በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥምቀት

ጥምቀት

ፍቺ:- “ማጥመቅ” የሚል ትርጉም ያለው “ባፕታይዝ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ባፕቲዜን ከሚለው የግሪክኛ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም “መንከር፣ ማጥለቅ” ማለት ነው። (ግሪክ–ኢንግሊሽ ሌክሲከን (ግሪክኛ–እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት) በሊዴልና ስኮት የተዘጋጀ ) የክርስቲያን የውኃ ጥምቀት የሚያመለክተው ተጠማቂው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የይሖዋ አምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ፍጹም የሆነ፣ ያልተቆጠበና ገደብ የሌለው ውሳኔ ማድረጉን ለሌሎች የሚያሳይበት ውጫዊ ድርጊት ነው። በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎች ከሚጠቅሷቸው የተለያዩ ጥምቀቶች መካከል የዮሐንስ ጥምቀት፣ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና የእሳት ጥምቀት ይገኙባቸዋል።

የአምላክን ቃል በትክክል የሚያምኑ ሰዎች ከመጠመቅ ወደ ኋላ ማለት ይገባቸዋልን?

ማቴ. 28:19, 20:- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”

ሥራ 2:41:- “ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ።”

ሥራ 8:12:- “ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እየሰበከላቸው ፊልጶስን ባመኑት ጊዜ፣ ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ።”

ሥራ 8:36–38:- “በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ [ኢትዮጵያዊ] ጃንደረባውም:- እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው። ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፣ . . . [ፊልጶስም] አጠመቀው።”

የክርስቲያን የውኃ ጥምቀት የሚከናወነው ውኃ በመርጨት ነው ወይስ ሙሉ በሙሉ በውኃ ውስጥ በመንከር?

ማር. 1:9, 10 የ1980 ትርጉም:- “ኢየሱስ . . . በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ። [“ሙሉ በሙሉ በውኃ ውስጥ ተነክሮ ተጠመቀ።” ኤዳ፣ ሮዘ ] ከውሃው እንደወጣ ወዲያውኑ ሰማይ ሲከፈት [አየ።]”— ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

ሥራ 8:38:- “ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፣ አጠመቀውም።” [“ሙሉ በሙሉ በውኃ ውስጥ ነከረው።” ኤዳ፣ ሮዘ]—ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሕፃናትን ያጠምቁ ነበርን?

ማቴ. 28:19:- “እንግዲህ ሂዱና . . . እያጠመቃችኋቸው . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”— ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

ሥራ 8:12:- “ፊልጶስን ባመኑት ጊዜ፣ ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ።”— ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

ከጊዜ በኋላ ግን ኦሪገን (185–254 እዘአ የኖረ) “ሕፃናትንም ቢሆን ማጥመቅ የቤተ ክርስቲያን ልማድ ነው” በማለት ጽፏል። (ሴሌክሽንስ ፍሮም ዘ ኮሜንታሪስ ኤንድ ሆሚሊስ ኦቭ ኦሪገን (ኦሪገን ካዘጋጃቸው ማብራሪያዎችና ድርሳኖች የተመረጡ)፣ ማድራስ፣ ሕንድ፤ 1929፣ ገጽ 211) ሕፃናትን የማጥመቁ ልማድ በካርቴጅ ጉባኤ (252 እዘአ) ላይ ጸደቀ።

