ምዕራፍ 5
“ልጄ ይህ ነው”
ልጆች ጥሩ ነገር ሲሠሩ ወላጆቻቸው ይደሰታሉ። አንዲት ልጅ አንድን ነገር ጥሩ አድርጋ ስትሠራ አባቷ “እሷኮ የኔ ልጅ ናት” ብሎ በኩራት ይናገራል። ወይም አንድ ልጅ ጥሩ ነገር ሲሠራ አባቱ “እሱኮ የኔ ልጅ ነው” ብሎ መናገር ያስደስተዋል።
ኢየሱስ ሁልጊዜ አባቱን የሚያስደስት ነገር ያደርጋል። ስለዚህ አባቱ በእሱ ደስ ይለዋል። አንድ ቀን ኢየሱስ ከሦስት ተከታዮቹ ጋር በነበረበት ጊዜ አባቱ ምን እንዳደረገ ታስታውሳለህ?— አዎ፣ የኢየሱስ ተከታዮች እየሰሙት “በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ ከሰማይ ተናግሯል።—ማቴዎስ 17:5
ኢየሱስ ሁልጊዜ አባቱ የሚደሰትበትን ነገር ማድረግ ያስደስተዋል። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? አባቱን በጣም ስለሚወድ ነው። አንድ ሰው ሳይወድ በግድ አንድ ነገር እንዲያደርግ ቢታዘዝ የታዘዘውን ማድረግ ከባድ ይሆንበታል። ፈቃደኛ ከሆነ ግን የታዘዘውን ማድረግ ቀላል ይሆንለታል። ፈቃደኛ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?— ፈቃደኛ መሆን ማለት አንድን ነገር ለማድረግ ከልብ መፈለግ ማለት ነው።
ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊትም እንኳን አባቱ ያዘዘውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር። ፈቃደኛ የሆነው አባቱን ማለትም ይሖዋ አምላክን ስለሚወደው ነው። ኢየሱስ በሰማይ ከአባቱ ጋር በክብር ይኖር ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ ለኢየሱስ አንድ ልዩ ሥራ አዘጋጅቶለት ነበር። ኢየሱስ ይህን ሥራ ለመሥራት ሰማይን ትቶ መምጣት ነበረበት። በምድር ላይ ሕፃን ሆኖ መወለድ ነበረበት። ኢየሱስ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነው ይሖዋ ይህን እንዲያደርግ ስለፈለገ ነው።
ኢየሱስ በምድር ላይ ሕፃን ሆኖ እንዲወለድ እናት ያስፈልገው ነበር። የኢየሱስ እናት ማን እንደሆነች ታውቃለህ?— ማርያም ትባላለች። ይሖዋ ማርያምን እንዲያነጋግራት መልአኩን ገብርኤልን ከሰማይ ላከው። ገብርኤል
ለማርያም ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ነገራት። የሕፃኑ ስም ኢየሱስ ይባላል። የሕፃኑ አባትስ ማን ሊሆን ነው?— የሕፃኑ አባት ይሖዋ አምላክ እንደሚሆን መልአኩ ተናገረ። ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ተብሎ የሚጠራው ለዚህ ነው።በዚህ ጊዜ ማርያም ምን የተሰማት ይመስልሃል?— “የኢየሱስ እናት መሆን አልፈልግም” ብላ ይሆን? በፍጹም፤ ማርያም አምላክ የፈለገውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ነበረች። ይሁን እንጂ በሰማይ የነበረው የአምላክ ልጅ በምድር ላይ ሕፃን ሆኖ ሊወለድ የሚችለው እንዴት ነው? የኢየሱስ አወላለድ ከሌሎች ሕፃናት አወላለድ የተለየ የሆነውስ እንዴት ነው? ይህን ታውቃለህ?—
አምላክ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የሆኑትን አዳምና ሔዋንን ልዩ በሆነ መንገድ አንድ ላይ እንዲኖሩ አድርጎ ፈጠራቸው። በመሆኑም ከጊዜ በኋላ በእናቲቱ ሆድ ውስጥ ሕፃን ማደግ ሊጀምር ይችላል። ሰዎች ይህ ተአምር ነው ይላሉ። አንተም በዚህ እንደምትስማማ እርግጠኛ ነኝ።
አምላክ ከዚህም የበለጠ አስደናቂ የሆነ ተአምር ፈጸመ። የልጁን ሕይወት ከሰማይ ወስዶ ማርያም ሆድ ውስጥ አስገባው። አምላክ ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ ወዲህ እንደዚህ ያለ ነገር አድርጎ አያውቅም። ሌሎች ሕፃናት በእናቶቻቸው ሆድ ውስጥ እንደሚያድጉ ሁሉ ኢየሱስም በዚህ ተአምር አማካኝነት በማርያም ሆድ ውስጥ ማደግ ጀመረ። ከዚያ በኋላ ማርያም ዮሴፍን አገባች።
ኢየሱስ የሚወለድበት ጊዜ ሲደርስ ማርያምና ዮሴፍ ወደ ቤተልሔም ከተማ ሄደው ነበር። ሆኖም በቤተልሔም ከተማ ውስጥ በጣም ብዙ ሰው ነበር። ማርያምና ዮሴፍ የሚያርፉበት አንድ ክፍል እንኳን ማግኘት ስላልቻሉ
