በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 9

“ከፆታ ብልግና ሽሹ!”

“ከፆታ ብልግና ሽሹ!”

“በምድር ያሉትን የአካል ክፍሎቻችሁን ግደሉ፤ እነሱም የፆታ ብልግና፣ ርኩሰት፣ ልቅ የሆነ የፍትወት ስሜት፣ መጥፎ ፍላጎትና ጣዖት አምልኮ የሆነው ስግብግብነት ናቸው።”—ቆላስይስ 3:5

1, 2. በለዓም የይሖዋን ሕዝብ ለመጉዳት ምን አደረገ?

 ዓሣ አጥማጁ መያዝ የሚፈልገው ዓይነት ዓሣ ወደሚገኝበት ቦታ ሄዷል። ዓሣውን ሊስበው የሚችል ምግብ መንጠቆው ጫፍ ላይ ካደረገ በኋላ ማጥመጃውን ውኃው ውስጥ አስገባው። ከዚያም በትዕግሥት መጠበቅ ጀመረ፤ ዓሣው መንጠቆው ላይ ያለውን ምግብ ሲጎርሰው አጥማጁ ዓሣውን በፍጥነት ጎትቶ አወጣው።

2 እንዲህ ዓይነቱ ዘዴ ሰዎችን ለማጥመድም ሊሠራበት ይችላል። እስራኤላውያን ያጋጠማቸውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በጣም ተቃርበው ሳለ በሞዓብ ሜዳ ላይ ሰፍረው ነበር። በዚህ ጊዜ የሞዓብ ንጉሥ፣ በለዓም የተባለውን ሰው ካስጠራ በኋላ እስራኤላውያንን ከረገመለት ብዙ ገንዘብ እንደሚሰጠው ቃል ገባለት። በለዓም እስራኤላውያንን መርገም ባይችልም ሕዝቡ በራሳቸው ላይ እርግማን እንዲያመጡ ማድረግ የሚችልበት መንገድ አዘጋጀ። በለዓም ሕዝቡን ለማታለል የሚያስችለው ወጥመድ የመረጠው በደንብ አስቦበት ነው። የእስራኤልን ወንዶች ለማሳሳት ሲል ወጣት ሞዓባውያን ሴቶችን ወደ እስራኤላውያን ሰፈር ላከ።—ዘኁልቁ 22:1-7፤ 31:15, 16፤ ራእይ 2:14

3. እስራኤላውያን በለዓም ባዘጋጀው ወጥመድ የወደቁት እንዴት ነው?

3 ታዲያ በለዓም ያሰበው ተሳካለት? አዎ። በሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ወንዶች “ከሞዓብ ሴቶች ጋር የፆታ ብልግና [ፈጸሙ]።” በተጨማሪም የፌጎር ባአል የተባለውን አስጸያፊ የመራባት አምላክና ሌሎች የሐሰት አማልክትን አመለኩ። በዚህም ምክንያት 24,000 የሚሆኑ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ትንሽ ሲቀራቸው ሕይወታቸውን አጡ።—ዘኁልቁ 25:1-9

4. በሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን የፆታ ብልግና የፈጸሙት ለምንድን ነው?

4 በርካታ እስራኤላውያን በለዓም ባዘጋጀው ወጥመድ የወደቁት ለምንድን ነው? የራሳቸውን ፍላጎት ስለማርካት ብቻ ስላሰቡ ነው፤ ይሖዋ ያደረገላቸውን ነገሮች ሁሉ ረስተው ነበር። እስራኤላውያን ለአምላክ ታማኝ እንዲሆኑ የሚያነሳሷቸው ብዙ ምክንያቶች ነበሯቸው። አምላክ ከግብፅ ባርነት ነፃ አውጥቷቸዋል እንዲሁም በምድረ በዳ እያሉ ተንከባክቧቸዋል፤ በተጨማሪም አንዳች ጉዳት ሳይደርስባቸው ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ተቃርበዋል። (ዕብራውያን 3:12) ያም ሆኖ በፆታ ብልግና ተሸነፉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ከእነሱ አንዳንዶቹ የፆታ ብልግና እንደፈጸሙ እኛም የፆታ ብልግና አንፈጽም’ ሲል ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 10:8

5, 6. እስራኤላውያን በሞዓብ ሜዳ ካጋጠማቸው ነገር ምን እንማራለን?

