በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምድር አምላክ በሚሰጠው እውቀት ስትሞላ

ምድር አምላክ በሚሰጠው እውቀት ስትሞላ

ምዕራፍ 19

ምድር አምላክ በሚሰጠው እውቀት ስትሞላ

1, 2. የይሖዋ ፍጥረት ብልሽት የደረሰበት እንዴት ነው?

አንድ ታላቅ ሠዓሊ በጣም አስደናቂ የሆነ ሥዕል ሠርቶ ጨርሷል እንበል። ሥራውን እጅግ በጣም ግሩም ሥዕል እንደሆነ አድርጎ ይመለከተዋል! ይሁን እንጂ አንድ ምቀኛ ሰው በሌሊት ይሄድና ሥዕሉን በቀለም ለቅልቆ ውበቱን ያጠፋበታል። ሠዓሊው ሥራው እንደተበላሸ ሲመለከት እንዴት ያለ ሐዘን እንደሚሰማው ገምት። ወንጀለኛው ሰው ተይዞ እንዲታሠርለት ምን ያህል ይመኝ ይሆን! የፈጠራ ሥራው እንደገና ታድሶ ወደ ቀድሞ ውበቱ እንዲመለስ ምን ያህል እንደሚጓጓ ልትገምት ትችላለህ።

2 ይሖዋ አምላክም ከዚህ ሠዓሊ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ዕጹብ ድንቅ የሆነች ምድር አዘጋጅቶ የሰው ልጆችን በላይዋ ላይ አሰፈረ። አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ ምድራዊ ሥራው በሙሉ “መልካም” እንደሆነ ተናገረ። (ዘፍጥረት 1:​31) አዳምና ሔዋን የአምላክ ልጆች ነበሩ፤ በጣም ይወዳቸውም ነበር። የወደፊት ኑሯቸውም ደስታ የሞላበት እንዲሆን ፍላጎቱ ነበር። እርግጥ ሰይጣን አሳመፃቸው፤ ቢሆንም አስደናቂ የሆነችው የአምላክ የፍጥረት ሥራ ወደፊት ልትጠገን እንደማትችል ሆና አልተበላሸችም።​— ዘፍጥረት 3:​23, 24፤ 6:​11, 12

3. “እውነተኛው ሕይወት” ምንድን ነው?

3 አምላክ ሁኔታውን በሙሉ ለማስተካከል ወስኗል። እንደ መጀመሪያው ዓላማው ስንኖር ለማየት በጣም ይፈልጋል። በመከራ የተሞላው አጭር ሕይወታችን “እውነተኛው ሕይወት” አይደለም፤ ምክንያቱም ይሖዋ ወደፊት ሊሰጠን ካሰበው ሕይወት ጋር ሲወዳደር በጣም ዝቅ ያለ ነው። አምላክ እንድናገኝ የሚፈልገው “እውነተኛ ሕይወት” ፍጹም ሁኔታዎች የሰፈኑበት “የዘላለም ሕይወት” ነው።​— 1 ጢሞቴዎስ 6:​12, 19

4, 5. (ሀ) የገነት ተስፋ የሚፈጸምልን እንዴት ነው? (ለ) ለወደፊቱ ጊዜ ስለሚኖረን ተስፋ ማሰብ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

