በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ?

አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ?

ምዕራፍ 8

አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ?

1, 2. ብዙዎች በሰው ልጆች ላይ ስለሚደርሰው ሥቃይ እንዴት ይሰማቸዋል?

የተፈጥሮ አደጋ ደርሶ ብዙ ንብረትና ሕይወት ሲጠፋ ብዙ ሰዎች እንደነዚህ ያሉት አሠቃቂ ሁኔታዎች ለምን እንደሚደርሱ መረዳት ይከብዳቸዋል። ሌሎች ደግሞ የወንጀልና የዓመፅ ብዛት፣ ጭካኔና ኢሰብዓዊነት ያስጨንቃቸዋል። አንተም ‘አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

2 ብዙ ሰዎች ለዚህ ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ለማግኘት ባለመቻላቸው በአምላክ ላይ እምነት አጥተዋል። ስለ ሰው ልጆች ፈጽሞ ደንታ ቢስ ሆኗል ብለው ያስባሉ። ሥቃይና መከራን የማይቀሩ የሕይወት እውነታዎች አድርገው የተቀበሉ ሌሎች ሰዎች ደግሞ በሁኔታዎቹ ይማረራሉ፤ በሰው ልጅ ማኅበረሰብ ውስጥ ለሚታየውም ክፋት ሁሉ አምላክን ተወቃሽ ያደርጉታል። እንዲህ ያለ ስሜት ከነበረህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚሰጠውን መግለጫ ለማወቅ መጓጓትህ አይቀርም።

መከራ ያመጣው አምላክ አይደለም

3, 4. ክፋትንና ሥቃይን ያመጣው ይሖዋ አንዳልሆነ እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

3 በአካባቢያችን ለምናየው መከራና ሥቃይ ምክንያቱ ይሖዋ አምላክ እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል። ለምሳሌ ያህል ያዕቆብ የተባለው ክርስቲያን ደቀ መዝሙር “ማንም ሲፈተን:- በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 1:​13) እንዲህ ከሆነ የሰው ልጆችን ያጥለቀለቀውን መከራ ያመጣው አምላክ ሊሆን አይችልም ማለት ነው። ሰዎችን ለሰማያዊ ሕይወት ብቁ ለማድረግ ሲል ፈተና አያመጣባቸውም ወይም በፊተኛው ሕልውናቸው ወቅት ፈጽመዋቸዋል ተብሎ ለሚታመንባቸው መጥፎ ድርጊቶች ቅጣት እንዲሆን መከራ እንዲቀበሉ አያደርግም።​— ሮሜ 6:​7

4 በተጨማሪም በአምላክ ወይም በክርስቶስ ስም የተፈጸሙ ብዙ አስከፊ ነገሮች ቢኖሩም አምላክም ሆነ ክርስቶስ እነዚህን ድርጊቶች ደግፈዋቸው እንደነበረ የሚያመለክት የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ አናገኝም። አምላክም ሆነ ክርስቶስ እነርሱን እናገለግላለን እያሉ ከሚያጭበረብሩና ከሚያታልሉ፣ ከሚገድሉና ከሚዘርፉ እንዲሁም በሰው ልጆች ላይ ሥቃይ የሚያስከትሉ ሌሎች ብዙ ነገሮች ከሚፈጽሙ ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ኅብረት የላቸውም። እንዲያውም “የኀጥአን መንገድ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው።” “እግዚአብሔር ከኀጥአን ይርቃል።”​— ምሳሌ 15:​9, 29

5. ከይሖዋ ባሕርያት አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ስለ ፍጥረቶቹስ እንዴት ይሰማ⁠ዋል?

5 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “እጅግ የሚምር የሚራራም” እንደሆነ ይናገራል። (ያዕቆብ 5:​11) “እግዚአብሔር ፍርድን [“ፍትሕን” አዓት] ይወድዳል” ይላል። (መዝሙር 37:​28፤ ኢሳይያስ 61:​8) ቂመኛ አምላክ አይደለም። ፍጥረቶቹን በርህራሄ የሚንከባከብ አምላክ ስለሆነ ለደኅንነታቸው የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ይሰጣል። (ሥራ 14:​16, 17) ይሖዋ በምድር ላይ ሕይወት ብቅ ካለበት ጊዜ ጀምሮ ይህን ሲያደርግ ቆይቷል።

ፍጹም የሆነ ጅምር

6. አንዳንድ አፈ ታሪኮች ስለ ሰው ልጅ የመጀመሪያ ታሪክ ምን ይጠቁማሉ?

