ደም
ፍቺ:- በሰዎችና በአብዛኞቹ ባለብዙ ሴል እንስሶች የደም ሥር ውስጥ እየተዘዋወረ ምግብና ኦክስጅን ለሰውነት ክፍሎች የሚያደርስ፣ ቆሻሻን ከሰውነት ውስጥ የሚያስወግድ፣ ሰውነትን ከበሽታ በመከላከል ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወት አስደናቂ ፈሳሽ ነው። ደም ከሕይወት ጋር በጣም የተያያዘ ስለሆነ መጽሐፍ ቅዱስ “የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነው” ይላል። (ዘሌ. 17:11) ይሖዋ የሕይወት ምንጭ ስለሆነ ደም ለምን ጥቅም መዋል እንደሚገባው መመሪያ ሰጥቷል።
ክርስቲያኖች ‘ከደም እንዲርቁ’ ታዘዋል
ሥራ 15:28, 29:- “ለጣዖት ከተሠዋ፣ ከደምም፣ ከታነቀም [ደሙ ሳይፈስስ ከተገደለ፣] ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና [የክርስቲያን ጉባኤ የአስተዳደር አካልና] መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና፤ ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ።” (እዚህ ላይ ደም መብላት ልንፈጽማቸው ከማይገቡን ከጣዖት አምልኮና ከዝሙት ጋር እኩል ተደርጎ ተገልጿል።)
የእንስሳ ሥጋ ሊበላ ይችላል፣ ደሙ ግን አይበላም
ዘፍ. 9:3, 4:- “ሕይወት ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ መብል ይሁናችሁ፤ ሁሉን እንደ ለመለመ ቡቃያ ሰጠኋችሁ። ነገር ግን ነፍሱ ደሙ ያለችበትን ሥጋ አትብሉ።”
ለምግብ የሚሆን ማናቸውም እንስሳ በመጀመሪያ ደሙ በደንብ መፍሰስ ይኖርበታል። የታነቀ ወይም በወጥመድ ተይዞ የሞተ ወይም ሞቶ የተገኘ እንስሳ ለምግብነት አይሆንም። (ሥራ 15:19, 20፤ ከዘሌዋውያን 17:13–16 ጋር አወዳድር።) በተመሳሳይም ሙሉ በሙሉ ከደም የተሠራ ወይም ጥቂት ደም የተጨመረበት ማንኛውም ምግብ ሊበላ አይገባም።
አምላክ የፈቀደው ደም ለመሥዋዕትነት እንዲያገለግል ብቻ ነው
ዘሌ. 17:11, 12:- “የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ ደሙም ከሕይወቱ የተነሣ ያስተሰርያልና በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ እኔ ለእናንተ ሰጠሁት። ስለዚህ የእስራኤልን ልጆች:- ከእናንተ ማንም ደምን አይበላም፣ በመካከላችሁ ከሚኖሩ እንግዶች ማንም ደምን አይበላም አልሁ።” (በሙሴ ሕግ ሥር ይቀርቡ የነበሩት የእንስሳት መሥዋዕቶች ሁሉ ወደፊት የሚመጣው የኢየሱስ ክርስቶስን አንድ መሥዋዕትነት በትንቢታዊ ጥላነት ያመለክቱ ነበር።)
ዕብ. 9:11–14, 22:- “ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፣ . . . የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። የኮርማዎችና የፍየሎች ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ፣ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያዉን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን? . . . ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም።”
ኤፌ. 1:7:- “በውድ ልጁም፣ [በኢየሱስ ክርስቶስ] እንደ ፀጋው ባለ ጠግነት መጠን፣ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት።”
በመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናት እዘአ የነበሩት ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደም የሰጠውን ትእዛዝ እንዴት ተረድተውት ነበር?
