በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 15

በሥራህ መደሰት ትችላለህ

በሥራህ መደሰት ትችላለህ

“ለሰው . . . ተግቶ በሚሠራው ሥራ ሁሉ ደስታ ከማግኘት የተሻለ ነገር የለም።”—መክብብ 3:13

1-3. (ሀ) ብዙ ሰዎች ስለ ሥራቸው ምን አመለካከት አላቸው? (ለ) በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን?

 በዓለም ዙሪያ ያሉ ብዙ ሰዎች ለራሳቸውም ሆነ ለቤተሰባቸው መተዳደሪያ ለማግኘት ተግተው ይሠራሉ። የሚያሳዝነው ግን ብዙዎች ሥራቸውን አይወዱትም፤ እንዲያውም አንዳንዶች ገና ወደ ሥራ ለመሄድ ሲያስቡ ጭንቅ ይላቸዋል። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ሥራህ ይበልጥ አስደሳች እንዲሆንልህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ሥራህን ልትወደው የምትችለውስ እንዴት ነው?

2 ይሖዋ እንዲህ ብሎናል፦ “ለሰው ከመብላትና ከመጠጣት እንዲሁም ተግቶ በሚሠራው ሥራ ሁሉ ደስታ ከማግኘት የተሻለ ነገር የለም። ይህ የአምላክ ስጦታ ነው።” (መክብብ 3:13) ይሖዋ የፈጠረን የመሥራት ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ነው። በሥራችን እንድንደሰትም ይፈልጋል።መክብብ 2:24⁠ን እና 5:18ን አንብብ።

3 ታዲያ በሥራችን ደስተኞች ለመሆን ምን ይረዳናል? ለክርስቲያኖች ተገቢ የማይሆኑት ምን ዓይነት ሥራዎች ናቸው? ሰብዓዊ ሥራችን ለይሖዋ አምልኮ የምናውለውን ጊዜ እንዳይሻማብን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ልናከናውነው የምንችለው ከሁሉ የላቀ ሥራስ የትኛው ነው?

ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው ሠራተኞች

4, 5. ይሖዋ ለሥራ ምን አመለካከት አለው?

4 ይሖዋ መሥራት ይወዳል። ዘፍጥረት 1:1 “በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” ይላል። አምላክ ምድርንና በምድር ላይ ያሉ ነገሮችን ሁሉ ሠርቶ ከጨረሰ በኋላ የፍጥረት ሥራው “እጅግ መልካም” እንደሆነ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 1:31) ፈጣሪያችን ባከናወነው ሥራ ተደስቷል።—1 ጢሞቴዎስ 1:11

5 ይሖዋ መቼም ቢሆን መሥራቱን አላቆመም። ኢየሱስ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው” በማለት ተናግሮ ነበር። (ዮሐንስ 5:17) ይሖዋ እስከ ዛሬ ያከናወናቸውን አስደናቂ ነገሮች በሙሉ ማወቅ ባንችልም አንዳንዶቹን ማወቅ እንችላለን። ይሖዋ፣ ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚገዙትን ሰዎች ሲመርጥ ቆይቷል። (2 ቆሮንቶስ 5:17) በተጨማሪም ለሰው ልጆች አመራር እየሰጠና የሚያስፈልጋቸውን እያሟላ ነው። ይሖዋ በዓለም ዙሪያ የስብከቱ ሥራ እንዲከናወን በማድረጉ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እሱን ማወቅና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ማግኘት ችለዋል።—ዮሐንስ 6:44፤ ሮም 6:23

6, 7. ኢየሱስ ሥራውን ያከናወነው እንዴት ነበር?

