በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 3

አምላክን የሚወዱ ጓደኞችን ምረጥ

አምላክን የሚወዱ ጓደኞችን ምረጥ

“ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል።”—ምሳሌ 13:20

1-3. (ሀ) ምሳሌ 13:20 ምን ያስተምረናል? (ለ) ጓደኞቻችንን በጥበብ መምረጥ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

 አንድ ሕፃን ወላጆቹን እንዴት በትኩረት እንደሚመለከት አስተውለህ ታውቃለህ? ልጁ አፍ ከመፍታቱ በፊትም እንኳ የሚያያቸውና የሚሰማቸው ነገሮች በአእምሮው ውስጥ ይቀረጻሉ። እያደገ ሲሄድ ደግሞ ሳያውቀው ወላጆቹን መምሰል ይጀምራል። አዋቂዎችም ቢሆኑ፣ አብረዋቸው ብዙ ጊዜ የሚያሳልፉትን ሰዎች አስተሳሰብና ድርጊት ይኮርጃሉ።

2 ምሳሌ 13:20 “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል” ይላል። እዚህ ላይ የተጠቀሰው “የሚሄድ” የሚለው ቃል፣ አንድ ሰው ከሌላ ግለሰብ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ መምረጡን ያመለክታል። ይህ ሐሳብ ከአንድ ግለሰብ ጋር መሆንን ብቻ የሚያመለክት አይደለም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንደገለጹት ከአንድ ሰው ጋር መሄድ ሲባል ግለሰቡን መውደድንና መቅረብን ይጨምራል። አብረናቸው ሰፋ ያለ ጊዜ የምናሳልፍ በተለይም የምንቀርባቸው ሰዎች ይበልጥ ተጽዕኖ ያሳድሩብናል።

3 ጓደኞቻችን ጥሩ ወይም መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን ይችላሉ። ምሳሌ 13:20 “ከሞኞች ጋር የሚገጥም . . . ጉዳት ይደርስበታል” በማለት አክሎ ይናገራል። “የሚገጥም” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ አገላለጽ ከአንድ ሰው ጋር ‘አብሮ መሆንን’ ማለትም ከግለሰቡ ጋር ጓደኝነት መመሥረትን ሊያመለክት ይችላል። (መሳፍንት 14:20) ጓደኞቻችን አምላክን የሚወዱ ከሆነ ምንጊዜም ለእሱ ታማኝ እንድንሆን ያበረታቱናል። ታዲያ ጓደኞቻችንን በጥበብ ለመምረጥ ምን ይረዳናል? ይሖዋ ወዳጆቹ አድርጎ የሚመርጠው ምን ዓይነት ሰዎችን እንደሆነ መመልከታችን በዚህ ረገድ ይጠቅመናል።

የአምላክ ወዳጆች እነማን ናቸው?

4. የአምላክ ወዳጅ መሆን ታላቅ ክብር ነው የምንለው ለምንድን ነው? ይሖዋ አብርሃምን “ወዳጄ” በማለት የጠራው ለምንድን ነው?

4 የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ የሆነው ይሖዋ ከእሱ ጋር ወዳጅነት የመመሥረት አጋጣሚ ከፍቶልናል። ይህ እጅግ ታላቅ ክብር ነው። እርግጥ ይሖዋ ወዳጆቹን የሚመርጠው በጥንቃቄ ነው። ወዳጆቹ አድርጎ የሚመርጠው በእሱ ላይ እምነት ያላቸውንና የሚወዱትን ሰዎች ነው። አብርሃምን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አብርሃም፣ አምላክ የሚጠይቀውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነበር። በተጨማሪም ታማኝና ታዛዥ መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል። ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት ለማድረግ እንኳ ፈቃደኛ ነበር። አብርሃም “አምላክ [ይስሐቅን] ከሞት እንኳ ሳይቀር ሊያስነሳው እንደሚችል” እምነት ነበረው። (ዕብራውያን 11:17-19፤ ዘፍጥረት 22:1, 2, 9-13) አብርሃም ታማኝና ታዛዥ ስለነበር ይሖዋ “ወዳጄ” በማለት ጠርቶታል።—ኢሳይያስ 41:8፤ ያዕቆብ 2:21-23

5. ይሖዋ ለእሱ ታማኝ የሚሆኑ ሰዎችን የሚመለከተው እንዴት ነው?

