በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአምላክ ሕዝብ መካከል ተረጋግተህና ተማምነህ ኑር

በአምላክ ሕዝብ መካከል ተረጋግተህና ተማምነህ ኑር

ምዕራፍ 17

በአምላክ ሕዝብ መካከል ተረጋግተህና ተማምነህ ኑር

1, 2. የሰው ልጅ የሚገኝበት ሁኔታ አውሎ ነፋስ በተቀላቀለበት ኃይለኛ ዝናብ ከወደመ ሰፈር ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

የምትኖርበት አካባቢ አውሎ ነፋስ በቀላቀለ ኃይለኛ ዝናብ ምክንያት ፈራርሷል እንበል። ቤትህ እንዳለ ወድሟል፣ ንብረትህ ሁሉ ጠፍቷል። ምግብ የለም። ሁኔታው ፈጽሞ ተስፋ ቢስ መስሏል። ነገር ግን ሳይታሰብ በድንገት እርዳታ ደረሰ። የተትረፈረፈ ምግብና ልብስ መጣ። አዲስ ቤት ተሠራልህ። ይህን ሁሉ እርዳታ ያደረገልህን ሰው እንደምታመሰግነው የታወቀ ነው።

2 በዛሬው ጊዜ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር በመፈጸም ላይ ነው። የአዳምና የሔዋን ዓመፅ አውሎ ነፋስ እንደተቀላቀለበት ዝናብ በሰው ዘሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። የሰው ልጅ መኖሪያ የነበረችው ገነት ጠፍታለች። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ሰብዓዊ መንግሥታት ሰዎችን ከጦርነት፣ ከወንጀልና ከግፍ የሚጠብቅ ከለላ ሊያዘጋጁላቸው አልቻሉም። ሃይማኖቶች እጅግ ብዙ ሰዎችን ለመንፈሳዊ ችጋር ዳርገዋል። ይሖዋ አምላክ ግን መንፈሳዊ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ በማቅረብ ላይ ነው። ይህን የሚፈጽመው እንዴት ነው?

“ታማኝና ልባም ባሪያ”

3. ይሖዋ ለሰው ልጆች የሚያስፈልጉትን ነገሮች የሚያቀርበው እንዴት ነው? ይህስ በየትኞቹ ምሳሌዎች ታይቷል?

3 አብዛኛውን ጊዜ የእርዳታ ቁሳቁሶች የሚከፋፈሉት በአንድ ድርጅት በኩል ነው። ይሖዋም ለሕዝቦቹ መንፈሳዊ እርዳታ የሚያቀርበው ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ነው። ለምሳሌ ያህል እስራኤላውያን 1,500 ለሚያክሉ ዓመታት “የይሖዋ ጉባኤ” በመሆን አገልግለዋል። በመካከላቸውም የአምላክ መልእክት አቀባይ በመሆን ሕጉን የሚያስተምሩ ሰዎች ነበሩ። (1 ዜና መዋዕል 28:​8፤ 2 ዜና መዋዕል 17:​7–9) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ይሖዋ የክርስቲያንን ድርጅት አቋቋመ። ጉባኤዎች በተለያዩ አካባቢዎች ተቋቁመው ከሐዋርያትና ከሽማግሌዎች በተውጣጣ የአስተዳደር አካል አመራር ሥር ሆነው ይንቀሳቀሱ ነበር። (ሥራ 15:​22–31) ዛሬም ቢሆን ይሖዋ ሕዝቡን የሚመራውና የሚያስተምረው በአንድ የተደራጀ አካል በኩል ነው። ይህን እንዴት እናውቃለን?

