በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን ለዘላለም ማገልገልን ዓላማህ አድርግ

አምላክን ለዘላለም ማገልገልን ዓላማህ አድርግ

ምዕራፍ 18

አምላክን ለዘላለም ማገልገልን ዓላማህ አድርግ

1, 2. አምላክ የሚሰጠውን እውቀት ከማግኘት በተጨማሪ ምን ነገር ይፈለግብ⁠ናል?

በጣም ውድ የሆኑ ዕቃዎች ወደ ተከማቹበት ክፍል በሚያስገባ የተቆለፈ በር ፊት ቆመሃል እንበል። መብት ያለው ሰው የበሩን ቁልፍ ሰጥቶ ውድ ከሆኑት ዕቃዎች መካከል የቻልከውን ያህል እንድትወስድ ይጋብዝሃል። ቁልፉን ካልተጠቀምክበት የሚፈይድልህ ነገር አይኖርም። በተመሳሳይም እውቀት ጥቅም እንዲያስገኝልህ ከተፈለገ እንድትሠራበት ያስፈልጋል።

2 በተለይ አምላክ በሚሰጠው እውቀት ረገድ ይህ አባባል ትክክል ነው። ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት የዘላለም ሕይወት እንደሚያስገኝ የተረጋገጠ ነው። (ዮሐንስ 17:​3) ይሁን እንጂ እውቀት ስለኖረህ ብቻ ይህን የዘላለም ሕይወት ልታገኝ አትችልም። ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው አድርገህ የምትመለከተውን ቁልፍ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለብህ ሁሉ አምላክ የሚሰጠውንም እውቀት በሕይወትህ እንድትሠራበት ያስፈልጋል። ኢየሱስ ‘ወደ አምላክ መንግሥት የሚገቡት’ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉ ብቻ እንደሆኑ ተናግሯል። እንደነዚህ ያሉት ግለሰቦች አምላክን ለዘላለም የማገልገል መብት ያገኛሉ!​— ማቴዎስ 7:​21፤ 1 ዮሐንስ 2:​17

3. አምላክ ምን እንድናደርግ ፈቃዱ ነው?

3 የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ካወቅህ በኋላ ፈቃዱን ማድረግ ያስፈልግሃል። አምላክ ምን እንድታደርግ የሚፈልግ ይመስልሃል? ፈቃዱ ኢየሱስን እንድትመስል ነው በማለት ነገሩን ማጠቃለል ይቻላል። አንደኛ ጴጥሮስ 2:​21 “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና” ይላል። ስለዚህ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ የኢየሱስን ምሳሌ በተቻለ መጠን አሟልተህ መከተል ያስፈልግሃል። ከአምላክ ያገኘኸውን እውቀት የምትጠቀምበት በዚህ መንገድ ነው።

ኢየሱስ ስለ አምላክ የነበረውን እውቀት እንዴት ተጠቅሞበታል?

4. ኢየሱስ ስለ ይሖዋ ከፍተኛ እውቀት ሊኖረው የቻለው ለምንድን ነው? ይህንንስ እውቀት እንዴት ተጠቅሞበታል?

4 ኢየሱስ ክርስቶስ ከማንኛውም ፍጡር ይበልጥ አምላክን በቅርብ ያውቃል። ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ለብዙ ዘመናት በሰማይ ከይሖዋ አምላክ ጋር ይኖርና ይሠራ ነበር። (ቆላስይስ 1:​15, 16) ታዲያ ይህን ሁሉ እውቀት ምን አደረገበት? እውቀት በማግኘቱ ብቻ ረክቶ አልተቀመጠም። ኢየሱስ በዚህ እውቀት ሕይወቱን መርቷል። ከሰዎች ጋር በነበረው ግንኙነት ሁሉ ደግ፣ ታጋሽና አፍቃሪ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው። ኢየሱስ በዚህ መንገድ ሰማያዊ አባቱን መስሏል፤ ስለ ይሖዋ መንገዶችና ባሕርይ ካገኘው እውቀት ጋር በሚስማማ መንገድ ኖሯል።​— ዮሐንስ 8:​23, 28, 29, 38፤ 1 ዮሐንስ 4:​8

5. ኢየሱስ የተጠመቀው ለምን ነበር? ጥምቀቱ ከነበረው ትርጉም ጋር በሚስማማ መንገድ የኖረውስ እንዴት ነው?

