በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ የሰው ልጆችን ለማዳን ምን አድርጓል?

አምላክ የሰው ልጆችን ለማዳን ምን አድርጓል?

ምዕራፍ 7

አምላክ የሰው ልጆችን ለማዳን ምን አድርጓል?

1, 2. (ሀ) አንድ ሮማዊ መቶ አለቃ የአምላክን ልጅ ማንነት ሊያውቅ የቻለው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ እንዲሞት ይሖዋ የፈቀደው ለምን ነበር?

የዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ በጸደይ ወራት አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ አንድ ሮማዊ መቶ አለቃ ሦስት ሰዎች ረዘም ላለ ሰዓት አጣጥረው ሲሞቱ ተመለከተ። በተለይ የዚህን ወታደር ትኩረት የሳበው አንደኛው ሰው ነበር። እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር። ኢየሱስ በአንድ የእንጨት አምድ ላይ ተቸንክሮ ነበር። የመሞቻው ጊዜ እየተቃረበ ሲሄድ የቀትሯ ጀምበር ጨለመች። በሞተበት ጊዜም ምድሪቱ በኃይል ተናወጠች። ወታደሩም “ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ አለ።”​— ማርቆስ 15:⁠39

2 የእግዚአብሔር ልጅ! ወታደሩ አልተሳሳተም። በምድር ላይ ከተፈጸሙት ነገሮች ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ነገር ሲፈጸም ተመልክቷል። ቀደም ሲል አምላክ ራሱ ኢየሱስን የምወደው ልጄ ሲል ጠርቶት ነበር። (ማቴዎስ 3:​17፤ 17:​5) ይሖዋ ልጁ እንዲሞት የፈቀደው ለምን ነበር? አምላክ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን ያሰበው በዚህ ዝግጅት አማካኝነት ስለ ነበረ ነው።

ልዩ ለሆነ ዓላማ የተመረጠ

3. አምላክ ለሰው ልጆች ለነበረው ልዩ ዓላማ የአምላክ አንድያ ልጅ መመረጡ ተገቢ የሆነው ለምን ነበር?

3 ቀደም ስንል በዚህ መጽሐፍ እንዳጠናነው ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት በሰማይ ይኖር ነበር። ይሖዋ በቀጥታ የፈጠረው ስለሆነም የአምላክ “አንድያ ልጅ” ተብሏል። ከዚያ በኋላ አምላክ በኢየሱስ በመጠቀም የቀሩትን ፍጥረታት በሙሉ ወደ ሕልውና አምጥቷል። (ዮሐንስ 3:​18፤ ቆላስይስ 1:​16) ኢየሱስ በተለይ የሰው ልጆችን ይወድ ነበር። (ምሳሌ 8:​30, 31) ስለዚህ የሰው ልጅ በኃጢአት ኩነኔ ሥር በወደቀ ጊዜ አንድያ ልጁን ልዩ ዓላማ እንዲፈጽም መምረጡ የተገባ ነበር።

4, 5. ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መሲሐዊው ዘር ምን ገልጾ ነበር?

4 አምላክ በኤደን የአትክልት ሥፍራ በአዳም፣ በሔዋንና በሰይጣን ላይ የፍርድ ብያኔ ባስተላለፈበት ጊዜ “ዘር” በማለት ወደፊት ስለሚመጣ አዳኝ ተናግሯል። ይህ ዘር የሚመጣው “የቀደመው እባብ” ሰይጣን ዲያብሎስ ያመጣቸውን አስከፊ ሁኔታዎች በሙሉ ለማጥፋት ነው። እንዲያውም አምላክ እልክላችኋለሁ በማለት ቃል የገባልን ይህ ተስፋ የተደረገ ዘር ሰይጣንንና የሰይጣን ተከታዮች የሆኑትን በሙሉ ይቀጠቅጣል።​— ዘፍጥረት 3:​15፤ 1 ዮሐንስ 3:​8፤ ራእይ 12:​9

