በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዓለም መንፈስ

የዓለም መንፈስ

ፍቺ:- ከይሖዋ አምላክ አገልጋዮች ውጭ ያለውን ሰብዓዊ ማኅበረሰብ የሚቆጣጠረውና የሚመራው እንዲሁም ይህ ማኅበረሰብ የራሱ የሆነ አነጋገርና አሠራር እንዲኖረው የሚያደርገው ኃይል ነው። ሰዎች የሚያደርጓቸውን ነገሮች በየራሳቸው ምርጫ የሚወሰኑ ቢሆኑም የዓለም መንፈስ የሚታይባቸው ሁሉ ሰይጣን ገዢና አምላክ የሆነበት የዚህ ሥርዓት የተለየ ባሕርይ የሆነው መሠረታዊ ዝንባሌ፣ አሠራርና የሕይወት ዓላማ ይታይባቸዋል።

የዓለም መንፈስ መበከል በጣም አሳሳቢ ነገር የሆነው ለምንድን ነው?

1 ዮሐ. 5:19:- “ዓለምም በሞላው በክፉው [ተይዟል።]” (የይሖዋ አገልጋዮች ያልሆኑትን ሰዎች አስተሳሰብና እንቅስቃሴ የሚገዛውን መንፈስ የሚያስፋፋውና የሚያዳብረው ሰይጣን ነው። ይህ መንፈስ የራስ ወዳድነትና የኩራት መንፈስ ከመሆኑም በላይ በጣም የተስፋፋ በመሆኑ ሰዎች እንደሚተነፍሱት አየር ሆኗል። ይህ መንፈስ አኗኗራችንን እንዲቀርጽ ባለመፍቀድ ራሳችንን ለሰይጣን ኃይል እንዳናስገዛ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል።)

ራእይ 12:9:- “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ፣ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።” (መንግሥቲቱ በ1914 ከተወለደች በኋላ ከተፈጸመው ከዚህ እርምጃ በኋላ ሰይጣንና አጋንንቱ በሰው ልጆች ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ በጣም ተጠናክሯል። ሰዎች በይበልጥ ራስ ወዳዶችና ዓመፀኞች እንዲሆኑ የሰይጣን መንፈስ ገፋፍቷቸዋል። በተለይ ይሖዋ አምላክን ለማገልገል የሚፈልጉ ሰዎች የዓለም ክፍል እንዲሆኑ፣ ሌሎች የሚያደርጉትን እንዲያደርጉና እውነተኛ አምልኮን እንዲተዉ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያደርስባቸዋል።)

ልንከላከላቸው ከሚገቡን የዓለም መንፈስ ባሕርያት አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

1 ቆሮ. 2:12:- “እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።” (የዓለም መንፈስ በአንድ ሰው አስተሳሰብና ፍላጎት ውስጥ ሥር ከሰደደ ፍሬው በሰውዬው ድርጊቶችና መንፈስ ይገለጻል። ስለዚህ ከዓለም መንፈስ መራቅ ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ድርጊቶችንና ልከኝነት የጎደላቸውን ነገሮች በማስወገድ ብቻ ሳንወሰን የአምላክን መንፈስና ለአምላክ መንገዶች ያለንን ልባዊ ፍቅር የሚያንጸባርቁ ጠባዮችን በመኮትኮት ችግሩን ከሥር መንቀል ይኖርብናል። የዓለም መንፈስ የሚገለጽባቸውን የሚከተሉትን መንገዶች በምትመረምርበት ጊዜ ይህንን በአእምሮህ መያዝ ይኖርብሃል።)

የአምላክን ፈቃድ ችላ ብሎ የፈለጉትን ማድረግ

ሰይጣን ሔዋን መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር ራሷ እንድትወስን መክሯታል። (ዘፍ. 3:3–5፤ የዚህን ተቃራኒ በ⁠ምሳሌ 3:5, 6 ላይ ተመልከት።) የሔዋንን መንገድ የሚከተሉ ብዙ ሰዎች አምላክ ለሰው ልጆች ያወጣውን ፈቃድ አያውቁም። ለማወቅም አይጨነቁም። ራሳቸው እንደሚናገሩት “የፈለጉትን ያደርጋሉ።” የአምላክን ትእዛዛት የሚያውቁና ከእነዚህም ትእዛዛት ጋር ተስማምተው ለመኖር የሚፈልጉ ሁሉ የዓለም መንፈስ የአምላክን ቃል ምክሮች ‘ትንንሽ’ ናቸው ብለው በሚገምቷቸው ነገሮች እንኳን ሆን ብለው እንዲተላለፉ እንዳያደርጋቸው መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።—ሉቃስ 16:10፤ በተጨማሪም “በራስ መመራት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

አንዳንድ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በኩራት ላይ የተመሠረተ እርምጃ መውሰድ