5 በተጨማሪም ኢየሱስ የነበረው እውቀት ግልጽ የሆነ እርምጃ እንዲወስድ ገፋፍቶታል። ከገሊላ ተነስቶ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ከመጣ በኋላ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ። (ማቴዎስ 3:​13–15) የኢየሱስ ጥምቀት ምን ያመለክት ነበር? አይሁዳዊ በመሆኑ የተወለደው ለአምላክ ከተወሰነ ብሔር ነበር። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ከልደቱ ጀምሮ ለአምላክ የተወሰነ ሰው ነበር። (ዘጸአት 19:​5, 6) ኢየሱስ ራሱን ለጥምቀት ሲያቀርብ በዚያ ጊዜ መፈጸም የነበረበትን መለኮታዊ ፈቃድ ለማድረግ ራሱን ለይሖዋ ማቅረቡ ነበር። (ዕብራውያን 10:​5, 7) ኢየሱስ የጥምቀቱን ትርጉም ሙሉ በሙሉ ፈጽሟል። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለ አምላክ የነበረውን እውቀት ለሰዎች በማካፈል መላ ሕይወቱን ለይሖዋ አገልግሎት አውሏል። ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ከፍተኛ ደስታ ያገኝ ነበር። እንዲያውም የአምላክን ፈቃድ ማድረግ እንደ መብል እንደሚሆንለት ተናግሯል።​— ዮሐንስ 4:​34

6. ኢየሱስ የራሱን ባለቤትነት የካደው በምን መንገድ ነው?

6 ኢየሱስ የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ ከፍተኛ ዋጋ መክፈል እንደሚጠይቅበት፣ እንዲያውም ሕይወቱን እስከመሠዋት እንደሚያደርሰው ያውቅ ነበር። ቢሆንም ኢየሱስ የራሱን ባለቤትነት በመካድ የግል ጥቅሞቹ በሁለተኛ ደረጃ እንዲቀመጡ አድርጓል። ምን ጊዜም የአምላክን ፈቃድ ማድረግን ያስቀድም ነበር። በዚህ ረገድ ፍጹም የሆነውን የኢየሱስ ምሳሌ ልንከተል የምንችለው እንዴት ነው?

ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሱ እርምጃዎች

7. አንድ ሰው ለጥምቀት ብቁ ለመሆን ምን እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርበታል?

7 ሁላችንም እንደ ኢየሱስ ፍጹማን ባለመሆናችን ከፍተኛ ወደሆነው የጥምቀት ደረጃ የምንደርሰው ሌሎች ትልልቅ እርምጃዎችን ከወሰድን በኋላ ነው። የመጀመሪያው እርምጃ ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት ወደ ልባችን እንዲገባ ማድረግ ነው። ይህ እርምጃ እምነትና ለአምላክ የጠለቀ ፍቅር እንዲኖረን ያስችላል። (ማቴዎስ 22:​37–40፤ ሮሜ 10:​17፤ ዕብራውያን 11:​6) የአምላክን ሕግጋት፣ መሠረታዊ ሥርዓቶችና የሥነ ምግባር መስፈርቶች ለማክበር ያለን ፍላጎት ንስሐ እንድንገባ፣ ይኸውም ቀደም ሲል ስለሠራናቸው ኃጢአቶች አምላክን ከማክበር የመነጨ ጸጸት እንዲሰማን ሊያደርገን ይገባል። ይህም አካሄዳችንን ወደ መለወጥ ይመራናል፤ ማለትም የጉዞ አቅጣጫችንን በመቀየር አምላክን ሳናውቅ እናደርጋቸው የነበሩትን መጥፎ ነገሮች እርግፍ አድርገን ወደ መተው ያደርሰናል። (ሥራ 3:​19) ጽድቅ የሆነውን ከማድረግ ይልቅ በስውር የምንፈጽመው ኃጢአት ካለ ንስሐ እንዳልገባንና አቋማችን እንዳልተለወጠ ግልጽ ነው። አምላክን ልናሞኝ አንችልም። ይሖዋ ማንኛውንም ዓይነት ግብዝነት ያውቃል።​— ሉቃስ 12:​2, 3

8. በመንግሥቱ ስብከት ሥራ ለመካፈል በምትፈልግበት ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