6 ሁላችንም በሌሎች ላይ ሥቃይ ሲደርስ ተመልክተናል፤ ራሳችንም ብዙ ሥቃይና መከራ ቀምሰናል። በዚህም ምክንያት ሥቃይ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣል ብሎ ማሰብ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ይሁን እንጂ በሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ ላይ ምንም ዓይነት ሥቃይና መከራ አልነበረም። የአንዳንድ ሕዝቦች አፈ ታሪኮች እንኳን እንዲህ ያለ ዘመን እንደነበረ ይገልጻሉ። በግሪካውያን አፈ ታሪክ ከ“ሰው አምስት ዘመናት” መካከል የመጀመሪያው “ወርቃማው ዘመን” ተብሎ ይጠራ ነበር። በዚህ ዘመን የሰው ልጆች አለምንም ድካም፣ ሕመምና እርጅና ደስ ብሏቸው ይኖሩ ነበር ይባላል። ቻይናውያን በአፈ ታሪክ ብቻ በሚታወቀው ቢጫ ንጉሠ ነገሥት (ሁዋንግ–ቲ) ዘመነ መንግሥት ሰዎች ከአየር፣ ከውኃ፣ ከእንስሳት፣ ከአፈርና ከአራዊት እንኳን ሳይቀር ሙሉ ስምምነት ኖሯቸው በሰላም ይኖሩ ነበር ይባላል። ፋርሳውያን፣ ግብፃውያን፣ ቲቤታውያን፣ ፔሩውያንና ሜክሲካውያን በሰው ልጆች ታሪክ መጀመሪያ ላይ የደስታና የፍጽምና ዘመን እንደነበረ የሚተርኩ አፈ ታሪኮች አሏቸው።

7. አምላክ ምድርንና የሰው ልጆችን የፈጠረው ለምን ነበር?

7 እነዚህ የብሔራት አፈ ታሪኮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እጅግ ጥንታዊ የሆነ የሰው ልጆች ታሪክ የሚያስተጋቡ ናቸው። ይህ መጽሐፍ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ማለትም አዳምንና ሔዋንን የኤደን አትክልት በሚባል ገነት እንዳስቀመጣቸውና “ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም” ብሎ እንዳዘዛቸው ይነግረናል። (ዘፍጥረት 1:⁠28) የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ፍጹማን ከመሆናቸውም በላይ መላዋ ምድር ዘላቂ ሰላምና ደስታ አግኝተው በሚኖሩ ፍጹማን ሰዎች የምትሞላ ገነት ስትሆን የማየት ተስፋ ነበራቸው። አምላክ ምድርንና የሰው ልጆችን የፈጠረበት ዓላማ ይህ ነበር።​— ኢሳይያስ 45:​18

ክፋት ያዘለ ግድድር

8. አዳምና ሔዋን የትኛውን ትእዛዝ እንዲያከብሩ ይጠበቅባቸው ነበር? ይሁን እንጂ ምን ሆነ?

8 አዳምና ሔዋን የአምላክን ሞገስ እንዳያጡ ከፈለጉ “መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ” ፍሬ መብላት አልነበረባቸውም። (ዘፍጥረት 2:​16, 17) የይሖዋን ሕግ ቢታዘዙ ኖሮ በሰው ልጅ ሕይወት ላይ የሐዘን ጥላ ያጠላ መከራና ሥቃይ አይኖርም ነበር። አምላክ የሰጣቸውን ትእዛዝ በመጠበቅ ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅርና ታማኝነት ሊያረጋግጡ ይችሉ ነበር። (1 ዮሐንስ 5:​3) ይሁን እንጂ በምዕራፍ 6 ላይ እንደተመለከትነው ያደረጉት ከዚህ የተለየ ነገር ነበር። ሔዋን በሰይጣን ተገፋፍታ ከዛፉ ፍሬ በላች። በኋላ አዳምም ጭምር ከተከለከለው ፍሬ በላ።

9. ሰይጣን ይሖዋን የሚመለከት ምን ጥያቄ አስነሳ?