5 ይሖዋ ወዳጆቹን ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል። ወዳጆቹም ከምንም በላይ የሚያሳስባቸው ለእሱ ታማኝ መሆናቸው ነው። (2 ሳሙኤል 22:26ን አንብብ።) የይሖዋ ወዳጆች እሱን ስለሚወዱት ይታዘዙታል፤ እንዲሁም ለእሱ ታማኝ ይሆናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ “ከቅኖች” ይኸውም እሱን ከሚታዘዙ ሰዎች ጋር “የጠበቀ ወዳጅነት” እንዳለው ይናገራል። (ምሳሌ 3:32) ይሖዋ ወዳጆቹን ‘በድንኳኑ’ ውስጥ በእንግድነት እንዲስተናገዱ ጋብዟቸዋል። ይህም ሲባል እሱን የማምለክና በማንኛውም ጊዜ ወደ እሱ የመጸለይ መብት ሰጥቷቸዋል ማለት ነው።—መዝሙር 15:1-5

6. ኢየሱስን እንደምንወደው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

6 ኢየሱስ “ማንም ሰው እኔን የሚወደኝ ከሆነ ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:23) ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው፣ የይሖዋ ወዳጅ ለመሆን ልጁን መውደድና እሱ ያስተማረንን ተግባራዊ ማድረግም ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ምሥራቹን እንድንሰብክና ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የሰጠንን ትእዛዝ እንፈጽማለን። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ዮሐንስ 14:15, 21) ኢየሱስን ስለምንወደው “የእሱን ፈለግ በጥብቅ” እንከተላለን። (1 ጴጥሮስ 2:21) ይሖዋ፣ በንግግራችንም ሆነ በተግባራችን ኢየሱስን ለመምሰል የምንችለውን ያህል እንደምንጥር ሲያይ ይደሰታል።

7. ይሖዋ የሚመርጣቸው ዓይነት ወዳጆች መምረጥ ያለብን ለምንድን ነው?

7 ይሖዋ ወዳጆቹ አድርጎ የሚመርጠው ለእሱ ታማኝ የሆኑና የሚታዘዙትን እንዲሁም ልጁን የሚወዱ ሰዎችን ነው። እኛስ ጓደኞቻችን እንዲሆኑ የምንመርጠው እንዲህ ያሉ ሰዎችን ነው? ጓደኞችህ ኢየሱስን የሚመስሉ እንዲሁም ስለ አምላክ መንግሥት በማስተማሩ ሥራ የተጠመዱ ሰዎች ከሆኑ፣ አንተም ጥሩ ባሕርያት እንድታዳብርና ምንጊዜም ለይሖዋ ታማኝ እንድትሆን ሊረዱህ ይችላሉ።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች መማር

8. ሩትና ናኦሚ ከነበራቸው ጓደኝነት የሚያስገርምህ ምንድን ነው?

8 መጽሐፍ ቅዱስ፣ የተለያዩ ሰዎች ስለነበራቸው ጓደኝነት ይናገራል፤ ከእነዚህ መካከል በሩትና በአማቷ በናኦሚ መካከል የነበረውን ጓደኝነት እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። የእነዚህ ሴቶች የትውልድ አገርም ሆነ አስተዳደግ የተለያየ ሲሆን ናኦሚ ሩትን በዕድሜ በጣም ትበልጣት ነበር። ሆኖም ሁለቱም ይሖዋን ይወዱ ስለነበር የቅርብ ጓደኛሞች መሆን ችለዋል። ናኦሚ ሞዓብን ለቅቃ ወደ እስራኤል ለመመለስ ስትነሳ፣ ሩት “ከእሷ ላለመለየት የሙጥኝ አለች።” ሩት ለናኦሚ “ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል” አለቻት። (ሩት 1:14, 16) ሩት ለናኦሚ በጣም ደግ ነበረች። እስራኤል ከደረሱ በኋላ፣ ሩት ወዳጇን ናኦሚን ለመንከባከብ ተግታ ትሠራ ነበር። ናኦሚም ሩትን ከልቧ ትወዳት የነበረ ሲሆን ጥሩ ምክር ሰጥታታለች። ሩት የናኦሚን ምክር በመስማቷ ሁለቱም የተትረፈረፈ በረከት አግኝተዋል።—ሩት 3:6

9. በዳዊትና በዮናታን መካከል የነበረውን ጓደኝነት እንድታደንቅ የሚያደርግህ ምንድን ነው?

