በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 6

ጥሩ መዝናኛ መምረጥ የምንችለው እንዴት ነው?

ጥሩ መዝናኛ መምረጥ የምንችለው እንዴት ነው?

“ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ።”—1 ቆሮንቶስ 10:31

1, 2. መዝናኛ ስንመርጥ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

 አንድን ፍሬ ለመብላት ስትዘጋጅ ፍሬው በአንድ ጎኑ እንደተበላሸ ተመለከትክ እንበል። ታዲያ ምን ታደርጋለህ? ፍሬውን ዝም ብለህ ትበላዋለህ? እንዳለ ትጥለዋለህ? ወይስ የተበላሸውን ቆርጠህ በመጣል ጤነኛውን ክፍል ትበላለህ?

2 መዝናኛ እንዲህ ካለው ፍሬ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አንዳንዱ መዝናኛ አስደሳች ሊሆን ይችላል፤ በዓለም ላይ ያለው አብዛኛው መዝናኛ ግን የሥነ ምግባር ብልግና፣ ዓመፅ ወይም አጋንንታዊ ድርጊት የሚንጸባረቅበት በመሆኑ ግማሽ ወገኑ እንደተበላሸ ፍሬ ሊቆጠር ይችላል። ታዲያ መዝናኛ የምትመርጠው እንዴት ነው? “የፈለግኩትን መዝናኛ መምረጥ መብቴ ነው” የሚል አመለካከት አለህ? “ሁሉም ዓይነት መዝናኛ መጥፎ ነው” ብለህ ታስባለህ? ወይስ መጥፎ ከሆነ መዝናኛ በመራቅ ጥሩ የሆኑ መዝናኛዎችን በጥንቃቄ ትመርጣለህ?

3. መዝናኛ ስንመርጥ ልናስብበት የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

3 ሁላችንም መዝናኛ እንደሚያስፈልገን የታወቀ ነው፤ በዚህ ረገድ ጥሩ ምርጫ ማድረግም እንፈልጋለን። በመሆኑም የመዝናኛ ምርጫችን ለይሖዋ የምናቀርበውን አምልኮ እንዴት እንደሚነካው ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል።

“ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ”

4. መዝናኛ ስንመርጥ የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ሊረዳን ይችላል?

4 ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን ሕይወታችንን እሱን ለማገልገል እንደምንጠቀምበት ቃል ገብተናል። (መክብብ 5:4ን አንብብ።) በሌላ አባባል “ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር” ለማድረግ ተስማምተናል። (1 ቆሮንቶስ 10:31) በመሆኑም በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ወይም በአገልግሎት ስንካፈል ብቻ ሳይሆን በምንዝናናበት ጊዜም ጭምር ራሳችንን ለአምላክ የወሰንን አገልጋዮቹ መሆናችንን ማስታወስ ይኖርብናል።

5. ለይሖዋ ምን ዓይነት አምልኮ ልናቀርብ ይገባል?

5 በሕይወታችን ውስጥ የምናደርገው እያንዳንዱ ነገር ለይሖዋ ከምናቀርበው አምልኮ ጋር ግንኙነት አለው። ጳውሎስ “ሰውነታችሁን ሕያው፣ ቅዱስና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አድርጋችሁ [አቅርቡ]” በማለት ይህን ነጥብ አጉልቷል። (ሮም 12:1) ኢየሱስ ደግሞ “አንተም አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ” ብሏል። (ማርቆስ 12:30) ምንጊዜም ቢሆን ለይሖዋ ምርጣችንን መስጠት እንፈልጋለን። በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ሕዝቡ ለይሖዋ መሥዋዕት ሲያቀርቡ ጤናማ የሆነ እንስሳ መስጠት ይጠበቅባቸው ነበር። መሥዋዕቱ ጉድለት ካለው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም። (ዘሌዋውያን 22:18-20) እኛም ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ተቀባይነት እንዲያጣ ሊያደርግ የሚችል ነገር አለ። ይህ ሲባል ምን ማለት ነው?

6, 7. የምንመርጠው መዝናኛ ለይሖዋ ከምናቀርበው አምልኮ ጋር ምን ግንኙነት አለው?

