በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 13

ሃይማኖቶች ወደፊት ምን ይጠብቃቸዋል?

ሃይማኖቶች ወደፊት ምን ይጠብቃቸዋል?

1. ሁሉም ሃይማኖቶች ጥሩ ናቸው?

በሁሉም የሃይማኖት ቡድኖች ውስጥ ልበ ቅን ሰዎች አሉ። አምላክ እነዚህ ሰዎች የሚያደርጉትን ጥረት የሚያስተውል ከመሆኑም ሌላ ስለ እነሱ የሚያስብ መሆኑ የሚያስደስት ነው። የሚያሳዝነው ግን በሃይማኖት ስም መጥፎ ድርጊቶች ተፈጽመዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:3, 4፤ 11:13-15) የዜና ዘገባዎች እንደሚያሳዩት አንዳንድ ሃይማኖቶች እንደ ሽብርተኝነት፣ የዘር ማጥፋት ዘመቻ፣ ጦርነት፣ ልጆችን ማስነወርና በእነሱ ላይ ጥቃት መፈጸም ባሉት ድርጊቶች እንኳ ተካፍለዋል። እነዚህ ነገሮች፣ በአምላክ የሚያምኑ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎችን ምንኛ ያሳዝኗቸዋል!​—ማቴዎስ 24:3-5, 11, 12ን አንብብ።

እውነተኛ ሃይማኖት አምላክን የሚያስከብረው ሲሆን ሐሰተኛ ሃይማኖት ግን በተቃራኒው እሱን ያሳዝነዋል። ሐሰተኛ ሃይማኖት አምላክንና የሞቱ ሰዎችን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይገኙ የተሳሳቱ ትምህርቶችን ያስተምራል። ይሖዋ ግን ሰዎች ስለ እሱ እውነቱን እንዲያውቁ ይፈልጋል።​—ሕዝቅኤል 18:4ን እና 1 ጢሞቴዎስ 2:3-5ን አንብብ።

2. ሃይማኖቶች ወደፊት ምን ይጠብቃቸዋል?

አምላክ፣ እሱን እንደሚወዱ ቢናገሩም እንኳ የሰይጣንን ዓለም እንደሚወዱ በሚያሳዩ ሃይማኖቶች አይታለልም። (ያዕቆብ 4:4) የአምላክ ቃል፣ ሁሉንም የሐሰት ሃይማኖቶች “ታላቂቱ ባቢሎን” በማለት ይጠራቸዋል። በኖኅ ዘመን ከነበረው የጥፋት ውኃ በኋላ የሐሰት ሃይማኖት የመነጨው ባቢሎን ከተባለችው ጥንታዊት ከተማ ነበር። አምላክ የሰውን ዘር በሚያታልሉና በሚጨቁኑ ሃይማኖቶች ላይ በቅርቡ ድንገተኛ ጥፋት ያመጣል።​—ራእይ 17:1, 2, 5, 16, 17ን እና 18:8ን አንብብ።

ሌላም አስደሳች ነገር አለ። ይሖዋ በዓለም ዙሪያ በሚገኙት የሐሰት ሃይማኖቶች ውስጥ ያሉትን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች አይረሳም። እንዲህ ያሉት ሰዎች እውነትን እንዲማሩ መንገድ በመክፈት አንድ ላይ እንዲሰባሰቡ እያደረገ ነው።​—ሚክያስ 4:2, 5ን አንብብ።

3. ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ምን ማድረግ አለባቸው?

እውነተኛው ሃይማኖት ሰዎች አንድነት እንዲኖራቸው እያደረገ ነው

ይሖዋ እውነትና ትክክል የሆነውን ነገር ለሚወዱ ሰዎች ያስባል። እነዚህ ሰዎች ከሐሰት ሃይማኖት እንዲወጡ እያሳሰባቸው ነው። አምላክን የሚወዱ ሰዎች እሱን ለማስደሰት ሲሉ በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኞች ናቸው።​—ራእይ 18:4ን አንብብ።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ምሥራቹን ከሐዋርያት ሲሰሙ በደስታ ተቀብለውታል። እነዚህ ሰዎች ደስተኛ እንዲሆኑ እንዲሁም ዓላማ ያለው ሕይወት እንዲመሩና ተስፋ እንዲኖራቸው የሚያስችል አዲስ ዓይነት አኗኗር ከይሖዋ ተምረዋል። ምሥራቹን ተቀብለው በሕይወታቸው ውስጥ ለይሖዋ ቅድሚያ በመስጠታቸው በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ጥሩ አርዓያ ይሆናሉ።​—1 ተሰሎንቄ 1:8, 9ን እና 2:13ን አንብብ።

ይሖዋ ከሐሰት ሃይማኖት የሚወጡ ሰዎችን፣ የእሱ አምላኪዎችን ካቀፈው ቤተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ይጋብዛቸዋል። ይሖዋ ያቀረበልህን ሞቅ ያለ ግብዣ ከተቀበልህ ከእሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረት፣ እንደ አንተው ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎችን ያቀፈ አዲስና አፍቃሪ ቤተሰብ አባል መሆን እንዲሁም የዘላለም ሕይወት ማግኘት ትችላለህ።​—ማርቆስ 10:29, 30ን እና 2 ቆሮንቶስ 6:17, 18ን አንብብ።

4. አምላክ በመላው ምድር የሚኖሩ ሰዎች ደስተኞች እንዲሆኑ የሚያደርገው እንዴት ነው?

የሐሰት ሃይማኖቶች በቅርቡ የሚፈረድባቸው መሆኑ የምሥራች ነው። ይህ የፍርድ እርምጃ ጭቆናን ከምድር ላይ ያስወግዳል። ከዚያ በኋላ የሐሰት ሃይማኖቶች የሰውን ዘር ማሳሳትም ሆነ መከፋፈል አይችሉም። በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ ብቻውን እውነተኛ የሆነውን አምላክ በማምለክ አንድ ይሆናሉ።​—ራእይ 18:20, 21ን እና 21:3, 4ን አንብብ።