በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ምን ይሆናሉ?

በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ምን ይሆናሉ?

ምዕራፍ 9

በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ምን ይሆናሉ?

1. ብዙ ሰዎች የሚወዱት ሰው ሲሞትባቸው እንዴት ይሰማቸዋል?

“ሞት ለመረዳት የሚያዳግት የባዶነት ስሜት ስለሚያሳድር የሚወዱትን ሰው በሞት መነጠቅ ከባድ ሥቃይ ያስከትላል።” ይህን የተናገረው አባቱና እናቱ በተከታታይ የሞቱበት አንድ ልጅ ነው። ወላጆቹን ማጣቱ ያስከተለበት ሐዘንና ሥቃይ ‘በጭንቀት ባሕር ውስጥ እየሰጠመ’ እንዳለ ሆኖ እንዲሰማው አድርጎት ነበር። አንተም ይህን የመሰለ ሐዘን አጋጥሞህ ይሆናል። እነኚህ የምወዳቸው በሞት የተለዩኝ ሰዎች የት ናቸው? ዳግመኛስ ላያቸው እችል ይሆን? ብለህ ራስህን ትጠይቅ ይሆናል።

2. ሞትን በሚመለከት እንዴት ያሉ ግራ የሚያጋቡ ጥያቄዎች ይነሳሉ?

2 ልጅ የሞተባቸው አንዳንድ ወላጆች “እግዚአብሔር በጣም የሚያማምሩትን አበቦች ቀጥፎ ለራሱ ወደ ሰማይ ይወስዳል” ተብሎ ይነገራቸዋል። ይህ እውነት ነውን? በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ወደ መንፈሳዊው ዓለም ተወስደዋልን? አንዳንዶች እንደሚሉት ማንኛውም ሥቃይና ምኞት በሚከስምበት ኒርቫና በሚባል የደስታ ዓለም ውስጥ እየዋኙ ናቸውን? ለእነዚህ የምናፈቅራቸው ሰዎች ሞት በገነት ውስጥ ወደሚገኝ የማይጠፋ ሕይወት የሚያስገባ በር ሆኖላቸዋልን? ወይም አንዳንዶች እንደሚሉት ሞት አምላክን ያሳዘኑ ሰዎችን ፍጻሜ የሌለው መከራና ሥቃይ ወደሚቀበሉበት ዓለም የሚያስገባ ነውን? ሙታን በሕይወት በምንኖረው ሰዎች ኑሮ ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉን? እንደነዚህ ላሉት ጥያቄዎች እውነተኛውን መልስ ለማግኘት የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ መመርመር ያስፈልገናል።

በሰው ውስጥ ያለው “መንፈስ” ምንድን ነው?

3. ሶቅራጥስና ፕላቶ ስለ ሞት ምን ዓይነት አስተሳሰብ ነበራቸው? ይህስ በዛሬው ጊዜ የሚኖሩትን ሰዎች የነካው እንዴት ነው?

3 ሶቅራጥስና ፕላቶ የተባሉት የጥንትዋ ግሪክ ፈላስፎች በሰዎች አካል ውስጥ እንዳይሞት ሆኖ የተሠራ አንድ ነገር መኖር አለበት ይሉ ነበር። ሰው ሲሞት ሕያው ሆና የምትቀጥል የማትሞት ነፍስ አለች የሚል እምነት ነበራቸው። በአሁኑ ጊዜ በመላው ምድር ይህን የመሰለ እምነት ያላቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ይህ እምነት ሰዎች ሙታንን እንዲፈሩና ሙታን ስለሚገኙበትም ሁኔታ እንዲጨነቁ አድርጓቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሙታን የሚያስተምረው ነገር ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ነው።

4. (ሀ) የዘፍጥረት መጽሐፍ ስለ ነፍስ ምን ይገልጽልናል? (ለ) አምላክ አዳምን ሕያው ለማድረግ ወደ አካሉ ምን ነገር አስገባ?