6 ይሖዋ “እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ብሎናል። (1 ጴጥሮስ 1:14-16፤ 2 ጴጥሮስ 3:11) ይሖዋ ለእሱ የምናቀርበውን አምልኮ የሚቀበለው አምልኳችን ቅዱስ ወይም ንጹሕ ከሆነ ብቻ ነው። (ዘዳግም 15:21) እንደ ሥነ ምግባር ብልግና፣ ዓመፅ ወይም አጋንንታዊ ድርጊቶች ያሉ ይሖዋ የሚጠላቸው ነገሮችን የምንፈጽም ከሆነ አምልኳችን ንጹሕ እንደማይሆን የታወቀ ነው። (ሮም 6:12-14፤ 8:13) እንዲህ ያሉ ነገሮች በሚንጸባረቁበት መዝናኛ የምንካፈል ከሆነም ይሖዋ ያዝንብናል። እንደዚህ ባለው መዝናኛ መካፈል አምልኳችን ንጹሕ እንዳይሆንና በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዳያገኝ ያደርጋል፤ ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድናም ያበላሽብናል።

7 ታዲያ ጥሩ መዝናኛ መምረጥ የምንችለው እንዴት ነው? ተቀባይነት ያለውንና የሌለውን መዝናኛ ለይተን ለማወቅ የሚረዱን የትኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው?

ክፉ የሆነውን ጥሉ

8, 9. ከምን ዓይነት መዝናኛ መራቅ ይኖርብናል? ለምንስ?

8 በዛሬው ጊዜ የተለያዩ ዓይነት መዝናኛዎች አሉ። አንዳንዱ መዝናኛ በክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት አለው፤ አብዛኛው ግን ለክርስቲያኖች የማይሆን ነው። እስቲ በመጀመሪያ፣ ልንርቃቸው የሚገቡ መዝናኛዎች የትኞቹ እንደሆኑ እንመልከት።

9 የበርካታ ፊልሞች፣ ድረ ገጾች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ የቪዲዮ ጨዋታዎች እንዲሁም ዘፈኖች ይዘት ከሥነ ምግባር ብልግና፣ ከዓመፅና ከአጋንንታዊ ድርጊት ጋር የተያያዘ ነው። ብዙውን ጊዜ እነዚህ መዝናኛዎች መጥፎ ነገሮችን የሚያቀርቡት ምንም ጉዳት እንደሌላቸው በሚያስመስል እንዲያውም አስቂኝ በሆነ መልኩ ነው። ክርስቲያኖች ግን ንጹሕ ከሆኑት የይሖዋ መሥፈርቶች ጋር ከሚጋጩ መዝናኛዎች ለመራቅ የቻሉትን ያህል ጥረት ያደርጋሉ። (የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) እንዲህ ካሉ መዝናኛዎች ስንርቅ ክፉ የሆነውን እንደምንጠላ እናሳያለን፤ ይህን ማድረጋችን ይሖዋን ያስደስተዋል።—መዝሙር 34:14፤ ሮም 12:9

10. መጥፎ መዝናኛ መምረጥ ምን ሊያስከትል ይችላል?

10 ሆኖም አንዳንድ ሰዎች ከዓመፅ፣ ከሥነ ምግባር ብልግና ወይም ከአጋንንታዊ ድርጊቶች ጋር የተያያዘ መዝናኛ ምንም ጉዳት እንደሌለው ይሰማቸዋል። ‘ምን ችግር አለው? እኔ እኮ በምንም ዓይነት እነዚህን ነገሮች አልፈጽምም’ ብለው ያስባሉ። እንደዚህ ብለን ካሰብን ራሳችንን እያታለልን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ልብ ከምንም ነገር በላይ ከዳተኛ ነው፤ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ አይመለስም” ይላል። (ኤርምያስ 17:9) ይሖዋ በማይወዳቸው ነገሮች የምንዝናና ከሆነ እነዚህን ድርጊቶች እንጠላቸዋለን ማለት እንዴት እንችላለን? እንዲህ ያሉ መዝናኛዎችን ባዘወተርን መጠን ድርጊቶቹ ስህተት እንዳልሆኑ ማሰብ እንጀምራለን። ውሎ አድሮም ሕሊናችን በትክክል መሥራቱን ያቆማል፤ ይባስ ብሎም መጥፎ ውሳኔ ልናደርግ ስንል ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ይተዋል።—መዝሙር 119:70፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:1, 2

11. ገላትያ 6:7 በመዝናኛ ምርጫችን ረገድ የሚረዳን እንዴት ነው?