9 ዳዊትና ዮናታንም ጥሩ ጓደኛሞች ነበሩ፤ ሁለቱም ለይሖዋ ታማኝ መሆናቸውን አሳይተዋል። ዮናታን ዳዊትን 30 ዓመት ገደማ የሚበልጠው ሲሆን አባቱን ተክቶ በእስራኤል ላይ ንጉሥ የመሆን አጋጣሚም ነበረው። (1 ሳሙኤል 17:33፤ 31:2፤ 2 ሳሙኤል 5:4) ይሁንና ዮናታን፣ ይሖዋ ንጉሥ እንዲሆን የመረጠው ዳዊትን እንደሆነ ሲያውቅ የቅናት ወይም የፉክክር መንፈስ አላሳየም። ከዚህ ይልቅ ዳዊትን ለመደገፍ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አድርጓል። ለምሳሌ ያህል፣ ዳዊት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ በነበረበት ወቅት “በይሖዋ ላይ ያለው ትምክህት እንዲጠናከር” ዮናታን ረድቶታል። እንዲያውም ዳዊትን ለመርዳት ሲል ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሏል። (1 ሳሙኤል 23:16, 17) ዳዊትም ቢሆን ታማኝ ወዳጅ ነበር። የዮናታንን ቤተሰብ ለመንከባከብ ቃል የገባ ሲሆን ዮናታን ከሞተ በኋላም ይህን ቃሉን ጠብቋል።—1 ሳሙኤል 18:1፤ 20:15-17, 30-34፤ 2 ሳሙኤል 9:1-7

10. የሦስቱ ዕብራውያን ምሳሌ ስለ ጓደኝነት ምን ያስተምርሃል?

10 ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የተባሉትን ሦስት ዕብራውያን ወጣቶችም እንመልከት፤ እነዚህ ጓደኛሞች ከአገራቸው ወደ ባቢሎን የተወሰዱት ልጆች እያሉ ነበር። ከቤተሰባቸው ርቀው የሚኖሩት እነዚህ ወጣቶች እርስ በርስ መደጋገፋቸው ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት ለመጠበቅ ረድቷቸዋል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ፣ ንጉሥ ናቡከደነጾር አንድን የወርቅ ምስል እንዲያመልኩ ባዘዛቸው ወቅት እምነታቸው ተፈትኖ ነበር። ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ለንጉሡ “የአንተን አማልክት እንደማናገለግልና ላቆምከው የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ እወቅ” በማለት ምስሉን ለማምለክ ፈቃደኞች አለመሆናቸውን ገልጸዋል። እነዚህ ሦስት ጓደኛሞች እምነታቸው በተፈተነበት ወቅት ለአምላካቸው ታማኝ ሆነዋል።—ዳንኤል 1:1-17፤ 3:12, 16-28

11. ጳውሎስና ጢሞቴዎስ ጥሩ ጓደኛሞች እንዲሆኑ የረዳቸው ምንድን ነው?

11 ሐዋርያው ጳውሎስ ከጢሞቴዎስ ጋር በተገናኘበት ወቅት ወጣቱ ጢሞቴዎስ ይሖዋን እንደሚወድና ለጉባኤው ከልቡ እንደሚያስብ አስተውሎ ነበር። በመሆኑም ጢሞቴዎስ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ወንድሞችንና እህቶችን እንዲረዳ ጳውሎስ አሠልጥኖታል። (የሐዋርያት ሥራ 16:1-8፤ 17:10-14) ጢሞቴዎስ በትጋት ይሠራ ስለነበር ጳውሎስ “ምሥራቹን በማስፋፋቱ ሥራ ከእኔ ጋር እንደ ባሪያ [አገልግሏል]” በማለት ተናግሯል። ጢሞቴዎስ ለወንድሞችና ለእህቶች ‘ከልቡ እንደሚጨነቅ’ ጳውሎስ ያውቅ ነበር። ጳውሎስና ጢሞቴዎስ አብረው ይሖዋን በትጋት ማገልገላቸው ጥሩ ጓደኛሞች እንዲሆኑ ረድቷቸዋል።—ፊልጵስዩስ 2:20-22፤ 1 ቆሮንቶስ 4:17

ጓደኛ መምረጥ የምንችለው እንዴት ነው?