4. በዘመናችን “ታማኝና ልባም ባሪያ” መሆኑን ያረጋገጠው ማን ነው? የሚያስፈልገን የአምላክ መንፈሳዊ ምግብ የሚቀርበውስ እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ በሚገኝበት ጊዜ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ለተከታዮቹ “ምግባቸውን በሰዓቱ” ሲሰጥ እንደሚገኝ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:​45–47 አዓት) ታዲያ ኢየሱስ የሰማያዊ ንግሥና ሥልጣኑን በተቀበለበት በ1914 ‘ታማኝና ልባም ባሪያ’ ሆኖ የተገኘው ማን ነበር? የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት እንዳልነበሩ የተረጋገጠ ነው። እነዚህ ቀሳውስት በአብዛኛው መንጎቻቸውን ይመግቡ የነበረው በአንደኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ ገብተው በማዋጋት ላይ የነበሩትን የየአገራቸውን መንግሥታት የሚደግፍ ፕሮፖጋንዳ ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ “ታናሽ መንጋ” ብሎ የጠራው የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን አባላት እንዲሆኑ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ በተቀቡት እውነተኛ ክርስቲያኖች በኩል ትክክለኛና ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ እየተዘጋጀ ይቀርብ ነበር። (ሉቃስ 12:​32) እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይሰብኩ የነበረው የሰዎችን መንግሥት ሳይሆን የአምላክን መንግሥት ነበር። በዚህም ምክንያት ባለፉት ዓመታት በሚልዮን የሚቆጠሩ የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸው “ሌሎች በጎች” ከቅቡዓኑ “ባሪያ” ጋር በእውነተኛው ሃይማኖት ተቀላቅለዋል። (ዮሐንስ 10:​16) አምላክ ‘በታማኙ ባሪያና’ በዘመናችን በሚገኘው የባሪያው የአስተዳደር አካል እየተጠቀመ እነዚህ የተደራጁ ሕዝቦቹ ለሚፈልግ ሁሉ መንፈሳዊ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ እንዲያቀርቡ በማድረግ ላይ ነው።

‘በሰዓቱ የሚቀርብ ምግብ’

5. ዛሬ በዓለም ውስጥ ምን ዓይነት መንፈሳዊ ሁኔታ ይገኛል? ይሁን እንጂ ይሖዋ ምን በማድረግ ላይ ነው?

5 ኢየሱስ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ብሏል። (ማቴዎስ 4:​4) አብዛኞቹ የሰው ልጆች ግን ለአምላክ ቃል ደንታ ቢስ መሆናቸው በእጅጉ የሚያሳዝን ነገር ነው። አሞጽ የተባለው የይሖዋ ነቢይ አስቀድሞ እንደተናገረው “የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት” ያልሆነ ረሀብ በመላው ምድር ላይ ተስፋፍቷል። (አሞጽ 8:​11) በጣም ሃይማኖተኛ የሆኑ ሰዎች እንኳን በመንፈሳዊ ረሀብ የተጎዱ ናቸው። የይሖዋ ፈቃድ ግን “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን [በትክክል] እንዲያውቁ ነው።” (1 ጢሞቴዎስ 2:​3, 41980 ትርጉም) በዚህም ምክንያት በጣም የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ በማቅረብ ላይ ነው። ታዲያ ይህን ምግብ የት ማግኘት ይቻላል?

6. ይሖዋ በቀደሙት ዘመናት ሕዝቦቹን በመንፈሳዊ የመገበው እንዴት ነበር?

6 በታሪክ ዘመናት ሁሉ ይሖዋ ለሕዝቡ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርብ የነበረው በጋራ እንጂ በተናጠል አልነበረም። (ኢሳይያስ 65:​13) ለምሳሌ ያህል እስራኤላውያን ካህናት ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ተሰብስበው አንድ ላይ የአምላክን ሕግ እንዲማሩ ያደርጉ ነበር። (ዘዳግም 31:​9, 12) የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችም በአስተዳደር አካሉ ሥር ሆነው ጉባኤዎችን ያደራጁና የጉባኤው አባሎች በሙሉ ትምህርትና ማበረታቻ የሚያገኙባቸውን ስብሰባዎች ያዘጋጁ ነበር። (ሮሜ 16:​5፤ ፊልሞና 1, 2) የይሖዋ ምሥክሮችም የእነርሱን አርዓያ ይከተላሉ። በሁሉም ስብሰባዎቻቸው እንድትገኝ ሞቅ ያለ ግብዣ ቀርቦልሃል።

7. በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት ከእውቀትና ከእምነት ጋር ተዛምዶ ያለው እንዴት ነው?

7 እስካሁን ካደረግከው የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ብዙ እውቀት እንዳገኘህ አይካድም። በዚህ ጥናትህም የረዳህ ሰው እንዳለ የታወቀ ነው። (ሥራ 8:​30–35) ይሁን እንጂ እምነትህ ተገቢውን እንክብካቤ ካላገኘ ጠውልጎ እንደሚደርቅ ተክል ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ተስማሚ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ማግኘት ይኖርብሃል። (1 ጢሞቴዎስ 4:​6) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አስፈላጊውን መንፈሳዊ ምግብ እንድታገኝና ከአምላክ በሚገኘው እውቀት እያደግህ በሄድክ መጠን በእምነትህም ጭምር እንድታድግ የሚያስችል የማያቋርጥ የትምህርት መስጫ ፕሮግራም አለ።​— ቆላስይስ 1:​9, 10

8. በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ እንድንገኝ የምንበረታታው ለምንድን ነው?