6 ኢየሱስም ቢሆን ልክ እንደ አባቱ፣ መሥራት ይወዳል። ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ቀደም ብሎ፣ በአምላክ ፊት “የተዋጣለት ሠራተኛ” የነበረ ሲሆን በሰማይም ሆነ በምድር ያሉ ነገሮችን ሁሉ በመፍጠሩ ሥራ ተካፍሏል። (ምሳሌ 8:22-31፤ ቆላስይስ 1:15-17) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣ በኋላም በትጋት መሥራቱን ቀጥሏል። ወጣት እያለ የአናጺነትን ሙያ በሚገባ የቀሰመ ሲሆን የቤት ዕቃዎችንና ቤቶችን ሳይሠራ አልቀረም። ኢየሱስ በሙያው የተካነ ሠራተኛ በመሆኑ ሰዎች “አናጺው” በማለት ይጠሩት ነበር።—ማርቆስ 6:3

7 ይሁንና ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ከምንም በላይ ቅድሚያ የሰጠው፣ ምሥራቹን ለማወጁና ሰዎችን ስለ ይሖዋ ለማስተማሩ ሥራ ነው። አገልግሎቱን በሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ ስለነበረበት ከማለዳ አንስቶ እስከ ምሽት ድረስ በትጋት ይሠራ ነበር። (ሉቃስ 21:37, 38፤ ዮሐንስ 3:2) ኢየሱስ አቧራማ በሆኑ መንገዶች ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ በተቻለው መጠን ለብዙዎች ምሥራቹን ሰብኳል።—ሉቃስ 8:1

8, 9. ኢየሱስ በሥራው እንዲደሰት የረዳው ምንድን ነው?

8 ኢየሱስ፣ አምላክ የሰጠውን ሥራ መሥራትን እንደ ምግብ ይቆጥረው ነበር። ይህን ሥራ መሥራቱ ብርታትና ጥንካሬ ሰጥቶታል። እንዲያውም አንዳንድ ቀን ኢየሱስ በሥራው ከመጠመዱ የተነሳ ምግብ ለመብላት እንኳ ፋታ አልነበረውም። (ዮሐንስ 4:31-38) ሌሎች ስለ አባቱ እንዲያውቁ ለመርዳት ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይጠቀም ነበር። “እንድሠራው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርኩህ” በማለት ለይሖዋ መናገር የቻለው ለዚህ ነው።—ዮሐንስ 17:4

9 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ በትጋት የሚሠሩ ሲሆን በሥራቸውም ደስታና እርካታ ያገኛሉ። እኛም ‘አምላክን መምሰል’ እንዲሁም የኢየሱስን ‘ፈለግ በጥብቅ መከተል’ እንፈልጋለን። (ኤፌሶን 5:1፤ 1 ጴጥሮስ 2:21) ተግተን ለመሥራትና ሥራችንን በጥራት ለማከናወን የምንጥረው ለዚህ ነው።

ለሥራችን ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

10, 11. ለሥራችን አዎንታዊ አመለካከት ለማዳበር ምን ይረዳናል?

10 የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን መተዳደሪያ ለማግኘት ተግተን እንሠራለን። በሥራችን ደስተኞች መሆን እንፈልጋለን፤ ሆኖም ይህ ቀላል የማይሆንበት ጊዜ አለ። ታዲያ ሥራችን የማያስደስተን ቢሆን ምን ማድረግ እንችላለን?

አዎንታዊ አመለካከት መያዛችን ማንኛውንም ሥራ በደስታ ለማከናወን ያስችለናል

11 አዎንታዊ አመለካከት ማዳበር። ሥራ መቀየር ወይም የምንሠራበትን ሰዓት መቀነስ ባንችልም እንኳ አመለካከታችንን ማስተካከል እንችላለን። ይሖዋ ምን እንደሚጠብቅብን ማወቃችን ይህን ለማድረግ ይረዳናል። ለምሳሌ፣ ይሖዋ አንድ የቤተሰብ ራስ የቤተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ እንዲያደርግ ይጠብቅበታል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር የማያቀርብ ሰው “እምነት የለሽ ከሆነ ሰው የከፋ ነው” ይላል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) አንተም የቤተሰብ ራስ ከሆንክ የቤተሰብህን ፍላጎት ለማሟላት ተግተህ እንደምትሠራ የታወቀ ነው። የምትሠራውን ሥራ ወደድከውም አልወደድከው፣ የቤተሰብህን ፍላጎት ለማሟላት የምትጥር ከሆነ ይሖዋ እንደሚደሰትብህ ታውቃለህ።

12. ታታሪና ሐቀኛ ሠራተኞች መሆናችን ምን ጥቅሞች ያስገኝልናል?

