በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተጨማሪ ሐሳብ

ተጨማሪ ሐሳብ

 1 መሠረታዊ ሥርዓቶች

የአምላክ ሕጎች የተመሠረቱት እሱ ባወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ነው። እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ እውነታዎች ናቸው። መሠረታዊ ሥርዓቶች የአምላክን አስተሳሰብና ስሜት ለማወቅ ያስችሉናል። ከዚህም ሌላ በሕይወታችን ውስጥ ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግና ትክክለኛ የሆነውን አካሄድ ለመከተል ይረዱናል። በተለይም ደግሞ አምላክ ቀጥተኛ ሕግ ካልሰጠባቸው ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ምን ማድረግ እንዳለብን ለመወሰን ይጠቅሙናል።

ምዕራፍ 1 አንቀጽ 8

 2 መታዘዝ

ይሖዋን መታዘዝ ሲባል እሱ የሚነግረንን ነገር በፈቃደኝነት ማድረግ ማለት ነው። ይሖዋ ለእሱ ባለን ፍቅር ተነሳስተን እንድንታዘዘው ይፈልጋል። (1 ዮሐንስ 5:3) አምላክን የምንወደውና የምንተማመንበት ከሆነ የሚሰጠንን ምክር በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች እንከተላለን። እሱን መታዘዝ አስቸጋሪ እንደሆነ በሚሰማን ጊዜም ጭምር እንታዘዘዋለን። ይሖዋን መታዘዝ ጥቅሙ ለራሳችን ነው፤ ምክንያቱም ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ የተሻለ ሕይወት መምራት የምንችልበትን መንገድ ያስተምረናል፤ ወደፊት ደግሞ የተትረፈረፈ በረከት እንደምናገኝ ቃል ገብቶልናል።—ኢሳይያስ 48:17

ምዕራፍ 1 አንቀጽ 10

 3 የመምረጥ ነፃነት

ይሖዋ ለሁላችንም የመምረጥ ነፃነት ማለትም የራሳችንን ምርጫ የማድረግ ችሎታ ሰጥቶናል። ይሖዋ የፈጠረን እንደ ሮቦት አድርጎ አይደለም። (ዘዳግም 30:19፤ ኢያሱ 24:15) እሱ የሰጠንን ነፃነት ጥሩ ምርጫዎች ለማድረግ ልንጠቀምበት እንችላለን። ካልተጠነቀቅን ግን መጥፎ ውሳኔዎች ልናደርግ እንችላለን። የመምረጥ ነፃነት ተሰጥቶናል ሲባል ለይሖዋ ታማኝ ለመሆንና እሱን ከልባችን እንደምንወደው ለማሳየት እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ መምረጥ ይኖርብናል ማለት ነው።

ምዕራፍ 1 አንቀጽ 12

 4 የሥነ ምግባር መሥፈርቶች

ይሖዋ አኗኗራችንን በተመለከተ መመሪያ የሚሆኑን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች አውጥቷል። እነዚህ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ፤ መሥፈርቶቹን መከተላችን ጥሩ ሕይወት ለመምራት የሚረዳን እንዴት እንደሆነም ከአምላክ ቃል እንማራለን። (ምሳሌ 6:16-19፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9-11) የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹ፣ አምላክ ትክክል ወይም ስህተት አድርጎ የሚመለከታቸው ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ ለማወቅ ያስችሉናል። በተጨማሪም አፍቃሪና ደግ መሆን እንዲሁም ጥሩ ውሳኔዎችን ማድረግ የምንችልበትን መንገድ ያስገነዝቡናል። ዓለም የሚመራባቸው መሥፈርቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሹ መጥተዋል፤ የይሖዋ መሥፈርቶች ግን ምንጊዜም አይለወጡም። (ዘዳግም 32:4-6፤ ሚልክያስ 3:6) በይሖዋ መሥፈርቶች መመራት ከአካላዊና ከስሜታዊ ጉዳት ይጠብቀናል።

ምዕራፍ 1 አንቀጽ 17

 5 ሕሊና

ሕሊናችን፣ ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ለመለየት የሚረዳን ችሎታ ነው። ይሖዋ ለሁላችንም ሕሊና ሰጥቶናል። (ሮም 2:14, 15) ሕሊናችን በተገቢው መንገድ እንዲሠራ ከፈለግን ይሖዋ ባወጣቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መሠረት ልናሠለጥነው ይገባል። እንዲህ ካደረግን ሕሊናችን አምላክን የሚያስደስቱ ውሳኔዎች ለማድረግ ሊረዳን ይችላል። (1 ጴጥሮስ 3:16) ሕሊናችን የተሳሳተ ውሳኔ ከማድረግ እንድንቆጠብ ሊያስጠነቅቀን ይችላል፤ መጥፎ ነገር በመፈጸማችን እንድንጸጸት የሚያደርገንም ሕሊናችን ነው። ሕሊናችን አንዳንድ ጊዜ በትክክል ላይሠራ ይችላል፤ ሆኖም ሕሊናችን የሚሠራበትን መንገድ በይሖዋ እርዳታ ማስተካከል እንችላለን። ጥሩ ሕሊና፣ ውስጣዊ ሰላምና ለራሳችን አክብሮት እንዲኖረን ይረዳናል።

ምዕራፍ 2 አንቀጽ 3

 6 ፈሪሃ አምላክ

ፈሪሃ አምላክ ካለን አምላክን በጣም ስለምንወደውና ስለምናከብረው እሱን የሚያሳዝን ምንም ነገር ላለማድረግ እንጠነቀቃለን። ፈሪሃ አምላክ ወይም አምላክን መፍራት፣ ጥሩ ነገር እንድናደርግና ከመጥፎ ድርጊት እንድንርቅ ይረዳናል። (መዝሙር 111:10) ይሖዋ የሚነግረንን ሁሉ ትኩረት ሰጥተን እንድንሰማ ያነሳሳናል። በተጨማሪም ለእሱ የገባነውን ቃል እንድንጠብቅ ይገፋፋናል፤ ይህን የምናደርገው ይሖዋን በጥልቅ ስለምናከብረው ነው። ፈሪሃ አምላክ ያለን መሆኑ በአስተሳሰባችን፣ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት እንዲሁም በየዕለቱ በምናደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ ለውጥ ያመጣል።

ምዕራፍ 2 አንቀጽ 9

 7 ንስሐ

ንስሐ መግባት፣ መጥፎ ነገር በመሥራታችን ምክንያት በጥልቅ ማዘንን ይጨምራል። አምላክን የሚወዱ ሰዎች ከእሱ መሥፈርት ጋር የሚጋጭ ነገር እንደፈጸሙ ሲገነዘቡ በጣም ያዝናሉ። መጥፎ ነገር ከሠራን፣ ይሖዋ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅር እንዲለን ልንለምነው ይገባል። (ማቴዎስ 26:28፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2) ከልባችን ንስሐ ከገባንና መጥፎ ነገር መሥራታችንን ካቆምን ይሖዋ ይቅር እንደሚለን መተማመን እንችላለን። ከዚህ ቀደም ስለሠራነው ኃጢአት እያሰብን የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማን አይገባም። (መዝሙር 103:10-14፤ 1 ዮሐንስ 1:9፤ 3:19-22) ከስህተታችን ለመማር፣ የተሳሳተ አስተሳሰባችንን ለማስተካከልና በይሖዋ መሥፈርቶች መሠረት ሕይወታችንን ለመምራት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለብን።

