በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 6

ታላቁ አስተማሪ ሌሎች ሰዎችን አገልግሏል

ታላቁ አስተማሪ ሌሎች ሰዎችን አገልግሏል

አንድ ሰው ጥሩ ነገር ሲያደርግልህ ደስ አይልህም?— ሰዎች አንድ ሰው ጥሩ ነገር ሲያደርግላቸው ደስ ይላቸዋል። ሁላችንም ጥሩ ነገር ሲደረግልን ደስ ይለናል። ታላቁ አስተማሪ ይህን ያውቅ ስለነበር ለሰዎች ሁልጊዜ ጥሩ ነገር ያደርግ ነበር። ‘የመጣሁት ሰዎችን ለማገልገል እንጂ እኔን እንዲያገለግሉኝ አይደለም’ ብሏል።—ማቴዎስ 20:28

የኢየሱስ ተከታዮች የተከራከሩት ስለምን ጉዳይ ነበር?

እኛም እንደ ታላቁ አስተማሪ መሆን ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?— ሌሎችን ማገልገል አለብን። ለሰዎች ጥሩ ነገር ማድረግ ይኖርብናል። እርግጥ ብዙ ሰዎች ለሌሎች ጥሩ ነገር አያደርጉም። እንዲያውም አብዛኞቹ ሰዎች ሁልጊዜ ሌሎች እንዲያገለግሏቸው ይፈልጋሉ። በአንድ ወቅት የኢየሱስ ተከታዮችም እንኳን ሳይቀር ሌሎች ብቻ እንዲያገለግሏቸው ፈልገው ነበር። እያንዳንዳቸው ታላቅ የመሆን ወይም ከሁሉ የበላይ የመሆን ፍላጎት ነበራቸው።

አንድ ቀን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ማለትም ከተከታዮቹ ጋር እየተጓዘ ነበር። በገሊላ ባሕር አጠገብ ወደነበረችው ቅፍርናሆም ወደተባለችው ከተማ ሲደርሱ ሁሉም ወደ አንድ ቤት ገቡ። እዚያም ኢየሱስ “በመንገድ ላይ ስትከራከሩ የነበረው ስለ ምን ጉዳይ ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። እነሱ ግን ‘ከሁላችን የሚበልጠው ማን ነው’ እያሉ ሲከራከሩ ስለ ነበር ዝም አሉ።—ማርቆስ 9:33, 34

ኢየሱስ የእሱ ደቀ መዝሙር የሆነ ሰው ራሱን ከሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው እንደሆነ አድርጎ መመልከት እንደሌለበት ያውቅ ነበር። ስለዚህ በዚህ መጽሐፍ በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ እንደተማርነው አንድ ሕፃን ልጅ በመካከላቸው አቁሞ እንደ ሕፃኑ ልጅ ትሑት መሆን እንዳለባቸው ነገራቸው። እነሱ ግን እንዲህ ቢያስተምራቸውም አልተለወጡም። ስለዚህ ኢየሱስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ አንድ የማይረሱት ትምህርት አስተማራቸው። ምን ያደረገ ይመስልሃል?—

ሁሉም አብረው በመመገብ ላይ እንዳሉ ኢየሱስ ተነስቶ ከላይ ደርቦት የነበረውን ልብስ አውልቆ አስቀመጠ። ፎጣ አንስቶ በወገቡ ላይ ታጠቀ። ከዚያም በመታጠቢያ ሳህን ውስጥ ውኃ ጨመረ። ተከታዮቹ ምን ሊያደርግ ነው ብለው ሳይገረሙ አይቀሩም። ከዚያም እነሱ እየተመለከቱት ሳለ እየዞረ ደቀ መዛሙርቱን በሙሉ አጎንብሶ እግራቸውን አጠበ። ከዚያም በፎጣ እግራቸውን አደረቀ! እስቲ አስበው! አንተ እዚያ ብትኖር ኖሮ ምን ይሰማህ ነበር?—

ኢየሱስ ተከታዮቹን ምን ትምህርት አስተምሯቸዋል?