8 እስከ አሁን ድረስ ከአምላክ የሚገኘውን እውቀት ስትሰበስብ ቆይተሃል። ታዲያ አሁን መንፈሳዊ ነገሮች ከግል ሕይወትህ ጋር ምን ዓይነት ዝምድና ሊኖራቸው እንደሚገባ በጥሞና ማሰብ አይገባህምን? ምናልባት ለዘመዶችህ፣ ለወዳጆችህና ለሌሎች ሰዎች ስለምትማረው ነገር ለመናገር ትጓጓ ይሆናል። እንዲያውም ኢየሱስ እንዳደረገው ምሥራቹን ለሌሎች ሰዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ መናገር ሳትጀምር አትቀርም። (ሉቃስ 10:​38, 39፤ ዮሐንስ 4:​6–15) አሁን ግን ከዚህም አልፈህ ለመሄድ ትፈልግ ይሆናል። ክርስቲያን ሽማግሌዎች የይሖዋ ምሥክሮች በሚያከናውኑት መደበኛ የመንግሥት ስብከት ሥራ ለመካፈል ብቃትና ችሎታ ያለህ መሆንህን አመዛዝነው ለመወሰን ያነጋግሩሃል። ብቃትና ችሎታ ካለህ አብሮህ የሚያገለግል የይሖዋ ምሥክር ይመድቡልሃል። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አገልግሎታቸውን ሥርዓት ባለው መንገድ ለማከናወን የኢየሱስን መመሪያ መከተል አስፈልጓቸው ነበር። (ማርቆስ 6:​7, 30፤ ሉቃስ 10:​1) አንተም የመንግሥቱን መልእክት ከቤት ወደ ቤት በመሄድና በሌሎች መንገዶች በምታሰማበት ጊዜ ከሚደረግልህ ተመሳሳይ እርዳታ ብዙ ጥቅም ታገኛለህ።​— ሥራ 20:​20, 21

9. አንድ ሰው ራሱን ለአምላክ የሚወስነው እንዴት ነው? ራሱን መወሰኑስ በሕይወቱ ላይ ምን ለውጥ ያስከትላል?

9 በጉባኤው የአገልግሎት ክልል ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች በሙሉ ምሥራቹን መስበክ የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ለማግኘት የሚቻልበት መንገድ ከመሆኑም በላይ እምነት እንዳለህ ከሚያረጋግጡ መልካም ሥራዎች አንዱ ነው። (ሥራ 10:​34, 35፤ ያዕቆብ 2:​17, 18, 26) በተጨማሪም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘትና በስብከቱ ሥራ ልባዊ ተሳትፎ ማድረግ ንስሐ ገብተህና ከቀድሞ አካሄድህ ተመልሰህ አምላክ ከሚሰጠው እውቀት ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ ያደረግህ መሆንህን ያሳያል። ከዚህ በኋላ መውሰድ የሚኖርብህ እርምጃ ምን ይመስልሃል? ራስህን ለይሖዋ አምላክ መወሰን ነው። ራስህን ስትወስን ከልብ በመነጨ ጸሎት ሕይወትህን በፈቃደኝነትና በሙሉ ልብ ለይሖዋና የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ መስጠትህን ለአምላክ ትገልጻለህ ማለት ነው። ራስህን ለይሖዋ የምትወስነውና የኢየሱስ ክርስቶስን ልዝብ ቀንበር የምትሸከመው በዚህ መንገድ ነው።​— ማቴዎስ 11:​29, 30

ጥምቀት ለአንተ ምን ትርጉም አለው?

10. ራስህን ለይሖዋ ከወሰንክ በኋላ መጠመቅ የሚኖርብህ ለምንድን ነው?

10 ኢየሱስ በተናገረው መሠረት ደቀ መዛሙርቱ ሊሆኑ የሚፈልጉ ሁሉ መጠመቅ ይኖርባቸዋል። (ማቴዎስ 28:​19, 20) ራስህን ለአምላክ ከወሰንህ በኋላ መጠመቅ የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው? ራስህን ለይሖዋ ስለ ወሰንክ ይሖዋ እንደምትወደው ያውቃል። ይሁን እንጂ ለአምላክ ያለህን ፍቅር ሌሎች ሰዎችም እንዲያውቁ ለማድረግ ሌላም እርምጃ መውሰድ እንደምትፈልግ ጥርጥር የለውም። ጥምቀት ራስህን ለይሖዋ አምላክ መወሰንህን በሰዎች ፊት የምታሳውቅበትን አጋጣሚ ይከፍትልሃል።​— ሮሜ 10:​9, 10

11. የጥምቀት ትርጉም ምንድን ነው?