12, 13. (ሀ) በጉባኤ ውስጥም እንኳ ጓደኞቻችንን በጥንቃቄ መምረጥ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 15:33 ላይ የሚገኘውን ምክር የሰጠው ለምንድን ነው?

12 በጉባኤ ውስጥ ካሉ ወንድሞችና እህቶች ብዙ ትምህርት መቅሰም እንዲሁም ታማኝ ሆነን ለመቀጠል እርስ በርስ መበረታታት እንችላለን። (ሮም 1:11, 12ን አንብብ።) ይሁን እንጂ በጉባኤ ውስጥም እንኳ የቅርብ ጓደኞቻችን የሚሆኑትን ሰዎች በጥንቃቄ መምረጥ አለብን። በጉባኤ ውስጥ የተለያየ ባሕልና አስተዳደግ ያላቸው ወንድሞችና እህቶች አሉ። አንዳንዶቹ አዲስ ክርስቲያኖች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን ሲያገለግሉ ቆይተዋል። አንድ ፍሬ ለመብሰል ጊዜ እንደሚወስድበት ሁሉ አንድ ሰው ከይሖዋ ጋር ያለው ዝምድና እንዲጠናከርም ጊዜ ያስፈልገዋል። በመሆኑም አንዳችን ለሌላው ትዕግሥትና ፍቅር ማሳየት እንዲሁም ምንጊዜም ጓደኞቻችንን በጥበብ መምረጥ ይኖርብናል።—ሮም 14:1፤ 15:1፤ ዕብራውያን 5:12 እስከ 6:3

13 አንዳንድ ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ችግር ይፈጠር ይሆናል፤ በዚህ ወቅት ለየት ያለ ጥንቃቄ ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል። አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት መጽሐፍ ቅዱስ የሚከለክለውን ነገር እያደረጉ ይሆናል። ወይም ደግሞ አንድ ሰው ጉባኤውን የሚጎዳ ዝንባሌ ሊያሳይ፣ ለምሳሌ ማጉረምረም ሊጀምር ይችላል። ይህ መሆኑ አያስገርመንም፤ ምክንያቱም በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው ጉባኤ ውስጥም እንኳ ችግሮች ያጋጠሙበት ጊዜ ነበር። እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ በወቅቱ የነበሩ ክርስቲያኖችን “አትታለሉ። መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል” በማለት መክሯቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:12, 33) በተጨማሪም ጳውሎስ፣ የቅርብ ወዳጆቹን በጥበብ እንዲመርጥ ጢሞቴዎስን አሳስቦታል። በዛሬው ጊዜም ቢሆን ጓደኞቻችንን በጥበብ መምረጥ ያስፈልገናል።2 ጢሞቴዎስ 2:20-22ን አንብብ።

14. የጓደኛ ምርጫችን ከይሖዋ ጋር ባለን ወዳጅነት ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?

14 ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት እጅግ ውድ ነገር ነው። ይህ ወዳጅነታችን እንዳይበላሽ ልንጠነቀቅ ይገባል። በመሆኑም እምነታችን እንዲዳከምና ከአምላክ ጋር ያለን ወዳጅነት እንዲበላሽ ሊያደርግ ከሚችል ሰው ጋር የቅርብ ወዳጅነት አንመሠርትም። ስፖንጅን ቆሻሻ ውኃ ውስጥ ከነከርን በኋላ ስንጨምቀው ንጹሕ ውኃ እናገኛለን ብለን እንደማንጠብቅ የታወቀ ነው፤ በተመሳሳይም መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች ጓደኛ ከሆንን ትክክል የሆነውን ማድረግ ቀላል ይሆንልናል ብለን መጠበቅ የለብንም። የቅርብ ጓደኞቻችንን በጥንቃቄ መምረጥ ይኖርብናል።—1 ቆሮንቶስ 5:6፤ 2 ተሰሎንቄ 3:6, 7, 14

ይሖዋን የሚወዱ ጥሩ ጓደኞችን ማግኘት ትችላለህ

15. በጉባኤ ውስጥ ጥሩ ጓደኞች ለማግኘት ምን ማድረግ ትችላለህ?

