በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 12

ኢየሱስ እንድንጸልይ አስተምሮናል

ኢየሱስ እንድንጸልይ አስተምሮናል

ይሖዋ አምላክን ታናግረዋለህ?— ይሖዋ እንድታናግረው ይፈልጋል። አምላክን በምታናግርበት ጊዜ እየጸለይክ ነው ማለት ነው። ኢየሱስ ብዙ ጊዜ በሰማይ ያለውን አባቱን ያነጋግረው ነበር። አንዳንድ ጊዜ አምላክን ሲያናግር ብቻውን መሆን ይፈልግ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ወቅት ኢየሱስ ‘ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ እንደወጣና በጣም መሽቶ የነበረ ቢሆንም በዚያ ብቻውን እንደቆየ’ ይናገራል።—ማቴዎስ 14:23

ብቻህን ወደ ይሖዋ ለመጸለይ ወዴት መሄድ ትችላለህ?— ምናልባት ማታ ከመተኛትህ በፊት ብቻህን ሆነህ ይሖዋን ማናገር ትችላለህ። ኢየሱስ ‘ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በርህንም ዘግተህ ወደ አባትህ ጸልይ’ ብሏል። (ማቴዎስ 6:6) በየቀኑ ማታ ማታ ከመተኛትህ በፊት ወደ ይሖዋ ትጸልያለህ?— መጸለይ ይኖርብሃል።

ኢየሱስ ብቻውን . . . እንዲሁም ከሌሎች ጋር ሆኖ ጸልዮአል

ኢየሱስ ሌሎች ሰዎች አብረውት በነበሩበት ጊዜም ጸልዮአል። ኢየሱስ ጓደኛው አልዓዛር በሞተ ጊዜ በመቃብሩ ቦታ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆኖ ጸልዮአል። (ዮሐንስ 11:41, 42) በተጨማሪም ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ስብሰባ በሚያደርግበት ጊዜ ይጸልይ ነበር። አንተስ ጸሎት ወደሚደረግባቸው ስብሰባዎች ትሄዳለህ?— አብዛኛውን ጊዜ በስብሰባው ላይ የሚጸልየው ትልቅ ሰው ነው። በስብሰባው ላይ የሚጸልየው ሰው በአንተ ፋንታ ሆኖ አምላክን ስለሚያናግር የሚለውን ነገር በደንብ አዳምጥ። በደንብ ካዳመጥክ ጸሎቱ ሲያበቃ “አሜን” ማለት ትችላለህ። በጸሎት መጨረሻ ላይ “አሜን” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?— አንተም ጸሎቱን ወደኸዋል ማለት ነው። በጸሎቱ እንደምትስማማና የአንተም ጸሎት እንዲሆን እንደምትፈልግ ያሳያል።

በስብሰባ ላይ የሚቀርቡ ጸሎቶችን በደንብ ማዳመጥ የሚኖርብህ ለምንድን ነው?

ኢየሱስ በምግብ ሰዓትም ይጸልይ ነበር። ለምግቡ ይሖዋን ያመሰግን ነበር። ሁልጊዜ ምግብ ከመብላትህ በፊት ትጸልያለህ?— መብላት ከመጀመራችን በፊት ለምግቡ ይሖዋን ብናመሰግን ጥሩ ነው። ከሌሎች ጋር ሆነህ ስትበላ የሚጸልየው ሌላ ሰው ሊሆን ይችላል። ብቻህን ሆነህ በምትበላበት ጊዜስ? ወይም ደግሞ ይሖዋን ከማያመሰግኑ ሰዎች ጋር በምትበላበት ጊዜስ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?— በዚህ ጊዜ የራስህን ጸሎት ማቅረብ ይኖርብሃል።

ሁልጊዜ ድምፅ እያሰማህ መጸለይ ይኖርብሃል? ወይስ ድምፅ ሳታሰማ የምታቀርበውን ጸሎት ይሖዋ ሊሰማ ይችላል?— የዚህን ጥያቄ መልስ ነህምያ ካጋጠመው ሁኔታ መረዳት እንችላለን። ነህምያ በፋርሱ ንጉሥ በአርጤክስስ ቤተ መንግሥት ይሠራ የነበረ ሲሆን ይሖዋን የሚያመልክ ሰው ነበር። አንድ ቀን ነህምያ የራሱ ሕዝብ ዋና ከተማ የነበረችው የኢየሩሳሌም አጥር መፍረሱን በሰማ ጊዜ በጣም አዘነ።

ነህምያ እንዳደረገው ድምፅ ሳታሰማ ልትጸልይ የምትችለው መቼ ነው?

ንጉሡ ለምን እንዳዘነ ሲጠይቀው ነህምያ በመጀመሪያ ድምፁን ሳያሰማ ጸሎት አቀረበ። ከዚያም ነህምያ ለንጉሡ ያዘነበትን ምክንያት በመንገር ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ አጥሯን እንደገና ለመሥራት ፈቃድ ጠየቀ። ከዚያስ ምን ሆነ?—

አዎ፣ አምላክ የነህምያን ጸሎት መለሰለት። በመሆኑም ንጉሡ እንዲሄድ ፈቀደለት! እንዲያውም ንጉሡ ለአጥሩ መሥሪያ እንዲሆን ብዙ እንጨት ለነህምያ ሰጠው። ስለዚህ አምላክ ድምፅ ሳናሰማ የምናቀርባቸውን ጸሎቶችም እንኳን ሳይቀር ሰምቶ መልስ መስጠት ይችላል።—ነህምያ 1:2, 3፤ 2:4-8

