በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 2

በአምላክ ፊት ጥሩ ሕሊና መያዝ

በአምላክ ፊት ጥሩ ሕሊና መያዝ

“ጥሩ ሕሊና ይኑራችሁ።”—1 ጴጥሮስ 3:16

1, 2. በማታውቀው አካባቢ ስትጓዝ መሪ የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው? ይሖዋ እንደ መሪ ሆኖ የሚያገለግለንን የትኛውን ስጦታ ሰጥቶናል?

 ወደ አንድ ቦታ ለመሄድ አስበሃል እንበል። ያሰብክበት ቦታ ለመድረስ ጭው ያለ በረሃ ማቋረጥ አለብህ። በጉዞህ ላይ አቅጣጫህን ስተህ እንዳትጠፋ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? የሚመራህ ሰው አሊያም አቅጣጫ ለማወቅ የሚረዳህ ነገር ማግኘት ያስፈልግሃል። ኮምፓስ፣ ፀሐይና ከዋክብት ወይም ካርታ አቅጣጫ ለማወቅ ይረዱሃል፤ በረሃውን በሚገባ የሚያውቅ ሰው አብሮህ ካለም አቅጣጫውን ሊጠቁምህ ይችላል። እነዚህ በጣም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው፤ ምክንያቱም የምትጓዝበትን አቅጣጫ ማወቅህ ሕይወትህን ከአደጋ ሊጠብቀው ይችላል።

2 ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ በርካታ ችግሮች ያጋጥሙናል፤ በመሆኑም አቅጣጫው እንደጠፋው ሰው አንዳንድ ጊዜ ግራ እንጋባ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ለሁላችንም ሕሊና ሰጥቶናል፤ ሕሊናችን እንደ መሪ ሆኖ ያገለግለናል። (ያዕቆብ 1:17) ለመሆኑ ሕሊና ምንድን ነው? የሚሠራውስ እንዴት ነው? ሕሊናችንን ማሠልጠን የምንችለው እንዴት ነው? የሌሎችን ሕሊና ግምት ውስጥ ማስገባት ያለብን ለምንድን ነው? ንጹሕ ሕሊና የተሻለ ሕይወት ለመምራት የሚረዳንስ እንዴት ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እስቲ እንመልከት።

ሕሊና ምንድን ነው? የሚሠራውስ እንዴት ነው?

3. ሕሊና ምንድን ነው?

3 ሕሊና ከይሖዋ ያገኘነው ግሩም ስጦታ ነው። ሕሊና፣ ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ለመለየት የሚረዳ በተፈጥሮ ያገኘነው ችሎታ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ሕሊና” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ስለ ራስ ያለ እውቀት” የሚል ፍቺ አለው። ሕሊናችን በትክክል የሚሠራ ከሆነ ራሳችንን እንድንገመግም ይረዳናል። ውስጣዊ ሐሳባችንንና ስሜታችንን በሐቀኝነት ለመመርመር ያስችለናል። መልካም የሆነውን እንድናደርግና ከመጥፎ ነገር እንድንርቅ ይገፋፋናል። በተጨማሪም ውሳኔያችን ትክክለኛ ሲሆን እንድንደሰት፣ የተሳሳተ ውሳኔ ስናደርግ ደግሞ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል።—ተጨማሪ ሐሳብ 5⁠ን ተመልከት።

4, 5. (ሀ) አዳምና ሔዋን ሕሊናቸውን ላለመስማት መምረጣቸው ምን አስከትሏል? (ለ) ሕሊና የሚሠራበትን መንገድ የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ጥቀስ።

4 ሕሊናችን የሚነግረንን መስማት ወይም አለመስማት ለእያንዳንዳችን የተተወ ጉዳይ ነው። አዳምና ሔዋን ሕሊናቸውን ላለመስማት ስለመረጡ ኃጢአት ሠርተዋል። እርግጥ በኋላ ላይ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቷቸዋል፤ ግን ይህ የሚያመጣው ለውጥ አልነበረም። ምክንያቱም የአምላክን ትእዛዝ ጥሰዋል። (ዘፍጥረት 3:7, 8) ሁለቱም ፍጹም ሕሊና የነበራቸው ከመሆኑም ሌላ አምላክን አለመታዘዝ ስህተት መሆኑን ያውቁ ነበር፤ ሆኖም ሕሊናቸውን ላለመስማት መርጠዋል።

