የፆታ ግንኙነት
ፍቺ:- ሁለት ወላጆች ለመራባት የሚፈጽሙት የምድራዊ ፍጥረታት ባሕርይ ነው። በተባእትና በእንስት ፆታዎች መካከል ያለው ልዩነት በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ከመራባት የበለጠ ውጤት አስከትሏል። የሕይወት ምንጭ አምላክ ራሱ ስለሆነና የሰው ልጆችም የአምላክን ባሕርያት ማንጸባረቅ ስለሚኖርባቸው በፆታ ግንኙነት አማካኝነት ሕይወትን የማስተላለፍ ችሎታ በታላቅ አክብሮት መያዝ ይኖርበታል።
መጽሐፍ ቅዱስ የፆታ ግንኙነት ኃጢአት ነው ብሎ ያስተምራልን?
ዘፍ. 1:28:- “እግዚአብሔርም [አዳምንና ሔዋንን] ባረካቸው፣ እንዲህም አላቸው:- ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት።” (ይህን መለኮታዊ ትእዛዝ ለመፈጸም የፆታ ግንኙነት መፈጸም ይኖርባቸዋል። ይህንንም ድርጊት መፈጸማቸው አምላክ ምድርን ለመሙላት ካወጣው ዓላማ ጋር የሚስማማ እንጂ ኃጢአት አይሆንም። አንዳንድ ሰዎች በኤደን ውስጥ የነበረችው ‘የተከለከለች ፍሬ’ አዳምና ሔዋን የፆታ ግንኙነት እንዳያደርጉ የተጣለባቸውን እገዳ ወይም ገደብ የሚያመለክት ምሳሌ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ከላይ ከተጠቀሰው የአምላክ ትእዛዝ ጋር ይቃረናል። በተጨማሪም አዳምና ሔዋን ከተከለከሉት ፍሬ ቢበሉም የፆታ ግንኙነት እንደፈጸሙ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጸው ከኤደን ከተባረሩ በኋላ ነበር።—ዘፍ. 2:17፤ 3:17, 23፤ 4:1)
ዘፍ. 9:1:- “እግዚአብሔር ኖኅንና ልጆቹን ባረካቸው እንዲህም አላቸው:- ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት።” (ይህ በረከትና ቀድሞ ለአዳምና ለሔዋን የተሰጠው የመራባት መለኮታዊ ትእዝዝ በድጋሚ በኖኅ ዘመን ከጥፋት በኋላ ተነግሮ ነበር። አምላክ የተፈቀደ የፆታ ግንኙነትን ስለመጸም የነበረው አመለካከት አልተለወጠም።)
1 ቆሮ. 7:2–5 የ1980 ትርጉም:- “በዝሙት ኃጢአት ላለመውደቅ፣ እያንዳንዱ ወንድ የራሱ ሚስት ትኑረው፤ እያንዳንዱዋም ሴት የራስዋ ባል ይኑራት። ባል ለሚስቱ ማድረግ የሚገባውን የጋብቻ መብትዋን አይከልክላት፤ እንዲሁም ሚስት ለባልዋ ማድረግ የሚገባትን የጋብቻ መብቱን አትከልክለው። . . . ሁለታችሁም ተስማምታችሁ ለተወሰነ ጊዜ ካልሆነ በቀር በመለያየት አንዱ የሌላውን የጋብቻ መብት አይከልክል። ራሳችሁን መቆጣጠር አቅቶአችሁ ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ።” (ስለዚህ ስህተት የሚሆነው በባልና ሚስት መካከል የሚደረገው ትክክለኛ የፆታ ግንኙነት ሳይሆን ምንዝር እንደሆነ ተገልጿል።)
ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ክልክል ነውን?