5 ከዚያ ወዲህ ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ አምላክ መሲሕ ተብሎ ስለሚጠራው ስለዚህ ዘር ተጨማሪ ነገሮችን ቀስ በቀስ ገልጿል። በገጽ 37 በሚገኘው ሰንጠረዥ ላይ እንደተመለከተው በርካታ ትንቢቶች በምድር ላይ ስለሚያሳልፈው ሕይወቱ ዝርዝር መግለጫዎችን ሰጥተዋል። ለምሳሌ ያህል በአምላክ ዓላማ ውስጥ የተመደበለትን ሚና ለማከናወን ብዙ መከራ መቀበል ነበረበት።​— ኢሳይያስ 53:⁠3–5

መሲሑ መሞት የነበረበት ለምንድን ነው?

6. በዳንኤል 9:​24–26 መሠረት መሲሑ ምን መፈጸም ነበረበት? እንዴትስ?

6 በዳንኤል 9:​24–26 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው ትንቢት መሲሑ ወይም የአምላክ ቅቡዕ ታላቅ ዓላማ እንደሚያከናውን በቅድሚያ ተገልጾ ነበር። ለዘላለም “ዓመፃን ይጨርስ፣ ኃጢአትንም ይፈጽም፣ በደልንም ያስተሰርይ፣ የዘላለምን ጽድቅ ያገባ” ዘንድ ወደ ምድር መምጣት ነበረበት። መሲሑ ከታማኝ የሰው ልጆች በሙሉ የሞትን ኩነኔ እንደሚያስወግድ ተገልጾ ነበር። ይህን የሚያደርገው ግን እንዴት ነው? ‘እንደሚቆረጥ’ ወይም እንደሚገደል ትንቢቱ ይናገራል።

7. አይሁዳውያን የእንስሳ መሥዋዕት ያቀርቡ የነበረው ለምንድን ነው? ይህስ ለምን ነገር ጥላ ሆኖ ነበር?

7 የጥንቶቹ እስራኤላውያን በደልን ስለማስተሰረይ አሳምረው ያውቁ ነበር። አምላክ በሙሴ በኩል በሰጣቸው ሕግ መሠረት ይከናወን በነበረው ሥርዓተ አምልኮ የእንስሳት መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር። እነዚህ መሥዋዕቶች የሰው ልጆች በሙሉ ኃጢአታቸውን የሚሸፍንላቸው ወይም የሚያስተሰርይላቸው ነገር እንደሚያስፈልጋቸው እስራኤላውያንን ያስገነዝቡ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በአንድ ዐረፍተ ነገር ሲያጠቃልል “ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም” ብሏል። (ዕብራውያን 9:​22) ክርስቲያኖች መሥዋዕት እንደማቅረብ ያሉ ግዳጆችን ያካትት በነበረው የሙሴ ሕግ አይገዙም። (ሮሜ 10:​4፤ ቆላስይስ 2:​16, 17) በተጨማሪም የእንስሳት መሥዋዕት የተሟላና ዘላቂ የሆነ የኃጢአት ይቅርታ ሊያስገኝ እንደማይችል ያውቁ ነበር። ከዚህ ይልቅ እነዚህ መሥዋዕቶች የበለጠ ዋጋ ላለው የመሲሑ ወይም የክርስቶስ መሥዋዕት ጥላ ሆነው ነበር። (ዕብራውያን 10:​4, 10፤ ከገላትያ 3:​24 ጋር አወዳድር።) ሆኖም ‘ታዲያ መሲሑ መሞት ያስፈልገው ነበርን?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

8, 9. አዳምና ሔዋን ያጡት ምን ውድ የሆነ ነገር ነበር? ያደረጉትስ ነገር ዘሮቻቸውን የነካው እንዴት ነው?