ምዕራፍ 2 አንቀጽ 18

 8 ውገዳ

ከባድ ኃጢአት የፈጸመ ሰው፣ ንስሐ ለመግባትና የይሖዋን መሥፈርቶች ለመከተል እንቢተኛ ከሆነ የጉባኤው አባል ሆኖ መቀጠል አይችልም። ግለሰቡ ከጉባኤው መወገድ ይኖርበታል። ከተወገደ ሰው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አይኖረንም፤ እንዲሁም ግለሰቡን አናነጋግረውም። (1 ቆሮንቶስ 5:11፤ 2 ዮሐንስ 9-11) የውገዳ ዝግጅት የይሖዋ ስም እንዳይነቀፍና ጉባኤው እንዳይበከል ያደርጋል። (1 ቆሮንቶስ 5:6) በተጨማሪም ውገዳ፣ ግለሰቡን የሚጠቅም ተግሣጽ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ዝግጅት ግለሰቡ ወደ ይሖዋ ለመመለስ ሲል ንስሐ እንዲገባ ሊያነሳሳው ይችላል።—ሉቃስ 15:17

ምዕራፍ 3 አንቀጽ 19

 9 መመሪያ እና ምክር

ይሖዋ ይወደናል እንዲሁም ሊረዳን ይፈልጋል። በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስና እሱን በሚወዱ ሰዎች አማካኝነት መመሪያና ምክር ይሰጠናል። እኛ የሰው ልጆች ፍጹም ስላልሆንን የእሱ እርዳታ በእጅጉ ያስፈልገናል። (ኤርምያስ 17:9) ይሖዋ መመሪያ ለመስጠት የሚጠቀምባቸውን ሰዎች የምናከብርና የምናዳምጥ ከሆነ እሱን እንደምናከብርና እንደምንታዘዝ እናሳያለን።—ዕብራውያን 13:7

ምዕራፍ 4 አንቀጽ 2

 10 ኩራት እና ትሕትና

ፍጹማን ስላልሆንን ብዙውን ጊዜ የራስ ወዳድነትና የኩራት ዝንባሌ ይታይብናል። ሆኖም ይሖዋ ትሑት እንድንሆን ይጠብቅብናል። ትሕትናን ለማዳበር የሚረዳን አንዱ ነገር፣ ከይሖዋ ጋር ስንነጻጸር ከቁጥር የማንገባ እንደሆንን መገንዘባችን ነው። (ኢዮብ 38:1-4) ትሕትናን ማዳበር የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ ከራሳችን አብልጠን ስለ ሌሎች ጥቅም ማሰብ ነው። ኩሩ የሆነ ሰው ራሱን ከሌሎች እንደሚሻል አድርጎ ይቆጥራል። ትሑት የሆነ ሰው ግን ራሱን በሐቀኝነት በመገምገም ጠንካራም ሆነ ደካማ ጎን እንዳለው አምኖ ይቀበላል። ስህተቱን ማመን፣ ይቅርታ መጠየቅ እንዲሁም ሌሎች የሚሰጡትን አስተያየትና ምክር መቀበል አይከብደውም። በተጨማሪም ትሑት ሰው በይሖዋ ይታመናል፤ የእሱን መመሪያም ይከተላል።—1 ጴጥሮስ 5:5

ምዕራፍ 4 አንቀጽ 4

 11 ሥልጣን

ሥልጣን የሚለው ቃል፣ ትእዛዝ የመስጠትና ውሳኔ የማድረግ መብትን ያመለክታል። በሰማይም ሆነ በምድር ከሁሉ የላቀ ሥልጣን ያለው ይሖዋ ነው። ሁሉንም ነገር የፈጠረው እሱ በመሆኑ በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ የእሱን ያህል ኃያል የሆነ አካል የለም። ይሖዋ ምንጊዜም ሥልጣኑን የሚጠቀመው ሌሎችን በሚጠቅም መንገድ ነው። ይሖዋ ለአንዳንድ ሰዎች ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ ወላጆች፣ የጉባኤ ሽማግሌዎችና መንግሥታት አንጻራዊ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፤ ይሖዋም ሥልጣናቸውን እንድናከብር ይጠብቅብናል። (ሮም 13:1-5፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:17) ይሁን እንጂ የሰዎች ሕግ ከአምላክ ሕግ ጋር በሚጋጭበት ጊዜ ከሰው ይልቅ አምላክን እንታዘዛለን። (የሐዋርያት ሥራ 5:29) ይሖዋ ሥልጣን የሰጣቸውን ሰዎች ስናከብር የእሱን ዝግጅት እንደምናከብር እናሳያለን።

ምዕራፍ 4 አንቀጽ 7

 12 ሽማግሌዎች

ይሖዋ ጉባኤውን ለመንከባከብ በሽማግሌዎች ይጠቀማል፤ ሽማግሌዎች ተሞክሮ ያላቸው ወንድሞች ናቸው። (ዘዳግም 1:13፤ የሐዋርያት ሥራ 20:28) እነዚህ ወንድሞች ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል እንዲሁም ሰላማዊ በሆነና በተደራጀ መንገድ ይሖዋን እንድናመልክ ይረዱናል። (1 ቆሮንቶስ 14:33, 40) አንድ ወንድም ሽማግሌ ሆኖ የሚሾመው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በተጻፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተዘረዘሩትን ብቃቶች ካሟላ ነው፤ በመሆኑም ሽማግሌዎች የሚሾሙት በመንፈስ ቅዱስ ነው ማለት ይቻላል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-7፤ ቲቶ 1:5-9፤ 1 ጴጥሮስ 5:2, 3) በይሖዋ ድርጅት ስለምንተማመንና ድርጅቱን መደገፍ ስለምንፈልግ ከሽማግሌዎች ጋር በደስታ እንተባበራለን።—መዝሙር 138:6፤ ዕብራውያን 13:17