1 ተሰ. 4:3–8 የ1980 ትርጉም:- “የእግዚአብሔር ፈቃድ . . . ከዝሙት እንድትርቁ ነው። ከእናንተ እያንዳንዱ የገዛ ሰውነቱን በቅድስናና በክብር መያዝን ይወቅ። እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አረማውያን የፍትወት ምኞት አይኑረው። በዚህ ነገር ማንም ወንድሙን አይበድል፣ ወይም አያታልል፤ ከዚህ በፊት እንደነገርናችሁ እንዳስጠነቀቅናችሁ፣ እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉትን ጌታ ይቀጣቸዋል። ምክንያቱም እግዚአብሔር የጠራን በቅድስና እንድንኖር ነው እንጂ በርኩሰት እንድንኖር አይደለም። ስለዚህ ይህን ምክር የሚቃወም የሚቃወመው ቅዱስ መንፈሱን የሚሰጣችሁን እግዚአብሔር እንጂ ሰውን አይደለም።” (“ዝሙት” ተብሎ የተተረጐመው ፖርኒያ የተባለ የግሪክኛ ቃል ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸመውንና ያገቡ ሰዎች ከጋብቻቸው ውጭ የሚፈጽሙትን የፆታ ግንኙነት ያመለክታል።)
ኤፌ. 5:5:- “አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኩስ ወይም የሚመኝ እርሱም ጣዖትን የሚያመልክ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም።” (ይህ ማለት ቀድሞ ዝሙት ይፈጽም የነበረ ሰው የአምላክን መንግሥት በረከቶች ሊያገኝ አይችልም ማለት አይደለም። የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ከፈለገ ይህን አድራጎቱን መተው ይኖርበታል። 1 ቆሮንቶስ 6:9–11ን ተመልከት።)
መጽሐፍ ቅዱስ ያለ ሕጋዊ ጋብቻ እንደ ባልና ሚስት ሆኖ አብሮ መኖርን ይደግፋልን?
በገጽ 248, 249 ላይ “ጋብቻ” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶም ምን ይናገራል?
ሮሜ 1:24–27:- “ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኩስነት አሳልፎ ሰጣቸው፤. . . ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ።”
1 ጢሞ. 1:9–11 የ1980 ትርጉም:- “ሕግ የተሠራው ለደጋግ [“ለጻድቃን” አዓት ] እንዳልሆነ እናውቃለን፤ ሕግ የተሠራው ለዐመፀኞችና ለወንጀለኞች፣ ለከሃዲዎችና ለኃጢአተኞች . . . ለአመንዝሮችና ግብረ ሥጋን ከወንዶች ጋር ለሚያደርጉ ወንዶች . . . የእውነተኛ ትምህርት ተቃራኒ የሆነውን ነገር ሁሉ ለሚያደርጉ ነው። ይህ . . . የሚገኘውም የተመሰገነውን [“የደስተኛውን” አዓት ] የእግዚአብሔርን ክብር ከሚያበሥረው ወንጌል ነው።” (ከዘሌዋውያን 20:13 ጋር አወዳድር።)
ይሁዳ 7:- “እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል።” (“ሰዶማዊነት” የሚለው ቃል ራሱ የተገኘው ከሰዶም ነው። ይህም ወንድ ከወንድ ጋር የሚፈጸም አስነዋሪ ግንኙነት ነው። ከዘፍጥረት 19:4, 5, 24, 25 ጋር አወዳድር።)
እውነተኛ ክርስቲያኖች ግብረ ሰዶም ይፈጽሙ ስለነበሩ ሰዎች ምን አመለካከት አላቸው?
1 ቆሮ. 6:9–11:- “ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል።” (እንዲህ ያለውን ተግባር ይፈጽሙ የነበሩ ሰዎች የቀድሞ ርኩስ ተግባራቸውን ትተው በይሖዋ የጽድቅ ሥርዓቶች ቢገዙና በክርስቶስ በኩል የሚገኘውን የኃጢአት ሥርየት ዝግጅት ቢያምኑበት በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም ሊያገኙ ይችላሉ። ራሳቸውን ካስተካከሉ በኋላ በክርስቶስ ጉባኤ ውስጥ ተቀባይነት ሊያገኙ ይችላሉ።)
እውነተኛ ክርስቲያኖች ሥር የሰደዱ የተሳሳቱ ፍላጎቶችን በዘር የተወረሱ ወይም በአካላዊና በአካባቢ ሁኔታዎች ምክንያት የመጡ ልማዶችም ጭምር ይሖዋን ለማስደሰት ከልባቸው በሚፈልጉ ሰዎች ሊሸነፉ እንደሚችሉ ያውቃሉ። አንዳንድ ሰዎች በተፈጥሯቸው የስሜት ግንፋሎት አለባቸው። ከዚህ በፊት ለቁጣቸው ምንም ዓይነት ገደብ አያደርጉ ኖረው ይሆናል። የአምላክን ፈቃድ ካወቁ፣ እርሱን የማስደሰት ፍላጎት ካደረባቸውና የመንፈሱን እርዳታ ካገኙ በኋላ ግን ራሳቸውን ለመግዛት ችለዋል። አንድ ሰው የአልኮል ሱስ ሊኖርበት ይችላል። ትክክለኛው የልብ ግፊት ከኖረው ግን ከመጠጥ ሊርቅና ከስካር ሊወገድ ይችላል። በተመሳሳይም አንድ ሰው ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች ሊሳብ ይችላል። የአምላክን ቃል ምክር ከተከተለ ግን ከግብረ ሰዶማዊ ድርጊቶች ንጹሕ ሆኖ ለመኖር ይችላል። (ኤፌሶን 4:17–24ን ተመልከት።) ይሖዋ መጥፎ ድርጊት ምንም ዓይነት ልዩነት አያመጣም እያልን በግዴለሽነት እንድንኖር አይፈቅድልንም። ክፉ ድርጊቶች የሚያስከትሉትን መዘዝ በደግነትና ጠንከር ባለ አነጋገር ያስጠነቅቃል። ‘አሮጌውን ሰው ከነሥራው አስወግደው አዲሱን ሰው ለመልበስ’ ለሚፈልጉ ሰዎች ብዙ እርዳታ ይሰጣቸዋል።—ቆላ. 3:9, 10
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት ያለው አቋም ዘመን ያለፈበትና አላስፈላጊ ገደብ የሚጭን ነውን?