5 የምንኖረው አዲሱ ዓለም የሚመጣበት ጊዜ በጣም በቀረበበት ዘመን ነው። በመሆኑም ያለንበት ሁኔታ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ተቃርበው ከነበሩት እስራኤላውያን ጋር ይመሳሰላል። (1 ቆሮንቶስ 10:11) ሞዓባውያን የፆታ ፍላጎታቸውን ማርካት በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ጉዳይ ነበር፤ በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ሰዎች አመለካከት ደግሞ ከሞዓባውያንም የባሰ ነው። እንዲህ ያለው አመለካከት በይሖዋ ሕዝቦች ላይም በቀላሉ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። እንዲያውም ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው ወጥመዶች ሁሉ ይበልጥ ውጤታማ የሆነው የፆታ ብልግና ነው።—ዘኁልቁ 25:6, 14፤ 2 ቆሮንቶስ 2:11፤ ይሁዳ 4

6 እንግዲያው ‘በፆታ ብልግና ከሚገኘው ቅጽበታዊ እርካታና በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለዘላለም በደስታ ከመኖር የቱን እመርጣለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። በእርግጥም ይሖዋ “ከፆታ ብልግና ሽሹ!” በማለት የሰጠውን መመሪያ መታዘዙ የተሻለ አይሆንም?—1 ቆሮንቶስ 6:18

የፆታ ብልግና ምንድን ነው?

7, 8. የፆታ ብልግና ምንድን ነው? ይህን ድርጊት አቅልለን ልንመለከተው የማይገባውስ ለምንድን ነው?

7 በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ዓይን ያወጣ የብልግና ድርጊት የሚፈጽሙ ሲሆን አምላክ ከፆታ ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ ላወጣቸው ሕጎችም ንቀት ያሳያሉ። የፆታ ብልግና የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት፣ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ከተጋቡ ወንድና ሴት ውጭ የሚፈጸም የፆታ ግንኙነትን ለማመልከት ነው። ይህም ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል እንዲሁም ከእንስሳት ጋር የሚፈጸም የፆታ ግንኙነትን ያጠቃልላል። የፆታ ግንኙነት ሲባል በአፍና በፊንጢጣ የሚደረግ ግንኙነትን ወይም የሌላን ግለሰብ የፆታ አካል ማሻሸትን ያካትታል።—ተጨማሪ ሐሳብ 23⁠ን ተመልከት።

8 አንድ ሰው የፆታ ብልግና የሚፈጽም ከሆነ የክርስቲያን ጉባኤ አባል ሆኖ መቀጠል እንደማይችል መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 6:9፤ ራእይ 22:15) ከዚህም ሌላ፣ የፆታ ብልግና የሚፈጽም ሰው ለራሱ አክብሮት አይኖረውም፤ ሌሎች ሰዎችም ቢሆኑ አያምኑትም። የፆታ ብልግና ምንጊዜም ቢሆን ችግሮች ማስከተሉ አይቀርም። ትዳር እንዲናጋ የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ የሕሊና ወቀሳ፣ ያልተፈለገ እርግዝና፣ በሽታ ይባስ ብሎም ሞት ያስከትላል። (ገላትያ 6:7, 8ን አንብብ።) አንድ ሰው የፆታ ብልግና መፈጸም የሚያመጣውን መዘዝ ቆም ብሎ ካሰበበት እንዲህ ካለው ድርጊት ይርቃል። ይሁንና አብዛኞቹ ሰዎች ስሜታቸውን ስለማርካት እንጂ ድርጊታቸው ስለሚያስከትለው መዘዝ አያስቡም። በመሆኑም የፆታ ብልግና ወደመፈጸም የሚመራቸውን ስህተት ይሠራሉ። ብዙውን ጊዜ የመጀመሪያው ስህተት የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን መመልከት ነው።

የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች—የመጀመሪያው ስህተት

9. የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች አደገኛ የሆኑት ለምንድን ነው?

