በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

()

()

ፍቺ:- የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የሚታሰብበት ራት ነው። በዚህ ራት ከማንኛውም ሰው ሞት የበለጠ ውጤት ያስገኘው የክርስቶስ ሞት ይታሰባል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ መታሰቢያ በዓል እንዲያከብሩለት ያዘዘው ለሞቱ ብቻ ነው። በተጨማሪም ይህ መታሰቢያው የጌታ ራት ተብሎ ይጠራል።—1 ቆሮ. 11:20

የመታሰቢያው በዓል ትርጉም ምንድን ነው?

ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ። (ሉቃስ 22:19) ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ለተወለዱት የክርስቲያን ጉባኤ አባሎች ሲጽፍ:- “ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፣ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና።” (1 ቆሮ. 11:26) ስለዚህ መታሰቢያው የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የይሖዋን ዓላማ በማስፈጸም ረገድ ያለውን ትልቅ ቦታ ያሳስባል። በተጨማሪም የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት በተለይ ከአዲሱ ቃል ኪዳን ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ ያለውን ትርጉምና ሞቱ አብረውት መንግሥተ ሰማያትን በሚወርሱ ሰዎች ላይ የሚኖረውን ውጤት አጉልቶ ያሳያል።—ዮሐ. 14:2, 3፤ ዕብ. 9:15

በተጨማሪም መታሰቢያው በዓል በ⁠ዘፍጥረት 3:15 እና ከዚያ በኋላ በተገለጸው የአምላክ ዓላማ መሠረት የተፈጸመው የኢየሱስ ሞትና አሟሟት በይሖዋ ስም ላይ የደረሰውን ነቀፋ ያስወገደ መሆኑን ያስታውሰናል። ኢየሱስ ለይሖዋ ያለውን ፍጹም አቋም እስከሞት ድረስ ሳያጐድፍ በመገኘቱ አዳም ኃጢአት የሠራው በሰው ልጅ ላይ የአፈጣጠር ጉድለት ስለኖረ እንዳልሆነና የሰው ልጅ ከባድ ተጽእኖ ቢደርስበት እንኳን ፍጹም አቋሙን ሊጠብቅ ይችል እንደነበረ አረጋግጧል። በዚህም ኢየሱስ የይሖዋን ፈጣሪነትና ጽንፈ ዓለማዊ የበላይ ገዥነት አረጋግጧል። ከዚህ በተጨማሪ የኢየሱስ ሞት የአዳም ዘሮችን ለመቤዠት የሚያስችል ፍጹም ሰብዓዊ መሥዋዕት እንዲሆን የይሖዋ ዓላማ ነበር። ይህም በመጀመሪያው የይሖዋ ዓላማና ለሰው ልጆች ባለው ታላቅ ፍቅር መሠረት በኢየሱስ የሚያምኑ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር የሚችሉበትን መንገድ ከፍቷል።—ዮሐ. 3:16፤ ዘፍ. 1:28

ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ ባሳለፋት የመጨረሻ ምሽት ላይ በጣም ከባድ ሸክም ወድቆበት ነበር። ሰማያዊ አባቱ ምን ዓላማ እንዳዘጋጀለት ጠንቅቆ የሚያውቅ ቢሆንም በሚደርስበት ፈተና ሁሉ ታማኝነቱን ማረጋገጥ እንደሚኖርበት ያውቅ ነበር። በፈተናው ተሸንፎ ቢሆን በአባቱ ላይ ከፍተኛ ነቀፋ ይመጣ ነበር። በሰው ልጆችም ላይ ከፍተኛ የሆነ ኪሣራ በደረሰ ነበር። ሞቱ በሚያስገኛቸው ከፍተኛ ውጤቶች ምክንያት ሞቱ እንዲታሰብ መመሪያ መስጠቱ ተገቢ ነበር።

በመታሰቢያው ላይ የሚቀርበው ቂጣና ወይን ትርጉሙ ምንድን ነው?

