ምዕራፍ 8
ከእኛ በላይ የሆኑ አሉ
በሥልጣንም ይሁን በኃይል ከእኛ በላይ የሆኑ እንዳሉ ታምናለህ፣ አይደል? ከሁላችንም በላይ የሆነው ማን ይመስልሃል?— ይሖዋ አምላክ ነው። ታላቅ አስተማሪ የሆነው ልጁስ? እሱም ከእኛ በላይ ነው?— አዎ፣ እሱም ከእኛ በላይ ነው።
ኢየሱስ በሰማይ ከአምላክ ጋር ኖሯል። በሰማይ ሳለ መንፈሳዊ የአምላክ ልጅ ወይም መልአክ ነበር። አምላክ ሌሎች መላእክት ወይም መንፈሳዊ ልጆች ፈጥሮ ነበር?— አዎ፣ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ መላእክት ፈጥሯል። እነዚህ መላእክትም ከእኛ በላይ ከመሆናቸውም ሌላ ከእኛ የበለጠ ኃይል አላቸው።—መዝሙር 104:4፤ ዳንኤል 7:10
ማርያምን ያናገራት መልአክ ስሙ ማን እንደሆነ ታስታውሳለህ?— ገብርኤል ነው። ማርያም የምትወልደው ልጅ የአምላክ ልጅ እንደሚሆን ገብርኤል ነግሯት ነበር። ኢየሱስ በምድር ላይ ሕፃን ሆኖ እንዲወለድ አምላክ የመንፈሳዊ ልጁን ሕይወት ወስዶ ማርያም ሆድ ውስጥ አስቀመጠው።—ሉቃስ 1:26, 27
ይህ ተአምር እንደተፈጸመ ታምናለህ? ኢየሱስ ከዚያ በፊት በሰማይ ከአምላክ ጋር እንደኖረ ታምናለህ?— ኢየሱስ ራሱ በሰማይ ይኖር እንደነበረ ተናግሯል። በሰማይ ይኖር እንደነበረ እንዴት አወቀ? ኢየሱስ ልጅ ሳለ ማርያም መልአኩ ገብርኤል የነገራትን ነገር ሳትነግረው አትቀርም። በተጨማሪም የኢየሱስ እውነተኛ አባት፣ አምላክ መሆኑን ዮሴፍ ነግሮት ሊሆን ይችላል።
ኢየሱስ ሲጠመቅ አምላክ ራሱ ከሰማይ “ልጄ ይህ ነው” ብሎ ተናግሯል። (ማቴዎስ 3:17) ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት “አባት ሆይ፣ ዓለም ከመመሥረቱ በፊት በጎንህ ሆኜ በነበረኝ ክብር አሁንም በጎንህ አድርገህ አክብረኝ” በማለት ጸልዮ ነበር። (ዮሐንስ 17:5) አዎ፣ ኢየሱስ እንደገና ከአባቱ ጋር በሰማይ መኖር እንዲችል ወደ ሰማይ ለመመለስ ጠይቋል። ታዲያ እንደገና በሰማይ መኖር የሚችለው እንዴት ነው?— ይህ ሊሆን የሚችለው ይሖዋ አምላክ እንደገና የማይታይ መንፈሳዊ አካል ወይም መልአክ ካደረገው ብቻ ነው።
አሁን አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ጥያቄ ልጠይቅህ። ሁሉም መላእክት ጥሩ ናቸው? አንተ ስለዚህ ጉዳይ ምን ትላለህ?— በአንድ ወቅት ሁሉም መላእክት ጥሩ ነበሩ። ይህን የምንልበት ምክንያት መላእክትን የፈጠራቸው ይሖዋ ስለሆነና እሱ የሚፈጥረው ነገር ሁሉ ደግሞ ጥሩ ስለሆነ ነው። ከጊዜ በኋላ ግን ከመላእክት አንዱ ክፉ ሆነ። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?