ተርቱሊያን (ከ160–230 እዘአ ገደማ የኖረ) እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ከተፈጥሮ ውጭ የሆነው መንገዳችሁ በክርስቲያኖች ፊት ሊያሳፍራችሁ
ይገባ ነበር። እኛ በምግባችን ውስጥ የእንስሳትን ደም እንኳ አንጨምርም። . . . እናንተ ግን [አረማውያን የሮማ ዜጎች] ክርስቲያኖችን ለመፈተን ደም ያለበትን ምግብ ትሰጣላችሁ። ከትክክለኛው መንገድ እንዲወጡ የምታደርጉት ሙከራ በእነርሱ ዘንድ ፈጽሞ ሕገ ወጥ የሆነ ድርጊት እንደሆነ እናንተም አምናችኋል። የእንስሳትን ደም መብላት እንደሚዘገንናቸው እያወቃችሁ የሰውን ደም ተስገብግበው ይጠጣሉ ብላችሁ እንዴት ታስባላችሁ?”—ተርቱሊያን፣ አፖሎጀቲካል ወርክስ ኤንድ ሚኑሽየስ ፊሊክስ፣ ኦክታቪውስ (ኒው ዮርክ፣ 1950)፣ በኢሚሊ ዳሊ የተተረጐመ፣ ገጽ 33ሚኑሽየስ ፊሊክስ (በ3ኛው መቶ ዘመን እዘአ) እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ሥጋቸው የሚበሉትን እንስሳት ደም እንኳ በምግባችን ውስጥ ስለማንጨምር የሰው ደም ከመውሰድ በጣም እንርቃለን።”—ዘ አንቲ–ናይሲየን ፋዘርስ፣ (ግራንድ ራፒድስ፣ ሚችጋን፤ 1956)፣ በኤ ሮበርትስና ጄ ዳኖልድሰን የተዘጋጀ፣ ጥራዝ 4፣ ገጽ 192
በደም ሥር አማካይነት ደም መውሰድ
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደም የሰጠው ሕግ የሰውንም ደም ይጨምራልን?
አዎ ይጨምራል። ሥራ 15:29 ‘ከደም ራቁ’ ይላል። ከእንስሳ ደም ብቻ ራቁ አይልም። (“ማናቸውም ዓይነት ደም” እንዳይበላ ከሚከለክለው ከዘሌዋውያን 17:10 አዓት ጋር አወዳድር።)
በደም ሥር አማካይነት ደም መውሰድ ደምን ከመብላት ያልተለየ ነውን?
በሆስፒታል ውስጥ የተኛ አንድ በሽተኛ በአፉ ምግብ መውሰድ ካልቻለ በደም ሥሩ ምግብ እንዲያገኝ ይደረጋል። በአፉ ደም ጠጥቶ የማያውቅ ሰው በመርፌ አማካይነት ደም ቢወስድ ‘ከደም ራቁ’ የሚለውን ትእዛዝ አክብሯል ሊባል ይችላልን? (ሥራ 15:29) ለማነጻጸር ያህል ፈጽሞ አልኮል እንዳይወስድ የታዘዘን የአንድ ሰው ምሳሌ እንመልከት። በአፉ አልኮል መጠጣቱን አቁሞ በደም ሥሩ ቢወስድ የሐኪሙን ትእዛዝ አክብሯል ለማለት ይቻላልን?
ደም አልወስድም ለሚል በሽተኛ ሊሰጡ የሚችሉ ሌሎች አማራጭ የሕክምና ዘዴዎች አሉን?
