በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ድርጅት

ድርጅት

ፍቺ:- ጥረታቸውን ለአንድ የተወሰነ ሥራ ወይም ዓላማ ያስተባበሩ ሰዎችን ያቀፈ ማኅበር ነው። የአንድ ድርጅት አባሎች በአስተዳደራዊ መዋቅርና ድርጅቱ በሚያወጣው ደንብና ሥርዓት አማካኝነት አንድነታቸው ይጠበቃል። ራሳቸውን የወሰኑና የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ይሖዋ ድርጅት የሚገቡት በትውልድ ወይም በግዴታ ሳይሆን በራሳቸው ምርጫ ነው። ወደዚህም ድርጅት የሚመጡት በድርጅቱ ትምህርቶችና ተግባሮች ተስበው እንዲሁም ድርጅቱ በሚፈጽማቸው ሥራዎች ለመካፈል ስለሚፈልጉ ነው።

በእርግጥ ይሖዋ በዚህ ምድር ላይ ድርጅት አለውን?

ይህን ጥያቄ ለመመለስ የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት:-

የአምላክ ሰማያዊ ፍጥረታት የሆኑት መላእክት የተደራጁ ናቸውን?

ዳን. 7:9, 10:- “ዙፋኖች እስኪዘረጉ ድረስ አየሁ፣ በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ፣ የራሱም ጠጉር እንደጥሩ ጥጥ ነበረ፤ ዙፋኑም የእሳት ነበልባል ነበረ፤ መንኰራኩሮቹም የሚነድድ እሳት ነበሩ። የእሳትም ፈሳሽ ከፊቱ ይፈልቅና ይወጣ ነበር፤ ሺህ ጊዜ ሺህ ያገለግሉት ነበር፣ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር፤ ፍርድም ሆነ፣ መጻሕፍትም ተገለጡ።”

መዝ. 103:20, 21:- “ቃሉን የምትፈጽሙ፣ ብርቱዎችና ኃይላን፣ የቃሉንም ድምፅ የምትሰሙ መላእክቱ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ። ሠራዊቱ ሁሉ ፈቃዱን የምታደርጉ አገልጋዮቹ እግዚአብሔርን ባርኩ።” (‘ሠራዊት’ አንድ የተደራጀ ቡድን ነው።)

አምላክ በድሮ ጊዜ በምድር ላይ ለነበሩት አገልጋዮቹ መመሪያዎችን ያስተላልፍ የነበረው እንዴት ነው?

የይሖዋ አምላኪዎች ጥቂት በነበሩበት ዘመን ይሖዋ ራሱ እንደ ኖኅና እንደ አብርሃም ላሉት የቤተሰብ ራሶች መመሪያ ያስተላልፍ ነበር፤ ከዚያ እነርሱ ለቤተሰቦቻቸው እንደ ይሖዋ ቃል አቀባይ ሆነው ያገለግሉ ነበር። (ዘፍ. 7:1, 7፤ 12:1–5) ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብጽ ነፃ ባወጣ ጊዜ መመሪያ ይሰጥ የነበረው በሙሴ በኩል ነበር። (ዘጸ. 3:10) አምላክ በሲና ተራራ ሕዝቡን እንደ አንድ ብሔር አድርጎ አደራጀና በአምልኮታቸውና እርስ በርሳቸው ባላቸው ግንኙነት የሚመሩበትን ሕግና ድንብ ሰጣቸው። (ዘጸ. 24:12) በአምልኮ ጉዳዮች ሕዝቡን የሚመራና ስለ ይሖዋ ሥርዓቶች የሚያስተምር የክህነት ሥርዓት አቋቋመላቸው። አንዳንድ ጊዜም አስፈላጊ ማስጠንቀቂያዎችንና ማሳሰቢያዎችን ለሕዝቡ ለማሰማት ነቢያትን ያስነሣ ነበር። (ዘዳ. 33:8, 10፤ ኤር. 7:24, 25) ስለዚህ ይሖዋ የግለሰብ አምላኪዎችን ሁሉ ጸሎት ቢሰማም መመሪያ ይሰጥ የነበረው በድርጅት መልክ ነበር።

