በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ

ይሖዋ

ፍቺ:- ብቻውን እውነተኛ የሆነው አምላክ የግል መጠሪያ ስም ነው። ይሖዋ ራሱ ለራሱ ያወጣው ስም ነው። ይሖዋ ፈጣሪና ትክክለኛው የጽንፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ ነው። “ይሖዋ” የሚለው ስም ዮድ ሔ ዋው ሔ (יהוה) ከተባሉት አራት የዕብራይስጥ ፊደላት (ቴትራግራማተን) የተተረጐመ ሲሆን ትርጉሙም “እንዲሆን የሚያደርግ” ማለት ነው። እነዚህ አራት የዕብራይስጥ ፊደላት በብዙ ቋንቋዎች JHVH ወይም YHWH (የ–ሐ–ወ–ሐ) በሚሉት ተነባቢ ፊደላት ተጽፈው ይገኛሉ።

ዛሬ በብዙ ቦታዎች በሚሠራባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ የአምላክ ስም የት ላይ ይገኛል?

በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ በ1879 እትም ውስጥ በ⁠ዘጸአት 6:3 ላይ ይገኛል (“ይሖዋ” ተብሏል።) በ1954 ትርጉም ውስጥ በ⁠ዘፍጥረት 22:14 እና በ⁠ዘጸአት 17:15 ላይ ይገኛል (“ያህዌህ” ተብሏል።) በ1980 ትርጉም ውስጥም በቃላት መፍቻው ላይ (“ይሖዋ” ተብሎ) ይገኛል።

ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል:- ይሖዋ የሚለው ስም በ⁠ዘጸአት 3:15፤ 6:3 ላይ ይገኛል። በተጨማሪ ዘፍጥረት 22:14፣ ዘጸአት 17:15፤ መሳፍንት 6:24፤ ሕዝቅኤል 48:35⁠ን ተመልከት። (ይሁን እንጂ ይህም ሆነ ሌሎች ትርጉሞች ብዙ ቦታዎች ላይ “ጅሆቫ” (“ይሖዋ”) በሚለው ስም የሚጠቀሙ ከሆነ በዕብራይስጥ ጽሑፎች ውስጥ ቴትራግራማተን በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ያላስገቡት ለምንድን ነው?)

ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ቨርሽን:- የ⁠ዘጸአት 3:15 የግርጌ ማስታወሻ እንዲህ ይላል:- “LORD (ጌታ) የሚለው ቃል በካፒታል ሌተርስ ሲጻፍ መለኮታዊውን ስም YHWH [የ–ሐ–ወ–ሐ]ን ያመለክታል።”

ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን:- በ⁠ዘጸአት 6:3 ላይ የቀረበው የግርጌ ማስታወሻ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “ጌታ (THE LORD):- . . . የዕብራይስጡ ጽሑፍ ያህዌህ (አብዛኛውን ጊዜ ጅሆቫ ተብሎ የሚተረጎመው) በሚልበት ቦታ ሁሉ ብዙዎቹ የእንግሊዘኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የሚጠቀሙበትን አሠራር በመከተል በካፒታል ሌተርስ በተጻፈ LORD (ጌታ) የሚል ቃል ተተክቷል።”

ኪንግ ጄምስ ቨርሽን:- ጅሆቫ የሚለው ስም በ⁠ዘጸአት 6:3፤ መዝሙር 83:18፤ ኢሳይያስ 12:2፤ 26:4 ላይ ይገኛል። በተጨማሪ ዘፍጥረት 22:14፤ ዘጸአት 17:15፤ መሳፍንት 6:24⁠ን ተመልከት።

አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርሽን:- በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ጅሆቫ የሚለው ስም በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከ⁠ዘፍጥረት 2:4 ጀምሮ ስሙ በሚገኝባቸው ቦታዎች በሙሉ ተጠቅሷል።