5 ከአዳምና ከሔዋን በተለየ፣ ፍጹም ያልሆኑ በርካታ ሰዎች ሕሊናቸው የሚነግራቸውን ሰምተዋል። ኢዮብ በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። ኢዮብ ሕሊናውን በማዳመጥ ጥሩ ውሳኔዎችን ስላደረገ “በሕይወት ዘመኔም ሁሉ ልቤ አይኮንነኝም” ብሎ መናገር ችሏል። (ኢዮብ 27:6) ኢዮብ “ልቤ” ሲል ስለ ሕሊናው ማለትም ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር ለመለየት ስለሚረዳው ችሎታ መግለጹ ነበር። በሌላ በኩል ግን ዳዊት ሕሊናው የሚነግረውን ችላ በማለት የይሖዋን ትእዛዝ የጣሰባቸው ጊዜያት ነበሩ። እርግጥ ነው፣ በኋላ ላይ የጥፋተኝነት ስሜት ስለተሰማው ‘ልቡ ወቅሶታል።’ (1 ሳሙኤል 24:5) ይህም ዳዊት የተሳሳተ ነገር በማድረጉ ሕሊናው እንደወቀሰው የሚያሳይ ነው። ዳዊት ሕሊናው የሚነግረውን ነገር መስማቱ ተመሳሳይ ስህተት በድጋሚ እንዳይፈጽም ይረዳዋል።

6. ሕሊና አምላክ ለሰው ዘር ሁሉ የሰጠው ስጦታ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

6 ይሖዋን የማያውቁ ሰዎችም እንኳ ትክክል ወይም ስህተት የሆኑ ነገሮች እንዳሉ አብዛኛውን ጊዜ አይጠፋቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሐሳባቸው በውስጣቸው እየተሟገተ አንዴ ይከሳቸዋል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጥፋተኛ አይደላችሁም ይላቸዋል” በማለት ይናገራል። (ሮም 2:14, 15) ለምሳሌ ያህል፣ አብዛኞቹ ሰዎች መግደል ወይም መስረቅ ስህተት እንደሆነ ያውቃሉ። ይህን እንዲገነዘቡ ያደረጋቸው ሕሊናቸው ማለትም ይሖዋ በውስጣቸው ያስቀመጠው ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን የመለየት ችሎታ ነው፤ እነዚህ ሰዎች ባያስተውሉትም እንኳ ሕሊናቸውን እያዳመጡ ነው። በተጨማሪም የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶች እየተከተሉ ነው ማለት ይቻላል፤ መሠረታዊ ሥርዓቶች፣ ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ ጥሩ ውሳኔዎች ማድረግ እንድንችል እኛን ለመርዳት ሲል ያስቀመጠልን መሠረታዊ እውነታዎች ናቸው።

7. ሕሊናችን አንዳንድ ጊዜ ሊሳሳት የሚችለው ለምንድን ነው?

7 እርግጥ ሕሊናችን አንዳንድ ጊዜ ሊሳሳት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ፍጹም ባለመሆናችን የተነሳ አስተሳሰባችንና ስሜታችን ሕሊናችንን ሊያዛቡት ይችላሉ፤ በዚህም ምክንያት ሕሊናችን በተሳሳተ አቅጣጫ ሊመራን ይችላል። ጥሩ ሕሊና በተፈጥሮ የምናገኘው ነገር አይደለም። በመሆኑም ሕሊናችን መሠልጠን ያስፈልገዋል። ዮሴፍ የተሳሳተ ነገር ከመፈጸም እንዲቆጠብ የረዳው ጥሩ ሕሊና ነው። (ዘፍጥረት 39:1, 2, 7-12) ሕሊናችንን ማሠልጠን እንድንችል ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱንና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሰጥቶናል። (ሮም 9:1) ሕሊናችንን ማሠልጠን የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ሕሊናችንን ማሠልጠን የምንችለው እንዴት ነው?

8. (ሀ) ስሜታችን በሕሊናችን ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? (ለ) ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ አለብን?