4 አምላክ የሚሰጠውን እውቀት ማግኘታችን በይሖዋ ፊት ኃላፊነት ያመጣብናል። (ያዕቆብ 4:​17) ይሁን እንጂ ይህን እውቀት ሥራ ላይ አውለህ የዘላለም ሕይወትን ተስፋ ብትጨብጥ ምን ዓይነት በረከት እንደምታገኝ አስብ። በቅርቡ በሚቋቋመው ገነት የምናገኘው ሕይወት ምን ዓይነት መልክ እንደሚኖረው ይሖዋ አምላክ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ውብ የሆነ መግለጫ ሰጥቶናል። እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ሕዝብ እንደመሆናችን መጠን አምላክን የምናገለግለው ሽልማት ለማግኘት ብቻ ብለን አይደለም። አምላክን የምናገለግለው ስለምንወደው ነው። (ማርቆስ 12:​29, 30) ከዚህም በላይ የዘላለም ሕይወት አምላክን በማገልገላችን የሚከፈለን የድካም ዋጋ አይደለም። የዘላለም ሕይወት የአምላክ ስጦታ ነው። (ሮሜ 6:​23) ስለዚሁ ሕይወት ማሰላሰላችን ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም የገነት ተስፋ ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ያስታውሰናል። ‘በቅንነት ለሚፈልጉት ዋጋቸውን የሚከፍል’ አምላክ መሆኑን ያሳስበናል። (ዕብራውያን 11:​6) በአእምሮአችንና በልባችን ውስጥ ደመቅ ብሎ የሚያበራ ተስፋ በሰይጣን ዓለም ውስጥ የሚያጋጥመንን መከራ በጽናት እንድንቋቋም ያስችለናል።​— ኤርምያስ 23:​20

5 አሁን ትኩረታችንን ወደፊት በምትቋቋመው ምድራዊት ገነት ውስጥ በምናገኘው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ላይ እናድርግ። ከአምላክ የሚገኝ እውቀት ምድርን በሚሞላበት ጊዜ ምን ዓይነት ሁኔታ ይኖራል?

ከአርማጌዶን በኋላ ምድር ገነት ትሆናለች

6. አርማጌዶን ምንድን ነው? ለሰው ልጆችስ ምን ትርጉም ይኖረዋል?

6 ቀደም ሲል እንደተገለጸው ይሖዋ አምላክ ይህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት በቅርቡ ያጠፋል። ዓለም መጽሐፍ ቅዱስ ሐርማጌዶን ወይም አርማጌዶን ብሎ ወደሚጠራው ሁኔታ በፍጥነት እየገሰገሰ ነው። አንዳንድ ሰዎች ይህን ቃል ሲሰሙ ወደ አእምሮአቸው የሚመጣው በብሔራት መካከል በሚደረግ ጦርነት ምክንያት የሚመጣ የኑክሌር እልቂት ሊሆን ይችላል። አርማጌዶን ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። ራእይ 16:​14–16 እንደሚያመለክተው አርማጌዶን ‘ሁሉን የሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን ነው።’ “የምድር ሁሉ ነገሥታት” ወይም ብሔራት የሚካፈሉበት ጦርነት ነው። ንጉሥ ሆኖ የተሾመው የይሖዋ አምላክ ልጅ በቅርቡ ወደዚህ ጦርነት ይዘምታል። የጦርነቱ ውጤት ምን እንደሚሆን ፈጽሞ አያጠራጥርም። የአምላክን መንግሥት የሚቃወሙና የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ክፍል የሆኑ ሁሉ ፈጽመው ይደመሰሳሉ። ከጥፋቱ በሕይወት የሚተርፉት ከይሖዋ ጎን በታማኝነት የሚቆሙ ብቻ ናቸው።​— ራእይ 7:​9, 14፤ 19:​11–21

7. ሰይጣንና አጋንንቱ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት የት ይሆናሉ? ይህስ የሰውን ልጆች የሚጠቅመው እንዴት ነው?

7 አንተ ከዚህ ታላቅ እልቂት ተርፈሃል እንበል። ታዲያ አምላክ አቋቁምላችኋለሁ ብሎ ቃል በገባልን አዲስ ዓለም ውስጥ መኖር ምን ዓይነት መልክ ይኖረው ይሆን? (2 ጴጥሮስ 3:​13) መጽሐፍ ቅዱስ ሁኔታውን ስለሚገልጽልን የግምት መልስ መስጠት አያስፈልገንም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መግለጫ ደግሞ የሚያስፈነድቅ ነው። ሰይጣንና አጋንንቱ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገዛበት የሺህ ዓመት ዘመን ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ሊያደርጉ በማይችሉበት ጥልቅ ውስጥ ታስረውና ከማንኛውም ዓይነት ሥራ ታግደው እንደሚቆዩ እናነባለን። እነዚህ ክፉና ተንኮለኛ ፍጥረታት በስውር እየተሹለኮለኩ ችግር ማነሳሳታቸውና በአምላክ ላይ እምነት የጎደለው ድርጊት እንድንፈጽም ለመገፋፋት መሞከራቸው ያበቃል። እንዴት ያለ ታላቅ ግልግል ይሆናል!​— ራእይ 20:​1–3

8, 9. በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሥቃይ፣ ሕመምና እርጅና ምን ይሆናሉ?