11 ጥምቀት በጣም ጥልቅ ትርጉም አለው። በውኃ ውስጥ “ስትቀበር” ወይም ስትጠልቅ ለቀደመው አኗኗርህ እንደሞትክ ያህል ሆነሃል ማለት ነው። ከውኃው ውስጥ ስትወጣ ደግሞ ለራስህ ፈቃድ ሳይሆን ለአምላክ ፈቃድ ወደሚገዛው አዲስ ዓይነት ሕይወት ተነስተሃል ማለት ነው። እርግጥ፣ እንዲህ ሲባል ከተጠመቅህ በኋላ ምንም ዓይነት ስህተት አትፈጽምም ማለት አይደለም። ሁላችንም ፍጽምና የጎደለን ስለሆንን በየቀኑ ኃጢአት እንሠራለን። ይሁን እንጂ አሁን ራስህን የወሰንክና የተጠመቅህ የይሖዋ አገልጋይ በመሆንህ ከይሖዋ ጋር ልዩ የሆነ ዝምድና መሥርተሃል። ንስሐ ስለገባህና ራስህን በትሕትና ዝቅ አድርገህ ስለ ተጠመቅህ ይሖዋ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ኃጢአቶችህን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነው። ስለዚህ ጥምቀት በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረን መንገድ ይከፍትልናል።​— 1 ጴጥሮስ 3:​21

12. (ሀ) ‘በአብ ስም’ (ለ) ‘በወልድ ስም’ (ሐ) “በመንፈስ ቅዱስ ስም” መጠመቅ ምን ማለት ነው?

12 ኢየሱስ ተከታዮቹ አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን “በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” እንዲያጠምቁ አዟል። (ማቴዎስ 28:​19) ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ‘በአብ ስም’ የሚጠመቀው ሰው ይሖዋ አምላክ የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪና ሉዓላዊ ገዥ መሆኑን ከልቡ ይቀበላል ማለት ነው። (መዝሙር 36:​9፤ 83:​18፤ መክብብ 12:​1) ‘በወልድ ስም’ መጠመቅ ማለት ደግሞ የሚጠመቀው ግለሰብ ኢየሱስ ክርስቶስ (በተለይም ቤዛዊ መሥዋዕቱ) ብቸኛው ከአምላክ የተሰጠን የመዳን ዝግጅት እንደሆነ አምኖ ይቀበላል ማለት ነው። (ሥራ 4:​12) “በመንፈስ ቅዱስ ስም” መጠመቅ ማለት እጩ ተጠማቂው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል አምላክ ዓላማውን የሚፈጽምበት፣ አገልጋዮቹ በመንፈስ ከሚመራው ድርጅቱ ጋር በመተባበር ጻድቅ የሆነውን ፈቃዱን እንዲፈጽሙ ኃይል የሚሰጥበት መሣሪያው መሆኑን አምኖ ይቀበላል ማለት ነው።​— ዘፍጥረት 1:​2፤ መዝሙር 104:​30፤ ዮሐንስ 14:​26፤ 2 ጴጥሮስ 1:​21

ለመጠመቅ ዝግጁና ብቁ ነህን?

13, 14. ይሖዋ አምላክን ለማገልገል መምረጡ ሊያስፈራን የማይገባው ለምንድን ነው?

13 መጠመቅ ይህን የመሰለ ከፍተኛ ትርጉም ያለውና በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ታላቅ እርምጃ በመሆኑ ይህን እርምጃ ለመውሰድ ፍርሃት ሊሰማህ ይገባልን? በፍጹም አይገባም! የጥምቀት ውሳኔ እንደ ቀላል ነገር የሚታይ እርምጃ ባይሆንም ከማንኛውም ውሳኔ የሚበልጥ የብልህነት ውሳኔ መሆኑ አያጠያ ይቅም።