የኢየሱስ ተከታዮች ታላቁ አስተማሪ በዚህ መንገድ እነሱን ማገልገሉ ትክክል መስሎ አልታያቸውም ነበር። ያደረገው ነገር አሳፍሯቸው ነበር። እንዲያውም ጴጥሮስ ይህ እንደ ዝቅተኛ ሥራ ተደርጎ የሚቆጠር ስለነበር እግሩን እንዳያጥበው ሊከለክለው ሞክሮ ነበር። ኢየሱስ ግን ይህን ማድረጉ አስፈላጊ እንደሆነ ተናገረ።

በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው አንዳችን የሌላውን እግር አናጥብም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በምድር በነበረበት ዘመን የሰዎችን እግር ማጠብ የተለመደ ነገር ነበር። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ኢየሱስና ተከታዮቹ በኖሩበት አገር ሰዎች የሚያደርጉት ክፍት ጫማ ነበር። ስለዚህ በአቧራማ መንገዶች ላይ ሲጓዙ እግራቸው አቧራ ብቻ ይሆን ነበር። ስለዚህ ሊጠይቃቸው ወደ ቤታቸው የሚመጣውን ሰው እግር በማጠብ ደግነት ያሳዩ ነበር።

ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ባጠበበት ጊዜ ግን ከኢየሱስ ተከታዮች መካከል የሌሎቹን እግር ለማጠብ ያሰበ አንድም ሰው አልነበረም። በመሆኑም ኢየሱስ ራሱ ተነስቶ እግራቸውን አጠበ። ይህን በማድረግ ለተከታዮቹ አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት አስተማራቸው። ይህን ትምህርት መማራቸው በጣም አስፈላጊ ነበር። እኛም ዛሬ ይህን ትምህርት መማር ያስፈልገናል።

ኢየሱስ ለማስተማር የፈለገው ትምህርት ገብቶሃል?— ኢየሱስ ያወለቀውን ልብስ ለብሶ እንደገና ምግቡ ወደቀረበበት ቦታ ከተመለሰ በኋላ እንዲህ አላቸው:- “ምን እንዳደረግኩላችሁ አስተዋላችሁ? እናንተ ‘መምህር’ እና ‘ጌታ’ ብላችሁ ትጠሩኛላችሁ፤ እንደዚያ ስለሆንኩም እንዲህ ብላችሁ መጥራታችሁ ትክክል ነው። ስለዚህ እኔ ጌታና መምህር ሆኜ ሳለሁ እግራችሁን ካጠብኩ እናንተም እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል።”—ዮሐንስ 13:2-14

ሌሎች ሰዎችን ለመርዳት ምን ልታደርግ ትችላለህ?

እዚህ ላይ ታላቁ አስተማሪ ተከታዮቹ አንዳቸው ሌላውን እንዲያገለግሉ እንደሚፈልግ አሳይቷል። ስለ ራሳቸው ብቻ የሚያስቡ ራስ ወዳዶች እንዲሆኑ አልፈለገም። ራሳቸውን ከፍ አድርገው በመመልከት ሁልጊዜ ሌሎች እነሱን ሊያገለግሉ እንደሚገባ አድርገው እንዲያስቡ አልፈለገም። ሌሎች ሰዎችን ለማገልገል ፈቃደኞች እንዲሆኑ ይፈልግ ነበር።

ይህ ጥሩ ትምህርት አይደለም?— አንተም ታላቁን አስተማሪ በመምሰል ሌሎችን ለማገልገል ፈቃደኛ ነህ?— ሁላችንም ለሌሎች ልናደርግላቸው የምንችለው ነገር ይኖራል። ሰዎች ጥሩ ነገር ስናደርግላቸው ደስ ይላቸዋል። ከሁሉ በላይ ግን ለሌሎች ሰዎች ጥሩ ነገር ማድረጋችን ኢየሱስንና አባቱን ያስደስታቸዋል።

ሌሎች ሰዎችን ማገልገል ከባድ ነገር አይደለም። ካሰብክበት ለሌሎች ልታደርግላቸው የምትችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። እስቲ ትንሽ ለማሰብ ሞክር:- እናትህን ለማገዝ ምን ማድረግ ትችላለህ? እናትህ ለአንተም ሆነ ለሌሎቹ የቤተሰባችሁ አባላት ብዙ ነገር እንደምታደርግላችሁ ታውቃለህ። ታዲያ ልታግዛት ትችላለህ?— ምን ላግዝሽ ብለህ ለምን አትጠይቃትም?

