በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላካዊ አኗኗር ደስታ የሚያስገኘው ለምንድን ነው?

አምላካዊ አኗኗር ደስታ የሚያስገኘው ለምንድን ነው?

ምዕራፍ 13

አምላካዊ አኗኗር ደስታ የሚያስገኘው ለምንድን ነው?

1. የይሖዋ መንገድ ደስታ ያስገኛል ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?

ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” ነው፤ አንተም በሕይወትህ እንድትደሰት ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 1:​11 አዓት) በይሖዋ መንገዶች ብትመላለስ ራስህን ትጠቅማለህ፤ እንዲሁም ሁልጊዜ እንደሚፈስ ወንዝ የጠለቀና ዘላለማዊ የሆነ ሰላም ታገኛለህ። በተጨማሪም አንድ ሰው በአምላክ መንገድ ቢመላለስ “እንደ ባሕር ሞገድ” የማያቋርጥ የጽድቅ ሥራ ሊሠራ ይችላል። ይህም እውነተኛ ደስታ ያስገኛል።​— ኢሳይያስ 48:​17, 18

2. ክርስቲያኖች አንዳንድ ጊዜ ሰዎች መጥፎ ነገር ቢፈጽሙባቸውም ደስተኞች ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው?

2 ‘ትክክለኛ የሆነውን ነገር በማድረጋቸው ሥቃይ የደረሰባቸው ሰዎች አሉ’ በማለት የተቃውሞ ሐሳብ የሚሰነዝሩ ይኖሩ ይሆናል። ነገሩ እውነት ነው፤ በኢየሱስ ሐዋርያት ላይ ይህን የመሰለ ነገር ደርሶ ነበር። ይሁን እንጂ ስደት ቢደርስባቸውም ደስ እያላቸው ወጥተው “ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ” መስበካቸውን ቀጥለዋል። (ሥራ 5:​40–42) ከዚህ ትልቅ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን። አንደኛ፣ አምላካዊ ኑሮ መኖራችን በሰዎች ዘንድ ሁልጊዜ በጥሩ ዓይን እንደምንታይ ዋስትና እንደማይሆነን እንረዳለን። እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ “በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” ሲል ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​12) ይህ የሆነበት ምክንያት ሰይጣንና የሰይጣን ዓለም አምላካዊ አኗኗር ያላቸውን ሰዎች ስለሚቃወሙ ነው። (ዮሐንስ 15:​18, 19፤ 1 ጴጥሮስ 5:​8) ይሁን እንጂ እውነተኛ ደስታ ውጪያዊ በሆኑ ነገሮች ላይ የተመካ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ትክክል የሆነውን ነገር በማድረግ ላይ እንደሆንና በዚህም ምክንያት አምላክ ደስ እንደሚሰኝብን እርግጠኛ ከመሆን የሚመጣ ነው።​— ማቴዎስ 5:​10–12፤ ያዕቆብ 1:​2, 3፤ 1 ጴጥሮስ 4:​13, 14

3. የይሖዋ አምልኮ የአንድን ሰው አኗኗር እንዴት ሊነካው ይገባል?

3 አልፎ አልፎ ብቻ የአምልኮ ተግባር በመፈጸም የአምላክን ሞገስ ሊያገኙና በሌሎች ጊዜያት ግን ፈጽመው ሊረሱት እንደሚችሉ የሚሰማቸው ሰዎች አሉ። እውነተኛው የይሖዋ አምልኮ ከዚህ የተለየ ነው። አንድ ሰው ከዕለት ዕለት፣ ከዓመት እስከ ዓመት ከእንቅልፍ ነቅቶ በሚንቀሳቀስባቸው ሰዓታት የሚያደርጋቸውን ነገሮች በሙሉ ይነካል። ‘መንገድ’ ተብሎ የተጠራውም በዚህ ምክንያት ነው። (ሥራ 19:​9፤ ኢሳይያስ 30:​21) እውነተኛው አምልኮ ከአምላክ ቃል ጋር የሚጣጣም ነገር ማድረግንና መናገርን የሚጠይቅ አምላካዊ አኗኗር ነው።

4. የአምላክን መንገዶች እየተከተሉ ለመኖር ለውጥ ማድረግ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?

4 መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመሩ አዳዲስ ሰዎች ይሖዋን ለማስደሰት በሕይወታቸው ውስጥ አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ እንደሚኖርባቸው ሲገነዘቡ ‘አምላካዊ አኗኗር ይህን ያህል ልንጨነቅለት የሚገባን አኗኗር ነውን?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። አዎን፣ ልንጨነቅለት የሚገባ አኗኗር እንደሆነ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። ለምን? ምክንያቱም “እግዚአብሔር ፍቅር ነው።” በመሆኑም መንገዶቹ ሁሉ ለእኛ ጥቅም የተዘጋጁ ናቸው። (1 ዮሐንስ 4:​8) በተጨማሪም አምላክ ጥበበኛ ስለሆነ ለእኛ የሚበጀንን ያውቃል። ይሖዋ አምላክ ሁሉን ቻይ በመሆኑም ማንኛውንም መጥፎ ልማድ በማስወገድ እርሱን ለማስደሰት ያለንን ፍላጎት እንድንፈጽም ኃይል ሊሰጠን ይችላል። (ፊልጵስዩስ 4:​13) አምላካዊ አኗኗር የሚያካትታቸውን አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመልከትና እነርሱን በሥራ ላይ ማዋል እንዴት ደስታ እንደሚያስገኝልን እንይ።

ሐቀኝነት ደስታ ያመጣል

5. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መዋሸትና ስለ መስረቅ ምን ይላል?