11 የአምላክ ቃል “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል” በማለት ይናገራል። (ገላትያ 6:7) መጥፎ ነገሮችን በሚያንጸባርቁ መዝናኛዎች የምንዝናና ከሆነ ውሎ አድሮ እነዚህን ድርጊቶች ልንፈጽም እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሥነ ምግባር የጎደለው መዝናኛ ያሳደረባቸው ተጽዕኖ የሥነ ምግባር ብልግና ወደመፈጸም መርቷቸዋል። በሌላ በኩል ግን ይሖዋ ጥሩ መዝናኛ ለመምረጥ የሚረዱ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሰጥቶናል።

ውሳኔ ስታደርጉ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተመሩ

12. በመዝናኛ ምርጫ ረገድ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ምን ይረዳናል?

12 አንዳንድ መዝናኛዎች በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌላቸው ምንም ጥያቄ የለውም፤ በመሆኑም እንደዚህ ካሉት መዝናኛዎች መራቅ እንዳለብን እናውቃለን። ይሁንና አንድ መዝናኛ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን ባንችልስ? ይሖዋ የትኞቹን ነገሮች መመልከት፣ ማዳመጥ ወይም ማንበብ እንደምንችልና እንደማንችል የሚገልጽ ዝርዝር መመሪያ አልሰጠንም። ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናችንን ተጠቅመን ውሳኔ እንድናደርግ ይፈልጋል። (ገላትያ 6:5ን አንብብ።) ይሖዋ የእሱን አመለካከት ለማወቅ የሚያስችሉ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሰጥቶናል። እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሕሊናችንን ለማሠልጠንና “የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ” ለማስተዋል ይረዱናል። ይህም አምላክን የሚያስደስቱ ምርጫዎችን ለማድረግ ያስችለናል።—ኤፌሶን 5:17

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥሩ መዝናኛ ለመምረጥ ይረዱናል

13. ክርስቲያኖች በመዝናኛ ረገድ የሚያደርጉት ምርጫ የተለያየ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሆኖም ሁሉንም ክርስቲያኖች ሊያሳስባቸው የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

13 ክርስቲያኖች በመዝናኛ ረገድ የሚያደርጉት ምርጫ ብዙውን ጊዜ የተለያየ ነው። ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሁላችንም የምንወደው ነገር የተለያየ ስለሆነ ነው። ከዚህም ሌላ፣ አንድ ሰው ተቀባይነት ያለው እንደሆነ የሚያስበውን መዝናኛ ሌላው ሰው ተቀባይነት እንደሌለው አድርጎ ሊመለከተው ይችላል። ያም ቢሆን ሁሉም ክርስቲያኖች ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራት አለባቸው። (ፊልጵስዩስ 1:9) እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መዝናኛ ለመምረጥ ይረዱናል።—መዝሙር 119:11, 129፤ 1 ጴጥሮስ 2:16

14. (ሀ) በጊዜ አጠቃቀማችን ረገድ ልናስብበት የሚገባው ጉዳይ ምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ ለክርስቲያኖች ምን የሚል ምክር ሰጥቷቸዋል?

14 ልናስብበት የሚገባው ሌላው ጉዳይ ደግሞ ‘በመዝናኛ ምን ያህል ጊዜ እናሳልፋለን?’ የሚለው ነው። ይህም ለመዝናኛ ምን ያህል ቦታ እንደምንሰጥ ያሳያል። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ ሊይዝ የሚገባው ለይሖዋ የምናቀርበው አገልግሎት ነው። (ማቴዎስ 6:33ን አንብብ።) ይሁን እንጂ ሳይታወቀን በመዝናኛ ብዙ ጊዜ ልናሳልፍ እንችላለን። ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “የምትመላለሱት ጥበብ እንደጎደላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ፤ . . . ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት” ብሏቸዋል። (ኤፌሶን 5:15, 16) በመሆኑም በመዝናኛ በምናሳልፈው ጊዜ ላይ ገደብ ማበጀትና ለአምላክ የምናቀርበው አምልኮ ምንጊዜም በሕይወታችን ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ እንዲይዝ ማድረግ ይኖርብናል።—ፊልጵስዩስ 1:10

15. ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና እንዳይበላሽ ከመዝናኛ ምርጫችን ጋር በተያያዘ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

