በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 16

ዲያብሎስን ተቃወሙት

ዲያብሎስን ተቃወሙት

“ዲያብሎስን . . . ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል።”—ያዕቆብ 4:7

1, 2. ስለ ሰይጣንና ስለ አጋንንቱ ልናውቀው የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

 ይሖዋ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖረን ሕይወት በጣም አስደሳች ይሆናል። አምላክ መጀመሪያ ከነበረው ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ እንኖራለን። ያ ጊዜ እስከሚመጣ ግን የምንኖረው ሰይጣንና አጋንንቱ በሚቆጣጠሩት ዓለም ውስጥ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ሰይጣንንና አጋንንቱን ማየት ባንችልም እንኳ እነዚህ ፍጥረታት መኖራቸውንና ከፍተኛ ኃይል ያላቸው መሆኑን እናውቃለን።

2 በዚህ ምዕራፍ ውስጥ፣ ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብና ራሳችንን ከሰይጣን ጥቃት መጠበቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን። ይሖዋ በዚህ ረገድ እንደሚረዳን ቃል ገብቷል። ያም ቢሆን ሰይጣንና አጋንንቱ እኛን ለማታለልና ለማጥቃት የሚጠቀሙባቸውን ዘዴዎች ማወቃችን አስፈላጊ ነው።

“እንደሚያገሳ አንበሳ”

3. ዲያብሎስ ምን ለማድረግ ይሞክራል?

3 ሰይጣን፣ የሰው ልጆች ይሖዋን የሚያመልኩት በራስ ወዳድነት ተነሳስተው እንደሆነና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ካጋጠሟቸው እሱን ማገልገላቸውን እንደሚያቆሙ ይናገራል። (ኢዮብ 2:4, 5ን አንብብ።) አንድ ሰው ስለ ይሖዋ ለማወቅ ጥረት ሲያደርግ ሰይጣንና አጋንንቱ የግለሰቡን ጥረት ለማደናቀፍ ታጥቀው ይነሳሉ። ግለሰቡ ራሱን ለይሖዋ ወስኖ ሲጠመቅ ደግሞ በጣም ይበሳጫሉ። ዲያብሎስ “የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ” እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ጴጥሮስ 5:8) ሰይጣን ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ወዳጅነት ማበላሸት ይፈልጋል።—መዝሙር 7:1, 2፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:12

ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን ሰይጣን ይበሳጫል

4, 5. (ሀ) ሰይጣን ምን ሊያደርግ አይችልም? (ለ) ‘ዲያብሎስን መቃወም’ የምንችለው እንዴት ነው?

4 ይሁንና ሰይጣንንና አጋንንቱን ልንፈራቸው አይገባም። ይሖዋ አቅማቸውን ገድቦታል። ይሖዋ እውነተኛ ክርስቲያኖች “ታላቁን መከራ” በሕይወት እንደሚያልፉ ቃል ገብቷል፤ እነዚህ ክርስቲያኖች “እጅግ ብዙ ሕዝብ” እንደሆኑም ተገልጿል። (ራእይ 7:9, 14) ዲያብሎስ፣ አምላክ የገባው ቃል እንዳይፈጸም ማድረግ የሚችለው አንዳች ነገር የለም፤ ምክንያቱም ይሖዋ ለሕዝቡ ጥበቃ ያደርጋል።

5 ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ጠብቀን ለመኖር ጥረት የምናደርግ ከሆነ ሰይጣን ወዳጅነታችንን ሊያበላሽብን አይችልም። የአምላክ ቃል “እናንተ ከእሱ ጋር እስከሆናችሁ ድረስ ይሖዋ ከእናንተ ጋር ይሆናል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (2 ዜና መዋዕል 15:2፤ 1 ቆሮንቶስ 10:13ን አንብብ።) በጥንት ዘመን የኖሩ እንደ አቤል፣ ሄኖክ፣ ኖኅ፣ ሣራ እና ሙሴ ያሉ በርካታ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ከይሖዋ ጋር የመሠረቱትን ወዳጅነት ጠብቀው በመኖር ዲያብሎስን ተቃውመውታል። (ዕብራውያን 11:4-40) እኛም እንደ እነሱ ማድረግ እንችላለን። የአምላክ ቃል “ዲያብሎስን . . . ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል” ብሎናል።—ያዕቆብ 4:7

‘ትግል ገጥመናል’

6. ሰይጣን ጥቃት የሚሰነዝርብን እንዴት ነው?