ምናልባት ቤተሰቡ ምሳ ወይም ራት የሚበላበት ሰዓት ሲደርስ ዕቃ ልታቀራርብ ትችል ይሆናል። ወይም ደግሞ ምግብ ተበልቶ ካበቃ በኋላ ከጠረጴዛው ላይ ዕቃዎቹን ልታነሳሳ ትችላለህ። አንዳንድ ልጆች በየቀኑ ቤት ይጠርጋሉ እንዲሁም ይወለውላሉ። ልታደርግ የምትችለው ነገር ምንም ይሁን ምን አንተም እንደ ኢየሱስ ሌሎችን ልታገለግል ትችላለህ።

ልታገለግላቸው የምትችላቸው ታናናሽ ወንድሞችና እህቶች አሉህ? ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስ ተከታዮቹንም እንኳን ሳይቀር እንዳገለገለ አስታውስ። ታናናሽ ወንድሞችህንና እህቶችህን በማገልገል ኢየሱስን መምሰል ትችላለህ። ታዲያ ለታናናሾችህ ምን ልታደርግላቸው ትችላለህ?— ምናልባት ተጫውተው ሲያበቁ መጫወቻቸው እንዳይዝረከረክ ሰብስበህ በማስቀመጥ ልታሠለጥናቸው ትችል ይሆናል። ወይም ልብሳቸውን እንዲለብሱ ልትረዳቸው ትችል ይሆናል። ወይም ደግሞ አልጋቸውን እንዲያነጥፉ ልትረዳቸው ትችል ይሆናል። ሌላስ ልታደርግላቸው የምትችለው ነገር ይኖር ይሆን?— እነዚህን ነገሮች ስታደርግላቸው ደስ ይላቸዋል። የኢየሱስ ተከታዮችም ኢየሱስ ባደረገላቸው ነገር ተደስተዋል።

በትምህርት ቤትም ሌሎች ሰዎችን ልታገለግል ትችላለህ። የምታገለግለው አብረውህ የሚማሩትን ልጆች ወይም አስተማሪህን ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው መጽሐፉ ቢወድቅበት መጽሐፉን በማንሳት ደግነት ልታሳየው ትችላለህ። ለአስተማሪህ ሰሌዳውን ልታጠፋለት ወይም ሌላ ነገር ልትሠራለት ትችላለህ። አንድ ሰው ሲገባ ወይም ሲወጣ በር ከፍቶ አስቀድሞ ማሳለፍም እንኳ ጥሩ ምግባር ነው።

አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ለተደረገላቸው ነገር እንደማያመሰግኑ እናውቃለን። ታዲያ ሰዎች የማያመሰግኑ መሆናቸው ጥሩ ነገር እንዳንሠራ ምክንያት ሊሆነን የሚገባ ይመስልሃል?— በጭራሽ! ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ጥሩ ነገር አድርጎላቸው አላመሰገኑትም። ነገር ግን የእነሱ አለማመስገን ጥሩ ነገር መሥራቱን እንዲተው አላደረገውም።

ስለዚህ እኛም ለሌሎች ሰዎች ጥሩ ነገር ማድረጋችንን መተው የለብንም። ታላቁን አስተማሪ ኢየሱስን በማስታወስ ምንጊዜም የእሱን ምሳሌ ለመከተል እንጣር።

ሌሎች ሰዎችን ስለመርዳት የሚናገሩትን የሚከተሉትን ተጨማሪ ጥቅሶች አንብቡ:- ምሳሌ 3:27, 28፤ ሮም 15:1, 2፤ ገላትያ 6:2