5 ይሖዋ “የእውነት አምላክ” ነው። (መዝሙር 31:​5) አንተም የእርሱን አርዓያ ለመከተልና በእውነተኝነትህ ለመታወቅ እንደምትፈልግ አያጠራጥርም። ሐቀኝነት ለራስህ አክብሮት እንዲኖርህና በራስህ እንድትደሰት ያስችልሃል። ይሁን እንጂ በዚህ ኃጢአተኛ ዓለም ውስጥ ማጭበርበርና ሸፍጥ በጣም የተስፋፋ በመሆኑ ክርስቲያኖች ቀጥሎ ያለውን ማሳሰቢያ ልብ ማለት አስፈልጓቸዋል:- “ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፣ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም።” (ኤፌሶን 4:​25, 28) ተቀጥረው የሚ⁠ሠሩ ክርስቲያኖች የየዕለቱን ተግባራቸውን በሐቀኝነት ተግተው ያከናውናሉ። አሠሪያቸው ካልፈቀደላቸው በስተቀር የአሠሪያቸውን ንብረት አይወስዱም። ይሖዋን የሚያመልክ ሰው በሥራ ቦታም ሆነ በትምህርት ቤት “በሁሉ ነገር ሐቀኛ” መሆን ይኖርበታል። (ዕብራውያን 13:​18 አዓት) የመዋሸት ወይም የመስረቅ ልማድ ያለበት ሰው የአምላክን ሞገስ ለማግኘት አይችልም።​— ዘዳግም 5:​19፤ ራእይ 21:​8

6. አምላካዊ አኗኗር ያለው አንድ ሰው ሐቀኛ መሆኑ ይሖዋን ሊያስከብር የሚችለው እንዴት ነው?

6 ሐቀኛ መሆን ብዙ በረከቶች ያስገኛል። ሴሊና ይሖዋ አምላክንና የይሖዋን የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች የምትወድ ችግረኛ አፍሪካዊት መበለት ነች። ከዕለታት አንድ ቀን ብዙ ገንዘብና የባንክ ደብተር የያዘ ቦርሳ ወድቆ አገኘች። የስልክ ማውጫ በመጠቀም የቦርሳውን ባለቤት አገኘች። የቦርሳው ባለቤት ንብረቱን የተዘረፈ ባለ ሱቅ ነበር። ሴሊና በጣም ሕመምተኛ ብትሆንም መጥታ በቦርሳው ውስጥ የነበረውን ገንዘብ በሙሉ ምንም ሳታጎድል ስታስረክበው ሰውዬው ዓይኑን ማመን አቃተው። “እንደዚህ ላለው የሐቀኝነት አድራጎት ተገቢውን ዋጋ መክፈል ያስፈልጋል” አለና በርከት ያለ ገንዘብ ሰጣት። ከዚህም በላይ ሰውዬው የሴሊናን ሃይማኖት አደነቀ። አዎን፣ የሐቀኝነት ድርጊቶች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ያስጌጣሉ፣ ይሖዋ አምላክን ያስከብራሉ፣ ሐቀኛ አምላኪዎቹንም ደስተኛ ያደርጋሉ።​— ቲቶ 2:​10፤ 1 ጴጥሮስ 2:​12

ለጋስ መሆን ደስታ ያመጣል

7. ቁማር መጫወት ስህተት የሆነው ለምንድን ነው?

7 ለጋስ መሆን ደስታ የሚያስገኝ ሲሆን ስግብግቦች ግን “የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።” (1 ቆሮንቶስ 6:​10) በጣም ከተለመዱት የስግብግብነት መግለጫዎች አንዱ ቁማር ነው። ቁማር በሌሎች ኪሣራ ገንዘብ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት ነው። ይሖዋ “ነውረኛ ረብ” ለማግኘት የሚስገበገቡ ሰዎችን አይቀበልም። (1 ጢሞቴዎስ 3:​8) ቁማር በሕግ የተፈቀደ ቢሆን ወይም አንድ ሰው ቁማር የሚጫወተው ለመዝናናት ብቻ ብሎ ቢሆንም እንኳ የቁማር ሱስ ሊይዘውና የብዙ ሰዎችን ሕይወት ያበላሸው የዚህ ልማድ አራማጅ ሊሆን ይችላል። ቁማር አብዛኛውን ጊዜ በቁማርተኛው ቤተሰብ ላይ ከባድ ችግር ያስከትላል። እንደ ልብስና ምግብ የመሰሉትን አስፈላጊ ነገሮች የሚገዙበትን ገንዘብ ሊያሳጣቸው ይችላል።​— 1 ጢሞቴዎስ 6:​10

8. ኢየሱስ በልግስና ረገድ ጥሩ ምሳሌ የተወልን እንዴት ነው? እኛስ ለጋሶች ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው?