12 ታታሪና ሐቀኛ መሆን። ይህን ማድረጋችን በሥራችን ደስታ ለማግኘት ይረዳናል። (ምሳሌ 12:24፤ 22:29) ታታሪና ሐቀኛ መሆናችን ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች አንዱ፣ የአሠሪያችንን አመኔታ ማትረፋችን ነው። ሐቀኛ የሆኑ ሠራተኞች ገንዘብና ንብረት ስለማይሰርቁ እንዲሁም የሥራ ሰዓት ስለማያባክኑ አሠሪዎቻቸው ያከብሯቸዋል። (ኤፌሶን 4:28) በዋነኝነት ደግሞ፣ ታታሪና ሐቀኛ መሆናችንን ይሖዋ ይመለከታል። “ሐቀኛ ሕሊና” ያለን መሆኑ እንዲሁም የምንወደውን አምላክ እያስደሰትን እንዳለን ማወቃችን እርካታ ያስገኝልናል።—ዕብራውያን 13:18፤ ቆላስይስ 3:22-24

13. በሥራ ቦታችን ሐቀኛ መሆናችን ምን ሌላ ጥቅም አለው?

13 በሥራ ቦታችን የምናሳየው ምግባር ይሖዋን እንደሚያስከብር ማስታወስ። በሥራችን ደስተኛ ለመሆን አስተዋጽኦ ከሚያበረክቱት ነገሮች አንዱ ይህ ነው። (ቲቶ 2:9, 10) አንተ በምታሳየው መልካም ምግባር የተነሳ ከሥራ ባልደረቦችህ አንዱ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል።ምሳሌ 27:11ን እና 1 ጴጥሮስ 2:12ን አንብብ።

ምን ዓይነት ሥራ መምረጥ ይኖርብኛል?

14-16. ሥራ በምትመርጥበት ጊዜ የትኞቹን ነገሮች ከግምት ማስገባት ይኖርብሃል?

14 ክርስቲያኖች የትኞቹን ሥራዎች መሥራት እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው የሚገልጽ ዝርዝር መመሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ከሥራ ምርጫ ጋር በተያያዘ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱን መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዟል። (ምሳሌ 2:6) የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በአእምሯችን በመያዝ ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን እንጠይቅ፦

ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር የማይጋጭ ሥራ ለማግኘት ጥረት አድርግ

15 ይህ ሥራ ይሖዋ የሚያወግዘውን ነገር እንድሠራ ያደርገኛል? ይሖዋ እንደ መስረቅና መዋሸት ያሉትን ድርጊቶች እንደሚጠላ ተምረናል። (ዘፀአት 20:4፤ ኤፌሶን 4:28፤ ራእይ 21:8) በመሆኑም ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር የሚጋጭ ማንኛውንም ሥራ ላለመሥራት እንጠነቀቃለን።1 ዮሐንስ 5:3ን አንብብ።

16 ይህ ሥራ ይሖዋ የሚያወግዘውን ድርጊት የሚደግፍ ነው? ለምሳሌ አንዲት እህት፣ በደም ባንክ እንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ ሥራ ብታገኝ ምን ማድረግ ይኖርባታል? እንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ መሥራት ስህተት እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ሆኖም ይሖዋ ደምን በተመለከተ ምን መመሪያ እንደሰጠን እናውቃለን። ይህች እህት ደም ከመለገስ ጋር በተያያዙ ሥራዎች በቀጥታ ባትካፈልም እንኳ ለሥራው ድጋፍ በመስጠቷ በይሖዋ ዘንድ ተጠያቂ አትሆንም?—የሐዋርያት ሥራ 15:29

17. አምላክን የሚያስደስት ውሳኔ ለማድረግ ምን ይረዳናል?

