በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 32

ኢየሱስ ጥበቃ ያገኘው እንዴት ነው?

ኢየሱስ ጥበቃ ያገኘው እንዴት ነው?

አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ትናንሾችንና ራሳቸውን መከላከል የማይችሉትን ለመጠበቅ ሲል አስደናቂ ነገሮች ያደርጋል። በገጠር አካባቢ በእግርህ ብትጓዝ ይሖዋ ይህን የሚያደርግበትን አንዱን መንገድ ትመለከት ይሆናል። ይሁን እንጂ መጀመሪያ ላይ ምን እየተፈጸመ እንዳለ ላይገባህ ይችላል።

አንዲት ወፍ አጠገብህ መሬት ላይ ስታርፍ ትመለከታለህ። ወፏ የተጎዳች ትመስላለች። ልትቀርባት ስትሞክር አንዱን ክንፏን እየጎተተች ትሸሻለች። ስትከተላት ፈጠን ፈጠን እያለች ትሄዳለች። ከዚያም በድንገት ተነስታ ትበራለች። ለካስ ክንፏ ምንም ጉዳት አልደረሰበትም! ወፏ ምን እያደረገች እንደነበረ ታውቃለህ?—

ወፏ መጥታ አንተ አጠገብ ባረፈችበት አካባቢ ጫጩቶቿ አትክልት ውስጥ ተደብቀዋል። ወፏ ጫጩቶቿን አግኝተህ ጉዳት እንዳታደርስባቸው ፈርታለች። ስለዚህ ጫጩቶቿ ካሉበት አካባቢ እንድትርቅላት መብረር ያቃታት በማስመሰል ከፊት ከፊትህ እየመራች ትወስድሃለች። ወፏ ጫጩቶቿን እንደምትጠብቅ ሁሉ እኛን ሊጠብቀን የሚችለው ማን እንደሆነ ታውቃለህ?— በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ ጫጩቶቿን ከምትንከባከብ ንስር ከተባለች ወፍ ጋር ተመሳስሎ ተገልጿል።—ዘዳግም 32:11, 12

ይህች ወፍ ጫጩቶቿን እየጠበቀች ያለችው እንዴት ነው?

በይሖዋ ፊት ከሁሉ ይበልጥ ተወዳጅ የነበረው ሕፃን፣ ልጁ ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ በሰማይ በነበረበት ጊዜ እንደ አባቱ ኃያል መንፈሳዊ አካል ነበር። በመሆኑም ራሱን መጠበቅ ይችል ነበር። ኢየሱስ በምድር ላይ ሕፃን ሆኖ በተወለደበት ጊዜ ግን ራሱን መርዳት የማይችል ልጅ ነበር። ስለዚህ ጥበቃ ያስፈልገው ነበር።

ኢየሱስ፣ አባቱ በምድር ላይ እንዲያከናውን የሚፈልገውን ነገር መፈጸም እንዲችል አድጎ ፍጹም የሆነ ትልቅ ሰው መሆን ነበረበት። ሰይጣን ግን ኢየሱስን እዚህ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት ሊገድለው ሙከራ አድርጓል። ኢየሱስን ገና ሕፃን ሳለ ለመግደል የተደረጉት ሙከራዎችና ይሖዋ እሱን ለመጠበቅ የተጠቀመባቸው መንገዶች አስገራሚ ታሪክ ሆነው ተመዝግበዋል። ታሪኩን መስማት ትፈልጋለህ?—

ኢየሱስ ከተወለደ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ሰይጣን በስተምሥራቅ በሰማይ ላይ አንድ ኮከብ የሚመስል ነገር እንዲያበራ አደረገ። ከዋክብትን የሚያጠኑ ኮከብ ቆጣሪዎች ኮከቡን በመከተል ረጅም ጉዞ አድርገው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። እዚያ እንደደረሱም የአይሁዳውያን ንጉሥ የሚሆነው ልጅ የሚወለደው የት እንደሆነ ጠየቁ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረውን የሚያውቁ ሰዎች ሲጠየቁ “በቤተልሔም ነው” ብለው መልስ ሰጡ።—ማቴዎስ 2:1-6

ኮከብ ቆጣሪዎቹ ኢየሱስን ካገኙት በኋላ አምላክ እሱን ለማዳን ለኮከብ ቆጣሪዎቹ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው?