8 ክርስቲያኖች ለጋስ መሆንን ስለሚወዱ ሌሎች ሰዎችን፣ በተለይም ችግር የደረሰባቸውን ሌሎች ክርስቲያኖች በመርዳት ይደሰታሉ። (ያዕቆብ 2:​15, 16) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት አምላክ ለሰው ልጆች ያሳየውን ልግስና ተመልክቶአል። (ሥራ 14:​16, 17) ኢየሱስ ራሱ ለሰው ልጆች ጊዜውን፣ ችሎታውን፣ ሕይወቱን እንኳን ሳይቀር ለግሷል። ስለዚህም “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ” አዓት] ነው” ለማለት ችሏል። (ሥራ 20:​35) በተጨማሪም ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ የገንዘብ ማጠራቀሚያ ሣጥን ውስጥ ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች የጨመረችው መበለት “ትዳርዋን ሁሉ” በመስጠቷ ስለ ልግስናዋ አመስግኗታል። (ማርቆስ 12:​41–44) የጥንቶቹ እስራኤላውያንና የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ለጉባኤውና ለመንግሥቱ ሥራ ቁሳዊ ድጋፍ በመስጠት ረገድ ባሳዩት ቸርነት ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑን ይችላሉ። (1 ዜና መዋዕል 29:​9፤ 2 ቆሮንቶስ 9:​11–14) የዘመናችን ክርስቲያኖችም ለእነዚህ ዓላማዎች ቁሳዊ አስተዋጽኦ ከማድረግ በተጨማሪ ለአምላክ ውዳሴ ያቀርባሉ፣ ሕይወታቸውንም እሱን ለማገልገል ይጠቀማሉ። (ሮሜ 12:​1፤ ዕብራውያን 13:​15) ይሖዋም ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ችሎታዎቻቸውን፣ ገንዘባቸውን ጭምር እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍና ምድር አቀፉን የመንግሥት ምሥራች የመስበክ ሥራ ለማስፋፋት ስለሚጠቀሙበት ይባርካቸዋል።​— ምሳሌ 3:​9, 10

ደስታ የሚያስገኙ ሌሎች ነገሮች

9. የአልኮል መጠጦችን ከልክ በላይ መጠጣት ስህተት የሆነው ለምንድን ነው?

9 ክርስቲያኖች ደስተኛ ለመሆን ከፈለጉ ‘የማሰብ ችሎታቸውን መጠበቅ’ ያስፈልጋቸዋል። (ምሳሌ 5:​1, 2 አዓት) ለዚህም የአምላክን ቃል እንዲሁም ጤናማ የሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማንበብና ማሰላሰል ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም ሊወገዱ የሚገባቸው ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው የአልኮል መጠጦችን አብዝቶ ቢጠጣ አስተሳሰቡን መቆጣጠር ሊያቅተው ይችላል። ብዙ ሰዎች እንዲህ ባለው ሁኔታ ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ይፈጽማሉ፣ ጠበኞች ይሆናሉ፣ ሕይወት እስከ ማጥፋት ለሚያደርሱ አደጋዎች ምክንያት ይሆናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ሰካራሞች የአምላክን መንግሥት አይወርሱም ማለቱ አያስደንቅም! (1 ቆሮንቶስ 6:​10) እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘ጤናማ አእምሮ’ ይዘው ለመኖር ስለሚፈልጉ ከስካር ይርቃሉ። ይህም ደስተኞች እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።​— ቲቶ 2:​2–6

10. (ሀ) ክርስቲያኖች ትንባሆ የማያጨሱት ለምንድን ነው? (ለ) ሱስ የሆኑ ልማዶችን በማቆም ምን ጥቅሞች ይገኛሉ?

10 ንጹሕ አካል ደስተኛ ለመሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል። ብዙዎች ግን ጎጂ ለሆኑ ነገሮች ሱሰኞች ይሆናሉ። ለምሳሌ ያህል ትንባሆ ማጨስን እንውሰድ። የዓለም የጤና ድርጅት ትንባሆ ማጨስ “በየዓመቱ ሦስት ሚልዮን ሰዎች ይገድላል” ሲል ሪፖርት አድርጓል። ሲጋራ ማቆም በመጀመሪያ ላይ አንዳንድ የስሜት ሥቃይ ስለሚያስከትል ከትንባሆ ሱስ መላቀቅ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ከዚህ በፊት ያጨሱ የነበሩ ብዙ ሰዎች ማጨስ በማቆማቸው ጤንነታቸው እንደተሻሻለላቸውና ለቤታቸው የሚያውሉት ተጨማሪ ገንዘብ እንዳተረፉ ይናገራሉ። በእርግጥም ከትንባሆና ከሌሎች ጎጂ ነገሮች ሱስ መላቀቅ ንጹሕ አካል፣ ንጹሕ ሕሊናና እውነተኛ ደስታ ለማግኘት አስተዋጽኦ ያደርጋል።​— 2 ቆሮንቶስ 7:​1

ከጋብቻ ሊገኝ የሚችል ደስታ

11. ሕጋዊነትና ዘላቂነት ያለው የተከበረ ጋብቻ ለመመሥረት ምን ያስፈልጋል?