8 ከጊዜ በኋላ ማንኛውም ዓይነት በሽታ ይከስማል። (ኢሳይያስ 33:​24) አንካሳ የነበሩ ሰዎች ጤናማና ብርቱ እግሮች አግኝተው ቀጥ ብለው ሊቆሙ፣ ሊራመዱ፣ ሊሮጡና ሊፈነጥዙ ይችላሉ። መስማት የተሳናቸው ለበርካታ ዓመታት ያሳለፉት ድምፅ አልባ ዓለም ተወግዶላቸው በዙሪያቸው የሚኖረውን የደስታ ውካታ ያዳምጣሉ። ማየት የተሳናቸው ሰዎች አስደናቂ የሆኑ የተለያዩ ቀለማትና ቅርጾች ያሉበትን ዓለም ድንገት ሲመለከቱ በአድናቆት ይዋጣሉ። (ኢሳይያስ 35:​5, 6) የሚወዷቸውን ሰዎች ፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ሊያዩ ነው! ዓይናቸው በደስታ እንባ ስለሚሞላ ምናልባት ለትንሽ ጊዜ ብዥ ይልባቸው ይሆናል።

9 እስቲ ለአንድ አፍታ ቆም ብለህ አስብ! በዚያን ጊዜ መነጽር አያስፈልግም፤ ምርኩዝ ወይም ከዘራ አያስፈልግም፤ መድኃኒቶች አያስፈልጉም፤ የጥርስ ክሊኒኮች አያስፈልጉም፤ ሆስፒታሎች አያስፈልጉም! ከዚያ በኋላ የሰዎችን ደስታ የሚነጥቅ የስሜት ቀውስና የመንፈስ ጭንቀት አይኖርም። የልጅነት ዕድሜውን በበሽታ እየተሠቃየ የሚገፋ ሕፃን አይኖርም። እርጅና ያዳከመው ሰውነት ይታደሳል። (ኢዮብ 33:​25) ከቀን ወደ ቀን ይበልጥ ጤነኞችና ጠንካሮች እንሆናለን። ጠዋት፣ ጠዋት ደስ የሚል እንቅልፍ ጠግበን ከመኝታ እንነሳለን። ኃይላችን ታድሶ፣ ጉልበታችን ጠንክሮ፣ ሰውነታችን ቅልል ብሎን አዲሱን ቀን እንጀምራለን። አርኪ ሥራ ስንሠራ እንውላለን።

10. ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉት ምን ሥራ ይሰጣቸዋል?

10 ከአርማጌዶን በሕይወት የተረፉ ሰዎች የሚሠሯቸው የሚያስደስቱና የሚያረኩ በርካታ ሥራዎች ይኖራሉ። ምድርን ወደ ገነትነት ይለውጣሉ። የአሮጌው ዓለም ብክለት የተወው ርዝራዥ በሙሉ ተጠርጎ ይወገዳል። የተጨናነቁ መኖሪያዎችና በረሃ በነበረባቸው ቦታዎች ግሩም የሆኑ የአትክልት ቦታዎችና መናፈሻዎች ብቅ ይላሉ። ሰዎች ሁሉ ምቹና አስደሳች በሆኑ ቤቶች ይኖራሉ። (ኢሳይያስ 65:​21) ወደ ገነትነት የተለወጡት የምድር ክፍሎች እየሰፉ ሄደው ከጊዜ በኋላ አንድ ላይ ይጋጠሙና መላዋ ምድር ፈጣሪ ለኤደን ገነት አውጥቶት የነበረውን የውበት ደረጃ ትላበሳለች። የቀድሞዋን ገነት ለመመለስ በሚደረገው ሥራ መሳተፍ ምን ያህል አርኪ ይሆናል!