15 ይሖዋን ከልባቸው የሚወዱ ክርስቲያኖችን በጉባኤ ውስጥ ታገኛለህ። እነዚህን ሰዎች የቅርብ ጓደኞችህ ማድረግ ትችላለህ። (መዝሙር 133:1) ጓደኞችህ መሆን የሚችሉት፣ እኩዮችህ ወይም ከአንተ ጋር ተመሳሳይ አስተዳደግ ያላቸው ሰዎች ብቻ እንደሆኑ አድርገህ አታስብ። ዮናታን ከዳዊት በዕድሜ በጣም እንደሚበልጥ አስታውስ፤ ሩትም ብትሆን ከናኦሚ በጣም ታንስ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱ” እንዲሁም “ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ” በማለት ይመክረናል፤ እነዚህን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ እንፈልጋለን። (2 ቆሮንቶስ 6:13፤ 1 ጴጥሮስ 2:17ን አንብብ።) ይሖዋን ይበልጥ እየመሰልክ በሄድክ መጠን ሌሎችም የአንተ ጓደኛ ለመሆን ይበልጥ ይነሳሳሉ።

ችግሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ

16, 17. በጉባኤ ውስጥ አንድ ሰው ቢያስቀይመን ምን ማድረግ የለብንም?

16 የየትኛውም ቤተሰብ አባላት ባሕርይና አመለካከት እንዲሁም ነገሮችን የሚያከናውኑበት መንገድ የተለያየ እንደሆነ ግልጽ ነው። በጉባኤ ውስጥም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እንዲህ ዓይነት ልዩነት መኖሩ ሕይወት አስደሳች እንዲሆን ያደርጋል፤ ደግሞም አንዳችን ከሌላው ብዙ ነገር መማር እንችላለን። ይሁን እንጂ ልዩነቶቻችን፣ አንዳንድ ጊዜ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር መግባባት አስቸጋሪ እንዲሆንብን ወይም በእነሱ እንድንበሳጭ ሊያደርጉን ይችላሉ። አልፎ አልፎ ቅር ልንሰኝ ወይም ስሜታችን ሊጎዳ ይችላል። (ምሳሌ 12:18) ታዲያ እንዲህ ያሉት ችግሮች ተስፋ እንድንቆርጥ ወይም ከጉባኤው እንድንርቅ ሊያደርጉን ይገባል?

17 በጭራሽ። አንድ ሰው ቢያስቀይመን እንኳ ከጉባኤው መራቅ የለብንም። ቅር ያሰኘን ይሖዋ አይደለም። ይሖዋ ሕይወታችንንም ሆነ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ ሰጥቶናል። በመሆኑም ልንወደውና ታማኝ ልንሆንለት ይገባል። (ራእይ 4:11) ጉባኤው እምነታችን ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን የሚረዳን ከይሖዋ ያገኘነው ስጦታ ነው። (ዕብራውያን 13:17) አንድ ሰው ስላስቀየመን ብቻ ከጉባኤ አንቀርም፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረግ ለይሖዋ ስጦታ አክብሮት አለማሳየት ይሆናል።መዝሙር 119:165ን አንብብ።

18. (ሀ) ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ተስማምተን ለመኖር የሚረዳን ምንድን ነው? (ለ) ሌሎችን ይቅር ማለት ያለብን ለምንድን ነው?

18 ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ስለምንወዳቸው ከእነሱ ጋር ተስማምተን መኖር እንፈልጋለን። ይሖዋ ከማናችንም ፍጽምናን አይጠብቅም፤ እኛም ብንሆን ከሌሎች ፍጽምናን መጠበቅ የለብንም። (ምሳሌ 17:9፤ 1 ጴጥሮስ 4:8) ሁላችንም ስህተት እንሠራለን፤ ሆኖም ፍቅር ‘በነፃ ይቅር መባባላችንን እንድንቀጥል’ ይረዳናል። (ቆላስይስ 3:13) ፍቅር ካለን ትንሿን አለመግባባት እንደ ትልቅ ችግር አድርገን አናይም። እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው ሲያስቀይመን ጉዳዩን መርሳት ቀላል ላይሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን በግለሰቡ እንበሳጭ ብሎም ቂም ለመያዝ እንፈተን ይሆናል። ይህን ማድረግ ግን ደስታችንን እንድናጣና እንድንመረር ከማድረግ ውጭ የሚጠቅመን ነገር የለም። በሌላ በኩል ግን ያስቀየመንን ግለሰብ ይቅር ካልነው የአእምሮ ሰላም እናገኛለን፤ በጉባኤው ውስጥ አንድነት እንዲኖር አስተዋጽኦ እናበረክታለን፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ወዳጅነት ይኖረናል።—ማቴዎስ 6:14, 15፤ ሉቃስ 17:3, 4፤ ሮም 14:19

አንድ ሰው ሲወገድ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

19. በጉባኤ ውስጥ ከሚገኝ ግለሰብ ጋር ያለንን ግንኙነት ማቋረጥ የሚኖርብን መቼ ነው?