የሃይማኖት ታሪክ ምሁር የነበሩት አውጉስተስ ኒያንደር እንዲህ ብለው ጽፈዋል:- “እምነትና ጥምቀት አንዳቸው ከሌላው የማይነጣጠሉ ነበሩ። [በአንደኛው መቶ ዘመን] የሕፃናት ጥምቀት ፈጽሞ የማይታወቅ መሆኑ . . . የተረጋገጠ ነው። . . . የሕፃናት ጥምቀት ለመጀመሪያ ጊዜ ሐዋርያዊ ልማድ ተብሎ ተቀባይነት ያገኘው በሦስተኛው መቶ ዘመን ላይ መሆኑ ከሐዋርያት ያልተገኘ ልማድ መሆኑን እንጂ ከሐዋርያት የተገኘ መሆኑን አያረጋግጥም።”—ሂስትሪ ኦቭ ዘ ፕላንቲንግ ኤንድ ትሬኒንግ ኦቭ ዘ ክርስቲያን ቸርች ባይ ዘ አፖስልስ (ሐዋርያት የክርስትናን እምነት ለመትከልና ለማሰልጠን ያደረጉት ተጋድሎ) (ኒው ዮርክ፣ 1864) ገጽ 162

የክርስቲያን የውኃ ጥምቀት የኃጢአት ሥርየት ያስገኛልን?

1 ዮሐ. 1:7:- “እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ . . . የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።” (እንግዲያውስ ከኃጢአት የሚያነጻን የኢየሱስ ክርስቶስ ደም እንጂ የውኃ ጥምቀት አይደለም።)

ማቴ. 3:11:- “እኔስ [ዮሐንስ መጥምቁ] ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን [ኢየሱስ ክርስቶስ] ከእኔ ይልቅ ይበረታል።” (ቁጥር 5, 6 እንዲሁም ሥራ 13:24 እንደሚያሳየው ዮሐንስ የጠቀሰው ጥምቀት ለሁሉም ሰዎች ሳይሆን ለአይሁድ ብቻ የሚያገለግል ነበር። ለምን? ምክንያቱም ይህ ጥምቀት ያስፈለገው አይሁዳውያን የሕጉን ቃል ኪዳን በመጣስ ኃጢአት በመሥራታቸው እነርሱን ለክርስቶስ ማሰናዳት በማስፈለጉ ነበር።)

ሥራ 2:38:- “ንስሐ ግቡ፣ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ።” (መጠመቁ ብቻ የኃጢአት ይቅርታ ያስገኝላቸው ነበርን? ይህ ነገር የተነገረው በክርስቶስ ሞት ተጠያቂዎች ለነበሩት አይሁዶች እንደነበር ልብ በል። [ቁጥር 22, 23⁠ን ተመልከት።] የእነርሱ ጥምቀት ኢየሱስ መሲሕ ወይም ክርስቶስ እንደሆነ ማመናቸውን ያመለክታል። ኃጢአታቸው ይቅር ሊባልላቸው የሚችለው ይህን ሲያደርጉ ብቻ ነው። [ሥራ 4:12፤ 5:30, 31])

ሥራ 22:16:- “ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (በተጨማሪ ሥራ 10:43⁠ን ተመልከት።)

በመንፈስ ቅዱስ የሚጠመቁት እነማን ናቸው?

1 ቆሮ. 1:2 አዓት፤ 12:13, 27:- “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ በመሆን ለተቀደሳችሁና ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ:- . . . አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል። እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ።” (ዳንኤል 7:13, 14, 27 እንደሚያሳየው እነዚህ “ቅዱሳን” የሰው ልጅ ተብሎ ከሚጠራው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የመንግሥቱ ተካፋዮች ይሆናሉ።)

ዮሐ. 3:5:- “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።” (አንድ ሰው ‘ከመንፈስ ቅዱስ የሚወለደው’ በመንፈስ ቅዱስ በሚጠመቅበት ጊዜ ነው። ሉቃስ 12:32 እንደሚያሳየው ይህን ስጦታ የሚያገኘው “ታናሽ መንጋ” ብቻ ነው። በተጨማሪ ራእይ 14:1–3⁠ን ተመልከት።)

በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቁ ሁሉ በልሳን የመናገርና የመፈወስ ስጦታ ይኖራቸዋልን?

1 ቆሮ. 12:13, 29, 30:- “በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። . . . ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? . . . ሁሉስ ተአምራትን ይሠራሉን? ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸውን? ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን?”

