በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 39

አምላክ ልጁን አልረሳውም

አምላክ ልጁን አልረሳውም

ኢየሱስ ጓደኛው አልዓዛር በሞተ ጊዜ አልቅሶ ነበር። ኢየሱስ ተሠቃይቶ ሲሞት አምላክ ምን የተሰማው ይመስልሃል?— መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ አንዳንድ ሁኔታዎች ‘ሊያስቆጡት’ አልፎ ተርፎም ‘እንዲያዝን’ ሊያደርጉት እንደሚችሉ ይናገራል።—መዝሙር 78:40, 41፤ ዮሐንስ 11:35

ይሖዋ በጣም የሚወደው ልጁ ሲሞት ባየ ጊዜ ምን ያህል እንዳዘነ መገመት ትችላለህ?— ኢየሱስ አምላክ እንደማይረሳው እርግጠኛ ነበር። ሊሞት ሲል “አባት ሆይ፣ [ሕይወቴን] በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” የሚሉትን የመጨረሻ ቃላት የተናገረው ለዚህ ነበር።—ሉቃስ 23:46

ኢየሱስ ከሞት እንደሚነሳና “በሲኦል” ወይም በመቃብር ውስጥ እንደማይቀር እርግጠኛ ነበር። ኢየሱስ ከሙታን ከተነሳ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ “ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ” በማለት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ኢየሱስ የተጻፈውን ጠቅሶ ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 2:31 የ1954 ትርጉም፤ መዝሙር 16:10) የኢየሱስ አስከሬን በመቃብር ውስጥ በስብሶ እስኪሸት ድረስ አልቆየም።

እንዲያውም ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ለደቀ መዛሙርቱ ሞቶ ብዙ እንደማይቆይ ነግሯቸው ነበር። ‘እንደሚገደልና በሦስተኛው ቀን እንደሚነሳ’ ገልጾላቸው ነበር። (ሉቃስ 9:22) ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ በሚነሳበት ጊዜ መደነቅ አልነበረባቸውም። ግን እነሱ ተደንቀው ነበር?— እስቲ እንመልከት።

ታላቁ አስተማሪ በመከራ እንጨት ላይ የሞተው ዓርብ ከሰዓት በኋላ በዘጠኝ ሰዓት ገደማ ነበር። ዮሴፍ የሚባል የሳንሄድሪን አባል የነበረ ሀብታም ሰው በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበር። ይህ ሰው ኢየሱስ መሞቱን ሲሰማ ወደ ሮማዊው ገዥ ወደ ጲላጦስ ሄደ። የኢየሱስን አስከሬን ከተሰቀለበት እንጨት ላይ አውርዶ ለመቅበር እንዲፈቅድለት ለመነው። ከዚያ በኋላ ዮሴፍ የኢየሱስን አስከሬን ተሸክሞ በአንድ የአትክልት ቦታ ወደሚገኝ መቃብር ወሰደው።

የኢየሱስ አስከሬን መቃብር ውስጥ ከተቀመጠ በኋላ መግቢያው በአንድ ትልቅ ድንጋይ ተዘጋ። ይህ ከሆነ በኋላ ሦስተኛው ቀን ማለትም እሁድ ደረሰ። ቀኑ ገና ስላልነጋ ጨለማ ነበር። ሰዎች መቃብሩን እየጠበቁ ነው። መቃብሩን እንዲጠብቁ የላኳቸው የካህናት አለቆቹ ናቸው። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?—

ካህናቱም ጭምር ኢየሱስ ከሞት እንደሚነሳ መናገሩን ሰምተው ነበር። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ አስከሬኑን ሰርቀው ከወሰዱ በኋላ ተነሳ ብለው እንዳያስወሩ ለማድረግ ሲሉ በወታደሮቹ አስጠበቁ። ድንገት መሬቱ መንቀጥቀጥ የጀመረ ከመሆኑም በላይ በጨለማው ውስጥ ብርሃን ታየ። የይሖዋ መልአክ ነበር! ወታደሮቹ በጣም ስለፈሩ መንቀሳቀስ እንኳ አልቻሉም። መልአኩ ወደ መቃብሩ ሄዶ ድንጋዩን አንከባለለው። መቃብሩ ባዶ ነበር!