4 ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ ስናስብ የመጀመሪያው አባታችን አዳም ነፍስ እንዳልነበረው ማስታወስ ይገባናል። እርሱ ራሱ ነፍስ ነበር። አምላክ በጣም አስደናቂ በሆነው የፍጥረት ሥራው ነፍስ የሆነውን ሰው መሠረታዊ ከሆኑት የምድር ንጥረ ነገሮች አበጅቶ “የሕይወትን እስትንፋስ” እፍ አለበት። ዘፍጥረት 2:​7 (የ1879 እትም) “እግዚአብሔርም አምላክ ሰውን ፈጠረ መሬት ከምድር። ባፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት። ሰውም ሕይወት ያለበት ነፍስ ሆነ” ይላል። የአዳም ሕይወት ሊቀጥል የሚችለው በመተንፈስ ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ በአዳም ላይ የሕይወትን እስትንፋስ እፍ አለበት ሲል አየር እንዲተነፍስ አደረገው ማለት ብቻ አልነበረም። መጽሐፍ ቅዱስ ምድራዊ በሆኑ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ላይ የሚሠራ ‘የሕይወት ኃይል’ እንዳለ ይናገራል።​— ዘፍጥረት 7:​22

5, 6. (ሀ) ‘የሕይወት ኃይል’ ምንድን ነው? (ለ) በመዝሙር 146:​4 (የ1879 እትም) ላይ የተጠቀሰው “መንፈስ” አንድን ሰው ማንቀሳቀሱን ሲያቆም ምን ይሆ⁠ናል?

5 ‘የሕይወት ኃይል’ ምንድን ነው? አምላክ በድን ወደነበረው የአዳም አካል ውስጥ ያስገባው ሕይወት የሚዘራ ኃይል ነው። ከዚያ በኋላ ይህ ኃይል ሳይጠፋ እንዲቆይ ለማስቻል መተንፈስ አስፈላጊ ሆነ። ታዲያ በመዝሙር 146:​4 (የ1879 እትም) ላይ የተጠቀሰው “መንፈስ” ምንድን ነው? ይህ ጥቅስ “መንፈሱ ትወጣለች ወደ መሬትም ይመለሳል። በዚያን ቀን ትምክሕቱ ሁሉ ይጠፋል” ይላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች “መንፈስ” የሚለውን ቃል በዚህ መንገድ በተጠቀሙበት ጊዜ ሥጋ ከሞተ በኋላ ለብቻው የሚኖር ከሥጋ የተለየ ነፍስ እንዳለ መጠቆማቸው አልነበረም።

6 ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ የሚለያቸው “መንፈስ” ከፈጣሪ የተገኘው የሕይወት ኃይል ነው። (መዝሙር 36:​9፤ ሥራ 17:​28) የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያንቀሳቅሰውን መሣሪያ ቅርጽና ባሕርይ እንደማይወስድ ሁሉ ይህ የሕይወት ኃይልም ሕያው አድርጎ የሚያንቀሳቅሰውን ፍጥረት ባሕርይ ወይም ቅርጽ ሊለብስ አይችልም። ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ ይበራ የነበረው መብራት እንደሚጠፋ ሁሉ አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜም መንፈሱ (የሕይወት ኃይሉ) የሰውነቱን ሴሎች ሕያው አድርጎ ማንቀሳቀሱን ያቆማል። ሰብዓዊው አካል በሕይወት ኃይል መንቀሳቀሱ ሲቆም ነፍስ የሆነው ሰው ይሞታል።​— መዝሙር 104:​29 አዓትመክብብ 12:​1, 71879 እትም

“ወደ አፈር ትመለሳለህ”

7. አዳም የአምላክን ትእዛዝ ቢጥስ ምን እንደሚሆን ተነግሮት ነበር?

7 ሞት ለኃጢአተኛው አዳም ምን ትርጉም እንደሚኖረው ይሖዋ በግልጽ አስረድቶታል። “ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፣ ወደ አፈርም ትመለሳለህ” ብሎታል። (ዘፍጥረት 3:​19) አዳም የሚመለሰው ወዴት ነበር? ወደ ተፈጠረበት መሬት ወይም አፈር ይመለሳል ማለቱ ነበር። አዳም በሚሞትበት ጊዜ ከሕልውና ውጭ ይሆናል ማለት ነው።

8. የሰው ልጆች ነፍስ በመሆናቸው ረገድ ከእንስሳት ብልጫ የማይኖራቸው በምን መንገድ ነው?