11 ባልና ሚስት ሆነው አንድ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ጋብቻቸው በተገቢው ሥርዓት በመንግሥት ባለ ሥልጣኖች የተመዘገበ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። (ማርቆስ 12:​17) በተጨማሪም በጋብቻ ሰንሰለት ውስጥ መግባት ከባድ ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። እርግጥ አንደኛው ባለትዳር ሆን ብሎ ቤተሰቡን የማይረዳ፣ አካላዊና ስሜታዊ ሥቃይ የሚያደርስ ወይም የትዳር ጓደኛውን መንፈሳዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ ተለያይቶ መኖር አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 5:​8፤ ገላትያ 5:​19–21) በ1 ቆሮንቶስ 7:​10–17 ላይ የሚገኙት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ባለ ትዳሮች አብረው እንዲኖሩ ያበረታታሉ። እርግጥ፣ እውነተኛ ደስታ ለማግኘት ከፈለጉ አንዳቸው ለሌላው ታማኝ መሆን ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል” ብሏል። (ዕብራውያን 13:​4) “መኝታ” የሚለው ቃል ሕጋዊ በሆነ ጋብቻ በተሳሰሩ ወንድና ሴት መካከል የሚደረገውን ሩካቤ ሥጋ ያመለክታል። ማንኛውም ሌላ ዓይነት ሩካቤ ሥጋ፣ ከአንድ ሚስት በላይ ማግባትም ጭምር “በሁሉ ዘንድ ክቡር” ነው ሊባል አይችልም። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ከጋብቻ በፊት የሚፈጸመውን ሩካቤ ሥጋና ግብረ ሰዶምን ያወግዛል።​— ሮሜ 1:​26, 27፤ 1 ቆሮንቶስ 6:​18

12. ዝሙት ከሚያስገኛቸው መጥፎ ፍሬዎች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

12 ዝሙት ቅጽበታዊ የአካል ደስታ ሊያስገኝ ይችል ይሆናል፤ እውነተኛ ደስታ ግን አያስገኝም። አምላክን ከማሳዘኑም በላይ በግለሰቡ ሕሊና ላይ ጠባሳ ሊጥል ይችላል። (1 ተሰሎንቄ 4:​3–5) ሕጋዊ ያልሆነ ሩካቤ ሥጋ ከሚያስከትላቸው መጥፎ ውጤቶች መካከል ኤድስና ሌሎች የአባለ ዘር በሽታዎች ይገኛሉ። አንድ የሕክምና ሪፖርት “በየዓመቱ በመላው ዓለም 250 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች በጨብጥ፣ 50 ሚልዮን የሚያክሉ ደግሞ በቂጥኝ በሽታ እንደሚለከፉ ይገመታል” ብሏል። ያልተፈለጉ እርግዝናዎችም አሉ። ኢንተርናሽናል ፕላንድ ፓረንትሁድ ፌደሬሽን የተባለው ድርጅት በመላው ዓለም ከ15 እስከ 19 ዓመት ዕድሜ የሚገኙ ከ15 ሚልዮን በላይ ልጃገረዶች በየዓመቱ እንደሚያረግዙ ሪፖርት አድርጓል። ከእነዚህ መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ያስወርዳሉ። አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው በአንድ የአፍሪካ አገር በወጣት ዕድሜያቸው ከሚሞቱ ልጃገረዶች መካከል 72 በመቶ የሚያክሉት የሚሞቱት በውርጃ ምክንያት በሚደርሱ ችግሮች ሳቢያ ነው። አንዳንድ ዘማውያን ከበሽታና ከእርግዝና ሊያመልጡ ቢችሉም ከስሜታዊ ጉዳት ግን ሊያመልጡ አይችሉም። ብዙዎች ለራሳቸው ያላቸው ግምት ዝቅ ይልባቸዋል። እንዲያውም ራሳቸውን እስከ መጥላት ይደርሳሉ።

13. ምንዝር ምን ተጨማሪ ችግሮች ያስከትላል? ዝሙትና ምንዝር መፈጸማቸውን የሚቀጥሉ ሁሉ ምን ይጠብቃቸዋል?

