ይህም በይሖዋ አምላክ ላይ ማመፅ ነው። አንዳንድ ከሃዲዎች አምላክን እንደሚያውቁና እንደሚያገለግሉ ይናገራሉ፤ ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የቀረቡትን ትምህርቶችና ትእዛዛት አይቀበሉም። ሌሎች ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ እናምናለን ይላሉ፤ የይሖዋን ድርጅት ግን አይቀበሉም።

በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከሃዲዎች ይነሣሉ ብለን መጠበቅ ይገባናልን?

1 ጢሞ. 4:1:- “መንፈስ ግን በግልጥ:- በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፣ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል።”

2 ተሰ. 2:3:- “ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ፤ ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዓመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ፣ [የይሖዋ ቀን] አይደርስምና።”

ከሃዲዎች ተለይተው የሚታወቁባቸው አንዳንድ ምልክቶች:-

ሌሎች ሰዎች ተከታዮቻቸው እንዲሆኑ ለማድረግ ይጥራሉ፤ ከዚህም የተነሣ መከፋፈልና ኑፋቄ ይፈጥራሉ

ሥራ 20:30:- “ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ [ይነሣሉ።]”

2 ጴጥ. 2:1, 3:- “በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ፤ . . . ገንዘብንም በመመኘት በተፈጠረ ነገር ይረቡባችኋል።”

በክርስቶስ እናምናለን ይሉ ይሆናል፤ ነገር ግን ክርስቶስ ለተከታዮቹ የሰጣቸውን የስብከትና የማስተማር ሥራ አቅልለው ይመ ለከታሉ

ሉቃስ 6:46:- “ስለ ምን:- ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ ትሉኛላችሁ፣ የምለውንም አታደርጉም?”

ማቴ. 28:19, 20:- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”

ማቴ. 24:14:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።”

አምላክን እናገለግላለን ብለው ይናገሩ ይሆናል፤ ነገር ግን የእርሱን ወኪሎችና የሚታየውን ድርጅቱን አይቀበሉም

ይሁዳ 8, 11:- “እንዲሁም እነዚህ ሰዎች ደግሞ እያለሙ ሥጋቸውን ያረክሳሉ ጌትነትንም ይጥላሉ። ሥልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ። ወዮላቸው፣ . . . በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል።”

ዘኍ. 16:1–3, 11, 19–21:- “ቆሬ . . . በሙሴ ላይ [ተነሣ።] ከእስራኤልም ልጆች ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች [ከእርሱ] ጋር [ወሰደ፤] . . . የማኅበሩ አለቆች ነበሩ። በሙሴና በአሮን ላይ ተሰብስበው:- ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፣ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ነውና እናንተ እጅግ አብዝታችኋል፤ በእግዚአብሔርም ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ? አሉ። . . . [ሙሴም እንዲህ አላቸው:-] አንተና ወገንህ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ተሰብስባችኋል፤ በእርሱም ላይ ታጉረመርሙ ዘንድ አሮን ማን ነው? ቆሬም ማኅበሩን ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእነርሱ ላይ ሰበሰበ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ለማኅበሩ ሁሉ ተገለጠ። እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው:- ሁሉን በቅጽበት አጠፋቸው ዘንድ ከዚህ ማኅበር መካከል ፈቀቅ በሉ።”

ከሃዲዎች እውነተኛውን እምነት በመተው ብቻ ሳይወሰኑ በሕዝብ ፊት ቀርበው የቀድሞ ባልንጀሮቻቸውን ለማጥላላትና ሥራቸውን ለማደናቀፍ በተለያዩ ዘዴዎች በመጠቀም ‘ይማታሉ።’ የእነዚህ ከሃዲዎች ጥረት ለማፍረስ እንጂ ለመገንባት አይደለም

ማቴ. 24:45–51:- “ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? . . . ያ ክፉ ባሪያ ግን:- ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ፣ ባልንጀሮቹን ባሮች ሊመታ ቢጀምር ከሰካሮችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፣ የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፣ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል፣ [“ያንንም ባሪያ በብርቱ ይቀጣዋል፤” የ1980 ትርጉም ] እድሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል።”

2 ጢሞ. 2:16–18:- “ነገር ግን ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍ ራቅ፤ ኃጢአተኝነታቸውን ከፊት ይልቅ ይጨምራሉና፣ ቃላቸውም እንደ ጭንቁር ይባላል። ከእነርሱም ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ናቸው፤ እነዚህም:- ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል እያሉ፣ ስለ እውነት ስተው፣ የአንዳንዶችን እምነት ይገለብጣሉ።”

የታመኑ ክርስቲያኖች ከሃዲዎችን በግንባር በማነጋገር ወይም ጽሑፎቻቸውን በማንበብ ያስጠጓቸዋልን?

2 ዮሐ. 9, 10 የ1980 ትርጉም:- “በክርስቶስ ትምህርት ጸንቶ የማይኖርና ከእርሱም ርቆ የሚሄድ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የለም፤ . . . ይህን ትምህርት ሳይዝ ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት፤ ሰላምታም እንኳ አትስጡት።”

ሮሜ 16:17, 18:- “ወንድሞች ሆይ፣ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን፣ መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፣ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ፤ . . . በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ።”

የሚሉትን ለማወቅ በመጓጓት የከሃዲዎችን ጽሑፎች ማንበብ ወይም ከሃዲዎችን ማነጋገር ከባድ አደጋ ሊያስከትል ይችላልን?

ምሳሌ 11:9 አዓት:- “ከሃዲ ሰው በአፉ ባልንጀራውን ያጠፋል።”

ኢሳ. 32:6 የ1980 ትርጉም:- “ሰነፍ በስንፍና ይናገራል፤ ዘወትር ክፉ ነገር ለማድረግ ያስባል፤ በክሕደት የሚሠራውም ሆነ የሚናገረው የእግዚአብሔርን ስም የሚያሰድብ ነው፤ የተራበውን አያበላም፤ የተጠማውንም አያጠጣም።” (ከ⁠ኢሳይያስ 65:13, 14 ጋር አወዳድር።)

ከሃዲነት የቱን ያህል ከባድ ነገር ነው?

2 ጴጥ. 2:1:- “እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ።”

ኢዮብ 13:16 አዓት:- “ከሃዲ በፊቱ [በአምላክ ፊት] አይቀርብም።”

ዕብ. 6:4–6:- “አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን መልካሙንም የእግዚአብሔር ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን በኋላም የካዱትን [“ክህደት ቢፈጽሙ” ሪስ] እንደ ገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው፤ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና ያዋርዱትማልና።”