8 አዎን፣ የሰው ልጅ እንዲድን ከተፈለገ መሲሑ መሞት ነበረበት። ይህ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ለመረዳት በኤደን ገነት የሆነውን ነገር መለስ ብለን ማስታወስና አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ባመፁ ጊዜ ያጡት መብት ምን ያህል ታላቅ እንደነበረ መገንዘብ ይኖርብናል። ከፊታቸው የዘላለም ሕይወት ተዘርግቶላቸው ነበር! በተጨማሪም የአምላክ ልጆች እንደመሆናቸው መጠን ከእርሱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ነበራቸው። የይሖዋን አገዛዝ ለመቀበል እምቢተኛ በሆኑ ጊዜ ግን ይህን ሁሉ መብት ከማጣታቸው በተጨማሪ በሰው ዘር ላይ ኃጢአትና ሞት አመጡ።​— ሮሜ 5:​12

9 የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የነበረውን ብዙ ሀብት አባክኖ ሊወጣ በማይችልበት የዕዳ ማጥ ውስጥ እንደገባ ሰው ሆኑ። አዳምና ሔዋን ይህን ዕዳቸውን ለልጆቻቸው አስተላለፉ። ሁላችንም ፍጹማንና ኃጢአት አልባ ሆነን ስላልተወለድን ኃጢአተኞችና ሟቾች ነን። ስንታመም ወይም ‘ምነው ባልተናገርኩ’ የምንለውን ጎጂ ነገር ስንናገር የወረስነው ዕዳ ወይም ሰብዓዊ አለፍጽምናችን ያስከተለብንን ውጤት መቅመሳችን ነው። (ሮሜ 7:​21–25) ተስፋ ሊኖረን የሚችለው አዳም ያጣውን ነገር መልሰን ለማግኘት ብንችል ብቻ ነው። ይሁን እንጂ በራሳችን ጥረት ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሕይወት ልናገኝ አንችልም። ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች በሙሉ ኃጢአት ስለሚሠሩ ልናገኝ የሚገባን ዋጋ ሞት እንጂ ሕይወት አይደለም።​— ሮሜ 6:​23

10. አዳም ያጠፋውን ነገር መልሶ ለመግዛት ምን ያስፈልግ ነበር?

10 ይሁን እንጂ አዳም ላጣው ሕይወት ልዋጭ ሆኖ ሊከፈል የሚችል ነገር ይኖር ይሆን? የአምላክ የፍትሕ ሚዛን ተመጣጣኝ የሆነ ፍርድ፣ ማለትም “ነፍስ ለነፍስ” እንዲከፈል ይጠይቃል። (ዘጸአት 21:​23) ስለዚህ ለጠፋው ሕይወት ምትክ ሌላ ሕይወት መከፈል ነበረበት። የማንኛውም ምድራዊ ፍጡር ሕይወት በቂ ሊሆን አይችልም። መዝሙር 49:​7, 8 (የ1980 ትርጉም) ፍጹማን ስላልሆኑ ሰዎች ሲናገር “ሰው ራሱን መቤዠትም ሆነ ለሕይወቱ ቤዛ የሚሆነውን ዋጋ ለእግዚአብሔር መክፈል አይችልም። ለሰው ሕይወት የሚከፈለው ዋጋ እጅግ ብዙ ነው” ይላል። ታዲያ ምንም ተስፋ የሌለው ሁኔታ ነው ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም።

11. (ሀ) “ቤዛ” የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ምን ያመለክታል? (ለ) የሰው ልጆችን ለመቤዠት የሚችለው ማን ብቻ ነው? ለምንስ?

11 በዕብራይስጥ ቋንቋ “ቤዛ” የሚለው ቃል አንድን ምርኮኛ ወይም የተያዘ ሰው ለማስለቀቅ የሚከፈለውን ዋጋ ያመለክታል። የተመጣጣኝነትንም ሐሳብ ያካትታል። አዳም ላጣው ሕይወት ተመጣጣኝ የሆነ ሕይወት ሊከፍል የሚችለው ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ያለው ሰው ብቻ ነው። ከአዳም በኋላ ፍጹም ሆኖ የተወለደ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “ኋለኛው አዳም” ብሎ በመጥራት ‘ለሰው ሁሉ ተመጣጣኝ ቤዛ’ እንደከፈለ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 15:​45፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:​5, 6 አዓት) አዳም ለልጆቹ ያወረሰው ሞት ሲሆን ከኢየሱስ ያገኘነው ውርሻ ግን የዘላለም ሕይወት ነው። አንደኛ ቆሮንቶስ 15:​22 “ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉ” በማለት ያስረዳል። ስለዚህም ኢየሱስ “የዘላለም አባት” ተብሎ መጠራቱ የተገባ ነው።​— ኢሳይያስ 9:​6, 7

