በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዘሮች

ዘሮች

ፍቺ:- ዘር እዚህ ላይ ባለው አጠቃቀም መሠረት ሊወረሱ የሚችሉና አንድን የተወሰነ የሰው ልጆች ወገን ከሌሎች ለመለየት የሚያስችሉ አካላዊ ባሕርያት ያሉት የሰው ልጆች ክፍል ነው። ይሁን እንጂ የተለያዩ ዘሮች እርስ በርሳቸው ሊጋቡና ሊዋለዱ መቻላቸው ሁሉም ከአንድ “ወገን” የሆኑ የሰው ልጅ ቤተሰብ አባሎች እንደሆኑ እንደሚያመለክት ልብ ማለት ያስፈልጋል። ስለዚህ የተለያዩት ዘሮች በተለያዩ ሕዝቦች መካከል ያለውን ልዩ ልዩ ገጽታ የሚያመለክቱ ብቻ ናቸው።

የተለያዩ ዘሮች ከየት መጡ?

ዘፍ. 5:1, 2፤ 1:28:- “እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፣ ባረካቸውም። ስማቸውንም በተፈጠረበት ቀን አዳም [ወይም የሰው ዘር] ብሎ ጠራቸው።” “እግዚአብሔርም ባረካቸው፣ እንዲህም አላቸው:- ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት።” (ስለዚህ የሰዎች ልጆች በሙሉ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት የአዳምና የሔዋን ዝርያዎች ወይም ተወላጆች ናቸው።)

ሥራ 17:26:- “[እግዚአብሔር] በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ [ከአዳም] ፈጠረ።” (ስለዚህ አንድ ብሔር ከየትኞቹም ዘሮች የተውጣጣ ቢሆን ሁሉም የአዳም ዘር ናቸው።)

ዘፍ. 9:18, 19:- “ከመርከብ የወጡት የኖኅ ልጆችም እነዚህ ናቸው፣ ሴም፣ ካም፣ ያፌት፤ . . . የኖኅ ልጆች እነዚህ ሦስቱ ናቸው፤ ከእነርሱም ምድር ሁሉ ተሞላች።” (አምላክ በኖኅ ዘመን ለአምላክ አክብሮት የሌለውን ዓለም በምድር አቀፍ ጎርፍ ካጠፋ በኋላ የተገኙት አዲሶቹ የምድር ነዋሪዎች፣ ዛሬ የሚታወቁት ዘሮች ጭምር ከኖኅ ሦስት ልጆችና ከሚስቶቻቸው የተገኙ ናቸው።)

አዳምና ሔዋን አፈ ታሪክ የፈጠራቸው ሰዎች ናቸውን?

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለውን አመለካከት አይደግፍም። “አዳምና ሔዋን” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት።

በምድር ላይ የነበረው አንድ ቤተሰብ ብቻ ከሆነ ቃየን ሚስቱን ከየት አገኘ?

ዘፍ. 3:20:- “አዳም ለሚስቱ ሔዋን ብሎ ስም አወጣ፣ የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና።” (ስለዚህ የሰው ልጆች በሙሉ የአዳምና የሔዋን ልጆች እንዲሆኑ ታስቦ ነበር።)

ዘፍ. 5:3, 4 የ1980 ትርጉም:- “አዳም መቶ ሠላሳ ዓመት በሆነው ጊዜ በመልክ እርሱን የሚመስል ወንድ ልጅ ወለደ፤ “ሤት” የሚል ስም አወጣለት። ከዚህ በኋላ አዳም 800 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወለደ።” (ከአዳም ወንድ ልጆች አንዱ ቃየን ነበር። የቃየን ሚስት የሆነችውም ከአዳም ሴት ልጆች አንዷ ነበረች። በዚያ ዘመን ይኖሩ የነበሩት ሰዎች ከፍተኛ የሆነ አካላዊ ጤንነትና ብርታት ስለነበራቸው የቅርብ ዘመድ በማግባት ምክንያት በልጆች ላይ አካላዊ ጉድለት የማስተላለፉ አደጋ አነስተኛ ነበር። ይህንንም ከዕድሜአቸው ርዝማኔ መረዳት ይቻላል። ይሁን እንጂ ከ2,500 ዓመታት የሰው ልጆች ታሪክ በኋላ የሰው ልጅ አካላዊ ሁኔታ በጣም እየተበላሸ ስለመጣ ይሖዋ የቅርብ ዘመድን ማግባት የሚከለክል ሕግ ለእስራኤላውያን ሰጠ።)

