በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓለም

ዓለም

ፍቺ:- “ዓለም” የሚለው ቃል ኮስሞስ ከሚለው ግሪክኛ ቃል ሲተረጐም (1) የሰውን ልጅ በሙሉ፣ የሥነ ምግባር ሁኔታውን ወይም የሕይወት መንገዱን ሳይጨምር፣ (2) አንድ ሰው የተወለደበትንና የሚኖርበትን ሰብዓዊ ሁኔታዎች ወይም (3) በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ካገኙት ባሪያዎቹ ውጭ ያለውን የሰው ዘር የሚያመለክት ትርጉም ሊኖረው ይችላል። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች “ዓለም” የሚለውን ቃል “ምድር” “ሰው የሚኖርበት ምድር”፣ “የነገሮች ሥርዓት” የሚል ትርጉም ላላቸው የግሪክኛ ቃሎችም በመጠቀማቸው ትክክለኛ ያልሆነ ሐሳብ አስተላልፈዋል። ከዚህ ቀጥሎ ያለው ማብራሪያ ይበልጥ ያተኮረው “ዓለም” ለሚለው ትርጉም ከተሰጡት ውስጥ በሦስተኛው ላይ ነው።

ዓለም በእሳት ይጠፋ ይሆን?

2 ጴጥ. 3:7:- “አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ [በአምላክ] ቃል ለእሳት ቀርተዋል።” (የሚጠፉት የሰው ልጆች በአጠቃላይ ሳይሆኑ “እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች” እንደሆኑ ልብ ማለት ይገባል። በተመሳሳይ ቁጥር 6 በኖኅ ዘመን ስለጠፋው “ዓለም” ይገልጻል። ክፉ ሰዎች ሲጠፉ ምድር እንዲሁም አምላክን ይፈራ የነበረው ኖኅና ቤተሰቡ ግን ተርፈዋል። የሚመጣው የፍርድ ቀን “እሳት” ቃል በቃል እሳት ነው ወይስ የፍጹም ጥፋት ምሳሌ ነው? ፀሐይና ከዋክብት በጣም የጋሉ ስለሆኑ በእነዚህ ሰማያዊ አካሎች ላይ እሳት ቃል በቃል ምን ውጤት ይኖረዋል? በዚህ ጥቅስ ላይ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት በገጽ 114–115 ላይ “ምድር” በሚለው ሥር ተመልከት።)

ምሳሌ 2:21, 22 አዓት:- “በምድር ላይ የሚኖሩት ትክክለኛ የሆኑት ናቸው፣ በእርስዋ ላይ የሚቀሩት ነቀፋ የሌለባቸው ናቸው። ክፉዎች ግን ከምድር ይጠፋሉ፤ አታላዮችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።”

ይህን ዓለም የሚገዛው ማን ነው? አምላክ ወይስ ሰይጣን?

ዳን. 4:35:- “[ከሁሉ በላይ የሆነው አምላክ ይሖዋ] በሰማይም ሠራዊት በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ እጁንም የሚከለክላት ወይም:- ምን ታደርጋለህ? የሚለው የለም።” (በተመሳሳይ መንገድ ኤርምያስ 10:6, 7 ይሖዋን “የአሕዛብ ንጉሥ” እንደሆነ ይገልጻል፤ ምክንያቱም እርሱ ሁሉንም ሰብዓዊ ነገሥታትና የሚገዟቸውን ሕዝቦች በኃላፊነት መጠየቅ የሚችልና የሚጠይቅ ደግሞም ከሁሉ በላይ የሆነ ንጉሥ በመሆኑ ነው። ይሖዋ የምድር ፈጣሪ በመሆኑ መብት ያለው የእርሷ ገዥ ነው፤ ይህን ሥልጣን በፍጹም ለቅቆ አያውቅም።)

ዮሐ. 14:30:- “[ኢየሱስ እንዲህ አለ]:- የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም።” (ይህ ገዥ ኢየሱስ ሁልጊዜ በታማኝነት ፈቃዱን የሚያደርግለት ይሖዋ አምላክ አይደለም። ይህ ‘የዓለም ገዥ’ በ⁠1 ዮሐንስ 5:19 ላይ እንደተገጸው ‘ዓለሙን በሞላው’ በኃይሉ ‘ሥር’ ያደረገው “ክፉው” ሰይጣን ዲያብሎስ መሆን አለበት። ምንም እንኳ ሰዎች የአምላክ ንብረት በሆነችው ምድር ላይ ቢኖሩም የይሖዋ ታዛዥ አገልጋዮች ካልሆኑት ሰዎች የተውጣጣው ዓለም በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ነው። ምክንያቱም እንዲህ የመሰሉት ሰዎች የሚታዘዙት እርሱን ስለሆነ ነው። ራሳቸውን ለይሖዋ አገዛዝ ከልብ የሚያስገዙት ግን የዚህ ዓለም ክፍል አይደሉም። ከ⁠2 ቆሮንቶስ 4:4 ጋር አወዳድር።)