መቃብሩ ባዶ የሆነው ለምንድን ነው? የተፈጸመውስ ነገር ምንድን ነው?

አዎ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ ከጊዜ በኋላ እንደተናገረው “ይህን ኢየሱስን አምላክ ከሞት አስነሳው።” (የሐዋርያት ሥራ 2:32) አምላክ፣ ኢየሱስን ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የነበረውን ዓይነት አካል በመስጠት ሕያው አድርጎታል። መላእክት ያላቸውን ዓይነት መንፈሳዊ አካል ይዞ ከሞት ተነስቷል። (1 ጴጥሮስ 3:18) ስለዚህ ሰዎች ኢየሱስን እንዲያዩት ከተፈለገ ሥጋዊ አካል መልበስ ያስፈልገዋል። ታዲያ ይህን አድርጎ ነበር?— እስቲ እንመልከት።

አሁን ሌሊቱ ነግቶ ፀሐይ ወጥታለች። መቃብሩን እንዲጠብቁ የተመደቡት ወታደሮች ሄደዋል። መግደላዊት ማርያምና ሌሎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሆኑ ሴቶች ወደ መቃብሩ እየሄዱ ነው። እርስ በርሳቸው ‘በመታሰቢያ መቃብሩ ደጃፍ ላይ ያለውን ያን ከባድ ድንጋይ ማን ያንከባልልልናል?’ ይባባሉ ነበር። (ማርቆስ 16:3) ይሁን እንጂ መቃብሩ ጋር ሲደርሱ ድንጋዩ ተንከባሎ አገኙት። መቃብሩ ደግሞ ባዶ ነበር! የኢየሱስ አስከሬን የለም! ወዲያውኑ መግደላዊት ማርያም አንዳንዶቹን የኢየሱስ ሐዋርያት ለማግኘት እየሮጠች ሄደች።

ሌሎቹ ሴቶች እዚያው መቃብሩ አጠገብ ቆዩ። ‘የኢየሱስ አስከሬን የት ሊሆን ይችላል?’ ብለው አሰቡ። በድንገት የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች ታዩአቸው። እነዚህ ሰዎች መላእክት ነበሩ! እነሱም ሴቶቹን ‘እዚህ ኢየሱስን የምትፈልጉት ለምንድን ነው? እሱ ተነስቷል። ቶሎ ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሯቸው’ አሏቸው። ሴቶቹ ምን ያህል እየሮጡ እንደሄዱ መገመት ትችላለህ! በመንገዳቸው ላይ ደግሞ አንድ ሰው አገኙ። ያገኙት ሰው ማን እንደሆነ ታውቃለህ?—

ኢየሱስ ነው፤ ሥጋዊ አካል ለብሶ ታያቸው። ሴቶቹንም ‘ሂዱና ለደቀ መዛሙርቴ ንገሯቸው’ አላቸው። ሴቶቹ በጣም ተደስተዋል። ደቀ መዛሙርቱን ፈልገው አገኟቸውና ‘ኢየሱስ ተነስቷል! እኛም አይተነዋል!’ ብለው ነገሯቸው። ማርያም ቀደም ብላ ለጴጥሮስና ለዮሐንስ መቃብሩ ባዶ እንደሆነ ነግራቸው ነበር። በሥዕሉ ላይ እንደምትመለከተው እነሱም መቃብሩን ሊያዩ መጡ። ኢየሱስ ተጠቅልሎበት የነበረውን ጨርቅ ሲያዩ ግራ ገባቸው። ኢየሱስ እንደገና ሕያው ሆኗል ብለው ለማመን የፈለጉ ቢሆንም ሁኔታው ለማመን የሚከብድ ሆነባቸው።

ጴጥሮስና ዮሐንስ ምን እያሰቡ ሊሆን ይችላል?