13 ምንዝር በይቅርታ ሊታለፍ ቢችልም በደል ያልፈጸመው የትዳር ጓደኛ ከፈለገ ሊፈታ የሚያስችለው ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ይኖረዋል። (ማቴዎስ 5:​32፤ ከሆሴዕ 3:​1–5 ጋር አወዳድር።) ጋብቻ እንዲህ ባለው የሥነ ምግባር ጉድለት ምክንያት ሲፈርስ በተበዳዩ የትዳር ጓደኛና በልጆች ላይ በቀላሉ የማይሽር የስሜት ጠባሳ ሊተው ይችላል። የአምላክ ቃል ለሰብዓዊው ቤተሰብ ጥቅም ሲል ንስሐ የማይገቡ አመንዝሮችና ዘማውያን የቅጣት ፍርድ እንደሚደርስባቸው ያመለክታል። ከዚህም በላይ የጾታ ብልግና እየፈጸሙ የሚኖሩ ሁሉ “የእግዚአብሔርን መንግሥት” እንደማይወርሱ በግልጽ ይናገራል።​— ገላትያ 5:​19, 21

‘የዓለም ክፍል አለመሆን’

14. (ሀ) አምላክን የሚፈራ ሰው ሊያስወግዳቸው የሚገቡ አንዳንዳድ የጣዖት አምልኮ ዓይነቶች ምንድን ናቸው? (ለ) በዮሐንስ 17:​14 እና በኢሳይያስ 2:​4 ላይ ምን መመሪያ ተሰጥቷል?

14 ይሖዋን ለማስደሰትና የመንግሥቱን በረከቶች ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ ይርቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ማንኛውንም ዓይነት ምስል፣ የክርስቶስንም ሆነ የኢየሱስ እናት የሆነችውን የማርያምን ምስል ጭምር ሠርቶ ማምለክ ስህተት እንደሆነ ይናገራል። (ዘጸአት 20:​4, 5፤ 1 ዮሐንስ 5:​21) ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ቅርጾችን፣ መስቀሎችንና ምስሎችን ቅዱስ አድርገው በመመልከት አያከብሩም። በተጨማሪም ለባንዲራ አምልኮ አከል ክብር እንደመስጠትና ብሔራትን የሚያወድሱ መዝሙሮችን እንደመዘመር ካሉት ስውር የሆኑ የጣዖት አምልኮ ዓይነቶች ይርቃሉ። እንደነዚህ ያሉትን ድርጊቶች እንዲፈጽሙ ተጽእኖ ሲደርስባቸው ኢየሱስ “ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ” በማለት ለሰይጣን የተናገረውን ቃል ያስታውሳሉ። (ማቴዎስ 4:​8–10) ኢየሱስ ተከታዮቹ “ከዚህ ዓለም” እንዳይደሉ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:​14) ይህ ማለት በፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ መሆንና ከኢሳይያስ 2:​4 ጋር የሚጣጣም ሰላማዊ ኑሮ መኖር አለባቸው ማለት ነው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “[ይሖዋ አምላክ] በአሕዛብም መካከል ይፈርዳል፣ በብዙ አሕዛብም ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።”

15. ታላቂቱ ባቢሎን ምንድን ነች? ብዙ አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችስ ከእርስዋ ለመውጣት ምን ያደርጋሉ?

15 በተጨማሪም ‘ከዓለም ክፍል አለመሆን’ ዓለም አቀፍ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ ጋር የነበረንን ግንኙነት ማቋረጥ ማለት ነው። ንጹሕ ያልሆነ አምልኮ ከጥንቷ ባቢሎን ተነስቶ በምድር ዙሪያ በመሰራጨት በሕዝቦች ላይ ሰልጥኗል። “ታላቂቱ ባቢሎን” ከአምላክ ከሚገኘው እውቀት ጋር የማይስማሙ መሠረተ ትምህርቶችና ልማዶች ያሏቸውን ሃይማኖቶች በሙሉ ታጠቃልላለች። (ራእይ 17:​1, 5, 15) ማንኛውም ታማኝ የሆነ ይሖዋን የሚያመልክ ሰው የተለያዩ ሃይማኖቶች በሚያከናውኑት አምልኮ በመካፈል ወይም ከማንኛውም የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል ጋር መንፈሳዊ ኅብረት በማድረግ ቅልቅል ሃይማኖት ለመያዝ አይፈልግም። (ዘኁልቁ 25:​1–9፤ 2 ቆሮንቶስ 6:​14) በዚህም ምክንያት ብዙ አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አባል ለነበሩባቸው ሃይማኖታዊ ድርጅቶች የስንብት ደብዳቤ ይልካሉ። ይህም “ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኩስንም አትንኩ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ:- እኔም እቀበላችኋለሁ፣ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ” በሚለው ቃል መሠረት ከእውነተኛው አምላክ ጋር የቅርብ ዝምድና እንዲመሠርቱ አስችሏቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 6:⁠17፤ ራእይ 18:​4, 5) አንተስ በሰማያዊ አባታችን ዘንድ ይህን የመሰለ ተቀባይነት ማግኘት የምትጓጓለት ነገር አይደለምን?