ቤዛው እንዴት ተከፈለ?

12. ኢየሱስ መሲሕ የሆነው መቼ ነበር? ከዚያስ በኋላ ምን ዓይነት አኗኗር ተከ ትሏል?

12 ኢየሱስ በ29 እዘአ የበልግ ወራት ዘመዱ ወደነበረው ወደ ዮሐንስ ሄዶ በመጠመቅ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ራሱን አቀረበ። በዚሁ ጊዜ ይሖዋ ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ ቀባው። በዚህ መንገድ ኢየሱስ መሲሕ ወይም ክርስቶስ ማለትም በአምላክ የተቀባ ሆነ። (ማቴዎስ 3:​16, 17) ከዚያ በኋላ ኢየሱስ የሦስት ዓመት ተኩል አገልግሎቱን ጀመረ። ስለ አምላክ መንግሥት እየሰበከና የታመኑ ተከታዮችን እያሰባሰበ በትውልድ አገሩ በሙሉ ተዘዋወረ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ አስቀድሞ እንደተነገረው ተቃውሞ እያየለበት መጣ።​— መዝሙር 118:​22፤ ሥራ 4:​8–11

13. ኢየሱስ እንከን የለሽ አቋሙን ጠብቆ ከመሞቱ በፊት ምን ነገሮች ደረ ሱበት?

13 ኢየሱስ የሃይማኖታዊ መሪዎችን ግብዝነት በድፍረት በማጋለጡ እርሱን የሚገድሉበትን መንገድ ይፈልጉ ጀመር። በመጨረሻም በጣም አደገኛ የሆነ ተንኮል ሸረቡበትና አለአግባብ እንዲታሰር፣ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ እንዲፈረድበትና መንግሥት ሊገለብጥ ሞክሯል የሚል የሐሰት ክስ እንዲቀርብበት አደረጉ። ኢየሱስ ተደበደበ፣ ተተፋበት፣ ተዘበተበት፣ ሰውነትን እንዲቦጫጭቅ ሆኖ በተሠራ ጅራፍ ተገረፈ። ከዚያም ጴንጠናዊ ጲላጦስ የተባለው ሮማዊ ገዥ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ እንዲገደል ፈረደበት። በእንጨት ምሰሶ ላይ ተቸንክሮ እንዲሰቀል ተደረገ። ለበርካታ ሰዓታት ተሰቅሎ በከባድ ሥቃይ ሲያጣጥር ከቆየ በኋላ ሞተ። ኢየሱስ እንዲህ ያለ ሥቃይ ሲደርስበት እንከን የማይወጣለት አቋሙን ጠብቆ ከአምላክ ጎን ቆሟል።

14. አምላክ ልጁ እንዲሠቃይና እንዲሞት የፈቀደው ለምን ነበር?