8 ስብሰባዎች ሌላም አስፈላጊ የሆነ ዓላማ ያከናውናሉ። ጳውሎስ “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፣ መሰብሰባችንን አንተው” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 10:​24, 25) “መነቃቃት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “መሳል” ወይም “ሹል ማድረግ” የሚል ተጨማሪ ትርጉም አለው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ብረት ብረትን ይስለዋል፣ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል” ይላል። (ምሳሌ 27:​17) ሁላችንም ዘወትር ‘እንድንሳል’ ያስፈልጋል። በየቀኑ ከዚህ ዓለም የሚደርስብን ተጽእኖ እምነታችንን ሊያደንዝብን ይችላል። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ግን እርስ በርስ እንበረታታለን። (ሮሜ 1:​11, 12) ሐዋርያው ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ አንዱም አንዱም ሌላውን ያንጸው” ሲል የሰጠውን ምክር የጉባኤ አባሎች ይከተላሉ። እንዲህ ያለው መመካከርና መተናነጽ እምነታችንን ይስልልናል። (1 ተሰሎንቄ 5:​11) በተጨማሪም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘታችን አምላክን እንደምንወድ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ እርሱን ለማወደስ ጥሩ አጋጣሚ ይሰጠናል።​— መዝሙር 35:​18

“ፍቅርን ልበሱት”

9. ይሖዋ ፍቅር በማሳየት ረገድ አርዓያ የሆነን እንዴት ነው?

9 ጳውሎስ “የፍጻሜ ማሠሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት” ሲል ጽፏል። (ቆላስይስ 3:​14) ይሖዋ በታላቅ ቸርነቱ ይህን ልብስ አዘጋጅቶልናል። እንዴት? ክርስቲያኖች ፍቅር ማሳየት የሚችሉት ፍቅር ከይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ፍሬዎች አንዱ ስለሆነ ነው። እነዚህን ፍሬዎች የሚሰጠው አምላክ ነው። (ገላትያ 5:​22, 23) ይሖዋ ራሱ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ሲል አንድያ ልጁን በመላክ ተወዳዳሪ የሌለው እጅግ ታላቅ ፍቅር አሳይቷል። (ዮሐንስ 3:​16) ይህ ታላቅ የሆነ የፍቅር መግለጫ ይህን ባሕርይ እንድናሳይ አብነት ይሆነናል። ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግም እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል” ሲል ጽፏል።​— 1 ዮሐንስ 4:​11

10. ‘ከመላው የወንድማማች ማኅበር’ የምንጠቀመው እንዴት ነው?

10 በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ መገኘትህ ፍቅር ለማሳየት ግሩም አጋጣሚ ይሰጥሃል። በእነዚህ ስብሰባዎች የተለያዩ ሰዎችን ታገኛለህ። ብዙዎቹን ወዲያው እንደምትወዳቸው አያጠራጥርም። እርግጥ ነው፣ ይሖዋን በሚያገለግሉ ሰዎች መካከል እንኳን የጠባይ ልዩነት ይኖራል። ከዚህ በፊት በጠባይ ወይም በፍላጎት የማይመስልህን ሰው ስትርቅ ኖረህ ይሆናል። ክርስቲያኖች ግን “መላውን የወንድማማች ማኅበር” መውደድ ይኖርባቸዋል። (1 ጴጥሮስ 2:​17 አዓት) ስለዚህ በመንግሥት አዳራሹ ከሚሰበሰቡት ሁሉ ጋር፣ ከአንተ ጋር በዕድሜ፣ በባሕርይ፣ በዘር ወይም በትምህርት ደረጃ ከሚለዩት ግለሰቦች ጭምር ለመተዋወቅ ዓላማህ ይሁን። ሁሉም የሚወደዱባቸው የየራሳቸው ጠባይ ያላቸው ሆነው ታገኛቸዋለህ።

11. በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ልዩ ልዩ ባሕርይ ማየትህ ቅር ሊያሰኝህ የማይገባው ለምንድን ነው?