የዓመት በዓሎችን ተገቢነት መመዘን

16. እውነተኛ ክርስቲያኖች ገናን የማያከብሩት ለምንድን ነው?

16 አምላካዊ ኑሮ መኖር አብዛኛውን ጊዜ ከባድ ሸክም ከሚጭኑ ዓለማዊ በዓላት ይገላግለናል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የተወለደበትን ትክክለኛ ቀን አይገልጽልንም። አንዳንዶች ‘ኢየሱስ የተወለደው ታኅሣሥ 25 ቀን ወይም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ታኅሣሥ 29 ቀን አይደለም እንዴ?’ ብለው በመገረም ይጠይቁ ይሆናል። ይህ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ የሞተው በ33 ዓመት ተኩል ዕድሜው በ33 እዘአ በሚያዝያ ወር መጀመሪያ አካባቢ ነው። ከዚህም በላይ ኢየሱስ በተወለደበት ጊዜ “መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ።” (ሉቃስ 2:​8) በእስራኤል አገር በታኅሣሥ ወር መጨረሻ ላይ ዝናብ የሚበዛበትና በጎች በቤት ውስጥ ከክረምቱ አየር ተጠልለው የሚያድሩበት ቀዝቃዛ ወቅት ነው። ታኅሣሥ 25 ሮማውያን የፀሐይ አምላክ የተወለደበት ቀን ነው ብለው ያከብሩት የነበረ ቀን ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖረ ከበርካታ መቶ ዘመናት በኋላ ከሃዲ ክርስቲያኖች ይህ ቀን የኢየሱስ የልደት ቀን ተብሎ እንዲከበር ወሰኑ። በዚህ ምክንያት እውነተኛ ክርስቲያኖች ገናንም ሆነ ማንኛውንም በሐሰት ሃይማኖታዊ እምነቶች ላይ የተመሠረተ በዓል አያከብሩም። አምልኮታቸው ለይሖዋ ብቻ የተወሰነ በመሆኑም ኃጢአተኛ የሰው ልጆች ወይም ብሔራት እንደ ጣዖት ተቆጥረው እንዲመለኩ የሚያደርጉ በዓሎችን አያከብሩም።

17. አምላክን የሚፈሩ ሰዎች የልደት ቀን የማይደግሱት ለምንድን ነው? ቢሆንም ክርስቲያን ልጆች ደስተኞች የሆኑት ለምንድን ነው?

17 መጽሐፍ ቅዱስ ለይቶ የሚጠቅሳቸው ሁለት የልደት በዓሎች አሉ። ሁለቱም አምላክን የማያመልኩ ሰዎች ያከበሯቸው በዓሎች ናቸው። (ዘፍጥረት 40:​20–22፤ ማቴዎስ 14:​6–11) ቅዱሳን ጽሑፎች ፍጹም ሰው የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት ቀን ለይተው የማይገልጹልን ከሆነ ፍጹማን ላልሆኑ ሰዎች የልደት ቀን ልዩ ትኩረት የምንሰጥበት ምን ምክንያት አለ? (መክብብ 7:​1) እርግጥ፣ አምላክን እያከበሩ የሚኖሩ ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽ የተወሰነ ቀን አይጠብቁም። አንዲት የ13 ዓመት ክርስቲያን ልጃገረድ “እኔና ቤተሰቤ ብዙ የሚያስደስቱ ነገሮችን አብረን እንሠራለን። . . . ከወላጆቼ ጋር በጣም እቀራረባለሁ። ሌሎች ልጆች ዓመት በዓሎችን ለምን እንደማላከብር ሲጠይቁኝ ሁሉም ቀን ለእኔ ዓመት በዓል እንደሆነ እነግራቸዋለሁ” ብላለች። አንድ የ17 ዓመት ክርስቲያን ወጣት “በእኛ ቤት ስጦታ የምንሰጣጠው ሙሉውን ዓመት ነው” ብሏል። ስጦታ ይበልጥ አስደሳች የሚሆነው በፍላጎት ሲደረግ ነው።

18. ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲያከብሩ ያዘዘው የትኛውን ዓመታዊ ቀን ብቻ ነው? ይህስ ምን ነገር ያስታውሰናል?

