በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 21

ጉራ መንዛት ይኖርብናል?

ጉራ መንዛት ይኖርብናል?

ጉራ መንዛት ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?— አንድ ምሳሌ እንመልከት። በደንብ የማትችለውን ነገር ለማድረግ ሞክረህ ታውቃለህ? ምናልባት ኳስ ለመምታት ወይም ገመድ ለመዝለል ሞክረህ ይሆናል። እንዲህ ለማድረግ በምትሞክርበት ጊዜ አንድ ልጅ ስቆብህ “እኔ ከአንተ እሻላለሁ” ብሎህ ያውቃል?— እንዲህ ካለህ ይህ ልጅ ጉራውን እየነዛብህ ነበር ማለት ነው።

ሌሎች ጉራቸውን ሲነዙ ስትመለከት ምን ይሰማሃል? ደስ ይልሃል?— ታዲያ አንተ ስለ ራስህ ጉራ ብትነዛ ሌሎች ምን የሚሰማቸው ይመስልሃል?— አንድን ሰው “እኔ እበልጥሃለሁ” ማለት ተገቢ ነው?— ይሖዋ ጉራ የሚነዙ ሰዎችን ይወዳል?—

ታላቁ አስተማሪ፣ ከሌሎች እንደሚበልጡ አድርገው የሚያስቡ ሰዎችን ያውቅ ነበር። እነዚህ ሰዎች ስለራሳቸው ጉራ የሚነዙ ወይም በራሳቸው የሚኩራሩና ሌሎችን ሁሉ በንቀት የሚመለከቱ ነበሩ። ስለዚህ አንድ ቀን ኢየሱስ ስለራሳቸው ጉራ መንዛታቸው ስህተት መሆኑን የሚያሳይ አንድ ታሪክ ነገራቸው። እስቲ እኛም ይህን ታሪክ እንመልከት።

ታሪኩ ስለ አንድ ፈሪሳዊና ስለ አንድ ቀረጥ ሰብሳቢ የሚገልጽ ነው። ፈሪሳውያን ከሌሎች ሰዎች ይበልጥ ጻድቃን ወይም ቅዱሳን እንደሆኑ አድርገው የሚያስቡ የሃይማኖት አስተማሪዎች ነበሩ። ኢየሱስ በታሪኩ ላይ የገለጸው ፈሪሳዊ ለመጸለይ በኢየሩሳሌም ወደነበረው የአምላክ ቤተ መቅደስ ሄዶ ነበር።

አምላክ በፈሪሳዊው ሳይሆን በቀረጥ ሰብሳቢው የተደሰተው ለምንድን ነው?

ቀረጥ ሰብሳቢውም ለመጸለይ ወደ ቤተ መቅደሱ እንደሄደ ኢየሱስ ተናገረ። አብዛኞቹ ሰዎች ቀረጥ ሰብሳቢዎችን አይወዷቸውም ነበር። ብዙ ሰዎች ቀረጥ ሰብሳቢዎቹ እነሱን ለማታለል እንደሚሞክሩ ይሰማቸው ነበር። ደግሞም ብዙዎቹ ቀረጥ ሰብሳቢዎች ለማታለል ይሞክሩ ነበር።

ፈሪሳዊው በቤተ መቅደሱ ቆሞ እንዲህ በማለት ወደ አምላክ ይጸልይ ጀመር:- ‘አምላክ ሆይ፣ እንደ ሌሎች ሰዎች ኃጢአተኛ ስላልሆንኩ አመሰግንሃለሁ። ሰዎችን አላታልልም ወይም ሌላ መጥፎ ነገር አልሠራም። እዚያ እንደቆመው ቀረጥ ሰብሳቢም አይደለሁም። እኔ ጻድቅ ሰው ነኝ። ስለ አንተ ለማሰብ የሚያስችል ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት ስል በሳምንት ውስጥ ሁለት ጊዜ ምግብ ሳልበላ እውላለሁ። እንዲሁም ከማገኘው ነገር ሁሉ አንድ አስረኛውን ለቤተ መቅደሱ እሰጣለሁ።’ በእርግጥም ፈሪሳዊው ከሌሎች እንደሚሻል አድርጎ አስቧል፣ አይደል?— ይህን ደግሞ ለአምላክ ነግሮታል።

ቀረጥ ሰብሳቢው ግን እንደ ፈሪሳዊው ዓይነት ሰው አልነበረም። በሚጸልይበት ጊዜ እንኳ ራሱን ወደ ሰማይ ቀና አላደረገም። አንገቱን ደፍቶ በርቀት ቆመ። ቀረጥ ሰብሳቢው በሠራው ኃጢአት በጣም ተጸጽቶ በሐዘን ደረቱን ይመታ ነበር። ምን ያህል ጥሩ ሰው እንደሆነ ለአምላክ ለመናገር አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ ‘አምላክ ሆይ፣ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ’ እያለ ይጸልይ ነበር።