6 ሰይጣን፣ ይሖዋ አቅሙን እንደገደበበት ቢያውቅም ከአምላክ ጋር ያለንን ወዳጅነት ለማበላሸት ማንኛውንም ጥረት ከማድረግ አይመለስም። በዛሬው ጊዜ ዲያብሎስ ጥቃት የሚሰነዝረው በተለያዩ መንገዶች ነው፤ ደግሞም በሺህዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የተጠቀመባቸውን ዘዴዎች ዛሬም ይጠቀምባቸዋል። ከእነዚህ ዘዴዎች አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት።

7. ሰይጣን በይሖዋ አገልጋዮች ላይ ጥቃት የሚሰነዝረው ለምንድን ነው?

7 ሐዋርያው ዮሐንስ “መላው ዓለም . . . በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:19) ሰይጣን ይህን ክፉ ዓለም በቁጥጥሩ ሥር ማድረግ ችሏል፤ የይሖዋን አገልጋዮችም መቆጣጠር ይፈልጋል። (ሚክያስ 4:1፤ ዮሐንስ 15:19፤ ራእይ 12:12, 17) ዲያብሎስ የቀረው ጊዜ አጭር እንደሆነ ያውቃል፤ በመሆኑም ለአምላክ ያለንን ታማኝነት እንድናጓድል ለማድረግ በእያንዳንዳችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። ዲያብሎስ አንዳንድ ጊዜ ቀጥተኛ ጥቃት ይሰነዝራል፤ በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ስውር የሆኑ ዘዴዎችን ይጠቀማል።

8. እያንዳንዱ ክርስቲያን ሊገነዘበው የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

8 ኤፌሶን 6:12 “የምንታገለው . . . በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ነው” ይላል። እያንዳንዱ ክርስቲያን ከዲያብሎስና ከአጋንንቱ ጋር በግለሰብ ደረጃ ትግል ገጥሟል። ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሁሉ በዚህ ትግል እንደሚካፈሉ መዘንጋት አይኖርብንም። ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‘ጸንተው እንዲቆሙ’ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል።—ኤፌሶን 6:11, 13, 14

9. ሰይጣንና አጋንንቱ ምን ሊያደርጉን ይሞክራሉ?

9 ሰይጣንና አጋንንቱ በተለያዩ መንገዶች ተጠቅመው እኛን ለማሳሳት ይጥራሉ። ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው ዘዴዎች በአንዱ ስላልተሸነፍን ብቻ በሌሎች ዘዴዎቹ እንደማንሸነፍ ሊሰማን አይገባም። ዲያብሎስ ድክመታችን ምን እንደሆነ ካወቀ በኋላ እኛን ለመያዝ የሚጠቀምበትን ወጥመድ ይመርጣል። እኛ ግን ዲያብሎስ የሚጠቀምባቸውን ወጥመዶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ስለተማርን ከወጥመዶቹ ማምለጥ እንችላለን። (2 ቆሮንቶስ 2:11ተጨማሪ ሐሳብ 31⁠ን ተመልከት።) ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው ወጥመዶች አንዱ አጋንንታዊ ሥራ ነው።

ከአጋንንት ራቁ

10. (ሀ) አጋንንታዊ ሥራ የሚባለው ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ስለ አጋንንታዊ ሥራዎች ምን አመለካከት አለው?

10 አጋንንታዊ ሥራ የሚባለው በተለያዩ መንገዶች አማካኝነት ከአጋንንት ጋር የሚፈጠር ግንኙነት ነው፤ አንዳንዶች እንደ ጥንቆላ፣ አስማትና ድግምት ባሉት ነገሮች አማካኝነት አሊያም ሙታንን ለማነጋገር በመሞከር በአጋንንታዊ ሥራ ይካፈላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አጋንንታዊ ሥራ “አስጸያፊ” እንደሆነና በእነዚህ ድርጊቶች እየተካፈልን ይሖዋን ማምለክ እንደማንችል ይገልጻል። (ዘዳግም 18:10-12፤ ራእይ 21:8) ክርስቲያኖች ከማንኛውም ዓይነት አጋንንታዊ ሥራ ሙሉ በሙሉ መራቅ አለባቸው።—ሮም 12:9

11. ስለ ምትሃታዊ ድርጊቶች ለማወቅ መጓጓት ምን ሊያስከትል ይችላል?