9 የተፈጸመው ነገር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ታስተውላለህን? ይሖዋ የሁሉም የበላይ ሲሆን ሰይጣን በዚህ የአምላክ ቦታ ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ነበር። “ሞትን አትሞቱም” ሲላት አምላክ ‘ሞትን ትሞታላችሁ’ ሲል የሰጠውን ቃል መቃረኑ ነበር። ሰይጣን የተናገራቸው ተጨማሪ ቃላት አዳምና ሔዋን እንደ አምላክ ለመሆን ሲችሉ ይሖዋ ግን ይህን እውቀት ደብቋቸዋል፤ እንዲሁም ምን ነገር ጥሩ ወይም ምን ነገር መጥፎ እንደሆነ ለመወሰን እርሱ አያስፈልጋቸውም የሚል ሐሳብ ያስተላልፋሉ። በዚህም ምክንያት የሰይጣን ግድድር ይሖዋ በአጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነቱ የያዘው ቦታ ትክክል እና አስፈላጊ በመሆኑ ላይ ጥያቄ አስነሳ።​— ዘፍጥረት 2:​17፤ 3:​1–6

10. ሰይጣን ስለ ሰው ልጆች በተዘዋዋሪ ምን ብሎ ተናገረ?

10 በተጨማሪም ሰይጣን ዲያብሎስ ሰዎች ይሖዋን የሚታዘዙት እርሱን መታዘዝ ጥቅም የሚያስገኝ እስከ ሆነ ድረስ ብቻ ነው በማለት በተዘዋዋሪ ተናግሯል። በሌላ አነጋገር የሰው ልጆች አቋማቸውን ሳያጎድፉ የመኖራቸው ጉዳይ አጠያያቂ ሆነ። ሰይ⁠ጣን በፈቃደኝነት ተነሳስቶ ለአምላክ ታማኝ ሆኖ የሚጸና ሰው አይኖርም በማለት ከሰሰ። ይህ ክፋት ያዘለ የሰይጣን አባባል ስለ ኢዮብ በሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል። ኢዮብ በ1600 ከዘአበ ገደማ ይኖር የነበረና ታላቅ ፈተና የተቋቋመ የታመነ የይሖዋ አገልጋይ ነበር። በኢዮብ መጽሐፍ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ምዕራፎች ብታነብ የሰው ልጅ መከራ መንስዔ ምን መሆኑንና አምላክም ይህን መከራ የፈቀደበትን ምክንያት በጥልቀት ለማስተዋል ትችላለህ።

11. ኢዮብ ምን ዓይነት ሰው ነበር? ሰይጣን ግን ምን ብሎ ከሰሰው?

11 ሰይጣን “ፍጹምና ቅን” የሆነውን ኢዮብን ለማጥቃት ተነሣ። በመጀመሪያ “በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን?” የሚል ጥያቄ በማንሳት ኢዮብ ይሖዋን የሚያመልከው በጥቅም ተደልሎ እንደሆነ አመለከተ። ከዚያም ዲያብሎስ ተንኮል በተሞላበት አነጋገር ይሖዋ ኢዮብን ከጉዳት በመጠበቅና በመባረክ ታማኝነቱን በጉቦ ገዝቷል ብሎ በመወንጀል አምላክንም ሆነ ኢዮብን ከሰሰ። “ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳብስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል” በማለት ይሖዋን ተገዳደረ።​— ኢዮብ 1:​8–11

12. (ሀ) ሰይጣን ኢዮብን እንዲፈትን አምላክ ቢፈቅድለት ብቻ ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉት ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው? (ለ) የኢዮብ ፈተና ምን ውጤት አስገኘ?

