በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ውይይት የሚያስቆሙ ሐሳቦች ሲሰነዘሩ እንዴት መልስ መስጠት ይቻላል?

ውይይት የሚያስቆሙ ሐሳቦች ሲሰነዘሩ እንዴት መልስ መስጠት ይቻላል?

አስተያየት:- ሰዎች ወደፊት ሕይወት ማግኘት አለማግኘታቸው የተመካው ለይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ገዥ ለሆነለት መንግሥት ባላቸው አቋም ላይ ነው። የአምላክ መንግሥት መልእክት ልብን በደስታ የሚያስፈነድቅ ሲሆን ብቸኛና አስተማማኝ የሆነውን የሰው ዘር ተስፋ ይጠቁማል። ይህ መልእክት የሰዎችን ሕይወት የሚለውጥ መልእክት ነው። ሁሉም ሰው ይህንን መልእክት እንዲሰማ እንፈልጋለን። የመንግሥቱን መልእክት በደስታ የሚቀበሉት ሰዎች ጥቂቶች ብቻ እንደሆኑ እናውቃለን። ቢሆንም ሰዎች በእውቀት ላይ የተመረኮዘ ምርጫ እንዲያደርጉ ከተፈለገ ቢያንስ ቢያንስ የመንግሥቱን መልእክት መስማት እንደሚያስፈልጋቸው እንገነዘባለን። ይሁን እንጂ ሁሉም ሰው ለማዳመጥ ፈቃደኛ አይሆንም። እኛም የግድ እንዲያዳምጡን ለማድረግ አንሞክርም። ሆኖም አስተዋዮች ከሆንን ብዙውን ጊዜ ውይይት የሚያስቆሙ ሐሳቦች ሲሰነዘሩ አጋጣሚውን ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ እንደ መንደርደሪያ አድርገን ልንጠቀምበት እንችላለን። አንዳንድ የጐለመሱ ምሥክሮች የመንግሥቱ መልእክት የሚገባቸውን ሰዎች ለማግኘት ባደረጉት ፍለጋ የተጠቀሙባቸው ምሳሌዎች ከዚህ ቀጥለው ቀርበዋል። (ማቴ. 10:11) እዚህ ላይ እነዚህን መልሶች እንዳሉ በቃልህ ሸምድዳቸው ብለን ሐሳብ ማቅረባችን ሳይሆን ሐሳቡን በአእምሮህ ይዘህ ለምታነጋግረው ሰው ከልብ እንደምታስብለት በሚያሳይ መንገድ በራስህ አነጋገር ግለጸው ማለታችን ነው። ይህን ስታደርግ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች እንደሚሰሙና ይሖዋ ሕይወት ሊያገኙ ወደሚያስችሏቸው ፍቅራዊ ዝግጅቶቹ እነርሱን ለመሳብ እያደረገ ያለውን ነገር በአድናቆት እንደሚቀበሉ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ።—ዮሐ. 6:44፤ ሥራ 16:14

‘ፍላጎት የለኝም’

● ‘አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት፤ እንደዚህ ሲሉ ፍላጎት የሌለዎት ለመጽሐፍ ቅዱስ ነው ወይስ በአጠቃላይ ለሃይማኖት? ይህን የጠየቅሁበት ምክንያት ከዚህ በፊት ሃይማኖተኛ የነበሩና አሁን ግን በቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ በሚታየው ግብዝነት ምክንያት ቤተ ክርስቲያን መሄድ ያቆሙ ብዙ ሰዎች ስላጋጠሙን ነው። (ወይም ሃይማኖት የገንዘብ ማግኛ ዘዴ ብቻ እንደሆነ ተሰምቷቸው ይሆናል፤ ወይም ሃይማኖት በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ መግባቱን አይደግፉ ይሆናል፤ ወዘተ) መጽሐፍ ቅዱስም እንደነዚህ የመሰሉትን ድርጊቶች አይፈቅድም። መጽሐፍ ቅዱስ የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት እንድንጠባበቅ የሚያስችለን ብቸኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ይገልጽልናል።’

● ‘ፍላጎት የሌለዎት ስለሌላ ሃይማኖት ለማወቅ ከሆነ ምክንያትዎ ይገባኛል። ይሁን እንጂ በዚህ ዓለም ላይ የኑክሌር ጦርነት ሥጋት ከመኖሩ (ወይም ልጆቻችንን በዕፅ ሱሰኝነት እንዳይጠመዱ እንዴት ልንጠብቃቸው እንደምንችል ከማሰብ፤ ወይም በጨለማ ያለ ሥጋት ለመሄድ እንድንችል ወንጀልን በተመለከተ መደረግ ከሚኖርበት ነገር፤ ወዘተ) አንጻር ምን ዓይነት የወደፊት ጊዜ ልንጠብቅ እንደምንችል የማወቅ ፍላጎት እንዳለዎት እርግጠኛ ነኝ። እውነተኛ መፍትሔ የሚገኝ ይመስልዎታል?’

● ‘አልፈልግም ያሉት የራስዎ ሃይማኖት ስላለዎት ነው? . . . ሁሉም ሰው የአንድ ሃይማኖት ተከታይ የሚሆንበት ጊዜ ወደፊት ይመጣል ብለው ያስባሉ? . . . ይህ እንዳይሆን እንቅፋት የሆነው ነገር ምንድን ነው? . . . ሰዎች ሁሉ አንድ ሃይማኖት እንዲኖራቸው ምን ዓይነት መሠረት የሚያስፈልግ ይመስልዎታል?’