11 በጉባኤው ውስጥ ያሉት ሰዎች በጠባያቸው የተለያዩ መሆናቸው ሊረብሽህ አይገባም። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል በአንድ አውራ መንገድ ላይ መኪና እየነዳህ ስትሄድ ከአንተ ጋር የሚጓዙ በርካታ ተሽከርካሪዎች አሉ እንበል። ሁሉም ተሽከርካሪዎች በአንድ ዓይነት ፍጥነት አይጓዙም፤ የሁሉም ይዞታ አንድ ዓይነት አይደለም። አንዳንዶቹ መኪኖች ብዙ ኪሎ ሜትር የሄዱ ሲሆን ሌሎቹ ግን አንተ እንደምትነዳው ተሽከርካሪ ብዙ ያልሠሩ ናቸው። ይሁን እንጂ ሁሉም ይህን የመሰለ ልዩነት ቢኖራቸውም በመንገዱ ላይ ይሽከረከራሉ። የአንድ ጉባኤ አባላት የሆኑ ግለሰቦችም እንዲሁ ናቸው። ሁሉም በአንድ ዓይነት ፍጥነት ክርስቲያናዊ ባሕርያትን አያዳብሩም። ከዚህም በላይ የሁሉም አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ሁኔታ አንድ ዓይነት አይደለም። አንዳንዶች ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን ሲያመልኩ የቆዩ ሲሆኑ አንዳንዶቹ በቅርቡ የጀመሩ ናቸው። ሆኖም ሁሉም “በአንድ ልብና በአንድ አሳብ” ተባብረው ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው ጎዳና በመጓዝ ላይ ናቸው። (1 ቆሮንቶስ 1:​10) ስለዚህ የጉባኤውን አባሎች ደካማ ጎኖች ሳይሆን ጠንካራ ጎናቸውን ተመልከት። እንዲህ ብታደርግ አምላክ በእርግጥ ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር እንደሆነ ስለ⁠ምትገነዘብ ልብህ በደስታ ይሞላል። አንተም እንደነዚህ ካሉት ሕዝቦች አንዱ ለመሆን እንደምትፈልግ አያጠራጥርም።​— 1 ቆሮንቶስ 14:​25

12, 13. (ሀ) በጉባኤው ውስጥ ያለ ሰው ቢጎዳህ ምን ልታደርግ ትችላለህ? (ለ) ቂም አለመያዝ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

12 የሰው ልጆች በሙሉ ፍጽምና የጎደላቸው ስለሆኑ በጉባኤው ውስጥ ያለ ግለሰብ ቅር የሚልህ ነገር ሊናገር ወይም ሊያደርግ ይችላል። (ሮሜ 3:​23) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው” በማለት ያለውን ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል። (ያዕቆብ 3:​2) አንድ ሰው ቅር ቢያሰኝህ ምን ይሰማሃል? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “የሰው አስተዋይነት ቁጣውን ያዘገይለታል፣ በደልንም ማለፍ ውበት ይሆንለታል” ይላል። (ምሳሌ 19:​11 አዓት) አስተዋይነት ሲባል ላይ ላዩን ከሚታየው አልፎ ውስጣዊ ሁኔታውን ማየት፣ አንድ ሰው አንድን ነገር ለመናገር ወይም ለማድረግ ምክንያት የሆነውን ነገር መረዳት ማለት ነው። አብዛኞቻችን ራሳችን ለሠራነው ስህተት ማሳበቢያ በማግኘት ረገድ በጣም አስተዋዮች ነን። ታዲያ ይህንኑ አስተዋይነታችንን ለምን የሌሎችን ጉድለት ለመረዳትና ለማለፍ አንጠቀምበትም?​— ማቴዎስ 7:​1–5፤ ቆላስይስ 3:​13

13 ይሖዋ ይቅር እንዲለን ከፈለግን እኛም ሌሎችን ይቅር ማለት እንደሚኖርብን ፈጽሞ መዘንጋት የለብህም። (ማቴዎስ 6:​9, 12, 14, 15) በእውነት የምንመላለስ ሰዎች ከሆንን ሌሎች ሰዎችን በፍቅር እንይዛቸዋለን። (1 ዮሐንስ 1:​6, 7፤ 3:​14–16፤ 4:​20, 21) ስለዚህ በጉባኤው ውስጥ ከሚገኝ አንድ ግለሰብ ጋር ብትጋጭ ይህን ግለሰብ እንድትቀየም የሚገፋፋህን ዝንባሌ ታግለህ አሸንፈው። ፍቅርን ከለበስክ ለችግሩ መፍትሔ ለማግኘት ትጥራለህ። ቅር ያሰኘኸው አንተ ከሆንክም ይቅርታ ከመጠየቅ ወደኋላ አትልም።​— ማቴዎስ 5:​23, 24፤ 18:​15–17

14. ምን ዓይነት ባሕርያት መልበስ ይኖርብናል?