ዘፍ. 4:16, 17:- “ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፤ ከዔድንም ወደ ምሥራቅ በኖድ ምድር ተቀመጠ። ቃየንም ሚስቱን አወቀ፤ [በፆታ ግንኙነት ማለት ነው፤ “ከሚስቱ ጋር ተኛ” ኒኢ፤ “ከሚስቱ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት አደረገ” የ1980 ትርጉም ] ፀነሰችም፣ ሔኖህንም ወለደች።” (ቃየን ሚስቱን ከሌላ ቤተሰብ እንደመጣች ሆና በመጀመሪያ ያገኛት ሸሽቶ በሄደበት ምድር አልነበረም። ከሚስቱ ጋር የፆታ ግንኙነት ያደረገውና ወንድ ልጅ የወለደው ግን በተሰደደበት አገር ነበር።)

የተለያዩ ዘሮች የተለያየ መልክ የኖራቸው ለምንድን ነው?

“በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ ሆሞ ሳፒየንስ የተባለው ዝርያ አባሎች ስለሆኑ ከአንድ የጋራ ግንድ የተገኙ ናቸው። . . . በሰው ልጆች መካከል ባዮሎጂያዊ ልዩነት የኖረው በዘር ውርሻና የአካባቢ ሁኔታዎች በባሕርይ አወራረስ ላይ ተጽዕኖ ስላሳደሩ ነው። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ልዩነቶች በእነዚህ ሁለት ነገሮች ምክንያት የመጡ ናቸው። . . . ብዙ ጊዜ የአንድ ዘር ወይም ሕዝብ አባሎች በሆኑ ግለሰቦች መካከል የሚኖረው ልዩነት በተለያዩ ዘሮች ወይም ሕዝቦች መካከል ካለው ልዩነት ይበልጣል።”— ዩኔስኮ የሰበሰባቸው ዓለም አቀፍ ሳይንቲስቶች ቡድን፣ ስቴትመንት ኦን ሬስ (ዘርን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ) በተባለው መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰ (ኒው ዮርክ፣ 1972፣ ሦስተኛ እትም) አሽሊ ሞንታጎ፣ ገጽ 149, 150

“ዘር የሰው ልጅ መበታተን በጀመረበት ጊዜና ከተበተነ በኋላ ከተከፋፈለባቸው የጂን ማዕከሎች አንዱ ነው። በአምስቱ አህጉራት ላይ በአብዛኛው በየአህጉሩ አንድ ዓይነት ዘር ተስፋፍቷል። . . . በእርግጥም የሰው ልጅ ጄኔቲካዊ ባሕርይ የተጀመረው በዚህ የሰው ልጅ ታሪክ ዘመን ነው። ይህ መለያየት ያስከተለውን ውጤት ከጥንቶቹ ጂኦግራፊያዊ ዘሮች ቅሪቶች ማጥናትና መለካት ይቻላል። ለመገመት እንደሚቻለው መለያየቱ ተገልሎ ከመኖር ጋር ከፍተኛ ዝምድና አለው። . . . በየአህጉራቱ ላይ የተለያዩ ዘሮች በተገኙና በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በመላው ዓለም ላይ ለየብቻቸው ተገልለው መኖር በጀመሩ ጊዜ አሁን የምንመለከተው የጂን ልዩነት ተፈጠረ። . . . አሁን ያጋጠመን እንቆቅልሽ እያንዳንዱ የሰው ልጆች ዘር በውጭ ሲታይ የተለያየ ሆኖ በውስጡ ግን መሠረታዊ ተመሳሳይነት ያለው መሆኑ ነው።” (ሄሪዲቲ ኤንድ ሂውማን ላይፍ (ውርስና ሰብዓዊ ሕይወት)፣ ኒው ዮርክ፣ 1963፣ ኤች ኤል ካርሰን፣ ገጽ 151, 154, 162, 163) (ስለዚህ በሰው ልጆች ታሪክ መጀመሪያ ላይ አንድ የሰዎች ቡድን ከሌሎቹ ተነጥሎ እርስ በእርሱ ብቻ እየተጋባ ሲኖር በሚወለዱት ልጆች ላይ ያንን ቡድን ልዩ የሚያደርጉት ጄነቲካዊ ባሕርያት መታየት ጀመሩ።)

መጽሐፍ ቅዱስ ጥቁሮች የተረገሙ ናቸው ብሎ ያስተምራልን?