ይሖዋ እውነተኛ አምላኪዎቹን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከራሱ ጋር የሚያስተባብርበት ጊዜ ሲደርስ ኢየሱስን ቃል አቀባዩ አድርጎ ወደ ምድር ላከው። (ዕብ. 1:1, 2) ከዚያም በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስን በማፍሰስ የክርስቲያን ጉባኤን አቋቋመ። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ ይህ ጉባኤ ለግለሰብ ክርስቲያኖች መመሪያ ለመስጠትና የየግላቸውን ጥረት ለማስተባበር የሚያገለግል የይሖዋ ዝግጅት ሆነ። በየጉባኤዎቹ ውስጥ ለሥራው ግንባር ቀደም የሚሆኑ የበላይ ተመልካቾችና አስፈላጊ ውሳኔዎችን የሚያደርግና ሥራውን የሚያስተባብር ማዕከላዊ የአስተዳደር አካል ነበሩ። ይሖዋ በምድር ላይ በእውነተኛ ክርስቲያኖች የተቋቋመ ድርጅት እንዲኖር እንዳደረገ ግልጽ ነበር።—ሥራ 14:23፤ 16:4, 5፤ ገላ. 2:7–10

ይሖዋ የፈጠራቸው ግዑዛን ነገሮች እርሱ የድርጅት አምላክ መሆኑን ያመለክታሉን?

ኢሳ. 40:26:- “ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቁጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፣ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛት በችሎቱ ብርታት አንድ እንኳ አይታጣውም።” (የእያንዳንዱ ኮከብ ባሕርይ የተለያየ ቢሆንም የከዋክብት ረጨት (ጋላክሲ) በመፍጠር ሁሉም ቦታቸውን ጠብቀው ይንቀሳቀሳሉ። ሁሉም ከዋክብት ጊዜያቸውን ጠብቀው በተወሰነላቸው ምህዋር ይዞራሉ። በእያንዳንዱ ንጥረ ነገር ውስጥ የሚገኙት አቶሞችም ምህዋር አላቸው። የቁስ አካል ቅንብር ዝንፍ የማይል የሒሳብ ሥርዓት ስለሚከተል ሳይንቲስቶች አንዳንዶቹን ንጥረ ነገሮች ከማግኘታቸው አስቀድመው ስለ መኖራቸው ለመናገር ችለዋል። እነዚህ ሁሉ እጅግ በጣም ትልቅ ድርጅት እንዳለ በቂ ማስረጃ ናቸው።)

እውነተኛ ክርስቲያኖች የተደራጀ ሕዝብ እንደሚሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያልን?

ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . እያጠመቃችኋቸው፣ . . . እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።” (ያለ ድርጅት ይህ እንዴት ሊከናወን ይችላል? ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለዚህ ሥራ ባሰለጠናቸው ጊዜ እያንዳንዳቸው ወደፈለጉት እንዲሄዱና እምነታቸውን በመረጡት መንገድ እንዲናገሩ አላስተማራቸውም። ከዚህ ይልቅ አሰልጥኖና መመሪያ ሰጥቶ በድርጅት መልክ ልኳቸዋል። ሉቃስ 8:1፤ 9:1–6፤ 10:1–16⁠ን ተመልከት።)

ዕብ. 10:24, 25:- “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው መሰብሰባችንን አንተው፣ እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።” (ዘወትር ስብሰባ እንዲደረግ የሚያስተባብር ድርጅት ከሌለ ለመልእክቱ ፍላጎት ያሳዩት ሰዎች ይህን ትእዛዝ አክብረው ለመሰብሰብ ወዴት ሊሄዱ ይችላሉ?)

1 ቆሮ. 14:33, 40:- “እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤ . . . ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን።” (ሐዋርያው ጳውሎስ እዚህ ላይ የገለጸው በጉባኤ ስብሰባዎች መኖር የሚገባውን ሥነ ሥርዓታዊ አሠራር ነው። ይህንን በመንፈስ አነሣሽነት የተሰጠ ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ለድርጅታዊ አሠራር አክብሮት ማሳየት ያስፈልጋል።)

1 ጴጥ. 2:9, 17:- “እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጐነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ . . . ወንድሞችን ውደዱ [“ለመላው የወንድሞች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ።” አዓት ]” (አንድ የተወሰነ ሥራ ለማከናወን ሰዎች ጥረታቸውን የሚያስተባብሩበት ማኅበር ድርጅት ነው።)

የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች በተለያዩ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ተሰበጣጥረው የሚገኙ ግለሰቦች ናቸውን?