17 አምላክ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች በመጠቀም በዕብራውያን 5:14 ላይ እንደተገለጹት ሰዎች ማድረግ እንችላለን፤ እነዚህ ሰዎች “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት [አሠልጥነዋል]።” ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ይህን ሥራ ብሠራ ሌሎች ይሰናከላሉ? ሥራው ከባለቤቴና ከልጆቼ ተለይቼ ራቅ ወዳለ ቦታ ወይም አገር እንድሄድ ያስገድደኛል? ይህን ማድረጌ በቤተሰቤ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?’

“ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች” ለይታችሁ እወቁ

18. ለአምልኳችን ቅድሚያ መስጠት ተፈታታኝ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

18 “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” በተባለው በዛሬው ጊዜ፣ በሕይወታችን ውስጥ የይሖዋን አምልኮ ማስቀደም ቀላል አይደለም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ሥራ ማግኘትም ሆነ ከሥራ ሳይፈናቀሉ መቀጠል ተፈታታኝ ነው። ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ማቅረብ ቢኖርብንም ለአምልኳችን ቅድሚያ መስጠት እንዳለብን እናውቃለን። ቁሳዊ ነገሮች በሕይወታችን ውስጥ ዋነኛውን ቦታ እንዲይዙ መፍቀድ አይኖርብንም። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ታዲያ ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ነገር ሳናጓድል፣ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች” ለይተን እንደምናውቅ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?—ፊልጵስዩስ 1:10

19. በይሖዋ መታመናችን ሥራን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት ለመያዝ ይረዳናል የምንለው ለምንድን ነው?

19 በይሖዋ ሙሉ በሙሉ ታመኑ። (ምሳሌ 3:5, 6ን አንብብ።) አምላክ፣ ምን እንደሚያስፈልገን በሚገባ እንደሚያውቅ እንዲሁም በጥልቅ እንደሚያስብልን እናውቃለን። (መዝሙር 37:25፤ 1 ጴጥሮስ 5:7) ቃሉ እንዲህ ይላል፦ “አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ። [አምላክ] ‘ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም’ ብሏልና።” (ዕብራውያን 13:5) ይሖዋ ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ነገር ስለ ማቅረብ ነጋ ጠባ እንድንጨነቅ አይፈልግም። ደግሞም የአገልጋዮቹን ፍላጎት ማሟላት እንደሚችል በተደጋጋሚ አሳይቷል። (ማቴዎስ 6:25-32) ሥራችን ምንም ይሁን ምን የአምላክን ቃል አዘውትረን ከማጥናት፣ ምሥራቹን ከመስበክ እንዲሁም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ ከመገኘት እንዲያግደን አንፈቅድም።—ማቴዎስ 24:14፤ ዕብራውያን 10:24, 25