ይህ አስተሳሰብ የመጣው ዘፍጥረት 9:25⁠ን በትክክል ካለመረዳት ነው። እዚህ ቦታ ላይ ኖኅ “ከነዓን እርጉም ይሁን፤ ለወንድሞቹም የባሪያዎች ባሪያ ይሁን” እንዳለ ተጠቅሷል። ይህን ጥቅስ በጥንቃቄ አንብብ። ስለ ቆዳ ቀለም የሚናገረው ነገር የለም። የካም ወንድ ልጅ ከነዓን የተረገመው አስነዋሪ ድርጊት ስለፈጸመ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ የከነዓን ዝርያዎች እነማን ናቸው? ከሜዲትራንያን ባሕር በስተምሥራቅ የሚኖሩ ነጣ ያለ የቆዳ ቀለም ያላቸው ሕዝቦች ናቸው እንጂ ጥቁሮች አይደሉም። እነዚህም ሕዝቦች በወራዳ ልማዳቸው፣ በአጋንንታዊ ሥራቸው፣ በጣዖት አምልኮታቸው እና ልጆቻቸውን በመሠዋታቸው መለኮታዊ ፍርድ ተፈጽሞባቸዋል። አምላክም ከነዓናውያን ይኖሩበት የነበረውን ምድር ለእስራኤላውያን ሰጥቷቸዋል። (ዘፍ. 10:15–19) ሁሉም ከነዓናውያን አልጠፉም። አንዳንዶቹ በእርግማኑ መሠረት የግዳጅ ሥራ እየሠሩ እንዲኖሩ ተደርገዋል።—ኢያሱ 17:13

ጥቁሮች የተወለዱት ከየትኞቹ የኖኅ ልጆች ነው? “የኩሽም ልጆች [ሌላው የካም ወንድ ልጅ ነው] ሳባ፣ ኤውላጥ፣ ሰብታ፣ ራዕማ፣ ሰበቃታ ናቸው።” (ዘፍ. 10:6, 7) ከዚያ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱት ኩሽና ኢትዮጵያ በአብዛኛው አንድ ናቸው። በኋላ ሳባ በአፍሪካ በስተምሥራቅ በኢትዮጵያ አጠገብ የሚኖሩ ሕዝቦችን ለማመልከት ተሠርቶበታል።—ኢሳ. 43:3 ባለማጣቀሻው የአዓት እትም የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

የሰው ልጆች በሙሉ የአምላክ ልጆች ናቸውን?

የአምላክ ልጅ መሆን ሁላችንም ፍጹም ያልሆን የሰው ልጆች በትውልድ የምናገኘው መብት አይደለም። ይሁን እንጂ ሁላችንም ፍጹም ሆኖ በተፈጠረበት ጊዜ “የአምላክ ልጅ” የነበረው የአዳም ልጆች ነን።—ሉቃስ 3:38

ሥራ 10:34, 35:- “እግዚአብሔር ለሰው ፊት [አያደላም፤] ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ [ነው።]”

ዮሐ. 3:16:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድርስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ሁላችንም ከአምላክ ጋር አዳም ያጣው ዓይነት የተቀራረበ ዝምድና እንዲኖረን ከፈለግን በኢየሱስ ማመን ያስፈልገናል። ይህ መብት ለሰው ዘሮች ሁሉ ክፍት ነው።)

1 ዮሐ. 3:10 የ1980 ትርጉም:- “የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁት እነሆ በዚህ ነው፤ ጽድቅ የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም።” (ስለዚህ አምላክ የሰው ልጆችን በሙሉ እንደ ልጆቹ አድርጎ አይመለከታቸውም። ሆን ብለው አምላክ የሚያወግዛቸውን ነገሮች የሚያደርጉ ሁሉ በመንፈሳዊ አመለካከት የዲያብሎስ ልጆች ናቸው። ዮሐንስ 8:44⁠ን ተመልከት። ይሁን እንጂ እውነተኛ ክርስቲያኖች አምላካዊ ባሕርያትን ያንጸባርቃሉ። ከእነዚህም መካከል የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ነገሥታት ሆነው እንዲገዙ አምላክ መርጧል። እነዚህን “ልጆቹ” እንደሆኑ ይናገራል። ለተጨማሪ ማብራሪያ “እንደገና መወለድ” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት።)