15 በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ከምናውቀው መዝናኛ መራቅ እንዳለብን አያጠራጥርም። ይሁንና በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ስለመሆኑ እርግጠኛ ያልሆንበትን መዝናኛ በተመለከተስ ምን ማድረግ ይኖርብናል? እንዲህ ካለው መዝናኛም መራቅ ያስፈልገናል? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። በተራራ ላይ ባለ መንገድ ላይ እየተጓዝክ ነው እንበል፤ መንገዱ በአንደኛው ወገን ገደላማ ነው። ታዲያ በገደሉ በኩል ወዳለው የመንገዱ ጠርዝ ተጠግተህ ዳር ዳሩን ለመሄድ ትሞክራለህ? በፍጹም እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው። ሕይወትህን የምትወድ ከሆነ በተቻለ መጠን ከአደጋ ለመራቅ ትጥራለህ። ከመዝናኛ ምርጫችን ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። የአምላክ ቃል “እግርህን ከክፉ ነገር መልስ” የሚል ምክር ይሰጣል። (ምሳሌ 4:25-27) እንግዲያው መጥፎ እንደሆነ ከምናውቀው መዝናኛ ብቻ ሳይሆን ተገቢ መሆኑን ከምንጠራጠረውና ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያበላሽብን እንደሚችል ከምናስበው መዝናኛም መራቅ ይኖርብናል።

የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ማዳበር

16. (ሀ) ይሖዋ የሚጠላቸው አንዳንድ ነገሮች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች እንደምንጠላ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

16 መዝሙራዊው “እናንተ ይሖዋን የምትወዱ፣ ክፉ የሆነውን ነገር ጥሉ” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 97:10) መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን አስተሳሰብና ስሜት ለማወቅ ይረዳናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ የምትማረው ነገር የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ለማዳበር እንዴት እንደሚረዳህ ቆም ብለህ አስብ። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ከሚጠላቸው ነገሮች መካከል “ውሸታም ምላስ፣ ንጹሕ ደም የሚያፈሱ እጆች፣ ክፉ ሐሳብ የሚያውጠነጥን ልብና ወደ ክፋት በፍጥነት የሚሮጡ እግሮች” እንደሚገኙበት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ምሳሌ 6:16-19) በተጨማሪም “የፆታ ብልግና፣ . . . ጣዖት አምልኮ፣ መናፍስታዊ ድርጊት፣ . . . ቅናት፣ በቁጣ መገንፈል፣ . . . ምቀኝነት፣ ሰካራምነት፣ መረን የለቀቀ ፈንጠዝያና እነዚህን የመሳሰሉ” ነገሮች መጥፎ እንደሆኑ ተምረናል። (ገላትያ 5:19-21) እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በመዝናኛ ምርጫህ ረገድ የሚረዱህ እንዴት እንደሆነ አስተዋልክ? ብቻችንን በምንሆንበት ጊዜም ሆነ ከሌሎች ጋር ስንሆን በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች የይሖዋን መሥፈርቶች መከተል እንፈልጋለን። (2 ቆሮንቶስ 3:18) እንዲያውም ብቻችንን ስንሆን የምናደርገው ምርጫ ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆንን ያሳያል።—መዝሙር 11:4፤ 16:8

17. መዝናኛ ስትመርጥ ራስህን የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ ይኖርብሃል?

17 እንግዲያው መዝናኛ ስትመርጥ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ምርጫዬ ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና የሚነካው እንዴት ነው? የመረጥኩት መዝናኛ ሕሊናዬ እንዲወቅሰኝ ያደርጋል?’ መዝናኛ በምንመርጥበት ጊዜ ሊረዱን የሚችሉ ተጨማሪ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እስቲ እንመልከት።

18, 19. (ሀ) ጳውሎስ ለክርስቲያኖች ምን ምክር ሰጥቷል? (ለ) መዝናኛ ለመምረጥ የትኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይረዱናል?

18 መዝናኛ ስንመርጥ፣ ወደ አእምሯችን የምናስገባውን ነገር እየመረጥን እንደሆነ እናስታውስ። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እውነት የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ቁም ነገር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ በመልካም የሚነሳውን ነገር ሁሉ፣ በጎ የሆነውን ሁሉና ምስጋና የሚገባውን ነገር ሁሉ ማሰባችሁን አታቋርጡ።” (ፊልጵስዩስ 4:8) እንዲህ ባሉ ጥሩ ነገሮች አእምሯችንን ስንሞላ “ይሖዋ ሆይ፣ የአፌ ቃልና በልቤ የማሰላስለው ነገር አንተን ደስ የሚያሰኝ ይሁን” ማለት እንችላለን።—መዝሙር 19:14