● ‘እንደዚህ ያሉበት ምክንያት ይገባኛል። እኔም ከጥቂት ዓመታት በፊት እንደርስዎ ይሰማኝ ነበር። ነገር ግን ጉዳዩን በሌላ አቅጣጫ እንድመለከት የረዳኝን ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አነበብኩ። (ምን እንደሆነ አሳያቸው)’

● ‘በሞት የተለዩዎት ያፈቅሯቸው የነበሩ ሰዎች ከሞት ተነሥተው ሊያዩአቸው እንደሚችሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ባሳይዎት ደስ አይልዎትም? (ወይም የሕይወት እውነተኛ ዓላማ ምን እንደሆነ፣ ወይም የቤተሰባችንን አንድነት ለመጠበቅ መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደሚረዳን ባሳይዎት ደስ አይልዎትም? ወዘተ)’

● ‘ፍላጎት የለኝም ሲሉ ምንም ነገር ለመግዛት አልፈልግም ማለትዎ ከሆነ በዚህ በኩል የሚያሳስብዎት ነገር የለም። እኔ በንግድ ሥራ ላይ የተሠማራሁ ሰው አይደለሁም። ይሁን እንጂ ከበሽታና ከወንጀል በጸዳች፣ ገነት በምትሆን ምድር ውስጥ ከሚወዱዎት ጐረቤቶችዎ ጋር የሚኖሩበት አጋጣሚ ቢያገኙ ደስ አይልዎትም?’

● ‘ይህ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያነጋግሩዎት ጊዜ ሁሉ የሚሰጡት የተለመደ መልስ ነው? . . . ደጋግመን ለምን እንደምንመጣ ወይም ምን ልንነግራችሁ እንደፈለግን ያውቃሉ? . . . በአጭሩ እርስዎን ለማነጋገር የመጣሁበት ምክንያት እርስዎም ጭምር ሊያውቁት የሚገባ አንድ ነገር እንዳለ ስለማውቅ ነው። ይህን ነገር ለአንድ አፍታ ቢሰሙኝ . . .?’

‘ለሃይማኖት ግድ የለኝም’

● ‘ለምን እንደዚህ እንደተሰማዎት ይገባኛል። በግልጽ ለመናገር አብያተ ክርስቲያናት ይህን ዓለም ሰላም የሰፈነበት የመኖሪያ ስፍራ አላደረጉትም፣ አድርገውታል እንዴ? . . . አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎትና ይህን የመሰለ ስሜት ያደረብዎት ከድሮ ጀምሮ ነው? . . . በአምላክስ ያምናሉ?’

● ‘እንደ እርስዎ ያለ አመለካከት ያላቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ሃይማኖታቸው ምንም ነገር አላደረገላቸውም። እኛም ሰዎችን የምናነጋግርበት አንዱ ምክንያት ይኸው ነው። አብያተ ክርስቲያናት ስለ አምላክ እውነትና ለሰዎች ልጆችም ስላለው አስደናቂ ዓላማ አልነገሯቸውም።’

● ‘የእርስዎ የወደፊት ሁኔታ ምን እንደሚሆን ለማወቅ እንደሚፈልጉ ግን እርግጠኛ ነኝ። መጽሐፍ ቅዱስ ዛሬ ስላለው ሁኔታ አስቀድሞ እንደተናገረ ያውቁ ነበር? . . . ውጤቱ ምን እንደሚሆንም ተናግሯል።’

● ‘ከመጀመሪያው ጀምሮ የሚሰማዎት እንደዚህ ነበር? . . . ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ይሰማዎታል?’

‘የይሖዋ ምሥክሮችን አልፈልግም’

● ‘ብዙ ሰዎች እንደዚህ ይሉናል። እኔና መሰሎቼ አብዛኞቹ ሰዎች ላይቀበሉን እንደሚችሉ እያወቅን ሰዎችን ለማነጋገር ለምን በፈቃደኝነት እንደምንሄድ ራስዎን ጠይቀው ያውቃሉ? (ማቴዎስ 25:31–33 ላይ ያለውን ፍሬ ሐሳብ ንገራቸው፤ በሁሉም አገሮች ሰዎችን በሁለት ወገን የመለያየቱ ሥራ እየተከናወነ እንዳለና በዚህ ረገድ ለመንግሥቱ መልእክት የሚሰጡት ምላሽ ወሳኝ እንደሆነ ግለጽ። ወይም ሕዝቅኤል 9:1–11 ላይ ያለውን ፍሬ ነገር ንገራቸው፤ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት በሚሰጡት ምላሽ መሠረት ከታላቁ መከራ ለመዳን ወይም ለመጥፋት በአምላክ “ምልክት” እንደሚደረግባቸው ግለጽላቸው።)’

● ‘እኔም እንደ እርስዎ ይሰማኝ ስለነበረ ለምን እንደዚህ እንዳሉ ለመረዳት እችላለሁ። ይሁን እንጂ የሚናገሩትን ሳልሰማ ላለመፍረድ ስል ከእነርሱ መካከል አንዱ የሚናገረውን ለማዳመጥ ወሰንኩ። ከዚያ በኋላ ስለ እነርሱ ተነግሮኝ የነበረው ነገር ትክክል እንዳልሆነ ለማወቅ ቻልኩ። (አንዱን የተለመደ የሐሰት ክስ ጥቀስና በትክክል ምን ብለን እንደምናምን ግለጽላቸው።)’

