በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 35

ከሞት ልንነሳ እንችላለን!

ከሞት ልንነሳ እንችላለን!

ብንሞት አምላክ እኛን የማስነሳት ማለትም እንደገና በሕይወት እንድንኖር የማድረግ ፍላጎት አለው?— ጥሩ ሰው የነበረው ኢዮብ አምላክ ሊያስነሳው እንደሚፈልግ ያምን ነበር። በመሆኑም ኢዮብ የሚሞትበት ጊዜ እንደተቃረበ በተሰማው ጊዜ አምላክን “ትጠራኛለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ” ብሎታል። ኢዮብ፣ ይሖዋ አምላክ እሱን ለማስነሳት እንደሚናፍቅ ወይም በጣም እንደሚፈልግ ተናግሯል።—ኢዮብ 14:14, 15

ኢየሱስ ልክ እንደ አባቱ እንደ ይሖዋ አምላክ ነው። በመሆኑም እኛን ሊረዳን ይፈልጋል። የሥጋ ደዌ የያዘው አንድ ሰው “ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” ብሎ ሲለምነው ኢየሱስ “እፈልጋለሁ” በማለት መልስ ሰጥቶታል። ደግሞም የታመመውን ሰው ከሥጋ ደዌው ፈውሶታል።—ማርቆስ 1:40-42

ይሖዋ ትንንሽ ልጆችን እንደሚወድ ያሳየው እንዴት ነው?

ኢየሱስ ለልጆች ፍቅር ማሳየትን ከአባቱ ተምሯል። ይሖዋ በድሮ ጊዜ በሁለት የተለያዩ ወቅቶች ሁለት አገልጋዮቹን ተጠቅሞ ትንንሽ ልጆችን ከሞት አስነስቷል። ኤልያስ እሱን በእንግድነት የተቀበለችው ሴት፣ ወንድ ልጇ በሞተባት ጊዜ ከሞት እንዲያስነሳላት ይሖዋን ለምኖት ነበር። ይሖዋም ከሞት አስነስቶታል። በተጨማሪም ይሖዋ በአገልጋዩ በኤልሳዕ ተጠቅሞ አንድን ትንሽ ልጅ ከሞት አስነስቷል።—1 ነገሥት 17:17-24፤ 2 ነገሥት 4:32-37

ይሖዋ በጣም እንደሚወደን ማወቅ በጣም የሚያስደስት ነገር አይደለም?— እሱ ስለ እኛ የሚያስበው በሕይወት እያለን ብቻ አይደለም። ብንሞትም እንኳን ያስታውሰናል። ይሖዋ የሚወዳቸው ሰዎች ቢሞቱም እንኳን በሕይወት እንዳሉ አድርጎ እንደሚቆጥራቸው ኢየሱስ ተናግሯል! (ሉቃስ 20:38) መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሞትም ሆነ ሕይወት፣ አሁን ያሉት ነገሮችም ሆኑ ወደፊት የሚመጡት ነገሮች ከአምላክ ፍቅር ሊለዩን እንደማይችሉ’ ይናገራል።—ሮም 8:38, 39

ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ይሖዋ ለትንንሽ ልጆችም እንደሚያስብ አሳይቷል። ኢየሱስ ጊዜ ወስዶ ከልጆች ጋር ስለ አምላክ ይነጋገር እንደነበረ ታስታውሳለህ። ይሁን እንጂ አምላክ ለኢየሱስ ትንንሽ ልጆችን ከሞት ማስነሳት እንዲችል ኃይል እንደሰጠው ታውቅ ነበር?— ኢያኢሮስ የሚባል ሰው የ12 ዓመት ሴት ልጁ በሞተች ጊዜ ኢየሱስ እንዳስነሳለት የሚገልጸውን ታሪክ እስቲ እንመልከት።

ኢያኢሮስ ከሚስቱና ከሴት ልጃቸው ጋር በገሊላ ባሕር አቅራቢያ ይኖር ነበር፤ ከእሷ ሌላ ምንም ልጅ አልነበራቸውም። አንድ ቀን ይህች ልጅ በጣም ስለታመመች ኢያኢሮስ ልትሞት እንደሆነ ተገነዘበ። ኢያኢሮስ፣ ኢየሱስ የሚባል አንድ ጥሩ ሰው የታመሙ ሰዎችን እንደሚፈወስ የሰማው ወሬ ትዝ አለው። ስለዚህ ኢየሱስን ሊፈልገው ሄደ። ኢያኢሮስ ኢየሱስን በገሊላ ባሕር ዳርቻ ብዙ ሰዎችን ሲያስተምር አገኘው።