ከእነዚህ ሁለት ሰዎች ውስጥ አምላክን ያስደሰተው የትኛው ይመስልሃል? ጥሩ ሰው እንደሆነ አድርጎ ያሰበው ፈሪሳዊ ነው? ወይስ ኃጢአት በመሥራቱ ያዘነው ቀረጥ ሰብሳቢ?—

ኢየሱስ አምላክን ያስደሰተው ቀረጥ ሰብሳቢው እንደሆነ ተናግሯል። ለምን? ኢየሱስ ይህን ያለበትን ምክንያት ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል:- ‘ራሱን ከሌሎች ሰዎች አስበልጦ የሚመለከት ሰው ሁሉ ይዋረዳል። ራሱን ዝቅ አድርጎ የሚመለከት ሰው ግን ከፍ ከፍ ይደረጋል።’—ሉቃስ 18:9-14

ኢየሱስ በዚህ ታሪክ አማካኝነት ሊያስተላልፍ የፈለገው ትምህርት ምንድን ነው?— ኢየሱስ ይህን ታሪክ የተናገረው ከሌሎች እንደምንበልጥ አድርገን ማሰብ ስህተት እንደሆነ ለማስተማር ፈልጎ ነው። ከሌሎች እበልጣለሁ ብለን አንናገር ይሆናል፤ ነገር ግን ሁኔታችን ወይም የምናደርገው ነገር ከሌሎች እበልጣለሁ ብለን እንደምናስብ ሊያሳይ ይችላል። አንተ ከሌሎች እበልጣለሁ ብለህ እንደምታስብ የሚያሳይ ድርጊት ፈጽመህ ታውቃለህ?— እስቲ ሐዋርያው ጴጥሮስ ያደረገውን እንመልከት።

ኢየሱስ በሚታሠርበት ጊዜ ሁሉም ጥለውት እንደሚሄዱ ለሐዋርያቱ ሲነግራቸው ጴጥሮስ ‘ሁሉም ጥለውህ ቢሄዱ እንኳ እኔ ጥዬህ አልሄድም’ ብሎ በጉራ ተናገረ። ሆኖም ጴጥሮስ ተሳስቷል። ከልክ በላይ በራሱ ተማምኖ ነበር። ኢየሱስ በተያዘበት ወቅት ጥሎት ሄዷል። ይሁን እንጂ በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 30 ላይ እንደምንመለከተው ጴጥሮስ በኋላ ወደ ኢየሱስ ተመልሷል።—ማቴዎስ 26:31-33

እስቲ በአሁኑ ጊዜ ሊፈጸም የሚችል አንድ ምሳሌ እንመልከት። ምናልባት አንተና አንድ የክፍልህ ተማሪ በትምህርት ቤት አንዳንድ ጥያቄዎች ትጠየቁ ይሆናል። አንተ ጥያቄዎቹን ወዲያውኑ መመለስ ብትችልና ሌላኛው ተማሪ መመለስ ባይችል ምን ታደርጋለህ? መልሶቹን በማወቅህ ደስ እንደሚልህ የተረጋገጠ ነው። ይሁን እንጂ ጥያቄውን በፍጥነት መመለስ ካልቻለው ተማሪ ጋር ራስህን ብታወዳድር ጥሩ ይሆናል?— ሌላኛው ልጅ ዝቅ ተደርጎ እንዲታይ በማድረግ አንተ የተሻልክ ሆነህ ለመታየት ብትሞክር ተገቢ ነው?—

ፈሪሳዊው ያደረገው እንደዚህ ነበር። ከቀረጥ ሰብሳቢው እንደሚሻል በጉራ ተናግሯል። ታላቁ አስተማሪ ግን ፈሪሳዊው ትክክል እንዳልሆነ ገልጿል። አንድ ሰው አንድን ነገር ከሌላው ሰው በተሻለ መንገድ ሊሠራው እንደሚችል የተረጋገጠ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ሰው ይህን ማድረግ ስለቻለ ብቻ እሱ የተሻለ ሰው ነው ማለት አይደለም።

ከሌላው ሰው የበለጠ ስላወቅክ ብቻ የተሻልክ ሰው ነህ ማለት ነው?