ምዕራፍ 4 አንቀጽ 8

 13 የቤተሰብ ራስ

ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲንከባከቡ ይሖዋ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። ይሁን እንጂ የቤተሰቡ ራስ፣ ባል እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። አባት በሌለበት ቤተሰብ ውስጥ ደግሞ እናትየው የቤተሰብ ራስ ትሆናለች። የቤተሰቡ ራስ ካሉበት ኃላፊነቶች መካከል ለቤተሰቡ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ማቅረብ ይገኙበታል። በተጨማሪም ቤተሰቡ ይሖዋን እንዲያመልክ ቅድሚያውን ወስዶ መርዳቱ በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ መላው ቤተሰብ አዘውትሮ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኝና በመስክ አገልግሎት እንዲካፈል ጥረት ያደርጋል፤ እንዲሁም ቤተሰቡ መጽሐፍ ቅዱስን አብሮ የሚያጠናበት ፕሮግራም ማዘጋጀት ይኖርበታል። በቤተሰብ ውስጥ ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነት ያለበትም የቤተሰቡ ራስ ነው። አንድ የቤተሰብ ራስ ምንጊዜም ደግና ምክንያታዊ በመሆን የኢየሱስን ምሳሌ ይከተላል እንጂ ቤተሰቡን አይጨቁንም። ይህም ቤታቸው ፍቅር የሰፈነበት እንዲሆንና የቤተሰቡ አባላት በሙሉ ተረጋግተው እንዲኖሩ ያደርጋል፤ እንዲሁም ከይሖዋ ጋር ያላቸው ዝምድና እየተጠናከረ እንዲሄድ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

ምዕራፍ 4 አንቀጽ 12

 14 የበላይ አካል

የበላይ አካል፣ አምላክ ሕዝቦቹ የሚያከናውኑትን ሥራ ለመምራት የሚጠቀምባቸውን ወንድሞች ያቀፈ ቡድን ነው፤ የዚህ ቡድን አባላት ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ያላቸው ወንድሞች ናቸው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይሖዋ፣ ከአምልኮና ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ለክርስቲያን ጉባኤ መመሪያ ለመስጠት በበላይ አካል ተጠቅሞ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 15:2) በዛሬው ጊዜ ያለው የበላይ አካልም የአምላክን ሕዝቦች ይመራል እንዲሁም ከጉዳት እንዲጠበቁ ይረዳቸዋል። የዚህ ቡድን አባላት የሆኑት ወንድሞች ውሳኔ በሚያደርጉበት ጊዜ በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን መመሪያና የመንፈስ ቅዱስን አመራር ይከተላሉ። ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ወንድሞችን ያቀፈውን ይህን ቡድን “ታማኝና ልባም ባሪያ” በማለት ጠርቶታል።—ማቴዎስ 24:45-47

ምዕራፍ 4 አንቀጽ 15

 15 ራስን መሸፈን

በጉባኤ ውስጥ ወንድሞች ሊሠሩት የሚገባውን ሥራ አንዳንድ ጊዜ እህቶች ማከናወን ሊኖርባቸው ይችላል። እህቶች እንዲህ ያሉ ሥራዎችን ሲያከናውኑ ራሳቸውን በመሸፈን ለይሖዋ ዝግጅት አክብሮት እንዳላቸው ያሳያሉ። ይሁንና እህቶች ራሳቸውን መሸፈን የሚያስፈልጋቸው በተወሰኑ ሁኔታዎች ሥር ብቻ ነው። ለምሳሌ አንዲት እህት፣ ባሏ ወይም አንድ የተጠመቀ ወንድም ባለበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስትመራ ራሷን መሸፈን ይኖርባታል።—1 ቆሮንቶስ 11:11-15

ምዕራፍ 4 አንቀጽ 17

 16 የገለልተኝነት አቋም

ገለልተኞች እንሆናለን ሲባል በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ የትኛውንም ወገን አንደግፍም ማለት ነው። (ዮሐንስ 17:16) የይሖዋ ሕዝቦች የሚደግፉት የአምላክን መንግሥት ነው። በመሆኑም ከዚህ ዓለም ጉዳዮች ጋር በተያያዘ እንደ ኢየሱስ የገለልተኝነት አቋም እንይዛለን።

ይሖዋ ‘ለመንግሥታትና ለባለሥልጣናት እንድንታዘዝ’ ይጠብቅብናል። (ቲቶ 3:1, 2፤ ሮም 13:1-7) በሌላ በኩል ደግሞ የአምላክ ቃል ነፍስ ማጥፋት እንደሌለብን ይናገራል። በዚህም ምክንያት ክርስቲያኖች ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠትም ሆነ በጦርነት ለመካፈል ሕሊናቸው አይፈቅድላቸውም። አንድ ክርስቲያን በወታደራዊ አገልግሎት ምትክ የሲቪል አገልግሎት የመስጠት ማለትም ከጦር ሠራዊት ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ሥራ የመሥራት አማራጭ ቢቀርብለት በሕሊናው ላይ ተመርቶ መወሰን ይኖርበታል።

ይሖዋ ፈጣሪያችን ስለሆነ የምናመልከው እሱን ብቻ ነው። ብሔራዊ አርማዎችን የምናከብር ቢሆንም ለባንዲራ ሰላምታ አንሰጥም፤ ብሔራዊ መዝሙርም አንዘምርም። (ኢሳይያስ 43:11፤ ዳንኤል 3:1-30፤ 1 ቆሮንቶስ 10:14) ከዚህም ሌላ የይሖዋ አገልጋዮች ለማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወይም እጩ ተመራጭ ድምፅ ላለመስጠት በግለሰብ ደረጃ ውሳኔ ያደርጋሉ። ምክንያቱም የአምላክን መንግሥት ለመደገፍ መርጠዋል።—ማቴዎስ 22:21፤ ዮሐንስ 15:19፤ 18:36

ምዕራፍ 5 አንቀጽ 2

 17 የዓለም መንፈስ

ይህ ዓለም የሰይጣንን አስተሳሰብ ያስፋፋል። የሰይጣን አስተሳሰብ፣ ይሖዋን በማይወዱና እሱን መምሰል በማይፈልጉ እንዲሁም የእሱን መሥፈርቶች ችላ በሚሉ ሰዎች ዘንድ ተስፋፍቶ ይታያል። (1 ዮሐንስ 5:19) እንዲህ ያለው አስተሳሰብና ከዚህ አስተሳሰብ የሚመነጨው ድርጊት “የዓለም መንፈስ” ተብሎ ተገልጿል። (ኤፌሶን 2:2) የይሖዋ ሕዝቦች ይህ መንፈስ ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን እንጠነቀቃለን። (ኤፌሶን 6:10-18) የይሖዋን መሥፈርቶች የምንወድ ሲሆን በእሱ አስተሳሰብ ለመመራት ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን።

ምዕራፍ 5 አንቀጽ 7

 18 ክህደት

ክህደት የሚለው ቃል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነት መቃወምን ያመለክታል። ከሃዲዎች በይሖዋና የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በተሾመው በኢየሱስ ላይ ያምፃሉ፤ እንዲሁም ሌሎች ከእነሱ ጋር ተባብረው እንዲያምፁ ለማድረግ ይሞክራሉ። (ሮም 1:25) በይሖዋ አገልጋዮች አእምሮ ውስጥ ጥርጣሬ ለመዝራት ይፈልጋሉ። በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ሰዎች ከሃዲ ሆነው ነበር፤ በዛሬው ጊዜም የእነሱን አካሄድ የሚከተሉ አሉ። (2 ተሰሎንቄ 2:3) ለይሖዋ ታማኝ የሆኑ ሁሉ ከከሃዲዎች ጋር በምንም መንገድ ግንኙነት አይፈጥሩም። ከሃዲዎች ምን እንደሚሉ ለማወቅ በመጓጓት አሊያም ሌሎች በሚያደርጉብን ተጽዕኖ በመሸነፍ፣ እነሱ የሚያዘጋጇቸውን ጽሑፎች ከማንበብ ወይም ሐሳባቸውን ከመስማት እንቆጠባለን። ለይሖዋ ታማኝ እንሆናለን እንዲሁም እሱን ብቻ እናመልካለን።

