በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 11

ከሠርጋችሁ ቀን በኋላ

ከሠርጋችሁ ቀን በኋላ

“ፍቅር ለዘላለም ይኖራል።”—1 ቆሮንቶስ 13:8

1, 2. በትዳር ውስጥ ችግሮች ማጋጠማቸው ትዳሩ እንዳልተሳካ የሚያሳይ ነው? አብራራ።

 ጋብቻ ከአምላክ የተገኘ ስጦታ ነው። ትዳር፣ አስደሳች ሕይወት ለመምራት አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። እርግጥ ነው፣ በየትኛውም ትዳር ውስጥ ችግሮች ማጋጠማቸው አይቀርም። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በትዳር ውስጥ የሚያጋጥሙት ችግሮች ማብቂያ የሌላቸው ይመስሉ ይሆናል፤ ባልና ሚስቱም እንደቀድሟቸው እንደማይቀራረቡ ሊሰማቸው ይችላል።

2 እኛም በትዳራችን ውስጥ አልፎ አልፎ ችግሮች ቢያጋጥሙን ልንገረም አይገባም። በትዳራችን ውስጥ ችግሮች ስላጋጠሙን ብቻ ጥሩ ትዳር የለንም ማለት አይደለም። በጣም ከባድ የሆኑ ችግሮች ያጋጠሟቸው ባለትዳሮችም እንኳ ግንኙነታቸውን ማሻሻል አልፎ ተርፎም ትዳራቸውን ማጠናከር ችለዋል። እንዴት?

ከአምላክም ሆነ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ይበልጥ ተቀራረቡ

3, 4. አንዳንድ ባለትዳሮች ምን ያጋጥማቸዋል?

3 ጋብቻ፣ የየራሳቸው አስተሳሰብ ባላቸው ሁለት የተለያዩ ሰዎች መካከል የሚመሠረት ጥምረት ነው፤ ሁለቱ ሰዎች ነገሮችን የሚያከናውኑበት መንገድ እንዲሁም የሚወዷቸውና የሚጠሏቸው ነገሮች የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪም የባልና ሚስቱ አስተዳደግም ሆነ ባሕል ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል። በመሆኑም አንድ ባልና ሚስት እርስ በርስ በደንብ ለመተዋወቅና አንዳቸው የሌላውን አመለካከት ለመረዳት ጊዜ መስጠት እንዲሁም ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።

4 ባልና ሚስት በየራሳቸው ጉዳዮች የሚጠመዱ ከሆነ በጊዜ ሂደት እየተራራቁ ሊሄዱ ይችላሉ። እንዲያውም በአንድ ጣሪያ ሥር እየኖሩ የየራሳቸውን ሕይወት መምራት ይጀምሩ ይሆናል። ታዲያ ይበልጥ እንዲቀራረቡ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

ትዳር የተሳካ እንዲሆን የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው

5. (ሀ) አንድ ክርስቲያን ከትዳር ጓደኛው ጋር ይበልጥ እንዲቀራረብ ምን ሊረዳው ይችላል? (ለ) ዕብራውያን 13:4 ለጋብቻ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ ይናገራል?

5 ይሖዋ፣ አንተም ሆንክ የትዳር ጓደኛህ ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ እንዲሁም እርስ በርስ የበለጠ ለመቀራረብ የሚረዳችሁ ግሩም ምክር በቃሉ ውስጥ አስፍሯል። (መዝሙር 25:4፤ ኢሳይያስ 48:17, 18) “ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር . . . ይሁን” ብሎናል። (ዕብራውያን 13:4) ውድ ዋጋ ያለውንና ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ነገር “ክቡር” እንደሆነ አድርገን እንደምንመለከተው የታወቀ ነው። እንዲህ ያለውን ነገር ከፍ አድርገን ስለምናየው ጉዳት እንዳይደርስበት እንጠነቀቅለታለን። ይሖዋ ለጋብቻ እንዲህ ያለ አመለካከት እንዲኖረን ይፈልጋል።

ለይሖዋ ያላችሁ ፍቅር ትዳራችሁን ያጠናክረዋል

6. ማቴዎስ 19:4-6 ይሖዋ ስለ ትዳር ምን አመለካከት እንዳለው ያሳያል?

