በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዕድል

ዕድል

ፍቺ:- መፈጸሙ የማይቀርና ብዙ ጊዜ መጥፎ ውጤት የሚያስከትል ነገር ነው። ማንኛውም ነገር በመለኮታዊ ፈቃድ ወይም ከሰው በላይ በሆነ ኃይል የተወሰነ ነው፤ ማንኛውም ነገር የሚፈጸመው አስቀድሞ በተወሰነው መሠረት ነው የሚል እምነት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አይደለም።

እያንዳንዱ ሰው ‘የሚሞትበት ጊዜ’ አስቀድሞ የተወሰነ ነውን?

ይህ እምነት በግሪኮችና በሮማውያን ዘንድ በሠፊው ተቀባይነት ያገኘነበር። አረማውያን በነበሩት ግሪካውያን አፈታሪክ መሠረት ዕድል የሕይወትን ክር የምትፈትል፣ ርዝመቱን የምትወስንና የምትቆርጥ የሦስት አማልክት ጥምረት ናት።

መክብብ 3:1, 2 “ለመሞትም ጊዜ አለው” በማለት ይናገራል። ነገር ግን ይህ ለግለሰቡ አስቀድሞ የተወሰነና የተቆረጠ ጊዜ አለመሆኑን ለማሳየት መክብብ 7:17 እንዲህ በማለት ይመክራል:- “እጅግ ክፉ አትሁን፣ እልከኛም አትሁን፣ ጊዜህ ሳይደርስ እንዳትሞት። ” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ምሳሌ 10:27 “የኀጥኣን ዕድሜ ግን ታጥራለች” ይላል። መዝሙር 55:23​ም በተጨማሪ “የደም ሰዎችና ሸንጋዮች ዘመናቸው ግማሽ አይሞላም” ይላል። ታዲያ የ⁠መክብብ 3:1, 2 ትርጉም ምንድን ነው? በዚህ ፍጽምና በጐደለው ሥርዓት ውስጥ ሕይወትና ሞት የማያቋርጥ ዑደት እንዳላቸው መግለጹ ነው። ሰዎች የሚወለዱበትና የሚሞቱበት ጊዜ አላቸው። ይህም ብዙ ጊዜ ከ70 ወይም ከ80 ዓመት ያልበለጠ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ከዚህ ሊቀድም ወይም ሊዘገይ ይችላል።—መዝ. 90:10፤ በተጨማሪ መክብብ 9:11 አዓት ተመልከት።

የእያንዳንዱ ሰው ሕይወት ርዝመትና አሟሟት ገና ሲወለድ ወይም ከዚያ ቀደም ብሎ የተወሰነ ከሆነ ከአደገኛ ሁኔታዎች መራቅ ወይም ጤንነትን መንከባከብ እና አደጋ እንዳያጋጥም ጥንቃቄ ማድረግ ሞትን ስለማያስቀር አስፈላጊ አይሆንም ነበር። ጦርነት የሚደረግበት አካባቢ ከጦርነት ክልል ርቆ ከሚገኝ የመኖሪያ አካባቢ የባሰ አደጋ የለውም ብለው ያምናሉን? ስለ ጤንነትዎ ይጠነቀቃሉ? ልጆችዎንስ ወደ ሐኪም ይወስዳሉ? ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች በአማካይ ከማያጨሱ ሰዎች ሦስት ወይም አራት ዓመት ቀድመው የሚሞቱት ለምንድን ነው? በመኪና የሚሳፈሩ ሰዎች ከመቀመጫው ጋር የተያያዘውን ቀበቶ ሲታጠቁና መኪና አሽከርካሪዎችም የትራፊክ ሕጐችን ሲያከብሩ የመኪና አደጋ የሚቀንሰው ለምንድን ነው? ጥንቃቄ ማድረግ ጥቅም ያለው መሆኑ ግልጽ ነው።

የሚፈጸም ነገር ሁሉ “የአምላክ ፈቃድ” ነውን?