12 ኢዮብ ይሖዋን ያመልክ የነበረው ከአምላክ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ስለተቀበለ ብቻ ነው? የኢዮብ ጥሩ አቋም ፈተና ለማለፍ ይችል ይሆን? ይሖዋስ በአገልጋዩ ሙሉ ትምክህት ኖሮት ፈተና እንዲደርስበት ይፈቅድ ይሆን? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ሊገኝ የሚችለው ሰይጣን በኢዮብ ላይ በጣም ከባድ የሆነ ፈተና እንዲያደርስ ይሖዋ ቢፈቅድለት ብቻ ነው። ኢዮብ በአምላክ ፈቃድ በደረሰበት ፈተና ሁሉ የታመነ ሆኖ መጽናቱ ይሖዋ ጻድቅ እንደሆነና ሰው አቋሙን ሳያጎድፍ መኖር እንደሚችል በማያሻማ ሁኔታ እንዳረጋገጠ በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ ተተርኳል።​— ኢዮብ 42:​1, 2, 12

13. በኤደን ውስጥ እና በኢዮብ ላይ የደረሰው ነገር እኛንም የሚመለከተን እንዴት ነው?

13 ይሁን እንጂ በኤደን ገነት የሆነውና በኢዮብ ላይ የደረሰው ነገር ከዚህ ይበልጥ የጠለቀ ትርጉም ነበረው። ሰይጣን ያስነሳቸው ጥያቄዎች ሁሉንም የሰው ልጆች፣ በአሁኑ ጊዜ የምንኖረውን እኛንም ጭምር ይመለከታሉ። የአምላክ ስም ተሰድቧል፣ ሉዓላዊነቱም ግድድር ደርሶበታል። የአምላክ ፍጡር የሆነው የሰው ልጅ ጥሩ አቋሙን ሳያጎድፍ ለመኖር መቻሉ ጥያቄ ላይ ወድቋል። እነዚህ አከራካሪ ጥያቄዎች በሙሉ ምላሽ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

ጥያቄዎቹ ምላሽ አግኝተው ክርክሩ የሚዘጋው እንዴት ነው?

14. በጥላቻ ላይ የተመሠረተ የሐሰት ክስ የቀረበበት ሰው ምን ሊያደርግ ይች⁠ላል?

14 ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ በርካታ ልጆች ያሉህ አፍቃሪ ወላጅ ነህ እንበል። ከጎረቤቶችህ አንዱ ብድግ ብሎ መጥፎ አባት ነው እያለ ውሸት ያሰራጫል። ይህ ጎረቤት ልጆችህ እንደማይወዱህ፣ ከአንተ ጋር የሚኖሩት የተሻለ አማራጭ ስለ ሌላቸው እንደሆነና ሌላ አማራጭ የሚያሳያቸው ቢያገኙ ኖሮ ሁሉም አንተን ጥለው እንደሚሄዱ ቢናገርስ? ‘ስሞታው ፈጽሞ ውሸት ነው!’ ትል ይሆናል። ይሁን እንጂ ውሸት መሆኑን እንዴት ልታረጋግጥ ትችላለህ? አንዳንድ ወላጆች በቁጣ ገንፍለው የኃይል እርምጃ ይወስዱ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ የኃይል እርምጃ ተጨማሪ ችግሮችን ከመፍጠሩም በላይ የተነገረውን ውሸት የሚደግፍ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለውን ችግር አጥጋቢ በሆነ መንገድ መፍታት የሚቻለው ከሳሽህ ራሱ ለክሱ ማስረጃ እንዲያቀርብ በመፍቀድና ልጆችህም ከልባቸው እንደሚወዱህ እንዲያረጋግጡ በማድረግ ነው።

15. ይሖዋ ለሰይጣን ግድድር ምላሽ ለመስጠት የመረጠው በምን መንገድ ነው?