2 ቆሮ. 6:15–18:- “የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? . . . ስለዚህም ጌታ:- ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኩስንም አትንኩ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ:- እኔም እቀበላችኋለሁ፣ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል።” (አንድ ሰው አማኝ አለመሆናቸውን በኑሯቸው ከሚያሳዩ ሰዎች ጋር በአምልኮ ቢካፈል ያ ሰው በእውነት የአምላክ ታማኝ አገልጋይ ነው ሊባል ይቻላልን? “ታላቂቱ ባቢሎን” በሚለው ዋና ርዕስ ሥር ተመልከት።)

1 ቆሮ. 1:10:- “ወንድሞች ሆይ፣ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።” (እንዲህ የመሰለ አንድነት በተለያዩ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ አይገኝም።)

ዮሐ. 10:16:- “ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል፤ ድምፄንም ይሰማሉ፣ አንድም መንጋ ይሆናሉ፣ እረኛውም አንድ።” (ኢየሱስ እነዚህን ጭምር “አንድ መንጋ” ለማድረግ ስለሚያመጣቸው በሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ውስጥ ተሰበጣጥረው ሊገኙ እንደማይችሉ ግልጽ አይደለምን?)

የሚታየው የይሖዋ ድርጅት በዘመናችን እንዴት ተለይቶ ሊታወቅ ይችላል?

(1) ይሖዋ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ መሆኑን በመቀበል ከፍ ከፍ ያደርገዋል፤ ስሙንም ጐላ አድርጎ ያስታውቃል።—ማቴ. 4:10፤ ዮሐ. 17:3

(2) በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚጫወተውን ከፍተኛ ሚና፣ ማለትም የይሖዋን ሉዓላዊነት የሚያረጋግጥ፣ የሕይወት ማስገኛ፣ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ፣ የመሲሐዊት መንግሥት ንጉሥ መሆኑን ሙሉ በሙሉ ይቀበላል።—ራእይ 19:11–13፤ 12:10፤ ሥራ 5:31፤ ኤፌ. 1:22, 23

(3) በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል በጥብቅ ይከተላል፣ ትምህርቶቹና የሚከተላቸው የሥነ ምግባር አቋሞች የተመሠረቱት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነው።—2 ጢሞ. 3:16, 17

(4) ከዓለም ለየት ብሎ ይቆማል።—ያዕ. 1:27፤ 4:4

(5) ይሖዋ ራሱ ቅዱስ ስለሆነ በአባሎቹ ዘንድ ከፍ ያለ የሥነ ምግባር ንጽሕና እንዲኖር ያደርጋል።—1 ጴጥ. 1:15, 16፤ 1 ቆሮ. 5:9–13

(6) ዋና ትኩረቱ መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን ይከናወናል ብሎ አስቀድሞ የተናገረለት ሥራ ማለትም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለምሥክርነት በዓለም ሁሉ ላይ የመስበኩ ሥራ ነው።—ማቴ. 24:14

(7) ሰብዓዊ አለፍጽምና ቢኖርም የድርጅቱ አባሎች የአምላክ መንፈስ ፍሬዎች የሆኑትን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ የዋህነት፣ ራስን መግዛት እየኮተኮቱ በማፍራት ላይ ናቸው። እነዚህን ፍሬዎች ከዓለም በደንብ የተለዩ እስኪሆኑ ድረስ በከፍተኛ ደረጃ ያፈራሉ።—ገላ. 5:22, 23 አዓት፤ ዮሐ. 13:35

ለይሖዋ ድርጅት እንዴት አክብሮት ልናሳይ እንችላለን?

1 ቆሮ. 10:31:- “ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት።”

ዕብ. 13:17:- “ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፣ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፣ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፣ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ።”

ያዕ. 1:22:- “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ . . . ሰሚዎች ብቻ አትሁኑ።”

ቲቶ 2:11, 12:- “ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፣ . . . ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል።”

1 ጴጥ. 2:17 አዓት:- “ለመላው የወንድሞች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ።”