11. የሰው ልጅ ከምድር አካባቢና ከእንስሳት ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ይኖረ⁠ዋል?

11 ይህ ሁሉ በሚከናወንበት ጊዜ በመኖሪያ አካባቢዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መለኮታዊ መመሪያ ይሰጣል። የሰው ልጆች ከእንስሳት ጋር በሰላም ይኖራሉ። የሰው ልጅ እንስሳትን አለምክንያት መጨፍጨፉ ይቀርና ምድርን ኃላፊነት በተሞላ ሁኔታ የማስተዳደር ተግባሩን በመጀመር እንስሳትን ተንከባክቦ ይይዛቸዋል። የቤት እንስሳትን የሚያስፈራሩ አራዊት ሳይኖሩ ተኩላና በግ፣ አንበሳና ጥጃ አንድ ላይ ተሰማርተው ሲመገቡ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ትንሽ ሕፃን እንኳን የዱር አራዊትን የሚፈራበት ምክንያት አይኖርም። የአዲሱ ዓለም ጸጥታና እርጋታ ጨካኝና ጠበኛ በሆኑ ሰዎች አይረበሽም። (ኢሳይያስ 11:​6–8) ሰላም የሰፈነበት እንዴት ያለ አዲስ ዓለም ይሆናል!

የሰው ልጅ ይለወጣል

12. ኢሳይያስ 11:​9 በዛሬው ጊዜ በመፈጸም ላይ የሚገኘው እንዴት ነው? በገነትስ ውስጥ እንዴት ይፈጸማል?

12 ኢሳይያስ 11:​9 በመላው ምድር ላይ ምንም ዓይነት መጎዳዳት የማይኖርበትን ምክንያት ይነግረናል። ጥቅሱ “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች” ይላል። ይህ ጥቅስ የሚናገረው ስለ ሰዎች እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም እንስሳት ‘ይሖዋን ሊያውቁና’ በዚህ ሳቢያ የጠባይ ለውጥ ሊያደርጉ አይችሉም። የሚመሩት በደመ ነፍስ ወይም በተፈጥሮ በተቀረጸባቸው እውቀት ነው። ሰዎች ግን አምላክን በማወቅ ሊለወጡ ይችላሉ። አንተም ራስህ አምላክ የሚሰጠውን እውቀት ሥራ ላይ በማዋል በሕይወትህ ውስጥ አንዳንድ ለውጦችን እንዳደረግህ የታወቀ ነው። ይህን የመሰለ ለውጥ ያደረጉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ስለዚህ ይህ ትንቢት ይሖዋን በሚያገለግሉ ሰዎች ላይ መፈጸም ጀምሯል። በተጨማሪ ግን በመላው ዓለም የሚኖሩ ሰዎች የነበራቸውን ማንኛውንም የአውሬነት ወይም የጠበኛነት ባሕርይ ሙሉ በሙሉ አውልቀው የሚጥሉበት ጊዜ እንደሚመጣ ያመለክታል።

13. በምድር ላይ ምን የትምህርት ዘመቻ ይካሄዳል?

13 መላዋ ምድር አምላክን በማወቅ ስትሞላ እንዴት ያለ ግሩም ሁኔታ ይሰፍናል! በንጉሡ በኢየሱስ ክርስቶስና በ144,000ዎቹ ተባባሪ ገዥዎች መሪነት የሚካሄድ ሰፊ የትምህርት ዘመቻ ይኖራል። በዚያ ጊዜ የሚሠራባቸው አዲስ “ጥቅልሎች” ይኖራሉ። እነዚህ ጥቅልሎች የምድርን ነዋሪዎች ለማስተማር የሚያገለግሉ በጽሑፍ የተዘጋጁ የአምላክ መመሪያዎች እንደሚሆኑ ግልጽ ነው። (ራእይ 20:​12) የሰው ልጅ ጦርነትን ሳይሆን ሰላምን ይማራል። አውዳሚ የጦር መሣሪያዎች በሙሉ ለአንዴና ለሁልጊዜ ይደመሰሳሉ። (መዝሙር 46:​9) የአዲሱ ዓለም ነዋሪዎች ባልንጀሮቻቸው የሆኑትን የሰው ልጆች እንዴት በፍቅር፣ በአክብሮትና በትሕትና እንደሚይዙ ትምህርት ይሰጣቸዋል።