8 አንዳንዶች ሕሊናቸውን መስማት ሲባል ስሜታቸውን ማዳመጥ ማለት እንደሆነ ይሰማቸዋል። እነሱን እስካስደሰታቸው ድረስ የፈለጉትን ቢያደርጉ ምንም ችግር እንደሌለው ያስባሉ። ሆኖም ፍጹም ባለመሆናችን ስሜታችን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ሊመራን ይችላል። ስሜታችን በሕሊናችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የማሳደር ኃይል አለው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ልብ ከምንም ነገር በላይ ከዳተኛ ነው፤ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ አይመለስም። ማንስ ሊያውቀው ይችላል?” (ኤርምያስ 17:9) በመሆኑም ስህተት የሆነውን ነገር እንኳ ትክክል እንደሆነ አድርገን ልናስብ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት በአምላክ ሕዝቦች ላይ ከባድ ስደት ያደርስ የነበረ ሲሆን ድርጊቱም ትክክል እንደሆነ ይሰማው ነበር። ጳውሎስ ጥሩ ሕሊና እንዳለው ያስብ ነበር። ይሁንና ጳውሎስ፣ ስለ ድርጊቱ ይሖዋ ምን አመለካከት እንዳለው ሲያውቅ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልገው ተገንዝቧል። ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ንጹሕ ሕሊና መያዝ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነም ተረድቷል። (የሐዋርያት ሥራ 23:1፤ 1 ቆሮንቶስ 4:4፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:3) ከዚህ መማር እንደምንችለው፣ ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት ‘ይሖዋ የሚፈልገው ምን እንዳደርግ ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው።

9. አምላክን መፍራት ሲባል ምን ማለት ነው?

9 አንድን ሰው የምትወደው ከሆነ ግለሰቡን ላለማሳዘን እንደምትጠነቀቅ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም ይሖዋን ስለምንወደው እሱን የሚያሳዝን ምንም ነገር ማድረግ አንፈልግም። ይሖዋን እንዳናሳዝነው ልንፈራ ማለትም ፈሪሃ አምላክ ሊኖረን ይገባል። ነህምያ በዚህ ረገድ ምሳሌ ይሆነናል። የሕዝቡ ገዢ ቢሆንም ሥልጣኑን ተጠቅሞ ለመበልጸግ አልሞከረም። ነህምያ እንዲህ ያላደረገው ለምንድን ነው? ‘አምላክን ስለሚፈራ’ መሆኑን ተናግሯል። (ነህምያ 5:15) ነህምያ ይሖዋን የሚያሳዝን ምንም ነገር ማድረግ አልፈለገም። እንደ ነህምያ ሁሉ እኛም፣ መጥፎ ነገር በመፈጸም ይሖዋን እንዳናሳዝን እንፈራለን። ይሖዋን የሚያስደስተው ምን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ማወቅ እንችላለን።—ተጨማሪ ሐሳብ 6⁠ን ተመልከት።

10, 11. ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው?

10 ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ክርስቲያን ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ ውሳኔ ማድረግ ያስፈልገው ይሆናል። በዚህ ረገድ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱት የትኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው? እስቲ ጥቂቶቹን እንመልከት፦ መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጥ መጠጣትን አይከለክልም። እንዲያውም የወይን ጠጅ ከአምላክ ያገኘነው ስጦታ እንደሆነ ይናገራል። (መዝሙር 104:14, 15) ሆኖም ኢየሱስ ተከታዮቹን ‘ከልክ በላይ እንዳይጠጡ’ አሳስቧቸዋል። (ሉቃስ 21:34) ጳውሎስም ‘መረን ከለቀቀ ፈንጠዝያና ከስካር’ እንዲርቁ ክርስቲያኖችን መክሯቸዋል። (ሮም 13:13) በተጨማሪም “ሰካራሞች . . . የአምላክን መንግሥት አይወርሱም” በማለት ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