6 የመጀመሪያውን ጋብቻ ያቋቋመው ይሖዋ ነው። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ፈጣሪ ከመጀመሪያውም ወንድና ሴት አድርጎ እንደፈጠራቸው አላነበባችሁም? ‘ከዚህ የተነሳ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ ብሎ እንደተናገረስ አላነበባችሁም? በመሆኑም ከዚህ በኋላ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።” (ማቴዎስ 19:4-6) ከመጀመሪያው አንስቶ የይሖዋ ዓላማ ትዳር ዘላቂ ጥምረት እንዲሆን ነው። አምላክ፣ ቤተሰቦች እርስ በርስ እንዲቀራረቡ እንዲሁም በደስታ አብረው እንዲኖሩ ይፈልጋል።

7. ባለትዳሮች ትዳራቸውን ለማጠናከር ምን ይረዳቸዋል?

7 በዛሬው ጊዜ ያሉ ባለትዳሮች ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ውጥረትና ጫና ያጋጥማቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎች በጣም ከመክበዳቸው የተነሳ ትዳራቸው ሊቀጥል እንደማይችል ይሰማቸዋል፤ በዚህም ምክንያት በትዳራቸው ተስፋ ይቆርጣሉ። ይሁንና ይሖዋ ስለ ትዳር ያለውን አመለካከት መገንዘባቸው ሊረዳቸው ይችላል።—1 ዮሐንስ 5:3

8, 9. (ሀ) ይሖዋ ስለ ጋብቻ የሰጠውን ምክር መታዘዝ ያለብን መቼ ነው? (ለ) ትዳራችንን እንደ ውድ ነገር እንደምንመለከተው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

8 ይሖዋ ምክር የሚሰጠን ምንጊዜም ለእኛው ጥቅም ነው። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ‘ጋብቻ ክቡር ይሁን’ የሚል ምክር ሰጥቶናል። (ዕብራውያን 13:4፤ መክብብ 5:4) የይሖዋን መመሪያ መከተል ከባድ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ የምንታዘዝ ከሆነ ብዙ ጥቅሞች እናገኛለን።—1 ተሰሎንቄ 1:3፤ ዕብራውያን 6:10

9 ትዳራችንን እንደ ውድ ነገር ስለምንመለከተው ትዳራችንን የሚጎዳ ነገር ከማድረግም ሆነ ከመናገር እንቆጠባለን። እንዲያውም ከትዳር ጓደኛችን ጋር ያለንን ጥምረት ለማጠናከር ጥረት እናደርጋለን። እንዴት?

በንግግራችሁም ሆነ በድርጊታችሁ ትዳራችሁን እንደምታከብሩ አሳዩ

10, 11. (ሀ) በአንዳንድ ትዳሮች ውስጥ ምን ዓይነት ከባድ ችግር ይስተዋላል? (ለ) የትዳር ጓደኛችንን የምናነጋግርበት መንገድ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ለምንድን ነው?

10 አንድ ሰው በትዳር ጓደኛው ላይ ጉዳት የሚያደርሰው በተለያዩ መንገዶች ሊሆን ይችላል። የትዳር ጓደኛን መምታትም ሆነ በትዳር አጋር ላይ አካላዊ ጉዳት ማድረስ ክርስቲያኖች ጨርሶ ሊያስቡት የማይገባ ነገር እንደሆነ እናውቃለን። ያም ቢሆን አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን በቃላት ሊጎዳ ይችላል። ቃላት እንደ ዱላ ሊያሳምሙ ይችላሉ። አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ በቃላት ይመታኛል። ከውጭ የሚታይ ጠባሳ ወይም ሰንበር የለብኝም። ይሁን እንጂ ‘ሸክም!’ እና ‘የማትረቢ!’ እንደሚሉት ያሉ ሁልጊዜ የሚሰነዝራቸው ጎጂ ቃላት ልቤን አቁስለውታል።” አንድ ባል ደግሞ ባለቤቱ ሁልጊዜ እንደምታንቋሽሸውና እንደምትሰድበው ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “የምትናገረኝ ነገር በሰው ፊት ለመድገም የሚከብድ ነው። ላነጋግራት የማልችለውና ሥራ ቦታ የማመሸው በዚህ ምክንያት ነው። ቤት ቶሎ ከመግባት እንዲህ ማድረግ ይሻለኛል።” ስድብ እንዲሁም ስሜትን የሚጎዳና ደግነት የጎደለው ንግግር በዛሬው ጊዜ በጣም የተለመደ ሆኗል።