2 ጴጥ. 3:9:- “ሁሉ ወደ ንሥሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።” (ነገር ግን ትዕግሥቱን አይተው የሚለወጡት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። አንዳንዶች ንስሐ ሳይገቡ መቅረታቸው “የአምላክ ፈቃድ” እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከ⁠ራእይ 9:20, 21 ጋር አወዳድር።)

ኤር. 7:23–26:- “ቃሌን ስሙ፣ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፤ መልካምም ይሆንላችሁ ዘንድ ባዘዝኋችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ ብዬ በዚህ ነገር [እስራኤላውያንን] አዘዝኋቸው። ነገር ግን . . . አልሰሙም። . . . በየዕለቱ እየማለድሁ ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበር። ነገር ግን አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙኝም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም።” (በእስራኤል ምድር ይፈጸም የነበረው መጥፎ ሥራ ሁሉ “የአምላክ ፈቃድ” እንዳልነበረ ግልጽ ነው።)

ማር. 3:35:- “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ እርሱ ወንድሜ ነው እህቴም እናቴም አለ።” (ስለዚህ ማንኛውም ሰው ምንም ነገር ቢያደርግ ‘የአምላክ ፈቃድ’ ከሆነ ከኢየሱስ ጋር እዚህ ላይ የተገለጸው ዓይነት ጥሩ ዝምድና ይኖረዋል ማለት ነው። ነገር ግን ኢየሱስ ስለ አንዳንድ ሰዎች ሲናገር “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ” ብሏል።—ዮሐ. 8:44)

ምክንያታቸው የማይታወቅ የሚመስሉ ነገሮች የሚፈጸሙት ለምንድን ነው?

መክ. 9:11 አዓት:- “ጊዜና አጋጣሚ [ኒኢ፣ ሪስ ] ሁሉንም ይገናኛቸዋል።” (አንድ ሰው አስቀድሞ ስለተወሰነበት ሳይሆን በአጋጣሚ ምክንያት መጥፎ ነገር ሊያገኘው ይችላል ማለት ነው።)

ሰዎች በራሳቸው ላይም ሆነ በሌሎች ሰዎች ላይ ለደረሱት ችግሮች ራሳቸው ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉን?

ሮሜ 5:12:- “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው [በአዳም] ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።” (ሁላችንም የፍጽምናን ጉድለት፣ ስህተት የመሥራትን ዝንባሌ ጭምር ከአዳም ወርሰናል።)

መክ. 8:9 አዓት:- “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።”

ምሳሌ 13:1 አዓት:- “የአባት ተግሣጽ ልጅን ጥበበኛ ያደርጋል።” (ወላጆች የሚያደርጉት ነገር በልጆቻቸው ሕይወት ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።)

ገላ. 6:7:- “አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና።” (በተጨማሪ ምሳሌ 11:17፤ 23:29, 30፤ 29:15፤ 1 ቆሮንቶስ 6:18 ተመልከት።)

በሰዎች ላይ መከራ የሚያመጡ ከሰው በላይ የሆኑ ኃይላት አሉን?

ራእይ 12:12:- “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።” (በተጨማሪም ሥራ 10:38⁠ን በአዓት ተመልከት።)

አምላክ እያንዳንዱን ነገር በቅድሚያ ያውቃል ወይም ይወስናል እንዴ?

ኢሳ. 46:9, 10:- “እኔ አምላክ ነኝና፣ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። በመጀመሪያ መጨረሻውን፣ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ።” (አምላክ ዓላማውን ያስታውቃል፣ የዓላማውን አፈጻጸም ስለሚመለከቱ አንዳንድ ጉዳዮችም በቅድሚያ ይወስናል። ዓላማውም በትክክል መፈጸሙን የሚያረጋግጥበት ሁሉን ማድረግ የሚችል ኃይል አለው።)

ኢሳ. 11:1–3:- “ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፣ ከሥሩም ቁጥቋጥ ያፈራል። [ኢየሱስ የተወለደው ከእሴይ የዘር ሐረግ ነው።] የእግዚአብሔር መንፈስ . . . ያርፍበታል። እግዚአብሔርን በመፍራት ደስታውን ያያል።” (ይሖዋ ልጁ ያለውን ዝንባሌና ጠባይ ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ በሰማይ ስለተመለከተ ስለ ልጁ ይህን በእርግጠኝነት አስቀድሞ ለመናገር ችሏል።) (ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ስለነበረው ሕልውና በገጽ 218 ላይ “ኢየሱስ ክርስቶስ” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።)