11 ሰይጣን፣ ምትሃታዊ ድርጊቶች (በሳይንስ ወይም በተፈጥሮ ሕጎች ሊብራሩ የማይችሉ ክንውኖች) ትኩረታችንን የሚስቡት ከሆነ በአጋንንታዊ ሥራዎች እንድንካፈል ማድረግ ቀላል እንደሚሆንለት ያውቃል። ማንኛውም ዓይነት አጋንንታዊ ሥራ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ያበላሽብናል።

ሰይጣን ሊያታልለን ይሞክራል

12. ሰይጣን በአስተሳሰባችን ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚጥረው እንዴት ነው?

12 ሰይጣን ሰዎችን ግራ ለማጋባት ይጥራል። በሰዎች አእምሮ ውስጥ ቀስ በቀስ ጥርጣሬ በመዝራት “ጥሩውን መጥፎ፣ መጥፎውንም ጥሩ” እንዲሉ ተጽዕኖ ያሳድርባቸዋል። (ኢሳይያስ 5:20) ዲያብሎስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ምክሮች ጠቃሚ እንዳልሆኑና የአምላክን ሕጎች ባንከተል ሕይወታችን አስደሳች እንደሚሆን ሊያሳምነን ይሞክራል።

13. ሰይጣን ጥርጣሬ ለመፍጠር የሞከረው እንዴት ነው?

13 ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው በጣም ውጤታማ መንገዶች አንዱ ጥርጣሬ መዝራት ነው። ይህን ዘዴ ለዘመናት ሲጠቀምበት ቆይቷል። ለምሳሌ በኤደን ገነት ውስጥ፣ ሔዋን ጥርጣሬ እንዲያድርባት ለማድረግ ሲል “በእርግጥ አምላክ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም ዛፍ አትብሉ’ ብሏችኋል?” በማለት ጠይቋታል። (ዘፍጥረት 3:1) ከጊዜ በኋላ በኢዮብ ዘመንም ተመሳሳይ ነገር አድርጓል፤ ሰይጣን “ኢዮብ አምላክን የሚፈራው እንዲያው በከንቱ ነው?” በማለት ይሖዋን በመላእክት ፊት ጠይቆታል። (ኢዮብ 1:9) ኢየሱስንም ከተጠመቀ በኋላ “የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ እነዚህ ድንጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ እዘዝ” በማለት ፈትኖታል።—ማቴዎስ 4:3

14. ሰይጣን አጋንንታዊ ሥራዎች አደገኛ መሆናቸውን ሰዎች እንዲጠራጠሩ ምን ያደርጋል?

14 በዛሬው ጊዜም ዲያብሎስ ጥርጣሬ ለመዝራት ጥረት ማድረጉን ቀጥሏል። ከአጋንንታዊ ሥራዎች ጋር ንክኪ ያላቸው አንዳንድ ነገሮችን ምንም ጉዳት እንደሌላቸው አድርጎ በማቅረብ እነዚህ ነገሮች መጥፎ እንዳልሆኑ ለማስመሰል ይጥራል። አንዳንድ ክርስቲያኖችም እንኳ እነዚህ ነገሮች አደገኛ መሆናቸውን ማስተዋል ተስኗቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 11:3) ታዲያ ራሳችንን ከአደጋው መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? በሰይጣን ዘዴዎች እንዳንታለል ምን ማድረግ እንችላለን? በሰይጣን ማታለያ ልንወድቅ የምንችልባቸውን ሁለት ነገሮች ይኸውም መዝናኛንና ሕክምናን እስቲ እንመልከት።

ሰይጣን በተፈጥሯዊ ፍላጎታችን ይጠቀማል

15. የምንመርጠው መዝናኛ ከአጋንንት ጋር ንክኪ እንድንፈጥር ሊያደርገን የሚችለው እንዴት ነው?

15 በዛሬው ጊዜ እንደ አስማት ያሉ አጋንንታዊ ሥራዎችን ጥሩ አድርገው ለማቅረብ የሚሞክሩ በርካታ ፊልሞች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ የኮምፒውተር ጨዋታዎች እንዲሁም የኢንተርኔት ድረ ገጾች አሉ። ብዙዎች እነዚህ ነገሮች ምንም ጉዳት የሌላቸው መዝናኛዎች እንደሆኑ የሚያስቡ ሲሆን ከአጋንንት ጋር ንክኪ መፍጠር የሚያስከትለውን አደጋም አይገነዘቡም። እንደ ኮከብ ቆጠራ፣ የእጅ መዳፍ ማንበብ፣ የጥንቆላ ካርዶችንና ክሪስታል ኳሶችን መመልከት ወይም ቡና ከጠጡ በኋላ ሲኒው ውስጥ የቀረውን ዝቃጭ ማየት ያሉት ነገሮችም አንድ ሰው በአጋንንታዊ ሥራ እንዲካፈል ያደርጉታል። ዲያብሎስ በእነዚህ ድርጊቶች መካፈል አደገኛ እንዳልሆነ እንዲያውም አጓጊና አስደሳች እንደሆነ ለማስመሰል ይሞክራል። አንዳንዶች ደግሞ በአጋንንታዊ ሥራ በቀጥታ እስካልተካፈሉ ድረስ አጋንንታዊ ሥራዎችና ምትሃታዊ (ሱፐርናቹራል) ነገሮች የሚታዩባቸውን ፊልሞች መመልከት ምንም ጉዳት እንደሌለው ያስባሉ። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?—1 ቆሮንቶስ 10:12