አሁን ደግሞ የሚከተለውን ጉዳይ እንመልከት። ስትጸልይ ራስህን ጎንበስ ማድረግ ያስፈልግሃል? በጉልበትህ መንበርከክስ ይኖርብሃል? ምን ይመስልሃል?— ኢየሱስ አንዳንድ ጊዜ ሲጸልይ በጉልበቱ ይንበረከክ ነበር። ቆሞ የጸለየበትም ጊዜ አለ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለአልዓዛር ሲጸልይ እንዳደረገው ራሱን ወደ ሰማይ ቀና አድርጎ ይጸልይ ነበር።

ታዲያ ይህ ሁሉ ምን ያመለክታል?— አዎ፣ ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ዋናው ነገር የምትጸልይበት ሁኔታ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ጎንበስ ብለህና ዓይንህን ጨፍነህ ብትጸልይ ጥሩ ነው። ሌላ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ እንዳደረገው በጉልበትህ ተንበርክከህ መጸለይ ትፈልግ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ፣ ቀንም ሆነ ማታ በማንኛውም ጊዜ ወደ አምላክ መጸለይ እንደምንችልና እሱም እንደሚሰማን አስታውስ። ጸሎትን በሚመለከት ዋናው ነገር ይሖዋ እንደሚያዳምጠን ማመናችን ነው። ይሖዋ ጸሎትህን እንደሚሰማ ታምናለህ?—

ለአምላክ በጸሎት ምን ልትነግረው ትችላለህ?

ወደ ይሖዋ መጸለይ ያለብን ስለ ምን ነገሮች ነው?— እስቲ ንገረኝ፣ በምትጸልይበት ጊዜ ለይሖዋ የምትነግረው ምንድን ነው?— ይሖዋ ብዙ ጥሩ ነገሮችን ስለሰጠን ስለ እነዚህ ስጦታዎቹ እሱን ማመስገን ተገቢ ነው፣ አይደል?— ስለምንበላው ምግብ ልናመሰግነው እንችላለን። የሚያምር ሰማያዊ ቀለም ስላለው ሰማይ፣ ስለ ዛፎችና ውብ ስለሆኑት አበቦች አመስግነኸው ታውቃለህ?— እነዚህንም ነገሮች የሠራቸው እሱ ነው።

አንድ ጊዜ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው እንዲያስተምራቸው ጠይቀውት ነበር። ታላቁ አስተማሪም እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው ያስተማራቸው ሲሆን ሊጸልዩባቸው የሚገቡ አስፈላጊ ነገሮች ምን እንደሆኑም ገልጾላቸዋል። እነዚህ አስፈላጊ ነገሮች ምን እንደሆኑ ታውቃለህ?— መጽሐፍ ቅዱስህን ግለጥና ማቴዎስ ምዕራፍ 6⁠ን አውጣ። ከቁጥር 9 እስከ 13 ላይ ብዙ ሰዎች አባታችን ሆይ ወይም የጌታ ጸሎት በማለት የሚጠሩትን ጸሎት እናገኛለን። እስቲ አብረን እናንብበው።

እዚህ ላይ ኢየሱስ ስለ አምላክ ስም እንድንጸልይ እንዳስተማረን መረዳት እንችላለን። የአምላክ ስም እንዲቀደስ እንድንጸልይ ነግሮናል። የአምላክ ስም ማን ነው?— አዎ፣ ስሙ ይሖዋ ነው፤ እኛም ይህን ስም መውደድ ይኖርብናል።

በሁለተኛ ደረጃ፣ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ እንድንጸልይ አስተምሮናል። ይህ መንግሥት አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ለምድር ሰላም የሚያመጣ ከመሆኑም በላይ ምድርንም ገነት ያደርጋል።

በሦስተኛ ደረጃ፣ ታላቁ አስተማሪ የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በምድርም እንዲሆን መጸለይ እንዳለብን ተናግሯል። የአምላክ ፈቃድ በምድር እንዲሆን የምንጸልይ ከሆነ አምላክ የሚፈልግብንን ማድረግ ይኖርብናል።

ቀጥሎም ኢየሱስ በየቀኑ ስለሚያስፈልገን ምግብ እንድንጸልይ አስተምሮናል። በተጨማሪም ስህተት ስንሠራ በፈጸምነው ድርጊት ማዘናችንን ለአምላክ መንገር ይኖርብናል። እንዲሁም አምላክ ይቅር እንዲለን መለመን አለብን። ሆኖም አምላክ እኛን ይቅር ከማለቱ በፊት እኛም የበደሉን ሰዎች ካሉ ይቅር ማለት አለብን። የበደሉህን ይቅር ማለት ይከብድሃል?—

በመጨረሻም ይሖዋ አምላክ ከክፉው ከሰይጣን ዲያብሎስ እንዲጠብቀን መጸለይ እንደሚኖርብን ኢየሱስ ተናግሯል። ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ልንጸልይባቸው የሚገቡ ጥሩ ነገሮች ናቸው።

ይሖዋ ጸሎታችንን እንደሚሰማ ማመን ይኖርብናል። እንዲረዳን መለመን ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ ልናመሰግነው ይገባል። ጸሎታችን ከልብ የመነጨ ሲሆንና ተገቢ ስለሆኑ ነገሮች ስንለምነው ደስ ይለዋል። የለመንነውን ነገርም ይሰጠናል። ይህን ታምናለህ?—

ጸሎትን በተመለከተ ተጨማሪ ምክር ለማግኘት ሮም 12:12፤ 1 ጴጥሮስ 3:12 እና 1 ዮሐንስ 5:14ን አንብቡ።