በኢየሩሳሌም የነበረው ክፉው ንጉሥ ሄሮድስ በአቅራቢያው በምትገኘው የቤተልሔም ከተማ በቅርቡ ስለተወለደው አዲስ ንጉሥ ሲሰማ ኮከብ ቆጣሪዎቹን ‘ሕፃኑን ፈልጋችሁ አግኙትና ተመልሳችሁ ለእኔ ንገሩኝ’ አላቸው። ሄሮድስ ኢየሱስ ያለበትን ቦታ ለማወቅ የፈለገው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ቅናት ስላደረበትና ሊገድለው ስለፈለገ ነበር!

ታዲያ አምላክ ልጁን እንዴት ይጠብቀው ይሆን?— ኮከብ ቆጣሪዎቹ ኢየሱስን ሲያገኙት ስጦታዎች ሰጡት። በኋላ ግን ኮከብ ቆጣሪዎቹ ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ አምላክ በሕልም አስጠነቀቃቸው። ስለዚህ ወደ ኢየሩሳሌም ሳይመለሱ በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ። ሄሮድስ ኮከብ ቆጣሪዎቹ መሄዳቸውን ሲያውቅ በጣም ተናደደ። ኢየሱስን ለመግደል በማሰብ በቤተልሔም ያሉትን ከሁለት ዓመት በታች ያሉ ወንዶች ልጆች በሙሉ አስገደለ! በዚያ ወቅት ግን ኢየሱስ በቤተልሔም አልነበረም።

ኢየሱስ ያመለጠው እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ?— ኮከብ ቆጣሪዎቹ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ይሖዋ የማርያም ባል የሆነውን ዮሴፍን፣ ማርያምንና ኢየሱስን ይዞ ወደ ግብፅ እንዲሸሽ ነገረው። ኢየሱስ እዚያ ከክፉው ንጉሥ ከሄሮድስ ተጠብቆ ኖረ። የተወሰኑ ዓመታት ካለፉ በኋላ ማርያምና ዮሴፍ ኢየሱስን ይዘው ከግብፅ ሲመለሱ አምላክ ለዮሴፍ ሌላ ማስጠንቀቂያ ሰጠው። ኢየሱስ ከአደጋ ተጠብቆ ሊኖር ወደሚችልበት ወደ ናዝሬት ሄደው እንዲኖሩ ለዮሴፍ በሕልም ነገረው።—ማቴዎስ 2:7-23

ኢየሱስ ትንሽ ልጅ እያለ በድጋሚ ከሞት የተረፈው እንዴት ነው?

ይሖዋ ልጁን የጠበቀው እንዴት እንደሆነ ገባህ?— ኢየሱስ ሕፃን ሳለ ከነበረበት ሁኔታ ጋር ወይም እናታቸው በአትክልት ውስጥ ከደበቀቻቸው የወፍ ጫጩቶች ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ላይ ያለው ማን ነው ትላለህ? አንተ እንደ እነሱ አይደለህም?— አንተንም ሊጎዱህ የሚፈልጉ አሉ። ሊጎዱህ የሚፈልጉት እነማን እንደሆኑ ታውቃለህ?—

ሰይጣን ሊበላን እንደሚፈልግ የሚያገሳ አንበሳ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። አንበሶች ትንንሽ እንስሳትን አድፍጠው ለመያዝ እንደሚሞክሩ ሁሉ ሰይጣንና አጋንንቱም ብዙውን ጊዜ ልጆችን ለማጥቃት ይጥራሉ። (1 ጴጥሮስ 5:8) ይሖዋ ግን ከሰይጣን የበለጠ ኃይል አለው። ይሖዋ የእሱ የሆኑትን ልጆች መጠበቅ ወይም ሰይጣን የሚያደርስባቸውን መጥፎ ነገር ሁሉ ማስወገድ ይችላል።

በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 10 ላይ እንደተገለጸው ዲያብሎስና አጋንንቱ ምን እንድንፈጽም ሊገፋፉን ይሞክራሉ?— አዎ፣ አምላክ የማይፈቅደውን የጾታ ግንኙነት እንድንፈጽም ሊገፋፉን ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ የጾታ ግንኙነት መፈጸም ያለባቸው እነማን ብቻ ናቸው?— አዎ፣ ዕድሜያቸው ለጋብቻ ደርሶ የተጋቡ ወንድና ሴት ብቻ ናቸው።

ይሁን እንጂ የሚያሳዝነው ነገር፣ አንዳንድ ትልልቅ ሰዎች ከሕፃናት ጋር የጾታ ግንኙነት ማድረግ ይወዳሉ። ትልልቅ ሰዎች ይህን ድርጊት በልጆች ላይ በሚፈጽሙበት ጊዜ ልጆቹም ከትልልቆቹ የተማሩትን መጥፎ ነገር ማድረግ ሊጀምሩ ይችላሉ። በተጨማሪም እነዚህ ልጆች የጾታ ብልታቸውን ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጠቀም ይጀምራሉ። ይህ ሁኔታ በጥንት ጊዜ በሰዶም ከተማ ተፈጽሞ ነበር። በሰዶም የነበሩ ሰዎች ‘ከልጅ አንስቶ እስከ ሽማግሌው ድረስ’ ወደ ሎጥ ቤት በእንግድነት ከመጡት ወንዶች ጋር የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም እንደሞከሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ዘፍጥረት 19:4, 5 የ1954 ትርጉም