ዘዳ. 31:20, 21:- “[የእስራኤልን ሕዝብ] ለአባቶቻቸው ወደ ማልሁላቸው፣ ወተትና ማር ወደምታፈሰው ምድር ካገባኋቸው በኋላ፣ ከበሉም ከጠገቡም ከደነደኑም በኋላ፣ ሌሎችን አማልክት ተከትለው ያመልካሉ፣ እኔንም ይንቃሉ፣ ቃል ኪዳኔንም ያፈርሳሉ። ዛሬ ወደ ማልሁላቸው ምድር ገና ሳላገባቸው የሚያስቡትን አሳብ አውቃለሁና፣ . . . ብዙ ክፉ ነገርና ጭንቀት በደረሰባቸው ጊዜ ይህች መዝሙር [የአምላክን ሞገስ ባለማድነቃቸው ምክንያት ያደረጉትን ነገር የምትተርከው መዝሙር] ምስክር ሆና በፊታቸው ትመሰክራለች።” (አምላክ እስራኤላውያን ይከተሉት የነበረው መንገድ የሚያመጣውን ውጤት አስቀድሞ ለማስተዋል መቻሉ ለደረሰባቸው ነገር ተጠያቂ ነበር ወይም እንደዚህ እንዲያደርጉ ፍላጎቱ ነበር ማለት አይደለም። አካሄዳቸውን በመመልከት ወደፊት የሚደርስባቸውን ውጤት ለማወቅ ችሏል። ስለ አየር ሁኔታ የሚተነብይ ባለሙያ የተመለከታቸውን መረጃዎች መሠረት በማድረግ የወደፊቱን የአየር ሁኔታ ሊተነብይ ይችላል። ነገር ግን ያን የመሰለ የአየር ሁኔታ እንዲኖር አድርጓል ወይም ይወደዋል ማለት አይደለም።)

አምላክ ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች የማወቅና የመወሰን ችሎታ ያለው መሆኑ ፍጡሮቹ በሙሉ የሚፈጽሟቸውን ነገሮች በቅድሚያ እንደሚያውቅ ወይም እንደሚወስን ያረጋግጣልን?

ራእይ 22:17:- “የሚሰማም:- ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፣ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (እያንዳንዱ ግለሰብ የሚያደርገው ምርጫ አስቀድሞ የተወሰነ አይደለም። ምርጫው ለግለሰቡ የተተወ ነው።)

ሮሜ 2:4, 5:- “ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቁጣ ቀን ቁጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ።” (ሰዎች የተወሰነ መንገድ እንዲከተሉ አምላክ አያስገድዳቸውም። ለሚሠሩት ሥራ ግን በኃላፊነት ይጠየቃሉ።)

ሶፎ. 2:3:- “እናንተ . . . የምድር ትሑታን ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፣ ትሕትናንም ፈልጉ፤ ምናልባት በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።” (ፍትሐዊና አፍቃሪ የሆነ አምላክ እንደማይድኑ አስቀድሞ የተወሰነባቸው ሰዎች ሽልማት ለማግኘት እንዲችሉ ትክክለኛ የሆኑ ነገሮችን እንዲያደርጉ ቢያበረታታ ትክክል ይሆናልን?)

ምሳሌ:- አንድ ሬዲዮ ያለው ሰው የዓለምን ዜናዎች ሊያዳምጥ ይችላል። ይሁን እንጂ አንድን የሬዲዮ ጣቢያ ሊያዳምጥ መቻሉ ያንን የሬዲዮ ጣቢያ ያዳምጣል ማለት አይደለም። በመጀመሪያ ሬዲዮውን መክፈትና የሚፈልገውን ጣቢያ መምረጥ ይኖርበታል። በተመሳሳይም ይሖዋ ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች አስቀድሞ የማወቅ ችሎታ አለው። ይህን ችሎታውን ግን የሚጠቀምበት ለሰብዓዊ ፍጡሮች የሰጣቸውን የፈቀዱትን የማድረግ ነፃነት ግምት ውስጥ በማስገባት ለማወቅ የሚፈልጋቸውን ነገሮች በመምረጥና ባለማብዛት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።—ከዘፍጥረት 22:12፤ 18:20, 21 ጋር አወዳድር።

አምላክ አዳምን በፈጠረው ጊዜ ኃጢአት እንደሚሠራ ያውቅ ነበርን?