ለመጀመሪያ ጊዜ ከሚገባው በላይ ራሱን ከፍ አድርጎ በመመልከት ልቡ ወደ ተሳሳተ መንገድ እንዲያመራ የፈቀደው ሰይጣን ነው። (ከ⁠ሕዝቅኤል 28:17⁠ና ከ⁠ምሳሌ 16:5 ጋር አወዳድር።) ሰይጣን ገዢው የሆነለትን ይህን ዓለም የሚከፋፍለው ኃይል ኩራት ነው። ሰዎች ከሌሎች ዘሮች፣ ብሔሮችና ቋንቋዎች የበለጡ እንደሆኑ፣ የኑሮ ደረጃቸውም የተሻለ እንደሆነ ስለሚያስቡ እርስ በርሳቸው ተከፋፍለዋል። አምላክን የሚያገለግሉ ሰዎች እንኳን እንደነዚህ ያሉት ስሜቶች ቅሪት እንዳይኖርባቸው መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም ኩራት ጥቃቅን ጉዳዮችን ትልቅ ነገር አድርገው እንዲጨቃጨቁና ስህተታቸውን ተቀብለው ይሖዋ በድርጅቱ በኩል ከሚሰጣቸው ፍቅራዊ እርዳታዎች እንዳይጠቀሙ እንዳያደርጋቸው መጠንቀቅ ያስፈልጋቸዋል።—ሮሜ 12:3፤ 1 ጴጥ. 5:5

ለባለ ሥልጣኖች የዓመፀኝነት ዝንባሌ ማሳየት

ዓመፅ የተጀመረው በሰይጣን ነው። ሰይጣን ማለት ራሱ “እምቢተኛ” ማለት ነው። “እናምፅ” የሚል ትርጉም ሊኖረው የሚችል ስም የተሰጠው ናምሩድም ይሖዋን በመገዳደር የሰይጣን ልጅ መሆኑን በተግባሩ አስመስክሯል። ይህንን ዓይነቱን መንፈስ ማስወገድ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ዓለማዊ ገዢዎችን እንዳይንቁ ያደርጋቸዋል። (ሮሜ 13:1) ትንንሽ ልጆች አምላክ ለወላጆቻቸው ለሰጠው ሥልጣን እንዲገዙ ይረዳቸዋል። (ቆላ. 3:20) ይሖዋ በሚታየው ድርጅቱ ውስጥ ኃላፊነት የሰጣቸውን ሰዎች ለሚያቃልሉት ከሃዲዎች የኀዘኔታ መንፈስ ከማሳየት ይጠብቃል።—ይሁዳ 11፤ ዕብ. 13:17

የውዳቂውን ሥጋ ፍላጎቶች ስድ መልቀቅ

በዚህ ረገድ የሚደርሰውን ተጽዕኖ በሁሉም ቦታ ማየትና መስማት ይቻላል። በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። (1 ዮሐ. 2:16፤ ኤፌ. 4:17, 19፤ ገላ. 5:19–21) በአንድ ሰው ውስጥ ከበድ ወዳለ መጥፎ ድርጊት ሊያመሩ የሚችሉ አስተሳሰቦችና ፍላጎቶች መኖራቸው በሰውዬው አነጋገር፣ ቀልዶች፣ በሚያዳምጣቸው ሙዚቃዎችና ግጥሞች፣ በሚጨፍራቸው የዳንስ ዓይነቶች የሥነ ምግባር ርኩሰት የሚታይባቸውን ፊልሞች በመመልከቱ ሊታይ ይችላል። ይህ የዓለም መንፈስ ዘርፍ አደንዛዥ ዕፆችን በመውሰድ፣ በስካር፣ በምንዝር፣ በዝሙትና በግብረ ሰዶም ይገለጣል። በተጨማሪም አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን ሕግ በሚፈቅደው ምክንያት ሊሆን ቢችልም ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆነ መንገድ ፈትቶ ሌላ በሚያገባበት ጊዜ ይገለጻል።—ሚል. 2:16

የአንድ ሰው ሕይወት የሚፈልገውን ሁሉ ለማግኘት ባለው ፍላጎት እንዲገዛ መፍቀድ

ሰይጣን ሔዋን እንዲያድርባት ያደረገው ይህን ዓይነቱን ፍላጎት ነበር። ከአምላክ ጋር ያላትን ዝምድና እንዲያበላሽባት ያደረገ ድርጊት እንድትፈጽም ገፋፋት። (ዘፍ. 3:6፤ 1 ዮሐ. 2:16) ኢየሱስ እንዲህ ያለውን ፈተና በጽናት ተቃውሞታል። (ማቴ. 4:8–10) ይሖዋን ለማስደሰት የሚፈልጉ ሁሉ የንግዱ ዓለም እንዲህ ያለው መንፈስ በውስጣቸው እንዲያድግ እንዳያደርግ መጠንቀቅ ይገባቸዋል። እንዲህ ባለው ፍላጎት የሚጠመዱ ሰዎች ሁሉ በራሳቸው ላይ ብዙ ኀዘንና መንፈሳዊ ጉዳት ያመጣሉ።—ማቴ. 13:22፤ 1 ጢሞ. 6:7–10