11 አንድ ክርስቲያን እንደሚከተለው ብሎ ራሱን መጠየቅ ይችላል፦ ‘ለመጠጥ ምን ያህል ቦታ እሰጣለሁ? ዘና እንዳልኩ የሚሰማኝ ስጠጣ ብቻ ነው? አልኮል የምጠጣው ድፍረት እንዲሰጠኝ ስል ነው? የምጠጣውን መጠን መቆጣጠር እችላለሁ? አዘውትሬ ካልጠጣሁ እቸገራለሁ? * ከጓደኞቼ ጋር ስዝናና የግድ የአልኮል መጠጥ መኖር እንዳለበት ይሰማኛል?’ በተጨማሪም ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ እንዲረዳን ይሖዋን መለመናችን በጣም አስፈላጊ ነው። (መዝሙር 139:23, 24ን አንብብ።) በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ማሰላሰላችንና ራሳችንን በሐቀኝነት መገምገማችን ሕሊናችንን ለማሠልጠን ይረዳናል። ይሁንና ቀጥለን እንደምንመለከተው ልናስብበት የሚገባ ሌላም ነገር አለ።

የሌሎችን ሕሊና ግምት ውስጥ ማስገባት ያለብን ለምንድን ነው?

12, 13. የሁሉም ሰው ሕሊና ተመሳሳይ ያልሆነው ለምንድን ነው? የሌሎች ሕሊና ከእኛ የተለየ በሚሆንበት ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

12 የሁሉም ሰው ሕሊና ተመሳሳይ አይደለም። የአንተ ሕሊና የሚፈቅደውን ነገር የሌላው ሰው ሕሊና ላይፈቅድለት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የአንተ ሕሊና የአልኮል መጠጥ ለመጠጣት ይፈቅድልህ ይሆናል፤ በሌላ በኩል ደግሞ መጠጣት እንደሌለበት የሚሰማው ሰው ይኖራል። ሁለት ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያየ አመለካከት ሊኖራቸው የቻለው ለምንድን ነው?

በሚገባ የሠለጠነ ሕሊና የአልኮል መጠጥ ለመጠጣት ወይም ላለመጠጣት እንድትወስን ይረዳሃል

13 አንድ ሰው ያደገበት አካባቢ፣ የቤተሰቡ አመለካከት፣ በሕይወቱ ውስጥ ያጋጠሙት ሁኔታዎች እንዲሁም ሌሎች ነገሮች ስለ አንድ ጉዳይ በሚኖረው አመለካከት ላይ ብዙውን ጊዜ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፤ ቀደም ሲል ከመጠን በላይ የመጠጣት ችግር የነበረበት ሰው ጨርሶ ላለመጠጣት ሊወስን ይችላል። (1 ነገሥት 8:38, 39) ታዲያ አንድን ሰው መጠጥ ስትጋብዘው ግብዣውን ባይቀበል ቅር ይልሃል? ካልጠጣህ ብለህ ትጫነዋለህ? አሊያም ደግሞ የማይጠጣበትን ምክንያት እንዲነግርህ ትወተውተዋለህ? የግለሰቡን ሕሊና የምታከብር ከሆነ እንዲህ አታደርግም።

14, 15. ጳውሎስ በኖረበት ዘመን ምን ዓይነት ሁኔታ ነበረ? ጳውሎስ ምን ግሩም ምክር ሰጥቷል?

14 ሐዋርያው ጳውሎስ በኖረበት ዘመን የተፈጠረ አንድ ሁኔታ የሰዎች ሕሊና የተለያየ እንደሆነ ያሳያል። በዚያ ዘመን፣ ለጣዖታት መሥዋዕት ሆኖ የቀረበ ሥጋ ገበያ ላይ ይሸጥ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 10:25) ጳውሎስ እንዲህ ያለውን ሥጋ ገዝቶ መብላትን ስህተት አድርጎ አልተመለከተውም። ጳውሎስ ሁሉንም ምግብ የሰጠን ይሖዋ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ቀደም ሲል ጣዖታትን ያመልኩ የነበሩ አንዳንድ ወንድሞች ግን ከዚህ የተለየ አመለካከት ነበራቸው። ለጣዖታት ተሠውቶ የነበረን ሥጋ መብላት ስህተት እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር። ታዲያ ጳውሎስ ‘ሕሊናዬን እስካልረበሸው ድረስ የፈለግኩትን ብበላ መብቴ ነው’ ብሎ አሰበ?

