በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 16

ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምንድን ነው?

ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምንድን ነው?

ይህ ሰው የነበረው ችግር ምንድን ነው?

አንድ ቀን፣ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ መጣ። ሰውየው ኢየሱስ በጣም ጥበበኛ እንደሆነ ያውቅ ስለነበር ‘መምህር፣ ወንድሜ ያለውን ነገር እንዲያካፍለኝ ንገረው’ አለው። ይህ ሰው ወንድሙ ካለው ነገር ላይ የተወሰነውን እሱ ማግኘት እንዳለበት ተሰምቶታል።

አንተ በኢየሱስ ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?— ኢየሱስ ይህ ሰው ችግር እንዳለበት ተገንዝቧል። ይሁን እንጂ ችግሩ ወንድሙ ያለውን ነገር ለማግኘት መፈለጉ አልነበረም። የሰውየው ችግር በሕይወት ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምን እንደሆነ አለማወቁ ነበር።

እስቲ አስበው። ለእኛ ይበልጥ አስፈላጊ ሊሆን የሚገባው ነገር ምንድን ነው? ለእኛ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑት ደስ የሚሉ መጫወቻዎች፣ አዳዲስ ልብሶች ወይም እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች ናቸው?— በፍጹም፤ ከእነዚህ ነገሮች ይበልጥ በጣም አስፈላጊ የሆነ ሌላ ነገር አለ። ኢየሱስም ሊያስተምር የፈለገው ይህንኑ ነው። ስለዚህ አምላክን ስለረሳ አንድ ሰው የሚገልጽ ታሪክ ተናገረ። ታሪኩን መስማት ትፈልጋለህ?—

ይህ ሰው በጣም ሀብታም ነበር። እርሻና ጎተራ ነበረው። የዘራው እህል በጥሩ ሁኔታ አፍርቶ ነበር። ሆኖም የሚሰበስበውን እህል የሚያከማችበት በቂ ጎተራ አልነበረውም። ታዲያ ምን ያደርግ ይሆን? ሰውየው በልቡ ‘ያሉኝን ጎተራዎች አፍርሼ ትልልቅ ጎተራዎች እሠራለሁ። ከዚያም እህሌንና ያሉኝን ጥሩ ነገሮች ሁሉ በአዲሶቹ ጎተራዎች አከማቻለሁ’ ብሎ አሰበ።

ሀብታሙ ሰው ትክክለኛ ነገር እንዳደረገ ተሰምቶት ነበር። ብዙ ሀብት ስላከማቸ በጣም ጥበበኛ የሆነ መሰለው። ስለዚህ በልቡ ‘ብዙ ጥሩ ነገር አከማችቻለሁ። ለብዙ ዓመት ይበቃኛል። ስለዚህ እንደ ልቤ መዝናናት እችላለሁ። እበላለሁ፣ እጠጣለሁ፣ ራሴንም አስደስታለሁ’ ብሎ አሰበ። ይሁን እንጂ ይህ ሀብታም ሰው ተሳስቶ ነበር። ስህተቱ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?— የሚያስበው ስለራሱና ስለሚያገኘው ደስታ ብቻ ነበር። አምላክን ግን ረስቶት ነበር።

ይህ ሀብታም ሰው ምን እያሰበ ነው?

ስለዚህ አምላክ ሀብታሙን ሰው እንዲህ አለው:- ‘አንተ ሞኝ፣ ዛሬ ሌሊት ትሞታለህ። ያከማቸኸው ሀብት ለማን ይሆናል?’ ይህ ሀብታም ሰው ያከማቸውን ሀብት ከሞተ በኋላ ሊጠቀምበት ይችላል?— በፍጹም፣ ሀብቱን በሙሉ ሌላ ሰው ይወስደዋል። ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ለራሱ ሀብት የሚያከማች በአምላክ ዘንድ ግን ሀብታም ያልሆነ ሰው መጨረሻው ይኸው ነው።”—ሉቃስ 12:13-21

እንደ ሀብታሙ ሰው መሆን አትፈልግም፣ አይደል?— ሀብታሙ ሰው በሕይወቱ ውስጥ፣ ዋና ዓላማው ቁሳዊ ነገር ወይም ሀብት ማግኘት ብቻ ነበር። ይህ ደግሞ ስህተት ነበር። ሁልጊዜ ተጨማሪ ነገሮችን ለማግኘት ይፈልግ ነበር። “በአምላክ ዘንድ ግን ሀብታም” አልነበረም።

ብዙ ሰዎች እንደ ሀብታሙ ሰው ናቸው። ሁልጊዜ ተጨማሪ ነገር ማግኘት ይፈልጋሉ። ይህ ግን ትልቅ ችግር ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ መጫወቻዎች አሉህ፣ አይደል?— ምን ምን መጫወቻዎች አሉህ? እስቲ ንገረኝ።— ከጓደኞችህ አንዱ አንተ የሌለህ ኳስ ወይም አሻንጉሊት ወይም ሌላ ነገር ቢኖረውስ? ለአንተም ወላጆችህ እንዲገዙልህ ማስቸገር ጥሩ ይመስልሃል?—

አንዳንድ ጊዜ መጫወቻ በጣም አስፈላጊ ነገር ሊመስል ይችላል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን መጫወቻው ምን ይሆናል?— ያረጃል። ሊወላልቅና አንተም ከዚያ ወዲያ ላትፈልገው ትችላለህ። ይሁንና ከመጫወቻ ይበልጥ እጅግ ውድ የሆነ ነገር አለህ። ምን እንደሆነ ታውቃለህ?—

ከመጫወቻዎች የሚበልጥ ምን ውድ ነገር አለህ?