● ‘እኔም ከጥቂት ጊዜያት በፊት ወደ ቤቴ መጥቶ በር ላንኳኳ አንድ ምሥክር ልክ ይህን የመሰለ መልስ ሰጥቼው ነበር። ከመሄዱ በፊት ግን አይመልሰውም ብዬ እርግጠኛ የሆንኩበትን አንድ ጥያቄ አቀረበኩለት። ጥያቄው ምን እንደነበረ ለማወቅ ይፈልጋሉ? . . . (ለምሳሌ ያህል ቃየን ሚስት ያገባው ከየት አምጥቶ ነው?)’ (እንዲህ ያለ ተሞክሮ አጋጥሟቸው የነበሩ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።)

● ‘ሃይማኖተኛ ሰው ከሆኑ ለምን እንደዚያ እንዳሉ ይገባኛል። ለራስዎ ሃይማኖት ትልቅ ግምት እንደሚሰጡ የታወቀ ነው። ነገር ግን ሁለታችንም ብንሆን ስለ (ተስማሚ መነጋገሪያ ርዕስ ጥቀስላቸው) ጉዳይ ለማወቅ እንፈልጋለን፤ በዚህ ይስማማሉ ብዬ አስባለሁ።’

● ‘እንግዲያው የራስዎ ሃይማኖት እንዳለዎት አያጠራጥርም። ሃይማኖትዎ ምን እንደሆነ ብጠይቅዎት ቅር ይሰኛሉ? . . . የእርስዎ እምነት ተከታዮች ከሆኑ ሰዎች ጋር ደስ የሚል ውይይት አድርገን ነበር። ስለ (ለውይይት የሚሆን አንድ ተስማሚ ጉዳይ አንሣ) ጉዳይ ምን ይሰማዎታል?’

● ‘አዎ፣ ይገባኛል። ነገር ግን በየቤቱ እየሄድን በር የምናንኳኳበት ምክንያት ሰዎች ሁሉ አንድ ሆነው እንዲኖሩ የምንፈልግ ሰዎች ስለሆንን ነው። በየምሽቱ የሚተላለፉት ዜናዎች የሚያቀርቡትን የጦርነትና የሥቃይ ሪፖርት መስማት ራሳችንን አሳምሞናል፤ በጣም ሰልችቶናል። እርስዎም እንደ እኛ የሚሰማዎት ይመስለኛል። . . . ነገር ግን አስፈላጊውን ለውጥ ማን ያመጣልን ይሆን? . . . መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጣቸው ተስፋዎች የሚያበረታታ ተስፋ እናገኛለን።’

● ‘የሚሰማዎትን ስለነገሩኝ ደስ ብሎኛል። ግን ስለ እኛ የማይወዱት ነገር ምን እንደሆነ ሊነግሩኝ ፈቃደኛ ነዎት? እርስዎ ያልወደዱት ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናሳይዎትን ነገር ነው ወይስ የእኛን መምጣት?’

‘የራሴ ሃይማኖት አለኝ’

● ‘የእርስዎ ሃይማኖት ትክክል የሆነውን ነገር የሚወዱ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም የሚኖሩበት ጊዜ እንደሚመጣ ያስተምር እንደሆን ሊነግሩኝ ይችላሉ? . . . ይህ ደስ የሚያሰኝ ሐሳብ ነው፤ አይደለም እንዴ? . . . መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ይናገራል። (መዝ. 37:29፤ ማቴ. 5:5፤ ራእይ 21:4)’

● ‘በዚህ ጉዳይ ላይ እያንዳንዱ ሰው የራሱን ውሣኔ ማድረግ እንዳለበት እስማማለሁ። ነገር ግን አምላክ አንድ ዓይነት ሰዎች እውነተኛ አምላኪዎቹ እንዲሆኑ በመፈለግ ላይ እንዳለ ያውቃሉ? ዮሐንስ 4:23, 24 ምን እንደሚል ልብ ይበሉ። አምላክን “በእውነት” ማምለክ ምን ማለት ነው? . . . አምላክ እውነት የሆነውንና ያልሆነውን ለማወቅ የሚረዳን ምን ነገር ሰጥቶናል? . . . (ዮሐ. 17:17) ይህ ነገር ለያንዳንዳችን በግል ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ልብ ይበሉ። (ዮሐ. 17:3)’

● ‘ዕድሜዎን በሙሉ ሃይማኖተኛ ሰው ሆነው ነው የኖሩት? . . . አንድ ቀን የሰው ዘር በሙሉ አንድ ሃይማኖት ይኖረዋል ብለው ያስባሉ? . . . እኔ ስለዚህ ጉዳይ ብዙ አስቤበታለሁ፤ ምክንያቱም በራእይ 5:13 ላይ የተመዘገበውን አንብቤአለሁ። . . . እኛም አምላክን አንድ ሆነው ከሚያመልኩት ከእነዚህ ፍጥረታት መካከል ለመገኘት ምን ያስፈልገናል?’