15 ጳውሎስ እንዲህ ብሎ አላሰበም። ለወንድሞቹ ስሜት ትልቅ ቦታ ስለሚሰጥ አንዳንድ መብቶቹን ለመተው ፈቃደኛ ነበር። ጳውሎስ “ራሳችንን የምናስደስት መሆን የለብንም” ብሏል። አክሎም “ክርስቶስ እንኳ ራሱን አላስደሰተም” በማለት ተናግሯል። (ሮም 15:1, 3) እንደ ኢየሱስ ሁሉ ጳውሎስም ከራሱ ይበልጥ ስለ ሌሎች ስሜት ያስብ ነበር።—1 ቆሮንቶስ 8:13⁠ን እና 10:23, 24, 31-33ን አንብብ።

16. የወንድማችን ሕሊና የሚፈቅድለትን ነገር እኛ ስህተት እንደሆነ አድርገን የምንመለከተው ቢሆን በወንድማችን ላይ መፍረድ የሌለብን ለምንድን ነው?

16 ይሁን እንጂ የሌላው ሰው ሕሊና የሚፈቅድለትን ነገር እኛ ስህተት እንደሆነ አድርገን የምንመለከተው ቢሆንስ? ግለሰቡ እንደተሳሳተና እኛ ትክክል እንደሆንን በመናገር ግለሰቡን ላለመንቀፍ በጣም መጠንቀቅ ይኖርብናል። (ሮም 14:10ን አንብብ።) ይሖዋ ሕሊና የሰጠን በራሳችን ላይ እንጂ በሌሎች ላይ እንድንፈርድ አይደለም። (ማቴዎስ 7:1) በግል ምርጫችን ምክንያት በጉባኤ ውስጥ መከፋፈል እንዲፈጠር በፍጹም አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ በመካከላችን ፍቅርና አንድነት እንዲሰፍን ለማድረግ እንጥራለን።—ሮም 14:19

ጥሩ ሕሊና መያዝ የሚያስገኘው ጥቅም

17. የአንዳንድ ሰዎች ሕሊና ምን ሆኗል?

17 ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጥሩ ሕሊና ይኑራችሁ” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 3:16) የሚያሳዝነው ግን ይሖዋ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተደጋጋሚ ችላ የሚሉ ሰዎች ሕሊና፣ ውሎ አድሮ እነሱን ማስጠንቀቅ ያቆማል። ጳውሎስ እንዲህ ያሉት ሰዎች “በጋለ ብረት የተተኮሰ ያህል ሕሊናቸው የደነዘዘባቸው” እንደሆኑ ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 4:2) የጋለ ብረት አቃጥሎህ ያውቃል? እንዲህ ዓይነት ነገር ካጋጠመህ ቆዳህ በጣም ስለሚቃጠል ይደነዝዛል። በተመሳሳይም አንድ ሰው በተደጋጋሚ መጥፎ ነገር የሚፈጽም ከሆነ ሕሊናው ‘ስለሚደነዝዝ’ ከጊዜ በኋላ መሥራቱን ያቆማል።

ጥሩ ሕሊና በሕይወታችን ውስጥ ሊመራን እንዲሁም ደስታና ውስጣዊ ሰላም ሊያስገኝልን ይችላል

18, 19. (ሀ) የጥፋተኝነትና የኀፍረት ስሜት ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል? (ለ) ለኃጢአታችን ንስሐ ከገባን በኋላም የጥፋተኝነት ስሜት የሚሰማን ከሆነ ምን ማድረግ እንችላለን?

18 ሕሊናችን ስህተት እንደፈጸምን ሲነግረን የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማናል። ይህም የሠራነውን ስህተት ለይተን ለማወቅ ይረዳናል። በመሆኑም ከስህተታችን በመማር ይህን ድርጊት በድጋሚ ከመፈጸም እንቆጠባለን። ለምሳሌ ያህል፣ ንጉሥ ዳዊት ኃጢአት ከፈጸመ በኋላ ሕሊናው ስለወቀሰው ንስሐ ገብቷል። የፈጸመውን ድርጊት የተጸየፈው ሲሆን ከዚያ በኋላ የይሖዋን ትእዛዝ ላለመጣስ ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል። ዳዊት በሕይወቱ ካጋጠመው ነገር በመነሳት፣ ይሖዋ ‘ጥሩና ይቅር ለማለት ዝግጁ’ እንደሆነ ተናግሯል።—መዝሙር 51:1-19፤ 86:5ተጨማሪ ሐሳብ 7⁠ን ተመልከት።