9 የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች የሚዘጋጁበት ዓላማ የፆታ ስሜትን መቀስቀስ ነው። በዛሬው ጊዜ የብልግና ይዘት ያላቸው ነገሮች የማይገኙበት ቦታ የለም ማለት ይቻላል፤ እነዚህ ነገሮች በመጽሔቶች፣ በመጻሕፍት፣ በሙዚቃዎች፣ በቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና በኢንተርኔት አማካኝነት ይተላለፋሉ። ብዙዎች የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ምንም ጉዳት እንደሌላቸው ይሰማቸዋል፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በጣም አደገኛ ናቸው። እነዚህ ነገሮች አንድ ሰው የፆታ ግንኙነት የመፈጸም ሱስ እንዲጠናወተው እንዲሁም ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ምኞት እንዲቀሰቀስበት ያደርጋሉ። የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን የሚመለከትና የሚያነብ ሰው፣ ማስተርቤሽን ልማድ ሊሆንበት እንዲሁም በትዳሩ ውስጥ ችግሮች ሊያጋጥሙት አልፎ ተርፎም ትዳሩ ሊፈርስ ይችላል።—ሮም 1:24-27፤ ኤፌሶን 4:19ተጨማሪ ሐሳብ 24⁠ን ተመልከት።

ኢንተርኔት ስንጠቀም ጥንቃቄ ማድረጋችን ጥበብ ነው

10. በያዕቆብ 1:14, 15 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ከፆታ ብልግና ለመራቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

10 የፆታ ብልግና ለመፈጸም ልንፈተን የምንችለው እንዴት እንደሆነ መገንዘባችን አስፈላጊ ነው። በያዕቆብ 1:14, 15 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ሐሳብ ልብ በል፦ “እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል። ከዚያም ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአት ሲፈጸም ደግሞ ሞት ያስከትላል።” እንግዲያው መጥፎ ምኞት ወደ አእምሮህ ከመጣ ወዲያውኑ ከአእምሮህ አውጣው። የፆታ ስሜትን ለመቀስቀስ ተብሎ የተዘጋጀ ምስል ድንገት ብትመለከት ቶሎ ብለህ ፊትህን ወደ ሌላ አቅጣጫ አዙር! ኮምፒውተሩን አጥፋው አሊያም የቴሌቪዥኑን ጣቢያ ቀይረው። መጥፎ ምኞቶች ወደ አእምሮህ እንዲገቡ አትፍቀድ። አለዚያ መጥፎ ምኞቶች እያየሉ ሄደው ምኞቶችህን መቆጣጠር የማትችልበት ደረጃ ላይ ልትደርስ ትችላለህ።ማቴዎስ 5:29, 30ን አንብብ።

11. መጥፎ ሐሳቦች ወደ አእምሯችን የሚመጡ ከሆነ ይሖዋ የሚረዳን እንዴት ነው?

11 እኛ ራሳችንን ከምናውቀው በላይ ይሖዋ ያውቀናል። በመሆኑም ፍጹማን አለመሆናችን ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚያሳድርብን ይረዳል። በሌላ በኩል ግን መጥፎ ምኞቶችን ማሸነፍ እንደምንችልም ይሖዋ ያውቃል። እንዲህ ብሎናል፦ “በምድር ያሉትን የአካል ክፍሎቻችሁን ግደሉ፤ እነሱም የፆታ ብልግና፣ ርኩሰት፣ ልቅ የሆነ የፍትወት ስሜት፣ መጥፎ ፍላጎትና ጣዖት አምልኮ የሆነው ስግብግብነት ናቸው።” (ቆላስይስ 3:5) መጥፎ ምኞቶችን ማሸነፍ ቀላል ባይሆንም ይሖዋ በትዕግሥት ይረዳናል። (መዝሙር 68:19) አንድ ወጣት ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት፤ ይህ ወንድም የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን መመልከት እንዲሁም ማስተርቤሽን መፈጸም ልማድ ሆኖበት ነበር። አብረውት የሚማሩት ልጆችም ቢሆኑ ይህ ድርጊት ማንም ሰው ወጣት እያለ የሚፈጽመው ነገር እንደሆነ ያስቡ ነበር። ይህ ወንድም “የማደርገው ነገር ሕሊናዬን ስላደነዘዘው በሥነ ምግባር ብልግና ውስጥ ተዘፈቅኩ” ብሏል። ውሎ አድሮ ግን መጥፎ ምኞቶቹን መቆጣጠር እንዳለበት ተገነዘበ፤ ደግሞም በይሖዋ እርዳታ መጥፎ ልማዱን ማሸነፍ ችሏል። አንተም መጥፎ ሐሳቦች ወደ አእምሮህ የሚመጡ ከሆነ “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነውን] ኃይል” እንዲሰጥህ ይሖዋን ለምነው፤ ይህም ንጹሕ አስተሳሰብ ለማዳበር ይረዳሃል።—2 ቆሮንቶስ 4:7፤ 1 ቆሮንቶስ 9:27