14 ጥምቀት ይሖዋ አምላክን ለማገልገል የመረጥክ መሆንህን ያረጋግጣል። እስቲ ለአንድ አፍታ ስለምታውቃቸው ሰዎች አስብ። ሁሉም በአንድ መንገድ ወይም በሌላ የሚያገለግሉት ጌታ ያላቸው አይደሉምን? አንዳንዶች የሀብት ባሮች ናቸው። (ማቴዎስ 6:​24) አንዳንዶች ለአንድ ዓይነት ሙያ የተገዙ ወይም የራሳቸውን ፍላጎት ማርካትን ከማንኛውም ነገር በላይ በማስቀደም ራሳቸውን የሚያገለግሉ ናቸው። ሌሎች ደግሞ የሐሰት አማልክትን ያገለግላሉ። አንተ ግን እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ለማገልገል መርጠሃል። የይሖዋን ያህል ደግነት፣ ርህራሄና ፍቅር የሚያሳይ ሌላ ማንም የለም። አምላክ የመዳንን አቅጣጫ የሚያሳይ ዓላማ ያለው ሥራ ለሰው ልጆች በመስጠት ከፍ ያለ ክብር ሰጥቷቸዋል። አገልጋዮቹ ላሳዩት ታማኝነት የዘላለም ሕይወትን ሽልማት ይሰጣቸዋል። በእርግጥም የኢየሱስን ምሳሌ መከተልና ሕይወትን ለይሖዋ አሳልፎ መስጠት ልትፈራው የሚገባህ ነገር አይደለም። እንዲያውም አምላክን የሚያስደስትና ፈጽሞ የማይቆጭ ብቸኛ አካሄድ ይህ ነው።​— 1 ነገሥት 18:​21

15. ለጥምቀት እንቅፋት ከሚሆኑት የተለመዱ ነገሮች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

15 ይሁን እንጂ ጥምቀት በሌሎች ሰዎች ግፊት የምንወስደው እርምጃ አይደለም። በአንተና በይሖዋ አምላክ መካከል ብቻ የተወሰነ የግል ጉዳይ ነው። (ገላትያ 6:​4) መንፈሳዊ እድገት ስላደረግህ “እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው?” ብለህ ራስህን ትጠይቅ ይሆናል። (ሥራ 8:​35, 36) እንዲህ እያልክ ራስህን ልትጠይቅ ትችላለህ:- ‘የቤተሰብ ተቃውሞ እንቅፋት እየሆነብኝ ነውን? አሁንም ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆነ ሁኔታ እየኖርኩ ነኝን? ወይም ልማድ የሆነብኝ ኃጢአት አለን? በአካባቢዬ ያሉ ሰዎች ይጠሉኛል ብዬ እፈራለሁን?’ እነዚህ በጥሞና ሊመረመሩ የሚገባቸው ጉዳዮች ናቸው፤ ሆኖም ነገሩን ከእውነታዎች አንፃር አመዛዝን።

16. ይሖዋን በማገልገል የምትጠቀመው እንዴት ነው?

16 ይሖዋን ከማገልገል የሚገኙትን ጥቅሞች ሳናገናዝብ የምንከፍለውን መሥዋዕትነት ብቻ ብናስብ ነገሩን ከእውነታዎቹ አንፃር በትክክል አመዛዝነናል ለማለት አይቻልም። ለምሳሌ ያህል የቤተሰብ ተቃውሞን እንመልከት። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እርሱን በመከተላቸው ምክንያት ዘመዶቻቸውን ቢያጡ በጣም ሰፊ የሆነ መንፈሳዊ ቤተሰብ እንደሚያገኙ ቃል ገብቷል። (ማርቆስ 10:​29, 30) እነዚህ የእምነት ባልደረቦች ወንድማዊ ፍቅር ያሳዩሃል፣ የሚመጣብህን ስደት እንድትቋቋምና እንድትጸና ይረዱሃል፣ ከሕይወት ጎዳና ተደናቅፈህ እንዳትወጣም ይደግፉሃል። (1 ጴጥሮስ 5:​9) በተለይ የጉባኤ ሽማግሌዎች የሚያጋጥሙህን ችግሮች ታግለህ እንድታሸንፍና ሌሎች ፈተናዎችንም በድል እንድትወጣ ሊያግዙህ ይችላሉ። (ያዕቆብ 5:​14–16) በዚህ ዓለም መጠላትን በተመለከተም ‘የአጽናፈ ዓለሙን ፈጣሪ ሞገስ ከማግኘትና በመረጥኩት አኗኗር ምክንያት እርሱን ከማስደሰት ጋር የሚወዳደር ምን ነገር ሊኖር ይችላል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።​— ምሳሌ 27:​11

ከውሳኔህና ከጥምቀትህ ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር

17. ጥምቀትን እንደ መጀመሪያ እንጂ እንደ መጨረሻ እርምጃ አድርገህ መመልከት የማይኖርብህ ለምንድን ነው?