● ‘ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት ያለው እንደ እርስዎ ያለ ሰው እንደማገኝ ተስፋ አድርጌ ነበር። በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ለመንፈሳዊ ነገሮች ግድ የላቸውም። አምላክ ከዚህች ምድር ላይ ክፋትን ሁሉ ጠራርጐ በማስወገድ ጽድቅን የሚያፈቅሩ ሰዎች ብቻ እንዲኖሩባት እንደሚያደርግ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ይህ ሐሳብ አይማርክዎትም? ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚሰማዎት ቢገልጹልኝ ደስ ይለኛል።’

● ‘በቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ንቁ ተሳታፊ ነዎት? . . . በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳሉ? . . . አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያን አባሎች የአምላክን ቃል የዕለታዊ ሕይወታቸው መመሪያ ለማድረግ ቅን ፍላጎት እንዳላቸውና እንደሚጥሩ ተመልክተዋል? (ወይም በዓለም ውስጥ ላሉት ችግሮች መፍትሔው ምን ስለመሆኑ በቤተ ክርስቲያን አባሎች መካከል የሐሳብ አንድነት እንዳለ ተመልክተዋል?) እኛ ግን በቤት ውስጥ በግል የሚሰጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ብዙ እንደሚረዳ ተገንዝበናል።’

● ‘በያዙት ሃይማኖት ረክተው ይኖራሉ ማለት ነው። ነገር ግን ብዙ ሰዎች በዓለም ሁኔታዎች አይደሰቱም። ምናልባት እርስዎም ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ሊሆኑ ይችላሉ። እርስዎም እንደዚያ ይሰማዎታል? . . . እነዚህ ሁኔታዎች ወዴት እያመሩ ያሉ ይመስልዎታል?’

● ‘መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ያስደስትዎታል? . . . ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ ጊዜ ያገኛሉ?’

● ‘ይህን ስለነገሩኝ ደስ ብሎኛል። የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ብንሆን ሁላችንም ዓለም ሰላም ሆና ለማየት እንፈልጋለን፤ (ወይም ልጆቻችንን ከመጥፎ ተጽዕኖ ለመከላከል በሚወሰዱት እርምጃዎች፤ ወይም እርስ በርስ የሚዋደዱ ጐረቤቶች ብናገኝ፤ ወይም ምንም እንኳን ሰው ሁሉ ሆደ ባሻ ስለሆነ ይህ ቀላል ባይሆንም ከሌሎች ሰዎች ጋር መልካም ግንኙነት ቢኖረን ደስ ይለናል፤) መቼም በዚህ እንደሚስማሙ እርግጠኛ ነኝ።’

● ‘የሃይማኖት ዝንባሌ እንዳለዎት በማወቄ ደስ ብሎኛል። ዛሬ ብዙ ሰዎች ሃይማኖትን በቁምነገር አይዙትም። እንዲያውም አንዳንዶች አምላክ የለም ብለው ያምናሉ። ነገር ግን እርስዎ በተማሩት መሠረት አምላክ ምን ዓይነት አምላክ ነው ብለው ያስባሉ? . . . መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ስም ማን እንደሆነ እንደሚናገር ልብ ይበሉ። (ዘጸ. 6:3 የ1879 እትም፤ መዝ. 83:18 አዓት )’

● ‘ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወደተለያዩ ቦታዎች በላካቸው ጊዜ ከእነርሱ የተለየ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች እንደሚያጋጥሟቸው ነግሯቸው ነበር። (ሥራ 1:8) ቢሆንም ጽድቅን የተራቡትና የተጠሙ ሁሉ እንደሚሰሟቸው ያውቅ ነበር። ኢየሱስ በዘመናችን የሚነገረው መልእክት ምንድን ነው ብሎ ነበር? (ማቴ. 24:14) ያች መንግሥት ለእኛ ምን ታደርግልናለች?’

‘እኛ ክርስቲያኖች ነን’

● ‘ይህን በማወቄ ደስ ይለኛል። እንግዲያውስ ኢየሱስ ራሱ ወደ ሰዎች ቤት እየሄደ ያነጋግራቸው እንደነበረና ደቀ መዛሙርቱም ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ ማዘዙን እንደሚያውቁ አያጠራጥርም። የስብከታቸው ዋና መልእክት ምን እንደነበር ያውቃሉ? . . . ዛሬ ልናነጋግርዎት የመጣነው ስለዚሁ መልእክት ነው። (ሉቃስ 8:1፤ ዳን. 2:44)’

● ‘እንግዲያው ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ የተናገረውን ቁም ነገር እንደሚገነዘቡ እርግጠኛ ነኝ። ኢየሱስ ቀጥሎ የምናነበውን ቃል በተናገረ ጊዜ ግልጽና አፍቃሪ መሆኑን አሳይቷል። . . . (ማቴ. 7:21–23) ስለዚህ ራሳችንን የሰማዩን አባት ፈቃድ ምን ያህል በሚገባ አውቀዋለሁ? ብለን መጠየቅ ይገባናል። (ዮሐ. 17:3)’

‘ሥራ አለብኝ’

● ‘እንግዲያው ንግግሬን በጣም አሳጥራለሁ። የመጣሁት አንድ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ጉዳይ ላወያይዎት ነው። (የመወያያውን ርዕስ ፍሬ ሐሳብ በሁለት ዐረፍተ ነገሮች ያህል ግለጽ።)’

● ‘እሺ። በሚመችዎት በሌላ ጊዜ እመጣለሁ። ነገር ግን ከመሄዴ በፊት ልናስብበት ስለሚገባ አስፈላጊ ጉዳይ የሚገልጽ አንድ ጥቅስ ባነብልዎት ደስ ይለኛል።’

● ‘ይገባኛል። እኔም እናት (ወይም ሠራተኛ ወይም ተማሪ) እንደመሆኔ በጣም ጊዜ ያጥረኛል። ስለዚህ ብዙ ጊዜ አልወስድብዎትም። ሁላችንም አንድ አሳሳቢ ሁኔታ ገጥሞናል። አምላክ የአሁኑን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ለማጥፋት በተቃረበበት ጊዜ እንደምንኖር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ከጥፋቱ የሚድኑ ሰዎች ግን ይኖራሉ። ነገር ግን እርስዎና እኔ ከሚድኑት መካከል ለመሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ለዚህ ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስ መልስ ይሰጠናል። (ሶፎ. 2:2, 3)’

