በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጸሎት

ጸሎት

ፍቺ:- ጮክ ብሎ ወይንም ድምፅ ሳያሰሙ በራስ አሳብ ብቻ ለእውነተኛው አምላክ ወይም ለሐሰት አማልክት በአምልኮ መንፈስ መናገር።

ብዙ ሰዎች ጸሎታችን መልስ አያገኝም ይላሉ፤ አንተስ እንደነርሱ ይሰማሃልን?

አምላክ ለመስማት ፈቃደኛ የሚሆነው የእነማንን ጸሎት ነው?

መዝ. 65:2፤ ሥራ 10:34, 35:- “ሥጋ ሁሉ ጸሎትን ወደምትሰማ ወደ አንተ ይመጣል።” “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ [ነው።]” (የአንድ ሰው ብሔር ወይም የቆዳው ቀለም ወይም የኢኮኖሚ ደረጃው በጸሎቱ ተሰሚነት ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ አያመጣም። ለውጥ የሚያመጣው የልቡ ዝንባሌና አኗኗሩ ነው።)

ሉቃስ 11:2:- “ስትጸልዩ እንዲህ በሉ:- . . . አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ።” (ጸሎት የምታቀርበው መጽሐፍ ቅዱስ ስሙ ይሖዋ እንደሆነ ለሚናገርለት ለአብ ነው ወይስ “ለቅዱሳን”?)

ዮሐ. 14:6, 14:- “ኢየሱስም:- እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።” (ኃጢአተኛ እንደመሆንህ መጠን የኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅነት እንደሚያስፈልግህ በመገንዘብ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ትጸልያለህን?)

1 ዮሐ. 5:14 የ1980 ትርጉም:- “ማንኛውንም ነገር እንደ እርሱ ፈቃድ ብንለምን እንደሚሰማን እርግጠኞች ነን።” (ይሁን እንጂ እንዲህ ያለውን የእርግጠኝነት መንፈስ ለማግኘት በመጀመሪያ የአምላክን ፈቃድ ማወቅ ይኖርብሃል። ከዚያ በኋላ የምትለምነው ነገር ሁሉ ከዚህ ፈቃድ ጋር የሚስማማ መሆኑን አረጋግጥ።)

1 ጴጥ. 3:12:- “የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፣ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፣ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው።” (መጽሐፍ ቅዱስ ጽድቅ ወይም ክፉ ናቸው የሚላቸውን ነገሮች ለይተህ ለማወቅ ይሖዋ በቃሉ የሚናገረውን ጊዜ ወስደህ አጥንተሃልን?)

1 ዮሐ. 3:22:- “ትእዛዙን የምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን የምናደርግ ስለ ሆንን የምንለምንውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን።” (አምላክን ለማስደሰት ልባዊ ፍላጎት አለህን? የምታውቃቸውን የአምላክ ትእዛዛት ለመፈጸም ከልብ ትጥራለህን?)

ኢሳ. 55:6, 7:- “እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፣ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤ ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም ሐሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፣ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ።” (ይሖዋ መጥፎ ነገር ያደረጉ ሰዎች እንኳ እንዲጸልዩለት በምሕረቱ ጋብዟል። ይሁን እንጂ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ከፈለጉ ከተሳሳተ መንገዳቸውና አስተሳሰባቸው ንስሐ ገብተው አካሄዳቸውን መለወጥ ይኖርባቸዋል።)

የአንድን ሰው ሎት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ሊያሳጡት የሚችሉ ነገሮች ምንድን ናቸው?

ማቴ. 6:5:- “ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፣ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።” (በተጨማሪም ሉቃስ 18:9–14)

ማቴ. 6:7:- “አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ።”

ምሳሌ 28:9:- “[የአምላክን] ሕግ ከመስማት ጆሮውን የሚመልስ ጸሎቱ አስጸያፊ ናት።”

ሚክ. 3:4:- “የዚያን ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉ፣ እርሱም አይሰማቸውም፤ ሥራቸውንም ክፉ አድርገዋልና በዚያን ጊዜ ፊቱን ከእነርሱ ይሰውራል።”

ያዕ. 4:3 የ1980 ትርጉም:- “ብትጸልዩም፣ የጸሎታችሁን መልስ የማታገኙት፣ የለመናችሁትን ነገር በሥጋዊ ደስታ ላይ ለማዋል በክፉ አሳብ ስለምትጸልዩ ነው።”