16. ከምትሃታዊ ድርጊቶች ጋር ግንኙነት ካላቸው መዝናኛዎች መራቅ ያለብን ለምንድን ነው?

16 ሰይጣንና አጋንንቱ የምናስበውን ነገር ማወቅ አይችሉም። ሆኖም ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን የምንመርጠውን መዝናኛ ጨምሮ የምናደርጋቸውን ውሳኔዎች በመመልከት ምን እንደምንፈልግና ምን እንደምናስብ ማስተዋል ይችላሉ። ስለ መናፍስት ጠሪዎችና ድግምት፣ በአጋንንት ስለተያዙ ሰዎች፣ ስለ ጠንቋዮችና ቫምፓየሮች ወይም እንደ እነዚህ ስላሉት ነገሮች የሚያወሱ ፊልሞችን፣ ሙዚቃዎችን ወይም መጻሕፍትን የምንከታተል ከሆነ ሰይጣንና አጋንንቱ ስለ እነሱ ለማወቅ እንደምንጓጓ ያስተውላሉ። በመሆኑም በአጋንንታዊ ሥራዎች ይበልጥ እንድንካፈል ሊያደርጉን ይሞክራሉ።—ገላትያ 6:7ን አንብብ።

17. ጤነኛ ለመሆን ያለንን ፍላጎት በመጠቀም ሰይጣን ሊያታልለን የሚችለው እንዴት ነው?

17 ሰይጣን፣ ጤነኛ ለመሆን ያለንን ፍላጎትም እኛን ለማታለል ይጠቀምበታል። በዛሬው ጊዜ ብዙዎች በተለያዩ በሽታዎች ይሠቃያሉ። የጤና እክል ያለበት አንድ ግለሰብ የተለያዩ ሕክምናዎችን ቢሞክርም ከሕመሙ መዳን አልቻለ ይሆናል። (ማርቆስ 5:25, 26) ግለሰቡ ለመዳን ካለው ጉጉት የተነሳ ማንኛውንም ነገር ለመሞከር ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል። ክርስቲያኖች ግን “አስማታዊ ድርጊት” የሚፈጸምባቸውን የሕክምና ዘዴዎች ላለመጠቀም መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።—ኢሳይያስ 1:13

በምትታመሙበት ጊዜ በይሖዋ ታመኑ

18. ክርስቲያኖች ከምን ዓይነት ሕክምና መራቅ ይኖርባቸዋል?

18 በጥንቷ እስራኤል ውስጥ “አስማታዊ ድርጊት” የሚፈጽሙ ሰዎች ነበሩ። ይሖዋ እነዚህን ሰዎች “እጆቻችሁን ስትዘረጉ ዓይኖቼን ከእናንተ እሰውራለሁ። ጸሎት ብታበዙም እንኳ አልሰማችሁም” ብሏቸው ነበር። (ኢሳይያስ 1:15) እስቲ አስበው፦ ይሖዋ የእነዚህን ሰዎች ጸሎት ለመስማት እንኳ ፈቃደኛ አልነበረም! እኛም ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት የሚያበላሽና በተለይ ደግሞ ታምመን ባለንበት ወቅት የእሱን እርዳታ እንዳናገኝ እንቅፋት የሚሆን ነገር ማድረግ አንፈልግም። (መዝሙር 41:3) በመሆኑም አንድን ሕክምና ከመጀመራችን በፊት፣ ሕክምናው ከአጋንንታዊ ሥራዎች ወይም ከምትሃታዊ ድርጊቶች ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንደሌለው ማረጋገጥ ያስፈልገናል። (ማቴዎስ 6:13) ሕክምናው ከእነዚህ ነገሮች ጋር ንክኪ እንዳለው ከጠረጠርን ሕክምናውን መቀበል አይኖርብንም።—ተጨማሪ ሐሳብ 32⁠ን ተመልከት።

ስለ አጋንንት የሚገልጹ ታሪኮች

19. ብዙ ሰዎች ዲያብሎስን እንዲፈሩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?