19 ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘አእምሮዬን እየሞላሁ ያለሁት በምንድን ነው? አንድን ፊልም ወይም ፕሮግራም ከተመለከትኩ በኋላ ወደ አእምሮዬ የሚመጣው ደስ የሚል ሐሳብ ነው? ውስጣዊ ሰላምና ንጹሕ ሕሊና ይኖረኛል? (ኤፌሶን 5:5፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:5, 19) ወደ ይሖዋ ለመጸለይ ነፃነት ይሰማኛል? ወይስ እሸማቀቃለሁ? የመረጥኩት መዝናኛ ዓመፅ የሚንጸባረቅበት ወይም ሥነ ምግባር የጎደለው ሐሳብ ወደ አእምሮዬ እንዲመጣ ያደርጋል? (ማቴዎስ 12:33፤ ማርቆስ 7:20-23) የምመርጠው መዝናኛ “ይህ ሥርዓት እንዲቀርጸኝ” ያደርጋል?’ (ሮም 12:2) ለእነዚህ ጥያቄዎች በሐቀኝነት መልስ መስጠታችን፣ ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ምን ማድረግ እንዳለብን ለማስተዋል ይረዳናል። እኛም እንደ መዝሙራዊው “ከንቱ ነገር እንዳያዩ ዓይኖቼን መልስ” ብለን መጸለይ እንፈልጋለን። *መዝሙር 119:37

የምናደርገው ውሳኔ ሌሎችንም ይነካል

20, 21. መዝናኛ ስንመርጥ ስለ ሌሎች ስሜት ማሰብ ያለብን ለምንድን ነው?

20 ልናስብበት የሚገባው ሌላው አስፈላጊ መሠረታዊ ሥርዓት ደግሞ የሚከተለው ነው፦ “ሁሉም ነገር ተፈቅዷል፤ ሆኖም ሁሉም ነገር ያንጻል ማለት አይደለም። እያንዳንዱ ሰው ምንጊዜም የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ።” (1 ቆሮንቶስ 10:23, 24) አንድን ነገር የማድረግ ነፃነት ስላለን ብቻ ልናደርገው ይገባል ማለት አይደለም። ውሳኔያችን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እንዴት እንደሚነካ ቆም ብለን ልናስብ ይገባል።

21 የሁሉም ሰው ሕሊና አንድ ዓይነት አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ የአንተ ሕሊና አንድን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለመመልከት ይፈቅድልህ ይሆናል። አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ግን ያንን ፕሮግራም ለማየት ሕሊናቸው አልፈቀደላቸውም። ይህን ብታውቅ ምን ታደርጋለህ? ፕሮግራሙን የማየት መብት ቢኖርህም ይህን ላለማድረግ ልትወስን ትችላለህ። ለምን? ‘ወንድሞችህን መበደል’ ይባስ ብሎም “በክርስቶስ ላይ ኃጢአት” መሥራት ስለማትፈልግ ነው። (1 ቆሮንቶስ 8:12) የእምነት ባልንጀራችንን የሚያሰናክል አንዳች ነገር ማድረግ አንፈልግም።—ሮም 14:1፤ 15:1፤ 1 ቆሮንቶስ 10:32

22. ሌሎች ክርስቲያኖች ከሚያደርጉት የመዝናኛ ምርጫ ጋር በተያያዘ ምክንያታዊ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

22 በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ወንድም ተቀባይነት እንዳለው የሚሰማውን ፊልም፣ መጽሐፍ ወይም ሌላ ዓይነት መዝናኛ የአንተ ሕሊና ባይቀበለውስ? ወንድምህን ስለምትወደውና ስለምታከብረው፣ ከአንተ ጋር ተመሳሳይ ምርጫ እንዲያደርግ አትጫነውም። የተለያዩ ሰዎች መኪና የሚያሽከረክሩበት ፍጥነት የተለያየ እንደሆነ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ሁሉም ጥሩ ሾፌሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መልኩ፣ አንተም ሆንክ የእምነት ባልንጀራህ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ብትከተሉም ተቀባይነት ያለውን መዝናኛ በተመለከተ ያላችሁ አመለካከት በመጠኑ ሊለያይ ይችላል።—መክብብ 7:16፤ ፊልጵስዩስ 4:5

23. ጥሩ መዝናኛ ለመምረጥ ምን ይረዳናል?

23 ታዲያ ጥሩ መዝናኛ ለመምረጥ ምን ይረዳናል? በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሠለጠነ ሕሊናችንን የምንጠቀም እንዲሁም ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ከልብ የምናስብ ከሆነ ጥሩ መዝናኛ መምረጥ እንችላለን። “ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር” በማድረጋችንም እንደሰታለን።

^ መዝናኛ ለመምረጥ የሚረዱ ተጨማሪ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ምሳሌ 3:31፤ 13:20፤ ኤፌሶን 5:3, 4 እና ቆላስይስ 3:5, 8, 20 ላይ እናገኛለን።