ትምህርት 6
የሞቱ ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው?
1. ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?
ኢየሱስ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ወደምትገኘው የቢታንያ መንደር ሲደርስ ወዳጁ አልዓዛር ከሞተ አራት ቀን አልፎት ነበር። ኢየሱስ ከሟቹ እህቶች ከማርታና ከማርያም ጋር ወደ መቃብሩ ስፍራ ሄደ። ወዲያው በርካታ ሰዎች ተሰበሰቡ። ኢየሱስ፣ አልዓዛርን ከሞት ሲያስነሳው ማርታና ማርያም ምን ያህል ተደስተው እንደሚሆን መገመት ትችላለህ?—ዮሐንስ 11:21-24, 38-44ን አንብብ።
ማርታ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎችን አስመልክቶ የሚናገረውን ምሥራች ታውቅ ነበር። ይሖዋ ሙታንን እንደሚያስነሳቸውና እንደገና በምድር ላይ መኖር እንደሚችሉ ተገንዝባ ነበር።—ኢዮብ 14:14, 15ን አንብብ።
2. ሙታን የሚገኙት በምን ዓይነት ሁኔታ ነው?
የሰው ልጆች የተሠራነው ከአፈር ነው። (ዘፍጥረት 2:7፤ 3:19) የሰው ልጆች ሥጋዊ አካል የለበስን መንፈሳዊ ፍጥረታት አይደለንም። ሥጋዊ ፍጥረታት ስለሆንን ስንሞት ከእኛ ወጥቶ በሕይወት የሚቀጥል ነገር የለም። ስንሞት አንጎላችን ሥራውን ስለሚያቆም የማሰብ ችሎታችን ይጠፋል። ሙታን ምንም የሚያውቁት ነገር የለም፤ አልዓዛር ከሞት ከተነሳ በኋላ ሞቶ እያለ ስለተመለከተው ሁኔታ ምንም የተናገረው ነገር አልነበረም።—መዝሙር 146:4ን እና መክብብ 9:5, 6, 10ን አንብብ።
አምላክ የሞቱ ሰዎችን በእሳት ያቃጥላቸዋል? መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎች ምንም እንደማያውቁ ስለሚናገር ስለ ገሃነም እሳት የሚገልጸው ትምህርት አምላክን የሚያስነቅፍ የሐሰት ትምህርት እንደሆነ ግልጽ ነው። አምላክ፣ ሰዎችን በእሳት ሊያቃጥል ቀርቶ ሐሳቡ እንኳ ይዘገንነዋል።—ኤርምያስ 7:31ን አንብብ።
ስንሞት ምን እንሆናለን? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት
3. ከሙታን ጋር መነጋገር እንችላለን?
የሞቱ ሰዎች መናገርም ሆነ መስማት አይችሉም። (መዝሙር 115:17) ይሁንና ክፉ መላእክት የሞተውን ሰው መስለው በመቅረብ ከሰዎች ጋር ሊነጋገሩ ይችላሉ። (2 ጴጥሮስ 2:4) ይሖዋ ከሞቱ ሰዎች ጋር ለመነጋገር መሞከር እንደሌለብን አስጠንቅቋል።—ዘዳግም 18:10, 11ን አንብብ።
4. ትንሣኤ የሚያገኙት እነማን ናቸው?
በመቃብር ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት ተነስተው በምድር ላይ ይኖራሉ። አምላክን ሳያውቁ መጥፎ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ የነበሩ ሰዎች እንኳ ይነሳሉ።—ሉቃስ 23:43ን እና የሐዋርያት ሥራ 24:15ን አንብብ።
ከሞት የተነሱ ሰዎች ስለ አምላክ እውነቱን መማር እንዲሁም ኢየሱስን በመታዘዝ በእሱ ላይ እምነት እንዳላቸው ማሳየት ይችላሉ። (ራእይ 20:11-13) ከሞት ተነስተው መልካም ሥራዎችን የሚሠሩ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።—ዮሐንስ 5:28, 29ን አንብብ።
5. ትንሣኤ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?
አምላክ ልጁን ለእኛ ሲል እንዲሞት በመላክ ሙታን ተስፋ እንዲኖራቸው አድርጓል። በመሆኑም ትንሣኤ የይሖዋ ፍቅርና ጸጋ መገለጫ ነው። ሙታን በሚነሱበት ወቅት በተለይ ማግኘት የምትፈልገው ማንን ነው?—ዮሐንስ 3:16ን እና ሮም 6:23ን አንብብ።