● ‘እኔም ወደ እርስዎ የመጣሁበት ምክንያት ይህ ነው። ሁላችንም ሥራ ይበዛብናል። ሥራ ከመብዛቱ የተነሣ አንዳንድ ጊዜ ለሕይወት በጣም አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ወደጎን ገሸሽ እናደርጋቸዋለን፤ አይደለም እንዴ? . . . ጊዜ አልወስድብዎትም። ነገር ግን አንድ ጥቅስ ባነብልዎት እንደሚደሰቱ እርግጠኛ ነኝ። (ሉቃስ 17:26, 27) ማንኛችንም ብንሆን እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ መገኘት አንፈልግም። ስለዚህ ኑሯችን ሩጫ የበዛበት ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ለመመርመር ጊዜ መዋጀት ያስፈልገናል። (የሚበረከት ጽሑፍ አቅርብ።)’

● ‘ጐረቤቶችዎን አነጋግረን ከግማሽ ሰዓት በኋላ ብንመለስስ ይመችዎታል?’

● ‘እንግዲያውስ ሥራ እንዲያቋርጡ አላደርግም። ምናልባት ሌላ ቀን ተመልሼ አነጋግርዎት ይሆናል። ነገር ግን ከመሄዴ በፊት ይህን ጽሑፍ እንዲያነቡ እጋብዝዎታለሁ። (በዚያ ወር የሚበረከተውን ጽሑፍ አሳይ።) ይህ ጽሑፍ እንዲህ ለመሰሉት ጥያቄዎች (አንድ ወይም ሁለት ጥያቄ ጥቀስ) መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ የሚያብራሩ አንድ በአንድ የሚጠኑ ርዕሶችን የያዘ ነው።’

● ‘በማይመችዎት ሰዓት በመምጣቴ አዝናለሁ። ምናልባት የሚያውቁ ከሆነ እኔ የይሖዋ ምሥክር ነኝ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኝ አንድ በጣም አስፈላጊ ነጥብ ላይ ላነጋግርዎት ፈልጌ ነበር። ነገር ግን አሁን ለማዳመጥ ጊዜ ስለሌለዎት ስለ . . . (ርዕሱን ተናገርና) የምትገልጸውን ይህችን ትራክት ልሰጥዎ እችላለሁ። ለማንበብ ብዙ ጊዜ አትፈጅብዎትም። ግን በጣም ጥሩ ሐሳብ ያላት ናት።’

● ‘ይህን መረዳት አያዳግትም። ሥራዎቻችንን ሁሉ ለመጨረስ በቂ ጊዜ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል። ይሁን እንጂ ለዘላለም መኖር ቢችሉ የአሁኑ ሕይወታችን ምን ያህል የተለየ እንደሚሆን አስበው ያውቃሉ? ለዘላለም መኖር የሚለው አነጋገር እንግዳ ሊሆንብዎት እንደሚችል አውቃለሁ። እንዴት ለዘላለም ለመኖር እንደሚቻል የሚገልጽ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላሳይዎት። (ዮሐ. 17:3) ስለዚህ አሁን ማድረግ የሚያስፈልገን ስለ አምላክና ስለ ልጁ እውቀት መቅሰም ነው። ይህንን ጽሑፍ ትተንልዎት የምንሄደው ለዚህ ነው።’

‘አዘውትራችሁ የምትመጡት ለምንድን ነው?’

● ‘የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ ቀኖች በሚላቸው ቀናት ውስጥ እንደሆነ ስለምናምን ነው። ሁላችንም በጊዜያችን የሚታዩት ሁኔታዎች ወደፊት ምን ውጤት እንደሚያስከትሉ ማሰብ እንደሚገባን ይሰማናል። (በቅርቡ በዓለም ላይ የተፈጸሙ ድርጊቶች ወይም በመፈጸም ላይ ያሉ አንድ ወይም ሁለት ሁኔታዎች ጥቀስ።) እዚህ ላይ መቅረብ ያለበት ጥያቄ ከዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት ለማለፍ ምን ማድረግ ያስፈልገናል? የሚል ነው።’

● ‘አምላክንና ጐረቤቶቻችንን ስለምንወድ ነው። ሁላችንም አምላክንና ጎረቤቶቻችንን መውደድ ይገባን የለም እንዴ?’

‘የእናንተን ሃይማኖት በሚገባ አውቀዋለሁ’

● ‘ይህን በመስማቴ በጣም ደስ ብሎኛል። የይሖዋ ምሥክር የሆነ የቅርብ ዘመድ ወይም ጓደኛ አለዎት? . . . እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት:- ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምናስተምረውን ትምህርት ይኸውም “በመጨረሻው ቀን” እንደምንኖር፣ አምላክ ክፉዎችን በቅርቡ እንደሚያጠፋ፣ ይህች ምድር ገነት እንደምትሆንና ሰዎች የተሟላ ጤንነት አግኝተው እርስ በርሳቸው በእውነት ከሚዋደዱ ጐረቤቶች ጋር ለዘላለም ሊኖሩ እንደሚችሉ ያምናሉ?’