15 ይሖዋ ልክ እንደዚህ አፍቃሪ አባት ነው። አዳምና ሔዋን በአባትዬው ልጆች ሊመሰሉ ሲችሉ ሰይጣን ደግሞ እንደ ውሸታሙ ጎረቤት ነው። አምላክ ጥበበኛ በመሆኑ ሰይጣን፣ አዳምና ሔዋን ለተወሰነ ጊዜ እንዲኖሩ ፈቀደላቸው እንጂ ወዲያው እንዲጠፉ አላደረገም። ይህም የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ልጆች ወልደው ሰብዓዊ ቤተሰብ እንዲመሠርቱና ዲያብሎስ ደግሞ ያስነሳው ክስ እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥበት ዕድል አግኝቶ የተነሳው አከራካሪ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ አስቻለ። ይሁን እንጂ አምላክ አንዳንድ ሰዎች ለእርሱ ታማኝ ሆነው እንደሚቆሙለትና ሰይጣን ውሸታም መሆኑን እንደሚያረጋግጡ ከመጀመሪያ ጀምሮ ያውቅ ነበር። ይሖዋ የሚወዱትን ሁሉ መባረኩንና መርዳቱን በመቀጠሉ ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን ይገባል!​— 2 ዜና መዋዕል 16:​9፤ ምሳሌ 15:​3

ምን ነገር ሊረጋገጥ ችሏል?

16. ዓለም በሰይጣን መዳፍ ላይ የወደቀው እንዴት ነው?

16 ሰይጣን በመላው የሰው ልጆች ታሪክ ዘመን ባሉት ዘዴዎች በሙሉ ተጠቅሞ የሰው ልጆችን እንዲገዛ ተፈቅዶለታል። ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ በፖለቲካ ኃይላት ላይ ተጽእኖ አሳድሯል። በረቀቀ ዘዴ ይሖዋ ሳይሆን ሰይጣን እንዲመለክ የሚያደርጉ ሃይማኖቶች እንዲስፋፉ አድርጓል። በዚህ መንገድ ዲያብሎስ “የዚህ ዓለም አምላክ” ሆኗል። በተጨማሪም “የዚህ ዓለም ገዥ” ተብሎ ተጠርቷል። (2 ቆሮንቶስ 4:​4፤ ዮሐንስ 12:​31) በእርግጥም “ዓለምም በሞላው በክፉው” ተይዟል። (1 ዮሐንስ 5:​19) ታዲያ ይህ ማለት የሰው ልጆችን በሙሉ ከይሖዋ አምላክ ለማራቅ እንደሚችል የተናገረውን ቃል ለመፈጸም ችሏል ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም! ይሖዋ ሰይጣን እንዲኖር በፈቀደበት ዘመን ሁሉ ዓላማውን ሲያስፈጽም ቆይቷል። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ክፋት እንዲኖር መፍቀዱን በተመለከተ ምን የሚገልጻቸው ነገሮች አሉ?

17. ስለ ክፋትና ሥቃይ መንስኤ ስናስብ ምን ነገር መዘንጋት አይገባንም?

17 የክፋትና የመከራ ምክንያት ይሖዋ አይደለም። ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዥና የዚህ ሥርዓት አምላክ በመሆኑ የሰው ልጅ ማኅበረሰብ ላጋጠሙት ሁኔታዎችና በሰው ልጆች ላይ ለደረሱት ችግሮችና መከራዎች ኃላፊዎቹ ሰይጣንና የሰይጣን ተባባሪዎች ናቸው። ማንም ሰው እነዚህን ችግሮች ሁሉ ያመጣው አምላክ ነው ቢል ትክክል አይሆንም።​— ሮሜ 9:​14

18. ይሖዋ ክፋትና ሥቃይ እንዲኖር መፍቀዱ ከአምላክ ተነጥሎና ራስን ችሎ ስለ መኖር ምን ሊያረጋግጥ ችሏል?