ሮሜ 8:19–21:- “የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና። . . . ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው።” (የሰው ልጅ ከጥፋት ባርነት የሚገላገለው “የአምላክ ልጆች” ሰማያዊ ሕይወት ካገኙ በኋላ በክርስቶስ አመራር ሥር ሆነው ለሰው ልጆች ጥቅም ተጨባጭ እርምጃ በመውሰድ ‘በሚገለጥበት’ ጊዜ ነው። [በዚህ ጥቅስ ላይ ፍጥረት የተባሉት] በምድር ላይ የሚኖሩ ታማኝ ሰዎች ሰብዓዊ ፍጽምና ካገኙና የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ለሆነው ለይሖዋ የማይናጋ የታማኝነት አቋማቸውን ካረጋገጡ በኋላ የአምላክን ልጅነት ያገኛሉ። ከዚህም ተስፋ ሁሉም ዓይነት ዘሮች ይካፈላሉ።)

ወደፊት ሁሉም ዘሮች አንድ የወንድማማቾችና የእህትማማቾች ቤተሰብ ይሆናሉን?

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ስለሚሆኑት ሰዎች ሲናገር “ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” ብሏል። (ማቴ. 23:8) በኋላም እንዲህ ብሏል:- “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።”—ዮሐ. 13:35

የጥንት ክርስቲያኖች ሰብዓዊ አለፍጽምና እያለባቸውም ቢሆን የአንድነት መንፈስ ይታይባቸው ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፣ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፣ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።”—ገላ. 3:28

በዚህ በ20ኛ መቶ ዘመን በዘር ልዩነቶች ያልተበከለ ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት በይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ ይገኛል። ዊሊያም ሁዌልን የተባሉት ጸሐፊ በዩ ኤስ ካቶሊክ ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “[ከይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት] ማራኪ ባሕርያት አንዱ በተለያዩ ዘሮች መካከል እኩልነትን ባሕል ማድረጋቸው መሆኑን አምናለሁ።” የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ማኅበራዊ ሊቅ የሆኑት ብራያን ዊልሰን በአፍሪካ በሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ሰፊ ጥናት ካደረጉ በኋላ እንዲህ ብለዋል:- “ምሥክሮቹ ከተመልማዮቻቸው መካከል የጐሣ ልዩነትን በማስወገድ ረገድ ከማንኛውም ቡድን በበለጠ ፍጥነት ተሳክቶላቸዋል።” ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ማጋዚን ከ123 አገሮች የተውጣጡ የይሖዋ ምሥክሮች ስለተሳተፉበት ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “ምሥክሮቹ የኒው ዮርክን ነዋሪዎች ያስደነቁት በብዛታቸው ብቻ አልነበረም፤ ከተለያዩ የኑሮ ዘርፎች የተውጣጡ በመሆናቸው፣ በመካከላቸው የዘር ልዩነት ባለመታየቱ (ብዙ ጥቁር ምሥክሮች አሉ) በዝግተኛነታቸውና በሥርዓታማ ጠባያቸው ጭምር ነው።”

በቅርቡ የአምላክ መንግሥት ለአምላክ ደንታ የሌለውን የአሁኑን ሥርዓትና ይሖዋ አምላክንና መሰሎቻቸውን የሰው ዘሮች ከልባቸው የማይወዱትን ሰዎች ታጠፋለች። (ዳን. 2:44፤ ሉቃስ 10:25–28) ከጥፋቱ በሕይወት የሚተርፉት ‘ከሕዝብና ከነገድ፣ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ’ የተውጣጡ እንደሚሆኑ የአምላክ ቃል ተስፋ ይሰጣል። (ራእይ 7:9) እነዚህ ሰዎች በእውነተኛው አምላክ አምልኮ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት እና እርስ በእርሳቸው ባላቸው ፍቅር ስለሚተሳሰሩ አንድ የተባበረ የሰው ልጆች ቤተሰብ ይሆናሉ።