ዱዌይ ቨርሽን:- ዘጸአት 6:3⁠ን በተመለከተ የቀረበው አንድ የግርጌ ማስታወሻ እንዲህ ይላል:- “ስሜ አዶናይ ነው። በዕብራይስጡ ጽሑፎች ውስጥ የአምላክ ትክክለኛ መጠሪያ ስም ዘላለማዊና በራሱ ሕያው ሆኖ የሚኖር መሆኑን የሚያመለክተው፣ (ዘጸ. 3:14) አይሁዳውያን ከአክብሮት የተነሣ ፈጽሞ የማይጠሩት፣ ከዚህ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሙ ከሚገኝበት ቦታ ላይ ሲደርሱ ጌታ መሆኑን በሚያመለክተው በአዶናይ የለወጡት ነው። ስለዚህም ጆድ፣ ሔ፣ ቫው፣ ሔ በተባሉት አራት ፊደላት በሚወከለው በሰው አፍ ሊጠራ የማይገባ ስም ምትክ አዶናይ የሚለውን ስም አናባቢዎች አስገብተዋል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ዘመናውያን በጥንቶቹ አይሁዳውያንም ሆነ ክርስቲያኖች ፈጽሞ የማይታወቀውን ጅሆቫ የተባለ ስም ፈጥረዋል። በዕብራይስጡ ጽሑፍ ውስጥ የሚገኘው ስም ትክክለኛ አጠራር ለብዙ ዘመናት ከአገልግሎት ውጭ ሆኖ ስለኖረ በአሁኑ ጊዜ ፈጽሞ ጠፍቷል።” (ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ [1913፣ ጥራዝ 8፣ ገጽ 329]:- “ጅሆቫ፣ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የአምላክ የግል መጠሪያ ስም ነው፤ ስለዚህም አይሁዳውያን ስሙን ከሁሉ የበለጠ፣ ታላቅ ስም፣ አቻ የማይገኝለት ስም ብለው ይጠሩት ነበር” በማለት ገልጿል።)

በሮናልድ ኤ ኖክስ በተተረጐመው ዘ ሆሊ ባይብል ላይ ያህዌህ የሚለው ስም በ⁠ዘጸአት 3:14 እና 6:3 የግርጌ ማስታወሻ ላይ ይገኛል።

ዘ ኒው አሜሪካን ባይብል:- የ⁠ዘጸአት 3:14 የግርጌ ማስታወሻ “ያህዌህ” የሚለውን ስም እንደሚመርጥ ቢናገርም ይህ ስም በትርጉሙ ዋና ክፍል ውስጥ አይገኝም። በተጨማሪ በቅዱስ ጆሴፍ እትም “ጌታ” እና “ያህዌህ” በሚሉት ቃላት ሥር የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት መግለጫ የሚለውን ተመልከት።

ዘ ጀሩሳሌም ባይብል:- ቴትራግራማተን ለመጀመሪያ ጊዜ ከሚገኙበት ከ⁠ዘፍጥረት 2:4 ጀምሮ ያህዌህ እያለ ተርጉሞታል።

የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም:- ይህ ትርጉም ጅሆቫ የሚለውን ስም በዕብራይስጥና በግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ 7,210 ጊዜ ተጠቅሞበታል።

አን አሜሪካን ትራንስሌሽን:- በ⁠ዘጸአት 3:15 እና 6:3 ላይ ያህዌህ የሚለውን ስም ከተጠቀመ በኋላ በቅንፍ ውስጥ “ጌታ” (THE LORD) ይላል።

በኤስ ቲ ባይንግተን የተተረጐመው ዘ ባይብል ኢን ሊቪንግ ኢንግሊሽ:- በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሙሉ ጅሆቫ በሚለው ስም ተጠቅሟል።

በጄ ኤን ዴርቢ የተተረጐመው ሆሊ ስክሪፕቸርስ ’:- ጅሆቫ የሚለው ስም በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሙሉ ይገኛል። እንዲሁም በግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከማቴዎስ 1:20 ጀምሮ በብዙ የግርጌ ማስታወሻዎች ላይ ይገኛል።

የቤንጃሚን ዊልሰን ዘ ኤምፋቲክ ዳይግሎት:- ጅሆቫ የሚለው ስም በዚህ የግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ውስጥ በ⁠ማቴዎስ 21:9 ላይ እንዲሁም በሌሎች 17 ቦታዎች ላይ ይገኛል።