8 በዚህ ረገድ የሰው ልጆች ሞት ከእንስሳት ሞት የተለየ አይደለም። እንስሳትም ነፍሳት ሲሆኑ በሕይወት የሚያቆማቸውና የሚያንቀሳቅሳቸው ያው መንፈስ ወይም የሕይወት ኃይል ነው። (ዘፍጥረት 1:​24) ጠቢቡ ሰሎሞን በመክብብ 3:​19, 20 ላይ እንዲህ ይለናል:- “አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል፤ የሁሉም እስትንፋስ [“መንፈስ” አዓት] አንድ ነው። . . . ሁሉ ወደ አንድ ቦታ ይሄዳል፤ ሁሉ ከአፈር ነው ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳል።” የሰው ልጅ የይሖዋን ባሕርያት የሚያንጸባርቅ ሆኖ በአምላክ አምሳል ስለ ተፈጠረ ከእንስሳት ብልጫ አለው። (ዘፍጥረት 1:​26, 27) በሚሞቱበት ጊዜ ግን ሰዎችም ሆኑ እንስሳት ወደ አፈር ይመለሳሉ።

9. ሙታን የሚገኙበት ሁኔታ ምንድን ነው? ወዴትስ ይሄዳሉ?

9 ሰሎሞን “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም” በማለት ስለ ሞት ምንነት ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥቷል። አዎን፣ ሙታን አንዳች ነገር አያውቁም። በዚህም ምክንያት ሰሎሞን እንዲህ ሲል አጥብቆ አሳስቦናል:- “አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ።” (መክብብ 9:​5, 10) ሙታን የሚሄዱት የት ነው? የሰው ልጆች የጋራ መቃብር ወደሆነው ወደ ሲኦል (በዕብራይስጥ ሺኦል) ነው። በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች አንዳች ነገር አይሰማቸውም ወይም አያውቁም። በምንም ዓይነት እየተሠቃዩ አይደለም፤ በእኛም ላይ ምንም ዓይነት ተጽእኖ ማሳደር አይችሉም።

10. የሰው ልጆች መጨረሻ ሞቶ መቅረት መሆን አያስፈልገውም ለማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

10 እኛም ሆንን የምንወዳቸው ሰዎች ያለን ዕድል ለጥቂት ዓመታት ብቻ በሕይወት ከኖርን በኋላ ለዘላለም ከሕልውና ውጭ ሆነን መቅረት ነውን? መጽሐፍ ቅዱስ አይደለም ይላል። ይሖዋ አምላክ አዳም ባመፀበት ጊዜ ኃጢአት ያስከተላቸውን ውጤቶች የሚያስወግድበትን ዝግጅት ወዲያው አቋቁሟል። የሰው ልጆች እንዲሞቱ የአምላክ ዓላማ አልነበረም። (ሕዝቅኤል 33:​11፤ 2 ጴጥሮስ 3:​9) ስለዚህ እኛም ሆንን የምንወዳቸው ሰዎች መጨረሻችን ሞቶ መቅረት ላይሆን ይችላል።

“ተኝቶአል”

11. ኢየሱስ የሞተው ወዳጁ አልዓዛር የነበረበትን ሁኔታ እንዴት ብሎ ገለጸው?

11 ይሖዋ እኛንም ሆነ የምንወዳቸውን ሰዎች ከአዳማዊው ሞት የማዳን ዓላማ አለው። በዚህም ምክንያት የአምላክ ቃል የሞቱ ሰዎች እንዳንቀላፉ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጁ አልዓዛር መሞቱን እንዳወቀ ለደቀ መዛሙርቱ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ አላቸው።” ደቀ መዛሙርቱ አባባሉን ወዲያው ባላስተዋሉ ጊዜ ግን በግልጽ “አልዓዛር ሞተ” አላቸው። (ዮሐንስ 11:​11, 14) ከዚያም ኢየሱስ የአልዓዛር እህቶች ማርታና ማር⁠ያም በወንድማቸው ሞት ምክንያት ሐዘን ወደተቀመጡበት ወደ ቢታንያ ከተማ ሄደ። ኢየሱስ ለማርታ “ወንድምሽ ይነሣል” ባላት ጊዜ ይሖዋ ሞት በሰው ልጆች ላይ ያስከተለውን ውጤት ለመሻር ባለው ዓላማ የምታምን መሆኑን ገለጠችለት። “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ” አለችው።​— ዮሐንስ 11:​23, 24

12. ሐዘንተኛዋ ማርታ ስለ ሙታን ምን ዓይነት ተስፋ ነበራት?