12. ‘ልባችንን መጠበቅ’ ያለብን ለምንድን ነው?

12 ሰለሞን “ከምንም ነገር በላይ ልብህን ጠብቅ፤ የሕይወት ምንጭ ከእሱ ዘንድ ነውና” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 4:23) ‘ልባችን’ ውስጣዊ ማንነታችንን ያመለክታል፤ ይሖዋም የሚመለከተው ውስጣዊ ማንነታችንን ነው። የምናየው ነገር በውስጣዊ ማንነታችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ታማኙ ኢዮብ “ከዓይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ። ታዲያ ለድንግሊቱ ተገቢ ያልሆነ ትኩረት እንዴት እሰጣለሁ?” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 31:1) እኛም እንደ ኢዮብ፣ የምናያቸውን ነገሮችና በአእምሯችን የምናውጠነጥናቸውን ሐሳቦች በተመለከተ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። እንዲሁም እንደ መዝሙራዊው “ከንቱ ነገር እንዳያዩ ዓይኖቼን መልስ” ብለን መጸለይ ያስፈልገናል።—መዝሙር 119:37

ዲና ያደረገችው ጥበብ የጎደለው ምርጫ

13. ዲና ምን ዓይነት ጓደኞች ነበሯት?

13 ጓደኞቻችን በጎም ይሁን መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን ይችላሉ። የአምላክን መሥፈርቶች የሚያከብሩ ጓደኞችን ከመረጥክ አንተም እንደዚያ እንድታደርግ ያበረታቱሃል። (ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33ን አንብብ።) ዲና ያጋጠማት ነገር የጓደኛ ምርጫችን ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ያሳያል። ዲና የያዕቆብ ልጅ እንደመሆኗ መጠን ያደገችው ይሖዋን በሚያመልክ ቤተሰብ ውስጥ ነው። ዲና መጥፎ ሥነ ምግባር ያላት ሴት አልነበረችም፤ ሆኖም ይሖዋን ከማያመልኩ ከነአናውያን ሴቶች ጋር ጓደኝነት መሥርታ ነበር። ከነዓናውያን ስለ ፆታ ሥነ ምግባር ያላቸው አመለካከት ከአምላክ ሕዝቦች በጣም የተለየ ነበር፤ እንዲያውም በመጥፎ ምግባራቸው የታወቁ ነበሩ። (ዘሌዋውያን 18:6-25) ዲና ጓደኞቿ ጋ ስትሄድ ሴኬም ከተባለ ከነአናዊ ጋር ተገናኘች፤ እሱም በዲና ተማረከ። ሴኬም በቤተሰቡ ውስጥ ካሉት ሰዎች ሁሉ “እጅግ የተከበረ” እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር። ያም ቢሆን ይሖዋን የሚወድ ሰው አልነበረም።—ዘፍጥረት 34:18, 19

14. ዲና ምን አጋጠማት?

14 ሴኬም ዲናን ስለወደዳት ተገቢ መስሎ የታየውን ነገር አደረገ። ዲናን “ወሰዳት”፤ ከዚያም ‘አስገድዶ ደፈራት።’ (ዘፍጥረት 34:1-4ን አንብብ።) ሴኬም በዲና ላይ ያደረሰው በደል እሷንም ሆነ መላ ቤተሰቧን ለሐዘን የዳረጉ ክስተቶች እንዲፈጸሙ ምክንያት ሆኗል።—ዘፍጥረት 34:7, 25-31፤ ገላትያ 6:7, 8