11 ባለትዳሮች እርስ በርስ ሲነጋገሩ ደግነት የጎደላቸው ቃላት የሚሰነዝሩ ከሆነ የትዳር ጓደኛቸውን ስሜት በእጅጉ ሊጎዱ ይችላሉ፤ እንዲህ ያለው የስሜት ቁስል ደግሞ በቀላሉ አይሽርም። ይሖዋ፣ ባልና ሚስት አንዳቸው ሌላውን በዚህ መንገድ እንዲይዙ በፍጹም አይፈልግም። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ሳያስበውም እንኳ የትዳር ጓደኛውን ሊጎዳ ይችላል። አንተ የትዳር ጓደኛህን በደግነት እንደምትይዛት ታስብ ይሆናል፤ ይሁንና ባለቤትህ እንደዚያ ይሰማታል? ባለቤትህ ስሜቷን የሚጎዳ ነገር እንደምትናገር የሚሰማት ከሆነ ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ ነህ?—ገላትያ 5:15፤ ኤፌሶን 4:31ን አንብብ።

12. ባለትዳር የሆነ ሰው ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ሊያበላሽበት የሚችለው ነገር ምንድን ነው?

12 በሰው ፊትም ሆነ ብቻችሁን ስትሆኑ ባለቤትህን የምታነጋግርበት መንገድ ከይሖዋ ጋር ባለህ ግንኙነት ላይ ለውጥ ያመጣል። (1 ጴጥሮስ 3:7ን አንብብ።) ያዕቆብ 1:26 እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው አምላክን እያመለከ እንዳለ ቢያስብም እንኳ አንደበቱን የማይገታ ከሆነ ይህ ሰው የገዛ ልቡን ያታልላል፤ አምልኮውም ከንቱ ነው።”

13. የትዳር ጓደኛን ስሜት የሚጎዳው ሌላው ነገር ምን ሊሆን ይችላል?

13 ባለትዳሮች ለትዳር ጓደኛቸው አሳቢነት ማሳየት የሚችሉባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ከአንዲት ሴት ጋር ሰፋ ያለ ጊዜ ማሳለፍ ብትጀምር ባለቤትህ ምን ይሰማታል? ይህን የምታደርገው ከዚህች ሴት ጋር በአገልግሎት ለመካፈል አሊያም ደግሞ ያጋጠማትን ችግር ለመፍታት ብለህ ብቻ እንኳ ቢሆን የባለቤትህ ስሜት ይጎዳ ይሆን? አንዲት ክርስቲያን “ባለቤቴ በጉባኤ ውስጥ ላለች እህት ይህን ያህል ጊዜና ትኩረት ሲሰጥ ማየት ይጎዳኛል። የበታችነት ስሜት እንዲሰማኝ ያደርጋል” ብላለች።

14. (ሀ) ከዘፍጥረት 2:24 ምን ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን? (ለ) ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?