12 ማርታ ከሞት በኋላ ሕያው ሆና ስለምትኖር ዘላለማዊት ነፍስ የተናገረችው ነገር የለም። አልዓዛር ወደ አንድ መንፈሳዊ ዓለም ሄዶ ሕያው ሆኖ ይኖራል የሚል እምነት አልነበራትም። ማርታ የነበራት እምነት አስደናቂ በሆነው የሙታን ትንሣኤ ነበር። ከአልዓዛር አካል ዘላለማዊት የሆነች ነፍስ እንደወጣች ሳይሆን ሟቹ ወንድሟ ከሕልውና ውጭ እንደሆነ ተረድታ ነበር። ለዚህም መፍትሔ የሚሆነው የወንድሟ ከሞት መነሳት ብቻ ነበር።

13. ኢየሱስ ከአምላክ የተቀበለው ምን የማድረግ ኃይል አለው? ይህንንስ በተግባር ያሳየው እንዴት ነው?

13 የሰው ልጆችን ከሞት እንዲታደግ ሥልጣን የተሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ሆሴዕ 13:​14) ስለዚህም ኢየሱስ ማርታ ለተናገረችው ቃል መልስ ሲሰጥ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል” አለ። (ዮሐንስ 11:​25) ኢየሱስ ከሞተ አራት ቀን ሆኖት ወደነበረው ወደ አልዓዛር መቃብር ሄዶ እርሱን ወደ ሕይወት በመመለስ ይህን ከአምላክ የተቀበለውን ኃይል በተጨባጭ አሳይቷል። (ዮሐንስ 11:​38–44) ይህንንም ሆነ ሌሎቹን ኢየሱስ ያደረጋቸውን የትንሣኤ ተአምራት የተመለከቱ ሰዎች እንዴት ያለ ደስታ እንደተሰማቸው ገምት!​— ማርቆስ 5:​35–42፤ ሉቃስ 7:​12–16

14. ትንሣኤ እና የማትሞት ነፍስ አለች የሚለው ሐሳብ እርስ በርስ የማይጣጣሙት ለምንድን ነው?

14 እዚህ ላይ ቆም ብለን እናስብ። ከሞት በኋላ ሕያው ሆና የምትቀጥል የማትሞት ነፍስ ብትኖር ኖሮ ከሙታን መነሣት ወይም ወደ ሕይወት መመለስ የሚያስፈልገው ሰው አይኖርም ነበር። እንዲያውም እንደ አልዓዛር ያለው ሰው አስደናቂ የሆነ ሰማያዊ ሽልማት አግኝቶ ከነበረ እርሱን ፍጹም ወዳልሆነው ምድራዊ ሕይወት መመለስ ደግነት አይሆንም። መጽሐፍ ቅዱስ በየትም ቦታ ላይ “የማትሞት ነፍስ” አለች ብሎ አይናገርም። ከዚህ ይልቅ ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እንደምትሞት ይናገራል። (ሕዝቅኤል 18:​4, 20) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ብቸኛው የሞት መፍትሔ ትንሣኤ እንደሆነ ያመለክታል።

“በመታሰቢያ መቃብር ያሉቱ ሁሉ”

15. (ሀ) “ትንሣኤ” የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ አምላክ ግለሰቦችን ከሞት ለማስነሳት አስቸጋሪ የማይሆንበት ለምንድን ነው?

15 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “ትንሣኤ” ለማለት የተጠቀሙበት ቃል “ብድግ ማለት” ወይም “መነሳት” የሚል ቀጥተኛ ትርጉም አለው። ይህም ሕይወት አልባ ከሆነው የበድንነት ሁኔታ ብድግ ማለት ወይም ከሰው ልጆች የጋራ መቃብር መነሣት ማለት ነው። ይሖዋ አምላክ አንድን ሰው በቀላሉ ከሞት ሊያስነሣ ይችላል። ለምን? ምክንያቱም የሕይወት ምንጭ ይሖዋ ነው። በዛሬው ጊዜ ሰዎች የሌሎች ሰዎችን ድም⁠ፅና ምስል በቪዲዮ ክሮች ላይ ቀርጸው ሊያስቀምጡና ሰዎቹ ከሞቱ በኋላ ሊያጫውቱ ይችላሉ። ስለዚህ ሁሉን የሚችለው ፈጣሪያችን የማንኛውንም ግለሰብ ባሕርይና መልክ መዝግቦ ሊያቆይና ያንኑ ሰው አዲስ አካል ሰጥቶ ሊያስነሣ ይችላል።

16. (ሀ) ኢየሱስ በመታሰቢያ መቃብር ውስጥ ስለሚገኙ ሰዎች ምን ተስፋ ሰጥቷል? (ለ) የአንድ ሰው ትንሣኤ የመጨረሻ ውጤት የሚወሰነው በምንድን ነው?