15, 16. ጥበበኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

15 የይሖዋ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ምንጊዜም እንደሚጠቅሙን ለመገንዘብ የዲና ዓይነት ስህተት መሥራት አያስፈልገንም። መጽሐፍ ቅዱስ “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል፤ ከሞኞች ጋር የሚገጥም ግን ጉዳት ይደርስበታል” ይላል። (ምሳሌ 13:20) እንግዲያው “የጥሩነትን ጎዳና በሙሉ” ለመረዳት ጥረት አድርግ፤ ይህም ሳያስፈልግ ሥቃይና መከራ ውስጥ ከመግባት ይጠብቅሃል።—ምሳሌ 2:6-9፤ መዝሙር 1:1-3

16 የአምላክን ቃል በማጥናት፣ ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት ወደ ይሖዋ በመጸለይ እንዲሁም ታማኝና ልባም ባሪያ የሚሰጠንን ምክር በመከተል ጥበበኞች መሆን እንችላለን። (ማቴዎስ 24:45፤ ያዕቆብ 1:5) እርግጥ ነው፣ ማናችንም ፍጹማን ስላልሆንን ድክመቶች አሉብን። (ኤርምያስ 17:9) ይሁን እንጂ አንድ ሰው አካሄድህን በማየት በፆታ ብልግና ወጥመድ ልትወድቅ እንደምትችል ቢያስጠነቅቅህ ምን ምላሽ ትሰጣለህ? በምክሩ ቅር ትሰኛለህ? ወይስ ትሑት በመሆን ምክሩን ትቀበላለህ?—2 ነገሥት 22:18, 19

17. የእምነት ባልንጀራችን የሚሰጠን ምክር ሊጠቅመን እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።

17 እስቲ የሚከተለውን ምሳሌ እንመልከት። የአንዲት እህት የሥራ ባልደረባ ለየት ያለ ትኩረት ይሰጣታል፤ እንዲያውም ከእሱ ጋር የፍቅር ጓደኝነት እንድትጀምር ጠይቋታል። ግለሰቡ ደግና በጣም ጥሩ ሰው ቢመስልም የይሖዋ አገልጋይ አይደለም። አንዲት ሌላ ክርስቲያን፣ እህታችንን ከሥራ ባልደረባዋ ጋር ጊዜ ስታሳልፍ ተመለከተቻት፤ በመሆኑም ሊያጋጥማት ስለሚችለው አደጋ በኋላ ላይ ምክር ሰጠቻት። የመጀመሪያዋ እህት ለምክሩ ምን ምላሽ ትሰጥ ይሆን? ምክሩን ላለመቀበል ሰበብ ትደረድራለች? ወይስ ምክሩ ጠቃሚ እንደሆነ ትገነዘባለች? ይህች እህት ይሖዋን ትወድ እንዲሁም ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ትፈልግ ይሆናል። ይሁንና ከሥራ ባልደረባዋ ጋር የፍቅር ግንኙነት እንዲኖራት ካደረገች ‘ከፆታ ብልግና እየሸሸች’ ነው? ወይስ ‘በገዛ ልቧ እየታመነች’?—ምሳሌ 22:3፤ 28:26፤ ማቴዎስ 6:13፤ 26:41

ከዮሴፍ ምሳሌ መማር

18, 19. ዮሴፍ በፆታ ብልግና ወጥመድ ከመያዝ ያመለጠው እንዴት ነው? ይህን ለማድረግ የረዳውስ ምንድን ነው?

18 ዮሴፍ ወጣት እያለ የአንድ ግብፃዊ ባሪያ ነበር። ከጊዜ በኋላ የጌታው ሚስት ከእሷ ጋር እንዲተኛ በየዕለቱ ትወተውተው ጀመር፤ ዮሴፍ ግን እንዲህ ማድረግ ስህተት እንደሆነ ያውቃል። ዮሴፍ ይሖዋን የሚወድና እሱን ማስደሰት የሚፈልግ ሰው ነበር። በመሆኑም ሴትየዋ ከእሷ ጋር እንዲተኛ ደጋግማ ብትጠይቀውም ዮሴፍ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም። ዮሴፍ ባሪያ በመሆኑ ጌታውን ትቶ መሄድ አይችልም። አንድ ቀን የጌታው ሚስት አብሯት እንዲተኛ ልታስገድደው ሞከረች፤ ሆኖም ዮሴፍ “ወደ ውጭ ሸሽቶ ወጣ።”—ዘፍጥረት 39:7-12ን አንብብ።