ታዲያ ከሌላው ሰው የበለጠ እውቀት ቢኖረን ይህ ጉራ ለመንዛት ምክንያት ይሆነናል?— እስቲ አስበው። አንጎላችንን የሠራነው እኛ ነን?— እኛ አይደለንም፤ ለእያንዳንዳችን አንጎል የሰጠን አምላክ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ብዙ ነገሮችን ያወቅነው ከሌሎች ሰዎች ተምረን ነው። ወይም ደግሞ እነዚህን ነገሮች ያወቅነው ከመጽሐፍ አንብበን ይሆናል። አለዚያም አንድ ሰው ነግሮን ሊሆን ይችላል። አንድን ነገር ያወቅነው ራሳችን አስበን ቢሆን እንኳ ይህን ማድረግ የቻልነው እንዴት ነው?— አዎ፣ አምላክ በሰጠን አንጎል ተጠቅመን ነው።

አንድ ሰው አንድ ነገር ለማድረግ የቻለውን ሁሉ ጥረት በሚያደርግበት ጊዜ ሰውየውን የሚያበረታታ ነገር ብትናገር ጥሩ ይሆናል። በሠራው ነገር መደሰትህን ንገረው። ምናልባትም ከዚያ የተሻለ እንዲሠራ ልትረዳው ትችላለህ። አንተም ብትሆን ሰዎች እንዲህ እንዲያደርጉልህ ትፈልጋለህ፣ አይደል?—

ከሌላው ሰው የበለጠ ጠንካራ ብንሆን ጉራ መንዛት የሌለብን ለምንድን ነው?

አንዳንድ ሰዎች ከሌሎች ይበልጥ ጠንካሮች ናቸው። አንተ ከወንድምህ ወይም ከእህትህ የበለጠ ጠንካራ ብትሆንስ? ይህ ጉራ እንድትነዛ ሊያደርግህ ይገባል?— በፍጹም አይገባም። ጠንካሮች እንድንሆን የሚረዳን የምንበላው ምግብ ነው። ለምግብነት የምንጠቀምባቸው ተክሎች እንዲያድጉ የፀሐይ ብርሃን፣ ዝናብና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን የሚሰጠው ደግሞ አምላክ ነው፣ አይደል?— ስለዚህ ጠንካሮች ከሆንን ማመስገን ያለብን አምላክን ነው።—የሐዋርያት ሥራ 14:16, 17

ማናችንም ብንሆን ሰው ስለ ራሱ ጉራ ሲነዛ መስማት ደስ አይለንም፤ ደስ ይለናል እንዴ?— ኢየሱስ ‘ሌሎች ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ እንደምትፈልጉ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው’ በማለት የተናገረውን ማስታወስ ይኖርብናል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ታላቁ አስተማሪ በተናገረው ታሪክ ላይ እንደተጠቀሰው ስለ ራሱ በጉራ እንደተናገረው ፈሪሳዊ አንሆንም።—ሉቃስ 6:31

በአንድ ወቅት አንድ ሰው ኢየሱስን ጥሩ ብሎ ጠርቶት ነበር። ታዲያ ታላቁ አስተማሪ ‘አዎ፣ ልክ ነህ፤ ጥሩ ነኝ’ አለው?— በፍጹም አላለውም። ከዚህ ይልቅ “ከአንዱ ከአምላክ በቀር ጥሩ የለም” አለው። (ማርቆስ 10:18) ታላቁ አስተማሪ ፍጹም የነበረ ቢሆንም ስለ ራሱ በጉራ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም አባቱ ማለትም ይሖዋ እንዲመሰገን ያደርግ ነበር።

ታዲያ ስለ ማን በኩራት ልንናገር እንችላለን?— አዎ፣ ፈጣሪያችን ስለሆነው ስለ ይሖዋ አምላክ በኩራት ልንናገር እንችላለን። ፀሐይ ስትጠልቅ የሚታየውን ውበት ወይም ሌላ ዓይነት አስደናቂ ፍጥረት ስንመለከት ‘ይህን የሠራው ማን እንደሆነ ታውቃለህ? አስደናቂው አምላካችን ይሖዋ እኮ ነው!’ በማለት ለሰው ልንናገር እንችላለን። ይሖዋ ስለሠራቸውና ወደፊትም ስለሚሠራቸው አስደናቂ ነገሮች ለመናገር ምንጊዜም ዝግጁ እንሁን።

ይህ ልጅ በኩራት እየተናገረ ያለው ስለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ጉራ ስለ መንዛት ምን እንደሚል አንብብና ስለ ራሳችን ጉራ ከመንዛት እንዴት መቆጠብ እንዳለብን ለመረዳት ሞክር:- ምሳሌ 16:5, 18፤ ኤርምያስ 9:23, 24፤ 1 ቆሮንቶስ 4:7፤ 13:4