አምላክ ለአዳምና ለሔዋን የሰጠው ትእዛዝ የሚከተለው ነበር:- “ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።” “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው:- ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።” (ዘፍ. 1:28፤ 2:16, 17) ልጆችህ ገና ከመጀመሪያው እንደማይሳካላቸው እያወቅህ አስደናቂ ውጤት የሚያመጣ ሥራ እንዲጀምሩ ታበረታታቸዋለህን? አሳዛኝ ሁኔታ እንዲያጋጥማቸው የሚያደርግ እቅድ እንዳወጣህ እያወቅህ ጉዳት እንዳያገኛቸው ታስጠነቅቃቸዋለህን? ታዲያ አምላክስ ይህን የመሰለ ነገር ያደርጋል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነውን?

ማቴ. 7:11:- “እንኪያስ እናንተ ክፉዎች [ወይም “መጥፎዎች” ኒኢ] ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ፣ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው?”

አምላክ አዳም ኃጢአት እንደሚሠራና ይህም ኃጢአት ይህን ሁሉ ውጤት እንደሚያስከትል አስቀድሞ ያወቀና የወሰነ ከሆነ አዳምን በመፍጠሩ በሰው ታሪክ የተፈጸመውን ክፋት ሁሉ ሆን ብሎ ያመጣው አምላክ ነው ማለት ይሆናል። የጦርነቶች፣ የወንጀል፣ የሥነ ምግባር መበላሸት፣ የጭቆና፣ የውሸት፣ የግብዝነት፣ የበሽታ ሁሉ ምንጭ አምላክ ይሆናል ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን በግልጽ እንዲህ ይላል:- “አንተ በደልን የማትወድድ አምላክ ነህ።” (መዝ. 5:4) “ክፉዎችንና ዐመፀኞችን ግን አጥብቆ ይጠላቸዋል።” (መዝ. 11:5 የ1980 ትርጉም ) “አምላክ . . . ሊዋሽ አይችልም።” (ቲቶ 1:2 አዓት ) አምላክ መሲሐዊ ንጉሥ አድርጎ የሾመው “ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል፤ ስማቸው [“ደማቸው” አዓት ] በፊቱ ክቡር ነው።” (መዝ. 72:14) “እግዚአብሔር ፍቅር ነው።” (1 ዮሐ. 4:8) “ጽድቅንና ፍርድን ይወድዳል።”—መዝ. 33:5

አምላክ የያዕቆብንና የዔሣውን ዕጣ አስቀድሞ ወስኗልን?

ዘፍ. 25:23:- “እግዚአብሔርም [ለርብቃ] አላት:- ሁለት ወገኖች በማኅፀንሽ ናቸው፣ ሁለቱም ሕዝብ ከሆድሽ ይከፈላሉ፤ ሕዝብም ከሕዝብ ይበረታል፤ ታላቁም [ዔሣው] ለታናሹ [ለያዕቆብ] ይገዛል።” (ይሖዋ ገና ያልተወለዱትን የሁለቱን መንትያዎች አፈጣጠር ወይም የባሕርይ አወራረስ ለማንበብ ችሎ ነበር። ሁለቱ ልጆች ወደፊት የሚኖራቸውን ባሕርይና ይህም ባሕርያቸው የሚያስከትለውን ውጤት አስቀድሞ ያወቀው ይህን በመመልከት ሊሆን ይችላል። [መዝ. 139:16] ይሁን እንጂ ስለ ዘላለማዊ ሕይወታቸው ወይም በሕይወታቸው ውስጥ ስለሚያጋጥማቸው ስለ እያንዳንዱ ሁኔታ አስቀድሞ እንደወሰነ የሚያመለክት ምንም ፍንጭ የለም።)

የአስቆሮቱ ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ እንደሚሰጥ አስቀድሞ ተወስኖ ነበርን?