17 ጥምቀት የመንፈሳዊ እድገትህ መቋጫ እንዳልሆነ ማስታወስ አስፈላጊ ነው። የወንጌል አገልጋይና የይሖዋ ምሥክር ሆነህ አምላክን ለምታገለግልበት የዕድሜ ልክ ጉዞ መጀመሪያ ይሆንልሃል። ጥምቀት በጣም አስፈላጊ እርምጃ ቢሆንም ለመዳን ዋስትና አይሆንም። ኢየሱስ ‘የተጠመቀ ሁሉ ይድናል’ አላለም። ከዚህ ይልቅ “እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:​13) ስለዚህ በሕይወትህ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጠውን ቦታ ለአምላክ መንግሥት በመስጠት የአምላክን መንግሥት ማስቀደምህን መቀጠልህ በጣም አስፈላጊ ነው።​— ማቴዎስ 6:​25–34

18. ከተጠመቅህ በኋላ ልትከታተላቸው ከሚገቡ ግቦች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

18 ለይሖዋ በምታቀርበው አገልግሎት ለመጽናት ለራስህ መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣት ይኖርብሃል። ጊዜና ጉልበት ልታጠፋለት የሚገባ አንዱ ግብ ቃሉን አዘውትረህ በግልህ በማጥናት ስለ አምላክ ያገኘኸውን እውቀት ማሳደግ ነው። በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ እቅድ አውጣ። (መዝሙር 1:​1, 2) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ ተገኝ፤ ምክንያቱም እዚያ ከምታገኛቸው ወንድሞች ጋር መቀራረብህ መንፈሳዊ ጥንካሬ እንድታገኝ ይረዳሃል። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት አለብኝ የሚል ግብ ለምን አታወጣም? ይህን በማድረግህ ይሖዋን ለማወደስና ሌሎችን ለማነጽ ትችላለህ። (ሮሜ 1:​11, 12) የጸሎትህን ይዘት ማሻሻልም ሌላው ግብህ ሊሆን ይችላል።​— ሉቃስ 11:​2–4

19. መንፈስ ቅዱስ ምን ዓይነት ባሕርያትን እንድታሳይ ሊረዳህ ይችላል?

19 ከጥምቀትህ ትርጉም ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ከፈለግህ በየቀኑ ለምታደርጋቸው ነገሮች የማያቋርጥ ትኩረት መስጠትና የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እንደ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ የዋህነትና ራስን መግዛት የመሰሉትን ባሕርያት እንድታፈራ እንዲያደርግህ መፍቀድ ይኖርብሃል። (ገላትያ 5:​22, 23፤ 2 ጴጥሮስ 3:​11) ይሖዋ ለሚለምኑትና የታመኑ አገልጋየቹ ሆነው ለሚታዘዙት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጥ ምን ጊዜም አስታውስ። (ሉቃስ 11:​13፤ ሥራ 5:​32) ስለዚህ አምላክ መንፈሱን እንዲሰጥህና እርሱን የሚያስደስቱትን ባሕርያት እንድታንጸባርቅ እንዲረዳህ ጸልይ። የአምላክ መንፈስ በአንተ ላይ የሚያሳድረውን በጎ ተጽእኖ በተቀበልክ መጠን እንደነዚህ ያሉት ባሕርያት በአነጋገርህና በጠባይህ ግልጽ ሆነው መታየት ይጀምራሉ። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ግለሰብ ክርስቶስን በይበልጥ ለመምሰል ሲል “አዲሱን ሰው” ለመልበስ ብርቱ ጥረት ያደርጋል። (ቆላስይስ 3:​9–14) እያንዳንዱ ግለሰብ የሚገኝበት የመንፈሳዊ እድገት ደረጃ ከሌላው የተለየ ስለሆነ ይህን “አዲስ ሰው” በመልበስ ረገድ የሚያጋጥመው ትግል ከሰው ወደ ሰው ይለያያል። ፍጹም ባለመሆንህ ምክንያት ክርስቶስን የሚመስል ባሕርይ ለመልበስ ብርቱ ትግል ማድረግ ይኖርብሃል። ይሁን እንጂ በአምላክ እርዳታ የማይቻል ነገር ስለሌለ ተስፋ አትቁረጥ።

20. በአገልግሎት ረገድ ኢየሱስን ልትመስል የምትችለው በምን መንገዶች ነው?

