በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ገነት

ገነት

ፍቺ:- በግሪክኛው ሴፕቱጀንት (ሰባ ሊቃናት ) ትርጉም ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የኤደንን የአትክልት ስፍራ ለማመልከት “ገነት” በሚል ቃል (ፓራዴሶስ ) መጠቀማቸው ትክክል ነበር፤ ምክንያቱም ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው ይህ ቦታ የተከለለ የአትክልት ስፍራ ነበር። ከዘፍጥረት ዘገባ በኋላ የሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ገነት በሚሉበት ጊዜ የሚያመለክቱት (1) ራሱን ኤደን ገነት ወይም (2) ወደ ፊት ተለውጣ ኤደንን የምትመስለውን መላዋን ምድር ወይም (3) በምድር ላይ በሚኖሩ የአምላክ አገልጋዮች ዘንድ የሚኖረውን እየዳበረ የሚሄድ መንፈሳዊ ሁኔታ ወይም (4) በሰማይ ውስጥ ያለ ኤደንን የሚያስታውስ ዝግጅት ነው።

“አዲስ ኪዳን” ወደፊት ምድራዊት ገነት እንደምትቋቋም ይናገራል ወይስ ስለ ገነት የሚናገረው “ብሉይ ኪዳን” ብቻ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን በሁለት ከፍሎ አንድ ነገር በ“ብሉይ” ወይም በ“አዲስ” ውስጥ መገኘቱን መሠረት በማድረግ ዋጋማነቱን መመዘን ቅዱስ ጽሑፋዊ አይደለም። በ⁠2 ጢሞቴዎስ 3:16 ላይ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት . . . ይጠቅማል” ተብሎ ተገልጾልናል። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ሮሜ 15:4⁠ም “አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአል” በማለት ከክርስትና በፊት ስለነበሩት በመንፈስ የተጻፉ ቅዱሳን መጻሕፍት ይናገራል። ስለዚህ ለዚህ ጥያቄ የሚቀርብ ማንኛውም መልስ መላውን መጽሐፍ ቅዱስ ግምት ውስጥ የሚያስገባ መሆን ይኖርበታል።

ዘፍጥረት 2:8 እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር አምላክም ምሥራቅ በዔድን ገነትን [“የአትክልት ስፍራ” ሞፋት፤ “የአትክልት ቦታ” አዓት፣ የ1980 ትርጉም፤ “ገነት” (ፓራዳይዝ) ዱዌይ፤ ፓራዴሶን፣ ሰባ ] ተከለ የፈጠረውንም ሰው [አዳምን] ከዚያው አኖረው።” እዚያ በርካታና አስደናቂ የሆኑ የተለያዩ ዕፅዋትና እንስሳት ነበሩ። ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ባርኮ “ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው” አላቸው። (ዘፍ. 1:28) አምላክ መላዋ ምድር ሕጎቹን በአድናቆት በሚታዘዙ ሰዎች የምትሞላ ገነት እንድትሆን ለማድረግ የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ከንቱ ሆኖ አይቀርም። (ኢሳ. 45:18፤ 55:10, 11) ኢየሱስም “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፣ ምድርን ይወርሳሉና” ያለው በዚህ ምክንያት ነው። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) በተጨማሪም “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብላችሁ ጸልዩ በማለት ደቀ መዛሙርቱን ያስተማረው ለዚህ ነው። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ማቴ. 5:5፤ 6:9, 10) ኤፌሶን 1:9–11⁠ም ከዚህ ጋር በመስማማት የአምላክ ዓላማ ምን እንደሆነ ሲገልጽ “በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ [“እንደገና” አዓት ] በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው” ብሏል። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ዕብራውያን 2:5 (አዓት) “ሰው የሚኖርባት ወደፊት የምትመጣዋ ምድር ” እያለ ይናገራል። ራእይ 5:10⁠ም ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ወራሾች በመሆን ‘በምድር ላይ የሚነግሡ’ ነገሥታትን ይጠቅሳል። ራእይ 21:1–5 እና 22:1, 2 “በአዲሲቱ ምድር” ውስጥ ስለሚኖሩት አስደሳች ሁኔታዎች ይገልጻል። ይህ መግለጫ የሕይወት ዛፍ የነበረበትን የመጀመሪያውን የኤደን ገነት ያስታውሰናል።—ዘፍ. 2:9

በተጨማሪም ኢየሱስ ወደ ፊት ስለሚመጣው ምድራዊ ገነት በሚናገርበት ጊዜ ፓራዴሶስ በተባለው የግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል። “ለእርሱም [ከኢየሱስ ጋር ጐን ለጐን ተሰቅሎ ለነበረውና ወደፊት በምትመጣው የኢየሱስ መንግሥት ያለውን እምነት ለገለጸው ክፉ አድራጊ] እንዲህ አለው:- ‘እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ።’”—ሉቃስ 23:43 አዓት

ኢየሱስ በ⁠ሉቃስ 23:43 ላይ በሚገኘው ቃሉ ለክፉ አድራጊው ስለ ገነት ሲናገር ምን ማለቱ እንደነበረ እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን?