የደም ክፍል የሆነውን የፕላዝማ መጠን ለመጨመር ብዙ ጊዜ ቀላል የሆኑ ሳላይን ሶሉሽን፣ ሪንገርስ ሶሉሽንና ዴክስትራን የተባሉትን መድኃኒቶች መጠቀም ይቻላል። እነዚህ ደግሞ በሁሉም ዘመናዊ ሆስፒታሎች ይገኛሉ ለማለት ያስደፍራል። እንዲያውም በእነዚህ መድሃኒቶች በመጠቀም የሰው ደም በመውሰድ የሚመጡትን አደጋዎች ማስቀረት ይቻላል። ካኔዲያን አንስቴሲስትስ ሶሳይቲ ጆርናል (የካናዳ አንስቴቲስቶች ማኅበር መጽሔት) (ጥር 1975፣ ገጽ 12) እንዲህ ይላል:- “የፕላዝማ ምትክ የሚሆኑ ፈሳሾችን መውሰድ የሌላውን ሰው ደም በመርፌ ከመውሰድ የሚመጣውን አደጋ ለማስቀረት ይጠቅማል። እነዚህ የፕላዝማን መጠን የሚጨምሩ ፈሳሾች በባክቴሪያና በቫይረስ የሚመጡትን በሽታዎች፣ የአንዱ ሰው ደም ከሌላው ሰው ጋር ሲደባለቅ የሚፈጠረውን ቀውስና የደም አለመስማማት ለማስቀረት ያገለግላሉ።” የይሖዋ ምሥክሮች የደም ተዋጽኦ ያልሆኑ ደምን የሚተኩ ፈሳሾችን እንዳይጠቀሙ የሚከለክል ሃይማኖታዊ ምክንያት የላቸውም።
የይሖዋ ምሥክሮች ደም ባለመውሰዳቸው ምክንያት የተሻለ ሕክምና ለማግኘት ችለዋል። አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ኦብስቴሪክስ ኤንድ ጋይናኮሎጂ በተባለ መጽሔት ላይ (ሰኔ 1፣ 1968፣ ገጽ 395) አንድ ዶክተር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “[የቀዶ ሕክምናው ዶክተር] ደም ሳይሰጥ ቀዶ ሕክምና በሚያደርግባቸው ቦታዎች ሁሉ የሰጠው ሕክምና የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ ጥርጥር የለውም። ደም እንዳይፈስ ከበፊቱ የበለጠ ይጠነቀቃል።”
ሁሉንም ዓይነት ቀዶ ሕክምናዎች ያለደም በተሳካ ሁኔታ ማከናወን ይቻላል። ይህም የልብ ቀዶ ሕክምናን፣ የአእምሮ ቀዶ ሕክምናን፣ እጆችንና እግሮችን ቆርጦ ማከምንና በካንሰር የተጠቃ የሰውነት ክፍልን ቆርጦ ማውጣትን ይጨምራል። በኒው ዮርክ ስቴት ጆርናል ኦቭ ሜዲስን (የኒው ዮርክ ክፍለ ሃገር የሕክምና መጽሔት) ላይ (ጥቅምት 15, 1972፣ ገጽ 2527) ዶክተር ፊሊፕ ሮን እንዲህ ብለው ጽፈዋል:- “በሽተኞች ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ የማይሆኑባቸው ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ሁሉ ማንኛውንም ዓይነት የቀዶ ሕክምና ከመፈጸም ወደኋላ አላልንም።” በቴክሳስ የልብ ሕክምና ኢንስቲትዩት የሚሠሩት ዶክተር ዴንተን ኮሊ እንዲህ ብለዋል:- “በይሖዋ ምሥክሮች ላይ [የደም ተዋጽኦ ባልሆኑ የደምን መጠን የሚጨምሩ መድኃኒቶች (ፕላዝማ ኤክስፓንደርስ) በመጠቀም] የታየው ውጤት በጣም ስላስደነቀን በሁሉም የልብ በሽተኞቻችን ላይ ይህን የሕክምና ዘዴ መጠቀም ጀምረናል።” (የሳንዲያጎ ዩኒየን መጽሔት፣ ታኅሣሥ 27, 1970፣ ገጽ ኤ–10) “‘ያለደም’ የልብ ቀዶ ሕክምና ማድረግ የተጀመረው ሃይማኖታቸው ደም መውሰድን በሚከለክላቸው በዕድሜ አዋቂ በሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ
ነበር። አሁን ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቀው የሕፃናትና የልጆች የልብ ቀዶ ሕክምና እንኳን ያላንዳች ችግር እየተከናወነ ነው።”—ካርዲዮቫስኩላር ኒውስ፣ የካቲት 1984፣ ገጽ 5አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-
