ፍልስፍና
ፍቺ:- “ፊሎዞፊ” (ፍልስፍና) የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “የጥበብ ፍቅር” የሚል መሠረታዊ ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃል የመጣ ነው። ፍልስፍና እዚህ ላይ ባለው አጠቃቀም መሠረት አምላክን በማመን ላይ የተገነባ ሳይሆን ሰዎች ስለ ጽንፈ ዓለሙ አንድ ወጥ አመለካከት እንዲኖራቸውና ስህተት ፈላጊ አስተሳሰብ ያላቸው እንዲሆኑ ለማድረግ የሚጥር ነው። እውነትን ለመፈለግ ጥረት የሚደረገው ያሉትን መረጃዎች በመመልከት ሳይሆን ግምታዊ አስተሳሰብን በመመርኮዝ ነው።
ማናችንም ብንሆን እውነተኛ እውቀትና ጥበብ ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው?
ምሳሌ 1:7፤ መዝ. 111:10 አዓት:- “እግዚአብሔርን መፍራት የእውቀት . . . [እና] የጥበብ መጀመሪያ ነው።” (ጽንፈ ዓለሙ የማሰብ ችሎታ ባለው ፈጣሪ የተገኘ ካልሆነና ምክንያታዊ ያልሆነ ጭፍን ኃይል ውጤት ከሆነ ስለ ጽንፈ ዓለሙ አንድ ወጥ የሆነ አመለካከት ሊኖር አይችልም፤ ይችላል እንዴ? ምክንያታዊ ያልሆነና ሥርዓት የሌለው ነገር ከማጥናት ደግሞ ምንም ዓይነት ጥበብ ሊገኝ አይችልም፤ ይቻላል? አምላክንና ዓላማውን ወደ ጎን ገሸሽ አድርገው ጽንፈ ዓለሙንም ሆነ ሕይወትን ራሱን ለመረዳት የሚሞክሩ ሁሉ ጥረታቸው ከንቱ ይሆናል። ለተማሩት ነገር የተሳሳተ ትርጉም ይሰጣሉ። ከዚህም ከዚያም የቃረሙትንም እውቀት አለአግባብ ይጠቀሙበታል። በአምላክ ማመንን ወደ ጎን ገሸሽ ማድረግ ለትክክለኛ እውቀት ቁልፍ የሆነውን ነገር አጥፍቶ አንድ ወጥና ምክንያታዊ የሆነ አስተሳሰብ እንዳይኖር ያደርጋል።)
ምሳሌ 2:4–7:- “እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፣ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፣ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ። እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፤ እርሱ ለቅኖች ደኅንነትን [“ተግባራዊ ጥበብን” አዓት] ያከማቻል።” (ይሖዋ አስፈላጊውን እርዳታ በተጻፈው ቃሉና በሚታየው ድርጅቱ አማካኝነት ይሰጣል። በተጨማሪም ልባዊ የሆነ ፍላጎትና የግል ጥረት ማድረግ፤ እንዲሁም የራስን የማሰብ ችሎታ ገንቢ በሆነ መንገድ ማሠራት ያስፈልጋል።)
ከዚህ መጽሐፍ ፍጹም የሆነውን እውነት አገኛለሁ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነውን?
2 ጢሞ. 3:16 አዓት፤ ዮሐ. 17:17:- “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ . . . ነው።” “[ኢየሱስ ለሰማያዊ አባቱ እንዲህ አለ:-] ቃልህ እውነት ነው።” (የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ ስለ ጽንፈ ዓለሙ የተሟላ እውቀት ይኖረዋል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይደለምን? አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ጽንፈ ዓለም ሁሉንም ነገር አልነገረንም። የገለጸልን ነገሮች ግን በግምት ላይ የተመሠረቱ ሳይሆኑ እውነት ናቸው። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ምን እንደሆነና ይህንንም ዓላማ እንዴት እንደሚፈጽም ገልጿል። የእርሱ ዓላማ ሙሉ በሙሉና ከሁሉ በተሻለ መንገድ የሚፈጸም ለመሆኑ ሁሉን የሚችለው ኃይሉ፣ በጣም ታላቅ የሆነው ጥበቡ፣ እንከን የማይገኝበት ፍትሑ እና ታላቅ ፍቅሩ ዋስትና ይሆናሉ። ስለዚህ ስለ ዓላማው የሰጠው መግለጫ አስተማማኝና እውነት መሆኑን የራሱ ባሕርያት ያረጋግጡልናል።)
የሰብዓዊ ፍልስፍናዎች ምንጭ ምንድን ነው?