14 መንፈሳዊ ልብሳችን ከፍቅር ጋር የቅርብ ተዛምዶ ያላቸውን ሌሎች ባሕርያት የሚጨምር መሆን አለበት። ጳውሎስ “ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ” ሲል ጽፏል። እነዚህ በፍቅር ውስጥ የሚካተቱ ባሕርያት አምላካዊ አቋም የሚያንጸባርቀው ‘አዲስ ሰውነት’ ክፍል ናቸው። (ቆላስይስ 3:​10, 12) ይህን ልብስ ለመልበስ ጥረት ታደርጋለህን? በተለይ ወንድማዊ ፍቅርን ከለበስክ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መለያ ምልክት የሆነው ባሕርይ ይኖርሃል፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል።​— ዮሐንስ 13:​35

ተረጋግቶና ተማምኖ መኖር የሚቻልበት ቦታ

15. ጉባኤው እንደ መጠለያ የሆነው እንዴት ነው?

15 በተጨማሪም ጉባኤው ጥላ ከለላ ሆኖ ስለሚያገለግል መረጋጋትና መተማመን ሊሰማህ ይችላል። በጉባኤው ውስጥ በአምላክ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የሚጣጣሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ታገኛለህ። ብዙዎቹ አንተ አሁን እየታገልካቸው ያሉትን መጥፎ ልማዶችና ዝንባሌዎች አሸንፈው ያስወገዱ ናቸው። (ቲቶ 3:​3) እነዚህ ሰዎች “እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም” የሚል ትእዛዝ የተሰጣቸው ስለሆኑ ሊረዱህ ይችላሉ። (ገላትያ 6:​2) እርግጥ፣ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን መንገድ የመከተል ኃላፊነት ዞሮ ዞሮ የሚወድቀው በአንተ ላይ ነው። (ገላትያ 6:​5፤ ፊልጵስዩስ 2:​12) ቢሆንም ይሖዋ አስደናቂ የሆነ እርዳታና ድጋፍ የምናገኝበትን የክርስቲያን ጉባኤ አዘጋጅቶልናል። ችግርህ የቱንም ያህል አስጨናቂ ቢሆን ድጋፍ ልታገኝበት የምትችል ጥሩ የእርዳታ ምንጭ አለህ። እርሱም በመከራና በዕጦት ጊዜ ከጎንህ የሚቆመው አፍቃሪ ጉባኤ ነው።​— ከሉቃስ 10:​29–37 እና ከሥራ 20:​35 ጋር አወዳድር።

16. የጉባኤ ሽማግሌዎች ምን እርዳታ ይሰጣሉ?

16 አንተን ለመርዳት ከሚሯሯጡት ሰዎች መካከል መንጋውን በፈቃደኝነትና በደስታ የሚጠብቁ “ስጦታ የሆኑ ወንዶች” የተባሉ ሽማግሌዎች ወይም የበላይ ተመልካቾች ይገኛሉ። (ኤፌሶን 4:​8, 11, 12 አዓት፤ ሥራ 20:​28፤ 1 ጴጥሮስ 5:​2, 3) ኢሳይያስ ስለ እነርሱ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “ሰውም ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፣ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፣ በበረሀም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ ይሆናል።”​— ኢሳይያስ 32:​2

17. (ሀ) ኢየሱስ በተለይ ምን ዓይነት እርዳታ ለመስጠት ይፈልግ ነበር? (ለ) አምላክ ለሕዝቦቹ ምን ነገር አዘጋጅቶ እንደሚያቀርብላቸው ቃል ገብቶ ነበር?

17 ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ ከሃይማኖታዊ መሪዎች ፍቅራዊ የበላይ ጥበቃ አያገኙም ነበር። የሕዝቡ ሁኔታ በጣም ስላሳዘነው በተለይ በመንፈሳዊ ሊረዳቸው ፈለገ። “እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም” ስለ ነበር ኢየሱስ አዘነላቸው። (ማቴዎስ 9:​36) ይህ ጥቅስ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ እርዳታና መጽናኛ የሚሰጣቸው ሳይኖር አስጨናቂ በሆኑ ችግሮች የሚማቅቁት የዘመናችን ብዙ ሰዎች የሚገኙበትን ሁኔታ ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። የይሖዋ ሕዝቦች ግን “የሚጠብቋቸውን እረኞች አስነሣላቸዋለሁ፣ ዳግመኛም አይፈሩምና አይደነግጡም፣ ከእነርሱም አንድ አይጎድልም” ብሎ ይሖዋ ራሱ ቃል ስለገባላቸው መንፈሳዊ እርዳታ ያገኛሉ።​— ኤርምያስ 23:​4

18. መንፈሳዊ እርዳታ ካስፈለገን ከሽማግሌዎች አንዱን ቀርበን ማነጋገር የሚኖርብን ለምንድን ነው?