14. የሰው ልጅ እንደ አንድ ቤተሰብ በሚሆንበት ጊዜ ዓለማችን ምን የተለየ መልክ ይኖራታል?

14 መላው የሰው ልጅ እንደ አንድ ቤተሰብ ሆኖ ይኖራል። ለአንድነትና ለወንድማማችነት እንቅፋት የሚሆን አንዳችም ነገር አይኖርም። (መዝሙር 133:​1–3) በሌቦች እንዳይደፈር ሰግቶ ቤቱን የሚቆልፍ ሰው አይኖርም። በእያንዳንዱ ሰው ልብ፣ በእያንዳንዱ ቤት፣ በእያንዳንዱ የምድር ክፍል ሰላም ይነግሣል።​— ሚክያስ 4:4

አስደሳቹ ትንሣኤ

15. በምድር ላይ የትኞቹ ሁለት ወገኖች ከሞት ይነሳሉ?

15 በዚህ የሺህ ዓመት ግዛት ውስጥ የሙታን ትንሣኤ ይከናወናል። የመንፈስ ቅዱስን ሥራና አመራር እየተቃወሙ ያለ ምንም ንስሐ በአቋማቸው የገፉ ሁሉ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል ላይ ሆን ብለው ኃጢአት የሠሩ ስለሆኑ ትንሣኤ አያገኙም። (ማቴዎስ 23:​15, 33፤ ዕብራውያን 6:​4–6) እርግጥ ሰዎች ይህን የመሰለውን ኃጢአት መሥራት አለመሥራታቸውን የሚወስነው አምላክ ነው። ቢሆንም ሁለት የተለያዩ ወገኖች ከሙታን ይነሳሉ። እነርሱም “ጻድቃንም ዓመፀኞችም” ናቸው። (ሥራ 24:​15) ትንሣኤ የሚከናወነው አግባብ ባለው ሥርዓትና ቅደም ተከተል ስለሆነ ከሙታን ተነስተው በምድር ላይ ለመኖር የመጀመሪያዎቹ የሚሆኑት ይሖዋን በታማኝነት ያገለገሉ ጻድቃን ናቸው ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው።​— ዕብራውያን 11:​35–39

16. (ሀ) በምድር ላይ ከሚነሱት “ጻድቃን” መካከል እነማን ይኖራሉ? (ለ) ከጥንቶቹ ታማኝ ሰዎች መካከል በተለይ ማንን አግኝተህ ለማነጋገር ትፈልጋለህ? ለም⁠ንስ?

16 የይሖዋ አገልጋዮች ስለ ጦርነት፣ ስለ ተፈጥሮ አደጋና ሞት በሚገልጽ ዜና ፋንታ ስለ ትንሣኤ የሚገልጽ አስደሳች ዜና ይሰማሉ። እንደ አቤል፣ ሄኖክ፣ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሣራ፣ ኢዮብ፣ ሙሴ፣ ረዓብ፣ ሩት፣ ዳዊት፣ ኤልያስና አስቴር ያሉት ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ወደ ሕይወት መመለሳቸውን መስማት በጣም የሚያስደስት ይሆናል። ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ስለተፈጸሙባቸው ሁኔታዎች ዝርዝር መግለጫ ሲሰጡን በጣም አስደናቂ የሆኑና ስሜታችንን የሚያነሳሱ ታሪኮች እንሰማለን። እነርሱና በቅርብ ዓመታት የሞቱ ጻድቃንም የሰይጣን ሥርዓት እንዴት እንደተደመሰሰ፣ ይሖዋ ቅዱስ ስሙን ለመቀደስና ሉዓላዊነቱን ለማረጋገጥ ስለወሰደው እርምጃ ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት እንደሚኖራቸው ምንም አያጠራጥ⁠ርም።

17. ታማኞቹ ከሞት ለሚነሱ ሌሎች ሰዎች ምን እገዛ ያደርጉላቸዋል?