14 እንግዲያው ኢየሱስ ሕይወቱን “ለብዙዎች ቤዛ” አድርጎ የሰጠው ኒሳን 14 ቀን በ33 እዘአ ነበር። (ማርቆስ 10:​45፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:​5, 6) ይሖዋ በሰማይ ሆኖ ውድ ልጁ በሥቃይ ሲሞት ይመለከት ነበር። አምላክ እንዲህ የመሰለው አሠቃቂ ነገር እንዲደርስ የፈቀደው ለምን ነበር? የሰው ልጆችን ስለሚወድ ነበር። ኢየሱስ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” ብሏል። (ዮሐንስ 3:​16) በተጨማሪም የኢየሱስ ሞት ይሖዋ ፍጹም ፍትሕ የሚጠብቅ አምላክ መሆኑን ያስተምረናል። (ዘዳግም 32:​4) አንዳንዶች አምላክ ነፍስ ስለ ነፍስ እንዲከፈል የሚያዘውን የፍትሕ መሠረታዊ ሥርዓት ሽሮ የአዳም ኃጢአት ምንም ዓይነት ክፍያ እንዳያስፈልገው ለምን አያደርግም ነበር ብለው ያስባሉ። ይህ የሆነበት ምክንያት ይሖዋ የቱንም ያህል ከፍተኛ ዋጋ ቢጠይቅበት ሕጎቹን ስለማይጥስና ስለሚያስከብር ነው።

15. ኢየሱስ ሞቶ እንዲቀር ማድረግ ፍትሕ ስለማይሆን ይሖዋ ምን አደረገ?

15 በተጨማሪም የይሖዋ ፍትሕ የኢየሱስ ሞት ደስ የሚያሰኝ ፍጻሜ እንዲኖረው ይጠይቅ ነበር። የታመነ ሆኖ የሞተው ኢየሱስ ለዘላለም በሞት አንቀላፍቶ እንዲቀር ቢደረግ ፍትሕ ይሆናልን? በፍጹም አይሆንም! የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የአምላክ ታማኝ ልጅ በመቃብር ውስጥ እንደተቀበረ እንደማይቀር ተንብየዋል። (መዝሙር 16:​10፤ ሥራ 13:​35) ኢየሱስ ሦስት ቀን ለማይሞላ ጊዜ በሞት አንቀላፍቶ ቆየ። ከዚያም ይሖዋ አምላክ ኃያል መንፈሳዊ አካል ሆኖ እንዲነሳ አደረገው።​— 1 ጴጥሮስ 3:​18

16. ኢየሱስ ወደ ሰማይ እንደተመለሰ ምን አደረገ?

16 ኢየሱስ በሞተበት ጊዜ ሰብዓዊ ሕይወቱን ለአንዴና ለሁልጊዜ አሳልፎ ሰጠ። ወደ ሰማያዊ ሕይወት በተነሳበት ጊዜ ሕይወት የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ከዚህም በላይ ኢየሱስ በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ ካሉት ቦታዎች ሁሉ እጅግ ቅዱስ ወደሆነው ሥፍራ አርጎ ከውድ አባቱ ጋር ከመገናኘቱም በላይ የፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ዋጋ አቀረበ። (ዕብራውያን 9:​23–28) ከዚያ ጊዜ ወዲህ ይህ ውድ ሕይወት ካስገኘው ፋይዳ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች እንዲጠቀሙ ተደርጓል። ታዲያ ይህ ለአንተ ምን ትርጉም ይኖረዋል?

አንተና የክርስቶስ ቤዛ

17. የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ከሚያስገኘው የኃጢአት ይቅርታ እንዴት ተጠቃሚዎች ልንሆን እንችላለን?

17 የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት በአሁኑ ጊዜ እንኳን ሊጠቅምህ የሚችልባቸውን ሦስት መንገዶች እንመልከት። በመጀመሪያ ደረጃ የኃጢአት ይቅርታ ያስገኛል። በፈሰሰው የኢየሱስ ደም በማመን “በቤዛው ኃጢአታችንን ተምረናል”፤ አዎን “በደላችንን ይቅር ተብለናል።” (ኤፌሶን 1:​7 አዓት) ስለዚህ ከባድ ኃጢአት ብንሠራ እንኳን አምላክ ይቅርታ እንዲያደርግልን በኢየሱስ ስም ልንለምነው እንችላለን። በእውነት ከተጸጸትን ይሖዋ የልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት ዋጋ ተጠቃሚዎች እንድንሆን ያስችለናል። አምላክ ኃጢአት በመሥራታችን ምክንያት መቀበል የሚገባንን የሞት ቅጣት እንድንቀበል ከማድረግ ይልቅ ይቅርታ በማድረግ ጥሩ ሕሊና ይሰጠናል።​— ሥራ 3:​19፤ 1 ጴጥሮስ 3:​21

18. የኢየሱስ መሥዋዕት ተስፋ ያስገኘልን በምን መንገድ ነው?