ይህ ስፍራ ‘ከሥጋ የተለዩ የጻድቃን ነፍሳት’ የሚኖሩበት ጊዜያዊ መኖሪያ የሆነ የሔድስ ክፍል ነውን?

ይህ ዓይነቱ አመለካከት ከየት የመጣ ነው? ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ቲኦሎጂ እንዲህ ይላል:- “ነፍስ አትሞትም የሚለው የግሪካውያን መሠረተ ትምህርት ሰርጐ ከገባ በኋላ ገነት ጻድቃን በመሸጋገሪያነት የሚኖሩበት ስፍራ ማለት ሆኗል።” (ግራንድ ራፒድስ፣ ሚቺጋን፤ 1976፣ በኮሊን ብራውን የተዘጋጀ፣ ጥራዝ 2፣ ገጽ 761) ይህን የመሰለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ አመለካከት በኢየሱስ ዘመን በነበሩት አይሁዳውያን ዘንድ የተስፋፋ ነበርን? የሔስቲንግስ ዲክሺነሪ ኦቭ ዘ ባይብል (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት) ይህ አጠራጣሪ እንደነበረ ያመለክታል።—(ኤድንበርግ፣ 1905)፣ ጥራዝ 3፣ ገጽ 669, 670

ይህ ዓይነቱ አመለካከት በመጀመሪያው መቶ ዘመን በአይሁዳውያን ዘንድ የተስፋፋ ቢሆንም እንኳን ኢየሱስ ንስሐ ለገባው ክፉ አድራጊ በሰጠው የተስፋ ቃል ላይ ይህን ዓይነቱን አመለካከት ደግፎ ይናገር ነበርን? የአይሁድ ፈሪሳውያንና ጸሐፊዎች ከአምላክ ጋር የሚቃረኑ ወጎችን በማስተማራቸው ምክንያት ኢየሱስ አጥብቆ አውግዟቸው ነበር።—ማቴ. 15:3–9፤ በተጨማሪም “ነፍስ” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት።

ኢየሱስ በሞተ ጊዜ በ⁠ሐዋርያት ሥራ 2:30, 31 ላይ እንደምንመለከተው ወደ ሲኦል በእርግጥ ሄዷል። (እዚህ ቦታ ላይ ሐዋርያው ጴጥሮስ መዝሙር 16:10⁠ን በመጥቀሱ ሔድስ የሲኦል አቻ መሆኑን አመልክቷል።) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ቦታ ላይ ሲኦልም ሆነ ሔድስ ወይም ማንኛውም የሲኦል ክፍል ደስታ የሚገኝበት ገነት እንደሆነ አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ መክብብ 9:5, 10 እንደሚለው በሲኦል ያሉ “አንዳች አያውቁም።”

በሉቃስ 23:43 ላይ የተጠቀሰው ገነት ሰማይ ወይም በሰማይ የሚገኝ አንድ ቦታ ነውን?

ኢየሱስና ክፉ አድራጊው ኢየሱስ ያን ቃል በተናገረበት ዕለት ወደ ሰማይ ሄደዋል የሚለውን አባባል መጽሐፍ ቅዱስ አይደግፍም። ኢየሱስ በሚገደልበት ጊዜ ከሦስተኛው ቀን በፊት ከሞት የማይነሣ መሆኑን ከመሞቱ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ሉቃስ 9:22) በዚህ ሦስት ቀን ወቅት በሰማይ አልነበረም፤ ምክንያቱም ከሙታን እንደተነሣ ለመግደላዊት ማርያም “ወደ አባቴ አላረግሁም” ብሏታል። (ዮሐ. 20:17) ኢየሱስ ከምድር ከፍ ከፍ ብሎ ወደ ሰማይ ሲያርግ ደቀ መዛሙርቱ የተመለከቱት ከሙታን ከተነሣ ከ40 ቀን በኋላ ነበር።—ሥራ 1:3, 6–11

ይህ ክፉ አድራጊ ወደ ሰማይ ለመሄድ የሚያስፈልገውን ብቃት በኋላ ጊዜም ቢሆን አላሟላም። በውኃ ስላልተጠመቀና ከአምላክ መንፈስም ስላልተወለደ ዳግም ልደት አላገኘም ነበር። መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ የፈሰሰው ይህ ክፉ አድራጊ ከሞተ ከ50 ቀናት በኋላ ነው። (ዮሐ. 3:3, 5፤ ሥራ 2:1–4) ኢየሱስ በሞተበት ዕለት ከእርሱ ጋር በፈተናዎቹ ከጸኑት ጋር የሰማይ መንግሥት እንደሚወርሱ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል። ክፉ አድራጊው ግን ይህን የመሰለ የታማኝነት አቋም ስላላስመዘገበ በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ አልገባም።—ሉቃስ 22:28–30

ይህ ገነት ምድራዊ መሆኑን የሚያመለክተን ምንድን ነው?

የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ታማኝ አይሁዳውያን የሰማያዊ ሕይወት ሽልማት የማግኘት ተስፋ እንደሚኖራቸው አያመለክቱም። እነዚህ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚጠቁሙት በምድር ላይ ተመልሳ የምትቋቋመውን ገነት ነበር። ዳንኤል 7:13, 14 “ግዛትና ክብር መንግሥትም” ለመሲሑ በሚሰጥበት ጊዜ ‘ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ እንደሚያገለግሉት’ ተንብዮአል። እነዚህ የመንግሥቱ ተገዢዎች የሚኖሩት በዚሁ ምድር ላይ ነው። ክፉ አድራጊውም ለኢየሱስ በተናገረው ቃል ይህ ጊዜ ሲመጣ ኢየሱስ እንደሚያስታውሰው ያለውን ተስፋ መግለጹ ነበር።

ታዲያ ኢየሱስ ከክፉ አድራጊው ጋር የሚሆነው እንዴት ነው? እሱን ከሙታን በማስነሣት፣ ሥጋዊ ፍላጎቶቹ የሚሟሉበትን ዝግጅት በማድረግና ይሖዋ ለዘላለም ሕይወት ያወጣውን ብቃት የሚያውቅበትንና ከብቃቶቹም ጋር የሚስማማበትን አጋጣሚ በመስጠት ነው። (ዮሐ. 5:28, 29) ኢየሱስ ክፉ አድራጊው ንስሐ የመግባትና የአክብሮት ዝንባሌ እንዳለው ስለተመለከተ ከሙታን ተነሥቶ በምድር ላይ የመኖር እና ለዘላለምም በገነት ለመኖር የሚበቁ መሆናቸውን የማረጋገጥ አጋጣሚ ከሚያገኙት በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል እንዲሆን ያደርጋል።

ክፉ አድራጊው በገነት ውስጥ የሚሆነው መቼ ነው?

ለ⁠ሉቃስ 23:43 የተለየ ትርጉም ለመስጠት ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ ተርጓሚዎች የተጠቀሙበት የሥርዓተ ነጥብ አቀማመጥ ነው። በጥንቱ የግሪክኛ መጽሐፍ ቅዱስ በኩረ ጽሑፍ ውስጥ ሥርዓተ ነጥብ አልነበረም። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና (1956፣ ጥራዝ 23፣ ገጽ 16) እንዲህ ይላል:- “በጥንቶቹ የግሪክኛ የብራናና ሌሎች ጽሑፎች ውስጥ ዓረፍተ ነገሮችን የሚለዩ ሥርዓተ ነጥቦች ለማድረግ የተደረገ ሙከራ አልነበረም።” በሥርዓተ ነጥቦች መጠቀም የተጀመረው ከ9ኛው መቶ ዘመን እዘአ በኋላ ነው። ሉቃስ 23:43 መነበብ የሚኖርበት “እውነት እልሃለሁ፣ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ተብሎ ነው ወይስ ‘እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ’ ተብሎ? የዚህን ጥቅስ ትርጉም መወሰን የሚኖርበት ኢየሱስ እነዚህን ቃላት ከተናገረ ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ የገባ ነጠላ ሰረዝ ሳይሆን የክርስቶስ ትምህርትና የቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መሆን ይኖርበታል።

በጄ ቢ ሮዘርሃም የተተረጐመው ዘ ኤምፈሳይዝድ ባይብል የሥርዓተ ነጥቡ አቀማመጥ ከአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ጋር ይስማማል። ጀርመናዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ ኤል ራይንሐርት በ⁠ሉቃስ 23:43 የግርጌ ማስታወሻ ላይ እንዲህ ብለዋል:- “በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹ ተርጓሚዎች በ⁠ሉቃስ 23:43 ላይ የሚጠቀሙበት ሥርዓተ ነጥብ ሐሰት እና ከክርስቶስና ከክፉ አድራጊው አስተሳሰብ የሚቃረን እንደሆነ አያጠራጥርም። . . . [ክርስቶስ] ገነትን የሚያውቀው የሙታን መኖሪያ አነስተኛ ክፍል እንደሆነ አድርጎ አልነበረም። እሱ የተናገረው በምድር ላይ እንደገና ስለምትቋቋመው ገነት ነው።”

ታዲያ ኢየሱስ ‘በመንግሥቱ የሚመጣውና’ አባቱ ምድርን ገነት ለማድረግ ያወጣውን ዓላማ የሚፈጽመው መቼ ነው? በ⁠ሉቃስ 23:42, 43 ላይ የሚገኘው መግለጫ ከተነገረ ከ63 ዓመታት በኋላ የተጻፈው የራእይ መጽሐፍ እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት ገና ወደ ፊት እንደሆነ ያመለክታል። (በገጽ 94–97 ላይ “የዘመናት ስሌት” እና “የመጨረሻ ቀኖች” በሚሉት ዋና ርዕሶች ሥር ተመልከት።)