ስለዚህ ኢየሱስ ጥበቃ እንዳስፈለገው ሁሉ አንተም፣ ከአንተ ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸም ከሚፈልጉ ትልልቅ ሰዎች እንዲሁም እንዲህ ማድረግ ከሚፈልጉ ልጆች ጭምር ጥበቃ ሊደረግልህ ያስፈልጋል። ከአንተ ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸም የሚፈልጉ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ እንደ ጓደኛ መስለው ይቀርቡሃል። እንዲያውም ከአንተ ጋር ስለሚፈጽሙት የጾታ ግንኙነት ለሌላ ሰው እንደማትናገርባቸው ቃል ከገባህላቸው ስጦታ እንደሚሰጡህ ይነግሩህ ይሆናል። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች እንደ ሰይጣንና እንደ አጋንንቱ ራስ ወዳዶች ስለሆኑ የሚፈልጉት ለራሳቸው ደስታ ማግኘት ብቻ ነው። ይህን ደስታ ለማግኘት የሚጥሩት ደግሞ ከልጆች ጋር የጾታ ግንኙነት በመፈጸም ነው። ይህ ደግሞ በጣም መጥፎ የሆነ ነገር ነው!

እነዚህ ሰዎች ለራሳቸው ደስታ ለማግኘት ሲሉ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ታውቃለህ?— የጾታ ብልትህን ማሻሸት ሊሞክሩ ይችላሉ። ወይም ደግሞ የራሳቸውን የጾታ ብልት ካንተ የጾታ ብልት ጋር ያፋትጉ ይሆናል። አንተ ግን ማንም ሰው የጾታ ብልትህን እንዲያሻሽ መፍቀድ የለብህም። ሌላው ቀርቶ ወንድምህ፣ እህትህ፣ እናትህም ሆነች አባትህ እንኳ እንዲህ እንዲያደርጉ ልትፈቅድላቸው አይገባም።

አንድ ሰው ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሊደባብስህ ቢሞክር ምን መናገርና ማድረግ ይኖርብሃል?

ታዲያ እንዲህ ያለ መጥፎ ነገር ከሚያደርጉ ሰዎች አካልህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?— በመጀመሪያ ደረጃ ማንም ቢሆን የጾታ ብልትህን እንዲያሻሽ መፍቀድ የለብህም። አንድ ሰው እንዲህ ሊያደርግብህ ከሞከረ በድፍረት ጮክ ብለህ “ተው! እናገርብሃለሁ!” በለው። ይህ ሰው ጥፋተኛው አንተ ነህ ቢልህ እንኳ አትመነው። ውሸቱን ነው። ግለሰቡ ማንም ይሁን ማን ያደረገውን ነገር ተናገርበት! ‘ያደረግነው ነገር በእኔና በአንተ መካከል መቅረት ያለበት ሚስጥር ነው’ ቢልህም እንኳ ልትናገርበት ይገባል። ይህ ሰው ጥሩ ስጦታ እንደሚሰጥህ ቃል ቢገባልህ ወይም ቢያስፈራራህም እንኳን እንደምንም ብለህ አምልጠኸው ሂድና ተናገርበት።

መፍራት ባይኖርብህም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልግሃል። ጉዳት ሊያደርሱብህ ከሚችሉ ሰዎች ወይም ለአደጋ እንድትጋለጥ ከሚያደርጉ ቦታዎች እንድትርቅ ወላጆችህ ሲያስጠነቅቁህ ልትሰማቸው ይገባል። ወላጆችህ የሚነግሩህን ማስጠንቀቂያ የምትሰማ ከሆነ ክፉ ሰዎች አንተን ለመጉዳት የሚያስችል አጋጣሚ አይኖራቸውም።

ተገቢ ካልሆኑ የጾታ ድርጊቶች ራስን ስለመጠበቅ የሚናገሩትን የሚከተሉትን ጥቅሶች እናንብብ:- ዘፍጥረት 39:7-12፤ ምሳሌ 4:14-16፤ 14:15, 16፤ 1 ቆሮንቶስ 6:18፤ 2 ጴጥሮስ 2:14