ችሎታቸው ውስን ከሆነ ሰዎች የመነጩ ናቸው:- መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።” ኤር. 10:23) ይህን የሰው ልጆችን የችሎታ ውስንነት አለመቀበል መጥፎ ውጤት እንዳስከተለ ታሪክ ይመሰክራል። አንድ ጊዜ “እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ እንዲህም አለ:- ያለ እውቀት በሚነገር ቃል ምክርን የሚያጨልም ይህ ማነው? እንግዲህ እንደ ሰው ወገብህን ታጠቅ፤ እጠይቅሃለሁ፣ አንተም ተናገረኝ። ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ ወዴት ነበርህ? ታስተውል እንደ ሆንህ ተናገር።” (ኢዮብ 38:1–4) (የሰው ልጆች በተፈጥሯቸው ያላቸው ችሎታ የተወሰነ ነው። በተጨማሪም የሕይወት ተሞክሯቸው አጭር ከመሆኑም በላይ አብዛኛውን ጊዜ የራሳቸው ባሕልና አካባቢ ግንዛቤያቸውን ያጠበዋል። በዚህም ምክንያት የሚኖራቸው እውቀት በጣም ውስን ነው። ከዚህም በላይ ሁሉም ነገር እርስ በርሱ የተያያዘ በመሆኑ ሁልጊዜ ግምት ውስጥ ያላስገቧቸው ነገሮች ብቅ ይላሉ። እንደነዚህ ካሉት ሰዎች የሚመነጭ ማንኛውም ፍልስፍና እነዚህን ድክመቶች የሚያንጸባርቅ ይሆናል።)
(ፍልስፍናዎቹ ፍጹም ባልሆኑ የሰው ልጆች የተፈጠሩ ናቸው:- “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል።” (ሮሜ 3:23) “ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው።” (ምሳሌ 14:12) (ይህን የመሰለ አለፍጽምና ስላለ ሰብዓዊ ፍልስፍናዎች በመሠረቱ ራስ ወዳድነትን ያንፀባርቃሉ። ይህ ደግሞ ምናልባት ጊዜያዊ ደስታ ሊሰጥ ቢችልም ብስጭትንና ምሬትን ያስከትላል።)
ፍልስፍናዎቹ የአጋንንታዊ መናፍስት እጅ አለባቸው:- “ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን።” (1 ዮሐ. 5:19) ‘ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ዓለሙን ሁሉ እያሳተ ነው።’ (ራእይ 12:9) “በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፣ በፊት ተመላለሳችሁባቸው።” (ኤፌ. 2:2) (ሰዎች የአምላክን ጤናማና ቅን ሕግጋት እንዲጥሱ የሚያደፋፍሩ ፍልስፍናዎች የአጋንንት እጅ ያለባቸው ናቸው። እንግዲያው ታሪክ እንደሚመሰክረው ሰብዓዊ ፍልስፍናዎችና ዕቅዶች ለበርካታ የሰው ልጆች ኀዘንና መከራ ማምጣታቸው አያስደንቅም።)
ከሰብዓዊ ፍልስፍና ይልቅ የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት ማጥናት ትክክለኛ አስተሳሰብ እንዳለን የሚያሳየው ለምንድን ነው?
ቆላ. 1:15–17:- “እርሱ [ኢየሱስ ክርስቶስ] የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ . . . በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፣ ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል።” (ኢየሱስ ከአምላክ ጋር ያለው የቅርብ ዝምድና ስለ አምላክ እውነቱን እንዲያሳውቀን ያስችለዋል። ከዚህም በላይ ሌላው ፍጥረት ሁሉ የተፈጠረው በሱ በኩል ስለሆነ ኢየሱስ በመላው ጽንፈ ዓለም ስላለው ፍጥረት የተሟላ እውቀት አለው። ይህን የመሰለ እውቀት ሊሰጥ የሚችል ሰብዓዊ ፈላስፋ አይገኝም።)
ቆላ. 1:19, 20:- “እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ [ኢየሱስ ክርስቶስ] እንዲኖር፣ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና።” (ስለዚህ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መላውን ፍጥረት ከራሱ ጋር ለማስማማት ዓላማ አለው። በተጨማሪም ዳንኤል 7:13, 14 እንደሚያመለክተው አምላክ ለኢየሱስ የመላውን ምድር ግዛት ሰጥቶታል። ስለዚህ ወደፊት የምናገኘው የሕይወት ተስፋ ኢየሱስንና ኢየሱስ የሰጣቸውን መመሪያዎች በመቀበል ላይ የተመካ ነው።)
ቆላ. 2:8:- “እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፣ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።” (በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከአምላክ ቀጥሎ ሁለተኛ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሆኖ ትክክለኛ እውቀት ከማግኘት ይልቅ እንዲህ ያለውን አታላይ የሰዎች ፍልስፍና ለመከተል መምረጥ እንዴት ያለ አሳዛኝ ስህተት ነው!)
ሰብዓዊ ፈላስፎች የሚሰጡትን “ጥበብ” አምላክ እንዴት ይመለከተዋል?
1 ቆሮ. 1:19–25:- “የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና። ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፣ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን [ለዓለም እንደሚመስለው] ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና። . . . ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት [ለዓለም እንደሚመስለው] ይጠበባልና፣ የእግዚአብሔርም ድካም [ዓለም እንደሚመለከተው] ከሰው ይልቅ ይበረታልና።” (እንዲህ ያለው የአምላክ አመለካከት ምክንያተ ቢስ ወይም ጭፍን አይደለም። እሱ በዓለም በሙሉ ከተጻፉት መጻሕፍት የበለጠ ሥርጭት ባለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዓላማውን በግልጽ አሳውቋል። ለመስማት ፈቃደኛ ለሆኑ ሁሉ እንዲያስረዱ ምሥክሮቹን ልኳቸዋል። ማንም ፍጥረት ከአምላክ የበለጠ ጥበብ አለኝ ብሎ ቢያስብ እንዴት ያለ ሞኝነት ይሆንበታል!)