ዘ ሆሊ ስክሪፕቸርስ አኮርዲንግ ቱ ዘ ማሶሬቲክ ቴክስትኤ ኒው ትራንስሌሽን በአሜሪካ የአይሁዳውያን የኅትመት ማኅበር፣ ዋና አዘጋጅ ማክስ ማርጐሊስ በእንግሊዝኛ በተተረጐመው ጽሑፍ ውስጥ ቴትራግራማተን በ⁠ዘጸአት 6:3 ላይ ይገኛሉ።

በሮበርት ያንግ የተተረጐመው ዘ ሆሊ ባይብል:- በዚህ ቃል በቃል በተተረጐመው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ውስጥ ጅሆቫ የሚለው ስም በሁሉም ቦታዎች ላይ ይገኛል።

ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በአምላክ የግል ስም የማይጠቀሙት ወይም በጥቂት ቦታዎች ላይ ብቻ የሚያስገቡት ለምንድን ነው?

ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ቨርሽን በመቅድሙ ላይ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “ኮሚቴው በሁለት ምክንያቶች የተነሣ ወደተለመደው የኪንግ ጄምስ ቨርሽን አጠቃቀም ተመልሷል:- (1) ‘ጅሆቫ’ የሚለው ቃል እስከ ዛሬ በዕብራይስጥ ቋንቋ የተሠራበትን ስም በምንም መልኩ በትክክል ስለማይወክልና (2) አንዱና ብቸኛ ከሆነው አምላክ መለየት የሚኖርባቸው ሌሎች አምላኮች ያሉ ይመስል እርሱን በተፀውኦ ስም መጥራት ከክርስትና ዘመን በፊት በአይሁዳውያን ሃይማኖት ውስጥ የቀረ ነገር ስለሆነ ለዓለም አቀፉ የክርስትና እምነትም አምላክን በተፀውኦ ስም መጥራት ተገቢ ስለማይሆን ነው።” (እነርሱ ትክክለኛ የመሰላቸውን አመለካከት መሠረት በማድረግ ከማንኛውም ስም ወይም ማዕረግ የበለጠ ብዙ ጊዜ በዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፍ ውስጥ የተጠቀሰውን የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነውን አምላክ የግል ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አውጥተውታል። በዚህ አድራጎታቸው የተከተሉት ኢየሱስ “ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ” በማለት የተናገራቸውን የአይሁድ ሃይማኖት ተከታዮች ምሳሌ መሆኑንም ራሳቸው ተናግረዋል።—ማቴ. 15:6)

የዕብራይስጡን ጽሑፍ ያህል ብዙ ጊዜ ባይሆንም ቢያንስ አንድ ወይም ጥቂት ጊዜ በዋናው ጽሑፍ ውስጥ የአምላክን የግል ስም ለማስገባት ግዴታ እንዳለባቸው የተሰማቸው ተርጓሚዎች በ1530 በታተሙት ፔንታቱች (ከዘፍጥረት እስከ ዘዳግም) የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ መለኮታዊውን ስም በመጨመር ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ የአምላክን ስም ጨርሶ የማስወጣትን ልማድ ያፈረሰውን የዊልያም ታይንደልን ምሳሌ እንደተከተሉ ግልጽ ነው።

የግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎችን በመንፈስ አነሣሽነት የጻፉት ጸሐፊዎች ይሖዋ በሚለው ስም ተጠቅመው ነበርን?

በአራተኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው ጀሮም አንዲህ ሲል ጽፏል:- “ማቴዎስ ተብሎ ይጠራ የነበረው ሌዊ ከቀራጭነት ወደ ሐዋርያነት የመጣ ሲሆን ለተገረዙት አማኞች ጥቅም ሲል በዕብራይስጥ ቋንቋና በዕብራይስጥ ፊደላት ስለ ክርስቶስ የሚገልጽ ወንጌል ጽፏል።” (ዲ ቪሪስ ኢንሉስትሪቡስ፣ ምዕራፍ 3) በዚህ ወንጌል ውስጥ ቴትራግራማተን ከሚገኝባቸው የዕብራውያን ቅዱሳን መጻሕፍት በቀጥታ የተወሰዱ 11 ጥቅሶች ይገኛሉ። ማቴዎስ እነዚህን ጥቅሶች በዕብራይስጡ ጽሑፎች ውስጥ ተጽፈው እንደሚገኙት አድርጎ በቀጥታ አልጠቀሳቸውም ብሎ ለማመን የሚያስደፍር ምንም ዓይነት ምክንያት የለም።

የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን በመንፈስ አነሣሽነት የጻፉ ሌሎች ጸሐፊዎችም ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክኛ ቋንቋ ከተተረጐመው የሴፕቱጀንት ትርጉም በመቶ የሚቆጠሩ ምንባቦችን ጠቅሰዋል። ከእነዚህ ምንባቦች ብዙዎቹ በጥንቱ የሴፕቱጀንት የግሪክኛ ጽሑፍ ቅጂ ውስጥ ቴትራግራማተንን አስገብተዋል። ኢየሱስ ለአባቱ ስም ከነበረው ዝንባሌ ጋር በመስማማት ደቀ መዛሙርቱ በእነዚያ ጥቅሶች ውስጥ ስሙ ተጠብቆ እንዲቆይ ማድረጋቸው የማይቀር ነው።—ከ⁠ዮሐንስ 17:6, 26 ጋር አወዳድር።

በጆርጂያ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ጆርጅ ሐዋርድ ዘ ጆርናል ኦቭ ባይብል ሊትረቸር በተባለው ጽሑፍ ላይ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ግሪክኛ ተናጋሪ የነበሩት አይሁዶች יהוה የሚሉትን በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ መጻፋቸውን እንደቀጠሉ ያለ ጥርጥር እናውቃለን። በተጨማሪ ወግ አጥባቂዎች የነበሩት ግሪክኛ ተናጋሪ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ከዚህ የተለየ ልማድ ነበራቸው ማለት የማይመስል ነገር ነው። ስለ አምላክ ለመናገር በፈለጉ ጊዜ [አምላክ] እና [ጌታ] በሚሉት ቃሎች በሁለተኛ ደረጃ ተጠቅመው ሊሆን ቢችልም ቴትራግራማተንን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ውስጥ አውጥተዋል ብሎ መገመት ፈጽሞ የማይታመን ነገር ነው። . . . የጥንቱ ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል በነበረው በግሪክኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቴትራግራማተን ይገኝ ስለነበር የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ከቅዱሳን መጻሕፍት በሚጠቅሱባቸው ጊዜያት ቴትራግራማተንን እንዳለ ጥቅሱ በሚገኝበት ቦታ ያስቀምጡት ነበር ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነው። . . . ቴትራግራማተንን ከግሪክኛው ብሉይ ኪዳን ባስወጡ ጊዜ ግን ከብሉይ ኪዳን ተወስደው በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከተጠቀሱት ጥቅሶችም እንዲጠፋ ተደርጓል። በሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ቴትራግራማተንን በሚተኩ ቃላት መጠቀም ሲጀመር ከሁለቱም ኪዳኖች ውስጥ ቃሉ ተገፍቶ ወጥቷል።”—ጥራዝ 96፣ ቁጥር 1፣ መጋቢት 1977፣ ገጽ 76, 77

መለኮታዊው ስም ትክክለኛ አጠራሩ የትኛው ነው—ይሖዋ ወይስ ያህዌህ?

የአምላክ ስም በመጀመሪያ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዴት ተብሎ ይጠራ እንደነበር በትክክል ሊያውቅ የሚችል ሰው ዛሬ የለም። ለምን? የመጽሐፍ ቅዱስ የዕብራይስጥ ቋንቋ በመጀመሪያ ጊዜ ይጻፍ የነበረው ያለ አናባቢ በተነባቢ ፊደላት ብቻ ነበር። ሰዎች በቋንቋው በየዕለቱ በሚጠቀሙበት ጊዜ ተገቢ አናባቢዎችን በቀላሉ ይጨምሩ ነበር። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ አይሁዶች የአምላክን የግል ስም ጮክ ብሎ መጥራት ስህተት ነው የሚል አጉል እምነት ያዙ። ስለዚህ በስሙ በመጠቀም ፈንታ የስሙ ምትክ የሆኑ ቃላትን መጠቀም ጀመሩ። በመቶ የሚቆጠሩ ዓመታት ካለፉ በኋላ አይሁዳውያን ምሁራን የጥንቱን ዕብራይስጥ ለማንበብ የትኞቹን አናባቢዎች የት ቦታ ላይ መጠቀም እንደሚቻል የሚያሳይ ዘዴ ፈጠሩ። ነገር ግን መለኮታዊውን ስም የሚወክሉት አራት ተነባቢ ፊደላት በሚገኙበት አካባቢ ሲደርሱ አናባቢዎቹን ለስሙ ምትክ ሆነው በገቡት ቃላት ላይ ጨመሯቸው። በዚህ መንገድ የመለኮታዊው ስም የመጀመሪያ አጠራር ጠፋ።