መዝ. 41:9:- “ደግሞ የሰላሜ ሰው የታመንሁበት እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ።” (ትንቢቱ የትኛው የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ አሳልፎ እንደሚሰጠው ለይቶ እንደማያመለክት ልብ ማለት ይገባል። የዳዊት አማካሪ የነበረው አኪጦፌል ዳዊትን እንዲከዳ በማድረግ ዲያብሎስ እንደተጠቀመበት ይሖዋ ያውቅ ነበር። ይህም ታሪክ ተመዝግቦ እንዲቆይ ያደረገበት ምክንያት ዲያብሎስ እንዴት እንደሚሠራና ወደፊት ምን እንደሚያደርግ ለማሳየት ነው። “በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ [ኢየሱስን] አሳልፎ እንዲሰጠው አሳብ” ያገባበት ዲያብሎስ ነው እንጂ አምላክ አይደለም። [ዮሐ. 13:2] ይሁዳ ዲያብሎስን ከመቃወም ይልቅ ለሰይጣን ግፊት በር ከፈተ።)

ዮሐ. 6:64:- “ኢየሱስ . . . አሳልፎ የሚሰጠው ማን እንደ ሆነ ከመጀመሪያ ያውቅ ነበር።” (ከፍጥረት መጀመሪያ ወይም ይሁዳ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ሳይሆን እምነት ማጉደል ‘ከጀመረበት’ ጊዜ ጀምሮ ማለት ነው። ከ⁠ዘፍጥረት 1:1፣ ሉቃስ 1:2 እና ከ⁠1 ዮሐንስ 2:7, 13 ጋር አወዳድር። በእነዚህ ጥቅሶች ላይ “መጀመሪያ” የሚለው ቃል የገባው አንጻራዊ በሆነ መንገድ ነው። በተጨማሪም ዮሐንስ 12:4–6 ላይ ያለውን ልብ በል።)

የክርስቲያኖች የወደፊት ሁኔታ ‘አስቀድሞ የተወሰነ’ መሆኑን ሐዋርያው ጳውሎስ ተናግሮ የለምን?

ሮሜ 8:28, 29:- “እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኩር ይሆን ዘንድ፣ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና።” (በተጨማሪም ኤፌሶን 1:5, 11) ይሁን እንጂ ለእነዚሁ ሰዎች 2 ጴጥሮስ 1:10 እንዲህ ይላል:- “መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ። እነዚህን ብታደርጉ [“ማድረጋችሁን ብትቀጥሉ ” “አዓት ”] ከቶ አትሰናከሉምና።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ግለሰቦቹ ለመዳን የተወሰኑ ከሆኑ ምንም ነገር ቢሠሩ ሊሰናከሉ አይችሉም ነበር። ከግለሰቦቹ ጥረት ማድረግ ይፈለግ ስለነበር አስቀድሞ የተወሰነው የጠቅላላው ቡድን ሁኔታ መሆን አለበት። ቡድኑ በአጠቃላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወው ምሳሌ ጋር እንዲስማማ የአምላክ ዓላማ ነው። ይሁን እንጂ የዚህ ቡድን አባላት እንዲሆኑ አምላክ የመረጣቸው ግለሰቦች ከፊታቸው የተቀመጠውን ሽልማት ለማግኘት የታመኑ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው።)

ኤፌ. 1:4, 5:- “ዓለም ሳይፈጠር፣ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በ[ኢየሱስ]ክርስቶስ መረጠን። በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ሉቃስ 11:50, 51 ላይ ኢየሱስ ‘የዓለምን መፈጠር’ ከአቤል ዘመን ጋር እንዳያያዘ ልብ ማለት ይገባል። አቤል በሕይወት በኖረበት ዘመን ሁሉ የአምላክን ሞገስ ያገኘ የመጀመሪያው ሰው ነበር። አምላክ መዳን የሚገኝበትን “ዘር” ለማስገኘት ዓላማ ያወጣው በኤደን ውስጥ ዓመፅ ከተፈጸመ በኋላና አቤል ከመፀነሱ በፊት ነበር። [ዘፍ. 3:15] በዚያ ጊዜ አምላክ ከዋነኛው ዘር ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚተባበር የታማኝ ተከታዮች ቡድን በምድር ላይ በምትቋቋመው አዲስ መሲሐዊት መስተዳድር እንደሚካፈል ዓላማ አወጣ።)