18 አምላካዊ አኗኗር የሚከተሉ ሰዎች በየዓመቱ የሚያከብሩት አንድ ቀን አለ። ይህም ቀን ብዙ ጊዜ የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ቀን ተብሎ የሚጠራው የጌታ እራት ነው። ኢየሱስ ስለዚህ እራት ተከታዮቹን ሲያዝ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሏል። (ሉቃስ 22:​19, 20፤ 1 ቆሮንቶስ 11:​23–25) ኢየሱስ ይህን እራት ኒሳን 14 ቀን በ33 እዘአ ምሽት ላይ ባቋቋመ ጊዜ የተጠቀመው ኃጢአት የሌለበትን ሰብዓዊ አካሉንና ፍጹም የሆነውን ደሙን በሚወክሉ ያልቦካ ቂጣና ቀይ የወይን ጠጅ ነበር። (ማቴዎስ 26:​26–29) ከእነዚህ ምሳሌያዊ ነገሮች የሚካፈሉት በአምላክ ቅዱስ መንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው። እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ወደ አዲሱ ቃል ኪዳንና ወደ መንግሥቱ ቃል ኪዳን የገቡ ሲሆን ሰማያዊ ተስፋ አላቸው። (ሉቃስ 12:​32፤ 22:​20, 28–30፤ ሮሜ 8:​16, 17፤ ራእይ 14:​1–5) ይሁን እንጂ በአይሁዳውያን የቀን አቆጣጠር መሠረት ኒሳን 14 ምሽት በሚከበረው በዓል ላይ የሚገኙ ሁሉ የሚያገኟቸው ጥቅሞች አሉ። ተሰብሳቢዎቹ መለኮታዊ ሞገስ ያገኙ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ያስቻለውን ኃጢአት የሚያስተሠርይ ቤዛዊ መሥዋዕት ለማዘጋጀት ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳዩትን ከፍተኛ ፍቅር ለማስታወስ ጥሩ አጋጣሚ ያገኛሉ።​— ማቴዎስ 20:​28፤ ዮሐንስ 3:​16

ሥራና መዝናኛ

19. ክርስቲያኖች ኑሯቸውን ለማሸነፍ በሚጥሩበት ጊዜ ምን ፈተና ሊያጋጥማቸው ይችላል?

19 እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማግኘት ተግተው የመሥራት ግዴታ አለባቸው። የቤተሰብ ራስ የሆኑ ወንዶች ይህን ለማከናወን መቻላቸው እርካታ ያስገኝላቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 4:​11, 12) እርግጥ፣ አንድ ክርስቲያን የተቀጠረበት ሥራ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ ከሆነ ደስታ ያሳጣዋል። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መስፈርቶች ጋር የሚስማማ ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆንበት ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ሠራተኞች ደንበኞችን እንዲያታልሉ ይታዘዛሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ታማኝ የሆነ ሠራተኛቸውን እንዳያጡ ሲሉ ሐቀኝነቱን ጠብቆ ለመሥራት የሚፈልገውን ሠራተኛ ሕሊና የሚያከብሩ ብዙ አሠሪዎች አሉ። በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን አምላክ ሕሊናህን ሳታቆሽሽ እንድትኖር የሚያስችልህን ሥራ ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንደሚባርክልህ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ።​— 2 ቆሮንቶስ 4:​2

20. በመዝናኛዎች ረገድ መራጭ መሆን የሚኖርብን ለምንድን ነው?

20 ጠንክረን መሥራት ቢኖርብንም አምላክ አገልጋዮቹ ደስተኞች እንዲሆኑ ስለሚፈልግ ለመዝናናትና ለዕረፍት ጊዜ በመመደብ ሚዛናችንን መጠበቅ ያስፈልገናል። (ማርቆስ 6:​31፤ መክብብ 3:​12, 13) የሰይጣን ዓለም አምላካዊ አክብሮት የማያሳዩ መዝናኛዎችን ያስፋፋል። አምላክን ለማስደሰት ግን በምናነባቸው መጻሕፍት፣ በምንሰማቸው የሬዲዮ ፕሮግራሞችና ሙዚቃዎች፣ በምንመለከታቸው የሙዚቃ፣ የፊልም፣ የቲያትር፣ የቴሌቪዥንና የቪዲዮ ዓይነቶች ረገድ መራጮች መሆን ይገባናል። ከአሁን በፊት እንመርጣቸው የነበሩት መዝናኛዎች እንደ ዘዳግም 18:​10–12፤ መዝሙር 11:​5 እና ኤፌሶን 5:​3–5 ባሉት ጥቅሶች ላይ ከተሰጡት ማስጠንቀቂያዎች ጋር የሚጋጩ ከሆነ አስፈላጊውን ማስተካከያ ብናደርግ የበለጠ ደስተኛ ከመሆናችንም በላይ ይሖዋን ለማስደሰት እንችላለን።

ለሕይወትና ለደም አክብሮት ማሳየት

21. ለሕይወት ያለን አክብሮት ስለ ውርጃ እንዲሁም ስለ ልማዶቻችንና ጠባያችን ያለንን አመለካከት ሊነካ የሚገባው ለምንድን ነው?