ብዙ ምሁራን “ያህዌህ” የሚለውን አጠራር ይደግፋሉ፤ ነገር ግን ይህም እርግጠኛ ባለመሆኑ በመካከላቸው ስምምነት የለም። በሌላ በኩል “ጅሆቫ” የሚለው ስም በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት በእንግሊዝኛ የተሠራበትና ከሌሎቹ ስሞች እኩል አራቱን የዕብራይስጥ ተነባቢ ፊደላት ያየዘ በመሆኑ በጣም የታወቀ ነው።

ጄ ቢ ሮዘርሃም ዘ ኤምፈሳይዝድ ባይብል በተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ያህዌህ የሚለውን ስም በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በሙሉ ተጠቅመውበታል። ይሁን እንጂ በኋላ ጊዜ ስተዲስ ኢን ዘ ሳምስ (የመዝሙራት ጥናት) በተባለው ጽሑፍ ውስጥ “ጅሆቫ” የሚለውን ስም ተጠቅመዋል። ምክንያቱንም ሲገልጹ:- “በእንግሊዝኛ JEHOVAH (ጅሆቫ) የሚለውን የመታሰቢያ ስም . . . በአሁኑ የመዝሙራት መጽሐፍ ትርጉም ውስጥ መጠቀም ያስፈለገው ያህዌህ የሚለው ስም በጣም ትክክለኛ አጠራር መሆኑን ከመጠራጠር የመነጨ ሳይሆን የተፈለገው ቁም ነገር መለኮታዊውን ስም በቀላሉ ለማወቅ መቻሉና ይህን በመሰለ ጉዳይ ከሕዝቡ ጆሮና ዓይን ጋር ለመገናኘት የሚያመች መሆኑ ስለሆነ ከተግባራዊ መረጃ በመነሣት የተደረገ የግል ምርጫ ነው።”—(ለንደን፣ 1911)፣ ገጽ 29

ጀርመናዊው ፕሮፌሰር ጉስታፍ ፍሬደሪክ ኧህለር ስለተለያዩት አጠራሮች ከገለጹ በኋላ እንዲህ በማለት ደምድመዋል:- “ከዚህ በኋላ ጅሆቫ የሚለውን አጠራር እጠቀማለሁ፤ ምክንያቱም አሁን ከመነጋገሪያ ቃሎቻችን አንዱ ስለሆነና መውጣትና መተካትም የማይችል ስለሆነ ነው።”—ቲዎሎጂ ዴ አልተን ቴስታመንትስ፣ ሁለተኛ እትም (ስቱትጋርት፣ 1882)፣ ገጽ 143

ኢየሱሳዊው ምሁር ፖል ዡዎን እንዲህ በማለት ገልጸዋል:- “በትርጉሞቻችን ውስጥ ያህዌህ ከሚለው (ግምታዊ) ስም ይልቅ ዤኦቫ በሚለው . . . በፈረንሳይኛ ሥነ ጽሑፍ የተለመደ አጠራር ተጠቅመናል።”—ግራሜር ደ ሌብሩ ቢቢሊክ (ሮም፣ 1923) የግርጌ ማስታወሻ ገጽ 49