16 ኢየሱስ ክርስቶስ “በመቃብር [“በመታሰቢያ መቃብር” አዓት] ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 5:​28, 29) ይሖዋ የሚያስታውሳቸው ሰዎች በሙሉ ከሞት ተነስተው የአምላክን መንገዶች ይማራሉ። ስለ አምላክ በቀሰሙት እውቀት መሠረት ለሚመላለሱ ሁሉ ትንሣኤያቸው የሕይወት ትንሣኤ ይሆንላቸዋል። የአምላክን ትምህርትና አገዛዝ ለመቀበል አሻፈረን ለሚሉት ግን ትንሣኤያቸው የሚኮነኑበት የፍርድ ትንሣኤ ይሆንባቸዋል።

17. ከሞት የሚነሱት እነማን ናቸው?

17 የይሖዋ አገልጋዮች በመሆን የጽድቅ አካሄድ የተከተሉ ሁሉ ከሞት እንደሚነሱ የታወቀ ነው። እንዲያውም ብዙዎች ስደት ባጋጠማቸው ጊዜ እስከ ሞት ድረስ እንዲጸኑ ያስቻላቸው የትንሣኤ ተስፋ ነው። አምላክ ወደ ሕይወት እንደሚመልሳቸው ያውቁ ነበር። (ማቴዎስ 10:​28) ይሁን እንጂ የአምላክን የጽድቅ መስፈርቶች ያከበሩ ወይም ያላከበሩ መሆናቸው ሳይታወቅ የሞቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። እነዚህም ሰዎች ከሞት ይነሣሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለዚህ የይሖዋ ዓላማ እርግጠኛ በመሆን “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ” ብሏል።​— ሥራ 24:​15

18. (ሀ) ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ትንሣኤ ምን ራእይ ተመልክቷል? (ለ) “በእሳት ባሕር ውስጥ” ተጥሎ እንዲጠፋ የተደረገው ምንድን ነው? ይህስ “ባሕር” የምን ምሳሌ ነው?

18 ሐዋርያው ዮሐንስ ከሞት ተነስተው በአምላክ ዙፋን ፊት ስለ ቆሙ ሰዎች የሚገልጽ አስደሳች ራእይ ተመልክቷል። ከዚያ በኋላ ዮሐንስ እንዲህ በማለት ጻፈ:- “ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፣ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፣ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ። ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው።” (ራእይ 20:​12–14) ይህ ምን ማለት እንደሚሆን ገምት! በአምላክ መዘክር ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙ ሁሉ የሰው ልጆች የጋራ መቃብር ከሆነው ከሲኦል (በግሪክኛ ሔድስ) የመውጣት ዕድል ያገኛሉ። (መዝሙር 16:​10፤ ሥራ 2:​31) አምላክን ለማገልገል ፈቃደኛ መሆንና አለመሆናቸውን በተግባር የማስመስከር አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። “ሞትና ሲኦል” ከዚያ በኋላ ወደ “እሳት ባሕር” ይጣላሉ። ይህ “የእሳት ባሕር” እንደ “ገሃነም” ሁሉ ፈጽሞ መጥፋትን ያመለክታል። (ሉቃስ 12:​5) የሰው ልጆች የጋራ መቃብር የሙታን ትንሣኤ ተጠናቅቆ ሲያበቃ ባዶ ሆኖ ከሕልውና ውጭ ይሆናል። አምላክ ማንንም እንደማያሠቃይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ መቻል ምንኛ የሚያጽናና ነገር ነው!​— ኤርምያስ 7:​30, 31

ትንሣኤ፣ ወዴት?

19. ከሰው ልጆች መካከል አንዳንዶች ከሞት ተነስተው ወደ ሰማይ የሚወሰዱት ለምንድን ነው? አምላክስ ምን ዓይነት አካል ይሰጣቸዋል?