14 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ወላጆቻችንን እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን የመርዳት ኃላፊነት አለብን። ያም ቢሆን ትዳር ከመሠረትን ከማንም በላይ ቅድሚያ መስጠት ያለብን ለትዳር ጓደኛችን ነው። ይሖዋ ባል ‘ከሚስቱ ጋር እንደሚጣበቅ’ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 2:24) በመሆኑም ለትዳር ጓደኛችን ስሜት ትልቅ ቦታ ልንሰጥ ይገባል። ‘የትዳር ጓደኛዬ ከእኔ ልታገኝ የሚገባትን ጊዜ፣ ትኩረትና ፍቅር እሰጣታለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።

15. ያገቡ ክርስቲያኖች የትዳር ጓደኛቸው ካልሆነ ሰው ጋር ከመጠን በላይ መቀራረብ የሌለባቸው ለምንድን ነው?

15 የትዳር ጓደኛችን ካልሆነ ሰው ጋር ከመጠን በላይ የምንቀራረብ ከሆነ በትዳራችን ውስጥ ችግር ሊፈጠር ይችላል። የትዳር ጓደኛችን ወዳልሆነው ሰው ልንሳብ ይባስ ብሎም ከግለሰቡ ፍቅር ሊይዘን ይችላል። (ማቴዎስ 5:28) እንዲህ ያለው ስሜት እያደገ ከሄደ ደግሞ ትዳራችንን የሚያዋርድ ድርጊት ወደመፈጸም ይመራናል።

“መኝታውም ከርኩሰት የጸዳ ይሁን”

16. መጽሐፍ ቅዱስ ጋብቻን በተመለከተ ምን ምክር ይሰጣል?

16 መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጋብቻ ክቡር ይሁን’ የሚል ምክር ከሰጠ በኋላ “መኝታውም ከርኩሰት የጸዳ ይሁን፤ አምላክ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ይፈርድባቸዋልና” ይላል። (ዕብራውያን 13:4) በዚህ ጥቅስ ላይ “መኝታ” የሚለው ቃል የተሠራበት በባልና በሚስት መካከል የሚፈጸመውን የፆታ ግንኙነት ለማመልከት ነው። (ምሳሌ 5:18) ባለትዳሮች ለዚህ ዝግጅት አክብሮት ማሳየትና ከርኩሰት የጸዳ እንዲሆን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

17. (ሀ) ብዙዎች ስለ ምንዝር ምን አመለካከት አላቸው? (ለ) ክርስቲያኖች ምንዝርን እንዴት ሊመለከቱት ይገባል?

17 በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ሰዎች ለትዳር ጓደኛቸው ታማኝ አለመሆን ስህተት እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። እንዲህ ያለው አመለካከት ተጽዕኖ ሊያሳድርብን አይገባም። ይሖዋ የፆታ ብልግናን እና ምንዝርን እንደሚጠላ በግልጽ ተናግሯል። (ሮም 12:9ን አንብብ፤ ዕብራውያን 10:31፤ 12:29) የትዳር ጓደኛችን ካልሆነ ሰው ጋር የፆታ ግንኙነት ከፈጸምን ትዳራችንን እናረክሳለን። እንዲህ ያለው ድርጊት ለይሖዋ መሥፈርቶች አክብሮት እንደሌለን የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና ያበላሽብናል። ስለዚህ ‘ክፉ የሆነውን መጸየፍ’ ይኖርብናል፤ እንዲሁም ምንዝር ወደመፈጸም ሊመራን የሚችለውን የመጀመሪያ እርምጃ እንኳ እንዳንወስድ ልንጠነቀቅ ይገባል። ይህም የትዳር ጓደኛችን ያልሆነን ሰው በምኞት ዓይን ከመመልከት መቆጠብን ይጨምራል።—ኢዮብ 31:1

18. (ሀ) ምንዝር የሐሰት አማልክትን ከማምለክ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ምንዝርን የሚመለከተው እንዴት ነው?