20 የኢየሱስን የደስተኝነት ምሳሌ መከተል ከመንፈሳዊ ግቦችህ አንዱ መሆን ይኖርበታል። (ዕብራውያን 12:​1–3) ኢየሱስ አገልግሎቱን በጣም ይወድ ነበር። በመንግሥቱ ስብከት የመካፈል መብት ካገኘህ ይህንን ሥራ እንዲሁ ልማድ ብቻ እንደሆነ አድርገህ አትመልከተው። ልክ እንደ ኢየሱስ አንተም ለሌሎች ስለ አምላክ መንግሥት በማስተማር እርካታ አግኝ። ጉባኤው የማስተማር ችሎታህን እንድታሻሽል አንተን ለማገዝ የሚሰጣቸውን ትምህርቶች ሥራ ላይ አውል። ደግሞም ይሖዋ አገልግሎትህን ለመፈጸም የሚያስችልህን ብርታት ሊሰጥህ እንደሚችል እርግጠኛ ሁን።​— 1 ቆሮንቶስ 9:​19–23

21. (ሀ) ይሖዋ ታማኝ የሆኑ የተጠመቁ ግለሰቦችን እንደ ውድ ንብረት አድርጎ እንደሚመለከት እንዴት እናውቃለን? (ለ) ጥምቀት በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ላይ ከሚመጣው የአምላክ ፍርድ በሕይወት ለመትረፍ አስፈላጊ የሆነ እርምጃ መሆኑን የሚያመለክተን ምንድን ነው?

21 ኢየሱስን ለመከተል በቁም ነገር የሚጥርን ራሱን የወሰነና የተጠመቀ ሰው አምላክ በልዩ ዓይን ይመለከተዋል። ይሖዋ በቢልዮን የሚቆጠሩትን ሰዎች ልብ ስለሚመረምር እንደነዚህ ያሉ ግለሰቦች ምን ያህል ብርቅ እንደሆኑ ያውቃል። ውድ ሀብት ወይም ‘የተመረጠ ዕቃ’ አድርጎ ይመለከታቸዋል። (ሐጌ 2:​7) በተጨማሪም አምላክ እንደነዚህ ያሉት ሰዎች በክፉው ሥርዓት ላይ ከሚመጣው ጥፋት በሕይወት እንዲተርፉ ምልክት እንደተደረገባቸው ሰዎች አድርጎ እንደሚያያቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ያመለክታሉ። (ሕዝቅኤል 9:​1–6፤ ሚልክያስ 3:​16, 18) “ለዘላለም ሕይወት የሚያበቃ” ትክክለኛ አቋም አለህን? (ሥራ 13:​48 አዓት) አምላክን የሚያገለግል ሰው ነው ተብለህ ምልክት እንዲደረግብህ ከምር ፍላጎት አለህን? ራስን መወሰንና መጠመቅ የዚህ ምልክት ክፍል ሲሆን ከጥፋት በሕይወት ለመትረፍም አስፈላጊ የሆነ እርምጃ ናቸው።

22. “እጅግ ብዙ ሰዎች” የትኛውን ተስፋ በጉጉት ሊጠባበቁ ይችላሉ?

22 ኖኅና ቤተሰቡ ከጥፋት ውኃ በኋላ ከመርከቡ ወጥተው ንጹሕ በሆነች ምድር ላይ መኖር ጀምረዋል። ዛሬም በተመሳሳይ የአምላክን እውቀት በሕይወታቸው ውስጥ የሚሠሩበትና በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኙ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ከዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት ተርፈው ለዘለቄታው በጸዳች ምድር ላይ ዘላለማዊ ሕይወት ተቀብለው የመኖር ተስፋ አላቸው። (ራእይ 7:​9, 14) በዚህ ገነት ውስጥ የሰዎች ሕይወት ምን ይመስል ይሆን?

እውቀትህን ፈትሽ

ይሖዋ ከእርሱ ያገኘኸውን እውቀት እንዴት እንድትጠቀምበት ይፈልጋል?

ወደ ጥምቀት የሚያደርሱት አንዳንድ እርምጃዎች ምንድን ናቸው?

ጥምቀት የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ እርምጃ ያልሆነው ለምንድን ነው?

ራሳችንን ለአምላክ ከመወሰናችንና ከመጠመቃችን ጋር ተስማምተን ለመኖር የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 172 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ራስህን መወሰንህን ለአምላክ በጸሎት አስታውቀሃልን?

[በገጽ 174 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

እንዳትጠመቅ የሚከለክልህ ምንድን ነው?