ኢየሱስ መታሰቢያውን ባቋቋመበት ጊዜ ለሐዋርያቱ ስለሰጣቸው ያልቦካ ቂጣ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ይህ ሥጋዬ ማለት ነው።” (ማር. 14:22 አዓት ) ይህ ቂጣ ኃጢአት የሌለበትን ሥጋውን ይወክላል። ይህን ሥጋውን የሰው ልጆች የሕይወት ተስፋ እንዲያገኙ ሲል ሰጥቷል። በዚህ ዕለት ይህ መሥዋዕት ከኢየሱስ ጋር በሰማያዊው መንግሥት ተካፋዮች እንዲሆኑ ለሚመረጡት ሰዎች ለሚያስገኘው የሕይወት ተስፋ ልዩ ትኩረት ይደረጋል።

ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱ ወይኑን በሰጣቸው ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈሰው ‘የቃል ኪዳን ደሜ’ ማለት ነው።” (ማር. 14:24 አዓት ) ይህ ወይን የኢየሱስን ደመ ሕይወት ይወክላል። በፈሰሰው ደሙ የሚያምኑ ሁሉ በዚህ ደም አማካኝነት የኃጢአት ሥርየት ያገኛሉ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አጉልቶ የገለጸው ወደ ፊት ከእርሱ ጋር ተባባሪ ወራሾች የሚሆኑት ስለሚያገኙት የኃጢአት ሥርየት ነበር። በተጨማሪም የተናገረው ቃል በይሖዋ አምላክና በመንፈስ በተቀባው የክርስቲያን ጉባኤ መካከል የተደረገው አዲስ ቃል ኪዳን በዚህ ደም አማካኝነት ሥራውን እንደሚጀምር ያመለክታል።

በተጨማሪ በገጽ 261–263 ላይ “ቁርባን” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።

ከቂጣውና ከወይኑ የሚካፈሉት እነማን ናቸው?

ኢየሱስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ የጌታን ራት ባቋቋመበት ጊዜ ከቂጣውና ከወይኑ የተካፈሉት እነማን ነበሩ? ኢየሱስ “አባቴ ከእኔ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን እንዳደረገ እኔ ደግሞ ከእናንተ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን አደርጋለሁ” ያላቸው አሥራ አንድ ታማኝ ተከታዮች ነበሩ። (ሉቃስ 22:29 አዓት ) ሁሉም ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊው መንግሥት እንዲካፈሉ የተጋበዙ ሰዎች ነበሩ። (ዮሐ. 14:2, 3) ዛሬም ቢሆን ከቂጣውና ከወይኑ የሚካፈሉ ሁሉ ክርስቶስ ወደዚህ ‘የመንግሥት ቃል ኪዳን’ ያስገባቸው ሰዎች መሆን ይኖርባቸዋል።

ከቂጣውና ከወይኑ የሚካፈሉት ሰዎች ቁጥር ምን ያህል ነው? የሰማያዊ መንግሥት ሽልማት የሚያገኙት “ታናሽ መንጋ” ብቻ እንደሚሆኑ ኢየሱስ ተናግሯል። (ሉቃስ 12:32) ሙሉ ቁጥራቸው 144,000 ነው። (ራእይ 14:1–3) የዚህ ቡድን አባሎች መመረጥ የጀመሩት በ33 እዘአ ነበር። ስለዚህ ዛሬ ከቂጣውና ከወይኑ የሚካፈሉት ሰዎች ቁጥር በጣም ትንሽ ነው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው።

ዮሐንስ 6:53, 54 ከቂጣውና ከወይኑ የሚካፈሉት ብቻ ዘላለማዊ ሕይወት እንደሚያገኙ ያመለክታልን?

ዮሐ. 6:53, 54:- “ኢየሱስ እንዲህ አላቸው:- እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ፣ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፣ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።”

እዚህ ላይ የተናገረለት መብላትና መጠጣት በምሳሌያዊ ሁኔታ የሚፈጸም መሆን እንደሚገባው ግልጽ ነው። አለዚያ ሥጋና ደም የሚበላውና የሚጠጣው ሰው የአምላክን ሕግ ይጥሳል። (ዘፍ. 9:4፤ ሥራ 15:28, 29) ኢየሱስ በ⁠ዮሐንስ 6:53, 54 ላይ የሚገኘውን ቃል የተናገረው ከጌታ ራት መቋቋም ጋር አዛምዶ እንዳልሆነ ልብ ማለት ይገባል። ኢየሱስ ሲናገር ከሰሙት መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ የክርስቶስን ሥጋና ደም በሚወክል ቂጣና ወይን አማካኝነት ስለሚከበር በዓል የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ይህ ዝግጅት የተጀመረው ከአንድ ዓመት በኋላ ነበር። ሐዋርያው ዮሐንስ በስሙ በሚጠራው ወንጌል ውስጥ ስለ ጌታ ራት የገለጸው (በ⁠ዮሐንስ 14 ላይ) ከሰባት ምዕራፎች በኋላ ነው።