ምዕራፍ 5 አንቀጽ 9

 19 ስርየት

በሙሴ ሕግ ሥር፣ እስራኤላውያን ይሖዋ ኃጢአታቸውን ይቅር እንዲልላቸው የሚጠይቁበት ዝግጅት ነበር። ኃጢአታቸው እንዲሰረይላቸው ወይም ይቅር እንዲባልላቸው እህል፣ ዘይትና እንስሳት ወደ ቤተ መቅደሱ በመውሰድ መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ ነበር። ይህ ዝግጅት፣ ይሖዋ በብሔርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ኃጢአታቸውን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደሆነ እስራኤላውያንን ያስታውሳቸው ነበር። ኢየሱስ ኃጢአታችንን ለማስተሰረይ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ካቀረበ በኋላ ግን እንዲህ ያለው የስርየት መሥዋዕት አስፈላጊ መሆኑ ቀርቷል። ኢየሱስ ፍጹም የሆነ መሥዋዕት “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” አቅርቧል።—ዕብራውያን 10:1, 4, 10

ምዕራፍ 7 አንቀጽ 6

 20 ለእንስሳት ሕይወት አክብሮት ማሳየት

የሙሴ ሕግ፣ ሰዎች እንስሳትን ለምግብነት እንዲጠቀሙ ይፈቅድ ነበር። በተጨማሪም ሕዝቡ የእንስሳት መሥዋዕት ማቅረብ ይጠበቅባቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 1:5, 6) ሆኖም ሕዝቡ እንስሳትን በጭካኔ እንዲይዙ ይሖዋ ፈጽሞ አልፈቀደም። (ምሳሌ 12:10) እንዲያውም ሕጉ በእንስሳት ላይ ጭካኔ እንዳይፈጸም የሚከላከሉ ትእዛዞችን ይዞ ነበር። እስራኤላውያን እንስሶቻቸውን በሚገባ እንዲንከባከቡ መመሪያ ተሰጥቷቸው ነበር።—ዘዳግም 22:6, 7

ምዕራፍ 7 አንቀጽ 6

 21 ንዑሳን የደም ክፍልፋዮች እና አንዳንድ የሕክምና ዘዴዎች

ንዑሳን የደም ክፍልፋዮች። ደም አራት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት፤ እነሱም ቀይ የደም ሴል፣ ነጭ የደም ሴል፣ ፕሌትሌትና ፕላዝማ ናቸው። ከእነዚህ አራት ዋና ዋና የደም ክፍሎች የሚወጡ ንዑሳን ክፍልፋዮችም አሉ። *

ክርስቲያኖች ሙሉውን ደምም ሆነ ከአራቱ ዋና ዋና የደም ክፍሎች መካከል አንዱንም እንኳ አይወስዱም። ይሁንና ንዑሳን የደም ክፍልፋዮችን መውሰድ ይችላሉ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ በዝርዝር አይናገርም። በመሆኑም እያንዳንዱ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናውን በመጠቀም የግሉን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል።

አንዳንድ ክርስቲያኖች ንዑሳን የደም ክፍልፋዮችን ጨርሶ ላለመውሰድ ይወስናሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ ውሳኔ ላይ የደረሱት አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠውን፣ የእንስሳ ደም በሙሉ ‘መሬት ላይ መፍሰስ’ እንዳለበት የሚናገረውን ሕግ መሠረት በማድረግ ሊሆን ይችላል።—ዘዳግም 12:22-24

ሌሎች ደግሞ ከዚህ የተለየ ውሳኔ ያደርጋሉ። አንዳንዶቹን ንዑሳን የደም ክፍልፋዮች ለመውሰድ ሕሊናቸው ይፈቅድላቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ትናንሽ ክፍልፋዮች እንደ ደም ተቆጥረው የአንድን ፍጥረት ሕይወት ሊወክሉ እንደማይችሉ ያስቡ ይሆናል።

ንዑሳን የደም ክፍልፋዮችን በተመለከተ ውሳኔ በምታደርግበት ጊዜ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው፦

  • ሁሉንም ንዑሳን የደም ክፍልፋዮች ላለመውሰድ ከወሰንኩ፣ በሽታን ለመከላከል ወይም የደም መፍሰስን ለማስቆም ተብለው የሚሰጡ አንዳንድ መድኃኒቶችን ጭምር አልወስድም ማለቴ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ?

  • አንዳንድ ንዑሳን የደም ክፍልፋዮችን ለመውሰድ ፈቃደኛ የማልሆንበትን ወይም የምሆንበትን ምክንያት ለሐኪም ማስረዳት እችላለሁ?

አንዳንድ የሕክምና ዘዴዎች። ክርስቲያኖች ደም አንሰጥም፤ ወይም ደግሞ የራሳችን ደም ከቀዶ ሕክምና በፊት ተቀድቶ እንዲቀመጥ አናደርግም። ይሁን እንጂ የታካሚውን ደም የሚጠቀሙ ሌሎች የሕክምና ዘዴዎች አሉ። እያንዳንዱ ክርስቲያን ቀዶ ሕክምና፣ የጤና ምርመራ ወይም ደሙን ቀድቶ ማስቀመጥ የማይጠይቅ ሌላ ዓይነት ሕክምና በሚደረግለት ወቅት የራሱ ደም ጥቅም ላይ ስለሚውልበት መንገድ በግለሰብ ደረጃ ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። በእነዚህ የሕክምና ዘዴዎች የታካሚው ደም ከሰውነቱ ወጥቶ ለተወሰነ ጊዜ ያህል እንዲቆይ ይደረግ ይሆናል።—ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የጥቅምት 15, 2000 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 30-31⁠ን ተመልከት።

ለምሳሌ ያህል፣ ሂሞዳይሉሽን በመባል የሚታወቅ የሕክምና ዘዴ አለ፤ በዚህ ሕክምና፣ ታካሚው ልክ ቀዶ ሕክምና ሊያደርግ ሲል የተወሰነ ደም ከሰውነቱ ይወሰድና በምትኩ የደምን መጠን የሚጨምር ፈሳሽ ወደ ሰውነቱ እንዲገባ ይደረጋል። ከዚያም በቀዶ ሕክምናው ወቅት ወይም ቀዶ ሕክምናው ከተደረገ ብዙም ሳይቆይ የታካሚው ደም ወደ ሰውነቱ ተመልሶ እንዲገባ ይደረጋል።