ኢያኢሮስ በሕዝቡ መካከል አልፎ በኢየሱስ እግር ላይ ወደቀ። ከዚያም ኢየሱስን ‘ልጄ በጣም ታማለች። እባክህ መጥተህ ልትረዳት ትችላለህ? መጥተህ እንድታያት እለምንሃለሁ’ አለው። ኢየሱስም ወዲያውኑ ከኢያኢሮስ ጋር ሄደ። ታላቁን አስተማሪ ለማየት የመጡ ብዙ ሰዎችም ተከትለውት ሄዱ። ይሁን እንጂ ትንሽ ርቀት እንደተጓዙ የተወሰኑ ሰዎች ከኢያኢሮስ ቤት መጥተው “ልጅህ ሞታለች! ከዚህ በኋላ መምህሩን ለምን ታስቸግረዋለህ?” አሉት።

ኢየሱስ ሰዎቹ ይህን ሲናገሩ ሰማ። ኢየሱስ፣ ኢያኢሮስ አንድ ልጁን በማጣቱ ምን ያህል እንዳዘነ ተገንዝቧል። ስለዚህ ‘አትፍራ፤ ብቻ በአምላክ ላይ እምነት ይኑርህ፤ ልጅህ ትድናለች’ አለው። ከዚያም ወደ ኢያኢሮስ ቤት እስኪደርሱ ድረስ ጉዟቸውን ቀጠሉ። እዚያ ሲደርሱ የኢያኢሮስ ቤተሰብ ጓደኞች እያለቀሱ ነበር። ሰዎቹ ትንሿ ጓደኛቸው ስለሞተች በጣም አዝነዋል። ኢየሱስ ግን “በቃ አታልቅሱ፣ ልጅቷ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው።

ኢየሱስ ይህን ሲናገር ሰዎቹ ልጅቷ እንደሞተች ስላወቁ መሳቅ ጀመሩ። ታዲያ ኢየሱስ ልጅቷ ተኝታለች ብሎ የተናገረው ለምን ይመስልሃል?— ኢየሱስ ሰዎቹን ምን ትምህርት ሊያስተምራቸው የፈለገ ይመስልሃል?— ሞት ከከባድ እንቅልፍ ጋር ሊመሳሰል እንደሚችል ማስተማር ፈልጎ ነበር። እኛ አንድን ሰው ከእንቅልፉ በቀላሉ መቀስቀስ እንደምንችል ሁሉ ኢየሱስም ከአምላክ ባገኘው ኃይል አማካኝነት የሞተን ሰው ወደ ሕይወት መመለስ እንደሚችል ሊያስተምራቸው ፈልጎ ነበር።

ኢየሱስ የኢያኢሮስን ልጅ ከሞት እንዳስነሳ ከሚገልጸው ታሪክ ምን እንማራለን?

ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ማለትም ከጴጥሮስ፣ ከያዕቆብና ከዮሐንስ እንዲሁም ከልጅቷ አባትና እናት በስተቀር ሌሎቹ ሰዎች በሙሉ ከቤት እንዲወጡ አደረገ። ከዚያም ልጅቷ ወዳለችበት ክፍል ገባ። እጇን ይዞ ‘አንቺ ልጅ፣ ተነሽ!’ አላት። እሷም ወዲያውኑ ተነስታ ወዲያ ወዲህ መራመድ ጀመረች! በዚህ ጊዜ አባትና እናቷ በጣም ተደሰቱ።—ማርቆስ 5:21-24, 35-43፤ ሉቃስ 8:40-42, 49-56

አሁን እስቲ የሚከተለውን ነገር ለማሰብ ሞክር። ኢየሱስ ይህችን ትንሽ ልጅ እንደገና ሕያው ማድረግ ከቻለ ለሌሎችም እንዲሁ ማድረግ አይችልም?— በእርግጥ ያደርገዋል ብለህ ታስባለህ?— አዎ፣ ያደርገዋል። ኢየሱስ ራሱ “በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ . . . ይወጣሉ” ብሏል።—ዮሐንስ 5:28, 29