በዚያው ዕለት ትንሽ ቆየት ብሎ ኢየሱስ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር እየተጓዙ ለነበሩ ሁለት ደቀ መዛሙርቱ ታያቸው። ኢየሱስ ከእነሱ ጋር እየሄደ ያነጋግራቸው ነበር፤ ሆኖም የለበሰው የቀድሞውን ሥጋዊ አካል ስላልሆነ አላወቁትም ነበር። ኢየሱስ ከእነሱ ጋር ምግብ ለመብላት እስከጸለየበት ጊዜ ድረስ አላወቁትም ነበር። ደቀ መዛሙርቱ በጣም በመደሰታቸው ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቃ ወደምትገኘው ወደ ኢየሩሳሌም በፍጥነት ተመለሱ! ኢየሱስ ሕያው መሆኑን ለጴጥሮስ ለማሳየት የተገለጠለት ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሊሆን ይችላል።

ከዚያም በዚያው ዕለት ማለትም እሁድ ምሽት ብዙ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በአንድ ክፍል ውስጥ ተሰብስበው ነበር። በሮቹ ተቆልፈዋል። ኢየሱስ እዚያው ክፍል ውስጥ በመካከላቸው ድንገት ብቅ አለ! በዚህ ጊዜ ታላቁ አስተማሪ በእርግጥ እንደገና ሕያው እንደሆነ አወቁ። ምን ያህል እንደተደሰቱ አስበው!—ማቴዎስ 28:1-15፤ ሉቃስ 24:1-49፤ ዮሐንስ 19:38 እስከ 20:21

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሕያው መሆኑን ለማሳየት ለ40 ቀናት ያህል የተለያየ ሥጋዊ አካል በመልበስ ተገለጠላቸው። ከዚያም ምድርን ትቶ ወደ አባቱ ወደ ሰማይ ተመለሰ። (የሐዋርያት ሥራ 1:9-11) ደቀ መዛሙርቱም ወዲያውኑ ላገኙት ሰው ሁሉ አምላክ ኢየሱስን ከሞት እንዳስነሳው መናገር ጀመሩ። ካህናቱ ቢደበድቧቸውም እንዲሁም አንዳንዶቹን ቢገድሏቸውም እንኳን መስበካቸውን አላቋረጡም። ቢሞቱ እንኳን አምላክ ልጁን እንዳልረሳው ሁሉ እነሱንም እንደማይረሳቸው ያውቃሉ።

አብዛኞቹ ሰዎች ኢየሱስ ከሞት የተነሳበት ወቅት ሲደርስ የሚያስቡት ስለ ምን ነገር ነው? አንተስ የምታስበው ስለ ምንድን ነው?

እነዚያ የቀድሞ የኢየሱስ ተከታዮች በዛሬው ጊዜ ካሉት አብዛኞቹ ሰዎች በጣም የተለዩ ናቸው! በዛሬው ጊዜ በአንዳንድ አገሮች አብዛኞቹ ሰዎች ኢየሱስ ከሞት የተነሳበትን ጊዜ በሚያከብሩበት ወቅት የሚያስቡት ስለ በዓለ ትንሣኤ ጥንቸሎችና ቀለም ስለተቀቡ እንቁላሎች ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ስለ በዓለ ትንሣኤ ጥንቸሎችና እንቁላሎች ምንም የሚናገረው ነገር የለም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው አምላክን ስለማገልገል ነው።

ስለዚህ እኛ አምላክ ልጁን ከሞት ባስነሳበት ጊዜ ስላደረገው አስደናቂ ነገር ለሰዎች በመናገር እንደ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መሆን እንችላለን። ይህን በምናደርግበት ጊዜ ሰዎች እንደሚገድሉን ቢዝቱብን እንኳን ፈጽሞ መፍራት የለብንም። ብንሞት እንኳን ይሖዋ ኢየሱስን እንዳስነሳው እኛንም አስታውሶ ከሞት ያስነሳናል።

አምላክ የሚያገለግሉትን ሰዎች እንደማይረሳ አልፎ ተርፎም ከሞት እንደሚያስነሳቸው ማወቅ አያስደስትም?— እነዚህን ነገሮች ማወቃችን አምላክን ማስደሰት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ እንድንነሳሳ ሊያደርገን ይገባል። በእርግጥ አምላክን ማስደሰት እንደምንችል ታውቃለህ?— በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ስለዚህ ጉዳይ እንወያያለን።

በኢየሱስ ትንሣኤ ማመናችን ተስፋችንንና እምነታችንን ሊያጠነክረው ይገባል። እባካችሁ የሐዋርያት ሥራ 2:22-36፤ 4:18-20 እና 1 ቆሮንቶስ 15:3-8, 20-23ን አንብቡ።