ሌላው የሕክምና ዘዴ ደግሞ ሴል ሳልቬጅ ተብሎ ይጠራል። ሴል ሳልቬጅ፣ ታካሚው ቀዶ ሕክምና እየተደረገለት እያለ የሚፈሰው ደም ተጠራቅሞ ከተጣራ በኋላ፣ በቀዶ ሕክምናው ወቅት አሊያም ቀዶ ሕክምናው ከተደረገ ብዙም ሳይቆይ ወደ ታካሚው ሰውነት ተመልሶ እንዲገባ የሚደረግበት የሕክምና ዘዴ ነው።

እያንዳንዱ ሐኪም እነዚህን ዘዴዎች የሚጠቀምበት መንገድ ሊለያይ ይችላል። በመሆኑም እያንዳንዱ ክርስቲያን ማንኛውንም ቀዶ ሕክምና፣ የጤና ምርመራ ወይም ደሙን ቀድቶ ማስቀመጥ የማይጠይቅ ሌላ ዓይነት ሕክምና ለማድረግ ከመስማማቱ በፊት በሕክምናው ወቅት ደሙ ጥቅም ላይ ስለሚውልበት መንገድ በሚገባ ለማወቅ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል።

የራስህን ደም ጥቅም ላይ የሚያውሉ የሕክምና ዘዴዎችን በተመለከተ ውሳኔ በምታደርግበት ጊዜ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው፦

  • የተወሰነ ደም ከሰውነቴ ወጥቶ በሌላ መስመር እንዲያልፍ የሚደረግ ምናልባትም ዝውውሩ ለጥቂት ጊዜ የሚቋረጥ ከሆነ፣ ይህን ደም የሰውነቴ ክፍል እንደሆነና “መሬት ላይ [መፍሰስ]” እንደማያስፈልገው አድርጌ ለመመልከት ሕሊናዬ ይፈቅድልኛል?—ዘዳግም 12:23, 24

  • በሕክምና ወቅት ከሰውነቴ ውስጥ የተወሰነ ደም ተወስዶ አንድ ዓይነት ለውጥ ከተደረገበት በኋላ እንደገና ወደ ሰውነቴ እንዲገባ ቢደረግ ወይም ቀዶ ሕክምና በተደረገበት የሰውነቴ ክፍል ላይ ቢቀባ እንዲህ ዓይነቱን ሕክምና ለመቀበል በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናዬ ይፈቅድልኛል?

  • የራሴን ደም በመጠቀም የሚሰጡ ሕክምናዎችን በሙሉ አልቀበልም ብል የደም ምርመራን፣ ሂሞዳያሊስስን ወይም እንደ ልብና ሳንባ ሆኖ የሚያገለግል መሣሪያ መጠቀምን ጭምር እንደማልፈልግ መግለጼ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ?

ከንዑሳን የደም ክፍልፋዮችና የራሳችንን ደም ጥቅም ላይ ከሚያውሉ ሕክምናዎች ጋር በተያያዘ ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት ይሖዋ እንዲመራን መጸለይ እንዲሁም ስለ ሕክምናው ለማወቅ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። (ያዕቆብ 1:5, 6) ከዚያም በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናችንን በመጠቀም ውሳኔ እናደርጋለን። ‘አንተ በእኔ ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?’ ብለን ሌሎችን መጠየቅ ተገቢ አይደለም፤ ሌሎችም ቢሆኑ ምን ዓይነት ውሳኔ ማድረግ እንዳለብን ሊነግሩን አይገባም።—ሮም 14:12፤ ገላትያ 6:5

ምዕራፍ 7 አንቀጽ 11

 22 የሥነ ምግባር ንጽሕና

በሥነ ምግባር ረገድ ንጹሕ መሆን ሲባል ምግባራችንና ድርጊታችን በአምላክ ዓይን ንጹሕ እንዲሆን ማድረግ ማለት ነው። የሥነ ምግባር ንጽሕናን መጠበቅ፣ በአስተሳሰባችንና በንግግራችን እንዲሁም በድርጊታችን ንጹሕ መሆንን ይጨምራል። ይሖዋ ከማንኛውም ዓይነት የፆታ ብልግና ወይም ርኩሰት እንድንርቅ አዞናል። (ምሳሌ 1:10፤ 3:1) ምንጊዜም የይሖዋን ንጹሕ መሥፈርቶች ለመከተል መወሰን ያለብን፣ መጥፎ ነገር ለመፈጸም የሚፈትነን ሁኔታ ውስጥ ከመግባታችን በፊት ነው። አእምሯችን ሁልጊዜ ንጹሕ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ እንዲረዳን ወደ ይሖዋ መጸለይ አለብን፤ በተጨማሪም የሥነ ምግባር ብልግና እንድንፈጽም በሚቀርብልን ፈተና ላለመውደቅ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10, 18፤ ኤፌሶን 5:5

ምዕራፍ 8 አንቀጽ 11

 23 ዓይን ያወጣ ምግባር እና ርኩሰት

ዓይን ያወጣ ምግባር ሲባል የአምላክን መሥፈርቶች በግልጽ የሚጥስና እፍረተ ቢስነት የሚንጸባረቅበት ንግግርን ወይም ድርጊትን ያካትታል። ዓይን ያወጣ ምግባር ያለው ሰው ለአምላክ ሕጎች አክብሮት እንደሌለው ያሳያል። አንድ ሰው ዓይን ያወጣ ምግባር ከፈጸመ ጉዳዩ በጉባኤው የፍርድ ኮሚቴ ይታያል። በሌላ በኩል ደግሞ ርኩሰት የሚለው ቃል የተለያዩ መጥፎ ድርጊቶችን ለመግለጽ ይሠራበታል። ከርኩሰት ጋር የተያያዙ አንዳንድ ድርጊቶች እንደ ጉዳዩ ክብደት በፍርድ ኮሚቴ ሊታዩ ይችላሉ።—ገላትያ 5:19-21፤ ኤፌሶን 4:19፤ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በሐምሌ 15, 2006 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።