19 ዮሴፍ ሥነ ምግባር በጎደላቸው ሐሳቦች ላይ የሚያውጠነጥን ወይም ሴትየዋን በምኞት ዓይን የሚመለከታት ቢሆን ኖሮ በወጥመዱ ይወድቅ ነበር። ዮሴፍ ግን ከምንም ነገር በላይ ትልቅ ቦታ የሰጠው ከይሖዋ ጋር ላለው ዝምድና ነው። በመሆኑም ሴትየዋን “ጌታዬ ከአንቺ በስተቀር ምንም ያልሰጠኝ ነገር የለም፤ ይህን ያደረገውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው። ታዲያ እንዲህ ያለውን እጅግ መጥፎ ድርጊት በመፈጸም በአምላክ ላይ እንዴት ኃጢአት እሠራለሁ?” ብሏታል።—ዘፍጥረት 39:8, 9

20. ይሖዋ በዮሴፍ እንደተደሰተ እንዴት እናውቃለን?

20 ዮሴፍ የሚኖረው ከአገሩና ከቤተሰቡ ርቆ ቢሆንም ምንጊዜም ለአምላክ ታማኝ ነበር፤ ይሖዋም ዮሴፍን ባርኮታል። (ዘፍጥረት 41:39-49) ዮሴፍ ታማኝ በመሆን የይሖዋን ልብ አስደስቷል። (ምሳሌ 27:11) የሥነ ምግባር ብልግና እንድንፈጽም የሚቀርብልንን ፈተና መቋቋም ቀላል አይደለም። ሆኖም የሚከተለውን ሐሳብ እናስታውስ፦ “እናንተ ይሖዋን የምትወዱ፣ ክፉ የሆነውን ነገር ጥሉ። እሱ የታማኝ አገልጋዮቹን ሕይወት ይጠብቃል፤ ከክፉዎች እጅ ይታደጋቸዋል።”—መዝሙር 97:10

21. አንድ ወጣት ወንድም የዮሴፍን ምሳሌ የተከተለው እንዴት ነው?

21 የይሖዋ ሕዝቦች ‘ክፉ የሆነውን እንደሚጠሉ’ እና ‘መልካም የሆነውን እንደሚወድዱ’ የሚያሳይ እርምጃ በየዕለቱ በድፍረት ይወስዳሉ። (አሞጽ 5:15) አንተም በየትኛውም የዕድሜ ክልል ላይ ብትገኝ ለይሖዋ ታማኝ መሆን ትችላለህ። አንድ ወጣት ወንድም እምነቱን የሚፈትን ሁኔታ በትምህርት ቤት አጋጥሞት ነበር። አንዲት ልጅ በሒሳብ ፈተና ላይ መልስ ካስኮረጃት ከእሱ ጋር የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ፈቃደኛ እንደምትሆን ነገረችው። ታዲያ ወንድማችን ምን አደረገ? እንደ ዮሴፍ ዓይነት እርምጃ ወሰደ። እንዲህ ብሏል፦ “ልጅቷ ያለችኝን ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆኔን ወዲያውኑ ገለጽኩላት። ንጹሕ አቋሜን ባለማላላቴ ክብሬን ሳላጣ መኖር ችያለሁ፤ ለራሴም ጥሩ አመለካከት አለኝ።” የፆታ ብልግና መፈጸም “ጊዜያዊ ደስታ” ቢያስገኝም ብዙውን ጊዜ ከባድ ሥቃይና ሐዘን ማስከተሉ አይቀርም። (ዕብራውያን 11:25) ይሖዋን መታዘዝ ግን ምንጊዜም ቢሆን ዘላቂ ደስታ ያስገኛል።—ምሳሌ 10:22

የይሖዋን እርዳታ ተቀበል

22, 23. ከባድ ኃጢአት ብንፈጽምም እንኳ ይሖዋ የሚረዳን እንዴት ነው?