‘ገንዘብ የለንም’

● ‘የእርዳታ ገንዘብ ሰብሳቢዎች አይደለንም። ነፃ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንሰጣለን። በዚህ ትምህርት ከሚቀርቡት ርዕሶች አንዱ (በቅርቡ ከወጡት ጽሑፎች በአንደኛው ላይ የቀረቡትን ምዕራፎች ተጠቀም።) ትምህርቱን እንዴት እንደምንሰጥ ጥቂት ደቂቃዎች በመውሰድ ባሳይዎት ፈቃደኛ ነዎት? አንድ ሳንቲም እንኳ አይከፍሉም።’

● እኛ የምንፈልገው ሰዎችን እንጂ ገንዘባቸውን አይደለም። (ውይይቱን ቀጥል። አንድ ጽሑፍ አሳያቸውና ከጽሑፉ ምን ጥቅም እንደሚያገኙ ንገራቸው። ጽሑፉን የመውሰድ ልባዊ ፍላጎት እንዳላቸው የሚጠቁም ሁኔታ ካየህባቸው ወይም ማንበብ እንደሚፈልጉ የሚገልጽ ሐሳብ ከተናገሩ ጽሑፉን ስጣቸው። ከዚያም በዓለም ዙሪያ ለሚካሄደው የስብከት እንቅስቃሴ የገንዘብ ድጋፍ የምናገኘው እንዴት እንደሆነ ልትገልጽላቸው ትችላለህ።)

‘ቡዲስት ነኝ’ የሚል ሰው ሲያጋጥም

● የሰውዬው እምነት ከሌሎቹ የቡዲስት ሃይማኖት ተከታዮች ጋር አንድ ዓይነት ነው ብለህ አትደምድም። የቡዲስቶች ሃይማኖታዊ ትምህርት ግልጽ ያልሆነና ትርጉሙም እንደየሰዉ የተለያየ ነው። የጃፓን ቡዲዝም ከደቡብ ምሥራቅ እስያ ቡዲዝም ፈጽሞ የተለየ ነው። የግለሰቦች አመለካከትም እንዲሁ የተለያየ ነው። በአጠቃላይ ግን የሚከተሉትን ነጥቦች ማወቅ ይጠቅማል:- (1) ቡዲዝም ከሰው ውጭ የሆነ አምላክ፣ የተወሰነ አካል ያለው ፈጣሪ መኖሩን አይቀበልም። ብዙ ቡዲስቶች ግን ምስሎችንና የቡድሃ መጠቀሚያ የነበሩ የተለያዩ ቅርሶች ያመልካሉ። (2) ቡድሃ የሚል ማዕረግ የተሰጠው ሲድሃርታ ጋውታማ ለተከታዮቹ ሁሉ ምሳሌና አርዓያ እንዲሁም ሊከተሉት የሚገባቸው ዓይነተኛ የሃይማኖት ሰው እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። እርሱም ሰውን ከሰብዓዊ አመለካከት አንፃር በማጥናት ጥበብና ማስተዋል እንዲያገኙ ሰዎችን ሁሉ ያበረታታና ችግርን ከሥሩ መንቀል የሚቻለው አእምሮን ተቆጣጥሮ ምድራዊ ምኞቶችን በማስወገድ ነው ይል ነበር። በዚህ መንገድ አንድ ሰው ወደ ኒርቫና ደረጃ (ወደ ሌላ ነገር ተለውጦ እንደገና ከመወለድ ነፃ ወደ መሆን ደረጃ) ሊደርስ ይችላል። (3) ቡዲስቶች ሕይወታቸውን ያገኙት ከእነርሱ በፊት ይኖሩ ከነበሩት አባቶቻቸው እንደሆነ ስለሚያምኑ ያመልኳቸዋል።

ለውይይት የሚጠቅሙ ሐሳቦች:- (1) ከቡዲስቶች ጋር ስትወያይ የሕዝበ ክርስትና አባል አለመሆንህን ጠበቅ አድርገህ ንገራቸው። (2) ቡዲስቶች “ለቅዱሳን መጻሕፍት” አክብሮት አላቸው። ከዚህም የተነሣ አብዛኛውን ጊዜ ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ያሳያሉ። በቡዲስቶች ሃይማኖታዊ ፍልስፍና ላይ ጊዜ ከማጥፋት ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን አዎንታዊ መልእክት ተናገር። መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ፍልስፍና ሳይሆን የሰው ልጅ ፈጣሪ የሆነው የይሖዋ አምላክ የታመነ ቃል መሆኑን አሳውቃቸው። ከዚህ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ አንድ ደስ የሚል ሐሳብ ብታሳያቸው ፈቃደኞች ይሆኑ እንደሆነ በትሕትና ጠይቃቸው። (3) ብዙ ቡዲስቶች ስለ ሰላምና ስለ ቤተሰብ ኑሮ አጥብቀው ያስባሉ። በጥሩ ሥነ ምግባር መኖርም ይፈልጋሉ። አብዛኛውን ጊዜ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሚደረገውን ውይይት ይቀበላሉ። (4) የሰውን ልጅ ላጋጠሙት ችግሮች እውነተኛ መፍትሔ የሚገኘው ሰማያዊቷ ጻድቅ መንግሥት ምድርን ስትገዛ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያመለክት አሳያቸው። መጽሐፍ ቅዱስ የምድርን የወደፊት ሁኔታና በምድራዊ ገነት ላይ ለዘላለም የመኖርን አስደናቂ ተስፋ ይገልጻል። (5) ስለ ሕይወት አጀማመር፣ ስለ ሕይወት ትርጉም፣ ስለ ሙታን ሁኔታ፣ ስለ ትንሣኤ ተስፋ፣ ክፋት እስካሁን የኖረበትን ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጽ ማሳየት ያስፈልግሃል። በግ መሰል ሰዎች የአምላክ ቃል ግልጽ እውነት በደግነት ሲነገራቸው ልባቸው ተነክቶ መልእክቱን ሊቀበሉ ይችላሉ።