ምዕራፍ 9 አንቀጽ 7፤ ምዕራፍ 12 አንቀጽ 10

 24 ማስተርቤሽን

ይሖዋ፣ የፆታ ግንኙነት እንዲኖር ያደረገው ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር ንጹሕ በሆነ መንገድ መግለጽ እንዲችሉ ነው። ሆኖም ማስተርቤሽን የመፈጸም ወይም የፆታ ስሜቱን ለማርካት ሲል የፆታ አካሉን የማሻሸት ልማድ ያለው ሰው የፆታ ስሜቱን ንጹሕ ባልሆነ መንገድ እየተጠቀመበት ነው። እንዲህ ያለው ልማድ ግለሰቡ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ያበላሽበታል። በተጨማሪም ተፈጥሯዊ ያልሆኑ ምኞቶች እንዲፈጠሩበትና ስለ ፆታ ግንኙነት የተዛባ አመለካከት እንዲኖረው ሊያደርገው ይችላል። (ቆላስይስ 3:5) ይሁን እንጂ አንድ ሰው እንዲህ ያለ ርኩስ ልማድ ቢጠናወተውና ይህን ልማዱን ማሸነፍ ቢያስቸግረው ተስፋ ሊቆርጥ አይገባም። (መዝሙር 86:5፤ 1 ዮሐንስ 3:20) አንተም እንዲህ ያለ ችግር ካለብህ ከልብህ ወደ ይሖዋ በመጸለይ እንዲረዳህ ጠይቀው። ርኩስ የሆኑ ነገሮች ወደ አእምሮህ እንዲመጡ ሊያደርጉ ከሚችሉ ነገሮች ለምሳሌ ከብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ራቅ። ስለ ጉዳዩ ክርስቲያን ወላጆችህን ወይም የይሖዋን ሕጎች የሚያከብር የጎለመሰ ወዳጅህን አማክር። (ምሳሌ 1:8, 9፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14፤ ቲቶ 2:3-5) ይሖዋ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናህን ለመጠበቅ የምታደርገውን ጥረት እንደሚያስተውልና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—መዝሙር 51:17፤ ኢሳይያስ 1:18

ምዕራፍ 9 አንቀጽ 9

 25 ከአንድ በላይ ማግባት

የይሖዋ ዓላማ፣ ጋብቻ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚመሠረት ጥምረት እንዲሆን ነው። በጥንቷ እስራኤል ውስጥ አምላክ፣ ከአንዲት ሚስት በላይ ማግባትን ፈቅዶ ነበር፤ የመጀመሪያ ዓላማው ግን ይህ አልነበረም። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ከአንድ በላይ እንዲያገቡ አይፈቅድም። አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት በላይ ማግባት የለበትም፤ ሴትም ብትሆን ከአንድ ወንድ በላይ ማግባት የለባትም።—ማቴዎስ 19:9፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:2

ምዕራፍ 10 አንቀጽ 12

 26 ፍቺ እና መለያየት

የይሖዋ ዓላማ፣ ባልና ሚስት በሕይወት እስካሉ ድረስ አብረው እንዲኖሩ ነው። (ዘፍጥረት 2:24፤ ሚልክያስ 2:15, 16፤ ማቴዎስ 19:3-6፤ 1 ቆሮንቶስ 7:39) ይሖዋ ፍቺን የሚፈቅደው አንደኛው የትዳር ጓደኛ ምንዝር ከፈጸመ ብቻ ነው። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር፣ ታማኝ የሆነው የትዳር ጓደኛ ፍቺ ለመፈጸም ወይም ላለመፈጸም እንዲመርጥ ይሖዋ ፈቅዶለታል።—ማቴዎስ 19:9

በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ የትዳር ጓደኛቸው ምንዝር ባይፈጽምም እንኳ ተለያይተው ለመኖር ወስነዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:11) አንድ ክርስቲያን ከትዳር ጓደኛው ጋር ለመለያየት እንዲወስን ሊያደርጉት የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው፦

  • መሠረታዊ ነገሮችን ለማቅረብ ፈቃደኛ አለመሆን፦ አንድ ባል ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር ለማቅረብ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ቤተሰቡ ለከፍተኛ ችግር ቢዳረግ።—1 ጢሞቴዎስ 5:8

  • ከባድ አካላዊ ጥቃት፦ አንደኛው የትዳር ጓደኛ፣ ጤንነቱን ይባስ ብሎም ሕይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል የኃይል ጥቃት እንደተሰነዘረበት ቢሰማው።—ገላትያ 5:19-21

  • አንድ ሰው ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ሙሉ በሙሉ አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ፦ አንድ ሰው የትዳር ጓደኛው ፈጽሞ ይሖዋን ማገልገል እንዳይችል ጥረት ቢያደርግ።—የሐዋርያት ሥራ 5:29

ምዕራፍ 11 አንቀጽ 19

 27 ምስጋና እና ማበረታቻ

ሁላችንም ብንሆን ምስጋና እና ማበረታቻ ያስፈልገናል። (ምሳሌ 12:25፤ 16:24) ፍቅርና ደግነት የሚንጸባረቅባቸውን ቃላት በመናገር አንዳችን ሌላውን ማበረታታትና ማጽናናት እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም ይሖዋን በጽናት ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ይረዳቸዋል። (ምሳሌ 12:18፤ ፊልጵስዩስ 2:1-4) በተስፋ መቁረጥ ስሜት የተዋጠ ሰው ቢያጋጥመን በአክብሮት ልናዳምጠው እንዲሁም ስሜቱን ለመረዳት ጥረት ልናደርግ ይገባል። ይህም ምን ብለን እንደምናጽናናው ወይም እንዴት እንደምንረዳው ለማወቅ ያስችለናል። (ያዕቆብ 1:19) ወንድሞችህና እህቶችህ ምን እንደሚያስፈልጋቸው መገንዘብ እንድትችል ስለ እነሱ በሚገባ ለማወቅ ጥረት አድርግ። በተጨማሪም የመጽናናትና የማበረታቻ ምንጭ ወደሆነውና እረፍት ሊሰጣቸው ወደሚችለው አምላካችን ዘወር እንዲሉ ልትረዳቸው ትችላለህ።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4፤ 1 ተሰሎንቄ 5:11

ምዕራፍ 12 አንቀጽ 16

  28 የሠርግ ሥነ ሥርዓት

መጽሐፍ ቅዱስ የሠርግ ሥነ ሥርዓትን በተመለከተ ዝርዝር መመሪያዎችን አይሰጥም። ሠርግን የሚመለከቱ ባሕሎችና ሕግ ነክ ጉዳዮች ከቦታ ቦታ ይለያያሉ። (ዘፍጥረት 24:67፤ ማቴዎስ 1:24፤ 25:10፤ ሉቃስ 14:8) በሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ተጋቢዎቹ በይሖዋ ፊት የሚገቡት ቃል ነው። ብዙ ተጋቢዎች የጋብቻ ቃለ መሐላ ሲገቡ፣ በቦታው ቤተሰቦቻቸውና የቅርብ ወዳጆቻቸው እንዲገኙ እንዲሁም አንድ የጉባኤ ሽማግሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ንግግር እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ። ‘ከጋብቻ ንግግሩ በኋላ ግብዣ ቢኖር ይሻላል? ከኖረስ ምን ዓይነት ሊሆን ይገባል?’ የሚሉትን ጉዳዮች ሊወስኑ የሚገባው ተጋቢዎቹ ናቸው። (ሉቃስ 14:28፤ ዮሐንስ 2:1-11) ሙሽሮቹ የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን በተመለከተ የሚያደርጉት ውሳኔ ምንም ይሁን ምን፣ ሠርጋቸው ይሖዋን የሚያስከብር እንዲሆን ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው። (ዘፍጥረት 2:18-24፤ ማቴዎስ 19:5, 6) በዚህ ረገድ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይረዷቸዋል። (1 ዮሐንስ 2:16, 17) ተጋቢዎቹ በግብዣው ላይ የአልኮል መጠጥ እንዲቀርብ ከወሰኑ ተገቢው ቁጥጥር እንዲኖር ማድረግ አለባቸው። (ምሳሌ 20:1፤ ኤፌሶን 5:18) ሙዚቃ ወይም ሌላ ዓይነት መዝናኛ የሚኖር ከሆነም ዝግጅቱ ይሖዋን የሚያስከብር ሊሆን ይገባል። ክርስቲያን የሆኑ ተጋቢዎች ትልቅ ቦታ ሊሰጡት የሚገባው ነገር፣ ከአምላክ ጋር ያላቸው ዝምድና እንዲሁም የተሳካ ትዳር መመሥረታቸው እንጂ የሠርጋቸው ቀን ሊሆን አይገባም።—ምሳሌ 18:22፤ ተጨማሪ ሐሳቦችን ለማግኘት የ​ጥቅምት 15, 2006 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 18-31​ን ተመልከት።

ምዕራፍ 13 አንቀጽ 18

29 ጥሩ ውሳኔ ማድረግ

ክርስቲያኖች በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ተመሥርተን ጥሩ ውሳኔዎችን ማድረግ እንፈልጋለን። አንድ ምሳሌ እንውሰድ፦ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ የአንዲት ክርስቲያን የትዳር ጓደኛ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚጋጭ አንድ በዓል ላይ ከዘመዶቹ ጋር ምሳ ወይም ራት አብረው እንዲመገቡ ባለቤቱን ሊጠይቃት ይችላል። አንቺ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምሽ ምን ታደርጊያለሽ? ምናልባት ግብዣውን ለመቀበል ሕሊናሽ ይፈቅድልሽ ይሆናል፤ ሆኖም በግብዣው ላይ ከሐሰት አምልኮ ጋር የተያያዙ ልማዶች የሚኖሩ ከሆነ በእነዚህ ልማዶች እንደማትካፈዪ ለባለቤትሽ ልትነግሪው ትችያለሽ። በተጨማሪም በዝግጅቱ ላይ መገኘትሽ ሌሎችን ያሰናክል እንደሆነ ማሰብ ይኖርብሻል።—1 ቆሮንቶስ 8:9፤ 10:23, 24

የአንድ ክርስቲያን አሠሪ ደግሞ በበዓል ሰሞን ለሠራተኞቹ ጉርሻ ወይም ተጨማሪ ክፍያ ለመስጠት ሊወስን ይችላል። ታዲያ አንተ እንዲህ ያለውን ክፍያ አልቀበልም ማለት ይኖርብሃል? ላይኖርብህ ይችላል። አሠሪህ ስለ ጉርሻው ያለው አመለካከት፣ ይህን ክፍያ ለመቀበል ወይም ላለመቀበል በምታደርገው ውሳኔ ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። አሠሪህ ጉርሻውን የሰጠህ ለበዓሉ ብሎ ነው? ወይስ ጉርሻ ለመስጠት የተነሳሳው ለሠራተኞቹ አመስጋኝነቱን ለመግለጽ ፈልጎ ነው? በእነዚህና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ቆም ብለህ ማሰብህ ጉርሻውን መቀበልህ ተገቢ መሆን አለመሆኑን ለመወሰን ይረዳሃል።

በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው በበዓል ወቅት ስጦታ ይዞልህ በመምጣት “ይህን በዓል እንደማታከብር አውቃለሁ፣ ቢሆንም ስጦታዬን ብትቀበለኝ ደስ ይለኛል” ይልህ ይሆናል። ግለሰቡ ይህን ያደረገው በደግነት ተነሳስቶ ብቻ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ግለሰቡ እምነትህን ለመፈተን ወይም በዓሉን እንድታከብር ለማድረግ እየሞከረ እንደሆነ ቢሰማህስ? እነዚህን ነገሮች ካመዛዘንክ በኋላ ስጦታውን ለመቀበል ወይም ላለመቀበል መወሰኑ የአንተ ድርሻ ነው። የምናደርገው ማንኛውም ውሳኔ፣ ንጹሕ ሕሊና ለመያዝና ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ለመጠበቅ የሚያስችለን እንዲሆን እንፈልጋለን።—የሐዋርያት ሥራ 23:1

ምዕራፍ 13 አንቀጽ 22

 30 ከገንዘብ እና ከሕግ ጋር የተያያዙ ነገሮች

አለመግባባትን ሳይውል ሳያድር ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመፍታት ብዙውን ጊዜ ትልቅ ችግር እንዳይፈጠር ማድረግ ይቻላል። (ማቴዎስ 5:23-26) ሁሉም ክርስቲያኖች በዋነኝነት የሚያሳስባቸው ነገር፣ ለይሖዋ ክብር ማምጣታቸውና የጉባኤውን አንድነት መጠበቃቸው ሊሆን ይገባል።—ዮሐንስ 13:34, 35፤ 1 ቆሮንቶስ 13:4, 5

ክርስቲያኖች ገንዘብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች አለመግባባት ካጋጠማቸው፣ የእምነት ባልንጀራቸውን ፍርድ ቤት ከመክሰስ ይልቅ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ፍርድ ቤት ከመሄድ ጋር በተያያዘ ለክርስቲያኖች የሰጠው ምክር በ1 ቆሮንቶስ 6:1-8 ላይ ሰፍሯል። ወንድማችንን ፍርድ ቤት መክሰስ የይሖዋንም ሆነ የጉባኤውን ስም ያስነቅፋል። እንደ ስም ማጥፋት ወይም ማጭበርበር ካሉ ከበድ ያሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ክርስቲያኖች ሊወስዷቸው የሚገቡ ሦስት እርምጃዎች በማቴዎስ 18:15-17 ላይ ተጠቅሰዋል። (1) ማንንም ጣልቃ ሳያስገቡ ጉዳዩን ራሳቸው ለመፍታት ጥረት ማድረግ። (2) ይህ መፍትሔ ካላስገኘ፣ አንድ ወይም ሁለት የጎለመሱ የጉባኤው አባላት እንዲረዷቸው መጠየቅ። (3) እነዚህን እርምጃዎች ከወሰዱ በኋላ፣ አስፈላጊ ከሆነ ጉዳዩን የሽማግሌዎች አካል እንዲመለከተው ማድረግ። ጉዳዩ እዚህ ደረጃ ላይ ከደረሰ ሽማግሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በመጠቀም፣ አለመግባባት ያጋጠማቸውን ክርስቲያኖች ሰላም እንዲፈጥሩ ይረዷቸዋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው አንዳንድ ግለሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመከተል ፈቃደኛ ካልሆኑ ግን የጉባኤው ሽማግሌዎች የፍርድ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸው ይሆናል።

በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ፍርድ ቤት መሄድ ሕጋዊ ግዴታ የሚሆንባቸው ጊዜያት አሉ። ለምሳሌ ከፍቺ፣ ልጅ የማሳደግ መብት ከማግኘት፣ ከፍቺ በኋላ ተቆራጭ ከማስወሰን፣ የኢንሹራንስ ካሳ ከማግኘት፣ ኑዛዜን ከማስፈጸም ጋር በተያያዙ ጉዳዮች አሊያም ደግሞ አንድ ድርጅት በሚከስርበት ጊዜ ፍርድ ቤት መሄድ ሊያስፈልግ ይችላል። አንድ ክርስቲያን እንደ እነዚህ ያሉ ጉዳዮችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ሕጋዊ አካሄድ ቢከተል የጳውሎስን ምክር እንደጣሰ አይቆጠርም።

አንድ ክርስቲያን እንደ አስገድዶ መድፈር፣ ሕፃናትን ማስነወርና መበደል፣ የኃይል ጥቃት መፈጸም፣ ከባድ ስርቆት ወይም ነፍስ ግድያ የመሳሰሉትን ከባድ ወንጀሎች ለሕግ አካላት ቢያሳውቅ የጳውሎስን ምክር እየጣሰ አይደለም።

ምዕራፍ 14 አንቀጽ 14

  31 የሰይጣን ማታለያዎች

ሰይጣን የሰው ልጆችን ከተፈጠሩበት ጊዜ አንስቶ ሊያታልላቸው ሲሞክር ቆይቷል። (ዘፍጥረት 3:1-6፤ ራእይ 12:9) ሰይጣን፣ አስተሳሰባችንን ማዛባት ከቻለ መጥፎ ድርጊት እንድንፈጽም ሊያደርገን እንደሚችል ያውቃል። (2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ያዕቆብ 1:14, 15) የእሱን አስተሳሰብ ለማስፋፋትና ትክክል ለማስመሰል በፖለቲካው ዓለም፣ በሃይማኖት፣ በንግዱ ሥርዓት፣ በመዝናኛው ኢንዱስትሪ፣ በትምህርቱ ዘርፍ እንዲሁም በሌሎች በርካታ መስኮች ይጠቀማል።—ዮሐንስ 14:30፤ 1 ዮሐንስ 5:19

ሰይጣን የቀረው ጊዜ እያለቀበት እንደሆነ ያውቃል። በመሆኑም በተቻለ መጠን በርካታ ሰዎችን ለማታለል ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው። ሰይጣን በተለይ ደግሞ የይሖዋን አገልጋዮች ለማሳሳት ይሞክራል። (ራእይ 12:12) እኛም ካልተጠነቀቅን ዲያብሎስ አስተሳሰባችንን ቀስ በቀስ ሊያበላሸው ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 10:12) አንድ ምሳሌ እንውሰድ፦ ይሖዋ ጋብቻ ዘላቂ ጥምረት እንዲሆን ይፈልጋል። (ማቴዎስ 19:5, 6, 9) ይሁንና በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች ጋብቻን የሚመለከቱት በቀላሉ ሊፈርስ እንደሚችል ጥምረት አድርገው ነው። በርካታ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችም ይህን አስተሳሰብ ያስፋፋሉ። በመሆኑም ዓለም ለጋብቻ ያለው አመለካከት እንዳይጋባብን መጠንቀቅ ያስፈልገናል።

ሰይጣን እኛን ለማታለል የሚጠቀምበት ሌላው ዘዴ ደግሞ በራስ የመመራት ዝንባሌ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:4) ጠንቃቆች ካልሆንን ይሖዋ ሥልጣን ለሰጣቸው ሰዎች አክብሮት ልናጣ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወንድም የጉባኤ ሽማግሌዎች የሚሰጡትን መመሪያ መቃወም ሊጀምር ይችላል። (ዕብራውያን 12:5) ወይም ደግሞ አንዲት እህት ይሖዋ በቤተሰብ ውስጥ ላቋቋመው የራስነት ሥልጣን መገዛት ተገቢ መሆኑን መጠራጠር ትጀምር ይሆናል።—1 ቆሮንቶስ 11:3

ዲያብሎስ አስተሳሰባችንን እንዲያዛባው ላለመፍቀድ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብ ለማዳበርና አእምሯችን “ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር [ለማድረግ]” መጣር ይኖርብናል።—ቆላስይስ 3:2፤ 2 ቆሮንቶስ 2:11

ምዕራፍ 16 አንቀጽ 9

32 ሕክምና

ማናችንም ብንሆን ጥሩ ጤንነት ቢኖረን ደስ ይለናል፤ በምንታመምበት ጊዜ ደግሞ የተሻለ የሚባለውን ሕክምና ማግኘት እንፈልጋለን። (ኢሳይያስ 38:21፤ ማርቆስ 5:25, 26፤ ሉቃስ 10:34) በዛሬው ጊዜ ሐኪሞችና ሌሎች ባለሙያዎች፣ ሕመምተኞችን ለማከም የሚጠቀሙባቸው በርካታ የሕክምና ዘዴዎች አሉ። ምን ዓይነት ሕክምና እንደምንከታተል ከመወሰናችን በፊት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ግምት ውስጥ ማስገባታችን አስፈላጊ ነው። የተሟላ ጤንነት የሚኖረን በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ብቻ እንደሆነ ልናስታውስ ይገባል። ስለ ጤንነታችን ከልክ በላይ ከመጨነቃችን የተነሳ ለይሖዋ የምናቀርበውን አምልኮ ችላ እንዳንል መጠንቀቅ ይኖርብናል።—ኢሳይያስ 33:24፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:16

አንድ የሕክምና ዘዴ በአጋንንት ኃይል የሚከናወን እንደሆነ ከተሰማን ልንርቀው ይገባል። (ዘዳግም 18:10-12፤ ኢሳይያስ 1:13) ማንኛውንም ሕክምና ወይም መድኃኒት ከመጀመራችን በፊት በተቻለ መጠን የተሟላ መረጃ ለማግኘት መጣር ይኖርብናል፤ በተጨማሪም ሕክምናው በምን ዓይነት አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ለማስተዋል እንሞክር። (ምሳሌ 14:15) ሰይጣን እኛን በማታለል በአጋንንታዊ ድርጊቶች እንድንካፈል ሊያደርገን እንደሚሞክር መዘንጋት አይኖርብንም። አንድ ሕክምና ከአጋንንት ጋር ንክኪ ሊኖረው እንደሚችል ከጠረጠርን እንኳ ሕክምናውን መቀበል አይኖርብንም።—1 ጴጥሮስ 5:8

ምዕራፍ 16 አንቀጽ 18

^ አንዳንድ የሕክምና ባለሙያዎች አራቱ ዋና ዋና የደም ክፍሎች፣ ንዑሳን የደም ክፍልፋይ ሊባሉ እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። በመሆኑም ሙሉውን ደምም ሆነ አራቱን ዋና ዋና የደም ክፍሎች ማለትም ቀይ የደም ሴልን፣ ነጭ የደም ሴልን፣ ፕሌትሌትንና ፕላዝማን እንደማትወስድ ለሕክምና ባለሙያዎች በግልጽ ማስረዳት ሊኖርብህ ይችላል።