19 ፍቅር ባለበት ቤተሰብ ውስጥ እያንዳንዱ አባል ሌላውን ለማስደሰት ጥረት ያደርጋል። ይሁን እንጂ፣ አንዱ የቤተሰብ አባል ዓመፀ እንበል። ሌሎቹ የቤተሰቡ አባላት ሊረዱት በተደጋጋሚ ቢሞክሩም እሱ ግን አካሄዱን ለማስተካከል ፈቃደኛ አልሆነም። ይህ ግለሰብ ቤቱን ለቅቆ ለመውጣት ሊወስን ይችላል፤ ወይም ደግሞ የቤተሰቡ ራስ ዓመፀኛው ልጅ ከቤት እንዲወጣ ለማድረግ ይገደድ ይሆናል። በጉባኤ ውስጥም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚያጋጥምበት ጊዜ አለ። አንድ ሰው ይሖዋን የሚያሳዝንና ጉባኤውን የሚጎዳ አካሄድ ለመከተል ሊመርጥ ይችላል። የሚደረግለትን እርዳታ አይቀበል እንዲሁም የጉባኤው አባል መሆን እንደማይፈልግ በተግባሩ ያሳይ ይሆናል። ይህ ግለሰብ ራሱን ከጉባኤው ሊያገልል ይችላል፤ አሊያም ደግሞ ከጉባኤ መወገድ ይኖርበት ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ካለው ሰው ጋር ‘መግጠማችንን መተው’ እንዳለብን በግልጽ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 5:11-13ን አንብብ፤ 2 ዮሐንስ 9-11) ግለሰቡ ጓደኛችን ወይም የቤተሰባችን አባል ከሆነ ይህን ማድረግ በጣም ሊከብደን እንደሚችል የታወቀ ነው። ሆኖም እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲፈጠር፣ ከማንም ይበልጥ ታማኝ መሆን ያለብን ለይሖዋ ነው።—ተጨማሪ ሐሳብ 8⁠ን ተመልከት።

20, 21. (ሀ) ውገዳ፣ የይሖዋን ፍቅር የሚያሳይ ዝግጅት ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ጓደኞቻችንን በጥበብ መምረጣችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

20 ውገዳ፣ የይሖዋን ፍቅር የሚያሳይ ዝግጅት ነው። ይህ ዝግጅት፣ ለይሖዋ መሥፈርቶች አክብሮት የሌላቸው ሰዎች ጉባኤውን እንዳይበክሉ ይከላከላል። (1 ቆሮንቶስ 5:7፤ ዕብራውያን 12:15, 16) ይህን ዝግጅት በመደገፍ፣ ቅዱስ ለሆነው የይሖዋ ስምና ላቅ ላሉት መሥፈርቶቹ እንዲሁም ለይሖዋ ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። (1 ጴጥሮስ 1:15, 16) በተጨማሪም የውገዳ ዝግጅት፣ ይሖዋ ከጉባኤ ለተወገደው ግለሰብ ፍቅር እንዳለው ያሳያል። እንዲህ ዓይነቱ ጠንካራ ተግሣጽ፣ ግለሰቡ ድርጊቱ ስህተት መሆኑን እንዲገነዘብና ለውጥ ለማድረግ እንዲነሳሳ ሊረዳው ይችላል። ከጉባኤ ተወግደው የነበሩ በርካታ ሰዎች ከጊዜ በኋላ ወደ ይሖዋ የተመለሱ ሲሆን ጉባኤውም በደስታ ተቀብሏቸዋል።—ዕብራውያን 12:11

21 ጓደኞቻችን ጥሩ ወይም መጥፎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩብን ጥያቄ የለውም። ስለዚህ ጓደኞቻችንን በጥንቃቄ መምረጥ ይኖርብናል። ይሖዋ የሚወዳቸውን ሰዎች የምንወድ ከሆነ ለዘላለም እሱን በታማኝነት እንድናገለግል የሚረዱን ጓደኞች ይኖሩናል።