20. አኗኗራችን ቀላል እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

20 ዓይናችሁ በአንድ ነገር ላይ ያተኮረ ይሁን። (ማቴዎስ 6:22, 23ን አንብብ።) ይህ ሲባል፣ ይሖዋን በማገልገል ላይ ለማተኮር ስንል አኗኗራችንን ቀላል ማድረግ ማለት ነው። ገንዘብና የተደላደለ ሕይወት ወይም ዘመናዊ የሚባሉት ዕቃዎች፣ ከአምላክ ጋር ከመሠረትነው ወዳጅነት ይበልጥ በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲይዙ ማድረግ ሞኝነት መሆኑን እንገነዘባለን። ታዲያ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ቅድሚያ ለመስጠት ምን ይረዳናል? ዕዳ ውስጥ ላለመግባት የቻልነውን ያህል መጠንቀቅ ይኖርብናል። ዕዳ ካለባችሁ ደግሞ ዕዳውን ለመቀነስ አሊያም ከፍላችሁ ለመጨረስ ዕቅድ አውጡ። ካልተጠነቀቅን ቁሳዊ ነገሮች ጊዜያችንንና ጉልበታችንን በመሻማት ለጸሎት፣ ለጥናትና ለአገልግሎት የሚሆን ጊዜ ሊያሳጡን ይችላሉ። ቁሳዊ ነገሮች ሕይወታችንን እንዲያወሳስቡት ከመፍቀድ ይልቅ እንደ “ምግብና ልብስ” ባሉት መሠረታዊ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:8) ደግሞም ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋን ይበልጥ ለማገልገል ምን ማድረግ እንደምንችል አልፎ አልፎ ቆም ብለን ማሰባችን ጠቃሚ ነው።

21. በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን ነገር አስቀድመን መወሰናችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

21 ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን አስቀድሙ። ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን እና ቁሳዊ ንብረቶቻችንን በአግባቡ መጠቀም ይገባናል። ካልተጠነቀቅን እንደ ትምህርት ወይም ገንዘብ ያሉ ትልቅ ቦታ ሊሰጣቸው የማይገቡ ነገሮች ውድ ጊዜያችንን ሊያባክኑብን ይችላሉ። ኢየሱስ “ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥት . . . ፈልጉ” ብሏል። (ማቴዎስ 6:33) በሕይወታችን ውስጥ የምናደርጋቸው ምርጫዎች፣ ያሉን ልማዶች፣ የዕለት ተዕለት አኗኗራችን እንዲሁም ግቦቻችን በልባችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ነገር ምን እንደሆነ ይጠቁማሉ።

ልናከናውነው የምንችለው ከሁሉ የላቀ ሥራ

22, 23. (ሀ) ክርስቲያኖች ልናከናውነው የምንችለው ከሁሉ የላቀ ሥራ የትኛው ነው? (ለ) በሥራችን ደስተኞች ለመሆን ምን ሊረዳን ይችላል?

22 ልናከናውነው የምንችለው ከሁሉ የላቀ ሥራ ይሖዋን ማገልገልና ምሥራቹን ለሌሎች መስበክ ነው። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ኢየሱስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም በዚህ ሥራ አቅማችን የፈቀደውን ያህል መካፈል እንፈልጋለን። አንዳንዶች፣ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች ተዛውረዋል። የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ ሰዎች ለመመሥከር ሲሉ የእነሱን ቋንቋ የተማሩ ክርስቲያኖችም አሉ። እንዲህ ዓይነት እርምጃ የወሰዱ ክርስቲያኖችን ለምን ተሞክሯቸውን አትጠይቃቸውም? እነዚህ ክርስቲያኖች ሕይወታቸው ይበልጥ አስደሳችና ትርጉም ያለው እንደሆነላቸው ይነግሩሃል።ምሳሌ 10:22ን አንብብ።

ልናከናውነው የምንችለው ከሁሉ የላቀ ሥራ ይሖዋን ማገልገል ነው

23 በዛሬው ጊዜ ብዙዎቻችን የቤተሰባችንን መሠረታዊ ፍላጎት ለማሟላት ስንል ረጅም ሰዓት ለመሥራት አሊያም ከአንድ በላይ ሥራ ለመያዝ እንገደዳለን። ይሖዋ ይህን ይመለከታል፤ እንዲሁም ቤተሰባችንን ለመንከባከብ የምናደርገውን ጥረት ያደንቃል። እንግዲያው ሥራችን ምንም ይሁን ምን፣ ሁላችንም የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ትጉ ሠራተኞች ለመሆን እንጣር። እንዲሁም ከሁሉ የላቀው ሥራችን ይሖዋን ማገልገልና የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች መስበክ መሆኑን እናስታውስ። ይህ እውነተኛ ደስታ ያስገኝልናል።