ታዲያ አንድ ሰው ‘የሰውን ልጅ ሥጋ የሚበላውና ደሙን የሚጠጣው’ በመታሰቢያው ዕለት ከቂጣውና ከወይኑ በመካፈል ካልሆነ በምሳሌያዊ መንገድ ሥጋውን ሊበላና ደሙን ሊጠጣ የሚችለው እንዴት ነው? ቂጣውን የሚበሉና ደሙን የሚጠጡ “የዘላለም ሕይወት” እንደሚኖራቸው ኢየሱስ ተናግሯል። ከዚህ ቀደም ብሎ በቁጥር 40 ላይ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ከፈለጉ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሲገልጽ የአባቱ ፈቃድ ምን እንደሆነ ተናገረ? “ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት” ይኖረዋል። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) እንግዲያውስ በምሳሌያዊ አነጋገር ሥጋውን መብላትና ደሙን መጠጣት የሚቻለው የመዋጀት ኃይል ባለው በኢየሱስ ሥጋና መሥዋዕት ሆኖ በፈሰሰው ደሙ በማመን ነው። ይህ እምነት በሰማያት ከክርስቶስ ጋር ከሚሆኑትም ይሁን ገነት በምትሆነው በምድር ላይ ከሚኖሩት ይፈለግባቸዋል።

የመታሰቢያው በዓል መከበር የሚኖርበት በየስንት ጊዜው ነው? የሚከበረውስ መቼ ነው?

በየስንት ጊዜው መከበር እንደሚኖርበት ኢየሱስ በግልጽ አልተናገረም። ባጭሩ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሏል። (ሉቃስ 22:19) ጳውሎስ እንዲህ አለ:- “ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፣ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ።” (1 ቆሮ. 11:26) “ጊዜ ሁሉ” የሚለው አነጋገር በዓመት ውስጥ ብዙ ጊዜ እንዲህ ታደርጋላችሁ ማለት ላይሆን ይችላል። በየዓመቱ ለብዙ ዘመናት አድርጉት ማለት ሊሆን ይችላል። አንድ ትልቅ በዓል ለምሳሌ የጋብቻህን ቀን የምታከብር ብትሆን ወይም አንድ አገር በታሪኳ ውስጥ የተፈጸመን አንድ ትልቅ ድርጊት የምታከብር ቢሆን ይህ ቀን የሚከበረው ምን ያህል ጊዜ ነው? በዓሉ የሚከበረው በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ይህም የጌታ ራት የተቋቋመው አይሁዶች በየዓመቱ ያከብሩ በነበረውና ክርስቲያን በሆኑት አይሁዶች መከበሩ በቀረው የማለፍ በዓል ዕለት ከመሆኑ ጋር ይስማማል።

የይሖዋ ምሥክሮች የመታሰቢያውን በዓል የሚያከብሩት በአንደኛው መቶ ዘመን ይሠራበት በነበረው የአይሁዳውያን የዘመን አቆጣጠር መሠረት ኒሳን 14 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ነው። የአይሁዳውያን ቀን የሚጀምረው ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ሲሆን በማግሥቱ ፀሐይ እስከምትጠልቅበት ጊዜ ድረስ ይቆያል። ስለዚህ ኢየሱስ የሞተው በአይሁዳውያን አቆጣጠር መሠረት የመታሰቢያውን በዓል ባቋቋመበት ዕለት ነበር። የኒሣን ወር የሚጀምረው በፀደይ ወራት የቀኑና የሌሊቱ ርዝማኔ እኩል በሚሆንበት ጊዜ ቅርብ የሆነችው አዲስ ጨረቃ በኢየሩሳሌም ከታየች በኋላ ፀሐይ ስትጠልቅ ነው። የመታሰቢያው በዓል የሚከበረው ይህ ከሆነ ከ14 ቀን በኋላ ነው። (የመታሰቢያው በዓል የዛሬዎቹ አይሁዳውያን ከሚያከብሩት የማለፍ በዓል ጋር አይገጥምም። ለምን? ምክንያቱም የወሮቻቸው መባቻ አዲስ ጨረቃ በኢየሩሳሌም ከሚታይበት ጊዜ ጋር ሳይሆን በከዋክብት ጥናት መሠረት አዲስ ጨረቃ ከምትታይበት ጊዜ ጋር እንዲጋጠም ስላደረጉ ነው። በዚህም ምክንያት ከ18 እስከ 30 ሰዓት ልዩነት ሊኖር ይችላል። በተጨማሪም ዛሬ አብዛኞቹ አይሁዳውያን የማለፍን በዓል የሚያከብሩት ኒሳን 15 ላይ ነው። ይህም የሙሴ ሕግ በሚያዘው መሠረት ኢየሱስ በዓሉን ካከበረበት ከኒሣን 14 የሚለይ ነው።)