በተጨማሪም “ተአምራዊ ፈውስ” እና “በልሳናት መናገር” የሚሉትን አርዕስት ተመልከት።

‘ስለ ሙታን መጠመቅ’—ምን ማለት ነው?

1 ቆሮ. 15:29:- “እንዲያማ ካልሆነ፣ ስለ ሙታን የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ? ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ፣ ስለ እነርሱ የሚጠመቁ ስለ ምንድር ነው?”

በግሪክኛ ሃይፐር የተባለው መስተዋድድ እዚህ ላይ “ለ” ተብሎ የተተረጎመ ሲሆን በተጨማሪ “በ–ላይ”፣ “ስለ”፣ “በ–ፈንታ”፣ “ለ–ጉዳይ” ወዘተ የሚሉ ትርጉሞች አሉት። (ግሪክ–ኢንግሊሽ ሌክሲከን (ግሪክኛ–እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት)፣ በሊዴልና ስኮት የተዘጋጀ ) በዚህ ጥቅስ ላይ ቃሉ ምን ትርጉም አለው? ጳውሎስ በሕይወት ያሉት ሰዎች ሳይጠመቁ ለሞቱት እንዲጠመቁላቸው ጳውሎስ ሐሳብ ማቅረቡ ነበርን?

ሞትን በቀጥታ ከጥምቀት ጋር የሚያዛምዱ ሌሎች ጥቅሶች የሚገልጹት የሚሞተው ሰው ራሱ ስለሚፈጽመው ጥምቀት ነው እንጂ ለሌላ የሞተ ሰው ሲል ስለሚፈጽመው ጥምቀት አይደለም

ሮሜ 6:3:- “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደተጠመቅን አታውቁምን?” (በተጨማሪ ማርቆስ 10:38, 39⁠ን ተመልከት።)

ቆላ. 2:12:- “በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፣ [በሕይወት የነበሩት የቆላስይስ ጉባኤ አባሎች] በጥምቀት ደግሞ፣ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፣ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ።”

በ“አዲሲቱ ዓለም ትርጉም” ይህ ጥቅስ በትክክለኛ ሰዋስዋዊ አገባቡ የተተረጐመ ሲሆን ከሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር ይስማማል

1 ቆሮ. 15:29:- “እንዲያማ ካልሆነ እንደ ሙታን ለመሆን ሲሉ የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ? ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ፣ እንደ እነርሱ ለመሆን ሲሉ የሚጠመቁት ለምንድን ነው?” (የሚጠመቁት ወይም ውኃ ውስጥ የሚነከሩት እንደ ክርስቶስ ፍጹም አቋም ጠባቂዎች ሆነው እስከ ሞት የሚያደርስ ሕይወት ለማሳለፍና እንደ እርሱ መንፈሳዊ ሕይወት ይዘው ለመነሣት ነው።)

በእሳት መጠመቅ ምን ያስከትላል?

ሉቃስ 3:16, 17:- “እርሱ [ኢየሱስ ክርስቶስ] . . . በእሳት ያጠምቃችኋል፤ መንሹም በእጁ ነው፣ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፣ . . . ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” (የሚጠፋው ለዘላለም ነው።)

ማቴ. 13:49, 50:- “በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኃጢአተኞችን ከጻድቃን መካከል ይለዩአቸዋል፤ ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል።”

ሉቃስ 17:29, 30:- “ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን . . . ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ ሁሉንም አጠፋ። የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን እንዲሁ ይሆናል።”

ደቀ መዛሙርት ከሚጠመቁበት የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ጋር አንድ አይደለም

ሥራ 1:5:- “ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፣ እናንተ ግን [የኢየሱስ ታማኝ ሐዋርያት] ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ።”

ሥራ 2:2–4:- “ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፣ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። [ልክ እንደ ውኃ እያንዳንዳቸውን ሙሉ በሙሉ አልሸፈኗቸውም] በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፣ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሣኖች ይናገሩ ጀመር።”