አባት ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ የተባለችው የእንግሊዝኛ ቡክሌት የተዘጋጀችው በተለይ ቅን የሆኑ ቡዲስቶችን ለመርዳት ታስቦ ነው።

‘ሂንዱ ነኝ’ የሚል ሰው ሲያጋጥም

● የሂንዱ ፍልስፍና በጣም ውስብስብና ከተለመደው ምክንያታዊ አስተሳሰብ ጋር የማይስማማ መሆኑን ማወቅ አለብህ። የሚከተሉትን ነጥቦች በአእምሮህ መያዝ ጠቃሚ ሆኖ ልታገኘው ትችል ይሆናል:- (1) የሂንዱ ሃይማኖት ወይም ሂንዱኢዝም ብራህማን የሚባለው አምላክ ሦስት ገጽታዎች እንዳሉት ያስተምራል። እነርሱም ብራህማ ፈጣሪው፣ ቪሽኑ ጠባቂውና ሲቫ አጥፊው የሚባሉት ናቸው። ይሁን እንጂ ሂንዱዎች የራሱ ሕልውና ያለው አንድ አምላክ አለ ብለው አያምኑም። (2) ሂንዱዎች ሁሉም ፍጥረታት የማትሞት ነፍስ አለቻቸው ብለው ያምናሉ። አንድ ነገር ከሞተ በኋላ ነፍሱ ወደሌላ ነገር እየተለወጠች ለዘላለም ትኖራለች፤ እንደገና ስትወለድ የሚኖራት ቅርጽ የሚወሰነው በተግባሯ (ካርማ) ነው፤ ከዚህ “ፍጻሜ ከሌለው ቀለበት” መውጣት የሚቻለው ምኞትን ሁሉ በማጥፋት ሲሆን እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ከተቻለ ነፍስ ከጽንፈ ዓለማዊው መንፈስ ጋር አንድ ትሆናለች። (3) በአጠቃላይ ሂንዱዎች ሌሎችን ሃይማኖቶች ያከብራሉ። ሂንዱዎች ሁሉም ሃይማኖቶች እርስ በርሱ የሚጋጭ ትምህርት ቢያስተምሩም ወደ አንድ እውነት የሚያደርሱ ናቸው ብለው ያምናሉ።

ውስብስብ በሆነው የሂንዱ ፍልስፍና ላይ ለመነጋገር ከመሞከር ይልቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኘውን አርኪ የሆነ እውነት ተናገር። የይሖዋ ፍቅራዊ የሕይወት ዝግጅት ለሁሉም የሰው ዘሮች ክፍት ነው። በቃሉ ውስጥ የሚገኙት ግልጽ እውነቶች ጽድቅን የተራቡና የተጠሙ ሰዎችን ልብ ይነካል። ስለወደፊቱ ጊዜ እውነተኛና አስተማማኝ ተስፋ የሚሰጠው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም ሰዎች ለሚያጋጥሟቸው ከፍተኛ ችግሮች አርኪ የሆነ መልስ ይሰጣል። እነዚህን መልሶች እንዲሰሙ አጋጣሚ ስጣቸው። ሪግ ቬዳ የሚባለው የሂንዱ መዝሙር 10.121 “ለማይታወቀው አምላክ” የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል። ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴና “ለማይታወቅ አምላክ” የተሠራውን መሠዊያ ጠቅሶ እንደተናገረ ሁሉ አንተም በተመሳሳይ በአንዳንድ ሁኔታዎች ይህን ጠቅሰህ መናገር ተስማሚ ሆኖ ልታገኘው ትችል ይሆናል። (ሥራ 17:22, 23) ቪሽኑ የተባለው የሂንዱ አምላክ ስም በእንግሊዝኛ የመጀመሪያው ፊደል ሲጠፋ ኢሽ–ኑህ እንደሚሆን ልብ እንበል። ኢሽ–ኑህ በከለዳውያን ቋንቋ “ኖኅ የተባለ ሰው” ማለት ነው። በኖኅ ዘመን ስለተፈጸመው ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ግለጽላቸው። ነፍሳቸው ፍጻሜ በሌለው መንገድ ሲለዋወጥ መኖሩ ላስጨነቃቸው ሰዎች በገጽ 319, 320 ላይ “ሪኢንካርኔሽን” በሚለው ዋና ርዕስ ሥር ያለው ሐሳብ ሊረዳቸው ይችል ይሆናል።

ወደ ነፃነት የሚመራው የመለኮታዊ እውነት መንገድ እና ከክሩክሼትራ ወደ አርማጌዶንናየአንተ ከጥፋት መዳን የተባሉት የእንግሊዝኛ ቡክሌቶች ቅን ልብ ያላቸውን ሂንዱዎች ሊጠቅም የሚችል ትምህርት ይዘዋል።

‘አይሁዳዊ ነኝ’ የሚል ሰው ሲያጋጥም

● መጀመሪያ ሰውዬው አይሁዳዊ ነኝ ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ አረጋግጥ። ሃይማኖተኛ አይሁዶች ጥቂት ናቸው። ለብዙዎቹ አይሁዳዊ መሆን የዘር ጉዳይ ብቻ ነው።