22 ሰይጣን እኛን ለማሳሳት የፆታ ብልግናን እንደ ወጥመድ ይጠቀምበታል፤ ደግሞም ይህን ፈተና ማለፍ ቀላል አይደለም። ማናችንም ብንሆን ተገቢ ያልሆኑ ሐሳቦች አንዳንድ ጊዜ ወደ አእምሯችን ይመጣሉ። (ሮም 7:21-25) ይሖዋ ይህንን ያውቃል፤ እንዲሁም “አፈር መሆናችንን ያስታውሳል።” (መዝሙር 103:14) ታዲያ አንድ ክርስቲያን የፆታ ብልግና ቢፈጽምስ? እንዲህ ያለ ከባድ ኃጢአት በመሥራቱ ምሕረት አያገኝም ማለት ነው? በጭራሽ። ግለሰቡ ከልቡ ንስሐ ከገባ ይሖዋ ይረዳዋል። አምላካችን ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ ነው።—መዝሙር 86:5፤ ያዕቆብ 5:16፤ ምሳሌ 28:13ን አንብብ።

23 በተጨማሪም ይሖዋ በፍቅር የሚንከባከቡንን ሽማግሌዎች “ስጦታ አድርጎ [ሰጥቶናል]።” (ኤፌሶን 4:8, 12፤ ያዕቆብ 5:14, 15) እነዚህ ሽማግሌዎች ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና ለማስተካከል ይረዱናል።—ምሳሌ 15:32

“ማስተዋል” ይኑርህ

24, 25. “ማስተዋል” ከፆታ ብልግና ለመራቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

24 ጥሩ ውሳኔ ማድረግ እንድንችል፣ የይሖዋ ሕጎች ያላቸውን ጥቅም መረዳት ያስፈልገናል። በምሳሌ 7:6-23 ላይ እንደተጠቀሰው ወጣት መሆን አንፈልግም። ይህ ወጣት “ማስተዋል” ስለጎደለው በፆታ ብልግና ወጥመድ ወድቋል። ማስተዋል ከአእምሮ እውቀት የበለጠ ነገር ነው። ማስተዋል ካለን የአምላክን አስተሳሰብ ለመረዳትና ሕይወታችንን በዚያ ለመምራት ጥረት እናደርጋለን። የሚከተለውን ጥበብ ያዘለ ምክር እናስታውስ፦ “ማስተዋል የሚያገኝ ሰው ሁሉ ራሱን ይወዳል። ጥልቅ ግንዛቤን እንደ ውድ ሀብት አድርጎ የሚመለከት ሁሉ ይሳካለታል።”—ምሳሌ 19:8

25 የአምላክ መሥፈርቶች ትክክል እንደሆኑ ከልብህ ታምናለህ? ምክሮቹን ተግባራዊ ማድረግህ ደስታ እንደሚያስገኝልህ ትተማመናለህ? (መዝሙር 19:7-10፤ ኢሳይያስ 48:17, 18) እርግጠኛ ካልሆንክ፣ ይሖዋ ያደረገልህን በርካታ መልካም ነገሮች ለማስታወስ ሞክር። መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም” ይላል። (መዝሙር 34:8) ይሖዋ ባደረገልህ ነገሮች ላይ ባሰላሰልክ ቁጥር ለአምላክ ያለህ ፍቅር እያደገ ይሄዳል። ይሖዋ የሚወደውን ውደድ፤ እሱ የሚጠላውንም ጥላ። አእምሮህን በመልካም ሐሳቦች ለመሙላት ይኸውም እውነት፣ ጽድቅ፣ ንጹሕ፣ ተወዳጅና በጎ በሆኑ ነገሮች ላይ ለማተኮር ጥረት አድርግ። (ፊልጵስዩስ 4:8, 9) በእርግጥም ሁላችንም በይሖዋ ጥበብ የተመራውን ዮሴፍን መምሰል እንችላለን።—ኢሳይያስ 64:8

26. በቀጣዮቹ ምዕራፎች ላይ ምን እንመለከታለን?

26 ያገባህም ሆንክ ያላገባህ፣ ይሖዋ በሕይወትህ ደስተኛ እንድትሆን ይፈልጋል። የሚቀጥሉት ሁለት ምዕራፎች ትዳርን ስኬታማ ለማድረግ የሚረዱ ሐሳቦችን ይዘዋል።