አንድ ሰው ንብረቱና በጥረቱ የደረሰባቸው ደረጃዎች እንዲታዩለት ማድረግ

ይህም ‘የዓለም’ ልማድ ነው። የአምላክ አገልጋዮች የሆኑ ሁሉ እንዲህ ያለውን ባሕርይ ማስወገድ ይኖርባቸዋል። (1 ዮሐ. 2:16 አዓት) የዚህ ባሕርይ መሠረቱ ኩራት ሲሆን ሌሎችን በመንፈሳዊ ከማነጽ ይልቅ በቁሳዊ ነገሮች እንዲታለሉና ዓለማዊ ነገሮችን በማግኘት ቅዠት እንዲዋጡ ያደርጋል።—ሮሜ 15:2

የራስን ስሜት በቁጣና በስድብ መወጣት

ይህ ጠባይ ብዙዎች ለማሸነፍ በኃይል ከሚዋጓቸው “የሥጋ ሥራዎች” መካከል የሚገኝ ነው። የዓለም መንፈስ እንዲገዛቸው ከመፍቀድ ይልቅ እውነተኛ በሆነ እምነትና በአምላክ መንፈስ እርዳታ ዓለምን ድል ለመንሳት ይችላሉ።—ገላ. 5:19, 20, 22, 23፤ ኤፌ. 4:31፤ 1 ቆሮ. 13:4–8፤ 1 ዮሐ. 5:4

ተስፋችንንና ሥጋታችንን የሰው ልጆች ሊያደርጉ በሚችሏቸው ነገሮች ላይ እንዲመሠረት ማድረግ

ሥጋዊ የሆነ ሰው ትልቅ ግምት የሚሰጠው ማየትና መዳሰስ ለሚችላቸው ነገሮች ነው። ተስፋውና ፍርሃቱ ሰዎች በሚሰጡት ተስፋና በሚናገሩት ዛቻ ላይ የተመሠረተ ነው። እርዳታ ለማግኘት ተስፋ የሚያደርገው ሰዎችን ነው። ሰዎች የጠበቀውን ሳያደርጉለት ሲቀሩም ግራ ይጋባል። (መዝ. 146:3, 4፤ ኢሳ. 8:12, 13) እንዲህ ባለ ሰው አስተሳሰብ ከዚህ ከአሁኑ በስተቀር ሌላ ሕይወት የለም። የሞት ፍርሃት እንደ ባሪያ አድርጎ ይገዛዋል። (የዚህን ተቃራኒ በ​ማቴዎስ 10:28​ና በ​ዕብራውያን 2:14, 15 ላይ ተመልከት።) ይሁን እንጂ ይሖዋን የሚያውቁ፣ አእምሯቸውና ልባቸው በይሖዋ ተስፋዎች እንዲሞሉ የሚያደርጉና በችግራቸው ጊዜ ሁሉ የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት የሚጥሩ ሰዎች አእምሮ አዲስ በሆነ ኃይል ይመራል።—ኤፌ. 4:23, 24፤ መዝ. 46:1፤ 68:19

ለይሖዋ ብቻ ሊሰጥ የሚገባውን የአምልኮ ክብር ለሰዎችና ለሌሎች ነገሮች መስጠት

“የዚህ ዓለም አምላክ” የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ አምላክ ለሰው ልጆች የሰጠውን የአምልኮ ዝንባሌ ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ሊመሩ የሚችሉትን ልማዶች ሁሉ እንድንፈጽም ያበረታታል። (2 ቆሮ. 4:4) አንዳንድ ገዥዎች እንደ አማልክት ተቆጥረዋል። (ሥራ 12:21–23) በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለጣዖታት ይሰግዳሉ። ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ደግሞ የፊልም ተዋናዮችንና ታዋቂ ስፖርተኞችን እንደ ጣዖት ያመልካሉ። ብዙ ክብረ በዓሎች ለግለሰቦች የማይገባ ክብር ይሰጣሉ። ይህ መንፈስ በጣም የተስፋፋና የተለመደ ስለሆነ ይሖዋን የሚወዱና እርሱን ብቻ ለማምለክ የሚፈልጉ ሁሉ ይህ መንፈስ በየዕለቱ የሚያደርስባቸውን ተጽዕኖ በንቃት መከታተል ይገባቸዋል።