21 ይሖዋ ሰብዓዊ ሕይወትን ቅዱስ አድርጎ ይመለከታል፤ እኛም እውነተኛ ደስታ ለማግኘት ከፈለግን የእርሱን አመለካከት መያዝ ይኖርብናል። የይሖዋ ቃል ሰው እንዳንገድል ያዛል። (ማቴዎስ 19:​16–18) እንዲያውም ለእስራኤል የተሰጠው የአምላክ ሕግ ይሖዋ በማኅፀን ውስጥ ያለውን ጽንስ እንኳን ውድ እንደሆነ ሕይወትና ሊጠፋ እንደማይገባው ነገር አድርጎ እንደሚመለከት ያሳያል። (ዘጸአት 21:​22, 23) ትንባሆ በማጨስ ወይም አደንዛዥ ዕፅ በመውሰድ ወይም ከመጠን በላይ አልኮል በመጠጣት ወይም አስፈላጊ ባልሆነ መንገድ ሕይወታችንን አደጋ ላይ በመጣል እንኳን ሕይወታችንን ርካሽ እንደሆነ ነገር ከመቁጠር መራቅ ይኖርብናል። በተጨማሪም በሕይወት ላይ አደጋ ሊያደርሱ በሚችሉ እንቅስቃሴዎች አንካፈልም ወይም በጥንቃቄ ጉድለት የደም ዕዳ እንዲመጣብን አንፈልግም።​— ዘዳግም 22:​8

22. (ሀ) ስለ ደምና ስለ አጠቃቀሙ ሊኖረን የሚገባው አምላካዊ አመለካከት ምንድን ነው? (ለ) ሕይወት ሊያድን የሚችለው የማን ደም ብቻ ነው?

22 ይሖዋ ለኖኅና ለቤተሰቡ ደም ነፍስን ወይም ሕይወትን እንደሚወክል ተናግሮ ነበር። ስለዚህም አምላክ ማንኛውንም ደም እንዳይበሉ ከለከላቸው። (ዘፍጥረት 9:​3, 4) እኛም የኖኅ ተወላጆች በመሆናችን ይህ ትእዛዝ ሁላችንንም ይመለከታል። ደም መሬት ላይ መፍሰስ እንደሚኖርበትና ሰው በማንኛውም መንገድ ሊገለገልበት እንደማይገባ ይሖዋ ለእስራኤላውያን ተናግሮ ነበር። (ዘዳግም 12:​15, 16) በተጨማሪም ለመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ‘ከደም ራቁ’ የሚል ትእዛዝ በተሰጠ ጊዜ አምላክ ስለ ደም ያወጣው ሕግ በድጋሚ ተደንግጓል። (ሥራ 15:​28, 29) አምላክን የሚፈሩ ሰዎች ለሕይወት ቅድስና ባላቸው አክብሮት ምክንያት ሌሎች ሰዎች ሕይወታችሁን ለማትረፍ ከፈለጋችሁ የግድ ደም መውሰድ አለባችሁ ብለው ቢወተውቷቸው እንኳ ደም አይወስዱም። የይሖዋ ምሥክሮች የሚቀበሏቸው ብዙ ዓይነት የሕክምና አማራጮች በጣም ጥሩ ውጤት ከማስገኘታቸውም በላይ ደም መውሰድ ለሚያስክትላቸው አደጋዎች አያጋልጡም። ክርስቲያኖች ሕይወት ሊያድን የሚችለው የፈሰሰው የኢየሱስ ደም ብቻ እንደሆነ ያውቃሉ። በዚህ ደም ማመን የኃጢአት ሥርየትና የዘላለም ሕይወት ያስገኛል።​— ኤፌሶን 1:​7

23. አምላካዊ አኗኗር በአጸፋው የሚያስገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

23 አምላካዊ አኗኗር ጥረት የሚጠይቅ መሆኑ ግልጽ ነው። ከቤተሰብ አባሎችና ከምናውቃቸው ሰዎች ስድብና ዘለፋ ሊያመጣ ይችላል። (ማቴዎስ 10:​32–39፤ 1 ጴጥሮስ 4:​4) ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው አኗኗር የሚያስገኘው ዋጋ ማንኛውም ፈተና የሚያስከትለውን ችግር ያስንቃል። ንጹሕ ሕሊና ያስገኛል፤ በይሖዋ አምልኮ ባልደረቦቻችን ከሆኑ ሰዎች ጋርም ጥሩ ባልንጀርነት እንዲኖረን ያስችላል። (ማቴዎስ 19:​27, 29) ከዚህም በላይ በአምላክ አዲስ የጽድቅ ዓለም ውስጥ ለዘላለም መኖር መቻል ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን አስብ። (ኢሳይያስ 65:​17, 18) የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ማክበርና በዚህ ምክንያት የይሖዋን ልብ ደስ ማሰኘት መቻል እንዴት የሚያስፈነድቅ ነው! (ምሳሌ 27:​11) አምላካዊ አኗኗር ደስታ የሚያስገኝ መሆኑ አያስደንቅም!​— መዝሙር 128:​1, 2

እውቀትህን ፈትሽ

አምላካዊ አኗኗር ደስታ ከሚያስገኝባቸው ምክንያቶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

አምላካዊ አኗኗር ምን ለውጦች ማድረግን ይጠይቃል?

አምላካዊ ኑሮ ለመኖር የምትፈልገው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 124, 125 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የመዝናኛ ጊዜያት መታከላቸው አምላካዊ አኗኗር ለሚከተሉ ሰዎች ደስታ ያስገኛል