19 ይሁንና አንድ ሰው ለሠራው ኃጢአት ንስሐ ከገባ ከረጅም ጊዜ በኋላም የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማው ይችላል። እንዲህ ያለው ስሜት ግለሰቡን ሊያሠቃየውና ዋጋ ቢስ እንደሆነ እንዲሰማው ሊያደርግ ይችላል። አንተም አልፎ አልፎ እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ያለፈውን ነገር መለወጥ እንደማትችል ማስታወስ ይኖርብሃል። ድርጊቱን የፈጸምከው፣ ስህተት መሆኑን እያወቅክ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ይቅር ብሎሃል፤ የሠራኸው ኃጢአትም ተደምስሷል። ይሖዋ ንጹሕ እንደሆንክ አድርጎ ይመለከትሃል፤ አንተም ብትሆን በአሁኑ ወቅት፣ ትክክል የሆነውን ነገር እያደረግክ እንዳለህ ታውቃለህ። እንደዚያም ሆኖ ልብህ ሊኮንንህ ይችላል፤ ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው” እንደሚል አስታውስ። (1 ዮሐንስ 3:19, 20ን አንብብ።) ይህም ሲባል የይሖዋ ፍቅርና ምሕረት ማንኛውንም የጥፋተኝነትና የኀፍረት ስሜት ለማሸነፍ ይረዳናል ማለት ነው። ይሖዋ ይቅር እንዳለህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። አንድ ሰው ይሖዋ ይቅር እንዳለው አምኖ ሲቀበል ሕሊናው ሰላም ይሰጠዋል፤ እንዲሁም አምላክን በደስታ ማገልገል ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 6:11፤ ዕብራውያን 10:22

20, 21. (ሀ) ይህ መጽሐፍ ምን ለማድረግ ይረዳሃል? (ለ) ይሖዋ የሰጠንን ነፃነት እንዴት ልንጠቀምበት ይገባል?

20 ይህ መጽሐፍ የተዘጋጀው ሕሊናህን ለማሠልጠን እንዲረዳህ ታስቦ ነው፤ ሕሊናህ ከሠለጠነ በእነዚህ አስቸጋሪ የመጨረሻ ቀናት ማስጠንቀቂያ ሊሰጥህና ጥበቃ ሊሆንልህ ይችላል። በተጨማሪም በሕይወትህ ውስጥ ከሚያጋጥሙህ የተለያዩ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳሃል። እርግጥ ይህ መጽሐፍ በእያንዳንዱ ሁኔታ ምን ማድረግ እንዳለብን የሚገልጽ ዝርዝር መመሪያ አልያዘም። የምንመራው አምላክ ባወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ በተመሠረተውና ነፃነት በሚሰጠው ‘የክርስቶስ ሕግ’ ነው። (ገላትያ 6:2) ይሁንና አንድን ጉዳይ በተመለከተ ቀጥተኛ ሕግ አለመኖሩ መጥፎ ነገር ለመፈጸም ሰበብ ሊሆነን አይገባም። (2 ቆሮንቶስ 4:1, 2፤ ዕብራውያን 4:13፤ 1 ጴጥሮስ 2:16) ከዚህ ይልቅ ነፃነታችንን ለይሖዋ ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ እንጠቀምበታለን።

21 በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ማሰላሰላችንና እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረጋችን፣ ‘የማስተዋል ችሎታችንን’ ለማሠራት እንዲሁም የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ይረዳናል። (ዕብራውያን 5:14) ይህም በሕይወታችን ውስጥ የሚመራንና ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር የሚረዳን የሠለጠነ ሕሊና እንድንይዝ ያደርጋል።

^ የአልኮል ሱሰኛ የሆኑ ሰዎች፣ የሚጠጡትን መጠን መቆጣጠር በጣም እንደሚያስቸግራቸው ብዙ ሐኪሞች ይናገራሉ። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች ጨርሶ ባይጠጡ የተሻለ እንደሆነ ሐኪሞች ይመክራሉ።