17 እነዚህ የታመኑ ሰዎች በቢልዮን የሚቆጠሩት “ዓመፀኞች” ከሞት እሥራት በሚፈቱበት በቀጣዩ የትንሣኤ ክፍለ ጊዜ በጣም ጠቃሚ እገዛ ያደርጋሉ። አብዛኛው የሰው ልጅ ይሖዋን የማወቅ አጋጣሚ አላገኘም። ሰይጣን ‘ዓይናቸውን አሳውሮ’ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 4:​4) ይሁን እንጂ የዲያብሎስ ሥራ ፈጽሞ እንዳልነበረ ይሆናል። ዓመፀኞቹ ሰዎች ከሞት ተነስተው ውብና ሰላማዊ በሆነ ምድር ላይ መኖር ይጀምራሉ። እነርሱን ስለ ይሖዋና ስለ ነገሠው ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ለማስተማር በጥሩ ሁኔታ የተደራጁ ሰዎች ሞቅ ያለ አቀባበል ያደርጉላቸዋል። በቢልዮን የሚቆጠሩ ከሞት የተነሡ ሰዎች ፈጣሪያቸውን ማወቅና መውደድ ሲጀምሩ ከይሖዋ የሚገኘው እውቀት ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ መጠን ምድርን ይሞላል።

18. በሞት የተለዩህን የምትወዳቸው ሰዎች በምትቀበልበት ጊዜ ምን የሚሰማህ ይመስልሃል?

18 የሙታን ትንሣኤ እንዴት ያለ ታላቅ ደስታ ያመጣልናል! ጠላታችን ሞት ያላሠቃየው ማን አለ? በበሽታ ወይም በእርጅና ወይም በድንገተኛ አደጋ የመጣ ሞት የሚያፈቅሩትን ሰው ሲነጥቅ ቅስሙ የማይሰበር ማን ነው? ከእነዚህ በሞት ከተለዩን ሰዎች ጋር ስንገናኝ ምን ያህል ደስታ እንደሚኖር ገምት። እናቶችና አባቶች፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወዳጆችና ዘመዶች ተቃቅፈው እልልታቸውን ያቀ ልጣሉ።

በመጨረሻ ፍጽምና እንላበሳለን!

19. በሺው ዓመት ዘመን ምን ተአምር ይፈጸማል?

19 ሺው ዓመት ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ አንድ አስደናቂ ተአምር ይከናወናል። ለሰው ልጆች ከክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ገጽታዎች በሙሉ በጣም አስደሳች የሚሆነው ይኸኛው ሳይሆን አይቀርም። ይሖዋ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ታማኝና ታዛዥ የሆነውን እያንዳንዱን ወንድና ሴት የቤዛዊ መሥዋዕቱ ሙሉ ተጠቃሚ እንዲያደርግ ያዛል። በዚህ አማካኝነት ማንኛውም ዓይነት ኃጢአት ተወግዶ የሰው ልጅ ወደ ፍጽምና ደረጃ ከፍ ይላል።​— 1 ዮሐንስ 2:​2፤ ራእይ 21:​1–4

20. (ሀ) ፍጹም መሆን ምን ማለት ይሆናል? (ለ) ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉትም ሆኑ ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች ሙሉ በሙሉ በሕይወት የሚኖሩት መቼ ነው?