ብዙ ስሞች በተለያዩ ቋንቋዎች በሚጠሩበት ጊዜ በአጠራራቸው ላይ መጠነኛ ለውጥ ይኖራል። ኢየሱስ አይሁዳዊ ስለነበር በዕብራይስጥ ቋንቋ የሚጠራው የሹዋ ተብሎ ሳይሆን አይቀርም። ይሁን እንጂ በመንፈስ አነሣሽነት የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎችን የጻፉት ጸሐፊዎች ኢየሱስ የሚለውን የግሪክኛ አጠራር ከመጠቀም ወደ ኋላ አላሉም። የስሙ አጠራር በሌሎች ቋንቋዎችም ትንሽ ይለያል፤ ይሁን እንጂ በቋንቋችን የተለመደውን አጠራር አለምንም ማመንታት እንጠቀማለን። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ስሞችንም ቢሆን በተመሳሳይ መንገድ ስንጠቀም ምንም ቅር አይለንም። እንግዲያውስ ከስሞች ሁሉ የበለጠ አስፈላጊ የሆነው ስም ባለቤት ለሆነው አምላክ ተገቢ አክብሮት ለማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ስሙ በመጀመሪያ እንዴት ተብሎ በትክክል ይጠራ እንደነበር ስለማይታወቅ ስሙን መጥራት ወይም መጻፍ አይገባንም በማለት ነው ወይስ እርሱን የምናመልክ እንደመሆናችን እርሱን በሚያስከብር መንገድ ራሳችንን እየመራን በቋንቋችን የተለመደውን አጠራርና ሆሄያት በመጠቀም?

የአምላክን የግል ስም ማወቅና መጠቀም ያስፈለገው ለምንድን ነው?

ስሙን የማታውቀው የቅርብ ጓደኛ አለህ? የአምላክን ስም የማያውቁ ሰዎች ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይደለም። እርሱን የሚመለከቱት የተወሰነ አካል እንደሆነ አድርገው ሳይሆን የተወሰነ አካል እንደሌለው ኃይል አድርገው ነው። ስም የለሽ አምላክ ለሚያመልኩ ሰዎች እርሱ እውን አካል ሳይሆን የማያውቁት፣ የማይወዱትና ከልባቸው በጸሎት የማያነጋግሩት የተወሰነ አካል የሌለው አንድ ኃይል ነው። ጸሎት ቢያቀርቡ እንኳ ጸሎታቸው ለተለምዶ ሥርዓት ወይም ለፎርማሊቲ ያህል ብቻ በቃል የሚደገም ጸሎት ይሆናል።

እውነተኛ ክርስቲያኖች ከአሕዛብ ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ኢየሱስ ክርስቶስ አዟቸዋል። እነዚህን ሰዎች በሚያስተምሩበት ጊዜ እውነተኛ አምላክ ከአሕዛብ የሐሰት አማልክት የተለየ መሆኑን የሚያሳውቁት እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው በአምላክ የግል ስም በመጠቀም ብቻ ነው።—ማቴ. 28:19, 20፤ 1 ቆሮ. 8:5, 6

ዘጸ. 3:15:- “እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] ደግሞ ሙሴን አለው:- ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ትላለህ:- የአባቶቻችሁ አምላክ፣ . . . እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ወደ እናንተ ላከኝ፤ ይህ ለዘላለሙ ስሜ ነው፣ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ይህ ነው።”

ኢሳ. 12:4:- “እግዚአብሔርን [“ይሖዋን” አዓት] አመስግኑ፣ ስሙንም ጥሩ፤ በአሕዛብ መካከል ሥራውን አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ያለ እንደሆነ ተናገሩ።”

ሕዝ. 38:17, 23:- “ጌታ እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] እንዲህ ይላል:- . . . ታላቅ እሆናለሁ እቀደስማለሁ በብዙ አሕዛብም ዓይን የታወቅሁ እሆናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] እንደ ሆንኩ ማወቅ ይኖርባቸዋል።”

ሚል. 3:16:- “እግዚአብሔርን [“ይሖዋን” አዓት] የሚፈሩ እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔርም [“ይሖዋም” አዓት] አደመጠ፣ ሰማም፣ እግዚአብሔርንም [“ይሖዋንም” አዓት] ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ።”—ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

ዮሐ. 17:26:- “[ኢየሱስ ወደ አባቱ እንዲህ በማለት ጸለየ:-] እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፣ ስምህን [ለተከታዮቼ] አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ።”

ሥራ 15:14 የ1980 ትርጉም:- “እግዚአብሔር በስሙ የሚጠራ ሕዝብን ለመምረጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አረማውያንን [“አሕዛብን” አዓት ] እንዴት እንደጐበኘ ስምዖን አስረድቶአል።”— ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

በ“ብሉይ ኪዳን” ውስጥ ይሖዋ የተባለው በ“አዲስ ኪዳን” ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ የተባለው ነውን?