18 ይሖዋ ክፋትና መከራ እንዲኖር መፍቀዱ ከአምላክ ውጭ ራስን ችሎ መኖር የተሻለ ዓለም እንዳላስገኘ አረጋግጧል። የሰው ልጅ ታሪክ የተለያዩ ችግሮችና ሥቃዮች መፈራረቂያ ሆኖ እንደቆየ ሊክድ የሚችል ሰው የለም። ይህ የሆነበት ምክንያት የሰው ልጆች ከአምላክ ተነጥለው የራሳቸውን አካሄድ ለመከተል መምረጣቸውና ለአምላክ ቃልና ፈቃድ ደንታ ቢሶች መሆናቸው ነው። የጥንቶቹ የይሖዋ ሕዝቦችና መሪዎቻቸው በከሃዲነት በሰዎች ዘንድ የሚያስወድዳቸውን አካሄድ በመምረጥ ከቃሉ በራቁ ጊዜ በጣም አስከፊ ሁኔታ ደርሶባቸዋል። አምላክም በነቢዩ ኤርምያስ በኩል “ጥበበኞች አፍረዋል ደንግጠውማል ተማርከውማል፤ እነሆ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ጥለዋል፤ ምን ዓይነት ጥበብ አላቸው?” ብሏል። (ኤርምያስ 8:​5, 6, 9) የሰው ልጅ በአጠቃላይ የይሖዋን የሥነ ምግባር ደንቦች ለመከተል እምቢተኛ በመሆኑ በማዕበል በሚነዋወጥ ባሕር ውስጥ ወዲያና ወዲህ እየተገፋ እንደሚንከራተት መቅዘፊያ የሌለው መርከብ ሆኗል።

19. ሰይጣን ሁሉንም የሰው ልጆች በአምላክ ላይ ለማሳመፅ እንዳልቻለ የሚያረጋግጥ ምን ማስረጃ አለ?

19 በተጨማሪም አምላክ ክፋትና መከራ እንዲኖር መፍቀዱ ሰይጣን የሰው ልጆችን በሙሉ ከይሖዋ ለማራቅ ያልቻለ መሆኑን አረጋግጧል። ምንም ዓይነት ፈተናና መከራ ቢደርስባቸው ለአምላክ ታማኝ ሆነው የጸኑ ግለሰቦች በማንኛውም ዘመን እንደነበሩ ታሪክ ይመሰክራል። ባለፉት መቶ ዘመናት ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ሲል በወሰዳቸው ርምጃዎች ኃያልነቱ ታይቷል። ስሙም በመላው ምድር ላይ ታውቋል። (ዘጸአት 9:​16፤ 1 ሳሙኤል 12:​22) ዕብራውያን ምዕራፍ 11 አቤልን፣ ሄኖክን፣ ኖኅን፣ አብርሃምንና ሙሴን ጨምሮ ለአምላክ የታመኑ ሆነው የጸኑ በርካታ ሰዎችን ይዘረዝራል። እነዚህን ሰዎች ዕብራውያን 12:​1 ‘እንደ ደመና ያሉ ምሥክሮች’ በማለት ይጠራቸዋል። በይሖዋ ላይ ለነበራቸው የማያወላውል እምነት በአርዓያነት የሚጠቀሱ ናቸው። በዚህ በእኛ ዘመንም ቢሆን ጥሩ አቋማቸውን ሳያጎድፉ ከአምላክ ጋር በመጣበቃቸው ምክንያት ሕይወታቸውን እስከማጣት የደረሱ አሉ። እነዚህ ግለሰቦች በእምነታቸውና በፍቅራቸው ሰይጣን የሰው ልጆችን በሙሉ በአምላክ ላይ ለማሳመፅ የማይችል መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጠዋል።

20. ይሖዋ ክፋትና ሥቃይ እንዲኖር መፍቀዱ በአምላክና በሰው ልጆች ረገድ ምን ሐቅ ሊያረጋግጥ ችሏል?

20 በመጨረሻም ይሖዋ ክፋትና መከራ እንዲኖር መፍቀዱ የሰው ልጆችን ለመግዛት መብት ያለውና ዘላለማዊ በረከትና ደስታ በሚያስገኝላቸው መንገድ ሊገዛቸው ችሎታ ያለው ፈጣሪያቸው የሆነው ይሖዋ ብቻ መሆኑን አረጋግጧል። የሰው ልጅ ባለፉት መቶ ዘመናት በሙሉ የተለያዩ የመስተዳድር ዓይነቶችን ሞክሯል። ይሁን እንጂ ውጤቱ ምን ሆነ? በአሁኑ ጊዜ በብሔራት ላይ ተደቅነው የሚገኙት የተወሳሰቡ ችግሮች መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ” መሆኑን በሚገባ ያረጋግጣሉ። (መክብብ 8:​9 አዓት) ከእነዚህ ችግሮች ሊያድነንና የመጀመሪያ ዓላማውን ሊፈጽምልን የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ይህን የሚያደርገው እንዴትና መቼ ነው?