20 ፍጽምና! ምን ማለት ይሆናል? አዳምና ሔዋን በይሖዋ አምላክ ላይ ኃጢአት ከመሥራታቸው በፊት ወደነበሩበት ሕይወት መመለስ ማለት ይሆናል። በአካል፣ በአእምሮ፣ በስሜት፣ በሥነ ምግባር፣ በመንፈሳዊ ሁኔታና በማንኛውም ሌላ መንገድ ፍጽምና የተላበሱት የሰው ልጆች ሁሉንም የአምላክ መስፈርቶች ያሟሉ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ በዚያ ጊዜ የሚኖሩት ሰዎች አንድ ዓይነት ይሆናሉ ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም! ዛፎች፣ አበቦች፣ እንስሳትና በአጠቃላይ የይሖዋ ፍጥረታት በሙሉ ይሖዋ በዓይነት ልዩነት የሚደሰት አምላክ መሆኑን ያሳያሉ። ፍጹም የሆኑ የሰው ልጆች የተለያየ ጠባይና የተፈጥሮ ችሎታ ይኖራቸዋል። ሁሉም ሰው አምላክ በመጀመሪያ ያሰበውን ዓይነት ኑሮ በማግኘት ይደሰታል። ራእይ 20:​5 “የቀሩቱ ሙታን ግን ይህ ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በሕይወት አልኖሩም” ይላል። ከሙታን የሚነሱት ሰዎች ከአርማጌዶን በሕይወት ከሚተርፉት እጅግ ብዙ ሰዎች ባልተለየ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ሕያዋን የሚሆኑት ኃጢአት የለሽ ወደሆነ የፍጽምና ደረጃ ሲደርሱ ነው።

21. (ሀ) በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ማለቂያ ላይ ምን ይሆናል? (ለ) ሰይጣንና ከሰይጣን ጎን የሚሰለፉ ሁሉ ምን ይሆናሉ?

21 ፍጹም የሆኑት የሰው ልጆች አንድ የመጨረሻ ፈተና ይመጣባቸዋል። የሺህ ዓመቱ ዘመን ሲያልቅ ሰይጣንና አጋንንቱ ለአጭር ጊዜ ከጥልቁ ተፈትተው ሰዎችን ከይሖዋ ለማራቅ የመጨረሻ ሙከራ እንዲያደርጉ ይፈቀድላቸዋል። የራሳቸውን መጥፎ ምኞት ከአምላክ ፍቅር የሚያስበልጡ አንዳንድ ሰዎች ይኖራሉ፤ ሆኖም ይህ ዓመፅ በአጭሩ ይቀጫል። ይሖዋ እነዚህን ራስ ወዳዶች ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ጋር ያጠፋል። ከዚያ በኋላ መጥፎ አድራጊዎች ለዘላለም ከአጽናፈ ዓለሙ ይወገዳሉ።​— ራእይ 20:​7–10

ምን ለማድረግ ታስባለህ?

22. በገነት ውስጥ ምን ለመሥራት ትመኛለህ?

22 ይሖዋን የሚወዱና በገነቲቱ ምድር የሚኖሩ ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም የመኖር ዕድል ከፊታቸው ወለል ብሎ ይዘረጋላቸዋል። የሚኖራቸውን ደስታ መገመት ያስቸግራል። አንተ ራስህ የዚህ ተቋዳሽ ልትሆን ትችላለህ። ፍጹም የሆነው የሰው ልጅ በሙዚቃ፣ በሥነ ጥበብ፣ በእጅ ሥራና በጠቅላላው በሚሠራቸው ሥራዎች በአሮጌው ምድር የነበሩ ታላላቅ የፈጠራ ሰዎች ከደረሱባቸው ደረጃዎች እጅግ ልቆ ይሄዳል። የሰው ልጆች ፍጹም ከመሆናቸውም በላይ ገደብ የሌለው ዕድሜና ጊዜ ይኖራቸዋል። ፍጹም ሰው ስትሆን ምን ዓይነት ድንቅ ሥራ ልትሠራ እንደምትችል አስብ። በተጨማሪም አንተም ሆንክ ሌሎች የሰው ልጆች በአጽናፈ ዓለሙ ከተረጩት በቢልዮን የሚቆጠሩ ከዋክብት አንስቶ የአቶም ክፋይ እስከሆኑት ቅንጣቶች ድረስ ስለ ይሖዋ ፍጥረታት ምን ያህል ብዙ እውቀት ልታካብት እንደምትችል ገምት። የሰው ልጅ የሚደርስባቸው ክንውኖች በሙሉ አፍቃሪ ሰማያዊ አባታችን ለሆነው ለይሖዋ ተጨማሪ ደስታ ያመጡለታል።​— መዝሙር 150:​1–6

23. በገነት ውስጥ መኖር አሰልቺ የማይሆነው ለምንድን ነው?