ሕይወትህ ነው። ሕይወትህ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ሕይወት ከሌለህ ምንም ነገር ማድረግ አትችልም። ይሁንና ሕይወትህ የተመካው አምላክን የሚያስደስተውን ነገር በማድረግ ላይ ነው፤ አይመስልህም?— ስለዚህ አምላክን እንደረሳው እንደሞኙ ሰው መሆን የለብንም።

እንደ ሀብታሙ ሰው የሞኝነት ሥራ ሊሠሩ የሚችሉት ልጆች ብቻ አይደሉም። ብዙ ትልልቅ ሰዎችም የሞኝነት ሥራ ይሠራሉ። አንዳንዶቹ ትልልቅ ሰዎች ሁልጊዜ ባላቸው ሀብት ላይ ሌላ ሀብት መጨመር ይፈልጋሉ። ለዕለቱ የሚሆን ምግብ፣ የሚለብሱት ልብስ ወይም የሚኖሩበት ቤት ይኖራቸው ይሆናል። ቢሆንም ተጨማሪ ነገር ለማግኘት ይፈልጋሉ። ብዙ ልብስ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። እንዲሁም ትልልቅ ቤቶች እንዲኖሯቸው ይፈልጋሉ። እነዚህን ነገሮች ለማግኘት ደግሞ ገንዘብ ያስፈልጋል። ስለዚህ ብዙ ገንዘብ ለማግኘት በጣም ይሠራሉ። ብዙ ገንዘብ ባገኙ ቁጥር ደግሞ ተጨማሪ ነገር ለማግኘት ይፈልጋሉ።

አንዳንድ ትልልቅ ሰዎች ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ በጣም ስለሚሠሩ ከቤተሰባቸው ጋር ለመሆን እንኳ ጊዜ ያጣሉ። ለአምላክም ቢሆን ጊዜ የላቸውም። ታዲያ ገንዘባቸው በሕይወት ሊያኖራቸው ይችላል?— በፍጹም አይችልም። ከሞቱ በኋላ ገንዘባቸውን ሊጠቀሙበት ይችላሉ?— በፍጹም። ምክንያቱም የሞቱ ሰዎች ምንም ነገር መሥራት አይችሉም።—መክብብ 9:5, 10

ታዲያ ይህ ሲባል ገንዘብ ቢኖረን ስህተት ነው ማለት ነው?— ስህተት ነው ማለት አይደለም። በገንዘብ ምግብና ልብስ ልንገዛ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብ ጥበቃ እንደሚያስገኝ ይናገራል። (መክብብ 7:12) ይሁን እንጂ ገንዘብ የምንወድ ከሆነ ከባድ ችግር ያመጣብናል። ለራሱ ሀብት እንዳከማቸውና በአምላክ ዘንድ ግን ሀብታም እንዳልነበረው እንደ ሞኙ ሰው እንሆናለን።

በአምላክ ዘንድ ሀብታም መሆን ምን ማለት ነው?— በአምላክ ዘንድ ሀብታም መሆን ማለት በሕይወታችን ውስጥ ለአምላክ አንደኛ ቦታ መስጠት ማለት ነው። አንዳንድ ሰዎች በአምላክ እንደሚያምኑ ይናገራሉ። የሚያስፈልገው ነገር በአምላክ ማመን ብቻ ይመስላቸዋል። ሆኖም እነዚህ ሰዎች በእርግጥ በአምላክ ዘንድ ሀብታም ናቸው?— በፍጹም፣ እነሱ አምላክን እንደረሳው እንደ ሀብታሙ ሰው ናቸው።

ኢየሱስ በሰማይ ያለውን አባቱን በፍጹም ረስቶ አያውቅም። ብዙ ገንዘብ ለማግኘት አልሞከረም። ብዙ ቁሳዊ ነገሮችም አልነበሩትም። ኢየሱስ በሕይወት ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምን እንደሆነ ያውቅ ነበር። አንተስ በሕይወት ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ?— በአምላክ ዘንድ ሀብታም መሆን ነው።

ይህች ልጅ እያደረገችው ያለው ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር ምንድን ነው?

እስቲ ንገረኝ፣ በአምላክ ዘንድ ሀብታም መሆን የምንችለው እንዴት ነው?— በአምላክ ዘንድ ሀብታም መሆን የምንችለው እሱን የሚያስደስት ነገር በማድረግ ነው። ኢየሱስ ‘ሁልጊዜ እሱን ደስ የሚያሰኘውን አደርጋለሁ’ ብሏል። (ዮሐንስ 8:29) አምላክ እሱ እንድናደርግ የሚፈልገውን ነገር ስናደርግ ደስ ይለዋል። እስቲ ንገረኝ፣ አምላክን ለማስደሰት ምን ልታደርግ ትችላለህ?— አዎ፣ አምላክን ለማስደሰት መጽሐፍ ቅዱስን ልታነብ፣ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ልትሄድ፣ ወደ አምላክ ልትጸልይና ሌሎች ስለ እሱ እንዲማሩ ልትረዳ ትችላለህ። በሕይወት ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች እነዚህ ናቸው።

ኢየሱስ በአምላክ ዘንድ ሀብታም ስለነበረ ይሖዋ ይንከባከበው ነበር። ይሖዋ ለኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ሽልማት ሰጥቶታል። እኛም እንደ ኢየሱስ ከሆን ይሖዋ ይወደናል፤ እንዲሁም ይንከባከበናል። ስለዚህ እንደ ኢየሱስ መሆን አለብን እንጂ አምላክን እንደረሳው እንደዚያ ሀብታም ሰው ፈጽሞ መሆን የለብንም።

ለቁሳዊ ነገሮች ተገቢ አመለካከት ሊኖረን የሚችለው እንዴት እንደሆነ ከሚገልጹት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው:- ምሳሌ 23:4፤ 28:20፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:6-10፤ ዕብራውያን 13:5