በአእምሮ ሊያዙ የሚገባቸው ጥቂት ጠቃሚ ነጥቦች እነሆ:- (1) ሃይማኖታዊ አይሁዳውያን የአምላክን ስም መጥራት እንደተከለከለ ነገር አድርገው ይቆጥሩታል። (2) ብዙ አይሁዳውያን “መጽሐፍ ቅዱስ” የክርስቲያኖች ብቻ መጽሐፍ እንደሆነ አድርገው ይቆጥራሉ። “የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት”፣ “ቅዱሳን መጻሕፍት”፣ ወይም “ቶራህ” እያልህ ብትጠራ ግን ችግር አይኖርም። (3) ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ወግ የአይሁዳውያን እምነት ዋነኛ ክፍል ሆኗል። ብዙ ሃይማኖታዊ አይሁዶች ወጋቸው ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የሚተካከል ሥልጣን እንዳለው አድርገው ያስባሉ። (4) አይሁዳውያን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለው ስም ሲጠራ የሚታያቸው ሕዝበ ክርስትና በእርሱ ስም ያደረሰችባቸው ጭካኔ ነው። (5) አይሁዳውያን አምላክ ሰንበትን እንዲያከብሩ እንደሚፈልግባቸው አድርገው ያምናሉ። ይህም እምነታቸው በሰንበት ቀን ገንዘብን እንኳን አለመንካትን ይጨምራል።

ለውይይት መንደርደሪያ የሚሆን በጋራ የሚያስማማ መሠረት ለመጣል እንዲህ ማለት ትችላለህ:- (1) ‘ምንም ያህል የሃይማኖት ልዩነት ቢኖረንም ዛሬ በምድር ላይ የሚታዩት ብዙ ችግሮች ሁላችንንም የሚነኩ እንደሆኑ ያለ ጥርጥር ይስማማሉ። ይህን ትውልድ ላጋጠሙት ትልልቅ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ይኖራል ብለው ያምናሉ? (መዝ. 37:10, 11, 29፤ መዝ. 146:3–5፤ ዳን. 2:44)’ (2) ‘እኛ የሕዝበ ክርስትና ክፍል አይደለንም። የአብርሃምን አምላክ እናመልካለን እንጂ በሥላሴ አናምንም። በተለይ ሃይማኖታዊ እውነት በጣም የሚስበን ጉዳይ ነው። አንድ ጥያቄ ብጠይቅዎት:- በአይሁድ ሕዝቦች መካከል ከፍተኛ የእምነት መለያየት ይታያል፤ ታዲያ እውነቱን ለማወቅ ምን መመዘኛ መጠቀም ይቻላል? . . . (ዘዳ. 4:2፤ ኢሳ. 29:13, 14፤ መዝ. 119:160)’ (3) ‘አምላክ በአብርሃም ዘር በኩል የሁሉም አገር ሰዎች እንደሚባረኩ በሰጠው ተስፋ ከልብ እንደሰታለን። (ዘፍ. 22:18)’

ሰውዬው በአምላክ እንደማያምን ከተናገረ፣ እምነት ያልነበረው ከመጀመሪያው ጀምሮ መሆኑን ጠይቀው። ከዚያም አምላክ ክፋትንና ግፍን እስከ አሁን ለምን እንደፈቀደ ምናልባት ልታወያየው ትችላለህ። ናዚዎች የፈጸሙት ታላቅ እልቂት ትዝታ ብዙ አይሁዳውያን ስለዚህ ጉዳይ በጣም እንዲያስቡ አድርጓቸዋል።

በአምላክ ስም መጠቀም አስፈላጊ ስለመሆኑ ለማወያየት ካሰብህ በመጀመሪያ ሰውዬው ስለዚህ ጉዳይ የሚሰማውን ለማወቅ ሞክር። ዘጸአት 20:7 የአምላክን ስም ለከንቱ ነገር መጠቀምን ቢከለክልም በአክብሮት መጠቀምን እንደማይከለክል ግለጽ። ዘጸአት 3:15 (ወይም መዝሙር 135:13)፣ 1 ነገሥት 8:41–43፤ ኢሳይያስ 12:4፤ ኤርምያስ 10:25፤ ሚልክያስ 3:16 የመሳሰሉትን ጥቅሶች በመጥቀስ ጉዳዩን እንዲያጤን እርዳው።

ስለ መሲሑ ስታወያየው:- (1) ስለ መሲሑ ማንነት ከመናገርህ በፊት ወደፊት በእርሱ አገዛዝ ሥር ስለሚመጡት በረከቶች ተናገር። (2) ከዚያ በኋላ ስለ መሲሑ በአካል መምጣት የሚናገሩትን ጥቅሶች እያወጣህ ምክንያቶችህን እንዲያጤን እርዳው። (ዘፍ. 22:17, 18፤ ዘካ. 9:9, 10፤ ዳን. 7:13, 14) (3) መሲሑ ሁለት ጊዜ ስለመምጣቱ ማስረዳት ያስፈልግህ ይሆናል። (ዳንኤል 7:13, 14⁠ን ከዳንኤል 9:24–26 ጋር አነጻጽር።) (4) ስለ ኢየሱስ ለመናገር ካሰብህ በየጊዜው እየተገለጠ ከሄደው የአምላክ ዓላማ ጋር በማያያዝ ጥቀስ። ኢየሱስ በሚያስተምርበት ጊዜ ሁለተኛው ቤተ መቅደስ እንደገና እንደማይሠራ ሆኖ እንዲደመሰስ አምላክ የፈቀደበት ጊዜ ተቃርቦ እንደነበር ግለጽ። ኢየሱስ በሕጉና በነቢያት የተነገሩት ትንቢቶች መፈጸማቸውን እንዲሁም ሕጉና ነቢያት የእምነት ሰዎችን ወደ ክብራማው ታላቅ የወደፊት ጊዜ የሚመሩ መሆናቸውን ተናግሯል።