18 ለጥንቶቹ እስራኤላውያን በተሰጠው የሙሴ ሕግ ውስጥ ምንዝር ከጣዖት አምልኮ የማይተናነስ ከባድ ኃጢአት እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ለሁለቱም ኃጢአቶች ቅጣቱ ሞት ነበር። (ዘሌዋውያን 20:2, 10) ይሁንና ምንዝር የሐሰት አማልክትን ከማምለክ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? አንድ እስራኤላዊ የሐሰት አማልክትን ካመለከ ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን የገባውን ቃል አፍርሷል። ምንዝር የሚፈጽም እስራኤላዊም ለትዳር አጋሩ ታማኝ ለመሆን የገባውን ቃል አጥፏል። (ዘፀአት 19:5, 6፤ ዘዳግም 5:9፤ ሚልክያስ 2:14ን አንብብ።) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በጥንት ዘመን፣ ይሖዋ ምንዝርን በጣም ከባድ እንደሆነ ኃጢአት አድርጎ ይመለከተው ነበር።

19. ምንዝር እንዳንፈጽም ምን ሊረዳን ይችላል?

19 ዛሬስ? ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ባንሆንም ይሖዋ ለምንዝር ያለው አመለካከት እንዳልተለወጠ እናውቃለን። የሐሰት አማልክትን በምንም ዓይነት እንደማናመልክ ሁሉ ለትዳር ጓደኛችን ያለንን ታማኝነትም በፍጹም ልናጓድል አይገባም። (መዝሙር 51:1, 4፤ ቆላስይስ 3:5) ታማኝነታችንን ብናጓድል ትዳራችንንም ሆነ አምላካችንን ይሖዋን እንደማናከብር እናሳያለን።—ተጨማሪ ሐሳብ 26⁠ን ተመልከት።

ትዳራችሁን ማጠናከር የምትችሉት እንዴት ነው?

20. ጥበብ ትዳርን ለማጠናከር የሚረዳው እንዴት ነው?

20 ትዳራችሁን ማጠናከር የምትችሉት እንዴት ነው? የአምላክ ቃል “ቤት በጥበብ ይገነባል፤ በማስተዋልም ይጸናል” ይላል። (ምሳሌ 24:3) አንድ ቤት ባዶና ቀዝቃዛ ሊሆን ይችላል፤ አሊያም ደግሞ ሞቅ ያለ፣ ምቹ እንዲሁም አስተማማኝ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል። ከትዳር ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ጠቢብ የሆነ ሰው ትዳሩ ከስጋት ነፃ እንዲሁም አስደሳች እንዲሆን ለማድረግ ይጥራል።

21. እውቀት ትዳርን የሚያጠናክረው እንዴት ነው?

21 መጽሐፍ ቅዱስ እንደዚህ ስላለው ቤት ሲናገር “በእውቀት አማካኝነት ክፍሎቹ በተለያዩ ውድ የሆኑና ያማሩ ነገሮች ተሞልተዋል” ይላል። (ምሳሌ 24:4) ከአምላክ ቃል የምትማሩት ነገር በትዳራችሁ ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። (ሮም 12:2፤ ፊልጵስዩስ 1:9) መጽሐፍ ቅዱስን እና ጽሑፎቻችንን ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ሆናችሁ ስታነቡ ትምህርቱን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምትችሉ ተወያዩ። አንዳችሁ ለሌላው ፍቅር፣ አክብሮት፣ ደግነትና አሳቢነት ለማሳየት ጥረት አድርጉ። ትዳራችሁን የሚያጠናክሩና የትዳር ጓደኛችሁ ይበልጥ እንዲወዳችሁ የሚያደርጉ ባሕርያትን ለማዳበር እንዲረዳችሁ ይሖዋን ለምኑት።—ምሳሌ 15:16, 17፤ 1 ጴጥሮስ 1:7

የቤተሰብ አምልኮ ስታደርጉ ይሖዋ እንዲመራችሁ ጠይቁት

22. የትዳር ጓደኛችንን በፍቅርና በአክብሮት መያዝ ያለብን ለምንድን ነው?

22 የትዳር ጓደኛችንን በፍቅርና በአክብሮት ለመያዝ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን ትዳራችን ፍቅር የሞላበትና ጠንካራ ይሆናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋን ደስ እናሰኛለን።—መዝሙር 147:11፤ ሮም 12:10