‘ደም አንወስድም እያላችሁ ልጆቻችሁ እንዲሞቱ ታደርጋላችሁ። ይህ ጭካኔ ይመስለኛል’
እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘አደጋ የማያደርሱ ሌሎች በደም ሥር የሚሰጡ የሕክምና ዓይነቶችን እንዲወስዱ ግን እንፈቅዳለን። እንደ ኤድስ፣ ሄፓታይተስና ወባ የመሳሰሉትን በሽታዎች የማስተላለፍ አደጋ የሌለባቸውን በደም ሥር የሚሰጡ ሕክምናዎችን እንቀበላለን። ማንኛውም ልጁን የሚወድ ወላጅ እንደሚያደርገው ሁሉ እኛም ልጆቻችን ከሁሉ የተሻለ ሕክምና እንዲያገኙ እንፈልጋለን።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘አንድ ሰው ብዙ ደም ከፈሰሰው አንገብጋቢው ነገር በደም ሥር የሚዘዋወረውን ፈሳሽ መጠን መተካት ነው። እንደሚያውቁት ደማችን ከመቶ 50 እጅ በላይ የሚሆነው ውኃ ሲሆን ቀይና ነጭ የደም ሴሎች እንዲሁም ሌሎች ንጥረ ነገሮች ይገኙበታል። ብዙ ደም በሚፈስበት ወቅት ሰውነት ራሱ ለመጠባበቂያ ያስቀመጣቸውን የደም ሴሎች ወደ ደም ሥር በመጨመር አዲስ ሴሎች በአፋጣኝ እንዲፈጠሩ ያደርጋል። ሆኖም የፈሳሹን መጠን ዝቅ እንዳይል ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህም የደም ተዋጽኦ በማይጨመርበትና የፈሳሹን መጠን ከፍ በሚያደርገው ፕላዝማ ኤክስፓንደር መጠቀም ይቻላል። እኛም ይህን ዓይነት ሕክምና እንቀበላለን።’ (2) ‘የደምን ፈሳሽ መጠን ከፍ የሚያደርጉ ፕላዝማ ኤክስፓንደርስ በሺህ በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ተሞክረው እጅግ በጣም ጥሩ የሆኑ ውጤቶችን አስገኝተዋል።’ (3) ‘ለእኛ ከዚህም የበለጠ በጣም አስፈላጊ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በሥራ 15:28, 29 ላይ የሚናገረው ነው።’
ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘ሐሳብዎ ይገባኛል። የእርስዎ ልጅ በዚህ ሁኔታ ላይ ቢገኝ ምን እንደሚያደርጉ አስበው የተናገሩ መሰለኝ። ወላጆች እንደመሆናችን የልጆቻችንን ደህንነት ለመጠበቅ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፤ አይደለም እንዴ? ስለዚህ እንደ እርስዎና እንደ እኔ ያሉ ሰዎች ለልጆቻችን አንዳንድ የሕክምና ዓይነቶች እንዲደረጉላቸው አንፈቅድም የምንልበት በቂ የሆነ አስገዳጅ ምክንያት እንደሚኖረን አያጠራጥርም።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘የአምላክ ቃል በሥራ 15:28, 29 ላይ የሚናገረው ቃል የአንዳንድ ወላጆችን አስተሳሰብ የሚነካው አይመስልዎትም?’ (2) ‘እንግዲያው ጥያቄው የአምላክን ትእዛዞች ለማክበር የሚያስችለን በቂ እምነት አለን ወይ? የሚል ነው።’
‘ደም በመውሰድ አታምኑም’
እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ጋዜጦች የይሖዋ ምሥክሮች ደም አንወስድም በማለታቸው ሊሞቱ ነው የሚሉ ዜናዎችን አውጥተዋል። እርስዎም እንዲህ ያሉት ይህን በማስታወስ ይሆን? . . . እንዲህ ያለውን አቋም የያዝነው ለምንድን ነው?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘ሕይወትዎን አሳልፈው እስከሚሰጧቸው ድረስ ባለቤትዎን ይወዷቸዋል? . . . ሕይወታቸውን ለአገራቸው ሲሉ የሚሠዉ ሰዎችም አሉ፤ ጀግኖች ይባሉ የለም? ነገር ግን በዚህ ምድር ላይ ካለ ከማንኛውም ሰው ወይም ነገር የሚበልጥ አለ፤ እርሱም አምላክ ነው። ለእርሱ ባለዎት ፍቅር ወይም ለአገዛዙ ባለዎት ታማኝነት የተነሣ ሕይወትዎን አይሠዉም?’ (2) ‘በእርግጥ እዚህ ላይ የሚነሣው ጥያቄ ለአምላክ ታማኝ የመሆን ጉዳይ ነው። ከደም እንድንርቅ የሚያዘን የአምላክ ቃል ነው። (ሥራ 15:28, 29)’
ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች የማያደርጓቸው በሰዎች ግን የተለመዱ እንደ ውሸት፣ ምንዝር፣ ስርቆት፣ ሲጋራ ማጨስና እርስዎ እንደጠቀሱት ደም መውሰድ የመሳሰሉ ብዙ ነገሮች አሉ። ከነዚህ ነገሮች የምንርቀው ለምንድን ነው? ሕይወታችንን የምንመራው በአምላክ ቃል ስለሆነ ነው።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) “ከደም ራቁ’ ብሎ የሚያዘን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ያውቁ ነበርን? ባሳይዎት ደስ ይለኛል። (ሥራ 15:28, 29)’ (2) ‘አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን አዳምንና ሔዋንን ከአንዷ ዛፍ ፍሬ በስተቀር በገነት ከሚገኙት ዛፎች ሁሉ እንዲበሉ ነግሯቸው እንደነበረ ሳያስታውሱ አይቀሩም። እነርሱ ግን ሳይታዘዙ ቀርተው ከተከለከለው ፍሬ በመብላታቸው የነበራቸውን ነገር በሙሉ አጡ። እንዴት ያለ ሞኝነት ነበር! እርግጥ ዛሬ ከፍሬው እንዳይበላ የተከለከለ ዛፍ የለም። ይሁን እንጂ ከኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ በኋላ አምላክ የሰው ልጆች እንዳያደርጉ የከለከላቸው አንድ ነገር አለ። እርሱም ደም መውሰድ ነው። (ዘፍ. 9:3, 4)’ (3) ‘ስለዚህ እዚህ ላይ ጥያቄው በአምላክ ላይ እምነት አለን ወይ? የሚል ነው። እርሱን ብንታዘዘው በመንግሥቱ ውስጥ ፍጽምና ያለበት የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ይኖረናል። ብንሞትም እንኳ ትንሣኤ እንደሚኖረን አረጋግጦልናል።’
‘ዶክተር “ደም የማትወስድ ከሆነ ትሞታለህ” ቢልስ ምን ታደርጋላችሁ?’
እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ሁኔታው የዚያን ያህል አስጊ ከሆነ በሽተኛው ደም ቢሰጠው እንደማይሞትስ ዶክተሩ ዋስትና ሊሰጥ ይችላል?’ ዮሐ. 11:25)’
ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘ይሁን እንጂ መልሶ ሕይወት ሊሰጥ የሚችል አለ፣ እርሱም አምላክ ነው። ከሞት ጋር ፊት ለፊት በምንፋጠጥበት ጊዜ የአምላክን ሕግ በመጣስ ለአምላክ ጀርባችንን መስጠት ትክክለኛ ውሳኔ ይመስልዎታል? እኔ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት አለኝ። እርስዎስ? የአምላክ ቃል በልጁ የሚያምኑ ሁሉ ትንሣኤ እንዳላቸው ተስፋ ይሰጣል። ይህን ያምናሉ? (ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘እሱ ያለ ደም ቀዶ ሕክምና ማድረግ እንዴት እንደሚቻል አያውቅ ይሆናል። ከተቻለ በዚህ ረገድ ልምድ ካለው ዶክተር ጋር እንዲገናኝ ለማድረግ እንሞክራለን ወይም ሌላ ዶክተር እንዲያክመን እናደርጋለን።’