ኢየሱስ ሰዎችን ከሞት ማስነሳት የሚፈልግ ይመስልሃል?— በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ ሌላ ምሳሌ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ይረዳናል። አንድ ቀን በናይን ከተማ አቅራቢያ የሆነው ነገር ኢየሱስ ሰው ሞቶባቸው ሐዘን ላይ ላሉ ሰዎች ምን እንደሚሰማው በግልጽ ያሳያል።

አንዲት ሴት ከብዙ ሰዎች ጋር ሆና ልጇን ለመቅበር ከናይን ከተማ እየወጣች ነበር። ቀደም ሲል ባሏ ሞቷል፤ አሁን ደግሞ ያላት አንድ ልጅ ሞተ። ምን ያህል አዝና ይሆን! የልጇ ሬሳ ከናይን ከተማ ሲወጣ ብዙ የከተማዋ ሰዎች ተከትለዋት ነበር። ሴትየዋ እያለቀሰች የነበረ ሲሆን ሰዎቹ ደግሞ እሷን ለማጽናናት ሊያደርጉ የሚችሉት ምንም ነገር አልነበረም።

በዚያን ቀን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ድንገት ወደ ናይን ከተማ መጡ። ወደ ከተማዋ መግቢያ ሲቃረቡ የሴትየዋን ልጅ ለመቅበር ከሚሄዱት ሰዎች ጋር ተገናኙ። ኢየሱስ የምታለቅሰውን ሴት ሲመለከት አዘነላት። በደረሰባት ከባድ ሐዘን ልቡ በጣም ተነካ። ስለዚህ ሊረዳት ፈለገ።

ኢየሱስ የርኅራኄ ስሜት ያሳያት ቢሆንም እሷ እንድትሰማው በሚያስችል ጠንከር ያለ ድምፅ “በቃ፣ አታልቅሺ” አላት። ሁኔታውና ድርጊቱ ሁሉም ሰዎች በትኩረት እንዲመለከቱት አደረጋቸው። ኢየሱስ ወደ ሬሳው ሲጠጋ ሁሉም ምን ሊያደርግ ይሆን ብለው አስበው መሆን አለበት። ኢየሱስ በትእዛዝ መልክ “አንተ ወጣት፣ ተነስ እልሃለሁ!” ብሎ ተናገረ። የሞተውም ወጣት ወዲያውኑ ተነሥቶ ተቀመጠ! መናገርም ጀመረ።—ሉቃስ 7:11-17

ሴትየዋ ምን ተሰምቷት ሊሆን እንደሚችል አስበው! በሞት የተለየህ የምትወደው ሰው ከሞት ተነስቶ ብትቀበለው ምን ይሰማሃል?— ኢየሱስ ያደረገው ነገር እሱ በእርግጥም ሰዎችን እንደሚወድና ሊረዳቸው እንደሚፈልግ የሚያሳይ አይደለም?— አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ እንደገና ሕያው የሚሆኑትን ሰዎች መቀበል ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን አስበው!—2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:3, 4

ይህች ሴት ያላት አንድ ልጅ ከሞት መነሳቱ ምን ያሳያል?

በዚያን ጊዜ ከሚነሱት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ፣ ልጆችን ጨምሮ ከዚህ በፊት እናውቃቸው የነበሩ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ኢያኢሮስ ሴት ልጁን ኢየሱስ ሲያስነሳለት እንዳወቃት ሁሉ እኛም ከሙታን የሚነሱት ሰዎች እነማን እንደሆኑ ለይተን እናውቃቸዋለን። ሌሎቹ ደግሞ ከብዙ መቶ ወይም ሺህ ዓመታት በፊት ሞተው የነበሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ከረጅም ዘመናት በፊት የኖሩ ቢሆኑም አምላክ አይረሳቸውም።

ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ይህን ያህል እንደሚወዱን ማወቁ አያስደስትም?— ለጥቂት ዓመታት ብቻ ሳይሆን ለዘላለም እንድንኖር ይፈልጋሉ!

መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎች ያላቸውን አስደናቂ ተስፋ በሚመለከት ኢሳይያስ 25:8፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15 እና 1 ቆሮንቶስ 15:20-22 ላይ ምን እንደሚል እባካችሁ አንብቡ።