18 በሁለተኛ ደረጃ የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የወደፊት ተስፋ እንዲኖረን መሠረት ሆኗል። ሐዋርያው ዮሐንስ በተመለከተው ራእይ “አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሰዎች” ይህን ሥርዓት ከሚያወድመው እልቂት በሕይወት እንደሚያልፉ አይቷል። አምላክ በጣም ብዙ ሌሎች ሰዎችን ሲያጠፋ እነዚህ ብቻ ከጥፋቱ በሕይወት የሚተርፉት ለምንድን ነው? እጅግ ብዙ ሰዎች “ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም” እንዳነጹ መልአኩ ለዮሐንስ ነግሮታል። (ራእይ 7:​9, 14) በፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም እስካመንና መለኮታዊ ብቃቶችን አሟልተን እስከኖርን ድረስ በአምላክ ዓይን ንጹሐን ሆነን ለመታየትና የዘላለም ሕይወት ተስፋ ሊኖረን ይችላል።

19. የክርስቶስ መሥዋዕት ኢየሱስና አባቱ እንደሚወዱህ ያረጋገጠው እንዴት ነው?

19 ሦስተኛ፣ ቤዛዊው መሥዋዕት የመጨረሻው ከፍተኛ የይሖዋ ፍቅር ማረጋገጫ ነው። በክርስቶስ ሞት በአጽናፈ ዓለሙ ታሪክ ውስጥ ከተፈጸሙት የፍቅር ድርጊቶች ሁሉ የሚበልጡት ሁለት የፍቅር መግለጫዎች ታይተዋል። እነርሱም:- (1) አምላክ ለእኛ ሲል ልጁ እንዲሞት ወደ ምድር በመላኩ ያሳየው ፍቅር፣ (2) ኢየሱስ ራሱን በፈቃደኝነት ቤዛ አድርጎ በማቅረብ ያሳየው ፍቅር ናቸው። (ዮሐንስ 15:​13፤ ሮሜ 5:​8) ከልብ የምናምን ከሆነ ሁላችንም በዚህ ፍቅር እንታቀፋለን። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የወደደኝና ስለ እኔ ራሱን የሰጠው የእግዚአብሔር ልጅ’ ብሏል።​— ገላትያ 2:​20፤ ዕብራውያን 2:​9፤ 1 ዮሐንስ 4:​9, 10

20. በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ማመን የሚኖርብን ለምንድን ነው?

20 ስለዚህ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመን አምላክና ክርስቶስ ላሳዩን ፍቅር አመስጋኞች መሆናችንን እናሳይ። ይህን ማድረጋችን የዘላለም ሕይወት ያስገኝልናል። (ዮሐንስ 3:​36) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በምድር ላይ የኖረበትና የሞተበት ዋነኛ ምክንያት የእኛን መዳን ለማስፈጸም አይደለም። ከዚህ ይበልጥ አሳሳቢ የሆነና አጽናፈ ዓለማዊ ይዘት ያለው ጥያቄ ተነስቶ ነበር። በሚቀጥለው ምዕራፍ እንደምንመለከተው ይህ ጥያቄ አምላክ ይህን ለሚያክል ረዥም ጊዜ ክፋትና ሥቃይ እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያት ስለሚገልጽልን ሁላችንንም የሚመለከት ጥያቄ ነው።

እውቀትህን ፈትሽ

ኢየሱስ የሰው ልጆችን ለማዳን መሞት ያስፈለገው ለምንድን ነው?

ቤዛው የተከፈለው እንዴት ነው?

የቤዛው ተጠቃሚ የምትሆነው በምን መንገዶች ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 67 ላይ የሚገኝ ሥዕል]