መልሱን ለማግኘት አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ማለትም አዳምንና ሔዋንን በፈጠረበት ጊዜ የነበረውን ሁኔታ እንመልከት። አንዳንድ ሰዎች ስለ አዳምና ሔዋን የሚገልጸው ታሪክ ተረት ነው ይላሉ። ታላቁ አስተማሪ ግን ስለ አዳምና ሔዋን የሚገልጸው ታሪክ እውነት መሆኑን ያውቅ ነበር።
አምላክ አዳምንና ሔዋንን ከፈጠራቸው በኋላ ኤደን በተባለው ውብ የአትክልት ቦታ አስቀመጣቸው። ይህ ቦታ የመናፈሻ ሥፍራ ወይም ገነት ነበር። አዳምና ሔዋን ብዙ ልጆች ወልደው አንድ ትልቅ ቤተሰብ በመመሥረት በገነት ውስጥ ለዘላለም ሊኖሩ ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ መማር የሚያስፈልጋቸው አንድ
አስፈላጊ ትምህርት ነበር። ይህን ጉዳይ ቀደም ሲል ተወያይተንበታል። እስቲ ለማስታወስ እንሞክር።ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን በገነት ካሉት ፍሬዎች የፈለጉትን ያህል መብላት እንደሚችሉ ነግሯቸው ነበር። ይሁን እንጂ መብላት ያልነበረባቸው አንድ ፍሬ ነበር። ይህን ፍሬ ከበሉ ምን እንደሚሆኑ አምላክ ገልጾላቸዋል። ‘ከበሉ እንደሚሞቱ’ ነግሯቸዋል። (ዘፍጥረት 2:17፤ 3:3) ታዲያ አዳምና ሔዋን መማር የሚያስፈልጋቸው ትምህርት ምን ነበር?—
ታዛዥነትን መማር ያስፈልጋቸው ነበር። አዎ፣ ሕይወት የተመካው ይሖዋ አምላክን በመታዘዝ ላይ ነው! አዳምና ሔዋን አምላክን እንደሚታዘዙ መናገራቸው ብቻ በቂ አልነበረም። ታዛዥነታቸውን በተግባር ማሳየት ነበረባቸው። አምላክን ቢታዘዙ እሱን እንደሚወዱትና ገዥያቸው እንዲሆን እንደሚፈልጉ ያሳዩ ነበር። ከዚያም በገነት ለዘላለም ሊኖሩ ይችሉ ነበር። ነገር ግን ከተከለከለው ፍሬ መብላታቸው ምን ያሳያል?—
ከተከለከለው ፍሬ መብላታቸው አምላክ ለሰጣቸው ነገር አመስጋኝ አለመሆናቸውን ያሳያል። በዚያን ጊዜ በገነት ውስጥ ብትሆን ኖሮ ይሖዋን ትታዘዝ ነበር?— መጀመሪያ ላይ አዳምና ሔዋንም ታዘው ነበር። በኋላ ግን ከእነሱ በላይ የሆነ አንድ አካል ሔዋንን አታለላት። ይህ አካል ሔዋን የይሖዋን ትእዛዝ እንድትጥስ አደረገ። እሱ ማን ነበር?—
መጽሐፍ ቅዱስ አንድ እባብ ሔዋንን እንዳነጋገራት ይገልጻል። ይሁን እንጂ እባብ በራሱ መናገር እንደማይችል ታውቃለህ። ታዲያ እባቡ እንዴት መናገር ቻለ?— እባቡ እየተናገረ ያለ እንዲመስል ያደረገው አንድ መልአክ ነበር። ነገር ግን እየተናገረ የነበረው መልአኩ ራሱ ነበር። ይህ መልአክ ክፉ ነገር ማሰብ ጀምሮ ነበር። አዳምና ሔዋን እሱን እንዲያመልኩትና እሱን እንዲታዘዙት ማድረግ ፈለገ። የአምላክን ቦታ ለመውሰድ ፈለገ።
ስለዚህ ያ ክፉ መልአክ ሔዋን መጥፎ ነገር እንድታስብ አደረጋት። በእባቡ አማካኝነት ሔዋንን ‘አምላክ እውነቱን አልነገረሽም። የዚህን ዛፍ ፍሬ ብትበዪ አትሞቺም። እንዲያውም እንደ አምላክ ጥበበኛ ትሆኛለሽ’ አላት። አንተ ብትሆን ኖሮ ይህን አምነህ ትቀበል ነበር?—