23 በዚያ ጊዜ ሕይወት አሰልቺ አይሆንም። እንዲያውም እያደር ይበልጥ አስደሳች እየሆነ ይሄዳል። ከዚህ ማየት እንደምትችለው ከአምላክ የሚገኘው እውቀት ዳርቻ የለውም። (ሮሜ 11:​33) ለዘላለም ስንኖር የምንማራቸው አዳዲስ ነገሮችና ገና የሚዳሰሱ የእውቀት አድማሶች ይኖራሉ። (መክብብ 3:​11) ስለ ይሖዋ ይበልጥ እያወቅህ ስትሄድም ለጥቂት ዓመታት ሳይሆን ለዘላለም ዓለም ሕያው ሆነህ ትኖራለህ!​— መዝሙር 22:​26

24, 25. በአሁኑ ጊዜ ስለ አምላክ ካገኘኸው እውቀት ጋር በሚጣጣም መንገድ መኖር የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው?

24 ታዲያ ወደፊት በዚች አስደሳች ምድራዊት ገነት የመኖር ተስፋ ማንኛውም ዓይነት ጥረት ሊደረግለትና ማንኛውም መሥዋዕት ሊከፈልለት የሚገባ አይደለምን? በእርግጥ ነው! ይሖዋ ወደፊት ይህን ሕይወት ለመጨበጥ የሚያስችለውን ቁልፍ ስጥቶሃል። ይህም ቁልፍ ከአምላክ የሚገኝ እውቀት ነው። ታዲያ በዚህ ቁልፍ ትጠቀማለህ?

25 ይሖዋን የምትወድ ከሆነ የእርሱን ፈቃድ በማድረግ ትደሰታለህ። (1 ዮሐንስ 5:​3) በዚሁ አቋምህ ከቀጠልክ በጣም ብዙ በረከቶችን ታገኛለህ። ከአምላክ ያገኘኸውን እውቀት ከሠራህበት በዚህ በመከራ በተዋጠ ዓለም ውስጥ እንኳን ከበፊቱ የላቀ ደስታ ይሰጥሃል። ከዚህም በላይ ይህ እውቀት ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ በመሆኑ ወደፊት የምታገኘው ሽልማት በጣም ከፍተኛ ነው! እርምጃ ልትወስድ የምትችልበት አመቺ ጊዜ አሁን ነው። ስለ አምላክ ካገኘኸው እውቀት ጋር በሚጣጣም ሁኔታ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ለይሖዋ ያለህን ፍቅር በተግባር ግለጽ። ቅዱስ ስሙን አክብር፤ ሰይጣን ሐሰተኛ መሆኑን አሳይ። በምላሹ የእውነተኛ ጥበብና እውቀት ምንጭ የሆነው ይሖዋ አምላክ ታላቅና አፍቃሪ በሆነው ልቡ ውስጥ ደስ ይሰኝብሃል። (ኤርምያስ 31:​3፤ ሶፎንያስ 3:​17) ለዘላለምም ይወድሃል!

እውቀትህን ፈትሽ

“እውነተኛው ሕይወት” ምንድን ነው?

ከአርማጌዶን በኋላ በምድር ላይ ምን ነገር ይሆናል?

እነማን ትንሣኤ አግኝተው በምድር ላይ ይኖራሉ?

የሰው ልጅ ፍጹም የሚሆነውና በመጨረሻ የሚፈተነው እንዴት ነው?

ገነትን በተመለከተ ያለህ ተስፋ ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 188, 189 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምድር አምላክ በሚሰጠው እውቀት ስትሞላ በገነት ውስጥ ለመኖር ተስፋ ታደርጋለህ?