1 ተሰ. 4:3–8:- “የእግዚአብሔር ፈቃድ . . . ከዝሙት እንድትርቁ [ነው።] . . . እንግዲህ የሚጥል ሰውን የጣለ አይደለም፣ መንፈስ ቅዱስን በእናንተ እንዲኖር የሰጠውን እግዚአብሔርን ነው እንጂ።” (መጽሐፍ ቅዱስ የፆታ ግንኙነት ስለማድረግ ያለው አመለካከት ጥንት ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የደነገጉት ተራ ትእዛዝ አይደለም። የሰው ልጅ ፈጣሪ ከሆነው አምላክ የመጣ ነው። ይህ ትእዛዝ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ በግልጽ ያመለክታል። በተጨማሪም ጠንካራ ቤተሰብና ከቤተሰብ ውጭ ጤናማና ደስተኛ ዝምድና ስለሚገኝበት መንገድ መምሪያ ይሰጣል። ይህን ምክር የሚከተሉ ሰዎች በጣም ከባድ ከሆነው የስሜት ቁስልና ከሥነ ምግባር ውጭ በሆኑ ድርጊቶች ምክንያት ከሚመጡ አስነዋሪ በሽታዎች ራሳቸውን ይጠብቃሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና ለማግኘትና አላስፈላጊ የሆኑ ብስጭቶች የሌሉበት ሕይወት መኖር ለሚፈልጉ ሁሉ የሚጠቅም ወቅታዊ ምክር ነው።)
አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-
‘ስለ ግብረ ሰዶም ያላችሁ አቋም ምንድን ነው?’
እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘የኛ አመለካከት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው አመለካከት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር የሰው ልጆች ፈጣሪ ያለውን አስተሳሰብ የሚገልጽልን ስለሆነ ከማንኛውም ሰብዓዊ አስተያየት እንደሚበልጥ አምናለሁ። (1 ቆሮ. 6:9–11) ክርስቲያኖች ከሆኑት ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ግብረ ሰዶም ይፈጽሙ የነበሩ እንደሆኑ ለማስተዋል ይችላሉ። ይሁን እንጂ ለአምላክ ፍቅር ስለነበራቸውና የመንፈሱን እርዳታ ስላገኙ ተለውጠዋል።’
ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘ግብረ ሰዶም መከልከል እንደማይገባው የሚሰማቸው ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን እንደማያምኑ አስተውያለሁ። እርስዎ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?’ ሰውዬው በመጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያምን ከተናገረ እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችል ይሆናል:- ‘ግብረ ሰዶም አዲስ የተፈጠረ ነገር አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ የማይለወጠውን የይሖዋ አምላክን አመለካከት ግልጽ በሆኑ ቃላት ይገልጻል። ( በገጽ 367, 368 ላይ የቀረበውን ሐሳብ መጠቀም ይቻላል።)’ ሰውዬው አምላክ ስለመኖሩም ሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥርጣሬ እንዳለው ከተናገረ እንዲህ በማለት መቀጠል ትችላለህ:- ‘አምላክ ከሌለ በአምላክ ዘንድ ተጠያቂነት ሊኖርብን ስለማይችል እንደፈለገን መኖር እንችላለን። ስለዚህም እዚህ ላይ የሚነሡት ዋና ዋናዎቹ ጥያቄዎች አምላክ አለ? ሕይወቴንስ ያገኘሁት ከእርሱ ነው? የሚሉ ናቸው። [በተጨማሪም ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ ነውን? የሚለው ነው።] (በገጽ 146–152 ወይም 56–67 የቀረበውን ሐሳብ ተጠቀም።)’