ሔዋን አምላክ ያልሰጣትን ነገር መመኘት ጀመረች። በዚህም ምክንያት የተከለከለውን ፍሬ በላች። ከዚያም ለባልዋ ሰጠችው። አዳም እባቡ የተናገረውን ነገር አላመነም። ሆኖም ከሔዋን ጋር ለመሆን ያለው ምኞት ለአምላክ ከነበረው ፍቅር በለጠበት። ስለዚህ እሱም የተከለከለውን ፍሬ በላ።—ዘፍጥረት 3:1-6፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:14
ውጤቱ ምን ሆነ?— አዳምና ሔዋን ፍጽምና የጎደላቸው ሆኑ፤ እንዲሁም አርጅተው ሞቱ። አዳምና ሔዋን ፍጽምና የጎደላቸው በመሆናቸው ልጆቻቸው በሙሉ ልክ እንደነሱ ፍጽምና የጎደላቸው ሆኑ፤ እነሱም ከጊዜ በኋላ አርጅተው ሮም 5:12) ሔዋንን የዋሻት መልአክ ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሚባልና እንደ ሰይጣን ክፉ የሆኑ ሌሎች መላእክት ደግሞ አጋንንት ተብለው እንደሚጠሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።—ያዕቆብ 2:19፤ ራእይ 12:9
ሞቱ። አምላክ አልዋሸም! በእርግጥም ሕይወት የተመካው እሱን በመታዘዝ ላይ ነው። (አምላክ የፈጠረው ጥሩ መልአክ እንዴት ክፉ ሊሆን እንደቻለ አሁን ገባህ?— ክፉ ነገር ማሰብ ስለ ጀመረ ነው። ከሁሉም በላይ መሆን ፈለገ። ሰይጣን፣ አዳምና ሔዋን ልጆች እንዲወልዱ አምላክ እንደነገራቸው ያውቅ ነበር፤ በመሆኑም ሁሉም እሱን እንዲያመልኩት ፈለገ። ዲያብሎስ ሁሉም ሰው ይሖዋን እንዳይታዘዝ ማድረግ ይፈልጋል። ስለዚህ መጥፎ ሐሳብ ወደ አእምሯችን ለማስገባት ይጥራል።—ያዕቆብ 1:13-15
ዲያብሎስ ይሖዋን ከልቡ የሚወድ ሰው እንደሌለ ይናገራል። አንተም ሆንክ እኔ ይሖዋን እንደማንወደውና እሱ የሚያዘንን ማድረግ እንደማንፈልግ ይናገራል። ይሖዋን የምንታዘዘው ሁሉ ነገር እኛ እንደምንፈልገው ሲሆን ብቻ እንደሆነ አድርጎ ይናገራል። ታዲያ ዲያብሎስ ትክክል ነው? እኛ ዲያብሎስ እንደሚናገረው ዓይነት ሰዎች ነን?
ታላቁ አስተማሪ፣ ዲያብሎስ ውሸታም መሆኑን ተናግሯል! ኢየሱስ ይሖዋን በመታዘዝ በእርግጥ እንደሚወደው በተግባር አሳይቷል። ደግሞም ኢየሱስ አምላክን ይታዘዝ የነበረው ትእዛዙ ቀላል በሚሆንበት ጊዜ ብቻ አልነበረም። በማንኛውም ጊዜ፣ ሌላው ቀርቶ ሌሎች ሰዎች አምላክን እንዳይታዘዝ ተጽዕኖ ባደረጉበት ጊዜም እንኳን አምላክን ታዟል። ኢየሱስ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ለይሖዋ ታማኝ መሆኑን አሳይቷል። ኢየሱስ ለዘላለም እንዲኖር ይሖዋ ከሞት ያስነሳው ለዚህ ነው።
ስለዚህ ታላቁ ጠላታችን ማን ይመስልሃል?— አዎ፣ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ሰይጣንን ልታየው ትችላለህ?— ልታየው አትችልም! ነገር ግን ሰይጣን ዲያብሎስ እንዳለ፣ ከእኛ በላይ እንደሆነና ከእኛ ይበልጥ ኃይል እንዳለው እናውቃለን። ከዲያብሎስ የሚበልጠው ግን ማን ነው?— ይሖዋ አምላክ ነው። ስለዚህ አምላክ ከሰይጣን ሊጠብቀን እንደሚችል እናውቃለን።
ማንን ማምለክ እንዳለብን የሚናገሩትን የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቡ:- ዘዳግም 30:19, 20፤ ኢያሱ 24:14, 15፤ ምሳሌ 27:11፤ ማቴዎስ 4:10