እንስሳት በሚመገቡበት ቤት ለማረፍ ተገደዱ። እዚያ እያሉ ማርያም ኢየሱስን ወለደችና በሥዕሉ ላይ እንደምታየው ኢየሱስን ግርግም ውስጥ አስተኛችው። ግርግም ላሞችና ሌሎች እንስሳት የሚመገቡት ምግብ የሚቀመጥበት ቦታ ነው።ኢየሱስ በተወለደበት ሌሊት አስገራሚ ነገሮች ተፈጽመው ነበር። በቤተልሔም አቅራቢያ እረኞች በግ እየጠበቁ ሳሉ አንድ መልአክ ታያቸው። መልአኩ ኢየሱስ ታላቅ ሰው እንደሚሆን ለእረኞቹ ነገራቸው። መልአኩ ‘እነሆ፣ ሰዎችን ሁሉ የሚያስደስት ምሥራች እነግራችኋለሁ፤ ዛሬ ሰዎችን የሚያድን አንድ ሰው ተወልዷል’ አላቸው።—ሉቃስ 2:10, 11
መልአኩ ለእረኞቹ ኢየሱስን በቤተልሔም በግርግም ተኝቶ እንደሚያገኙት ነገራቸው። ከዚያም በድንገት ሌሎች የሰማይ መላእክት ከመጀመሪያው መልአክ ጋር ሆነው አምላክን ሲያመሰግኑ ታዩ። መላእክቱ “ለአምላክ ክብር ሉቃስ 2:12-14
ይሁን፤ በምድርም አምላክ ለሚወዳቸው ሰዎች ሰላም ይሁን” በማለት ዘመሩ።—መላእክቱ ሲሄዱ እረኞቹ ወደ ቤተልሔም ሄደው ኢየሱስን አገኙት። ከዚያም የሰሙትን ጥሩ ነገር ሁሉ ለዮሴፍና ለማርያም ነገሯቸው። ማርያም የኢየሱስ እናት ለመሆን ፈቃደኛ በመሆኗ ምን ያህል ተደስታ እንደሚሆን መገመት ትችላለህ?
በኋላም ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስን ወደ ናዝሬት ከተማ ይዘውት ሄዱ። ኢየሱስ ያደገው በናዝሬት ነው። ኢየሱስ ካደገ በኋላ ታላቅ የማስተማር ሥራ ጀመረ። ይሖዋ አምላክ ልጁ በምድር ላይ እንዲያከናውናቸው ከሚፈልጋቸው ሥራዎች አንዱ ይህ ሥራ ነበር። ኢየሱስ በሰማይ ያለውን አባቱን በጣም ስለሚወደው ይህን ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ ነበር።
ማቴዎስ 3:17) ወላጆችህ እንደሚወዱህ ሲነግሩህ ደስ አይልህም?— ኢየሱስም አባቱ እንደሚወደው ሲናገር ሲሰማ እንደተደሰተ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
ኢየሱስ ታላቅ አስተማሪ ሆኖ የሚሠራውን ሥራ ከመጀመሩ በፊት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄዶ በመጥምቁ ዮሐንስ ተጠምቋል። እዚያ እያለ አንድ የሚያስገርም ነገር ተፈጸመ! ኢየሱስ ከውኃው ሲወጣ ይሖዋ ከሰማይ “በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ ተናገረ። (ኢየሱስ ሁልጊዜ ትክክል የሆነውን ነገር ያደርግ ነበር። ያልሆነውን ሆኖ በመታየት ለማስመሰል አልሞከረም። ለሰዎች ‘እኔ አምላክ ነኝ’ ብሎ አልተናገረም። መልአኩ ገብርኤል ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ይባላል ብሎ ለማርያም ነግሯታል። ኢየሱስ ራሱም የአምላክ ልጅ እንደሆነ ተናግሯል። በተጨማሪም ለሰዎች ‘እኔ ከአባቴ ይበልጥ አውቃለሁ’ ብሎ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ ‘አባቴ ከእኔ ይበልጣል’ ብሏል።—ዮሐንስ 14:28
ኢየሱስ በሰማይ እያለም እንኳ አባቱ እንዲሠራ ያዘዘውን ሥራ ሁሉ ይሠራ ነበር። እሺ እሠራለሁ ብሎ ከተናገረ በኋላ የተሰጠውን ሥራ ትቶ ሌላ ነገር አይሠራም ነበር። ኢየሱስ አባቱን በጣም ይወዳል። ስለዚህ አባቱ የሚነግረውን ሁሉ ይሰማል። ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣ በኋላም በሰማይ ያለው አባቱ ያዘዘውን ሥራ ሠርቷል። አባቱ ያላዘዘውን ነገር በመሥራት ጊዜውን አላጠፋም። ይህ ሁሉ ሲታይ ይሖዋ በልጁ የሚደሰት መሆኑ ምንም አያስገርምም!
እኛም ይሖዋን ማስደሰት እንፈልጋለን፣ አይደል?— ስለዚህ ኢየሱስ እንዳደረገው እኛም አምላክን ከልብ የምንሰማ መሆናችንን ማሳየት አለብን። አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ምን ማድረግ እንዳለብን ይነግረናል። አምላክ የሚለንን የምንሰማ እያስመሰልን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይስማማ ነገር ብናምንና ብንሠራ ትክክል ይመስልሃል?— ደግሞም ይሖዋን በእርግጥ የምንወደው ከሆነ እሱን ማስደሰት እንደምንፈልግ አስታውስ።
አሁን ስለ ኢየሱስ ምን ማወቅና ማመን እንደሚያስፈልገን የሚገልጹትን የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አንብቡ:- ማቴዎስ 7:21-23፤ ዮሐንስ 4:25, 26፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6