19 የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ወንዶችና ሴቶች ወደ ሰማያዊ ሕይወት ይነሳሉ። እነዚህ ከኢየሱስ ጋር ነገሥታትና ካህናት ሆነው መላው የሰው ልጅ ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም የወረሰው ሞት ያስከተለውን ጉዳት ለማስተካከል በሚደረገው ሥራ ይካፈላሉ። (ሮሜ 5:​12፤ ራእይ 5:​9, 10) አምላክ ከክርስቶስ ጋር እንዲገዙ ወደ ሰማይ የሚወስዳቸው ሰዎች ስንት ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው 144,000 ብቻ ናቸው። (ራእይ 7:​4፤ 14:​1) ይሖዋ ለእነዚህ ከሞት የሚነሱ ሰዎች በሰማይ ለመኖር የሚያስችላቸውን መንፈሳዊ አካል ይሰጣቸዋል።​— 1 ቆሮንቶስ 15:​35, 38, 42–45፤ 1 ጴጥሮስ 3:​18

20. ከሞት የሚነሱትን ጨምሮ ታዛዥ የሰው ልጆች ምን ይሆናሉ?

20 እስከ ዛሬ ድረስ ከሞቱት ሰዎች አብዛኞቹ ግን በገነቲቱ ምድር ለመኖር ይነሣሉ። (መዝሙር 37:​11, 29፤ ማቴዎስ 6:​10) አንዳንዶች ለሰማያዊ ሕይወት ከሚነሱባቸው ምክንያቶች አንዱ አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ ዳር ማድረስ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስና 144,000ዎች በሰማይ ሆነው ታዛዥ የሰው ልጆች የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አሽቀንጥረው የጣሉትን ፍጽምና ቀስ በቀስ እንዲላበሱ ያደርጋሉ። ከእነዚህ መካከል ከሞት የሚነሡ ሰዎች ይገኛሉ። ኢየሱስ ይህንን ሲያረጋግጥ ከጎኑ ተሰቅሎ ሲያጣጥር ለነበረው ሰው “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ብሎታል።​— ሉቃስ 23:​42, 43

21. ነቢዩ ኢሳይያስና ሐዋርያው ዮሐንስ በተናገሩት መሠረት ሞት ምን ይሆናል?

21 ምድር ገነት ስትሆን በአሁኑ ጊዜ የሰዎችን ሕይወት ከንቱ የሚያደርገው ሞት ይወገዳል። (ሮሜ 8:​19–21) ነቢዩ ኢሳይያስ ይሖዋ አምላክ “ሞትን ለዘላለም ይውጣል” ብሏል። (ኢሳይያስ 25:​8) ሐዋርያው ዮሐንስ ታዛዥ የሰው ልጆች ከበሽታና ከሞት የሚገላገሉበትን ጊዜ የሚያሳይ ራእይ ተመልክቷል። አዎን፣ “እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”​— ራእይ 21:​1–4

22. ስለ ትንሣኤ ያገኘኸው እውቀት እንዴት ይነካሃል?

22 ግልጽ የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ የሚፈጠረውን ግራ መጋባት ያስወግዳል። ቅዱሳን ጽሑፎች የሚሻረው “የኋለኛው ጠላት” ሞት እንደሆነ በግልጽ ያመለክታሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:​26) ስለ ትንሣኤ ተስፋ ካገኘነው እውቀት እንዴት ያለ ብርታትና ማጽናኛ ልናገኝ እንችላለን! በአምላክ መዘክር ውስጥ ያሉት በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ከእንቅልፋቸው ተነስተው አምላክ ለሚወዳቸው ሰዎች ካዘጋጃቸው አስደናቂ ነገሮች ተካፋይ ለመሆን መቻላቸው በጣም ሊያስደስተን አይገባምን? (መዝሙር 145:​16) እነዚህ በረከቶች የሚገኙት በአምላክ መንግሥት አማካኝነት ነው። ይሁን እንጂ ይህቺ መንግሥት መግዛት የምትጀምረው መቼ ነው? እስቲ እንመልከት።

እውቀትህን ፈትሽ

በሰው ውስጥ ያለው መንፈስ ምንድን ነው?

ሙታን የሚገኙበትን ሁኔታ እንዴት ትገልጻለህ?

ከሞት የሚነሱት እነማን ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 85 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ አልዓዛርን ጠርቶ ከመቃብሩ እንዳስነሳው ሁሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም ከሞት ይነሣሉ

[በገጽ 86 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘አምላክ ሞትን ለዘላለም ሲውጥ’ ደስታ ይሰፍናል