በሕይወታችን ውስጥ በሚያጋጥሙን ነገሮች ላይ ከዋክብትና ፕላኔቶች ተፅዕኖ የማሳደር ኃይል አላቸውን? ውሣኔ በምናደርግበትስ ጊዜ ሊመራን የሚችልና በትኩረት ልንከታተለው የሚገባ ምልክት ይሰጡናልን?

ኮከብ ቆጠራ የተጀመረው የት ነው?

“በምዕራባውያን አገሮች ዘንድ የተስፋፋው ኮኮብ ቆጠራ በ2,000ዎቹ ዓመታት ከዘአበ ከነበረው የከለዳውያንና የባቢሎናውያን ኮኮብ ቆጠራ በቀጥታ የመጣ ነው።”—ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና (1977)፣ ጥራዝ 2፣ ገጽ 557

“የኮኮብ ቆጠራ በሁለት የባቢሎናውያን ሐሳቦች ላይ የተመሠረተ ነው:- እነርሱም ዞዲያክና የሰማያዊ አካላት መለኮታዊነት ናቸው። . . . ባቢሎናውያን ፕላኔቶች ከአማልክቶቻቸው ጋር ተመሳሳይ የሆነ ኃይል እንዳላቸው ያምኑ ነበር።”—ግሬት ሲቲስ ኦቭ ዘ ኤንሸንት ወርልድ (የጥንቱ ዓለም ታላላቅ ከተሞች)፣ (ኒው ዮርክ፣ 1972)፣ ኤል ስፕራግ ደ ካምፕ፣ ገጽ 150

“በባቢሎንም ሆነ የባቢሎናውያን ባሕል ተቀጽላ በሆነው የአሦራውያን ባሕል ውስጥ . . . ቀሳውስቱ የአማልክቱን ፈቃድና ፍላጎት ለማወቅ ከሚጠቀሙባቸው ሁለት ዋና ዋና መንገዶች አንዱ ኮከብ ቆጠራ ነበር። . . . ሁለተኛው መንገድ ደግሞ ለመሥዋዕት የታረዱ እንስሳትን ጉበት መመርመር ነበር። . . . የፀሐይ፣ የጨረቃና የአምስቱ ፕላኔቶች እንቅስቃሴ የጨረቃ አምላክ ሲን፣ የፀሐይ አምላክ ሻማሽ፣ እንዲሁም ሌሎቹ አምስት አማልክት በምድር ላይ የሚፈጸሙትን ክንውኖች በሚያዘጋጁበት ጊዜ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንደሚያመለክት ይታመን ነበር።”—ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ (1911)፣ ጥራዝ 2፣ ገጽ 796

የሰው ልጆች ፈጣሪ እንደዚህ ስላለው ድርጊት ያለው አመለካከት ምንድን ነው?

ዘዳ. 18:10–12:- “ምዋርተኛም፣ ሞራ ገላጭም፣ አስማተኛም፣ . . . በአንተ ዘንድ አይገኝ። ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው።”

አምላክ ለባቢሎናውያን እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “አሁንም የሰማይን ከዋክብት የሚቆጥሩ፣ ከዋክብትንም የሚመለከቱ፣ በየመባቻውም የሚመጣውን ነገር የሚናገሩ ተነሥተው ከሚመጣብሽ ነገር ያድኑሽ። እነሆ፣ እንደ እብቅ ይሆናሉ፣ . . . የደከምሽባቸው ነገሮች እንዲህ ይሆኑብሻል፤ ከሕፃንነትሽ ጀምረው ከአንቺ ጋር ይነግዱ የነበሩ እያንዳንዳቸው ወደ ስፍራቸው ይሄዳሉ፣ የሚያድንሽም የለም።”—ኢሳ. 47:13–15