ራእይ 13:2:- “ዘንዶውም [ሰይጣን ዲያብሎስ ለአውሬው] ኃይሉንና፣ ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን ሰጠው።” (ይህን ለአውሬው የተሰጠውን መግለጫ ከዳንኤል 7 ጋር ማወዳደር “አውሬው” ሰብዓዊ መንግሥታትን የሚወክል መሆኑን ያሳያል። አንድን መንግሥት ሳይሆን ዓለም አቀፉን የፖለቲካ አገዛዝ ሥርዓት ይወክላል። ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዥ መሆኑ ከ⁠ሉቃስ 4:5–7 እና የአጋንንት ቃል የምድር ገዥዎች አምላክን በመቃወም እንዲዋጉ ወደ አርማጌዶን እንደሚመራቸው ከሚያሳየው ከ⁠ራእይ 16:14, 16 ጋር ይስማማል። አምላክ የሰይጣንን የዚህ ዓለም ገዥነት የታገሠው የጽንፈ ዓለም ሉዓላዊነትን በተመለከተ ለተነሣው አከራካሪ ጉዳይ መፍትሔ ለመስጠት የቆረጠው ጊዜ እስኪደርስ ነው።)

ራእይ 11:15:- “የዓለም መንግሥት ለጌታችንና [ለይሖዋና] ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች።” (ይህ በ1914 በሆነ ጊዜ የዚህ ክፉ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀኖች’ ጀመሩ። የይሖዋ ሉዓላዊነት አዲስ መግለጫ መሲሐዊ ገዥ በሆነው በልጁ በኩል ታየ። በቅርቡ ክፉው ዓለም ይጠፋል። የዚህ ዓለም ክፉ መንፈሳዊ ገዥ ሰይጣን በሰዎች ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ እንዳይችል ወደ ጥልቁ ይጣላል።)

እውነተኛ ክርስቲያኖች ለዓለምና የዓለም ክፍል ለሆኑት ሰዎች ያላቸው አቋም ምንድን ነው?

ዮሐ. 15:19 አዓት:- “እናንተ [የክርስቶስ ተከታዮች] የዚህ ዓለም ክፍል አይደላችሁም።” (ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከአምላክ የራቀው የጠቅላላው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ክፍል አይደሉም። ተገቢ የሆኑትን ሰብዓዊ ሥራዎች ያከናውናሉ፣ ነገር ግን የዓለም መለያ ከሆኑት ዝንባሌዎች፣ ንግግርና ጠባይ እንዲሁም ከይሖዋ የጽድቅ መንገዶች ጋር ከሚጋጩት ይርቃሉ።) (ገጽ 269–275⁠ን እንዲሁም ገጽ 388–391 ተመልከት።)

ያዕ. 4:4:- “አመንዝሮች ሆይ፣ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።” (ክርስቲያኖች ፍጽምና የጐደላቸው ስለሆኑ አንዳንድ ጊዜ ከዓለም ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ሊበከሉ ይችላሉ። ነገር ግን ከአምላክ ቃል ምክር ሲሰጣቸው ንስሐ ገብተው መንገዳቸውን ያስተካክላሉ። ይሁን እንጂ አንዳንዶች በውዴታ ከዓለም ጐን ለመሰለፍ ወይም የዓለምን መንፈስ ለመከተል ቢመርጡ እውነተኛ ክርስቲያኖች አለመሆናቸውን ያሳያሉ፤ ከአምላክ ጋር የተጣላው የዓለም ክፍል ይሆናሉ።)

ሮሜ 13:1:- “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው።” (ይህን ምክር ሰምተው የሚሠሩበት የዓለምን መንግሥት ለመገልበጥ የሚሞክሩ ዓመፀኞች አይደሉም። ራሳቸውን ለፖለቲካ ገዥዎች ሥልጣን የሚያስገዙ፣ የእነዚህ ገዥዎች ጥያቄ ከአምላክ ብቃቶች ጋር እስካልተጋጨ ድረስ የሚታዘዟቸው ናቸው። እነዚህ መንግሥታት ከመምጣታቸው በፊት አምላክ አስቀድሞ አይቷቸዋል፤ ይመጣሉ ብሎም አስቀድሞ ተናግሯል። በሥልጣን ቦታ ላይ የተቀመጡት በአምላክ ሿሚነት አይደለም። ሆኖም አምላክ እንዲገዙ ፈቅዶላቸዋል። እርሱ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ግን ያስወግዳቸዋል።)

ገላ. 6:10:- “ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ።” (ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ለሰው ልጆች መልካምን ከመሥራት ወደኋላ አይሉም። በክፉዎችና በመልካሞች ላይ ፀሐይን የሚያወጣውን አምላክ አርአያ ይከተላሉ።—ማቴ. 5:43–48)

ማቴ. 5:14–16:- “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። . . . መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለው አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።” (ክርስቲያኖች በሚያደርጓቸው ነገሮች የተነሣ ሌሎች ሰዎች ለአምላክ ክብር እንዲሰጡ ከተፈለገ ክርስቲያን የሆኑት ስለ አምላክ ስምና ስለ ዓላማው ተግተው ለዓለም ምሥክርነት መስጠት አለባቸው። እውነተኛ ክርስቲያኖች ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጡት ለዚህ ሥራ ነው።)

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ያሉት ሁኔታዎች ትርጉም ምንድን ነው?

“የመጨረሻ ቀኖች” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት።