በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 13

አምላክን የሚያስደስቱት ሁሉም በዓላት ናቸው?

አምላክን የሚያስደስቱት ሁሉም በዓላት ናቸው?

“በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ምን እንደሆነ ምንጊዜም መርምራችሁ አረጋግጡ።”—ኤፌሶን 5:10

1. አምልኳችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ለምንስ?

 ኢየሱስ “እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩበት ሰዓት ይመጣል፤ . . . ምክንያቱም አብ እንዲያመልኩት የሚፈልገው እንዲህ ያሉ ሰዎችን ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 4:23፤ 6:44) ሁላችንም “በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ምን እንደሆነ” ምንጊዜም መርምረን ማረጋገጥ ይኖርብናል። (ኤፌሶን 5:10) በእርግጥ ይህን ማድረግ ቀላል የማይሆንበት ጊዜ አለ። ምክንያቱም ሰይጣን እኛን በማሳሳት ይሖዋን የሚያሳዝኑ ነገሮች እንድንፈጽም ሊያደርገን ይሞክራል።—ራእይ 12:9

2. በሲና ተራራ አጠገብ ምን እንደተፈጠረ ግለጽ።

2 ሰይጣን ሊያሳስተን የሚሞክረው በምን መንገድ ነው? ከሚጠቀምባቸው መንገዶች አንዱ፣ ትክክል ወይም ስህተት የሆኑትን ነገሮች መለየት እንድንቸገር ማድረግ ነው። የእስራኤል ብሔር በሲና ተራራ አጠገብ ሰፍሮ በነበረበት ወቅት የተፈጠረውን ሁኔታ እስቲ እንመልከት። ሙሴ ወደ ተራራው ወጥቶ እያለ ሕዝቡ በሰፈሩ ውስጥ ሆነው እየጠበቁት ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሕዝቡ፣ ሙሴን መጠበቅ ስለሰለቻቸው አሮንን አምላክ እንዲሠራላቸው ጠየቁት። እሱም የጥጃ ቅርጽ ያለው የወርቅ ጣዖት ሠራላቸው። ከዚያም ሕዝቡ በምስሉ ዙሪያ በመጨፈርና ለምስሉ በመስገድ በዓል አከበሩ። ሕዝቡ ለዚህ ጥጃ ሲሰግዱ ይሖዋን እያመለኩ እንዳሉ ተሰምቷቸው ነበር። ሆኖም ሥነ ሥርዓቱ “ለይሖዋ የሚከበር በዓል” እንደሆነ ስለገለጹ ብቻ ድርጊታቸው ትክክል ነበር ማለት አይደለም። ይሖዋ ድርጊታቸውን እንደ ጣዖት አምልኮ የቆጠረው ሲሆን ይህን በማድረጋቸው ብዙዎቹ ሕይወታቸውን አጥተዋል። (ዘፀአት 32:1-6, 10, 28) ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን? ሰይጣን እንዲያታልለን ልንፈቅድ አይገባም። “ማንኛውንም ርኩስ ነገር አትንኩ!” ተብለናል፤ በሌላ አባባል ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ ሊኖረን አይገባም። ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር መማር ያለብን ከይሖዋ ነው።—ኢሳይያስ 52:11፤ ሕዝቅኤል 44:23፤ ገላትያ 5:9

3, 4. የብዙዎቹን ታዋቂ በዓላት አመጣጥ መመርመራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

3 ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ሐዋርያቱ፣ ንጹሑን አምልኮ በማስፋፋት ረገድ ጥሩ ምሳሌ እንዲሆኑ አሠልጥኗቸዋል። እሱ ከሞተ በኋላም ሐዋርያቱ የይሖዋን መመሪያዎች ለአዳዲስ ደቀ መዛሙርት ማስተማራቸውን ቀጥለዋል። ሐዋርያቱ ከሞቱ በኋላ ግን ሐሰተኛ አስተማሪዎች፣ የተሳሳቱ ሐሳቦችንና የአረማውያን ልማዶችንና በዓላትን ወደ ጉባኤው ማስገባት ጀመሩ። እንዲያውም አንዳንድ የአረማውያን በዓላትን ስም በመቀየር የክርስትና በዓል ለማስመሰል ጥረት አድርገዋል። (2 ተሰሎንቄ 2:7, 10፤ 2 ዮሐንስ 6, 7) ከእነዚህ በዓላት ብዙዎቹ በዛሬው ጊዜም ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል፤ በዓላቱ የሐሰት እምነቶችን የሚያስፋፉ ከመሆናቸውም ሌላ ከአጋንንት ጋር ንክኪ አላቸው። *ራእይ 18:2-4, 23

4 በዛሬው ጊዜ በመላው ዓለም የሚኖሩ ሰዎች ለበዓላት ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። ይሁንና የይሖዋን አመለካከት እየተማርክ ስትሄድ ስለ አንዳንድ በዓላት ባለህ አመለካከት ላይ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግህ መገንዘብህ አይቀርም። እንዲህ ያለ ማስተካከያ ማድረግ ቀላል ላይሆን ይችላል፤ ሆኖም ይሖዋ እንደሚረዳህ መተማመን ትችላለህ። የአንዳንድ ታዋቂ በዓላትን አመጣጥ መመልከታችን ይሖዋ ስለ እነዚህ በዓላት ያለውን አመለካከት ለመረዳት ያስችለናል።

የገና በዓል አመጣጥ

5. ኢየሱስ በታኅሣሥ ወር እንዳልተወለደ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

5 በብዙ የዓለም ክፍሎች ገና የሚከበረው ታኅሣሥ 25 (በኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር ታኅሣሥ 29) ነው፤ አብዛኞቹ ሰዎች ኢየሱስ የተወለደው በዚህ ቀን እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የተወለደበትን ቀን፣ ሌላው ቀርቶ የተወለደበትን ወር እንኳ አይገልጽም፤ ሆኖም ኢየሱስ የተወለደው በየትኛው ወቅት እንደሆነ ይጠቁማል። ኢየሱስ በቤተልሔም በተወለደበት ወቅት “ሌሊት ሜዳ ላይ መንጎቻቸውን ሲጠብቁ የሚያድሩ እረኞች” እንደነበሩ ሉቃስ ዘግቧል። (ሉቃስ 2:8-11) በታኅሣሥ ወር በቤተልሔም አየሩ ቀዝቃዛና ዝናባማ ከመሆኑም ሌላ በረዶ ይጥላል፤ በመሆኑም እረኞች መንጎቻቸውን እየጠበቁ ሜዳ ላይ ማደር አይችሉም። ታዲያ ይህ ምን ይጠቁመናል? ኢየሱስ የተወለደው በታኅሣሥ ወር ሳይሆን አየሩ ቀዝቃዛ ባልሆነበት ወቅት ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ከታሪክ የተገኙ ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኢየሱስ የተወለደው በመስከረም ወይም በጥቅምት አካባቢ ነው።

6, 7. (ሀ) ከገና ጋር የተያያዙት አብዛኞቹ ልማዶች የመጡት ከየት ነው? (ለ) ስጦታ ለመስጠት የሚያነሳሳን ምን ሊሆን ይገባል?

6 ታዲያ የገና በዓል መከበር የጀመረው እንዴት ነው? በዓሉ በጥንት ጊዜ ይከበሩ ከነበሩ የአረማውያን በዓላት የመነጨ ነው፤ ከእነዚህም መካከል ሮማውያን የግብርና አምላክ የሆነውን ሳተርንን ለማሰብ የሚያከብሩት ሳተርናሊያ የተባለው በዓል ይገኝበታል። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና እንዲህ ይላል፦ “በገና በዓል ላይ ለሚንጸባረቁት ለአብዛኛዎቹ የበዓል ልማዶች መሠረት የሆነው በታኅሣሥ አጋማሽ ላይ ይከበር የነበረው ሳተርናሊያ የተባለው የሮማውያን በዓል ነው። ለምሳሌ ያህል ትልቅ ድግስ ማዘጋጀት፣ ስጦታ መለዋወጥና ሻማ ማብራት ከዚህ በዓል የተወረሱ ልማዶች ናቸው።” በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “[ገና የሚለው ቃል] ከግሪክ የተገኘ ነው። . . . በዓሉ በቆስጠንጢኖስ ጊዜ በ325 ዓ.ም. እንደተከበረ በዓለም ታሪክ እናነባለን። ከዚያ በፊት ግን ይከበር እንደነበር ማረጋገጫ አልተገኘም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ በዓሉ አይናገርም፤ ጊዜውንም ለመወሰን በቂ ማስረጃ አይሰጥም።”

7 ይሁንና በዛሬው ጊዜ ገናን የሚያከብሩ ብዙ ሰዎች ይህ በዓል አረማዊ አመጣጥ ያለው መሆኑ ትዝ አይላቸውም። እነዚህ ሰዎች ገናን የሚመለከቱት ከቤተሰባቸው ጋር ጊዜ ለማሳለፍ፣ ጥሩ ምግብ ለመመገብ እንዲሁም ስጦታ ለመለዋወጥ እንደሚያስችል አጋጣሚ አድርገው ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰቦቻቸውንና ወዳጆቻቸውን ይወዳሉ፤ ይሖዋም አገልጋዮቹ ለሌሎች ልግስና እንዲያሳዩ ይፈልጋል። በ2 ቆሮንቶስ 9:7 ላይ እንደተገለጸው ‘አምላክ በደስታ የሚሰጥ ሰው ይወዳል።’ ሆኖም ይሖዋ ለየት ያሉ አጋጣሚዎችን ጠብቀን ብቻ ስጦታ እንድንሰጥ አይፈልግም። የይሖዋ አገልጋዮች በዓመት ውስጥ በየትኛውም ወቅት ለወዳጆቻቸውና ለቤተሰቦቻቸው ስጦታ በመስጠትና አብረው ጊዜ በማሳለፍ ይደሰታሉ፤ ይህን ሲያደርጉም በምላሹ ምንም ነገር አይጠብቁም። ለሌሎች ስጦታ ለመስጠት የሚያነሳሳቸው ፍቅር ነው።—ሉቃስ 14:12-14

የበዓላትን አመጣጥ ማወቃችን በየትኞቹ በዓላት መካፈል እንደሌለብን ለመወሰን ይረዳናል

8. ኮከብ ቆጣሪዎቹ ለኢየሱስ ስጦታ ያመጡለት እንደተወለደ ነው? አብራራ።

8 ብዙ ሰዎች በገና በዓል ላይ ስጦታ መለዋወጥ ተገቢ እንደሆነ ለማስረዳት፣ ሕፃኑ ኢየሱስ በከብቶች በረት ውስጥ እያለ ሦስት ጠቢባን ስጦታ እንዳመጡለት ይጠቅሳሉ። የተወሰኑ ሰዎች ወደ ኢየሱስ ስጦታ ይዘው መሄዳቸው እውነት ነው። በጥንት ዘመን ትልቅ ቦታ ለሚሰጠው ሰው ስጦታ ማበርከት የተለመደ ነገር ነበር። (1 ነገሥት 10:1, 2, 10, 13) ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች፣ ኮከብ ቆጣሪዎች ማለትም አስማት የሚሠሩና ይሖዋን የማያመልኩ ሰዎች መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገር ታውቅ ነበር? ከዚህም ሌላ ሰዎቹ ወደ ኢየሱስ የሄዱት አራስ ሕፃን ሆኖ በበረት ውስጥ በነበረበት ወቅት ሳይሆን የተወሰነ ጊዜ ካለፈ ማለትም ቤት ውስጥ መኖር ከጀመረ በኋላ ነው።—ማቴዎስ 2:1, 2, 11

መጽሐፍ ቅዱስ የልደት በዓልን ስለ ማክበር ምን ይላል?

9. የልደት በዓላቸውን እንዳከበሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች እነማን ናቸው?

9 ልጅ የተወለደበት ዕለት አስደሳች እንደሆነ የታወቀ ነው። (መዝሙር 127:3) ይህ ሲባል ግን የልደት በዓልን ማክበር ተገቢ ነው ማለት አይደለም። እስቲ አስበው፦ የልደት በዓላቸውን እንዳከበሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው። አንደኛው የግብጹ ፈርዖን ሲሆን ሌላው ደግሞ ንጉሥ ሄሮድስ አንቲጳስ ነው። (ዘፍጥረት 40:20-22ን እና ማርቆስ 6:21-29ን አንብብ።) እነዚህ ሁለቱም ገዢዎች የይሖዋ አገልጋዮች አልነበሩም። እንዲያውም የልደት በዓሉን እንዳከበረ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸ አንድም የይሖዋ አገልጋይ የለም።

10. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የልደት በዓልን ስለ ማክበር ምን ዓይነት አመለካከት ነበራቸው?

10 ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ “የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የማንኛውንም ሰው የልደት በዓል ማክበርን፣ የአረማውያን ልማድ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱት [ነበር]” ይላል። የልደት በዓልን ከማክበር ጋር የተያያዙት ልማዶች ደግሞ በሐሰት እምነቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ለምሳሌ የጥንቶቹ ግሪኮች፣ አንድ ግለሰብ በሚወለድበት ቀን የእሱ ጠባቂ የሆነ አንድ መንፈስ እንደሚኖር ያምኑ ነበር። ይህ መንፈስ ደግሞ ግለሰቡ በተወለደበት ቀን ከተወለደ አምላክ ጋር ግንኙነት እንዳለው ያስቡ ነበር። ግለሰቡ በሕይወት ዘመኑ ጥበቃ ማግኘት ከፈለገ የልደት በዓሉን ማክበር እንዳለበት ይታመን ነበር። እንደ እነዚህ ካሉት የአረማውያን እምነቶች በተጨማሪ የልደት በዓላት ከኮከብ ቆጠራ ጋር ይያያዛሉ።

11. ይሖዋ ልግስና ስናሳይ ምን ይሰማዋል?

11 ብዙ ሰዎች የልደታቸው ቀን፣ ልዩ ዕለት እንደሆነ ይሰማቸዋል፤ እንዲሁም በዚያ ዕለት፣ ሌሎች እንደሚወዷቸውና እንደሚያደንቋቸው ሊያሳዩአቸው እንደሚገባ ያስባሉ። ሆኖም ለቤተሰባችን አባላትና ለጓደኞቻችን ፍቅር ማሳየት የሚገባን ዓመቱን ሙሉ እንጂ በአንድ የተወሰነ ቀን ብቻ መሆን የለበትም። ይሖዋ ምንጊዜም ደጎችና ለጋሶች እንድንሆን ይፈልጋል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35ን አንብብ።) ሕይወታችን ከአምላክ ያገኘነው ውድ ስጦታ ነው፤ ለዚህ ስጦታ በልደት ቀናችን ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ አድናቆታችንን መግለጽ ይገባናል።—መዝሙር 8:3, 4፤ 36:9

እውነተኛ ክርስቲያኖች ለሌሎች ስጦታ የሚሰጡት በፍቅር ተነሳስተው ነው

12. የሞት ቀን ከልደት ቀን የሚሻለው እንዴት ነው?

12 መክብብ 7:1 “ጥሩ ስም ከጥሩ ዘይት፣ የሞትም ቀን ከልደት ቀን ይሻላል” ይላል። አንድ ሰው ከተወለደበት ቀን ይልቅ የሞተበት ቀን የተሻለ የሚሆነው እንዴት ነው? ግለሰቡ በተወለደበት ቀን፣ በሕይወቱ ውስጥ ምንም ነገር ለማከናወን ገና አጋጣሚ አላገኘም፤ በሌላ አባባል ጥሩም ይሁን መጥፎ ነገር አልሠራም። ግለሰቡ ሕይወቱን ይሖዋን ለማገልገልና ለሌሎች መልካም ለማድረግ ሲጠቀምበት ግን “ጥሩ ስም” ያተርፋል፤ ይሖዋም ይህን ሰው ከሞተ በኋላም እንኳ ያስታውሰዋል። (ኢዮብ 14:14, 15) የይሖዋ አገልጋዮች የራሳቸውንም ሆነ የኢየሱስን የልደት ቀን አያከብሩም። ኢየሱስ እንድናከብረው ያዘዘን ብቸኛው በዓል የሞቱ መታሰቢያ ነው።—ሉቃስ 22:17-20፤ ዕብራውያን 1:3, 4

በዓለ ትንሣኤ

13, 14. የበዓለ ትንሣኤ አከባበር የመጣው ከየት ነው?

13 ብዙዎች በዓለ ትንሣኤን የሚያከብሩት ኢየሱስ ከሞት የተነሳበትን ዕለት ለማሰብ ነው። ይሁንና ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ትንሣኤውን እንዲያከብሩለት አላዘዘም። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በዓለ ትንሣኤን እንዳላከበሩ እንዲያውም ይህ በዓል በአረማውያን ልማዶች ላይ የተመሠረተ እንደሆነ የታሪክ መጻሕፍት ያሳያሉ። * ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ “በአዲስ ኪዳን ውስጥ፣ በዓለ ትንሣኤ እንደተከበረ የሚጠቁም ምንም ፍንጭ የለም” ይላል።

14 ታዲያ ይሖዋ፣ የልጁ ትንሣኤ ከሐሰት ሃይማኖታዊ ልማዶች ጋር መቀላቀሉ ያስደስተዋል? በጭራሽ። (2 ቆሮንቶስ 6:17, 18) ይሖዋ የኢየሱስን ትንሣኤ እንድናከብር በፍጹም አላዘዘንም።

የዘመን መለወጫ በዓል

15. የዘመን መለወጫ በዓል አመጣጥ ምን ይመስላል?

15 የዘመን መለወጫ በዓል የሚከበርበት ቀንና ከዚህ በዓል ጋር የሚያያዙት ልማዶች እንደየአገሩ ሁኔታ ይለያያሉ። የዘመን መለወጫ በዛሬው ጊዜ የተጀመረ በዓል አይደለም። ጥንታዊ ጽሑፎች እንደሚያመለክቱት በሦስተኛው ሺህ ዓመት ዓ.ዓ. እንኳ በባቢሎን ይከበር ነበር። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል፦ “በጥንቷ ሮም የዓመቱ የመጀመሪያ ቀን፣ የደጆችና የበሮች እንዲሁም የመጀመሪያዎችና የፍጻሜዎች አምላክ . . . የሚከበርበት ቀን ነበር። የዘመን መለወጫ ቀን የክርስትና በዓል ሆኖ በቤተ ክርስቲያን መከበር የጀመረው በ487 ዓ.ም. ነበር።” የዘመን መለወጫ በዓል በብዙ ቦታዎች የሚከበረው በመጠጥ፣ በጭፈራና በፈንጠዝያ ነው። ይሁን እንጂ ሮም 13:13 “መረን በለቀቀ ፈንጠዝያና በስካር፣ ልቅ በሆነ የፆታ ግንኙነትና ዓይን ባወጣ ምግባር . . . ሳይሆን በቀን ብርሃን እንደምንመላለስ በጨዋነት እንመላለስ” ይላል።

አምላክን የሚያስደስት የሠርግ ሥነ ሥርዓት

16, 17. ለሠርግ ዝግጅት ስናደርግ የትኞቹን ጉዳዮች ልናስብባቸው ይገባል?

16 የሠርግ ቀን አስደሳች ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች የሠርጋቸውን ሥነ ሥርዓት በተለያየ መንገድ ያካሂዳሉ። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ከሠርግ ጋር የተያያዙ ልማዶች ከየት እንደመጡ ቆም ብለው አያስቡም፤ በመሆኑም አንዳንድ ልማዶች ከአረማውያን እምነቶች የመጡ መሆናቸውን ላያውቁ ይችላሉ። የሠርግ ዝግጅት እያደረጉ ያሉ ክርስቲያን ተጋቢዎች ግን ሠርጋቸው ይሖዋን የሚያስደስት እንዲሆን ይፈልጋሉ። ከሠርግ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ልማዶች ከየት እንደመጡ ማወቃቸው ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ይረዳቸዋል።—ማርቆስ 10:6-9

17 አንዳንድ የሠርግ ልማዶች ለተጋቢዎቹ “መልካም ዕድል” እንደሚያመጡላቸው ይታሰባል። (ኢሳይያስ 65:11) ለምሳሌ ያህል፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ሰዎች በሙሽሮቹ ላይ ሩዝ ወይም ሌላ ነገር ይበትናሉ። ይህም ባልና ሚስቱ ልጆች እንዲወልዱ፣ ደስተኞች እንዲሆኑና ረጅም ዕድሜ እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ እንዲሁም ከክፉ ነገር እንደሚጠብቃቸው ይታመናል። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ንክኪ ካለው ከማንኛውም ልማድ ይርቃሉ።—2 ቆሮንቶስ 6:14-18ን አንብብ።

18. ከሠርግ ጋር በተያያዘ የትኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ልናስብባቸው ይገባል?

18 ክርስቲያን የሆኑ ተጋቢዎች፣ ሠርጋቸው አስደሳችና ክብር ያለው እንዲሁም በቦታው የተገኙት ሁሉ ደስ የሚሰኙበት እንዲሆን ይፈልጋሉ። በክርስቲያኖች ሠርግ ላይ የተገኙ ተጋባዦች ደግነት የጎደለው፣ ስለ ፆታ ግንኙነት የሚጠቅስ ወይም ሙሽሮቹንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን ዝቅ የሚያደርግ ነገር ሊናገሩ አይገባም። (ምሳሌ 26:18, 19፤ ሉቃስ 6:31፤ 10:27) የክርስቲያኖች ሠርግ “ኑሮዬ ይታይልኝ” የሚል መንፈስ የሚንጸባረቅበት መሆን የለበትም። (1 ዮሐንስ 2:16) የሠርግ ዝግጅት እያደረጋችሁ ከሆነ ሠርጋችሁ ጥሩ ትዝታ ጥሎባችሁ የሚያልፍ እንዲሆን የምትችሉትን ሁሉ አድርጉ።—ተጨማሪ ሐሳብ 28⁠ን ተመልከት።

ጽዋ ማንሳት

19, 20. ጽዋ ማንሳት ከየት የመጣ ልማድ ነው?

19 በሠርግና በሌሎች ግብዣዎች ላይ ጽዋ ማንሳት የተለመደ ነገር ነው። በዚህ ወቅት አንድ ሰው መልካም ምኞቱን በመግለጽ ጽዋውን ሲያነሳ ሌሎችም አብረው ጽዋቸውን በማንሳት ድጋፋቸውን ይገልጻሉ። ክርስቲያኖች ይህን ልማድ በተመለከተ ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?

20 ኢንተርናሽናል ሃንድቡክ ኦን አልኮሆል ኤንድ ካልቸር የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው ጽዋን ማንሳት፣ ለአማልክት ደም ወይም ወይን ይቀርብበት ከነበረ ጥንታዊ የአረማውያን ልማድ የመጣ ሊሆን ይችላል። ጽዋ የሚነሳው፣ አማልክቱ ‘ረጅም ዕድሜ ለእገሌ!’ ወይም ‘ለጤናችን!’ በሚሉት ቃላት የቀረበላቸውን ጸሎት እንዲሰሙ ለመለመን ነበር። በጥንት ጊዜ ሰዎች አማልክት እንዲባርኳቸው ለመጠየቅ ጽዋቸውን ያነሱ ነበር። ይሖዋ በረከት እንዲሰጠን መጠየቅ ያለብን ግን በዚህ መንገድ አይደለም።—ዮሐንስ 14:6፤ 16:23

“እናንተ ይሖዋን የምትወዱ፣ ክፉ የሆነውን ነገር ጥሉ”

21. ክርስቲያኖች በምን ዓይነት ክብረ በዓላት መካፈል አይኖርባቸውም?

21 ‘በአንድ ክብረ በዓል ላይ ልካፈል ወይስ አልካፈል?’ የሚለውን ከመወሰንህ በፊት፣ በበዓሉ ላይ የሚገኙ ሰዎች ስለሚያሳዩት ባሕርይ ቆም ብለህ አስብ። ለምሳሌ ያህል፣ በአንዳንድ ክብረ በዓላት ላይ ሰዎች ከመጠን በላይ የሚጠጡ ከመሆኑም ሌላ የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ጭፈራ ይታያል፤ አልፎ ተርፎም የሥነ ምግባር ብልግና ይፈጸማል። በተጨማሪም እንደነዚህ ያሉት ዝግጅቶች የግብረ ሰዶማውያንን አኗኗር የሚያበረታቱ አሊያም ብሔራዊ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ሊሆኑ ይችላሉ። እንደነዚህ ባሉት ዝግጅቶች ላይ የምንካፈል ከሆነ ‘ይሖዋ የሚጠላውን ነገር እንጠላለን’ ማለት እንችላለን?—መዝሙር 1:1, 2፤ 97:10፤ 119:37

22. ክርስቲያኖች በአንድ በዓል መካፈልን በተመለከተ ውሳኔ ለማድረግ ምን ይረዳቸዋል?

22 ክርስቲያኖች አምላክን በማያስከብር በየትኛውም በዓል ላለመካፈል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 10:31ተጨማሪ ሐሳብ 29⁠ን ተመልከት።) እርግጥ ነው፣ ሁሉም በዓላት ከሥነ ምግባር ብልግና፣ ከሐሰት ሃይማኖት ወይም ከብሔራዊ ስሜት ጋር የተያያዙ ናቸው ማለት አይደለም። አንድ በዓል ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የማይጋጭ ከሆነ በሥነ ሥርዓቱ መካፈልን በተመለከተ የግላችንን ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል። በዚህ ረገድ ውሳኔያችን በሌሎች ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖም ማሰባችን አስፈላጊ ነው።

በንግግራችሁም ሆነ በድርጊታችሁ ይሖዋን አክብሩ

23, 24. አንዳንድ በዓላትን በተመለከተ ያደረግነውን ውሳኔ የይሖዋ ምሥክር ላልሆኑ የቤተሰባችን አባላት ማስረዳት የምንችለው እንዴት ነው?

23 ይሖዋን የማያስደስቱ በዓላትን ማክበር አቁመህ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ እርምጃ በመውሰድህ፣ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ አንዳንድ የቤተሰብህ አባላት እንደቀድሞህ እንደማትወዳቸው ወይም አብረሃቸው መሆን እንደማትፈልግ ሊሰማቸው ይችላል። ቤተሰባችሁ አንድ ላይ የሚሰባሰበው በበዓላት ወቅት ብቻ እንደሆነ ያስቡ ይሆናል። ታዲያ ምን ማድረግ ትችላለህ? የቤተሰብህን አባላት እንደምትወዳቸውና ትልቅ ቦታ እንደምትሰጣቸው ማሳየት የምትችልባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። (ምሳሌ 11:25፤ መክብብ 3:12, 13) በሌሎች ወቅቶች አብረውህ ጊዜ እንዲያሳልፉ ልትጋብዛቸው ትችላለህ።

24 ዘመዶችህ አንዳንድ በዓላትን የማታከብረው ለምን እንደሆነ ቢጠይቁህ ጽሑፎቻችን ላይ እንዲሁም jw.org ላይ የወጡ ሐሳቦችን በመጠቀም መልስ ልትሰጣቸው ትችላለህ። ይህን ስታደርግ ግን ዓላማህ እነሱን በክርክር ማሸነፍ እንዳልሆነ አትዘንጋ፤ የአንተን አመለካከት እንዲቀበሉ መጫንም የለብህም። እንዲህ ያለ የግል ውሳኔ ላይ የደረስከው የተለያዩ ነገሮችን አገናዝበህ መሆኑን እንዲያስተውሉ እርዳቸው። ንግግርህ እርጋታ የሰፈነበትና “በጨው የተቀመመ ያህል ለዛ ያለው ይሁን።”—ቆላስይስ 4:6

25, 26. ወላጆች ልጆቻቸው የይሖዋን መሥፈርቶች እንዲወዱ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

25 ሁላችንም፣ በአንዳንድ በዓላት የማንካፈልበትን ምክንያት በደንብ መረዳታችን አስፈላጊ ነው። (ዕብራውያን 5:14) ዓላማችን ይሖዋን ማስደሰት ነው። ወላጆች ከሆንን ደግሞ ልጆቻችን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲረዱና እንዲወዷቸው ለመርዳት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ልጆቻችሁ ይሖዋ እውን ከሆነላቸው እሱን ለማስደሰት መፈለጋቸው አይቀርም።—ኢሳይያስ 48:17, 18፤ 1 ጴጥሮስ 3:15

26 ይሖዋ ለእሱ የምናቀርበው አምልኮ ንጹሕ እንዲሁም ሐቀኝነት የሚንጸባረቅበት እንዲሆን፣ የምንችለውን ያህል እንደምንጥር ሲመለከት ደስ ይለዋል። (ዮሐንስ 4:23) ይሁንና ሐቀኛ ያልሆኑ ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ሐቀኛ መሆን የማይቻል ነገር እንደሆነ ብዙዎች ይሰማቸዋል። እንዲህ ያለው አመለካከት ትክክል ነው? የሚቀጥለው ምዕራፍ ይህን ያብራራል።

^ ስለተለያዩ በዓላት መረጃ ለማግኘት የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች እና የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ (እንግሊዝኛ) የተባሉትን ጽሑፎች እንዲሁም jw.org​ን መመልከት ትችላለህ።

^ የበዓለ ትንሣኤ የእንግሊዝኛ መጠሪያ ማለትም ኢስተር፣ አንግሎ ሳክሰን የሚባሉት ሕዝቦች ከሚያመልኳት ኢስትራ የተባለች የንጋትና የጸደይ አምላክ ጋር ግንኙነት አለው። በተጨማሪም ዘ ዲክሽነሪ ኦቭ ሚቶሎጂ እንደሚገልጸው ኢስትራ የመራባት አምላክ ነበረች። ኢስተር ከተባለው በዓል ጋር የተያያዙት አንዳንድ ነገሮች (ለምሳሌ እንቁላልና ጥንቸል) ለኢስትራ ከሚቀርበው አምልኮ ጋር ዝምድና አላቸው።