21. ሰይጣን ምን ይደረጋል? ይህንንስ የሚያደርገው ማን ነው?

21 አዳምና ሔዋን በሰይጣን ሴራ እንደተሸነፉ አምላክ የሰው ልጆችን የሚያድንበትን ዓላማ አስታወቀ። ይሖዋ ስለ ሰይጣን ሲናገር “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ” አለ። (ዘፍጥረት 3:​15) ይህ መግለጫ ብቻውን ዲያብሎስ እኩይ ተግባሩን ለዘላለም እንዲቀጥል እንደማይፈቀድለት ዋስትና ይሰጣል። ተስፋ የተደረገው ዘር ኢየሱስ ክርስቶስ የመሲሐዊው መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ‘የሰይጣንን ራስ ይቀጠቅጣል።’ አዎን፣ በቅርቡ ኢየሱስ ዓመፀኛውን ሰይጣን ይቀጠቅጠዋል!​— ሮሜ 16:​20

አንተስ ከማን ጎን ትሰለፋለህ?

22. (ሀ) ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ይኖርብሃል? (ለ) ሰይጣን ለአምላክ ታማኝ በሆኑ ሰዎች ላይ ንዴቱን ቢወጣም ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ?

22 የተነሱትን ትልልቅ ጥያቄዎች አውቀሃል፤ ታዲያ ከማን ጎን ትሰለፋለህ? የይሖዋ ታማኝ ደጋፊ መሆንህን በምታደርጋቸው ነገሮች ታረጋግጣለህ? ሰይጣን የቀረው ጊዜ በጣም አጭር መሆኑን ስለሚያውቅ አቋማቸውን ሳያጎድፉ ከአምላክ ጋር ተጣብቀው ለመኖር በሚፈልጉ ሰዎች ላይ ንዴቱን ለመወጣት የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። (ራእይ 12:​12) ይሁን እንጂ “ይሖዋ ለአምላክ ያደሩትን ሰዎች ከፈተና እንዴት እንደሚያድን” ስለሚያውቅ እርዳታውን ለመጠየቅ ትችላለህ። (2 ጴጥሮስ 2:​9 አዓት) ከአቅምህ በላይ እንድትፈተን አይፈቅድም። በተጨማሪም በፈተናው ለመጽናት እንድትችል መውጫውን መንገድ ያዘጋጅልሃል።​— 1 ቆሮንቶስ 10:​13

23. የትኛውን ጊዜ በልበ ሙሉነት ልንጠባበቅ እንችላለን?

23 እንግዲያው ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰይጣንና በተከታዮቹ ላይ እርምጃ የሚወስድበትን ጊዜ በልበ ሙሉነትና በናፍቆት እንጠብቅ። (ራእይ 20:​1–3) ኢየሱስ የሰው ልጅ ለደረሰበት ወዮታዎችና ችግሮች ተጠያቂ የሆኑትን ሁሉ ያስወግዳል። ይህ እስኪሆን ድረስ ከሚያጋጥሙን አስጨናቂ መከራዎች አንዱ የምንወዳቸውን ሰዎች በሞት ማጣት ነው። እነዚህ በሞት የሚለዩን ወዳጆቻችንና ዘመዶቻችን ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚያጋጥማቸው ለመረዳት ትችል ዘንድ የሚቀጥለውን ምዕራፍ አንብብ።

እውቀትህን ፈትሽ

ይሖዋ በሰዎች ላይ ሥቃይና መከራ እንደማያመጣ እንዴት እናውቃለን?

ሰይጣን በኤደን ያስነሳቸውና በኢዮብ ዘመን ይበልጥ ግልጽ የሆኑት ትልልቅ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው?

አምላክ ሥቃይ እንዲኖር በመፍቀዱ ምን ነገሮችን አረጋግጧል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]