19 አንዳንድ ሰዎች፣ ዲያብሎስና አጋንንቱ በእውን ያሉ ፍጥረታት እንዳልሆኑ ይሰማቸዋል፤ ሌሎች ግን በሕይወታቸው ውስጥ ያጋጠማቸው ነገር ዲያብሎስና አጋንንቱ መኖራቸውን እንዲያምኑ አድርጓቸዋል። በመሆኑም ብዙ ሰዎች ክፉ መናፍስትን በጣም የሚፈሩ ሲሆን በአጉል እምነት ላይ ለተመሠረቱ ልማዶችም ባሪያ ሆነዋል። አንዳንዶች፣ አጋንንት በሰዎች ላይ የፈጸሟቸውን አስከፊ ነገሮች የሚገልጹ ታሪኮችን ያወራሉ፤ ይህም ሰዎች አጋንንትን እንዲፈሩ ያደርጋል። ብዙውን ጊዜ ሰዎች እንዲህ ያሉ ታሪኮችን መስማት የሚያጓጓቸው ሲሆን ለሌሎች ይህን ማውራትም ያስደስታቸዋል። እንደነዚህ ያሉት ታሪኮች ሰዎች ዲያብሎስን እንዲፈሩት ያደርጋሉ።

20. የሰይጣንን ውሸት ልናስፋፋ የምንችለው እንዴት ነው?

20 ሰይጣን ሰዎች እንዲፈሩት ይፈልጋል። (2 ተሰሎንቄ 2:9, 10) ሰይጣን ውሸታም ነው፤ አጋንንታዊ ሥራዎች የሚማርኳቸውን ሰዎች አስተሳሰብ በማዛባት፣ እውነት ያልሆኑ ነገሮችን እንዲያምኑ ማድረግ የሚችለው እንዴት እንደሆነ ያውቃል። እነዚህ ሰዎች እንዳዩት ወይም እንደሰሙት የሚያስቡትን ነገር ለሌሎች ያወሩ ይሆናል። እንደነዚህ ያሉት ታሪኮች ተደጋግመው በተወሩ ቁጥር ይበልጥ እየተጋነኑ መሄዳቸው አይቀርም። እኛ ግን እንዲህ ያሉ ታሪኮችን ለሌሎች በማውራት ሰዎች ሰይጣንን እንዲፈሩት ማድረግ አንፈልግም።—ዮሐንስ 8:44፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:16

21. ስለ አጋንንት የሚገልጹ ታሪኮችን ከማውራት ይልቅ ትኩረት ማድረግ ያለብን በምን ላይ ነው?

21 አንድ የይሖዋ ምሥክር ቀደም ሲል ከአጋንንት ጋር ንክኪ ከነበረው፣ ሌሎችን ለማስደመም ሲል እነዚህን ታሪኮች አያወራም። የይሖዋ አገልጋዮች፣ ዲያብሎስም ሆነ አጋንንቱ የሚያደርጓቸውን ነገሮች በማሰብ በፍርሃት መዋጥ አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ ትኩረት ማድረግ ያለብን በኢየሱስና ይሖዋ ለእሱ በሰጠው ኃይል ላይ ነው። (ዕብራውያን 12:2) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለማስገረም ሲል ስለ አጋንንት የሚገልጹ ታሪኮችን አላወራላቸውም። ኢየሱስ በዋነኝነት ያስተማረው ስለ መንግሥቱ ምሥራችና “ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ” ነው።—የሐዋርያት ሥራ 2:11፤ ሉቃስ 8:1፤ ሮም 1:11, 12

22. ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

22 የሰይጣን ዓላማ ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ወዳጅነት ማበላሸት መሆኑን ፈጽሞ አንዘንጋ። ይህን ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። እኛ ግን የዲያብሎስን ዘዴዎች ስለምናውቅ ከማንኛውም ዓይነት አጋንንታዊ ሥራ ለመራቅ ቆርጠናል። ዲያብሎስ ይህንን አቋማችንን ለመሸርሸር “አጋጣሚ እንዲያገኝ” አናደርግም። (ኤፌሶን 4:27ን አንብብ።) በእርግጥም ዲያብሎስን የምንቃወመው ከሆነ ከወጥመዶቹ ማምለጥ ብሎም የይሖዋን ጥበቃ ማግኘት እንችላለን።—ኤፌሶን 6:11