18 በጉባኤው ውስጥ ያሉትን የተሾሙ ሽማግሌዎች ተዋወቃቸው። እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለበላይ ተመልካቾች ያወጣቸውን ብቃቶች የሚያሟሉ በመሆናቸው ከአምላክ የሚገኘውን እውቀት ሥራ ላይ በማዋል ረገድ ብዙ ተሞክሮ ያላቸው ናቸው። (1 ጢሞቴዎስ 3:​1–7፤ ቲቶ 1:​5–9) ለማሸነፍ የምትታገለው ልማድ ወይም ከአምላክ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ ጠባይ ካለህ ከመካከላቸው አንዱን ቀርበህ ከማነጋገር ወደኋላ አትበል። እነዚህ ሽማግሌዎች “የተጨነቁትን ነፍሳት በሚያጽናና ቃል ተናገሯቸው፣ ደካሞችን ደግፉ፣ ሁሉን ታገሡ” የሚለውን የጳውሎስ ምክር ሥራ ላይ የሚያውሉ ሆነው ታገኛቸዋለህ።​— 1 ተሰሎንቄ 2:​7, 8፤ 5:​14 አዓት

ከይሖዋ ሕዝብ ጋር ተረጋግተህና ተማምነህ ኑር

19. ይሖዋ በድርጅቱ ውስጥ ተጠልለው ለመኖር ለሚፈልጉ ሁሉ ምን ዓይነት በረከት ሰጥቷል?

19 ዛሬ የምንገኝበት ሁኔታ ከፍጽምና በጣም የራቀ ቢሆንም ይሖዋ መንፈሳዊ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ አብዝቶ እያቀረበልን ነው። በገነት ውስጥ ከሚገኙት ሥጋዊ በረከቶች ተቋዳሽ ለመሆን ግን የአምላክ አዲስ ዓለም የሚቋቋምበትን ጊዜ መጠበቅ እንደሚኖርብን የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ የይሖዋ ድርጅት አባላት የሆኑ ሁሉ በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ተረጋግተውና ተማምነው በደስታ ይኖራሉ። ሕዝቅኤል ስለ እነዚህ ሰዎች ሲተነብይ “ተዘልለውም ይቀመጣሉ የሚያስፈራቸውም የለም” ብሏል።​— ሕዝቅኤል 34:​28፤ መዝሙር 4:​8

20. ይሖዋ ለአምልኮቱ ስንል ምንም ነገር ብንሠዋ መልሶ የሚክሰን እንዴት ነው?

20 ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ በኩል ፍቅራዊ የሆኑ መንፈሳዊ ዝግጅቶችን ስላደረገልን በጣም አመስጋኞች መሆን ይገባናል። ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ተቀራረብ። አምላክ የሚሰጠውን እውቀት ለመቅሰም በምታደርገው ጥረት ምክንያት ዘመዶችህ ወይም ወዳጆችህ የሚናገሩትን በመፍራት ወደኋላ አትበል። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መቀራረብህን ወይም በመንግሥት አዳራሹ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ መገኘትህን አንዳንዶች ይቃወሙ ይሆናል። ነገር ግን አምላክ ለአምልኮቱ ስትል ለምትሠዋው ማንኛውም ነገር አብዝቶ ይክስሃል። (ሚልክያስ 3:​10) ከዚህም በላይ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፣ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንም እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፣ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።” (ማርቆስ 10:​29, 30) ትተህ የመጣኸው ነገር ወይም የተቋቋምካቸው ችግሮች ምንም ያህል ብዙ ቢሆኑ በአምላክ ሕዝቦች መካከል የሚያስደስቱ ባልንጀሮችና መንፈሳዊ ደኅንነት አግኝተህ ለመኖር ትችላለህ።

እውቀትህን ፈትሽ

“ታማኝና ልባም ባሪያ” ማን ነው?

ይሖዋ እኛን በመንፈሳዊ ለመመገብ ምን ዝግጅቶች አድርጎልናል?

በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሰዎች እንዴት ሊረዱን ይችላሉ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 165 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]