ኢሳ. 42:8፤ ማቴ. 4:10:- “እኔ እግዚአብሔር [“ያህዌህ” ጀባ፤ “ይሖዋ” አዓት] ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም።” “ለጌታህ ለአምላክህ [“ለይሖዋ አምላክህ” አዓት] ስገድ፣ እርሱንም ብቻ አምልክ።” (በተጨማሪም መዝሙር 115:4–8፤ 113:4–8) (ጸሎት አንዱ የአምልኮ ዘርፍ ነው። በተቀረጸ ምስል ፊት ቆመህ ብትጸልይ አምላክ ይደሰትበታልን?)

ኢሳ. 8:19:- “እነርሱም:- የሚጮኹትንና ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው የሚናገሩትን መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ጠይቁ ባሏችሁ ጊዜ፣ ሕዝቡ ከአምላኩ መጠየቅ አይገባውምን? ወይስ ለሕያዋን ሲሉ ሙታንን ይጠይቃሉን?”

ያዕ. 1:6, 7:- “በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና። . . . ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው።”

ልንጸልይባቸው የሚገቡ ትክክለኛ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

ማቴ. 6:9–13:- “እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ:- [1] በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ፤ [2] መንግሥትህ ትምጣ፤ [3] ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ [4] የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤ [5] እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፤ [6] ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።” (የአምላክ ስምና ዓላማ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን አስተውል።)

መዝ. 25:4, 5:- “አቤቱ፣ መንገድህን አመልክተኝ፣ ፍለጋህንም አስተምረኝ። አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፣ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሁሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ።”

ሉቃስ 11:13:- “እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁ፣ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?”

1 ተሰ. 5:17, 18:- “ሳታቁርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ።”

ማቴ. 14:19, 20:- “[ኢየሱስ] አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፣ እንጀራውንም ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፣ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ። ሁሉም በልተው ጠገቡ።”

ያዕ. 5:16:- “እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ።”

ማቴ. 26:41:- “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ።”

ፊልጵ. 4:6:- “በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ።”

አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-

‘መጀመሪያ አብረን እንጸልይና ከዚያ በኃላ መልእክትህን ታሰማኛለህ’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘የጸሎትን አስፈላጊነት የሚገነዘቡ ሰው በመሆንዎ ደስ ብሎኛል። የይሖዋ ምሥክሮችም አዘውትረው ይጸልያሉ። ይሁን እንጂ መቼና እንዴት መጸለይ እንደሚገባን ኢየሱስ የተናገራቸው ነገሮች አዲስ ሊሆኑብዎት ይችላሉ። ደቀ መዛሙርቱ ጸሎተኛ ወይም ጻድቅ ሰው መስሎ ለመታየት ሲሉ በሰዎች ፊት መጸለይ እንደማይገባቸው መናገሩን ያውቃሉ? . . . (ማቴ. 6:5)’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘ልናተኩርበትና በጸሎታችን በመጀመሪያ ደረጃ ልንጠይቅ የሚገባን ምን መሆን እንዳለበት መግለጹንም ልብ ይበሉት። ዛሬ ልነግርዎ የመጣሁት ስለዚህ ጉዳይ ነው። (ማቴ. 6:9, 10)’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘የአንዳንድ ሃይማኖት ተወካዮች እንዲህ እንደሚያደርጉ አውቃለሁ። የይሖዋ ምሥክሮች ግን እንዲህ አያደርጉም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ የስብከት ሥራቸውን ከዚህ በተለየ መንገድ እንዲያከናውኑ ነግሯቸዋል። “ወደ ቤት በገባችሁ ጊዜ በመጀመሪያ ጸልዩ” ከማለት ይልቅ በ⁠ማቴዎስ 10:12, 13 ላይ ምን እንደተናገረ ልብ ይበሉ። . . . እዚህ ቁጥር 7 ላይ ስለምን ነገር መናገር እንደሚገባቸው የተናገረውን ይመልከቱ። . . . ይህች መንግሥት እንደ እርስዎና እንደ እኔ ላሉት ሰዎች ምን እርዳታ ልትሰጥ ትችላለች? (ራእይ 21:4)’