ማቴ. 4:10:- “ኢየሱስ:- ሂድ፣ አንተ ሰይጣን፤ ለጌታህ [“ለይሖዋ” አዓት ] ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው።” (ኢየሱስ እርሱ ራሱ መመለክ እንዳለበት መናገሩ አልነበረም።)

ዮሐ. 8:54:- “ኢየሱስ [ለአይሁዳውያን] መለሰ አለም:- እኔ ራሴን ባከብር ክብሬ ከንቱ ነው፤ የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው።” (ይሖዋ አይሁዳውያን እናመልከዋለን የሚሉት አምላክ እንደሆነ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በግልጽ ያሳያሉ። ኢየሱስ የተናገረው እርሱ ራሱ ይሖዋ እንደሆነ ሳይሆን ይሖዋ አባቱ እንደሆነ ነው። እርሱና አባቱ የተለያዩ አካሎች እንደሆኑ ኢየሱስ በግልጽ ተናግሯል።)

መዝ. 110:1:- “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት ] ጌታዬን [ለዳዊት ጌታ]:- ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው።” (በዚህ መዝሙር ውስጥ የተጠቀሰው የዳዊት “ጌታ” ኢየሱስ መሆኑን እርሱ ራሱ በ⁠ማቴዎስ 22:41–45 ላይ ገልጿል። ስለዚህ ኢየሱስ ይሖዋ ራሱ ሳይሆን የይሖዋ ቃል የተነገረለት ነው።)

ፊልጵ. 2:9–11:- “በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር [ኢየሱስ ክርስቶስን] ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፣ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፣ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።” [ዱዌይ እንዲህ ይላል:- “ . . . ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር አብ ክብር እንዳለ ምላስ ሁሉ ያምን ዘንድ ነው።” ኖክስ እና ኮክ ተመሳሳይ ሐሳብ አላቸው። ይሁን እንጂ በኖክስ ውስጥ የሚገኝ አንድ የግርጌ ማስታወሻ እንዲህ ብሏል:- “የግሪክኛው አገላለጽ ምናልባት ‘ለእርሱ ክብር’ ተብሎ ሊተረጐም ይችላል።” ኒአባ እና ጀባ በዚሁ ዓይነት ተርጉመውታል።] (እዚህ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር አብ የተለየ እንደሆነና ለአምላክ እንደሚገዛ መገለጹን ልብ በል።)

አንድ ሰው ይሖዋን መፍራት ካለበት እንዴት ሊወደው ይችላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን መውደድና (ሉቃስ 10:27) መፍራት እንዳለብን ይናገራል። (1 ጴጥ. 2:17፤ ምሳሌ 1:7፤ 2:1–5፤ 16:6) ለአምላክ ያለን ጤናማ ፍርሃት እርሱን የሚያስከፋውን ከማድረግ እንድንጠነቀቅ ያደርገናል። ለይሖዋ ያለን ፍቅር እርሱን የሚያስደስቱትን ነገሮች ለመሥራትና ከመጠን በላይ ለሆነ ፍቅሩና የማይገባ ደግነቱ አድናቆታችንን እንድንገልጽ ይገፋፋናል።

ምሳሌ:- አንድ ልጅ አባቱን ላለማስከፋት ይፈራል። ይህ ተገቢ ቢሆንም አባቱ ላደረገለት ነገር ያለው አድናቆት እውነተኛ ፍቅሩንም እንዲገልጽለት ሊገፋፋው ይገባል። ውኃ ውስጥ ጠልቆ የሚዋኝ አንድ ዋናተኛ ባሕር እወዳለሁ ሊል ይችላል። ሆኖም ያለው ጤናማ ፍርሃት ሊጠነቀቅባቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮችም እንዳሉ እንዲያውቅ ያደርገዋል። በተመሳሳይ ለአምላክ ያለን ፍቅር እርሱን የማያስደስት ነገር እንዳንሠራ ከምናሳየው ጤናማ ፍርሃት ጋር አብሮ የሚሄድ መሆን ይኖርበታል።